You can paste your entire post in here, and yes it can get really really long.
እንደ መግቢያበ1997 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተደረገው ምርጫ የብዙዎችን ቀልብ ስቦ ነበር፡፡ በተለይ ቅድመ ምርጫ ሂደቱ ነጻ እና ፍትሓዊ ነበር ለማለት የሚያስደፍር ነበር፡፡ በምርጫውም በአዲስ አበባ እና ብዙ ሊባል በሚችል የሀገሪቱ ክፍል ተቃዋሚዎች በከፍተኛ ድምጽ ከማሸነፋቸው ጋር ተያይዞ በአገሪቷ በሞላ ከፍተኛ ቀውስ ተፈጥሮ በርካታ ሰዎች በመንግስት የፀጥታ ሐይሎች ተገድለዋል፤ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፤ አባላትና ደጋፊዎች በጅምላ ታስረዋል፡፡ ይህ ወቅት በአንድ በኩል ለእውነተኛ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መልካም ዕድልን ፈጥሮ የነበረ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ኢሕአዴግ እንዲህ ዓይነቱ ሥልጣን ሊያሳጡ የሚችሉ ዕድሎች ዳግመኛ እንዳይመጡ ለመከላከል ያስችለኛል ያላቸውን ልዩ ልዩ የእመቃ እርምጃዎችን እንዲወስድ ያነቃው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ለዚህም መንግስት በምርጫው ሂደት የመንግስትን በሥልጣን ላይ የመቆየት ፍላጎት በሚፃረር መልኩ ተንቀሳቅሰዋል ያላቸውን የሲቪል ማህበራት የማሽመድመድ ዓላማ ይዞ የተቀረፀውን የበጎ አድራጎትና ማህበራት አዋጅ፤ የሕዝቡን ሐሳብን በነፃ የመግለፅ መብት ለማዳፈን የታወጀውን የሚዲያ ሕግ እና የተቃውሞ ፖለቲካውን በማደናቀፍ የዲሞክራሲውን ምህዳር በማጥበብ ጥቅም ላይ የዋለውን የፀረ-ሽብር አዋጅ በተከታታይ አውጥቶ ሥራ ላይ ማዋሉ ዓይነተኛ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ የበጎ አድራጎትና ማህበራት አዋጅ፣ እንዲሁም የሚዲያ ሕጉ የሕዝቡን የመደራጀት እና ሐሣብን በነፃ የመግለፅ መብት በመግታት የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይ ግን የፀረ-ሽብር አዋጅ ጥቅም ላይ የዋለበት መንገድ የዲሞክራሲውን ምህዳር ከማጥበብ ባሻገር በሕዝቡ ውስጥ በዋነኛነት በኦሮሚያና በአማራ ክልል የታየው ዓይነት ሕዝባዊ ተቃውሞ እንዲነሣ ከፍተኛውን ሚኛ እንደተጫወተ የሚካድ አይደለም፡፡ በመንግስት በኩልም ዘግይቶም ቢሆን እንኳን በአገሪቷ የነበረው አስተዳደር በተለይ ከሰብዓዊ መብትና ዲሞክራሲን ከማስፋት አንፃር ብዙ ድክመት እንዳለበት ከማመኑም በላይ በዚህ ምክንያት ለደረሰው ጉዳትም ኃላፊነቱን ወስዷል፡፡ በዚህ ጽሑፍም ይህ አዋጅ ስለተተገበረበት ሁኔታ እና ሲተገበርም ስላስከተለው አሉታዊ ውጤት ለመግለጽ ተሞክሯል፡፡መነሻየሽብር ተግባር እና አሸባሪ የሚሉት ቃላት እና ሐሳቦች እንደ የፍልስጤም ነፃ አውጪ ድርጅት (PLO) እና የሰሜን አየርላንድ ነፃ አውጪ ድርጅት (Shinfain) ዓላማቸውን ለማራመድ ይጠቀሙበት ከነበረው የሐይል እርምጃ ጋር ተያይዞ ዓላማቸውን በማይደግፍ አካላት ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ እንደዋለ በመስኩ የተደረጉ ጥናቶች ይገልፃሉ፡፡ የተለያዩ አገር መንግስታት በአገር ውስጥ የሚቃወሟቸውን ሐይሎች ለመደምሰስ የሚወስዱት እርምጃ በዓለም አቀፍ ሕብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት እንደሚያስገኝላቸው በማሰብ የተቃውሞ እንቅስቃዎቹን የሽብርተኝነት መልክ ሲሰጡ እና የተቃውሞ መሪዎቹንም አሸባሪ በማለት ሲያሣድዱ ቆይተዋል፡፡ 9/11 በመባል የሚታወቀው በመስከረም 11 ቀን 2001 እ.አ.አ. የኒውዮርክ መንትያ ሕንፃዎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት አብዛኛው የዓለም ክፍል በሽብርተኝነት እና በአሸባሪዎች ላይ ተመሣሣይ ወይም ተቀራራቢ አቋም እንዲይዝ አድርጎታል ማለት ይቻላል፡፡ ዓል-ቃይዳ የተባለው ጽንፈኛ ቡድን ለጥቃቱ ኃላፊነቱን መውሰዱ እና ይህ ቡድንም ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በሙሉ ሥጋት መሆኑ አገሮች በሽብርተኝነት ዙሪያ እንዲተባበሩ አድርጓቸዋል፡፡ ይህን ተከትሎም የተባበሩት መንግስታት ሁሉም አባል አገሮች የሽብርተኝነት ወንጀልን ለመከላከል የሚያስችል በቂ ሕግ እንዲያወጡ ውሣኔ አስተላልፏል፡፡ ውሣኔውን ተከትሎም የጥቃቱ ቀጥተኛ ሰለባ የነበረችው አሜሪካን ጨምሮ በርካታ የዓለማችን አገሮች የሽብርተኝነት ድርጊትን ከባድ ወንጀል አድርጎ የሚፈርጅ እና ከመፈፀሙ በፊት በብቃት ለመከላከልና ሲፈፀምም አድራጊውን በአግባቡ የሚቀጣ የሚችል ሕግ አውጥቷል፡፡አገራችንም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አንድ አካል እንደመሆኗ እንዲህ ዓይነቱን ሕግ እንድታወጣ መጠበቋ አልቀረም፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት ድርጊቱን ለመከላከል የሚያስችል በቂ ሕግ ያለው መሆኑን በመጥቀስ ሌላ ሕግ ለማውጣት እንደማያስፈልግ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ይህ የመንግስት አቋም ግን እስከመጨረሻው የዘለቀ አልነበረም፡፡ ይልቁንም በ2001 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ ወራት አካባቢ መንግስት የፀረ-ሽብር አዋጅ አርቅቆ ለውይይት አቅርቧል፡፡ በወቅቱም በዋነኛነት ከእስር እና ስደት የተረፉት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ይህ አዋጅ ሆን ተብሎ ተቃውሞን ለማፈን ታልሞ የተረቀቀ ነው በሚል በጽኑ የተቃወሙት ሲሆን በሥራ ላይ ያለው ሕግ ሽብርተኝነትን ለመከላከልም ሆነ ለመቅጣት በቂ ነው በማለት የተረቀቀው የፀረ-ሽብር ሕግ እንዳይፀድቅ የተቃወሙት የመስኩ ምሑራን እና የሕብረተሰብ ክፍሎችም አልጠፋም፡፡ያም ሆኖ ግን ረቂቅ ሕጉን የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 252/2001 ተብሎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመጽደቅ አላስቀረውም፡፡የሕጉ ዓላማና በሥራ ላይ መዋልየፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ ሲታወጅ በኋላ ላይ ሲተገበር እንደታየው የዜጎችን መብት ለመጨፍለቅ ሣይሆን እንዲያውም ሕዝቦች በሰላም፤በነፃነትና በተረጋጋ ሁኔታ ለመኖር ያላቸውን መብት ከሽብርተኝነት አደጋ ለመጠበቅ እንደሆነ ተገልጿል። (የፀረ-ሽብር አዋጁ መግቢያ የመጀመሪያ ሐይለ ቃል) በርግጥም በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን የፀረ-ሽብር ትግል በአጠቃላይ የዜጎችን መብት ማስከበር እንደሆነ በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡በዚህ አዋጅም ከአላማ አንፃር ከዚህ የተለየ ሊባል አይችልም፡፡ይሁን እንጂ የዜጎችን መብት ማስከበር የአዋጁ አላማ ነው በሚል መገለፁ በርግጥም የመንግስት ፍላጎት ይህ የነበረ መሆኑን አያረጋግጥም፡፡ይልቁንም ሕጉ ከፀደቀ በኋላም ለሽብርተኝነትየተሰጠው ትርጓሜ ሰፊና ወሰን አልባ መሆኑ፤መሠረታዊ የወንጀል ሕግ መርሆዎችን በሚቃረን ሁኔታ የማስረዳት ሸክምን ወደ ተከሣሽ ማዞሩ፣ለስሚ-ስሚ ማስረጃ ዕውቅና መስጠቱ፤በጅምላ የዋስትና መብትን መከልከሉ፤የግል ነፃነት መብትን የሚጥስ መሆኑ፤ሃሣብን በነፃነት የመግለጽ መብትን መገደቡ እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች እየተነሱ አዋጁ ተቃውሞን ለማፈን የወጣ ነው በሚል አንዲቀር ወይም እንዲሻሻል ብርቱ ጥያቄ ሲቀርብ የነበረ ቢሆንም በመንግስት በኩል አዋጁ በመስኩ የዳበረ ልምድ ካላቸው እንደ እንግሊዝ ካሉ አገሮች የፀረ-ሽብር ሕጎች ቃል በቃል የተወሰደ ነው በሚል ለማስፈፀም ከመንቀሣቀስ አልተቆጠበም፡፡እዚህ ላይ በአዋጁ ላይ ተቃውሞ ሲቀርብ የነበረው ከአገር ውስጥ ብቻ ሣይሆን ሕጋችንን ከሕጎቻቸው ነው የቀዳነው የተባሉትን አገሮች መንግስታት ጨምሮ ከበርካታ የዓለም አገሮችና ዓለም አቀፋዊ የሰበአዊ መብት ድርጅቶች መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡በሌላም በኩል አዋጁ ከሌሎች አገሮች የፀረ-ሽብር ሕጎች የተቀዳ ነው ቢባል እንኳን የእነዚህ አገሮች ሕጎች በወንጀሉ የተጠረጠሩ ሰዎች የመብት ጥሰት እንዳይደርስባቸው በቂ ጥበቃ የሚያደርጉ ዝርዝር ድንጋጌዎችን የያዙ ከመሆኑም በላይ ሕጎቹ ተፈፃሚ የሚሆኑበት አዋጅ የዴሞክራሲ እሴቶች የዳበሩበት፤የሕግ የበላይነት የሰፈነበት፤ለሰብአዊ መብቶች መከበር ትልቅ ዋጋ የሚሰጥበት እና የዳኝነት ነፃነት የሚከበርበት እና ሕጉን በማስከበር እና በመተርጎም የሚሳተፉተ ተቋማትም በሁሉም ረገድ ብቃት ያላቸው እና እነዚህን ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እሴቶች አጥብቀው የሚተገብሩ ከመሆናቸው አንፃር ጠንካራ አቅም ያለው የፀረ-ሽብር ሕግ ቢያወጡ የሚያሳስብ አይደለም፡፡ በእኛ አገር ግን የዲሞክራሲው ባሕል ያልዳበረ፤ለሰብአዊ መብቶች መከበር የሚሰጠውም ትኩረት አነስተኛ እና የፍትህ እና የሕግ አስከባሪ ተቋማቱም አቅም በእጅጉ ውስን በሆነበት ሁኔታ እንዲህ አይነቱን ሕግ በማውጣት ለመተግበር መሞከር ለሕፃን ልጅ በሁለቱም በኩል ስለት የሆነ ቢላዋ የመስጠት ያህል አደገኛ ነው በሚል ተቃውሞው ተጠናክሮ ቢቀጥልም መንግስት አዋጁን ለማስፈፀም ከመንቀሣቀስ አልታቀበም፡፡ከዚህ በላይ እንደተገለፀው አዋጁ አፋኝ እና በቀላሉ የጥቃት መሣሪያ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ሆኖ እያለ እና በአንፃሩ አገራችን ከሌሎች አገሮች በተለየ ሁኔታ ለሽብር ድርጊት የተጋለጠች መሆኑን የሚያሣይ በቂ ሁኔታ የሌላ መሆኑ እየታወቀ መንግስት ለሚቀርቡት ተቃውሞዎች ሁሉ ጆሮ ደባ ልበስ በማለት በአቋሙ መጽናቱ በአዋጁ መግቢያ ላይ ከተገለፀው ውጭ አንዳች የተደበቀ ዓላማ እንዳልነበረው በርግጠኝነት ለመናገር አይቻልም፡፡አዋጁ በእነማን ላይ ተፈፃሚ ሆነ፤ምን ዓይነት ክሶችስ ቀረቡ በእነማን ላይ ተፈፃሚ ሆነአዋጁ ሽብርተኝነትን ለመከላከል፤ለመቆጣጠር እና ለማምከን አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እንደታወጀ በመግቢያው ላይ ተገልፆ ይገኛል፡፡ በሌላም በኩል የሽብርተኝነት ድርጊት የሚባሉት የትኞቹ እንደሆኑ በአዋጁ ተዘርዝረው ተቀምጠዋል፡፡(የአዋጁ አንቀጽ3) እነዚህን የሽብርተኝነት ድርጊቶች በቀጥታ ከመፈፀም በፊት ድርጊቶቹን ለመፈፀም ማቀድ፤መዘጋጀት፤ማሴር፤ማነሣሣት እና መሞከርም እንደሚያስቀጣ በአዋጁ ተደንግጓል፡፡(የአዋጁ አንቀጽ4)ከዚህም ባሻገር ለሽብርተኝነት ድጋፍ መስጠት(የአዋጁ አንቀጽ5) ሽብርተኝነትን ማበረታታት (የአዋጁ አንቀጽ6)እና በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ መሣተፍ(የአዋጁ አንቀጽ7) ከፍተኛ የወንጀል ቅጣትን የሚያስከትሉ እንደሆኑ ተደንግጓል፡፡እነዚህ ድንጋጌዎች በአብዛኛው ግልጽነት የጎደላቸው እና ወሰን አልባ ትርጓሜ ያላቸው ከመሆኑ የተነሣ የሕጋዊነትን መርህን በመጣስ ማንኛውም ሰው በቀላሉ በሽብር ወንጀል ሊከሰስ የሚችልበትን ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው፡፡በመሆኑም በርካቶች መንግስትን የሚተቹ ጽሑፎችን በጋዜጣ እና በማህበራዊ ሚዲያ በማውጣታቸው ወይም በአደባባይ በመግለፃቸው የሽብርተኝነት ወንጀልን በማቀድ ወይም በማነሣሣት ተከሰዋል፡፡በዚህ ውስጥ በዋነኛነት ጋዜጦች፤የኢንተርኔት ፀሐፊዎች(ብሎገሮች)እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ወይም አክቲቪስቶች ተካተዋል፡፡በሌላ በኩል በርካታ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች እና አባላት የፓርቲ ሥራቸውን እየሰሩ ባሉበት በአዋጁ መሠረት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብለው ከተፈረጁት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦ.ኤል.ኤፍ) እና አርበኞች ግንቦት ሰባት ከተባሉት ድርጅቶች ጋር በተያያዘ አባል ሆናችኋል፤ ድጋፍ ሰጥታችኋል ወይም በማናቸውም ሁኔታ ተሣትፋችኋል እየተባለ በሽብር ወንጀል ተከሰዋል፡፡በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሽብርተኛ ድርጅት ተብለው ከተፈረጁት ድርጅቶች ውጪ የሆኑ ነገር ግን መንግስትን በሃይል እንቀይራለን ብለው የተነሱ ድርጅቶችን አመራሮችን እና አባላትንም መንግስት በሽብር ወንጀል ከሷል፡፡(በኋላ ላይ ፍ/ቤቶች እንዲህ ያሉ ክሶችን ወደ ጦርነት ማነሣሣት ወንጀል ጉዳይ ቀይረዋችዋል)፡፡በሐይማኖት ጉዳይ መንግስት ጣልቃ ገብቷል በሚል ተቃውሞ ያነሱ የእስልምና እምነት ተከታዮችን በመወከል ከመንግስት ጋር በግልጽ ሲደራደሩ የነበሩትን የሙስሊሙ ማህበረሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን መንግስት ሲያወያያቸው ቆይቶ በድንገት በሽብር ወንጀል ክስ እስር ቤት እንደወረወራቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ በዋነኛነት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል ተቀስቅሶ ከነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር ተያይዞም ወጣቶች፤አዛውንቶች፤ሴቶች፤ተማሪዎች፤ገበሬዎች፤ድምፃዊያን እና የመንግስት ሠራተኞች ሣይቀሩ በሽብር ወንጀል ክስ እየቀረበባቸው ዘብጥያ ወርደዋል፡፡ከዚህ ሁሉ ክስ ውስጥ በርግጥም አንድን የፖለቲካ፤የሃይማኖታዊ ወይም የአይዲዮሎጂ አላማን ለማራመድ በማሰብ በመንግስት ላይ ተፅእኖ ለማሣደር ፤ሕብረተሰቡን ወይም የሕብረተሰቡን ክፍል ለማስፈራራት ወይም ማህበራዊ ተቋማትን ለማናጋት ወይምለማፍረስ በማሰብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸውን መመዘኛዎች ባሟላ እና አብዛኞቻንን በሚያግባባ ደረጃ በሽብር ወንጀል መከሠሣቸው ተገቢ ነው ልንላቸው የሚችሉ ጉዳዮች ከመቶ ሁለት ወይም ሦስት የሚበልጡ አይደሉም፡፡በጥቅሉም የአዋጁ ልዩልዩ አንቀፆች እየተጠቀሱ የሽብር ክስ ይቀርብባቸውየነበሩት በፍትህ፤በዲሞክራሲ እና በሕግ የበላይነት ጉዳይ ከመንግስት የተለየ ሃሣብ ያላቸውና ሐሣባቸውንም ለማራመድ በመረጡት መንገድ የተንቀሣቀሱ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ሰዎች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡በሌላ አነጋገር በሽብር ወንጀል እየተከሰሱ ፍ/ቤት ይቀርቡ የነበሩት ግለሰቦች ይሁኑ እንጂ ክሶቹ ያነጣጠሩት አስተሣሰቦች ላይ ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ምን ዓይነት ክሶች ቀረቡ ከላይ እንደተገለፀው ከቀረቡት ክሶች ውስጥ በሐይል ተግባር ላይ የተመሠረተ እና በርግጥም የሽብር ወንጀል ባሕርይ አለው የሚባለው ክስ ቁጥር በእጅጉ አነስተኛ ነው፡፡ይልቁንም መንግስትን የሚተች ንግግር አድርጋችኋል፤በጋዜጣ ላይ ጽፋችኋል ወይም በማህበራዊ ሚዲያ አሠራጭታችኋል በሚል እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብለው በተፈርጁ ድርጅቶች ውስጥ ተሣትፋችኋል በሚል ነው፡፡በአንድ ጉዳይ ለምሣሌ ተከሣሾቹ በሕገ-መንግስቱ ዕውቅና የተሠጣቸውን መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶች እያነሱ በመብቶቹ ዙሪያ አጫጭር ጽሑፎችን በማዘጋጀት በኢንተርኔት ላይ በመለጠፍ የውይይት መድረክ በመፍጠራቸው እና ይህን በኢንተርኔት የሚያደርጉትን የመልዕክት ልውውጥ ከመንግስት ጥቃት ለመከላከል የሚያስችላቸውን ሥልጠና በዓለም አቀፍ ደረጃ በታወቁ የሰብአዊ መብት ተቋማት አማካኝነት በመውሰዳቸው ይኸው ጉዳይ የክስ ምክኒያት ሆኖ በሽብር ወንጀል ተከሰዋል(የዞን 9 ጦማሪያን ጉዳይ፣ የከ/ፍ/ቤ/መ/ቁ 155040)፡፡በአንድ በሌላ ጉዳይም ተከሣሹ ጋዜጠኛ መሆኑ እየታወቀ ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ በነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ በተለያዩ ቦታዎች ስለነበሩት ክስተቶች እየተከታተለ በመዘገቡ እና ኢሣት እየተባለ ከሚታወቀው በውጭ አገር ከሚገኝ የሣተላይት ቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ግንኙነት በማድረጉ በሽብር ወንጀል የተከሰሰ ሲሆን በጉዳዩ አንድ ዓመት ከአምስት ወር ከታሠረ በኋላ ግን በጋዜጠኝነት ለሠራው ሥራ በወንጀል አይጠየቅም የተባለ ቢሆንም የዚህ የቴሌቭዥን ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ የሆነው ግለሰብ በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ እንዳሉ በሐይለ ቃል መቃወሙን አስመልክቶ አዲስ የሰላማዊ ትግል ሥልት በመሆኑ ወጣቱ ሊከተለው ይገባል በማለት በግለሰቡ የፌስቡክ ገጽ ላይ አስተያየት መስጠትህ እና ግለሰቡ ደግሞ ቀደም ሲል የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል ሆኖ በመገኘቱ የተፈረደበት ስለሆነ የአንተ ድጋፍ የአሸባሪ ድርጅቱን የትግል ስልት መከተልህን ያሣያል በሚል የሽብር ክሱ ወደ ሕዝብን ለአመጽ ማነሣሣት ወንጀል ተቀይሮ ጥፋተኛ ተብሏል፡፡(ጌታቸው ሽፈራው ጉዳይ፣ የከ/ፍ/ቤ/መ/ቁ 178980) በጋምቤላ ክልል በሕብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው ግለሰብ በክልልሉ የሚካሄደውን ከፍተኛ የመሬት ቅርምት ሂደት አጥብቀው መቃወማቸው እና ይህንንም ለመከላከል ከአገር ውጪ ካሉ የክልሉ ነዋሪዎች እና ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመነጋገራቸው በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በዚሁ በመሬት ጉዳይ ሊመክር በተጠራ ዓለም አቀፍስብሰባ ላይ ለመገኘት ከሌሎች እሣቸው ከተለያዩ ክልሎች ካስተባበሯቸው ግለሰቦች ጋር በመሆን ወደ ናይሮቢ ለመጓዝ በቦሌ የአውሮፕላን ማረፊያ እንደተገኙ ተይዘው በፌደራልና በክልሉ አስተዳደር በከፍተኛ ሐላፊነት ተመድበው እየሰሩ ያሉ በርካታ የክልሉ ነዋሪ የሆኑ ሰዎችን በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ እንዲሣተፉ መልምለሃል፤አስተባብረሃል ወይም መርተሃል በሚል የሽብር ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡(በእነኦሞት አጉዋ ጉዳይ፣ የከ/ፍ/ቤ/መ/ቁ …)፡፡ከ2008 ዓ.ም ጅምሮ በኦሮሚያ ክልል የነበረው ሕዝባዊ አመጽ መንስኤው የመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑን የፌደራሉ እና ክልሉ ባለሥልጣናት በግልጽ በሚዲያ ጭምር አምነው እያለ በርካታ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦ.ፌ.ኮ)አባላት እና አመራሮች በአመፁ አደረጉ የተባሉት ጥቃቅን አስተዋጽዎ እየተመዘዘ ወይም በአካባቢው በመገኘታቸው ብቻ በሽብር ወንጀል ሲከሰሱ ቆይቷል፡፡(በእነ ጉርሜሣ አያኖ ጉዳይ፣ የከ/ፍ/ቤ/መ/ቁ 176385) ሰዎች የኦ.ነ.ግ ወይም የአርበኞች ግንቦት ሰባት ባንድራዎች፤አርማዎች ወይም ሌላ ማንኛውም ከድርጅቶቹ ጋር ግንኙነት ያላቸው ጽሑፎች ወይም ሰነዶችን ይዘው ተገኝተዋል፤ቤታቸው አስቀምጠዋል፤በኢ-ሜይል መልዕክት ሣጥናቸው ውስጥ ተገኝቷል በሚል መነሻ ብቻ የአዋጁ አንቀጽ 7/1እየተጠቀሰ የአሸባሪ ድርጅት አባል ናቸው በሚል በሽብር ወንጀል ተከሠዋል፡፡በአንዳንድ ጉዳዮችም የተባሉትን ባንዲራዎች ወይም ጽሑፎች ለብርበራ የተሠማሩት መርማሪዎች ራሣቸው በዘዴ በቤት ውስጥ አስቀምጠዋል የሚሉ ክርክሮች ቀርበዋል፡፡(በእነ ጉርሜሣ አያኖ ጉዳይ፣ የከ/ፍ/ቤ/መ/ቁ 176385) በሌላም በኩል በዚህ የአዋጁ አንቀጽ 7/1 ላይ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ “በማንኛውም መልክ የተሣተፈ” የሚለውን ወሰን አልባ አገላለጽ ተከትሎ በርካታ ሰዎች ከኦ.ነ.ግ ወይም አርበኞች ግንቦት ሰባት ጋር ተመሣሣይ ጥያቄዎች በማንሣታቸው ብቻ ከድርጅቶቹ ጋር ምንም ዓይነት ተግባራዊ ግንኙነት ባይኖራቸውም የድርጅቶቹን ዓላማ አራምዳችኋል በሚል በሽብር ወንጀል ተከሰዋል፡፡በአጠቃላይ አዋጁ ሽብርተኝነትን ለመከላከል፤ለመቆጣጠር እና ለማምከን የወጣ መሆኑ የተገለፀ ቢሆንም በዋነኛነት ያገለገለው ተቃውሞን ለማፈን ነው ለማለት ይቻላል፡፡ይህ ሁኔታም የታሰበውን ሰላም ከማምጣት ይልቅ ይበልጥ ቅራኔን በማስፋ ባለፉት ሦስት ዓመታት የታየውን ሕዝባዊ አመጽ እንዲቀጣጠል ምክኒያት ሆኗል፡፡በሕብረተሰቡ ዘንድም ሽብርተኝነት አንደ ተራ እና ቀላል ወንጀል እንዲቆጠር አድርጎታል፡፡የሽብርተኝነት ሕጉ በአመዛኙ የወንጀል ሕግ እንደመሆኑ መጠን በአፈፃፀሙ በማንኛውም የወንጀል ሕግ አፈፃፀም ሚና ያላቸው ተቋማት ሁሉ ይሳተፋሉ። ከዚህ አንጻር አዋጁን ልዩ የሚያደርገው ነገር ቢኖር በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የደህንነት ተቋሙ ሚና እንዲኖረው ግልጽ ሥልጣን የተሰጠው መሆኑ ነው። ተቋሙ በአዋጁ አፈፃፀም ስለነበረው ሚና በቦታው የሚገለጽ ይሆናል።የብሔራዊ (መረጃና) ደህንነት አገልግሎት መ/ቤትእንዲህ ዓይነቱ መ/ቤት የተለያየ ስያሜ ሊይዝ ቢችልም በሁሉም ወይም በአብዛኛው አገሮች የሚገኝ ተቋም ነው። የጋራ የሆነው ሥልጣኑም አገርን ከጥቃት መከላከል ነው። በእኛም አገር ተቋሙ ይህም ኃላፊነት ያለው ቢሆንም በተለያዩ ጊዜያት ግን ከዚህ ኃላፊነቱ ባሻገር የገዢውን ኃይል ሥልጣን ለማስጠበቅ ሲሠራና በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጫና ሲያደርግ ታይቷል። (ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በአንድ ወቅት ለፓርላማው ባደረጉት ገለጻ ይህንን ተቋም ጠቅሰው “በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ነው ወይ ያደራጀነው?” ብለው መጠየቃቸው ለዚህ አስረጂ ነው።)ይህ ተቋም በአዋጁ ሁለት ዓይነት ሥልጣን ተሠጥቶት እናገኛለን፡ የመጀመሪያው በሽብር ወንጀል ተጠርጥረዋል ያላቸውን ሰዎች የስልክ፣ የፋክስ፣ የሬዲዮ፣ የኢንተርኔት፣ የኤሌክትሮኒክስ፣ የፖስታና የመሳሰሉት ግንኙነቶችን መጥለፍ ሲሆን (የአዋጁ አንቀጽ 14) ሁለተኛው ደግሞ የመረጃ ሪፖርት ማዘጋጀት ነው (የአዋጁ አንቀጽ 23)። በአዋጁ አፈፃፀም ወቅት ተቋሙ እነዚህን በሕጉ የተሰጡትን ሥልጣኖች እንዴት ተጠቀመባቸው ብለን ስናይ አዋጁ በእነማን ላይ ተፈጻሚ ሆነ ከሚለው ጋር በቀጥታ ተያያዥነት ያለው ሆኖ እናገኘዋለን።በእርግጥም አሸባሪዎች ሣይሆኑ ከመንግስት የተለየ አስተሳሰብ ያላቸው ዜጎች ሁሉ የግል የነጻነት መብት ተጥሶ የሚያደርጉት የግል ግንኙነት ሁሉ በዚህ ተቋም ቁጥጥር ሥር ወድቆ ነበር ለማለት ይቻላል። በእርግጥ በአዋጁ የንጹሐን ዜጎች የግል ነጻነት ያለአግባብ እንዳይጣስ ጥበቃ እንዲያደርጉ ታስበው የተደነገጉ ገደቦች ያሉ ቢሆንም እነዚህ ገደቦች በትክክል ስለመጠበቃቸው የሚከታተል አካል አልነበረም።ለጉዳዩ ቅርበት ያለው ፍ/ቤት እንኳን ተከሣሾች በስልክ ሲነጋገሩ በጠለፋ የተገኘ ነው በሚል ከተቋሙ የተላከ ማስረጃ ሲቀርብለት በሕጉ መሠረት በፍ/ቤት ፈቃድ የተደረገ ለመሆኑ ለማጣራት ሲሞክር አይታይም። እንዲያውም በዚህ ረገድ በተከሣሾች በኩል ለሚቀርብ ጥያቄ ተቋሙ በላከው ማስረጃ ላይ “በፀረ-ሽብር አዋጅ አንቀጽ 14 መሠረት የተገኘ ነው” ተብሎ መገለፁ ፍ/ቤቱ ጠለፋው የተደረገው በፍ/ቤት ፈቃድ መሆኑን ይገምታል በሚል የታለፈበት አጋጣሚም በርካታ ነው። (በእነ ጉርሜሣ አያኖ ጉዳይ፣ የከ/ፍ/ቤ/መ/ቁ 176385) ከዚህ ውጪ ተቋሙ በጠለፋ አገኘሁት የሚለው መረጃ በምስጢር መጠበቁን ማረጋገጫ ሥርዓትም የለም።ተቋሙ ለፍ/ቤት ሊያቀርብ እንደሚችል ከተገለጸው የመረጃ ሪፖርት (የአዋጁ አንቀጽ 23) ጋር በተያያዘም በአንድ በኩል የመረጃውን ምንጭ ወይም መረጃው እንዴት እንደተገኘ ባይገለጽም እንኳን በፍ/ቤት በማስረጃነት ተቀባይነት ሊኖረው እንደሚገባ በመደንገጉ ፍ/ቤቶች ‘በዚህ መንገድ የቀረበውን ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን የለንም’ በማለት በዚህ የመረጃ ሪፖርት ላይ ብቻ በመወሰን የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥተዋል። ተቋሙ የመረጃውን ምንጭ እንዲገልጽ አይገደድም የሚል አቋም በመያዙም ተከሣሾች በዚህ መልክ የሚቀርብባቸውን ማስረጃ ለማስተባበል የሚችሉበት ዕድል አልነበረም።በሌላም መንገድ የሚቀርበው የመረጃ ሪፖርት እውነተኛ መሆኑን ለማጣራት የሚቻልበት ሁኔታ አልነበረም። በአንድ ከቀረበ የመረጃ ሪፖርት ጋር በተያያዘ ተከሳሾቹ የደህንነት መ/ቤቱ አገኘሁ የሚለውን መረጃ በራሱ ቋንቋ ጽፎ ሳይሆን እንዳለ ጥሬውን እንዲያቀርብ ጠይቀው ፍ/ቤቱም በዚህ አንጻር እንዲፈጸም ትዕዛዝ ቢሰጥም ተቋሙ በፍ/ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት ለመፈፀም ያለመቻሉ (እነ ሐብታሙ አያሌው) ምናልባትም የሐሰት የመረጃ ሪፖርት ሊቀርብም እንደሚችል አመላካች ሆኗል።በምርመራ ወቅት ተቋሙ ከሕግ ውጪ በማይታወቁ ቦታዎች ሰዎችን ያስር እንደነበር በበርካታ የክስ ሂደቶች ላይ ተከሣሾች ለፍ/ቤት ሲገልጹ ተሰምተዋል። ብዙዎቹ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ መምሪያ (ማዕከላዊ) ከመግባታቸው በፊት ለቀናት ወይም ለወራት የት እንደሆነ ለይተው የማያውቁት ቦታ ታስረው መቆየታቸውን ገልጸው ፍ/ቤትም መዝግቦታል።በአጠቃላይ ተቋሙ በአዋጁ በግልጽ ከተሰጠው ሥልጣን ባሻገርም በአዋጁ አፈፃፀም ዙሪያ በምርመራ፣ በክስ ዝግጅት እና በፍርድ ሥራ ጭምር ዋነኛ ወሣኝ አካል እንደሆነ ሰፊ ግንዛቤ ተይዟል።ፖሊስ (የፌደራል ፖሊስ)ከዚህ በላይ እንደተገለጸው በአዋጁ አፈፃፀም ጉዳይ የደህንነት ተቋሙ ጡንቻ ብርቱ የነበረ ከመሆኑ አንጻር ፖሊስ በዚሁ ተቋም ተጽዕኖ ሥር ሆኖ ከሕግ አንጻር ሰዎችን በወንጀል ለመጠርጠር የሚያበቃ ማስረጃ ሳይሰበሰብ ያስር እና ካሰረ በኋላ ማስረጃ ያሰባስብ እንደነበር በጊዜ ቀጠሮ ክርክር ወቅት ዘወትር የሚነሳ ጉዳይ ነው። ይህም በመሆኑ ፖሊስ በሕጉ ከተቀመጠው የአራት ወር የምርመራ ጊዜ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ምርመራዬን ጨርሻለሁ ያለባቸው አጋጣሚዎች እጅግ አነስተኛ ናቸው። ሰዎች በዚህ መልክ በፖሊስ እጅ ከገቡ በኋላ እንደነገሩ ሁኔታ ለመጀመሪያዎቹ ቀናት ወይም ሳምንታት አልፎ አልፎም ወራት ከቤተሰቦቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው እና ከጠበቆቻቸው ጋር ጭምር እንዳይገናኙ ይከለከሉ ነበር። ፖሊስ ለዚህ ይሰጥ የነበረው መልስም “ምርመራ አልጨረስኩም” የሚል ነበር። ይህ በዋናነት የተያዘው ሰው የእምነት ቃል አልሰጠም ማለት እንደሆነ ብዙ ጊዜ ጠበቆች ከታሰሩት ሰዎች ጋር እንድንገናኝ በተፈቀደልን ጊዜ የሚነግሩን ነው።ፖሊስ የተያዙ ሰዎች በሕግ የታወቀውን ከቤተሰቦቻው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከትዳር ጓደኞቻቸው እና ከጠበቆቻቸው ጋር የመገናኘት መብታቸውን እንዳይጠቀሙ ከመከልከል ባሻገር ታሳሪዎቹን በማስፈራራት እና ልዩ ልዩ የኃይል ተግባሮችን በመፈጸም የእምነት ቃል ለማግኘት ይሰሩ እንደነበር አብዛኞቹ ታሳሪዎች በማማረር የሚገልጹት ነው። እጅግ ውስን በሆኑ ጉዳዮችም ቢሆን ፍ/ቤቶችም በማስረጃነት የቀረበላቸውን የእምነት ቃል ከሕግ ውጪ በማስገደድ የተገኘ ነው በማለት ውድቅ ሲያደርጉ ታይቷል።ሌላው ፖሊስ ዋነኛ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ የታየው፤ ሰዎችን ቸኩሎ በማሰር እና በምርመራ ስም እንዲንገላቱ ማድረግ እንጂ ከዚህ በኋላ ባለው ሂደት በተለይ ክስ ከተመሠረተ በኋላ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን በጊዜው በማቅረብ፤ ‘ኤግዚቢቶች’ ካሉ እንዲቀርቡ በታዘዘበት ጊዜ ወዲያውኑ በማቅረብ፤ ሌሎች ከፍ/ቤት ለሚሰጡ ትዕዛዞች አጥጋቢ እና ወቅታዊ ምላሽ በመስጠት በኩል ደስተኛ በመሆኑ የተከሰሱ ሰዎች አፋጣኝ ፍትህ እንዳያገኙ እና በተራዘመ የክርክር ሂደት ተጨማሪ እንግልት እንዲደርስባቸው አስተዋጽኦ ሲያደርግ ቆይቷል። እንዲያውም አብዛኞቹ ተከሣሾች ፖሊስ ሆነ ብሎ ጉዳያቸው እንዲጓተት እንደሚያደርግ በተደጋጋሚ ስሞታ ሲያሰሙ ተደምጠዋል።በአጠቃላይ ፖሊስ በወንጀል ጉዳይ የምርመራ ሥራን በመምራት ረገድ ያለው የተለመደ እና የቆየ ሥልጣን በፀረ-ሽብር አዋጁ አፈፃፀም ጊዜ በደህንነት ተቋሙ ተቀምቷል ለማለት የሚቻል ሲሆን ይህም የምርመራ ሂደቱን ከሕግ የማስከበር ጉዳይነት ይልቅ ይበልጥ የፖለቲካ ሥራ እንዲመስል ወይም እንዲሆን አድርጎታል።ዐቃቤ ሕግ (የፌደራል ዐቃቤ ሕግ)በፀረ-ሽብር አዋጅ አፈፃፀም ዋነኛ ከሣሽ የነበረው በቀድሞ መጠሪያው የፍትህ ሚኒስቴር በኋላ ደግሞ የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ነው። ይህ ተቋም የፌደራል መንግስቱ ዋነኛ ከሣሽ ከመሆኑ በተጨማሪ በሕግ ጉዳዮች የፌደራል መንግሥት አማካሪ መሆኑ በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ተገልጾ ይገኛል። በሌላ በኩል ተቋሙ ለበርካታ ዓመታት በአመራር መፈራረቅ እና በሌሎች ውስጣዊ ምክንያቶች የዐቃቤ ሕግ ኃላፊነትን ጠንቅቀው የሚያውቁ እና ኃላፊነት የሚሰማቸውን በርካታ ባለሙያዎች አጥቷል። ታድያ ተቋሙ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ነው ይህን ቀድሞውንም ላልተገባ አፈፃፀም የተመቻቸውን አዋጅ የማስፈፀም ኃላፊነት የተረከበው።በመሆኑም ተቋሙ አዋጁ በግልጽ ከተቀመጠለት ዓላማ አንፃር ሳይሆን ተቃውሞን ለማፈን ሲውል፤ ሕዝብ ሊከሰስበት፣ የከሰሣቸው ሰዎች በየእሥር ቤቶች ፍዳቸውን ሲያዩ ሁኔታው ትክክል አለመሆኑን ለመንግሥት ምክር ከመስጠት ይልቅ ዋነኛው ተዋናይ ሆኖ ቀጥሏል።ተቋሙ በታሰሩት ሰዎች ላይ ለዚያውም የሽብር ወንጀል ክስ ለማቅረብ በቂ ማስረጃ መኖር አለመኖሩ ብዙም ሳይገደው እና የፍ/ቤቱን አቅምም ባላገናዘበ ሁኔታ የደህንነት ተቋሙና ፖሊስ ባስተላለፉት ጉዳይ ሁሉ ክስ እየመሠረተ ወደ ፍ/ቤት መላኩ ሳያንሰው የሚልካቸው ክሶች በአመዛኙ ተከሣሹ ተገዶ ለፖሊስ የሚሰጠው የእምነት ቃል ግልባጭ ከመሆናቸው በተጨማሪ ጨርሶ ጥራት የሌለው፣ ለተደጋጋሚ የክስ መቃወሚያ የተጋለጡ እና ፍ/ቤት ለተደጋጋሚ ጊዜ እንዲሻሻሉ ትዕዛዝ የሚሰጥባቸው ነበሩ። በአንድ ጉዳይ በቀረበ ክስ ላይ ተከሣሾች አሥራ አምስት ያህል ጉድለት አንስተው ፍ/ቤት ስምንት ያህሉን በመቀበል ዐቃቤ ሕግ ክሱን እንዲያሻሽል ትዕዛዝ ቢሰጥም ዐቃቤ ሕግ ግን ለሦስት ተከታታይ ጊዜ ያህል በታዘዘው መሠረት ለማሻሻል ሣይችል የቀረ ከመሆኑም በላይ በመጨረሻም በአንድ ክሱ ይሻሻል በተባለበት ጉዳይ ፍሬ ነገሩ ከክሱ ዝርዝር ውስጥ እንዲሰረዝ ወይም እንደሌለ እንዲቆጠር ብይን ተሠጥቷል። (በዞን ዘጠኝ ጠማሪያን ጉዳይ፣ የከ/ፍ/ቤ/መ/ቁ 155040) ከክሱ ጥራት ጋር በተያያዘ ሌላው በዐቃቤ ሕግ በኩል በዘፈቀደ ሲፈጸም የነበረው ፈጽሞ የማይተዋወቁ እና ተፈጸመ በተባለው የወንጀል ድርጊትም ተሣትፏቸው ፈጽሞ የማይገናኙ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን በግብረ-አበርነት ጭምር በአንድ መዝገብ ከስሶ በዳኝነት አሠራር ላይ ከፍተኛ ችግር ከመፍጠሩም በላይ ሰዎች የተፋጠነ ፍትህ እንዳያገኙ ጉልህ ድርሻ ተጫውቷል።በክርክር ሒደቱ ዐቃቤ ሕግ ተከሣሾች ዋስትና ተከልክለው በእሥር ላይ መሆናቸውን ባገናዘበ መልኩ ለሚከራከርባቸው ጉዳዮች በቂ ትኩረት ሰጥቶ ምስክሮቹን በሰዓቱ ለማቅረብ ሳይችል የሚቀርባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው። በሌላ ጊዜ ደግሞ በተለየ ሁኔታ ትኩረት እንዲደረግባቸው በተፈለጉ ጉዳዮች ክስ በቀረበበት የወንጀል ጉዳይ ዋና ተሣታፊ ነበሩ ከተባሉ ተከሣሾች ጋር ጭምር በምርመራ ሰዓት ግልጽነት የጎደለው ድርድር በማድረግ ከተከሣሽነት አውጥቶ በምስክርነት ሲያቀርባቸው ታይቷል። በአንድ የክስ መዝገብ ጉዳይ የታጣቂዎች አዛዥ ወይም ኮማንደር ነው የተባለው ግለሰብ ተራ ታጣቂዎች ናቸው ተብለው ክስ በቀረበባቸው ግለሰቦች ላይ ምስክር ሆኖ እንዲቀርብ ተደርጓል። (በእነ ኦኬሎ አኳይ ጉዳይ፣ 154647)። እዚህ ላይ ዋነኛ ተሣትፎ ያለው አነስተኛ ተሣትፎ ባላቸው ላይ ምስክር ሆኖ እንዲቀርብ ማድረጉ ብቻ ሣይሆን እዚህ ውሣኔ ላይ የሚደርሰው በአጠቃላይ በጉዳዩ ላይ የማስረጃ እጥረት ስለገጠመው ይሁን በሌላ ምክንያት (ከሙስና ጋር የተያያዘ ስሞታ መኖሩን ልብ ይሏል) ግልጽ ያለመሆኑ ጭምር ነው።በሌላም በኩል ዐቃቤ ሕግ ክሱን ያስረዱልኛል ብሎ የሚቆጥራቸው ምስክሮች በአብዛኛው በተለምዶ የደረጃ ምስክሮች የሚባሉት እና ተከሣሹ በምርመራ ወቅት የዕምነት ቃሉን ሣይገደድ በነፃ ፈቃዱ ሲሰጥ አይተናል ወይም የተከሣሽ ቤት ወይም ቢሮ ሲበረበር ወይም ኮምፒዩተሩ ተከፍቶ ሰነድ ሲወጣ ታዝበናል የሚሉ ናቸው። እነዚህ ዓይነት ምስክሮች በመሠረቱ የሕግ መሠረት የሌላቸው ከመሆኑም በላይ በአብዛኛው በቦታው ሳይኖሩ ነበርን ብለው በሐሰት የሚመሰክሩ እና በተለምዶም ‘አዳፍኔ ምስክሮች’ እየተባሉ የሚታወቁ ከመሆኑም በላይ ከጸረ-ሽብር አዋጁ አፈፃፀም ጋር በተያያዘ ደግሞ ጭራሽ በዚህ ደረጃ በምስክርነት እየተቆጠሩ ይቀርቡ የነበሩት ገለልተኝነታቸው ፍጹም አጠራጣሪ የሆኑ የቀበሌ መስተዳድር አባላት፣ የወረዳ የፀጥታ ሠራተኞች እና የገዥው ፓርቲ አደረጃጀት አባላት መሆናቸውን ለችሎቱ ጭምር ሲገልጹ ተሰምተዋል። በመጨረሻም ዐቃቤ ሕግ የመንግስት ከሣሽ ብቻ ሣይሆን ዋና ሕግ አስከባሪና በሕገ-መንግስቱ መሠረትም የሰበአዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር ግዴታ የተጣለበት ቢሆንም ተከሣሾች በምርመራ ወቅትና በክርክር ሂደት በቀጠሮ እስረኛ ማቆያ እና በማረሚያ ቤቶች ለጆሮ ለመስማት የሚያሳቅቁ የሰበአዊ መብት ጥሰቶች አቤቱታዎች ሲቀርቡ ጉዳዩን በባለቤትነት ስሜት እና በንቃት ተከታትሎ የሚታረሙበትን መንገድ ከመፈለግና ጥሰት ፈፃሚዎቹም እንዲጠየቁ ከማድረግ ይልቅ የሙግቱ አካል አድርጎ በመውሰድ የተከሣሾችን አቤቱታ ሲቃወም እና ፍ/ቤትም ሊወሰድ የሚችለውን እርምጃ ሲከላከል ታይቷል።ፍርድ ቤቶች (የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤቶች)ከዚህ በላይ እንደተገለፀው ዐቃቤ ሕግ ከጸረ-ሽብር አዋጁ አፈፃፀም ጋር በተያያዘ የፍ/ቤቱን አቅም ባላገናዘበ ሁኔታ እጅግ በርካታ ክሶችን ለፍ/ቤት አቅርቧል። ይህ የዐቃቤ ሕግ ችግር ሆኖ መነሳቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የፍ/ቤቱ አስተዳደርም የሚቀርቡት ክሶች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱን እያወቀ ይህን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ክስ ለማስተናገድ የሚችል የችሎት አደረጃጀት ባለመፍጠር ተከሣሾች የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት እንዳይከበር ዋነኛውን ድርሻ ተጫውቷል ለማለት ይቻላል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተከሣሾችን የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት የማስከበር ቀዳሚ ኃላፊነት የዳኞች ሆኖ ሳለ፤ የሽብር ችሎቶች ላይ ሲሰየሙ የነበሩት ዳኞች በክስ መዛግብት መጥለቅለቃቸው ግልጽ ሆኖ እያለ አስተዳደሩ ተጨማሪ ችሎቶችን እንዲከፍት ለማስገደድ ሥልጣን እንዳላቸውና ግዴታም እንዳለባቸው ባለመረዳት ተከሣሾች የቀጠሮ ረዘመብን፣ ፍትህ ዘገየብን አቤቱታ ሲያቀርቡ አንዳንዴ አቤቱታው ተገቢ እንዳልሆነ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ችግሩ ከእነሱ ሣይሆን ከፍ/ቤቱ አስተዳደር መሆኑን እየገለፁ የተከሣሾች የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት ሳይከበር እንዲቀር አስተዋጽኦ አድርገዋል።እስካሁን ሲገለጽ እንደነበረው አብዛኞቹ በሽብር ወንጀል እየተከሰሱ ፍ/ቤት ሲቀርቡ የነበሩት የመብት ጥያቄ አንስተው በተለያየ መንገድ ሲታገሉ የነበሩ እና በንቃተ-ሕሊናቸውም ሆነ በሞራል ደረጃቸው ከሌሎች በተራ ወንጀሎች ከሚከሰሱ ሰዎች ከፍ ያለ እና የትኛውንም ኢ-ፍትሐዊ እርምጃ ሊታገሱ የሚችሉ እንዳልሆነ እየታወቀ ዳኞች ከራሳቸው እና ከፍ/ቤቱ አስተዳደር ጉድለት በሚመነጩ የፍትህ መዘግየት እና ሌሎች ችግሮችን ተከሣሾች አሜን ብለው እንዲቀበሉ የጠበቁ ቢሆንም ይህ በብዙ አጋጣሚዎች ሲሳካ አልነበረም። ይልቁንም በአንዳንድ አጋጣሚዎች ተከሣሾች እነዚህ ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን የታሰርነው በግፍ ነው ከሚለው እምነታቸው ጋር ደምረው በማየት ችሎቱን በአጠቃላይ እና ዳኞችን በስም እየጠቀሱ ያዋርዱ፣ ይዘልፉ እና ጥቃት ለመፈጸምም እንዲነሳሱ ተደርገዋል።በዚህም የችሎት ክብር እንዲዋረድ /እንዲናቅ እና በሕብረተሰቡም ዘንድ በአጠቃላይ ፍ/ቤት የገዥው ኃይል መሣሪያ ተደርጎ እንዲወሰድ አስተዋጽኦ አድርጓል። ዳኞች አሠራራቸውን በማቀላጠፍ እና በፍ/ቤቱ አስተዳደር ላይም ተገቢውን ጫና በማድረግ ሁኔታውን ለማሻሻል ከመምከር ይልቅ የተለመደውን አሠራር ተከትለው በምክንያት የተቆጡ ተከሣሾችን ችሎት በመድፈር ወንጀል በመቅጣት ጉዳዩን ይበልጥ እንዲወሳሰብ አድርገውታል። አንዳንድ ዳኞችም በግል ሥሜት በመነሣሣት በሚመስል ሁኔታ ከተከሣሾች ጋር እልህ በመጋባት ችሎቱ የዳኝነት ሥራ የሚከናወንበት ሳይሆን የፖለቲካ ትግል የሚደረግበት መድረክ እንዲመስል አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ታይቷል።ፍርድ ቤቱን በርግጥም ፍ/ቤት የሚያሰኘው ከሁሉም በላይ የዳኝነት ነፃነቱ ነው። ነፃነት የሌለው ፍ/ቤት ምንም ያህል ቀልጣፋ ወይም በቂ የሕግ እውቀት ባላቸው ዳኞች የተሞላ ቢሆንም ተቋማዊም ሆነ ግለሰባዊ ነፃነት ከሌለ ያ ፍትህን ሊያረጋጥ የሚችል ፍ/ቤት ሊሆን አይችልም። በሌላ በኩል የዳኝነት ነጻነት ለማረጋገጥ ሊረዱ የሚችሉ የሕግ ጥበቃዎች መኖራቸው አስፈላጊ ቢሆንም ፍ/ቤቶች በሕብረተሰቡ ዘንድ ነፃና ገለልተኛ ሆነው የመታየታቸው አስፈላጊነትም እጅግ ወሣኝ ጉዳይ ነው። ከጸረ-ሽብር አዋጁ አፈፃፀም ጋር በተያያዘ ይህ የተሣካ አይመስልም።ሕብረተሰቡ ቀድሞውንም የፖለቲካ ክስ ነው ብሎ ያመነውን የሽብር ክስ የሚዳኘውን ፍ/ቤት ነፃና ገለልተኛ ነው ብሎ ይወስደዋል ለማለት አይቻልም።አንዳንድ በፍ/ቤቶች ሲፈፀሙ የሚታዩ እና የሚሰጡ ትዕዛዞች እና ውሣኔዎች ደግሞ ይህን የሕብረተሰቡን አተያይ (perception) የሚያጠናክሩ ሆነው ተገኝተዋል። ለምሣሌ በአንድ የሽብር ክስ ጉዳይ ክሱን የመረመረው ፍ/ቤት ተከሣሾችን በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ ቁጥር141 መሠረት ክሱን መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ ያሠናብታቸዋል። በዚያው እለትም ከእስር እንዲፈቱ ለማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ይሁን እንጂ ትዕዛዝ የደረሰው ማረሚያ ቤት ተከሣሾችን በዕለቱ ቀርቶ በማግስቱም አልፈታም። በዚህ መካከል ዐቃቤ ሕጉ የሥር ፍ/ቤቱን ውሣኔ በመቃወም ይግባኝ ለጠቅላይ ፍ/ቤት ከማቅረቡም በላይ የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕጉን ቁጥር 188/5 ጠቅሶ ተከሣሾች በነጻ የተሰናበቱበት የሥር ፍ/ቤቱ ውሣኔ ሣይፈፀም ታግዶ እንዲቆይ አመልክቷል።ይሁን እንጂ ዐቃቤ ሕጉ ይግባኙን ሲቀርብ የሥር ፍ/ቤትን ውሣኔ አያይዞ እንዲያውም ዐቃቤ ሕጉ የሥር ፍ/ቤቱን ውሣኔ አለማያያዙን እና ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የሥርመዝገቡን አስቀርቦ እንዲመለከት ጠይቋል። ይህ ሆኖ እያለ ግን ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የሥር ፍ/ቤት ውሣኔን ሣይመለከት በዐቃቤ ሕጉ የይግባኝ ማመልከቻ ላይ ብቻ በመመሥረት እና ለጉዳዩ ምንም አግባብነት የሌለውን ሕግ መሠረት በማድረግ ተከሣሾች በነፃ ይሰናበቱ የተባለበትን የሥር ፍ/ቤት ውሣኔ እንዳይፈፀም አግዷል። (በእነ ሐብታሙ አያሌውጉዳይ፣ የጠ/ፍ/ቤ/መ/ቁ … ) በመዝገቡ በነጻ ተሠናብተው የነበሩት ተከሣሾች ለተጨማሪ ሰባት ወር ከታሰሩ በኋላ የሰበር ሰሚው ችሎት የይግባኝ ሰሚውን ውሣኔ ሽሮ ተከሣሾች ከእስር ተለቀዋል)በአንድ በሌላ ጉዳይ ደግሞ ተከሣሹ በሽብር ወንጀል ተከሰው ሲከራከሩ ከቆዩ በኋላ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ማስረዳት የቻለው የቀረበውን የሽብር ወንጀል ሣይሆን ሌላ ተራ ወንጀል ነው በሚል አንቀጽ ሲቀየር የተቀየረው አንቀጽየዋስትና መብትን የማያስከለክል ሆኖ በመገኘቱ ተከሣሹ የዋስትና መብቱ እንዲከበርለት ጥያቄውን አቅርቧል። ዐቃቤ ሕጉም ለጥያቄው ምላሽ ሰጥቷል። ክርክሩም ለመወሰን አስቸጋሪ ነው ሊባል የማይችል አጭርና በጣም ግልጽ ነበር። ይሁን እንጂ ጥያቄው የቀረበለት ችሎት መደበኛ የችሎት ዳኛ አልተገኘልንም በማለት ለተደጋጋሚ ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ እየሰጠ ከአንድ ወር በላይ በጉዳዩ ውሣኔ ሣይሰጥ ቆይቷል።በመጨረሻ ላይ ግን በጉዳዩ ላለመወሰን ሲሰጥ የነበረውን ምክኒያት ፈጽሞ በሚቃረን ሁኔታ በክርክሩ አንድም ጊዜ ተሰይመው የማያውቁት የፍ/ቤቱ ፕሬዚዳንት የፈረሙበት የዋስትና ጥያቄውን በመከልከል ውሣኔ ተሰጥቷል። (እነ ጉርሜሣ አያኖ በሚለው መዝገብ አቶ በቀለ ገርባ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ይመለከታል)።ከዚህ የዋስትና መብት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ተከሣሹ ከፍተኛው ፍ/ቤት የዋስትና መብታቸውን በመከልከል የሰጠውን ውሣኔ በመቃወም ይግባኝ ለጠቅላይ ፍ/ቤት አቅርበው ይግባኝ ሰሚው የሥር ፍ/ቤቱን ውሣኔ በመሻር በዋስ እንዲለቀቁ እና በእለቱም ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ይሁን እንጂ ትዕዛዙ የደረሰው ማረሚያ ቤት እንደተለመደው በዕለቱ ቀርቶ በማግስቱም ያልፈታቸው ሲሆን ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የይግባኝ ሰሚውን ውሣኔ በመቃወም አቤቱታውን ለሰበር ሰሚው ችሎት አቅርቧል። እዚህ ላይ ደግሞ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው የሰበር አቤቱታ ላይ የይግባኝ ሰሚው ውሣኔ እንዲታገድለት አልጠየቀም ይሁን እንጂ አቤቱታውን የተመለከተው የሰበር ሰሚ ችሎት ባልቀረበለት የዳኝነት ጥያቄ የጠቅላይ ፍ/ቤቱን ውሣኔ በማገድ ተከሣሽ በእስር እንዲቆዩ አዟል። (የአቶ በቀለ ገርባ የይግባኝ ማመልከቻ- የሰበር ሰሚ ችሎት መዝገብ…)ባለፉት ሦስት አመታት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል ከተከሰቱት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ጋር በተያያዘ በቀረቡ የሽብር ወንጀል ክሶች ጉዳይ ተከሣሾች መዳኘት ያለብን በክልላችን ነው በሚል ተደጋጋሚ የክስ መቃወሚያዎችን አቅርበዋል።መቃወሚያዎቹ የቀረቡላቸው ችሎቶች ጥያቄዎቹን ውድቅ በማድረግ ሁሉም ጉዳዮች በአዲስ አበባ ብቻ እንዲታይ ሲወስኑ የሰጧቸው ዝርዝር ምክንያቶች ወጥነት የሌላቸው እና ልዩ ልዩ ጉድለት ያለባቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በውጤታቸው ግን የክልሎችን ሕገ-መንግስታዊ የዳኝነት ሥልጣን የጣሰ ብቻ ሣይሆን ጉዳዮቹ በአዲስ አበባ ብቻ እንዲታዩ በሆነ ኃይል ተጽእኖ የተደረገ እንደሆነ አስመስሎታል። በክርክር ሒደት የተከሣሾች በቂ የሕግ ድጋፍ አለማግኘት፣ የተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት አቅም ውስን መሆን፣ ተከሣሾች ከተለያዩ ክልሎች እንደመምጣታቸው እና የፍ/ቤቱን የሥራ ቋንቋ የማይሰሙ እንደመሆናቸው በቂ አስተርጓሚ ያለመኖር ተከሣሾች ከማረሚያ ቤት አያያዝ ጋር በተያያዘ ለሚያነሱት የመብት ጥያቄ ተገቢውን ትኩረት አለመስጠትና በአጥፊዎች ላይ ተገቢውን እርምጃ አለመውሰድ ተደጋግመው የታዩ ችግሮች ነበሩ።የቀጠሮ እስረኞች ማቆያ (ቂሊንጦ) እና የማረሚያ ቤቶችየ17 ዓመቱ የትጥቅ ትግል እንደተጠናቀቀ ኢሕአዴግ ቅድሚያ ሰጥቶ ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠራቸው ተቋማት አንዱ የእስረኞች ማቆያ ወይም ማረሚያ ቤቶችን ነው። ለዚህም ይመስላል ዛሬም ድረስ ዋነኛው የግምባሩ አባል የሆነው የሕወሓት ሠራዊት አባላት ዛሬም ድረስ በእነዚህ ተቋማት አካባቢ ከከፍተኛ የአመራር ደረጃ እስከ ታችኛው የጥበቃ እርከን አብዛኛውን ቦታ ይዘው ይገኛሉ። መንግሥት ከዚህ አንጻር በመከላከያ ሠራዊቱ አካባቢ የማመጣጠን ሥራ ሠርቻለሁ ቢልም በእነዚህ ተቋማት አካባቢ ግን ተሞክሯል ለማለት እንኳን የሚቻል አይመስልም። ይህ በራሱ ችግር ሆኖ ላይወሰድ ይችላል። ችግሩ አብዛኞቹ የተቋሙ ኃላፊዎችና የጥበቃ ሠራተኞች በትጥቅ ትግሉ ወቅት በነበራቸው ሚና እና አሁን በተቋማቱ ውስጥ ባላቸው ሐላፊነት መካከል ስላለው ልዩነት በቂ ግንዛቤ ያላቸው አይመስልም።በመሆኑም አብዛኞቹ ኃላፊዎችና የጥበቃ ሠራተኞች በተቋማቱ ውስጥ ታስረው ያሉ ሰዎችን የሚመለከቱበት ዓይን የተዛባ ነው ማለት ይቻላል። አብዛኛዎቹ ኃላፊዎቹና ሠራተኞቹ ታሣሪዎቹን የሚመለከቱት በአንድ ወቅት ሕግን ተላልፈዋል ተብለው ተጠርጥረው እና ተከሰው ፍትህን እንደሚጠባበቁ ወይም ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ተፈርዶባቸው ታርመው መውጣት እንዳለባቸው ሣይሆን በጦር ሜዳ ሲፋለሟቸው እንደነበሩ የሥርዓት ጠላቶች ነው ማለት ይቻላል። በዚህም ምክንያት ለእስረኞች ደህንነት እና ለሚያነሷቸው የመብት ጥያቄዎች የሚሰጡት ትኩረት በእጅጉ አናሳ ነበር።ይህ ስለ እሥረኞች ያለው የተዛባ አመለካከት ቀደም ሲልም ጀምሮ ያለ ቢሆንም በተለይ የጸረ-ሽብር አዋጁ መተግበር ጀምሮ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ ጋዜጠኞች እና የሥርዓቱ ተቺዎች በብዛት ወደ እሥር ቤት መግባት ሲጀምሩ ተባብሶ ለመቀጠሉ በየጊዜው እሥረኞች በችሎት በመማረር እያነሷቸው የነበሩ እና አሁን ከእስር ሲፈቱ ደግሞ በይፋ እየተነገሩ ያሉት አሰቃቂ የመብት ጥሰቶች አስረጂ ናቸው።ከጸረ-ሽብር አዋጁ አፈፃፀም ጋር ተያይዞ ከእስር ቤቶች አንፃር ሊነሣ የሚችለው ሌላው ጉዳይ በእሥር ቤቱ ተፈጻሚ ይሆን ስለነበረው ‘የዲሲፕሊን’ ቅጣት አፈፃፀም ሁኔታ ነው። በየትኛውም እሥር ቤት በታሣሪዎች በኩል የእሥር ቤቱን ደንብ ያለመከተል ወይም የመጣስ ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ይገመታል። ይህ ሁኔታ ባጋጠመ ጊዜም ተገቢውን የሥነ-ሥርዓት እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ሊሆን እንደሚችል አያጠራጥርም። ነገር ግን የሚወሰደው የሥነ-ሥርዓት እርምጃ ሰብአዊ እና የአገሪቷን ሕጎች እና አገሪቷ የተቀበለቻውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሥምምነቶች የተከተለ መሆን ይጠበቅበታል። ከዚህ አንጻር በተለይ ከአዋጁ አፈፃፀም ጋር ተያይዞ በሽብር ወንጀል ተከሰው የሚታሰሩ ሰዎች የመብት ጥያቄ ባነሱ ጊዜ ጥያቂያቸውን በወቅቱ እና በተገቢው መንገድ ለመመለስ ከመሞከሩ ይልቅ ጥያቄውን እንደ የሥነ-ሥርዓት ጥፋት የመቁጠር ሁኔታ በስፋት ታይቷል። ታሣሪው ያነሣው ጥያቄ ወይም ጥያቄውን ያቀረበበት መንገድ በርግጥም የሥነ-ሥርዓት ጥፋት ነው ቢባል እንኳን የታሣሪውን የመሰማት መብት ባከበረ ሁኔታ ሥርዓቱን ጠብቆ ጉዳዩን ማየት ሲገባ በበርካታ ጉዳዮች የእሥር ቤቶቹ አስተዳዳሪዎች ግብታዊ ውሣኔ ስለመሰጠታቸው እሥረኞች ሲገልጹ ተደምጠዋል።ሌላው እጅግ አሣሣቢ የነበረው በእሥረኞቹ ላይ ተግባራዊ ይደረጉ የነበሩት የሥነ-ሥርዓት እርምጃ ዓይነቶች ናቸው። በቂሊንጦው የቀጠሮ እሥረኞች ማቆያ የሥነ-ሥርዓት ጥፋት ፈጽመዋል የተባሉ እስረኞች ለሳምንታት ወይም ለወራት ከሌሎች እስረኞች እንዳይገናኙ ለብቻቸው በጨለማ ቤት እንደሚታሰሩ፤ከቤተሰብ ጋር እንዳይገናኙ እንደሚደረጉ እና የኃይል ቅጣትም እንደሚፈፀምባቸው ለፍ/ቤት ሲያመለክቱ ተደምጠዋል። (ከቂሊንጦ የቀጠሮ እሥረኞች ቃጠሎ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ታሣሪዎች ዝዋይ ማረሚያ ቤት ድረስ ተወስደው እንደተደበደቡ ለፍ/ቤት ያመለከቱ ሲሆን ፍ/ቤቱም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጉዳዩን መርምሮ እንዲያቀርብ ባዘዘው መሠረት ኮሚሽኑ በእስረኞቹ ላይ ስለደረሰው ጉዳት ለፍ/ቤቱ አሣውቋል።) እሥረኞች ተለይተው ባልታሰሩበት ሁኔታም ከሌሎች እሥረኞች ጋር እንዳይነጋገሩ፣ በእሥር ቤቱ ውስጥ ባሉ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንዳይሣተፉ ክልከላ ማድረግና በእስር ቤቱ ውስጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴዎች ሁሉ አሣማኝ ባልሆነ ምክኒያት ጭምር በከፍተኛ ጥበቃ ሥር እንዲሆኑ ማድረግ እና በሌሎች እስረኞች ላይ ያልተደረጉ ገደቦችን ማድረግ የተስተዋለ ነበር። (በሽብር የተከሰሱ ሰዎች በቤተሰቦቻቸውና ጓደኞቻቸው የሚጎበኙበት ሁኔታ በተወሰኑ ሰዓታት ብቻ መወሰኑ እና እንዲጎበኟቸው የሚፈቀድላቸው ሰዎች ማንነት እና ቁጥር የተወሰነ የነበረ መሆኑን ይመለከታል።)በአጠቃላይ የጸረ-ሽብር አዋጁን አፈፃፀም ተከትሎ በእስር ቤቶች የነበረው የእስረኞች አያያዝ ሁኔታ ከምን ጊዜውም በበለጠ የከፋና የሰብአዊ መብት ጥሰቱም ሕይወትን እስከመቅጠፍ የደረሰበት ነበር ማለት ይቻላል።ጠበቆች(የግል ጠበቆች እና የተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት)የተከሰሱ ሰዎች በመረጡት ጠበቃ የመወከል እና በግል ጠበቃ ማቆም ያልቻሉ ደግሞ በመንግስት ነፃ የጥብቅና አገልግሎት ማግኘት በሕገ-መንግስት ደረጃ የተረጋገጠ መብት ነው።ይህ መብት ደግሞ በተለይ የሽብር ክስን ጨምሮ ከፍተኛ ቅጣትን ሊያስከትሉ በሚችሉ የወንጀል ክስ ጉዳዮች ፋይዳው ከፍተኛ ነው።ይሁን እንጂ በፌደራል ፍ/ቤቶች ደረጃ በርካታ ጠበቆች በወንጀል ጉዳይ ለከሣሾች የሕግ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንደሌላቸው ይናገራሉ።ብዙዎቹ ጠበቆች ለዚህ የሚሰጡት ምክኒያት ፍ/ቤቶች የዐቃቤ ሕግን ክስ ደግፈው ክርክሩን ስለሚመሩ የእኛ ሚና ውሱን ነው ወይም ዋጋ የለውም የሚል ነው። በሽብር ክስ ጉዳዮች ደግሞ ከመንግስት ይደርሣል ተብሎ የሚገመተውን ተፅእኖ መፍራት ተጨማሪ ምክኒያት ሆኖ በጣት ከሚቆጠሩ ጠበቆች ውጪ ሌሎች ጠበቆች በሽብር ለተከሰሱ ሰዎች አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።ፈቃደኛ የሆኑትም ቢሆኑ ለበርካታ ተከሣሾች አገልግሎት ለመስጠት ከነበራቸው ፍላጎት የተነሣ አንዳንዶቹ የደንበኞቻቸውን ስም እንኳን በቅጡ ለመያዝና በየቀጠሮው ሣያስተጓጉሉ ለመገኘት ሲቸገሩ ታይቷል።ሌላው በሽብር ወንጀል ለተከሰሱ ሰዎች ከመንግስት በኩል ነፃ የጥብቅና አገልግሎች ለመስጠት ሲሞክር የነበረው በፌደራል ጠ/ፍ/ቤት ሥር በተቋቋመው የተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት ነው።ጽ/ቤቱ ቀደም ሲልም ቢሆን በብዙ መልኩ ከፍተኛ የአቅም ውሱንነት የነበረበት ሲሆን የጸረ-ሽብር አዋጁ ተግባራዊ ሲሆን ደግሞ የጽ/ቤቱ አቅምና ለጽ/ቤቱ የሚላክለት ጉዳይ ብዛት ፈጽሞ የሚመጣጠን አልሆነም። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አብዛኞቹ በሽብር የተከሰሱ ሰዎች በየትኛውም የመንግስት ተቋም ላይ ያላቸው እምነት በጣም አነስተኛ በመሆኑ ጽ/ቤቱ በሚሰጠው አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ፍላጎት አልነበራቸውም።በዚህም ምክኒያት በርካታ በሽብር ወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ምንም ዓይነት የሕግ ሙያ ድጋፍ ሣያገኙ ከሰለጠነ ዐቃቤ ሕግ ጋር እንዲሟገቱ እየተገደዱ ከፍተኛ የቅጣት ውሣኔዎች ሲጣልባቸው እንደነበር ለመታዘብ ተችሏል።(እነ ትንሣኤ በሪሶ፣ የመዝገብ ቁጥር 178587)ምክረ ሐሣብ1. የጸረ-ሽብር አዋጁ አስፈላጊነት ገና ከጅምሩ ከፍተኛ ተቃውሞ የቀረበበት ነው።መተግበር ከጀመረ በኋላም በዋናነት ተፈፃሚ መሆን የጀመረው መንግሥትን በሚተቹት ላይ ሆኖ በመገኘቱ ተቃውሞው በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከአገር ውጪም በርትቶ ቀጥሏል።ከዚህም በኋላ በአዋጁ አፈፃፀም በርካታ ሰዎች ለግብታዊ እሥር ተዳርገዋል፤ በእሥር ቤት ለአሰቃቂ በደሎች ተዳርገዋል፤ አካላዊና መንፈሣዊ ስብራት ደርሶባቸዋል፤ ቤተሰብ ተበትኗል በተጨማሪም ሌሎች ብዙ ጉዳቶች ደርሰዋል። ዛሬ አዋጁ ለብዙዎች የሚያስደነብር (traumatic) ሆኗል። ስለሆነም አዋጁ ለተወሰነ ጊዜ ከኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ውስጥ ጨርሶ ቢወጣ፤ የጸረ-ሽብር ሕግ የግድ ያስፈልጋል የሚባል ከሆነም ለብቻው ተለይቶ ከሚወጣ ይልቅ በአጠቃላይ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች የሕግ ማዕቀፉ አካል ቢሆን፤2. የሽብር ወንጀልን ለመከላከል የደህንነት መ/ቤቱ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ የሚያከራክር አይደለም። የምርመራውንም ሥራ በሕግ አስከባሪው አመራር ሰጪነት ሥር ሆኖ ሊደግፍ ይገባል። ከዚህ አልፎ ግን የደህንነት መ/ቤቱ ሰዎችን እንዲያስር፣ የምርመራ ሥራውን እንዲመራና በክስ ጉዳይም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ እንዲወሰን ሊፈቅድለት አይገባም። የጸረ-ሽብር ሕግ ዞሮ ዞሮ እንደማንኛውም የወንጀል ሕግ ነው። በመሆኑም አፈፃፀሙ መመራት ያለበት በሕግ አስከባሪው ነው። የደህንነት መ/ቤቱም ሆነ ሌላ አካል ሊኖረው የሚችል የደጋፊነት ሚና ብቻ ነው።አዲስ የሚረቀቀው አዋጅ ይህን ያገናዘበ ቢሆን፤3. ትክክለኛው የሽብር ወንጀል በአንድ በኩል በሕዝብ እና በአገር ጥቅም ላይ የሚነጣጠር ከፍተኛ ወንጀል ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ጊዜ ከፍተኛ ቅጣትን የሚያስከትል ነው።በዚህም ምክኒያት የሕግ ማስከበሩ ሥራ የሕዝብን ጥቅም በማስጠበቅ እና የተከሣሹን መብት በማስከበር መሐል ከፍተኛ ውጥረትን የሚያስከትል ነው።በመሆኑም በተለይ የተከሣሾችን መብት መጠበቁን ከማረጋገጥ አንፃር የሕግ ማስከበር ሥራው በጥብቅ ሕግን የተከተለ እንዲሆን እና ሥራውን በማያደናቅፍ ሁኔታ ቢያንስ ለሰብአዊ መብት ተከራካሪ ተቋማት ቅኝት ክፍት እንዲሆን ያስፈልጋል።የሚረቀቀውም ሕግ ይህን ያገናዘበ ቢሆን፤4. በሽብር ወንጀል ክስ ጉዳይ የመንግስት ትኩረት ሁሌም ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።ይህ ወንጀሉን ከመመርመር እና ክሱን ከማቅረብ አንፃር በአዎንታዊነት ሊወሰድ ይችላል።ወደ ዳኝነት አሰጣጥ ሲመጣ ግን ሂደቱ ፍትሐዊ መሆን አለበት፤የዳኝነት ነፃነቱም መጠበቅ አለበት።በመሆኑም የሚረቀቀው ሕግ በዳኝነት አሠጣጡ ላይ ሊኖር የሚችለውን የአስፈፃሚውን ተፅእኖ ለመቀነስ የሚያስችል ድንጋጌ ቢኖረው፤5. ዐቃቤ ሕግ በሽብር ወንጀል ክስ ለመመስረት ሲወሰን ክስ እንዴት መመስረት እንዳለበት፤ በችሎት ሙግት እንዴት ማድረግ እንዳለበት፤ የተከሣሽ መብቶች መከበራቸውን እና በመሣሰሉት ጉዳዮች ሊከተላቸው ስለሚገባው አሠራር የሚያመለክት የአሠራር ማንዋል መዘጋጀት እንዳለበት በሚረቀቀው አዋጅ ቢደነገግ፤6. ጠበቆች በሽብር ወንጀሎች አገልግሎት እንዲሰጡ የሚበረታቱበት መንገድ እንዲፈለግና በተለይ ደግሞ ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ተፅእኖ እንደማይደርስባቸው ዋስትና ሊሰጣቸው እንደሚገባ በአዋጁ ቢካተት።