ጥቅምት 20 ፣ 2011

የዘውግ ፌደራሊዝም እና ከተሞች

ወቅታዊ ጉዳዮችኹነቶች

ከጉባኤው ከተሞች ምን አተረፉ?በሐዋሳ ከተማ የተካሄደው 11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ወቅታዊ ፖለቲካን የሚከታተሉ በርካታ ሰዎችን ትኩረት ስቦ ነበር፡፡ ከፊሉ…

የዘውግ ፌደራሊዝም እና ከተሞች

ከጉባኤው ከተሞች ምን አተረፉ?

በሐዋሳ ከተማ የተካሄደው 11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ወቅታዊ ፖለቲካን የሚከታተሉ በርካታ ሰዎችን ትኩረት ስቦ ነበር፡፡ ከፊሉ የለውጥ ኃይሎች ያሏቸው ሰዎች መሪነታቸውን አስጠብቀው እንዲወጡ ሲመኙ ሌሎቹ ደግሞ ግንባሩን በመሰረቱት ፓርቲዎች መካከል በሚፈጠር መተናነቅ ሰላም እና መረጋጋት የራቃት ሀገር ወደባሰ ብጥብጥ እንዳትገባ ሲጸልዩ ነበር፡፡ ከተማዋ በአዘቦት የሚስተዋልባት የመዝናናት እና ለቀቅ የማለት መንፈስ ጉባኤተኞቹንም እንደሚቃኛቸው የገመቱም አልጠፉም። (ሮቤል ሙላት፣ ሐዋሳና የኢህአዴግ ጉባኤ) ጉባኤው እንደተፈራው ወይም አንዳንድ ተንታኞች እንዳስቀመጡት የሀገሪቱን የፖለቲካ መዘውር ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋገር ሳይሆን በአቶ ንጉሡ ጥላሁን በተነበበና “በሀገራችን እየተመዘገበ ያለው ለውጥ ህዝባዊ፣ ህገ መንግስታዊ እና ኢህአዴጋዊ” በሚል የአቋም መግለጫ የታጀበ ለውጥን ተጋፍጦ ከመውለድ ይልቅ ማመቻመች ላይ ያተኮረ ነበር ለማለት የሚያስደፍር ነበር፡፡ ምንም እንኳን ከተለያዩ ምንጮች ቁርጥራጭ መረጃዎች ወደ አደባባይ ቢወጡም ከመጋረጃ ጀርባ የነበረውን ምስል የሚከስት ነገር ባለመኖሩ ቢያንስ በሐዋሳው ጉባኤ ከግንባሩ ባህል ‘ዲሞክራሲ ማዕከላዊነት’ አላፈነገጠም ማለት ይቻላል፡፡ሐዋሳ እና ሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ከጉባኤው ያገኙት ጠቃሚ ነገር ቢኖር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመክፈቻ ንግግራቸው ያስቀመጡት ሐሳብ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክልላዊ አስተዳደር ከብሔር ማንነት ጋር ካልተምታታ የፈደራሊዝም ሥርዓት ለሀገሪቱ ተመራጭ መሆኑን በንግግራቸው ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ንግግር ለከተሜው ማኀበረሰብ ያለው እርባና ብዙ ነው፡፡ ይህንን ለመረዳት የከተሞችን ሥሪት እና መሠረታዊ አሐድ መረዳት ይጠቅማል፡፡

ብዝሓነት የከተሞች መገለጫ

ከተሞች ከሰው ልጅ አኗኗር ዘይቤ ጋር የተቆራኘ ታሪክ ያላቸው ጥንታውያን ናቸው፡፡ ከተሞች በዕድሜ ከኢንዱስትሪ አብዮት የትና የት ይቀድማሉ፡፡ ቢሆንም በኋላው ዘመን የከተሞችን ትርጓሜ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ከመሸጋገር ጋር የሚያይዙት አልጠፉም፡፡ ሰዎች ከገጠር ወደ ከተማ የተሻለ የስራ ዕድል እና የገቢ ምንጭ ፍለጋ በሚያደርጉት ሂደት ከተሞች ይቆረቆራሉ፤ ያድጋሉ። በዚህ ምክንያት ከተሞች ቅይጥ ማኀበረሰብ የመያዝ ዕድላቸው የሰፋ ነው፡፡ ከፊሉ በንግድ ሌላኛው ለትምህርት ቀሪው ደግሞ ስራ ፍለጋ ሲኳትን አንድ የደረጀ ከተማ ላይ ያርፋል፡፡ ለዚህም ነው ብዝሓነት የከተሞች መገለጫ ከሆኑ አሐዶች አንዱ ነው ቢባል ማጋነን የማይሆነው፡፡አሁን አሁን ከመጓጓዣ እና መገናኛ መንገዶች መዘመን ጋር ተያይዞ የሰው ዘር መቀየጥም በዚያው ልክ በሚያስገርም ፍጥነት አድጓል፡፡ በዚህም ምክንያት የዓለማችን ትልልቅ ከተሞች የተለያየ ማንነት ባላቸው ሰዎች የተጥለቀለቁ ናቸው፡፡ ከለንደን እስከ ሳኦፖሎ፣ ከኒውዮርክ እስከ  ሲንጋፖር የሰው ዘር ተቀይጦ በሰላም ይኖራል። ለንደንን ብንወስድ ከጋና አንስቶ ጃማይካ ብሎም ህንድ ድረስ የሚዘረጉ የተለያዩ ሀገራት ውስጥ የተወለዱ ሰዎች የሚኖሩባት፣ ከሁለት መቶ በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ከተማ ናት፡፡ እንደ ኒውዮርክ ደግሞ ቅይጥ አልተገኘም፤ በዥንጉርጉሯ ኪዊንስ አውራጃ፣ በመገኛቸው ስፍራ፣ የጠፉ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ሰዎች የሚገኙባት፣ የምታስደንቅ ነች፡፡ የሀገራችን ከተሞችም የመጠን መለያየት ካልሆነ በስተቀር ከዚህ የተለየ መልክ የላቸውም፡፡ አርመኖች በመምህርነት እና በስደት፣ ባንያኖች እና የመኖች ለንግድ፣ አፍሪካውያን በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ለትምህርት እና ለነጻነት ትግል፣ እና ሌሎች በተለያየ ሙያ የተሰማሩ የበርካታ የተለያየ ዜግነት ያላቸው የሚኖሩባቸው  ህብር መልክ ያላቸው ከተሞች ነበሩ፡፡ የተለያየ ዜግነት ያላቸው ሰዎች እንደዚህ ተጋርተው የምድሪቱን ፍሬ እየበሉ ከኖሩ አንድ ሀገር፣ ታሪክ እና መስተጋብር ያለው ማኀበረሰብ በከተሞች መጠለያ ማግኘት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡

እውን የተምታታ ነገር አለን?

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መምታታት ሲሉ የገለጹት የክልላዊ አስተዳደር እና የብሔር ማንነት ጉዳይ ይህንን የከተሞች መሠረታዊ መገለጫቸውን የሚፈታተን ብዝሓነታቸውን የሚያኮስስ አደጋ ጋርጧል፡፡ ይህንን ለመረዳት ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎችን መመለስ ያስፈልጋል፡፡ የመጀመሪያው እውን በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ስርኣት የአስተዳደር ክልል እና የማንነት ድንበርን ያምታታ ነው የሚል ሲሆን ሁለተኛው ይሄ አወቃቀር የከተማውን ማኀበረሰብ እንዴት ፈተና ውስጥ ሊከት ይቻላል የሚል ነው፡፡ አሁን በስራ ላይ ያለው ህገ መንግስት የሁሉም ሉዓላዊ ሥልጣኖች ባለቤት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች ናቸው ይላል። ቋንቋ እና ማንነት ሀገሪቱን ለማዋቀር በዋናነት አገልግለዋል። የትግራይ ክልል፣ የአፋር ክልል፣ የአማራ ክልል፣ የኦሮሚያ ክልል እና የሱማሌ ክልል በማለት በማንነት ብቻ የተደራጁ እና የሚጠሩ ክልሎችን ከዘረጋ በኋላ፤ ከዚህ የተረፉትን ደቡብ በሚባል የአቅጣጫ ሥም የቋንቋ ቤተሰባቸው፤ የቆዳ ቀለማቸው ሥልጣኔያቸው ታሪካቸው ወዘተ የማይመሳሰሉትን አንድ ላይ አዳብሎ ሲያበቃ  በቀሩት ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የተለያየ የሥያሜና የአወቃቀር መንገድ ተጠቅሟል፡፡ ክልል ያጡትን ብሔሮች ደግሞ  በዞን እና ወረዳ በማከፋፈል የኔ የሚሉት ከሌላው ጋር ግን የማይጋሩት የማንነት ወሰን/ክልል ሰርቷል፡፡“Territories have become mono-ethnic, even if they were not so historically; they cannot be shared by two or more groups.”  “Ethnicity is the dominant rhetorical figure in political discourse in Ethiopia and has permeated people’s identities and daily politics, whether they like it or not. It has inspired the governance model, the division and administration of the regional states, educational-linguistic policies and party politics.” (Jon Abbink; Ethnic-based federalism and ethnicity in Ethiopia: reassessing the experiment after 20 years)ይህ የሚሳየው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የሚያምታታ ሳይሆን በግልጽ የኢትዮጵያ ክልሎች ማለት የማንነት ድንበሮች ናቸው፡፡ ይህም ማለት እያንዳንዱ ማንነት የራሱ የሆነ ድንበር ያለው ክልላዊ ግዛት፣ ወይም ዞናዊ ግዛት አልያም ወረዳዊ ወይም ልዩ ወረዳዊ ግዛት እንዲኖረው አድርጓል፡፡

የማንነት ወሰኖች እና ከተሞች

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ብዙ ነቃፊዎች እና  ደጋፊዎች   አሉት፡፡ ይሁን እንጂ በከተሞች ላይ ያለውን በጎም ሆነ መጥፎ ተጽዕኖ ግን ብዙም ትኩረት የተሰጠው አይመስልም፡፡ በ1999 ዓ.ም. የተካሄደውን የሕዝብ እና ቤተ ቆጠራ ውጤት በመንተራስ በሀገሪቱ በህዝብ ብዛት ትልልቅ የሚባሉት ከተሞች አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ሐዋሳ እና አዳማ  ናቸው፡፡ እነዚህ ከተሞች ቅይጥ ማንነት ያላቸው አንድ ብሔር/ዘውግ ብቻውን ሃምሳ በመቶ የማይሆንባቸው ናቸው። በዚህ ምክንያት የማንነት ወሰን ከሚያስቀምጠው ከሀገሩ አስተዳደር ጋር ባይተዋር ሆነው ለብዙ ችግር ተዳርገዋል። አስናቀ ክፍሌ “Ethnic Decentralization and the Challenges of Inclusive Governance in Multiethnic Cities: The Case of Dire Dawa, Ethiopia” በተሰኘው ጥናቱ ለችግሩ ምንም አይነት ትኩረት እንዳልተሰጠው በመረጃ አስደግፎ ጽፏል፡፡ ባንድ ወቅት የፈረንሳይ፣ የህንድ፣ የየመን፣ የሌሎች ሀገራት እና ቅይጥ የሆነውን የኢትዮጵያ ማኀበረሰብ አስተባብራ በፍቅር ስትኖር የነበረቸው ድሬዳዋ ጠቅልለው በሁለት ማንነቶች ወሰን ውስጥ ሊያስገቧት በሚሞከሩ ኃይሎች መሀል ሆና ተጠብቃ ለኢትዮጵያ ልጆች ጠባለች፡፡ ወትሮው የራሷን መልክ ይዛ በኮስሞፖሊታንነት የምትታወቀው ድሬ አሁን የዘውግ ማንነት ጉልቶ የሚሰማባት መሆን ጀምራለች፡፡ የከተማው ነዋሪም ለብዙ እንክርት እና እንግልት ተዳርጓል፡፡ የፌደራል መንግስት ነባራዊ ሁኔታውን ግምት ውስጥ ያስገባ ውሳኔዎች በማስተላለፍ ከሞላ ጎደል ሰላም እና መረጋጋትን ቢፈጥርም ዛሬም ከተማዋ ዘላቂ መፍትሔ አጥታ በቋፍ ትገኛለች። የማንነት ወሰንን ያሰመረው ሥርኣት ያደረሰው ጉዳት የሚጠገን አይመስልም።ድሬዳዋን ለአብነት አነሳን እንጂ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ከተሞች ተመሳሳይ በሆኑ ችግሮች እየተጠቁ ነው፡፡ ከተሞች በፊት የነበራቸውን ውበት እየለቀቁ የሚገኙበትን የማንነት ወሰን/ክልል የመሰለ አንድ አይነት ብቻ እየሆኑ ነው። ከተሞች በባህርያቸው ታታሪነት እና ልዩ ተሰጥኦን የሚሸልሙ ነበሩ፡፡ ለአዲስ አስተሳሰብ፣ ለአዲስ ባህል፣ ለአዲስ እውቀት ቦታ የሚሰጡ ሀገራዊ ለዛቸውን ሳይተው ዓለምአቀፍ ዕውቀቶች እና የአኗኗር ዘይቤን የራሳቸው የሚያደርጉ ነበሩ፡፡ ከአንድ ወር በፊት በመቀሌ ከተማ ያገኘኹት ወጣት በፊት በወልደያ ከተማ ልብስ በመሸጥ የሚተዳደር ነበር፡፡ የፖለቲካ ትኩሳቱን ተከትሎ ንብረቱን እንደተዘረፈና ወደ ትግራይ  ሸሽቶ እንደመጣ ያጫወተኝ የሚረሳ አይደለም፡፡ ተክሊት በወልዲያ ብዙ ጓደኞች እና ትዝታዎች አሉት፡፡ ከተማዋንም ይወዳታል፡፡ በታታሪነቱ አቅፋውና ሸልማው ነበር፡፡ አሁን ግን ሰላም ቢፈጠርም ተመልሶ መሄድ አይፈልግም፡፡ ተመሳሳይ ኹነቶች በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ከተሞች እየተስተዋለ ነው፡፡ ጎንደር፣ ወልዲያ፣ ሐዋሳ፣ አዳማ፣ አሶሳ፣ ጅግጅጋ፣ ሐረማያ፣ ቡራዮ፣ ጋምቤላ፣ አርባ ምንጭ፣ አዲስ አበባ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በማንነት ወሰኖች ከተሸበሩ ከተሞች ዝርዝር ውስጥ ናቸው። ምንአልባትም ዝርዝሩ ከዚህ ይሰፋ ይሆናል፡፡

በመቃብሬ ላይ…

ኢህአዴግ  እነዚህ ነገሮች ሊቀየሩ የሚችሉት በኢህአዴግ መቃብር ላይ ነው የሚሉ መሪ ነበሩት፡፡ ይህንን የተረዱ ሰዎች ኢህአዴግ ገድለው መለወጥ፣ ማስተካከል የሚፈልጉትን ለማስተካከል ብረት አንሰተው ወደ በርሓ ወርደው ነበር፡፡ አዲሱ የድርጅቱ ሊቀመንበር የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ መገዳደል ይብቃ የሚል ቁርጠኝነት በመያዝ ለሁሉም ኃይሎች ጥሪ በማድረጋቸው ብዙ ቡድኖች ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል፡፡ ይህ በመቃብሬ ላይ ከሚለው የግንባሩ ልማድ ያፈነገጠ ነው፡፡ የብሔር ማንነትን መሠረት ያደረገው መዋቅር ደጋፊዎችም ዛሬም ይህ መዋቅር የሚለወጠው/የሚስተካከለው በመቃብራችን ላይ እያሉ ነው፡፡ በዐቢይ አሕመድ የሚመራው መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ አቋም ግልጽ አይደለም፡፡ ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ባለፉት ስድስት ወራት እንደተወሰዱት ያሉ የለውጥ እርምጃዎች የሚወሰዱ አይመስሉም፡፡ መጠነኛ የለውጥ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚችሉ መገመት ቢቻልም ይህንን ብሔር ተኮር ሀገራዊ መዋቅር ማስተካከል ግን ቀዳሚ አጀንዳ የተደረገ አይመስልም፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከልም ይህንን የከተሞች አጀንዳ ይዞ የሚንቀሳቀስ የለም ለማለት ያስደፍራል። ከዚህ ነባራዊ ሁኔታ መረዳት የሚቻለው ከተሞች ከነዋሪዎቻው ጋር በቅርቡ መፍትሔ እንደማያገኙ ነው፡፡ ያለባቸው ችግር እንደቁስል እያመረቀዘ እና እየሰፋ የሚሄድ ነው፡፡ የአብሮነት ተምሳሌት የመሆን ዕድላቸው እየመነመነ፣ የኢትዮጵያ ማኀበረሰብ እሴቶችን ከዓለምአቀፍ እውቀቶች እና የአኗኗር ዘይቤዎች በመዋሐድ የነበራቸው ሚና እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ ተስጥኦን፣ ታታሪነት ከማበርታት ይልቅ ማንነትን ማስቀደም ሲጀመሩ የልህቀት ማዕከልነታቸው (Center of Excellence) እያከተመለት ይሄዳል፡፡ ሀገሪቱ እንደ አንድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማኀበረሰብ የመቀጠሏም ነገር ከተሞችን በምትመለከትበት መነጽር ይወሰናል፡፡ በዚህ ምክንያት የከተሞች ጉዳይ የፖለቲካ ትኩሳቱ ማጠንነጠኛ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ የሆነው ሆኖ ጉዳቱ ለጊዜው ለከተሜው ነዋሪ ከማንም በላይ ያሳምም ይሆናል። ነገር ግን የፌደራሊዝም አራማጅ ሹመኞች አንድ የሳቱትን ነገር በማውሳት ጽሁፌን ላጠቃልል፡፡ የትኛውም ዘመናዊ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሥርዓት መቀመጫ ማዕከሎች ከተሞች ናቸው። የአዲስ አበባን ነዋሪ ሳያቅፉ ከአዲስ አበባ ሆኖ ማስተዳደር፤ የድሬዳዋን ነዋሪ እየገፉ ከድሬዳዋ ሆኖ የከተማ አስተዳደር መምራት፤ የአዳማን ነዋሪ ገሸሽ አድርጎ አዳማ ተቀምጦ ክልል ማስተዳደር፤ በአንድ እጅ ሌላውን እጅ እንደመቁረጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሀሳቦችና አሰራሮች መፍለቂያ ማዕከሎች ከተሞች ናቸው፤  ሌላው ይቅርና ፖለቲከኞችም ትምህርትና ሥልጠና የሚወስዱት፤ ሀብት የሚያንቀሳቅሱት፤ ቤተሰቦቻቸውንም የሚያኖሩት የከተሜነት ትሩፋት ከሆኑ የትምህርት የባሕል የመኖሪያና የቴክኖሎጂ ማዕከላት በሆኑት አዲስ አበባ፤ ድሬዳዋ፤ አዳማ፤ ሐዋሳ፤ ጅማ፤ መቀሌ፤ ወልዲያ እና በመሰል ከተሞች ነው፡፡

አስተያየት