You can paste your entire post in here, and yes it can get really really long.
ከ29 ዓመታት በፊት እንዲህ ሆነ፡፡ የሶሻሊስታዊ ርዕዮት ተከታይ ነኝ ሲል የነበረው ደርግ፤ ረጅም ጊዜ ሲካሄድ የነበረው ፍልሚያ ታክሎበት፤ በግራ ቢለው በቀኝ አልሞላ ያለውን የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት እስኪ ወደቅይጥ ወስጄ ልሞክረው አለ፡፡ እናም በ1982 ዓ.ም. የቅይጥ ምጣኔ ሃብታዊ ስርዓት (Mixed Economy) በሥራ ላይ እንዲውል ሆነ። በዚህም አላበቃም፡፡ በ1984 ዓ.ም. ደርግ ከሥልጣን ከወረደ ከአንድ ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ የነፃ ገበያ ሥርዓት ታወጀ። የነፃ ገበያ ሥርዓት በኢትዮጵያ ከታወጀ 27 ዓመታትን ቢያስቆጥርም እስካሁን ድረስ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻችንም ላይም ሆነ የሕዝቡ አመለካከት ላይ ሶሻሊስታዊው ሥርዓት ያስቀመጠው ማህተም አልደበዘዘም፡፡ይህንን በምጣኔ ሃብት ፖሊሲዎቻችን ላይ ረጅም ዘመን የወደቀውን የሶሻሊስታዊ አስተሳሰብ ለማሳየት እና ውጤቱንም ለማመላከት የሚከተሉትን ማሳያዎች አቀርባለሁ፡፡ፊት የተነሳው የገበያ ሥርዓትሃገራችን ውስጥ ብዙ ያልተሟሉ ፍላጎቶች አሉ፡፡ የቤት፣ የትራንስፖርት፣ የመሠረታዊ ፍጆታ እቃዎች (ስኳር፣ ዘይት፣የዳቦ ዱቄት)፡፡ ባረጀው ባፈጀው ሶሻሊስታዊ እይታ እነዚህን ፍላጎቶች ለዜጎች የማዳረስ ሃላፊነት የመንግስት ነው፡፡በተለያዩ ምጣኔ ሃብታዊና መዋቅራዊ ውስንነቶች ምክንያት ለመንግሥት እነዚህን ፍላጎቶች ማሟላት የዳገት ያክል ይከብደዋል፡፡ ይህም በዜጎች ላይ የኑሮ ጫና ስለሚያስከትል መንግስትን የእናቴ መቀነት አደናቅፎኝ አይነት ሰበብ ውስጥ ይከተዋል፡፡ ማስተባበልና ሌሎችን መውቀስ የሰርክ ሥራው ይሆናል፡፡የዳቦ ዱቄት ማዳረስ ያልቻልኩት በኢኮኖሚ እድገት ምክንያት ብዙ ዜጎች ዳቦ ገዝተው መብላት በመቻላቸው ነው የሚል ቀልድ ሁሉ ይጀምራል፡፡ “የስኳር እጥረት የተከሰተው በስግብግብ ነጋዴዎች አሻጥር ምክንያት ነው” ይለናል፡፡ለነዚህ ሁሉ ችግሮች መሠረታዊው ምክንያትና መነሻ ግን እየተከተለው ያለው የግሉን ዘርፍ አግልግሎት “ለሁሉም ነገር መፍትሔው መንግስት ነው::” የሚል የተወላገደው አስተሳሰብ ነው፡፡በገበያ ሥርዓት እይታ ያልተሟላ ፍላጎት አለ ማለት ጥሩ የገበያ እድል እንዳለ ማሳያ ነው፡፡ያልተሟላ ፍላጎት ሁልጊዜም “የመንግስት ሸክም” ሳይሆን “የገበያ ዕድል” ነው፡፡ብዙ የቤት ፈላጊ አለ ማለት የግል አልሚዎች ለዜጎች ቤት ሠርተው፣ ሸጠውና አትርፈው ራሳቸውንም መጥቀም ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ባንኮች የቤት ብድር (mortgage finance) በመስጠት ትርፍ ለማገኘት ሰፊ እድል አላቸው ማለት ነው፡፡ በዘርፉም ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል።፡አዲስ አበባ ውስጥ የራስን ቤት መስራት ማለት ለናጠጠ ሃብታም የተተው ነገር ነው፡፡ መካከለኛ ገቢ ላለው ሰው አዲስ አበባ ውስጥ ቤት መግዛት የማይጨበጥ የሩቅ ህልም ነው፡፡ ይህ በዋነኛነት የአቅም ጉዳይ አይደለም የኢኮኖሚ ፖሊሲው ሶሻሊስታዊ ጥላ ስላጠላበት የመጣ ውጤት ነው፡፡አንድ ከፍተኛ የሚባል ገቢ የሚያገኝ ግለሰብ አዲስ አበባ ውስጥ ለተከራየው አፓርታማ በወር ብር 15,000 ኪራይ ሊከፍል ይችላል፡፡ ይህን ያህል መጠን ያለው ክፍያ ለበርካታው የከተማ ነዋሪ እጅግ ከባድ ቢሆንምና ለዓመታት ቢቀጥልም (ኪራዩ ሊጨምርም እንደሚችል መጠበቅ እንዳለ ሆኖ) ከዓመታት በኋላ እንኳን ቤቱን የራስ ማድረግ የሚቻልበት እድል ዝግ ነው። ይህ በአሜሪካን አገር ቢሆን ኖሮስ? አንድ ሰው 100,000 ዶላር (2.75 ሚሊዮን ብር) የሚያወጣ ቤት ቢፈልግ የቤቱን ወጪ ለሠላሳ አመት በሚከፈል 5 መቶኛ ወለድ በሚታሰብበት ብድር በመውሰድ በወር 14,763 (536.8 ዶላር) በመክፈል ቤቱን የራሱ ሊያደርገው ይችላል፡፡ እዚህ ጋር የግለሰቡ ቤት የመግዛት አቅም አይደለም የቤት ባለቤትነትን የወሰነው፤ የፖሊሲና የአመለካከት ውጤት እንጂ። አንዱ ሰው ብር 14,763 እየከፈለ ቤት እንዲኖረው ሲሆን ሌላኛው ብር 15,000 እየከፈለ እድሜውን ሙሉ ቤት እንዳማረው ይኖራል፡፡ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት መሬትን አንቆ በመያዝ (በዚህ ምክንያት የመሬት ዋጋ በማናር)፣የፋይናንስ ዘርፉን በማፈን፣ ለግል አልሚዎች ምቹ ሁኔታ ባለመፍጠር መካከለኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች ቤትን የማይታሰብ የመንግስተ ሰማይ ህልም እንዲሆንባቸው አድርጓል፡፡በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐቢይ ለረጅም ጊዜ ለተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ጋዜጠኞች እና አክቲቪስቶች ላይ ይለጠፍ የነበረውን የሽብርተኝነት ስም አንስተው “እንዲያውም መንግስት ነው ሽብርተኛ” ብለው ነበር። መንግስት ፖለቲካዊ ስሙ ‘ሽብርተኛ’ ከሆነ ምጣኔ ሃብታዊው ደግሞ ዋነኛው ‘ኪራይ ሰብሳቢ’ ነው፡፡የመሬት አቅርቦትን በማፈን እና ዋጋውን በማስወደድ የዜጎችን ወገብ የሚያጎብጥ ሂሳብ የሚጠይቀው ሌላ ማንም ሳይሆን መንግሥት ነውና፡፡በነገራችን ላይ መንግሥት የቤት ልማት ላይ ወይም ሌላ ዘርፍ ላይ ምንም አይነት ሚና ሊኖረው አይገባም የሚል አቋም የለኝም፡፡ ጣልቃ ገብነቱ ግን ሊመጠን ይገባዋል፡፡መንግሥት ገበያ ውስጥ እጁን ማስገባት ትክክል ከሚሆንባቸው ምክንያቶች አንዱ ገበያ በማይሰራበት ሁኔታ ነው፤ ይህም የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎቹ የገበያ ውድቀት (market failure)የሚሉት ሁኔታ ሲገጥም ነው፡፡ለምሳሌ የግል ሪል ስቴት አልሚዎች አነስተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ቤት ሊያቀርቡ ስለማይችሉ መንግሥት በድጎማ የጋራ መኖሪያ ቤት ቢገነባ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን መንግሥት ሌላ አንገብጋቢ ጉዳዮች እያሉበት ለግለሰቦች ቤት ለመስራት መጨነቅ አልነበረበትም፤ ባይሆን መንግሥት ለግል አልሚዎች ምቹ ሁኔታ በመፍጠርና ዘርፉን በአግባቡ በመቆጣጠር (regulate) እኔና መሰሎቼ ቤት እንድንሰራ ሜዳውን ቢያደላድልልን ብቻ በቂ ነበር፡፡ስለዚህም ይህንን ሸክም ከመንግስት ጫንቃ በማውረድ ለገበያ መስጠት የተሻለ አማራጭ ነው፡፡አንድ ሌላ የገበያ ውድቀት ማሳያ ልጨምር፡፡ከጥቂት ቀናት በፊት ነው፡፡ በአንድ አድካሚ ቀን የመኪና ነዳጅ ለመቅዳት ብዙ ቦታ ዞርኩ፡፡ከብዙ መንከራተት በኋላ አንድ ነዳጅ ማደያ ላይ ቆሜ፤ ለሁለት ሰዓታት ተሰልፌ ነዳጅ ቀዳሁ፡፡መንግሥት “የሕዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ” ሲባል የነዳጅን የትርፍ ህዳግ በሊትር 7 ሳንቲም ወስኖታል። ይሄ የትርፍ ህዳግ ደግሞ አዋጪ ስላልሆነ የግል ባለሀብቶች ዘርፉን እንዲሸሹት ሆነ፡፡ የነዳጅ ማደያዎችም በቂ ስላልሆኑ ረጅም ሠልፍ መሰለፍ ግድ ነው፡፡ የዚህ አሠራር (መመሪያ) ውጤት ህዝብን ማንገላታት እና ለተጨማሪ ወጪ መዳረግ ሲሆን ነዳጅ ለመቅዳት በየቦታው ረጃጅም ሰልፎችን (ባለ ሶስት እግር ተሸከርካሪዎችን ጨምሮ) መመልከት ብርቅ አይደለም፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ ሲወጣም ችግሩ የባሰ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡ይህን የመንግስት የተሳሳተ የገበያ ተኮር ኢኮኖሚ አመለካከት በግለሰብ ደረጃ ያለውን ተፅእኖ አይተን ነገሩን በሀገር አቀፍ ደረጃ ልንመለከተው ከፈቀድን እጅግ ገዝፎ ይታየናል፡፡ ለምሳሌ በዚህ ቀን ለነዳጅ ፍለጋ እና በሰልፍ ጥበቃ ሁለት ሊትር የሚጠጋ ነዳጅ አንተክትኬ ወደ 38 ብር አካባቢ ተጨማሪ ወጪ አውጥቻለሁ፡፡ በዕለቱ 30 ሊትር ነዳጅ የቀዳሁ ሲሆን በነዳጅ ፍለጋ ምክንያት አንድ ሊትር ለመቅዳት ተጨማሪ አንድ ብር ከሀያ ሳንቲም የፍለጋ ወጪ አውጥቻለሁ፡፡ “ለሕዝብ ጥቅም ሲባል” መንግስት የትርፍ ህዳጉን 0.7 ሳንቲም ላይ በመገደቡ በእያንዳንዱ ሊትር እኔ ለተጨማሪ አንድ ብር ከሃያ አምስት ሳንቲም ወጪ ተዳርጌያለሁ፡፡አስቡት እንግዲህ መንግሥት ጥቂት ሳንቲሞችን ለነዳጅ አከፋፋዮች ላለመጨመር ዜጎችን ለተጋነነ ተጨማሪ ወጪ እንዴት እንደሚዳርግ፡፡ከዚህ በተጨማሪ ነዳጅ ለመቅዳት በሚል ምክንያት በሰልፍ የሚባክነው ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚኖረው አሉታዊ የሆነ ተጨማሪ ዋጋም አገሪቱ ትከፍል ዘንድ ወይም በዚህ ምክንያት የአገሪቱ የምጣኔ ሃብት እድገት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖም በብር ተተምኖ ቢቀርብ የዋዛ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ በነዳጅ ላይ ያለው ይህ አነስተኛ የትርፍ ህዳግ ካልተስተካከለ በክልል ከተሞች የምናውቀው ረጅም የባጃጅ ሰልፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና አዲስ አበባም የዚህ ችግር ተጠቂ እንደምትሆን ለማወቅ ብዙ ማሰላሰል አያስፈልግም፡፡ የመኪናዎች ቁጥር እየጨመረ የነዳጅ ማደያዎች ቁጥር አለማደግ ሊያሳስበን ይገባል፡፡በሀገሪቷ የነዳጅ ማድያ እጥረት መኖሩን መንግስት ያምናል፡፡ ይሄ በጎ ነገር ነው፡፡ግን መጥፎ ነገሩ መንግስት ይሄንን ችግር ለመፍታት ያሰበው አማራጭና መፍትሄ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አንድ መቶ ስልሳ የነዳጅ ማደያዎችን እንዲገነባ ማድረግ፡፡ በሶሻሊስታዊ ቅኝት የሚያዜም ጭንቅላት ያለው ፖሊሲ አውጪ መንግሥት ለሁሉም ነገር መፍትሄ ሰጪ እንደሆነ ያምናል፡፡ የግሉን ዘርፍ የትርፍ ህዳግ ለገበያ መተውና ለነዳጅ ማደያ ስራ መሬት መስጠት ሲችል እኔው ራሴ ነዳጅ ችርቻሮ ስራ እሠራለሁ ይላል፡፡የሆነስ ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት የችርቻሮን ስራ መስራት እንደማይችልበት ለማወቅ ስንት ዓመት ያስፈልገናል? የስንት ችርቻሮ የመንግሥት ድርጅቶችን ውድቀት ማየት ይበቃናል? ስኳር እና ዱቄት በአግባቡ ማከፋፈል እንዳልቻለ እያየ አሁን ደግሞ እስቲ ነዳጅን ልሞክር ማለት በሀገሪቷ ሃብት ላይ ቁማር እንደመጫወት ይቆጠራል፡፡የገበያ ሕግ ፀር የሆኑ ሕጎችየሶሻሊስታዊ አመለካከት ሌላው መገለጫ የገበያ ሕግን የሚፃረሩ ሕጎችንና መመሪያዎችን ማብዛት ነው፡፡እኛም ሀገር ብዙ እንዲህ አይነት ሕጎች አሉ፡፡ በ2003 ዓ.ም ኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር በሚል ምክንያት በ17 መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ የዋጋ ገደብ (Price Cap) ጣለች፡፡ (ከ17ቱ መሠረታዊ ፍጆታ እቃዎች ውስጥ ቢራ መካተቱ በምን ስሌት እንደሆነ ባይገባኝም)፡፡ መንግስት በወቅቱ የዋጋ ገደብ ለማስቀመጥ ያቀረበው ምክንያት «በስግብግብ ነጋዴዎች» ምክንያት የተከሰተውን ባለሁለት አሀዝ የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል የሚል ነበር፡፡ነገር ግን የዋጋ ግሽበቱ መነሻ አገሪቷ የተከተለችው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤት ነበር፡፡የዋጋ ግሽበት መቼም እና የትም ቢሆን የገንዘብ ፖሊሲ ዉጤት ነው (“inflation is always and everywhere a monetary phenomenon” እንዲል ሚልተን ፍሬድማን የተባለው በምጣኔ ሐብት የኖቤል ፕራይዝ ተሸላሚ፡፡የሆነው ሆኖ ጥሬ ስጋ በኪሎ 52 ብር፣ ስኳር በኪሎ 14 ብር፣ ሙዝ በኪሎ 7 ብር፣ አንድ ጠርሙስ ቢራ 7 ብር ነው ተባልን፡፡ መንግስት “ስግብግብ ነጋዴዎች የእጃቸውን ያገኛሉ” አለ፡፡ ተጠቃሚ ይህ የሚሆን መስሎት ለጊዜው ተደሰተ፡፡ ይህ ደስታ ግን ብዙም አልቆየም፡፡ መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች ከሱቆች መደርደሪያ ላይ ጠፉ፡፡ ልጇን ዳቦ በሻይ አብልታ ወደ ት/ቤት የምትሸኝ ምስኪን እናት “ርካሹን” ቁርስ ማቅረብ አቃታት፡፡ ሥጋ ቤቶች ቁርጥ ሲባሉ “የመንግስት ወይስ የግል?” ብለው ማፌዝ ጀመሩ፡፡ውሳኔው ይልቁንም ሻጭና ገዢን በባላንጣነት እንዲተያዩ አድርጎ አልፎ አልፎም ለግጭት ዳርጎ አለፈ፡፡ከብዙ ውዥንብር እና ግራ መጋባት በኋላ የዋጋ ገደቡ የታሰበውን ውጤት ሳያመጣ ቀረ፡፡ በሶሻሊስታዊ አመለካከት የተቃኘ ውሳኔ እንደገና ቀለደብን፡፡ መንግሥትም ያወጣው ደንብ ውጤታማ እንዳልነበረ ሲረዳ ምንተፍረቱን በቃ ካሁን በኋላ የዋጋ ገደቡ ተነስቷል ነገር ግን ሦስት መሰረታዊ እቃዎችን (የስንዴ ዱቄት፣ዘይት እና ስኳር) መንግስት ያከፋፍላል አለን፡፡ወራጅ ውሃን የቱንም ያህል ብታፍነው መውጫ ፈልጎ መውጣቱ አይቀርም፡፡ቦይ በመስራት የውሃን አቅጣጫ መቀየስ ይቻላል፤ ሙሉ በሙሉ ማገድ ግን አይቻልም፡፡ ገበያም እንደዛው ነው፤ ልታፍነው አትችልም፤አቅጣጫ ልታስይዘው ግን ትችላለህ፡፡የሶሻሊስታዊ አመለካከት ተጽዕኖ ነው መሰል ብዙ የማይረቡ የገበያ ሕጎችን እና ደንቦችን እናወጣለን፡፡በቅርቡ ከገረሙኝ መመሪያዎች አንዱ የዲያስፖራ አካውንት ተቀማጭ ገንዘብ 50 ሺ ዶላር ላይ መገደቡ ነበር አሁን መነሳቱ በጀ እንጂ፡፡ መነሳቱ ጥሩ ግን መጀመሪያውንስ ዶላር ለተጠማች ሃገር ይህንን ገደብ ማስቀመጥ ለምን አስፈለገ? የመገደብ ሱስ ካልኖረብን በቀር!የአላስፈላጊ ደንቦች መብዛት እንዳለ ሆኖ ይበልጥ የሚገርመው ደግሞ የአስፈላጊ ደንቦች አለመኖር ነው፡፡ሰዎች በጠራራ ፀሃይ በአክሲዮን ማኅበር ስም ያስቀመጡትን ገንዘብ ሲዘረፉ ይህንን የሚከላከል የህግ ማእቀፍ የለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በሥርዓት የሚመሩት አክሲዮኖች የፋይናንስ ተቋማት ብቻ ናቸው ማለት ይቻላል ምክንያቱም የብሔራዊ ባንክ ክንድ የበረታ ስለሆነ፡፡ ዜጎችን “ቤት ልስራልህ፡ መኪና ላስመጣልህ” ብሎ መዝረፍ ቀላል ነው፥ለዚህ የሚሆን በቂ የህግ ማዕቀፍ ስለሌለ፡፡ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ላይ ሕግ ሳናወጣ የማያስፈልገው ላይ የሕግ እና ደንብ ጋጋታ እናበዛለን፡፡ከሶሻሊስታዊ ወይንም ሁሉን ድሃ እድርጎ እኩል ከሚያደርግ አስተሳሰብ የፖሊሲ አውጪዎቻችን ጭንቅላት ነጻ የሚወጣበትን ጊዜ እንናፍቃለን፡፡ እስከዚያው ይህን አመለከከት አዲዮስ እያልን በመራገም እንቆያለን፡፡