ኅዳር 5 ፣ 2011

የወላጅ አበሳ

ወቅታዊ ጉዳዮችፊቸር

ቀለሟ ታደሰ (ለዚህ ጽሁፍ ሲባል ስሟ ተቀይሯል) በተለምዶ ሲኤምሲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የምትኖር የሶስት ልጆች እናት ነች። በአንድ ዓለም ዓቀፍ…

የወላጅ አበሳ
ቀለሟ ታደሰ (ለዚህ ጽሁፍ ሲባል ስሟ ተቀይሯል) በተለምዶ ሲኤምሲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የምትኖር የሶስት ልጆች እናት ነች። በአንድ ዓለም ዓቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት ውስጥ በሂሳብ ባለሙያነት እየሰራች በእሷ ምልከታ “ደህና” ሊባል የሚችል ወርሃዊ ደመወዝ ታገኛለች።ልጆቿ በየሁለት ዓመታት ተራርቀው ሲወለዱ የመጀመሪያዋ 12 ዓመቷ ነው። ይህ እድሜያቸው ለቀለሟ ትርጉሙ ብዙ ነው። ሶስቱም ትምህርት ቤት ውለው ለመግባት የደረሱ ናቸው ማለት ነው።ቀለሟ የልጆቿ ትምህርት ቤት ምን ያህል ህይወቷን እንዳመሳቀለባት ምክንያት ፈልጋ ከመናገር አትቦዝንም። “ ነሃሴ አልቆ መስከረም በመጣ ቁጥር መውለዴን ብቻ ሳይሆን መወለዴን ሁሉ እጠላላሁ ትላለች በምሬት። ብታምነኝም ባታምነኝም፤ በዓመት ከ80 ሺህ ብር በላይ ለሶስቱ ልጆች ፤እዚህ ግባ ለማይባል ትምህርት አወጣለሁ” አለች። ቀጠለች “ ይህን ስልህ ደግሞ የትራንስፖርታቸውን ሳልጨምር ነው። ተመልከት እንደ እኔ ታክሲ ጥበቃ ወረፋ ላይ ተገትሮ ለሚውል ሰው ይህ ምን ያክል ከባድ እንደሆነ “ አለችና የትምህርት ቤት ወጪ ምን ያህል እንዳመረራት ተናገረች።የቀለሟን ችግር በርካታ በአዲስ አበባና በአንዳንድ የክልል ከተሞች የሚኖሩ ወላጆች የሚጋሩት ነው። ዛሬ ዛሬ ልጆችን ማስተማር ለወላጆች ከምንም በላይ ትልቁ ወገብ ሰባሪ ጉዳይ ነው። በየሰፈሩ ያሉ የግል ትምህርት ቤቶች የትምህርት ዓመቱ ገና ሊገባደድ ሁለት ወራት ሲቀረው “ ለሚቀጥለው ዓመት ካላስመዘገባችሁ ቦታ አታገኙም !” የሚል መልዕክት በመምህራንና በተማሪዎቹ በኩል እየሰደዱ ወላጆችን ማሳቀቅ ትንሽም ሳት የማያደርጉት ዓመታዊ ሥራቸው ነው።“ የመጨረሻውን ተርም መጋቢት ወይም ሚያዚያ ላይ እንደከፈልኩ በሳምንቱ የሚቀጥለውን ዓመት ምዝገባ አምጡ እያሉ ልጆችንም ወላጅንም ሲያስጨንቁ ምን እነደሚሰማቸው እንጃ። ምናለበት ለትምህርቱም እንዲህ ትኩረት በሰጡ “ ይላል ሌላው የሁለት ልጆች አባትና ቤተል አካባቢ የሚኖረው አብነት ዘውዱ። “ የሚገርምህ የሚያስተምሩትን መምህራን፤ አንዳንድ ጊዜ ህጻናት ልጆቼ ሁሉ ይሻሉዋቸዋል “ ብሎ አልፎ አልፎ በግል ትምህርት ቤት ያሉ አስተማሪዎችን ህጻናቱ በተለይ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ላይ እርማት ሲሰጡ እንደሚታዘብ እየሳቀ ነገረኝ።ሌላኛው አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቸቻው ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ የሚኖሩትና በሙያቸው የዩኒቨርሲቲ መምህር ሆነው ከከነባለቤታቸው በወር እስከ 20 ሺህ ብር የሚያገኙት አቶ ጌታቸው በለጠ አንዱ ናቸው። አቶ በለጠ ለስድስት ዓመት ሴት ልጃቸው በወር እስከ 1 ሺህ ብር ይከፍላሉ። እንደ አቶ በለጠ ወጪው ቢከብዳቸውም ልጃቸው የምታገኘው ትምህርት ከመንግስት ትምህርት ቤቶች ጋር ሲነፃጸር የተሸለ ጥራት እነዳለው ያምናሉ።አቶ አለበል ይሄነው ደግሞ ባልደራስ በሚባለው ኮንዶሚኒየም አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ ፤ለሁለቱ የአምስተኛና ሶስተኛ ክፍል ልጆቸቸው በድምሩ በዓመት እስከ 40 ሺህ ብር ለትምህርት ወጪ ያደርጋሉ። ወጪው ብዙ አያሳስባቸውም ፤የእሳቸው ጭንቀት ምን ያህል ጥራት ያለው ትምህርት ልጆቻቸው ያገኛሉ የሚለው ነው። እንደ አቶ አለበል ምንም እንኳን የግል ትምህርት ቤቶች ከሂሳብ ይልቅ ለእንግሊዘኛ ቋንቋ ትኩረት ይሰጣሉ ቢባልምና የብዙወቹ ስያሜም ከኢትዮጵያዊነት የራቀ ቢሆንም፤ ገባ ብሎ ለተመለከተው ግን ብዙዎቹ የግል ትምህርት ቤቶች የእንግሊዝኛ ቋንቋ አስተማሪዎቻቸውም ቢሆኑ “ከእጅ አይሻል ዶማዎች” ናቸው። ልጆቻቸውንም የግል ትምህርት ቤቶች የሚወስዱት የመንግስትም ከዚህ በላይ የባሰ ነው ብለው ስለሚሰጉ ነው። “ የመንግስት ትምህርት ቤቶች አንድ አስተማሪ ለስንት ልጅና በአንድ ክፍል ስንት ተማሪ የሚባል ምጣኔ ያላቸው አይመስለኝም” ሲሉ ይጨምራሉ። ከዚህም በላይ ልጆቻቸው ወደመንግስት ትምህርት ቤት ቢሄዱ ስነምግባራቸው የሚበላሽ እንደሚመስላቸው ያስባሉ። “ እንኳን የመንግስትና የግልም ውስጥ የስነምግባሩ ጉዳይ አስጨናቂ ነው ባክህ “ ይላሉ አቶ አለበል።በክፍያ ረገድ ያለውን የወላጆች ራስ ምታት ግን ትምህርት ቤቶቹ የሚረዱት አይመስልም።አቶ ተስፋዬ ተጠምቀ የዳይመንድ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ናችው።”ትምህርት ቤታችን ዝቅተኛ ክፍያ ያስከፍላል ለዚህም ምክንያታችን ከኬጂ እስከ 12 ክፍል ድረስ የተሟላ ስብዕና ለመቅረጽ አስፈላጊ ግብአቶች መሟላት ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር ዋጋው ዝቅተኛ ነው። ትምህርት ቤታችን በአዲስ አበባ ውስጥ ካሉ 2000 የግል ትምህርት ቤቶች አንዱ ሲሆን በትምህርት ሚኒሰቴር ደረጃ አሰጣጥ አራተኛ ደረጃን አግኝቷል። ይህም ማለት ዘጠና ከመቶ የሚሆነውን መስፈርት አሟልቷል ማለት ነው። ስለዚህ ተመጣጣኝ ከማለት ይልቅ ዝቅተኛ ነው ማለት እችላለን” ይላሉ።አቶ ደሳለኝ መኩሪያ የቤተሰብ አካዳሚ ስራ አስኪያጅ ሲሆኑ፤እሳችውም እንደሚሉት ተመጣጣኝ ክፍያ ሲባል የሚሰጠው አገልግሎት ከክፍያው አንጻር እኩል ሲሆን ነው። “ ይህ ብቻም ሳይሆን የወላጆች የመክፈል አቅም ወይም የገቢ ምንጭን መሰረት ያደረገ መሆን አለበት። በአካዳሚያችን የሚደረገው ማንኛውም ጭማሪ ወላጆችን ያሳተፈና እውቅና የሰጠ ነው። ስልዚህም ተመጣጣኝ ነው ማለት እንችላለን” ይላሉ።ጥራትን አስመልክተን የጠየቅናቸው አቶ ተሰፋዬ “ ወደ ስራ ከመግባታቸወው በፊት ስልጠና በመስጠት የምናበቃቸው ሲሆን ይህም የመምህራኑን ብቃት ጠንካራ እንዲሆን ያደርገዋል። ነገር ግን በሌሎ.ች የግል ትምህርት ቤቶች እንዲህ አይነት ችግር እንዳለ ይስተዋላል። የዚህም ምክንያት ደግሞ መምህር የሚሆኑት ግለሰቦች በውጤታቸው ዝቅተኛ የሆኑ መሆናቸው፣ የማስተማር ክህሎት ስልጠናን ያልወሰዱና የቋንቋ ክህሎት ማነስ ናቸው። በተጨማሪም የመምህራን የክፍያ መጠን አነስተኛ መሆን ሙያውን ተፈላጊ እንዳይሆን ያደርገዋል። እነዚህን መቅረፍ ከተቻለ ብቁ መምህራንን መፍጠር ይቻላል። ይህ ደግሞ ለአንድ ሃገር እድገት መሰረት ነው” ሲሉ ያከላሉ።ይህንኑ ሃሳብ አትኦ ደሳለኝም ይጋራሉ። እንደ አቶ ደሳለኝ መምህር የሚሆኑት ሰዎች በምርጫቸው አለመማራቸው ትልቁ የጥራት ችግር መነሻ ነው። “ ከዚህ ጋር ተያይዞ የትምህርት ስርአቱ በራሱ ያለበት ክፍተት ነው። ሌላኛው በተለይም ህጻናት ትምህርት ቤቶች ያሉት መምህራን የቋንቋ እና መሰረታዊ የማስተማር ክህሎት ያለመሟላት ዋነኞቹ ችግሮች ናቸው” በማለት ያከላሉ።መፍትሄውን ሲጠየቁም የትምህርት ስርአቱ መሻሻል አለበት፤ በተለየ መልኩ መምህራንን ለማብቃት በከፍተኛ ትኩረት መሰራት አለበት፤እንዲሁም ለመምህራን ክፍያ መሻሻል አለበት በማለት ይናገራሉ።ለመሆኑ የትምህርት ዋጋ ስንት ነው?ህጻናትን ለማስተማር የሳሳ ህብረተሰብ የሚከፍለው እዳ ከቆጠበው በብዙ እጥፍ ነው ይላሉ የማህበረሰብ ሳይንስ ባለሙያዎች። “ እንደወጉም ከሆነ ህጻናት፤ የቤተሰቦቻቻው አቅም ፈቀደም አልፈቀደ፤ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ከክፍያ ነጻ በሆነ መልኩ ሊያገኙ ግድ ይላቸዋል። በቂና ጥራት ያለው ትምህርት ያላገኙ ህጻናት ዞረው ዞረው የማህበረሰቡ እዳዎች ናቸውና ትምህርት ለህጻናት በማህበረሰቡና መንግስት መቅረብ ያለበት ማህበራዊ አገልግሎት እንጂ፤ እንዲሁ ለነጋዴ ትርፍ መሰብሰቢያ የሚተው ነገር አደለም በማለት የግል ትምህርት ቤት አስፈላጊ አደለም “ ብለው የሚከራከሩ የዘርፉ ምሁራን ጥቂት አደሉም።እነዚህ የግል ትምህርት ቤትን አስፈላጊነት የሚቃወሙ ወገኖች መከራከሪያቸው፤ የግል ትምህርት ቤቶች ድሃን አግላይና ገቢያቸው ከፍ ካለ ቤተሰብ ለሚወለዱ ህጻናት ብቻ ጥራት ያለው ትምህርት የሚያቀርቡ መሆናቸው ነው። በዚህ ጎን እንደቆሙት ተከራካሪዎች ከሆነ ትምህርት በእኩል ጥራት ለድሃም ለባለፀጋም ልጆች ሊቀርብ ይገባል። ይህ ካልሆነ፤ ምንም እንኳን ዛሬ የባለጸጎቹ ልጆች የተሟላ የትምህርት ቁሳቁስና የተሻለ መምህራን በሚገኙበት ትምህርት ቤቶች ጥራት ያለው ትምህርት ቢያገኙም፤በቂ የሆነና ጥራት ያለው ትምህርት ያላገኙ ድሃ-አደግ እኩዮቻቸው የነገ ማህበራዊ ህይወታቸው ላይ የሚደቅኑት አደጋ ቀላል አይሆንም ይላሉ። The cost of educating children is far outweighed by the cost of not educating them.በሌላ በኩል ቆመው የግል ትምህርት ቤቶችን አስፈላጊነት የሚናገሩ ባለሙያዎች ደግሞ የግል ትምህርት ቤቶች መኖራቸው ወላጆች ለልጆቻቸው የተሻለ ትምህርት ለመስጠት በሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት የራሳቸውንም የልጆቻቸውንም ህይወት ይቀይራሉ ባዮች ናቸው። ህጻናት ልጆቻቸውም በማሀበረሰቡ ውስጥ ካሉ በሃብት ደረጃቸው ከፍ ያሉ ሰዎች ልጆች ጋር ተግባቦት በመፍጠር ተምሮ የመለወጥና የማደግ ፍላጎትን ያዳብራሉ ባዮች ናቸው።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ1948 (እ.አ.አ.) ትምህርትን እንደ አንድ የሰብኣዊ መብት መገለጫ አድርጎ ሲያስቀምጠው፤በ1959 የህጻናት መብት ድንጋጌው ደግሞ መንግስታት ለህጻናቶቻቸው ቢያንስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን በአግባቡ የማድረስ ግዴታ አለባቸው ሲል ይገልጻል። አዲስ ዘይቤ ለዚህ ጽሁፍ እንደግብዓት የተጠቀመችባቸው በአዲስ አባባ ዩንቨረሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር ይህንን የሚያጠናክር ሃሳብ አላቸው።“ከ1948 የሰብኣዊ መብትና የ1959 የህጻናት መብቶች በተጫማሪ በ1966 የተ.መ.ድ ሌላ የማህበራዊ ፖለቲካዊና ምጣኔሃብታዊ መብቶችን ለዜጎቻቸው እንዲያጎናጽፉ ያስገድዳቸዋል። ትምህርት ማህበራዊ አገልግሎትና መንግስት ለዜጎቹ ማቅረብ ያለበት (Public Goods) ነው። መንግስት ይሁነኝ ብሎ እንደፈረመው ድንጋጌ ከሆነ ትምህርትን ለገበያ ብያኔ እንዲሁ የሚተወው ሳይሆን፤ ራስ በጥራትና በበቂ መልኩ ሊያቀርብ ይገባ ነበር” ሲሉ ይገልጻሉ።ምሁሩ የግል ትምህርት ቤቶች መኖራቸው ለመንግስትም ይሁን ለሀብረተሰቡ የሚጠቅሙት ጥቅም በርካታ ነው ሲሉ ያብራራሉ። ይሁንና መንግስት ለግሉ ዘርፍ ይህ ነው የሚባል ድጋፍ እያደረገ እንዳልሆነም ይናገራሉ።“ መንግስት የገባበትን ጥራት ያለው ትምህርት የማቅረብን ግዴታ እንዲወጣ የሚደግፉትን አካላት የግል ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ሊያበረታታ ይገባ ነበር፡፤ ይህ ግን እየሆነ አይደለም። የግል ትምህርት ቤትን የሚመሩ ግለሰቦች በቀላሉ መሬት የሚያጋኙበትን፤ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነጻ ሊያደርጋቸው ይገባ ነበር “ ይላሉ። መንግስት የትምህርት አገልግሎትን የሚያቀርቡ በላሃብቶችንና በሉሎች ንግዶች የሚሳተፉትን የሚያይበት ዓይን አንድ አይነት መሆኑ አግባብ አደለም ባይ ናቸው። ይህ አግባብ አደለም፤ምክንያቱም የግል ትምህርት ቤቶች መንግስት ራሱ ሊያሟላ ቃል የገባውን ግዴታውን የሚያግዙ በመሆናቸው ነው። መንግስት ድጋፍ ካላደረገለት ደግሞ የግሎችም ቢሆኑ በጊዜ ሂደት ጥራታቸውና ተቀባይነታቸው እየቀነሰ መሄዱና ከመንግስት ትምህርት ቤቶች ጋር አንድ ሆነው መታየታቸው አይቀርም ባይ ነቸው።ከአራት ዓመታት በፊት በአዲስ አባባ ከተማ ትምህርት ቢሮ የገንዘብ ድጋፍ የተጠና ጥናት እንደሚያመለክተው ሰባ ፐርሰንት የሚሆኑት ልጆቻቸውን ወደግል ትምህርት ቤት የሚሰዱ ወላጆች በቀደመው ዓመት ላይ የትምህርት ክፍያ ዋጋ ጭማሪ እንደተደረገባቸው ገልጸዋል። በዚያው ጥናት ላይ በቀደመው ዓመት ላይ ጭማሪ አድርገው እንደነበር ከተጠየቁት የግል ትምህርት ቤቶች መካከል ጭማሪውን ያመኑት 44 ፐርሰንቱ ብቻ ነበሩ። ይህም በወላጆችና በትምህርት ቤቶቹ መካከል የክፍያ ጭማሪ ላይ ያለውን አለመተማመንና ድብብቆሽ የሚያሳይ ነው።ክብር ለወላጆችቀለሟ ልጆቿን ከምታስተምርበት ትምህርት ቤት ጋር ያላትን ግንኙነት “ምንም አይልም” ስትል ትገልጸዋልች። “ የጠየቁት ከተከፈላቸው ምንም አይፈልጉም በገንዘብ ከመጣህባቸው ነው ነብር የሚሆኑት “ በማለት ፈገግ አለች ። አምና የትምህርት መገባደጃው ወቅት ላይ የፋና ቴሌቪዥን አንድ ዘገባ አቅርቦ ነበር። ይህ ዘገባ ላይ እንደሚታየው ከሆነ “ ስኩል ኦፍ ቱሞሮው ” በተባለ የግል ትምህርት ቤት ላይ ወላጆች ተገቢ አደለም ያሉትን የዋጋ ጭማሪ ሲቃወሙና ይህን ተከትሎም የተነሳውን ግብግብ ያሳያል። የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ሃላፊ ትእግሰቱ አልቆ የቴሌቪዥን ዘጋቢውንና የተወሰኑ ወላጆችንም ወደትምህርት ቤቱ ቅጽር ጊቢ ‘አትገቡም’ በማለት ሲገፈታትር ይታያል። ከላይ ያናገርናቸው ምሁር ይህ አይንቱ ወላጆችን ህዝብና ህጻናቱ በሚመለከተው የቴሌቪዥን ጣቢያ ካሜራ ፊት ማዋርድና መገፈታተር በተማሪ ሀጻናቱ ላይ የመጠቃት ስሜትን ሊያሳድርባቸው ይችላል ሲሉ ይህ ዓይነቱ አላስፈላጊ የትምህርት ቤቶች ባህሪ የነገ ታዳጊዎች ላይ ሊኖረው የሚችለውን ስነልቦናዊ ጉዳትም ያሳያሉ።አሁንስ የወላጆችና የተማሪዎች ተሰፋ ምንድነው?ቀለሟም ትሁን አብነት የሚከፍሉት ክፍያ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ወደ መንግስት ትምህርት ቤት ደግሞ ልጆቻቸውን መመለስ ደግሞ የማይታሰብ ነገር ነው። “ ክንዴን ካልተራስኩ በቀር ወደ መንግስት ትምህርት ቤቶች ልጆቼን አልወስድም “ ትላለች ቀለሟ ። “ የመምህራኖቹን ነገር የምታውቀው ነው። እንኳን በመንግስት ደህና ደመወዝ በሚያገኙበት የግል ትምህርት ቤት ውስጥ ያሉትም አልረቡም። አስበው መንግስት ቤት ያሉት ምን እንደሚሆኑ “ አለችና ትንሽ እንደመዘግነን አላት። አብነትም የመንግስት ትምህርት ቤት ውስጥ ከልክ ያለፈ የስርኣት እጦት እንዳለ ይሰማዋል። “ የልጆቹ መጣበብ በዚህ ላይ አሁን ያለው ጋጠወጥነትና ሃላፊነት ተሰምቶት ልጆችህን የማያርቅ መምህር ባለበት ሁኔታ እንዴት ብዬ ብዙ ሺህ ህጻናት ወዳሉበት ቦታ ልጆቼን እልካለሁ? ሲል ይጠይቃል።ይሁን እንጂ ሁለቱም በልጆቻቸው ትምህርት ተስፋ አይቆርጡም። ቀኑይለወጥ ይሆናል፡፤ ልጆቼ ሲያድጉ ልክ እንደድሮው የተማረ የሚከበርበት ጊዜ ይመጣ ይሆናል። ተስፋ አደርጋለሁ። እስከዚያው ከኔ የሚጠበቀው የምችለውን ማድረግ ብቻ ነው፡፤ ለኔስ ከልጆቼ ትምህርት ውጪ ሌላ ምን ተስፋ አለኝ ? ስትል ትጠይቃለች ቀለሟ።አቶ ጌታቸው ደግሞ “ የኔ ጥረትና ከትትል ካልታክለበት የልጆቼን ተስፋ በማስተምርበት የግል ትምህርት ቤት ብቻ መጣል ይከብደኛል “ ይላሉ። ትልቁ ችግር ለትምህርት ህብረተሰቡ የሚስጠው ክብር እጅግ ቀንሷል፤እንዲህም ተለፍቶና ተደክሞ ልጆቼ ተምረው ሰው ይሆኑልኝ ይሆን የሚለው ያሳስበኛል” ሲሉ የሚጨምሩት ደግሞ አቶ አለበል ናችው።መንግስትስ የወላጆቸን ተስፋና ስጋት ይጋራቸው ይሆን?

አስተያየት