ኅዳር 5 ፣ 2011

“ማነው ምንትስ”!? 

ኑሮማኪያቶ

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ፣ ጥቅምት 24 ዕለት በወጣው ኢትዮጲስ ጋዜጣ ላይ “የወ/ሮ ሣህለወርቅ ሹመት ትክክል አይደለም” ብለው…

“ማነው ምንትስ”!? 
ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ፣ ጥቅምት 24 ዕለት በወጣው ኢትዮጲስ ጋዜጣ ላይ “የወ/ሮ ሣህለወርቅ ሹመት ትክክል አይደለም” ብለው የፃፉትን በጣም አጭር ፅሁፍ አነበበኩት። ለዚህም የወ/ሮ ሣህለወርቅን ያለፉት አሥርተ ዓመታትን የሥራ ዳራ በምክንያትነት ያነሳሉ። ፕሮፌሰር መስፍን “ወ/ሮ ሣህለወርቅ ለሦሥት የኢትዮጵያ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዞች በታማኝነት ያገለገለች ሴት ነች” ይላሉ። ይሄን ሲሉ ወ/ሮ ሣህለወርቅ ሦሥት አገዛዞችን በታማኝነት በማገልገላቸው ጥብቅነታቸው (integrity) ላይ ጥያቄ እያነሱ እንደሆነ ገልፅ ነው። አክለውም “በውጭ ጉዳይ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ አገልግላለች፤ በውስጥ ጉዳይ አልገባችም” የሚሉ አላዋቂዎች እንደሆኑ ገልፀዋል። አስተያየታቸውን ተከትሎ በተለይ ማሕበራዊ ሚዲያው ላይ በድጋፍና በተቃውሞ መራር ምልልሶች ተደርገዋል። ቢሆንም የፕሮፌሰር ክርክር ትክክል ነው ወይም ስህተት የሚል ሀሳብ ላቀርብ አልፈለግኩም። ከመልስ ይልቅም ብዙ ጥያቄዎችን ለማንሳት መርጫለሁ። መቼም ለውይይት የሚጋብዙ ወሳኝ ሀገራዊ ርዕሰ-ጉዳዮችን በስድድብ የማምከን ልዩ ጥበብ ያለን ሕዝብ ሆነን እንጂ፤ ፕሮፌሰር ያነሱት ጉዳይ ላይ በሰከነ ሁኔታ ብንወያይበት ለአሁንና ለወደፊቱ በሹመት፣ በኃላፊነት፣ በመሪነት ሰለሚመጡ ግለሰቦች የሚኖረን ሚዛን እንዳይዛነፍ የሚረዳ ነው።ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የጣልያን ወረራ አብቅቶ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ የሀገሪቱን መንግስት በአዲስ መልክ ሲያዋቅሩ በሰጧቸው ትልልቅ ሹመቶች በመገለላቸው የተከፉ አርበኞች፡-ኢትዮጵያ ሀገሬ፡ ሞኝ ነሽ ተላላየሞተልሽ ቀርቶ፡ የገደለሽ በላ ብለው እንደተቀኙ ይወሳል። ነገር ግን ግርማዊነታቸው ከእንግሊዝ ቆይታቸው ኢትዮጵያ በብዙ ወደኋላ መቅረቷን ተረድተውና አስቆጭቷቸው በመመለሳቸው በአንድ በኩል ኢትዮጵያን ለማዘመን ትምህርትና ልምድ ያላቸውን ሰዎች መሾም ግድ ሲሆንባቸው፤ በሌላ በኩል በዱር በገደሉ ተዋድቀው ሀገር ያቆዩትን አርበኞች አለመሾማቸው በሚፈጥረው ጉዳት መዋለል (dilemma) ውስጥ ወድቀው ነበር። ዛሬ ያለንበት መዋለል በእርግጥም ከአርበኞችና ከተማሩ ሰዎች መካከል ከመመረጥ የባሰና የተወሳሰበ ነው። ባለፉት 45 ዓመታት በመንግስት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በመሥራት ልምድ ያካበቱ፣ በዕውቀትም የጎለበቱ በርካታ ባለሙያዎች እንዳሉ ሁሉ ከአገዛዞች ጋር ላለመተባበር በሀገር ውስጥ ተደብቀው (low profile)፣ በውጭ ሀገራት ተሰደው የሚኖሩ የትዬሌሌ ታላላቅ ምሁራንና ባለሙያዎች እንዳሉን ይታወቃል። ፕሮፌሰር መስፍንም “ለኢትዮጵያ አገዛዞች ያላገለገለ ሰው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ጠፍቶ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ በቅንነት ያገለገለ ሰው ጠፍቶ” ነው ወይ ለአገዛዞች ያገለገሉ የሚሾሙት? ብለው ይሞግታሉ። አሁንም ወገንተኝነቱን ትተን ከሞራል መመዘኛ አንፃር፣ እንዲሁም እውነታውን ተገንዝቦ የትኛው እንደሚበጅ ለመረዳት በመፈለግ (pragmatism) መነፅር ብናይ ምርጫዎቻችን ምንድናቸው?እውነት ለቀ.ኃ.ሥ፣ ለደርግ ወይም ለኢህአዴግ መንግስት ያገለገለ ሁሉ ሀገሩን አገለገለ ነው የሚባለው? ለህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት በኃላፊነት ያገለገለ ሁሉስ ለጠፉት ጥፋቶች፣ ለወደሙት ውድመቶች ተጠያቂ ነው? የትኛው ቦታ የሠራ ይወቀሳል? የትኛው ቦታስ ያገለገለ ይመሰገናል? አንድ ግለሰብ ለአምባገነን መንግስት ተባብሯል የሚባለው መቼ ነው? ሰብአዊነትን የገፈፉ የደህንነት መኮንኖች፣ እስረኞችን የገረፉ ፖሊሶችና በሀሰት የፈረዱ ዳኞች ብቻ ናቸው ተጠያቂዎቹ? በንግድ ያልተገባ ጠቀሜታን አግኝተው፣ በውድድሩ ተደግፈው ሀብት ያፈሩት፣ ንብረት የያዙትስ? ጥቁር ሱፍ ለብሰው፣ ነጭ ሸሚዝ አድርገው እጆቻቸው ላይ ምንም ደም ሳይታይ፤ ነገር ግን የመንግስትን ግፍ በዝምታ በማለፍ፣ ለመንግስት የዲፕሎማሲ ስራ በመስራት አምባገነኑ መንግስት ቅቡልነት እንዲያገኝ ላይ ታች ያሉት ዲፕሎማቶችስ የሕዝብን ሰቆቃ አላራዘሙም?ተመልሰን ደግሞ ስንጠይቅ፡ ሰው በሙያው፣ በዕውቀቱ፣ በልምዱ የሚቻለውን ችሎ፣ የሚታገሰውን ታግሶ ሀገሩን ለማገልገል መጣጣር አይገባውምን? ሁሉም ሰው አርበኛ፣ ሁሉም ሰው ገለልተኛ፣ ሁሉም ሰው አኩራፊ፣ ሁሉም ሰው ታጋይ ቢሆን ይበጃል? በአምባገነን ሥርዓትም ውስጥ ሆነው በመንግስት የኃላፊነት ቦታ እየሰሩ፣ በሚችሉት መጠን ግፉን ሸሽተው፣ በጎውን ያበረከቱልንስ የሉም? በደምሳሳው ለአገዛዞች አገልገሏል ተብሎ ዳኛውም፣ አቃቤ-ሕጉም፣ ጋዜጠኛውም፣ ኦዲተሩም፣ ኢኮኖሚስቱም፣ ዲፕሎማቱም…ሊወቀስ ይችላል? ሊወቀስ ይገባልስ?አሁንም የዐቢይ መንግስት ባህሪ ገና አልለየም በሚል ፍራቻ፣ በምናልባት ከመጥፎ መንግስት ጋር ላለማበር፣ ታሪካቸውን ላለማበላሸት ሹመት አልቀበልም ያሉ በርካታ ትልልቅ ምሁራንና ባለሙያዎች እንዳሉ አውቃለሁ። የእምቢታቸው ዋነኛ መንስኤ ነገ “ከአገዛዝ ጋር አብረው ነበር” ላለመባልም እንደሆነ ግልፅ ነው። ጥያቄዎቹ ይቀጥላሉ። ኢትዮጵያ በእምቢታቸው አልተጎዳችም? የሚቀርቡላቸውን የሹመት ጥያቄዎችን ተቀብለው ቢሠሩ ሀገር አይታደጉም? ግዙፍ ዕውቀትና ልምድ ኖሯቸው፣ እንደልብ የሚያሠራ ሥርዓትና ልማድ በሌለበት ሀገርና መንግስት ውስጥ የሚችሉትን ከሚያበረክቱልን ይልቅ በገለልተኝነት ንፅሕናቸውን ጠብቀው መቆየት መምረጣቸው የበለጠ ያስመሰግናቸዋል?ፕሮፌሰር መስፍን “ከቀበሯቸው መሀከል እያወጡ ሲጭኑብን እልል ካልን፣ ምን ቢጭኑብን እምቢ ልንል ነው? አምላክ አእመሮአችንን ያብራልን።” ብለው አምርረው ወቅሰውናል። እንደሳቸው ለምድር የከበዱ ታላቅ ምሁርና ሽማግሌን ወቀሳ አጣጥለን ማለፍ አንችልም። ነገር ግን በሰነዘሩት ወቀሳ ዙሪያ የሚነሱት ጥያቄዎች ቀላል መልስ የላቸውም፤ ለፍርጃም አያስደፍሩም።

አስተያየት