Photo credit should read OLIVIER MORIN/AFP/Getty Images)[/caption]ሁሉም "ከዚህ በኋላ ወደሀገሩ ይመለስ ይሆን?፤ በቀጣይስ እጣ ፈንታው ምን ይሆን?" እያለ አንዱ ለአንዱ መላሽ በሌለበት ጥያቄ አቅራቢ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ በሌላ ጥግ ግን የፈይሳ ተቃውሞ ከውድድሩ መጠናቀቅ በኋላም ቀጥሎ በሽልማት አሰጣጡ ላይም ተደገመ፡፡ውድድሩን በቀጥታ ያስተላልፍ የነበረውና የኢትዮጵያ መንግሥት ቀዳሚ የፕሮፓጋንዳ ማሽን ሆኖ ያገለግል የነበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጭምር ያልተጠበቀው ሁነት በድጋሚ ምስል እንዳይታይ ከማድረግ በዘለለ የተሻለ እድል አልነበረውም፡፡በወቅቱ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የፈይሳን ድርጊት በቀጥታ ስርጭት ከመመልከት ያገደው አልነበረም፡፡ድህረ ተቃውሞፈይሳ ከተቃውሞው በኋላ ወዲያው ድርጊቱን ላልተረዳው የዓለም ህዝብ ለማስረዳት አስተርጓሚ ፍለጋ የመገናኛ ብዙሀን ዘጋቢዎች ወደከተሙበት የስታዲየሙ ክፍል አመራ፡፡ ነገር ግን በአስተርጓሚነት የተመደበው ሰው ለአትሌቱ መልዕክቱን ተርጉሞ ለመገናኛ ብዙሀን ዘጋቢዎች ለመንገር አሻፈረኝ አለ፡፡ለመላው አለም በእንግሊዘኛ መልዕክቱን ማስተላለፍ በመቻሉ ዙሪያ እርግጠኛነት ያልነበረው ፈይሳ ግን እዚህም ላይ ተቃውሞ ለማሰማት የተጠቀመበትን ድፍረት በመነሳሻነት ይዞ በተሰባበረ እንግሊዘኛ የውስጡን ተናገረበት፡፡የኢትዮጵያ አምባገነን መንግሥት የሀገሩን ህዝቦች እየገደለበት መሆኑን እና ብዙዎች እስር ቤት እንደሚገኙ መብቱን የሚጠይቅ አካልም ምላሹ ግድያ መሆኑን በመናገር ያገኘውን እድል በአግባቡ ተጠቀመ፡፡በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ በመቀጠል "አሁን እኔ ወደ ኢትዮጵያ ብሄድ ሊገሉኝ፣ ሊከሱኝ ወይም ወደሌላ ሀገር እንድሰደድ ሊያደርጉኝ ይችላሉ፡፡" ሲል የወቅቱን መንግሥት ጉድ በአደባባይ አፍረጠረጠ፡፡በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት ባልጠበቀው መልኩ በአደባባይ የደረሰበትን ውግዘት ለመከላከል መውተርተር ጀመረ፡፡ ለዚህ እንዲረዳው በማሰብም በያኔው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚኒስቴር ጌታቸው ረዳ አማካኝነት አትሌቱ ወደሀገሩ ቢመለስ ምንም መጥፎ ነገር እንደማይደርስበትና የጀግና አቀባበል እንደሚደረግለት መግለጫ አሰጠ፡፡ የኮምኒኬሽን ሚኒስትሩን መግለጫ በማስመልከት ጥያቄ የቀረበለት ፈይሳ በበኩሉ የተመለስ ጥያቄውን ከመቀበል ይልቅ ሌሎች በመንግሥት ተፈፀሙ ያላቸውን ጉዶች ዘረዘረ፡፡ በ 1997 ዓ.ም. የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ አራት ጓደኞቹ እንደተገደሉበትና ወደሀገር ቤት ለመመለስ የማያስችሉት ብዙ አስፈሪ ምክንያቶች እንዳሉ ተናገረ፡፡በመጨረሻም ወደሀገሩ በመሄድ መከራን ከመቀበል ይልቅ የስደት ሕይወትን መረጠ፡፡ በላቲን አሜሪካዋ ብራዚል ባሉ የፖለቲካ አቀንቃኞች እገዛም ሌላ አማራጭ እስኪያገኝ በብራዚል መቆየት የሚያስችለውን እድል አገኘ፡፡ነገር ግን በወቅቱ ከቤተሰቡ ከሁለት ሳምንታት በላይ ተለይቶ ለማያውቀው ፈይሳ ሁኔታው ግራ አጋቢ ነበር፡፡ በተለይም ደግሞ አባታቸውን ያልጠገቡ ገና ከአምስት አመት በታች እድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ላሉበት ቤተሰብ የአባታቸው በወጣበት መቅረት ነገሩን አክፍቶታል፡፡በዚህ ሁሉ መሀከል ሀገር ቤት የባለቤቷ መለየትና ልጆቿን ለብቻዋ የማሳደግ እጣ ፈንታን የተጋፈጠችው ባለቤቱ ኢፍቱ እራሷን አጠንክራ ለልጆቿና ለወዳጅ ዘመዶቿ ብርታት ከመሆን ውጪ አማራጭ እንደሌላት ተረዳች፡፡ ከተቃውሞው በኋላ በነበሩት ቀጣይ ሶስት ወራትም እሷና ልጆቿ ፈይሳን በኢንተርኔት የተንቀሳቃሽ ምስል (Video Call) አማካኝነት እያገኙ ማውራትን ልማድ አደረጉ፡፡ በዚህ መሀከል ግን ፈይሳ ልቡን የሚሰብር ዜና ከሀገር ቤት ወደ ጆሮው ደረሰ፡፡ በብቸኝነት ውስጥ የነበረው አትሌቱ የቅርብ ጓደኛውን ከበደ ፈይሳ መርዶ ሰማ፡፡ ለፈይሳ የልብ ወዳጁን ሞት ይበልጥ አስከፊ ያደረገበት ደግሞ ከበደ የተሰዋው ከኦሎምፒኩ መጠናቀቅ በኋላ በቂሊንጦ በእስር ላይ በነበረበት ወቅት በተነሳ እሳት መሆኑ ነው፡፡"መያዙን እራሱ አልሰማሁም ነበር፤ መሞቱን በፌስቡክ ነበር የሰማሁት፡፡ እሱ በህይወቴ ብዙ መልካም ውለታዎችን የዋለልኝ ሰው ነበር፡፡" ሲልም መርዶውን የሰማበት ሁኔታ በራሱ ልብ የሚሰብር እንደነበር ፈይሳ በአንድ ቃለመጠይቅ ላይ ተናግሯል፡፡ አሜሪካ፡- አዲስ ሕይወት፣ አዲስ ፈተናከብራዚል የአንድ ወር ገደማ ቆይታ በኋላም ፈይሳ በአሜሪካ በነበረ አንድ ኤርትራዊ አትሌት ወዳጁ ግብዣ አማካኝነት በ አዲስ አመት 2009 ዓ.ም. መስከረም ወር ላይ ወደሰሜን አሜሪካዋ ሀገር አቀና፡፡አትሌቱ ከማራቶን ሯጭነቱ ጋር በተያያዘ በልምምድ የታጀበ ህይወት ያለው መሆኑ፣ ከአሜሪካ በውክቢያ የተሞላ የስደት ህይወትና የቤተሰቡ ናፍቆቱ ጋር ተደምሮ አስቸጋሪ ገጽታ ነበረው፡፡ በተለይም ደግሞ ከዕለታዊው አብዛኛውን ሰዓት ለልምምድ አጥፍቶ ወደቤት ለሚመለሰው ፈይሳ በአሜሪካ ከአዲስ የአናኗር ዘይቤ ጋር ለመጋፈጥ ተገደደ፡፡ አትሌቱ በሀገሩ ባህል እንደተለመደው ምግብ አብስላ የምትጠብቀው ባለቤቱም ሆነ የቤት ሰራተኛ በአጠገቡ የሌለ መሆኑ የስደት ህይወቱ ሌላኛ ፈተና ነበር፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም አብዛኛውን ጊዜ በዛ ከተባለ በቀን ለሁለት ጊዜያት ብቻ የሚመገብ ሲሆን በቀን አንድ ጊዜ ለመመገብ የሚገደድባቸው ቀናትም ጥቂት አልነበሩም፡፡ከወራት በኋላም ነገሮች ተረጋግተው የካቲት ወር በፈረንጆች የፍቅር ቀን ኢፍቱ ባለቤቷን ሁለት ልጆቿ ደግሞ የናፈቁትን አባታቸውን ለማግኘት ወደሚገኝበት አሜሪካ በረሩ፡፡ ኢፍቱ እግሯ የቦሌ አየር መንገድ ተርሚናልን ከረገጠበት ጊዜ አንስቶ እሷና ልጆቿን የያዘው አውሮፕላን ከቦሌ አለምአቀፍ አየር ማረፊያ ተንደርድሮ እስኪነሳ ድረስ ውስጧ በፍርሀት የተሞላ ነበር፡፡የኢትዮጵያ መንግሥት ከባለቤቷ የኦሎምፒክ መድረክ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ 'ከጉዞው ያግደን ይሆን?' የሚለው መጥፎ መንፈስ በውስጧ ቢመላለስም አውሮፕላኑ ከመሬት ሲነሳ ፍርሀቷ ወዲያው ተገፎ በደስታ ብርሀን ተጥለቀለቀ፡፡ኢፍቱና ልጆቿን አበዝቶ ከናፈቃቸው ሰው ጋር የሚያገናኘው ረጅሙ ጉዞም ከአዲስ አበባ ወደ ጀርመኗ ፍራንክፈርት ከዛም ፈይሳ ወደሚገኝበት የአሜሪካዋ ሚያሚ ግዛት የተለጠጠ የሁለት ዙር በረራን የያዘ ነበር፡፡
የጀግና አቀባበል ትርክት እና ተቃርኖከሁለት አመታት በኋላ ፈይሳ በአለም አደባባይ ተቃውሞውን ያሰማበት መንግሥት ለውጥን ብለው አደባባይ በወጡ ወጣቶችና በዛው በመንግሥት ውስጥ ባሉ ለለውጥ በቋመጡ ሀይሎች ተፍረክርኮ አንፃራዊ የነፃነት አየር በሀገሪቱ መንፈስ ጀምሯል፡፡ከዚህ ጋር በተያያዘም ከሀገሩ ተገፍቶ በወጣበት እንዲቀር ተወስኖበት የነበረው አትሌት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን 'ወደሀገርህ ተመለስና፤ ሀገርህን አገልግል' የሚል የክብር ጥሪ መሰረት ባሳለፍነው እሁድ የጀግና አቀባበል ተደርጎለታል፡፡የፈይሳ ወደሀገሩ መመለስም በጉጉት እየጠበቁት የነበሩትን ወዳጅ ዘመዶቹን ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያን ሕዝብ ሊባል በሚችል መልኩ ብዙዎችን ያስደሰተ ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ መሀከል ግን አቀባበሉን የተመለከቱ አንዳንዶች 'በኦሎምፒክ መድረክ ላይ እጁን ስላጣመረ ብቻ እንዴት ጀግና ልንለው እንችላለን?' ሲሉ ሲሟገቱ ይሰማል፡፡ነገርግን የፈይሳን ውለታ አሳንሶ የመመልከት እና አትሌቱ ተቃውሞውን ካሰማበት ጊዜ አንስቶ 'በስፖርት ስፍራ የፖለቲካ አቋምን ማንፀባረቅ ተገቢ አይደለም' በማለት ሲሟገቱ የነበሩትን አካላት አስተያየት ትኩረት ሰጥተው የሚፈትሹ ሰዎች ሁኔታውን አምርረው ይቃወሙታል፡፡የፈይሳን ተግባር ደግፈው የሚቆሙት አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ከሆነም የፈይሳን ተግባር የማጣጣሉ ሂደት አትሌቱ በተቃውሞው የፈጠረውን መነቃቃት እና በዛ ምክንያት የደረሰበትን መከራና እንግልት በጥልቀት አለማወቅ ነው ብለው ይከራከራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፈይሳን ተግባር ትክክለኛነት ይበልጥ ለማስረገጥ የስፖርት ስፍራዎች የፖለቲካ አቋም ማስተናገጃ ስፍራ ባይሆኑም ፈይሳ ከግላዊ የፖለቲካ አቋሙ ይልቅ በመንግሥት ጭቆና ውስጥ የነበረውን ሰፊውን የሀገሩን ህዝብ ድምፅ ማሰማቱን በአመክንዮነት ሲያቀርቡ ይደመጣል፡፡ ከወር በፊት ወደሀገር ቤት በገቡ እንግዶች አቀባበል ምክንያት ከተከሰቱ አሳዛኝ ሁነቶች ጋር በተያያዘ ህዝቡን ያሳተፈ ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ነገሮች አስቸጋሪ ሆኑ እንጂ ፈይሳ የሚገባውን ያህል የጀግና አቀባበል አለማግኘቱን ጭምር የሚናገሩም አሉ፡፡ፈይሳ ያንን አይረሴ ተቃውሞ ባሳየበት ቅፅበት በማህበራዊ ሚዲያ የነበረው የሕዝቡን ስሜት ማስታወስ እንዲሁም ደግሞ የመንግሥትን መደናገጥና ሁነቱን ለማስተባበል ያደረገውን የፈሪ ሩጫ ላስተዋለ በተቃውሞ ስትናጥ ለነበረችው ሀገር የአትሌቱ ተግባር ምን ያህል ተፅዕኖ እንዳሳረፈ ይናገራል፡፡ሌሎቹን አመክንዮዎች ወደጎን ብለን ኹነቱ የተከሰተበት ስፍራ በአለም ዙሪያ እጅግ ብዙ ተከታታይ ባለው የኦሎምፒክ መድረክ ላይ መሆኑን ተቃውሞው በቀጥታ ስርጭት ከተላለፈ የሩጫ ውድድር አጋጣሚ ጋር ስንደምረው በራሱ የአትሌቱ ውለታ ትልቅ እንደሆነ በቂ ማስረጃ መሆኑ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡አትሌቱ በስደት በነበረበት ወቅት የብቸኝነት ህይወቱን እያስታመመ ከመቆዘም ይልቅ ባገኘው አጋጣሚ በሙሉ የኢትዮጵያን ህዝብ ብሶት ለአለም ይፋ ማድረጉን መቀጠሉም የፈይሳን ግዝፈት ይበልጥ የሚጨምር ነው፡፡ፈይሳ ከሪዮ ክስተት በኋላ እንኳን በአራት ውድድሮች ላይ እጁን እያጣመረ በሀገሩ መንግሥት ላይ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡ከዚህ በተጨማሪም ፈይሳ ለብዙ ጊዜያት በሽብርተኝነት ላይ አጋርነት የመፍጠር ፖሊሲን በመከተል የቀድሞውን አምባገነን መንግሥት ትረዳ የነበረችው አሜሪካ በኢትዮጵያ በሚደረጉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ ጫና እንድታሳድር ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡በዚህ ተባለ በዚያ ግን ተቃውሞውን በአደባባይ ያሰማበት የአገሩ መንግሥት በዚህ ፍጥነት ተቀይሮና የፖለቲካ ለውጥ መጥቶ ሀገሬ እገባለሁ ብሎ ያላሰበው ፈይሳ በተገፋበት ሀገሩ የመጣውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ ወደሀገሩ ተመልሶ ሀገሩን በድጋሚ ወክሎ ለመሮጥ የሚያስችለው ዋዜማ ላይ ይገኛል፡፡ ፈይሳ እግሩ አብዝቶ የሚወዳትን ሀገሩ በተረገጠበት ቅፅበት በሰጠው መግለጫ ከሁሉም ቀድሞ ህይወታቸውን ገብረው በክብር ወደሀገሩ እንዲመለስ ያስቻሉትን የሀገሩን ልጆች በእንባ ታጅቦ አስታውሷል፡፡
አዲሱ የዐቢይ አሕመድ አስተዳደርም የሰፊው ሕዝብ ውጤት መሆኑን ተረድቶ ለረጅም አመታት ሕዝቡን ያማረሩና ለተቃውሞ የገፉ አስተዳደራዊና መሰል ችግሮች ለመቅረፍ እንደሚሰራ ያለውን ግምት በተስፋ መንፈስ ውስጥ ሆኖ ሲናገር መደመጡ በብዙዎች ዘንድ በሳል አስተሳሰብ እንዳለው የሚሰጠውን አስተያየት ያጠናከረ ሆኗል፡፡በሌላ በኩል ግን ያለፉትን ዓመታት በአለም መድረክ የቀድሞውን ጨቋኝ መንግሥት ከመቃወሙ ጋር በተያያዘ ብዙዎች እንደ ፖለቲከኛ እየተመለከቱት መሆኑ ስህተት መሆኑን ለማመልከት "ፖለቲካ ወደእኔ መጣ እንጂ፤ እኔ አልሄድኩበትም" ሲል ተደምጧል፡፡ 