ኅዳር 5 ፣ 2011

የዴሞክራሲያዊ ሽግግሩ ዕቅድ በቂ ትኩረት ተሰጥቶት ለህዝብ ይፋ ይደረግ!

ርዕሰ ዕንቀጽ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔያቸውን እንደገና ሲያዋቅሩ በርካታ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን አጥፈዋል። በዚህ ሂደት ከታጠፉት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ አንዱ…

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔያቸውን እንደገና ሲያዋቅሩ በርካታ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን አጥፈዋል። በዚህ ሂደት ከታጠፉት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ አንዱ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው። አቶ ፍጹም አረጋ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነው ከተሾሙ በኋላ ሚኒስቴር የሚመደብለትን ጽ/ቤት አላስፈላጊ እና በጣም ጥቂት ሥራዎችን የሚከውን አድረገውት ነበር። ምንም እንኳን ተግባቦት(communication) በሁለት ወገን ያለ ምልልስ ቢሆንም ፍጹም አረጋ በፌስቡክ እና ትዊተር ገጻቸው ተጠቅመው የመንግስትን እንቅስቃሴዎች እና አቋሞች በመዘገብ አብዮታዊ ሊባል የሚችል የመረጃ ተደራሽነት ፈጥረው ነበር። ብዙ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መንግሥትን መጠየቅ ፈልገው የጽሕፈት ቤት ኃላፊውን በር ቢያንኳኩም የሚናግሩ እንጂ የሚጠየቁ አልነበሩም።የመንግሥትን ወሬዎች ብቻ ሳይሆን ሚዲያው ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች የመመለስ ኃላፊነት ያለበት በቢልለኔ ስዩም የሚመራ ቃል አቀባይ ቢሮ(ፕሬስ ሴክሪታሪያት) ተቋቁሟል። ዘግይቶም ቢሆን መንግሥት የሚናገር ብቻ ሳይሆን የሚሰማ እና ጥያቄዎችን የሚመልስ ለመሆን ዝግጅት እያደረገ ነው።ይህ የመንግሥት አካል ከየትኛውም ዘገባዎች በላይ የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር ሀገሪቱን እንዴት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሻገር እንዳቀደ መግለጽ እንደሚገባው አዲስ ዘይቤ ታምናለች። ይህንን ማድረጉ ሁለት መሠረታዊ ጥቅሞች ይኖሩታል።የመጀመሪያው ከሀገረ መንግሥት አፈጣጠር ጋር ይሄዳል። የሰው ልጅ በዘፈቀደ በህግ አልባነት ከመኖር ይልቅ በስርዓት ለመመራት በመፍቀድ ሉዓላዊ መብቱን ቆርሶ በመስጠት ጥበቃ ያደርግለት ዘንድ መንግሥትን አቁሟል። ሀገር የሚገነባው ይህ ዜጋ ራሱ ነው። ሀገርን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማሸጋገርም የዚሁ የሀገር ግንባታ ሂደት ወሳኝ ምዕራፍ ነው። አንድ ሀገርን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርኣት ለማሻገር ቃል የገባ መንግሥት የዕቅዱን ፍኖተ ካርታ  ይፋ ማድረግ የሚገባው በመጀመሪያ ለዜጎች ነው። ዜጎች ያልተሳተፉበት ሀገርም አልተገነባ። መንገዱም በታሪክ እንዳየነው ከአንድ አምባገነን ወደሌላ አዲስ አምባገነን መንከባለል እንጂ  ወደ ዴሞክራሲ አያሻግርም።ሁለተኛው ዜጎች የመንግሥት ዕቅድ ግልጽ ሲሆንላቸው ሰላም እና መረጋጋት ይፈጠራል። በመንግስት ተሿሚዎች እና በማኀበረሰቡ መካከል መተማመን ይኖራል። ይህ እቅድ የግል ጥቅማቸውን የሚነካባቸውን እና ዕኩይ ዓላማ ያላቸው እንዳይሳካ ጥረት እንደሚያደርጉ ሳይታልም የሚፈታ ነው። ነገር ግን ማኀበረሰቡ በመረጃ እጥረት በፕሮፖጋንዳቸው በመጠለፍ ካላገዛቸው ተጽዕኗቸው የተራ ወንጀለኛ ነው። ይህ ደግሞ መንግሥት ባላው ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም መብት በቀላሉ መፍትሔ የሚሰጠው ነው።ይህንን መሰረት በማድረግ አስተዳደሩ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ሳያስፈልግ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲ እንደሚያሸጋግር ቃል ገብቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም መንገዳቸው ወደ ዴሞክራሲ መሆኑን ለማስረገጥ ብዙ ዲሰኩር ሲያሰሙ ቆይተዋል። ይህንን የገቡትን ቃል ለመፈጸም ያላቸውን ቁርጠኝነት በመጠኑ የሚያጠናክሩ በርካታ ሥራዎች አከናውነዋል። ይሁንና እነዚህ ብዙዎቹ መልካም ሥራዎች ተግባር ላይ የዋሉት በድንገቴ(surprise)ነው። እነዚህ በችሮታ መልክ ከስራ አስፈጻሚው የሚደረጉ ነገሮች ለጊዜው የብዙኀኑን ስሜት ቢጨመድዱም ከአፍታ በኋላ እንደጉም ተነው የሚጠፉ ነው። ይህም ዜጎች ለመንግሥት ምክንያታዊ በሆነ መረዳት እና ተጨባጭ ድጋፍ እንዳያደርጉ አግዷቸዋል። ሰላም እና መረጋጋቱም በቀላሉ የሚደፈርስ ማኀበረሰቡ በመንግሥት ያለው እምነት ሁልጊዜ በቋፍ ላይ ያለ እንዲሆን አድርጎታል። ይህ የአመኔታ መዋዠቅ የተፈጠረው የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት የሀገሪቱን እንዴት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማሸጋገር እንዳላበት እቅድ እንዳላዘጋጀ ወይም እቅዱ ቢዘጋጅም ለማኀበረሰቡ በግልጽ እና በዝርዝር ይፋ ባለመደረጉ ነው።የቃል አቀባይ ቢሮ(ፕሬስ ሴክሪተሪያት) ራሱን ችሎ መቋቋሙ በተወሰነ መልኩ ይህንን የመረጃ ክፍተት እንደሚሞላ ብዙዎች ተስፋ አድርገዋል። አዲሷ ቃል አቀባይ፣ ቢልለኔ ስዩምም  ጥቅምት 26 ቀን 2011 ዓ.ም. የመጀመሪያውን የፕሬስ መግለጫ አቅርበዋል፤ ከጋዜጠኞችም ጥያቄዎችን ተቀብለዋል። ጽሕፈት ቤታቸው ምን አይነት ቅርጽ እንደሚኖረው፣ ምን አይነት መጠን እና በምን ያህል የጊዜ ገደብ ውስጥ የመንግሥት መረጃዎች እንደሚያደርስ እና በሚዲያ አማካኝነት የሚቀርብለትን የዜጎችን ጥያቄ እንደሚመለስ ባይታወቅ ጅምሩ የሚደነቅ ነው።በዚህ የመጀመሪያ የሆነው የፕሬስ መግለጫ ላይ ይፋ የሆነዉ ባለ አንድ ገጽ የመንግስት እቅድ ሰሌዳ መንግሥት ፍኖተካርታውን እቅዱን ይገረን ሲሉ ለነበሩ ሰዎች በተወሰነ መልኩ ምላሽ የሚሰጥ ነው። አዲሱ ባለአንድ ገጽ የመንግሥት ዕቅድ “ኢትዮጵያ፡- አዲሲቷ የተስፋ አድማስ” የሚል መጠሪያ ሲኖረው ዴሞክራሲ እና የሕግ የበላይነት፣ የሥራ ፈጠራ እና ተወዳዳሪነት እና አስቸኳይ በሚሉ ዘርፎች የተከፈለ ሲሆን በወስጡ ዘጠኝ ቁልፍ ጉዳዮችን ይዟል። ከላይ በዋና ርዕሰ ጉዳይነት ያነሳነው ዴሞክራሲያዊ ሽግግር የሚወድቀው ከዘጠኙ ጉዳዮች በመጀመሪያ ቁልፍ ጉዳይ ላይ ነው።በመጀመሪያ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ከዘጠኙ ጉዳዮች አንዱ መታየቱ መንግሥት ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት አናሳ ነው ወደሚል ድምዳሜ ይደርሳል። በተጨማሪም በሁለተኛነት ከሰፈረው የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ በቀር ሌሎቹ ቁልፍ ጉዳዮች ከሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ ተያያዥነት ያላቸው ናቸው።በሁለተኛ ደረጃ አነጋጋሪ የሚሆነው በአንድ ቁልፍ ጉዳይነት የተያዘው የዴሞክራሲ እና የሕግ የበላይነት የሀገሪቱን ተጨባጭ ኹኔታ ሲገልጽ መንግሥት አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ከዚህ በፊት የነበረው የግንባሩ አስተዳደር ይል ከነበረው ችግሮችን የወለደው የአፈጻጸም ጉድለት ነው ከሚል ብዙ ያልራቀ እንደሆነ የሚያሳብቅ ነው። በዚህ ዕቅድ መሠረት መንግሥት ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የሚያከናውናቸው በቁልፍ ጉዳይ አንድ ላይ የሰፈሩት ተግባራት እና የሚያስገኙት ውጤቶች ዴሞክራሲን ነጻ የማድረግ እንጂ ወደ ዴሞክራሲ የሚያሻገር ይዘት የላቸውም ብሎ ለመናገር ያስደፍራል። ይህ ደግሞ ማኀበረሰቡን ለተጨማሪ ብዥታ የሚዳርግ መንግሥትን ደግሞ የሌለን ነገር ለማስተካከል የሚደረግ ጥረት ውስጥ የሚከት ነው። አንድ ነገር ለመኖሩ መግባባት ላይ ሳይደረስ እንዴት ጥሩ ለማድረግ እቅድ ይነደፋል?ይህንን ችግር ለማስወገድ መንግሥት ሁለት አማራጮች ይኖሩታል ብላ አዲስ ዘይቤ ታምናለች። የመጀመሪያው ዲሞክራሲያዊ ሽግግር በዚህ ባለአንድ ገጽ የመንግሥት ዕቅድ ውስጥ የተሰጠው ስፍራ አነስተኛ በመሆኑ እና ዴሞክራሲያዊ ሽግግርን በአግባቡ እና በበቂ ኹኔታ ያላካተተ በመሆኑ ተጨማሪ ቁልፍ ጉዳዮች በመጨመር ማስተካከል ይቻላል። ይህ ካልሆነ ደግሞ ሀገሪቱን ወደ ዴሞክራሲ ስርዓት ለማሻገር የሚያስችል ሌላ ዕቅድ ማዘጋጀት እና ለህዝብ ይፋ አድርጎ ከዚህኛው ባለአንድ ገጽ የመንግሥት ዕቅድ ጋር በመናነበብ የሚፈጸምበትን ስልት መንደፍ ነው።

አስተያየት