ጥቅምት 20 ፣ 2011

ከተማና ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት አይነጣጠሉም!

ርዕሰ ዕንቀጽሃሳብን-የመግለጽ-ነጻነትርዕሰ-አንቀጽከተማ

ከተሞች በተፈጥሯቸው ማግኔታዊ የሆነ የስበት ኃይል አላቸዉ፡፡ ይህ የስበት ኃይላቸው በዙሪያቸው ያሉ ሰዎቸን ከሁሉም አቅጣጫ ወደ ከተሞች እንዲሳቡና…

ከተሞች በተፈጥሯቸው ማግኔታዊ የሆነ የስበት ኃይል አላቸዉ፡፡ ይህ የስበት ኃይላቸው በዙሪያቸው ያሉ ሰዎቸን ከሁሉም አቅጣጫ  ወደ ከተሞች እንዲሳቡና እንዲፈልሱ ያደርጋል። የከተማ ሕይወት የስበት አስኳሉ በብዙ እድሎች  የተሞላ ቦታ መሆኑ ነው፡፡ ከተሞች ሰዎች ጉልበታቸዉን ችሎታና እዉቀታቸዉን በአንጻራዊ ውድድር ለመሸጥና የሚፈልጉትን ደግሞ ከሌሎች ለመግዛት እድል የሚያገኙባቸዉ ሥፍራዎች ናቸዉ፡፡እያንዳንዱ ከተማን የሚረግጥ ግለሰብ ወደ ከተማ የጎተተው የራሱ የሆኑ ምከንያቶች ይኖሩታል፡፡ በጥቅሉ ሲታይ ግን ከላይ እንደተባለው የተሻለ እድል የማግኘት ፍላጎት ነው፡፡ ሁሉም የሚፈልገውን ነገር ለማግኘት ሃሳቡና ምኞቱን ለማሳካት በሚፈጥረው የመስተጋብር  ሒደት እርስ በእርሱ  በሚያደርገው ግንኙነት፤ ከተማና የከተማ ነዋሪዎቸ ህይወት የፈጠነ የሐሳብ  መለዋወጫ ይሆናሉ፡፡ በዚህ የግንኙነት ሒደት ውስጥ የሚፈልጉትን ለማግኘትና ለማሳካት ሐሳብን መግለጽ የግድ ነው፡፡ስለዚህ ሐሳብን ከመግለጽ አንጻር ከተሞች ከዳር አገሩ  በተለየ መልኩ በውስጣቸው ለሚኖሩ ሰዎች ለዜጎች የሚያጎናጽፏቸው በረከቶች አሏቸው፡፡ ስለዚህም ሰዎች በአንጻራዊነት  ሐሳባቸውን የሚያንሸራሸሩበት ሻል ያለ ምህዳር እንዲኖር የሚጠበቀው በከተሞች መሆኑ ነው፡፡በአንጻሩ በዳር አገሩ ያሉ ሰዎች እንደ አንድ ግለሰብ ሳይሆን አኗኗራቸው በቡድን አመለካከቶች ተጽዕኖ ሥር ያረፈ ነው፡፡ ጫናው የሚመነጨውም የሚኖሩበት ሥፍራ በዘውግ ልማድ ወይም በሐይማኖት፤ በአመለካከት ተመሳሳይነት ያለው ስለሆነ ሊሆንም ይችላል፡፡ ይህ ተመሳሳይነት ያለው የቡድን ልማድ አንድ ሰው በራሱ የተሰማውን በሙሉ ልብ እንዳይገልጽ ተግዳሮት ሆኖ ሊታይ ይችላል፡፡ ከተሞች በአፈጣጠራቸው የተሻለ ሃሳብን የመግለጫ ቦታዎች ናቸው እንበል እንጂ፤ በሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን ሊደግፉ የሚችሉ ተቋማት በከተሞችም ቢሆን ውስንነት አለባቸው፡፡ ነጻ ሐሳብ የሚንሸራሸርባቸው ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ ራዲዮ ጣቢያዎች ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ በመዲናዋ አዲስ አበባ የከተሙ ቢሆንም ከተማን የሚመጥን የሐሳብ መንሸራሸሪያ ቦታዎች ሲሆኑ አይታይም፡፡ እንዲያውም ያሳለፍነው ታሪክ እንደሚያሳየው ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የተሻለ ይከበራል ተብሎ በሚጠበቅበት የከተማ አካባቢዎች መንግሥት መዋቅራዊ የሆነ ጫና በነዚህ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ሲያሳርፍ ነው፡፡ የኅትመት ውጤቶችን ብንመለከት እንኳን ለዓመታት በዚህ የሚዲያ ዘርፍ  ላይ በተደረገው ጫና ዛሬ ላይ የጋዜጦቻችን ቁጥር በአፍሪካ ደረጃ እንኳን ሲታይ እዚህ ግባ የማይባል ነው፡፡ ይህ ሳያንስ ዛሬ ላይ ሰዎች ስለሃገራቸዉ እጣ ፈንታ ስለ ፖለቲካ አመለካከታቸው የሚወያዩበት የሚከራከሩበት በቂ የሆኑ ቦታዎችም (ፎረሞች) የሉንም፡፡ አሁን አሁን ጥቂት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፈራ ተባ እያሉ የፖለቲካ ክርክሮችን ለማቅረብ መሞከራቸው የሚበረታታ ቢሆንም  ዛሬም ሰፊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ ጡንቻ ካለው የቡድን መብት ከሚያቀነቅን ሥርዓት ጋር የሚገዳደር የፖለቲካ መድረክን የፈጠረ ጠንካራ ሚዲያ የለንም፡፡ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፖለቲካ ምህዳሩ ላይ የታየው መነቃቃትና ተስፋ በፕሬስ ላይም የራሱ አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችል ተስፋ ማድረግ ይቻላል፡፡ ሰዎች ሃሳባቸውን በነጻነት ይግለጹ ሲባል ተፈጥሮአዊና  ሰው በመሆን ብቻ የሚገኝ መብት ስለሆነ ብቻ አይደለም፡፡ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት በመንግሥትም ሆነ አጠቃላይ በማኅረሰቡ ውስጥ የሚታዩ ደካማ አሠራሮችን አመለካከቶችን ለማረቅ ቁልፉ መሳሪያም ስለሆነ ነው፡፡ ሰዎች ሃሳባቸውን የመግለጽ መብታቸው ሲከበር የሚያሰተዳድራቸው አካል ያሉትን ችግሮች መረዳት ባለበት ጊዜ እንዲረዳና  የማስተካከያ  እርምጃ እንዲወስድ ያደርገዋል፡፡ ግለሰቦች ያለስጋት ሲናገሩ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ያጋልጣሉ፤ ለደካማ አሠራር መፍትሔ ይጠቁማሉ፤ ቢስተካከል ቢታረም የሚሉትን የማስፈጸም ኃላፊነት ላለበት አካል ያሳውቃሉ፤ ችግሮች ተባብሰው ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ አስቀድመው የማንቂያ ደወል ይደውላሉ፡፡መንግስት በከተሞች በግልጽ መሬት ላይ የሚታዩትንና ግብር ከፍለው የሚያድሩትን እንደ ግለሰብ የሚኖሩ ሚሊዮኖችን ግን ችላ ብሎ በከተሞች የሌለውን ቡድን ከመፈለግ ይልቅ የከተሞች ተፈጥሮ እንደሚፈቅደው የግለሰብ መብቶችን እውቅና በመስጠት  የሕግ ማዕቀፍና ከለላ  እንዲኖረው ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ይሄ ሲደረግ ተፈጥሮአዊ የሆነው የከተሞች መበልጸግ እነዚህን በከተማ የሚገኙ ዕሴቶች ቀስ በቀስ ወደ ዳር እንዲስፋፋ ያደርጋል፡፡ ወዲያውም ከላይ ያነሳናቸው የከተሜነት በረከቶች ለሁሉም ዜጋ ይደርሳል፡፡ ስለሆነም ጋዜጦች በማንኛውም ለሕብረተሰቡ ይጠቅማሉ ያሏቸዉ ጉዳዮችን በማንሳት በብዛት ወደ ሃሳብ ገበያው ሊወጡ ይገባል፡፡ በአደባባይ ሰዎች በነጻነት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማኅበራዊ ጉዳዮችን በማንሳት የሚወያዩባቸው መድረኮች ሊመቻቹ ይገባል፡፡ ጋዜጠኞች ይህን ጉዳይ ባነሳ ችግር ይገጥመኛል ብለዉ ሳይሰጉ በሙያቸዉ ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ  የህብረተሰቡን የተለያዩ ድምፆች ሊያሰሙ ይገባል ፡፡ሚዲያዎች ነጻ እና ገለልተኛ ሆነው እንዲቆዩ የማኀበረሰቡን ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የተለያየ ቅርጽ ያለው የፋይናንስ ድጋፍ በመስጠት፣ ተቋማዊ ቅርጻቸውን ይዘው እንዲቆዩ ሕጋዊ የንግድ ግንኙነት መፍጠር ይገባቸዋል፡፡ ማኀበረሰቡን በቁርጠኝነት እና በባለሙያነት የሚያገለግሉ ሚዲያዎችን የሚሸልም መሆን ይገባዋል፡፡ የኢትዮጵያ ማኀበረሰብ በታሪኩ ማኀበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን በመደገፍ የሚታማ አልነበረም፡፡ ያቃተው ያንን ተነሳሽነት ዘመናዊ ተቋማት እንዲደገፍ ማድረግ ነው፡፡በዚህም አዲስ ዘይቤ ከተሞችና በውስጣቸው ያሉ ዜጎች ተፈጥሮአዊ የሆነ ሐሳብን የመግለጽ መብታቸዉ እንዲከበር ታበረታታለች፤ ለዚህም ቀን ከሌት ትተጋለች፡፡ ሰዎች ሐሳባቸዉን በነጻነት የሚገልጹበት መድረክ እንዲሰፋ በስፋት እንዲከፈትና እንዲያድግ አዲስ ዘይቤ የቻለችውን ሁሉ ታደርጋለች፡፡ 

አስተያየት