- መጠለያው በህንጻው ላይ ሸክም እንዳይሆንና ክብደቱ የህንጻውን ሰውነት እንዳያደቀው የመጠለያው መሰረት ከህንጻው ሰውነት እርቆ ከዉጭ እንዲተከል
- መጠለያው ጊዜአዊ ስለሆነ በቀላሉ የሚቀለበስ እና አገልግሎቱን ሲጨርስ ያለ ችግር መወገድ የሚችል እንዲሆን
- መጠለያው በጣም ቀላል ከሆነ እቃ እንዲሰራና በባለሞያ ክትትል እንዲደረግበት የሚያዝ ሲሆን
የባለስልጣኑ እንቆቅልሽ የሆነ ሚና ከአውሮፓ ህብረት በተገኘው ድጋፍ መሰረት የመጠለያ ስራው ከመጀመሩ በፊት ግን ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የሚባል መስሪያ ቤት በነጋሪት ጋዜጣ ቁጥር 209/1992 ተቋቋመ።መስሪያ ቤቱ የሚገርም ሰፊ ስልጣን ተሰጠው። በማስታዋቂያና ባህል ሚኒስትር ስር ሆኖ ግን የቅርስ ሃብትን በተመለከተ አድራጊ ፈጣሪ ሆኖተቋቋመ። የላሊበላ ህንጻ እድሳትም በቅርስ ጠበቃ ባለስልጣን እጅ ውስጥ ወደቀ:: እንግዲህ እዚህ ላይ ነው ከትውልድ ትውልድ ሊሻገር የሚችለው አሳዛኝ በደል የተፈጸመው። አውሮፓ ህብረት በጨረታው በአንደኛ ደረጃ ያለፈውን ፕሮቶጀክት ለማሰራት ገንዘብ ከመደበ በኋላ የጨረታው ውጤት ተቀልብሶ ደረጃው ዝቅተኛ የሆነ ብቻ ሳይሆን የቅዱስ ላሊበላን ውድ ህንጻ ከፍተኛ አደጋ ላይ የጣለ ፕሮጀክት እንዲሰራ ተወሰነ:: ከዚያም አሁን ያለው አደገኛ መጠለያ በይድረስ ይድረስ እንዲሰራ ሆነ።ይህ የተደረገበት ምክንያት አስገራሚ እንቆቅልሽ ነው። መጠለያው ከህንጻው መሰረት እርቆና በቀላሉ የሚነሳ ሁኖ ይሰራል የተባለበት ዋና ምክንያት ህንጻው ከፍተኛ ክብደት ያለው አካል መሸከም እንደማይችል ስለሚታወቅ ነበር። ከዚህ ቀደምም ከህንጻው ቅርብ ከሆነ ቦታ የሚኖሩት የቦታው ተወላጆች ቤታቸው እንዲፈርስእና ከአካባቢው ርቀው እንዲኖሩ፣ከባድ መኪናዎች ሲያልፉ ህንጻዉን እንዳያናጉት ጥንቃቄ እንዲደረግ እየተባለ የቆየው ህንጻው የግፊትና የክብደት ጫና እንዳያርፍበት ታስቦ ነው በማለት የአካባቢው ሰው ያምናል። የላሊበላ ህዝብ ህንጻውን ለማዳን ከጠቀመ ይሁን በማለት መስዋእትነት ከፍሏል። የእናንተ እዚህ መኖር ለመቅደሶቹ ደህንነት ጥሩ አይደለም ሲባሉ ከቤተክርስቲያኑ አካባቢ ለትውልደ-ትውልድ እያስተማሩና እየዘከሩ ይኖሩ የነበሩ አገልጋዮችን ጨምሮ በርካታ አባወራዎች ቤታቸውን አፍርሰው ቦታቸውን ለቀው ከሚወዱት ህንጻ ርቀው ሰፍረዋል። ቢያንስ ህንጻው ከተጠበቀ ትራንስፖርት ባይኖርም፣ ረጅም ሰዓት ቢፈጅባቸውም እየተመላለሱ ይሳለሙታል በሚል ነበር ይህ የሆነው። ሆኖም በዓለም አቀፍ መንግስታት እና በመንግስት የተሰሩት ሁሉም ፕሮጀክቶች ፍሬ ቢስ ሆነው መታየት ከጀመሩ በኋላ– ግዙፍ የሆነው ብረት ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ህንጻው ላይ ሲቀመጥ፣ እውነት ይህ ሁሉ ተግባር የተደረገው ፕሮጀችት ለመስራት ወይስ ህንጻውን ለማዳን ነዉ የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም።ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ የመጀመሪያው ዲዛይኑ ተቀይሮ አሁን ባለዉ አደገኛ መጠለያ እንዲተካ ተደርጎ ከተሰራ በኋላ ነበር እንግዲህ በላሊበላ ህንጻ ላይ ብረት የመሸከም ስቃይ፣ በህዝቡ እና በካህናቱ ላይ ደሞ የጭንቀት ስቃይ ለአስር አመታት የተጫነባቸው። ለአስር አመታት ይህ ሁሉ ሲሆን ተስፋ የተደረገው ጊዜአዊው መጠለያ ጊዜውን ሲጨርስ በላሊበላ ላይ ያመጣው በደል ኋላ በጥናት ላይ ተመስርቶ በሚተካው ዘለቄታዊ ስራ ይካሳል የሚል ነበር። ሆኖም መጠለያው ከተመደበለት ጊዜ በላይ እጥፍ እድሜ ቢያስቆጥርም ምንም አይነት የሚታወቅ ጥናትና ጥገና ሳይደረግለት እንደውም ክብደቱና ተሸፍኖ መቆየቱ በፈጠረው ችግር ለአዲስ አደጋ እንዲጋለጥ ሆኗል።በተለይበህንጻው ሰውነት ላይ ያረፈው ከባድ ብረት አደገኛነቱ በመንግስትም ታምኖበት መገለጽ ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሰወች በተለይም ካህናቱ በከፍተኛ ጭንቀት ተውጠው እያንዳንድዋን ቀን በስጋት ያሳልፍሉ።መጠለያው ከተሰራ በኋላ ባለሞያወች እንዲከታተሉት የፕሮቶጀክት እቅዱ ይገልጻል። ሆኖም ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን መጠለያውን በተመለከተ ምንም አይነት የባለሞያወች ምርመራና ክትትል ሳያደርግ አስር አመት ያህል ከቆየ በኋላ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በቀን 28 January 2014 በቁጥር 01/አ-02/019 ለዩኔስኮ ባቀረበው የመንግስት ሪፖርት ላይ ባለሞያወች መጠለያውን ለመገምገም ላሊበላ ላይ እንዳሉ ገልፆ ጽፏል። በሌላ በኩል የላሊበላ ካህናት እጅግ በርካታ የሆነ የአቤቱታ ደብዳቤና በአካል ልመናም ጭምር ለመንግስት እያቀረቡ መጠለያው ያደጋ ምልክት እያሳየ ነውና ይነሳልን በማለት ቢጠይቁምምላሽ ሳያገኙ ቆይተዋል። ቅርስን ለመንከባከብ በህግ የተቋቋመው መስሪያቤት ማንን እንደሚንከባከብም የብዙዎች እንቆቅልሽ ነው።አሁን ያለው መጠለያ ያስከተለው ችግርየአካባቢው ሰዎች የመጠለያው ያሰራር ሂደት በህንጻው ሰውነት ላይ ጉዳት አስከትሏል ይላሉ። ከዚህ ቀደም በቆርቆሮ ተሰርቶ የነበረው መጠለያ ሲፈርስ እና አዲሱ ሲሰራ በህንጻው ላይ አደጋዎች ደርሰዋል። ለምሳሌ መድሃኔአለም ላይ ብረት ወድቆ የመሰንጠቅ ጉዳት አድርሷል። አማኑኤልም የመፈርከስ ጉዳት በመስኮት ጉጥ ላይ ደርሧል:: እነዚህ በግልጽ የታዩ ጉዳቶች ሲሆኑ ሌሎች ህዝብ የማያውቃቸው ጉዳቶች እንደሚኖሩ የገመታል። በእነዚህ አደጋዎች ግን አሰሪው ካምፓኒም ይሁን ሌላ አካል ተጠያቂ አልሆነም:: እንደውም መጠለያው የተሰራው የአካባቢውን ህዝብ በማግለል በማሸማቀቅ እና መረጃ ባለመስጠት ጭምር ነው። ወቅቱ የመንግስትን ስራ መቃወም ይቅርና መጠየቅ አስቸጋሪ በሆነበት ጊዜ ስለነበር የሚሰራውን አይተው የተቆጡ ሰዎች “ሰራተኞቹ ሳይሰሩ ለቀሩበት ኪሳራ ትከፍላላችሁ” የሚል ማሰፈራሪያ ደርሶባቸዋል::የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ባለፈው አመት ለህዝብ እንዳሳወቁት መጠለያው መጀመሪያ የተሰራው ለአምስት አመታት እንዲያገለግል ነበር::
ሆኖም የመጠለያው ክብደት ህንጻው ላይ እስካሁን ከአስር አመታት በላይ እንዲቆይ ተደርጓል። ይህ አልበቃ ብሎ የመጠለያው እግሮች ስስ ከሆኑ ቦታዎች ላይ እንዲቆሙ ተደርጓል። ቤተማሪያም ላይ ያለው መጠለያ አንዱ እግር ያረፈው ከስላሴ ቅድስተ ቅዱሳን አናት ላይ ነው። አማኑኤል የመጠለያው ብረት አንድ እግር የቆመው የውስጥ ለውስጥ ዋሻ ካለበት ከጨለማው አናት ላይ ነው።ቤተሊባኖስ ሁለቱ የመጠለያው እግሮች ከህንጻው አናት እጅግ ቅርብ ላይ ተጭነዋል። ይህ ግዙፍ ክብደት ያለው ብረት ከአስር አመት በላይ ከህንጻው አካል ላይ በመቀመጡ ህንጻው ከአንድ ዓለት ተፈልፍሎ የተሰራ በመሆኑ በመሰረቱ ላይ የመናጋት: ውስጣዊ ድቀትና መሰንጠቅ አደጋ እንደሚያስከትል ባለሞያወች ይናገራሉ። በተለይም በስላሴ ቤተክርስቲያን እና በቤተ ማርያም ቤተክርስቲያን መካከል ሊፈርስ የተቃረበ ስስ ቦታ እንዳለ አንድ ኢንጅነር አስጠንቅቀዋል። ቤተ ሊባኖስ የመመንሸራተት አደጋ እንደተጋረጠበት: አማኑኤልም ኣጣዳፊ ድጋፍ እንደሚያፈልገው ዩኔስኮ አረጋግጧል። ይህ እየታወቀ ከህንጻው ላይ ከባባድ ብረቶች ያሉት መጠለያ መትከል ያስፈለገበት ምክንያት አሁንም እንቆቅልሽ ሆኖ ቀርቷል:: የመጠለያው ጥንካሬ የአካባቢውን ከፍተኛ የነፋስ ግፊት የማይቋቋም እንደሆነ በባለሞያዎች ይነገራል።ከፍተኛው የአካባቢው የነፋስ ግፊት ከ28-35 m/s ሲሆን መጠለያው ሊቋቋም የሚችለው እስከ 14 አካባቢ ቢሆን ነው ይላሉ።ይህ ማለት እስካሁን ድረስ ከፍተኛ ነፋስ ቢነፍስ ኖሮ ብረቱን ወደ ላይ አንስቶ ሊጥለውና ህንጻውን ሊጎዳው ይችል ነበር ማለት ነው።የመፍትሄው እንቆቅልሽብዙ ሰዎች ያለፈውን ችግር እንርሳው። አሁን የሚያስፈልገው በፍጥነት መጠለያውን ማንሳት ነው ይላሉ።እርግጥ ነው መጠለያው መነሳት አለበት። ግን ደግሞ መጠለያው ያመጣው መዘዝ እንዳለ ሊሰመርበት ይገባል። ለስምንት መቶ አመታት ያለመጠለያ የቆዩ ታምራዊ ቤተ መቅደሶች እነሆ ለአስር አመታት በላይ ከዝናብና ጸሃይ ተከልለው ቆይተዋል። በዚህም ሳቢያ በመጠለያ የተጋረደው የህንጻው አካል ካልተሸፈነው ጋር ሲነጻጸር ወደ መቅላት ተቀይሯል። ባጋጣሚ ከቦታው አግንቸ ያነጋገርኋቸው ባለሞያም የህንጻው አካል የሸክላነት ባህሪ ስላለው ባለበት ለመቀጠል ልክ በህይወት እንዳለ ሰው ሊተነፍስ ይገባል። ይህ ማለት በዝናብ ጊዜ ዘና ይልና ጸሃይ ሲሆን ደግሞ ሰብሰብ ይላል።ሆኖም ዝናብና ፀሃይ ሳያገኝ ብዙ ጊዜ ከቆየ በኋላ በድንገት ለዝናብና ፀሃይ የሚጋለጥ ከሆነ ተኮማትሮ የቆየው የህንጻው አካል ወደ መሰንጠቅ ሊያመራ ይችላል በማለት ያስረዳሉ።እንግዲህ ላሊበላ በሁለት አጣብቂኝ ላይ ወድቋል ማለት ነው። መጠለያው ባለበት ቢቀጥል ክብደቱ ወይም የነፋስ ሃይል ህንጻው ላይ አስከፊ አደጋ እንደሚያደርስ በእጅጉ የፈራል። መጠለያው ቢነሳና ህንጻው ለዝናብና ጸሃይ ቢጋለጥም የመሰንጠቅ አደጋ ያሰጋዋል ይባላል። በሁለቱም አቅጣጫ ግልጽ የሆነው ጉዳይ ግን ላሊበላ የጥገና ፕሮጀክቶች ጥገኛና ለባለሞያወች የማይነጥፍ የስራ ምንጭ እንዲሆን የመደረጉ ጉዳይ ነው። በተለይ ምንም አይነት ጥናት ሳይደረግ ገንዘብን ብቻ እንደመፍትሄ በመውሰድ የሚደረገው እሩጫ እስካሁን የፈሰሰው ብዙ ሚሊዮን ገንዘብ አደጋን እንጅ መፍትሄን እንዳላመጣ በማስታወስ መቃኘት አለበት:: የእስከዛሬው አሳዛኝ ተግባር ግልጽ ያደረገው ጉዳይ ቅርስ ጥበቃም ሆነ ዩኔስኮ፣ አውሮፓ ህብረትም ሆነ የጣሊያን ኩባንያ የላሊበላ ጉዳይ እንደ አንድ ስራ የሚታያቸው እንጅ እንደ ግል ጉዳይ የሚያንገበግባቸውና እንደመለኮት ቤት የሚያስፈራቸው የህልውና ጉዳያቸው እንዳልሆነ ነው። እንዳለ መታደል ሆኖ በውድ ቅርስ ላይ የሚፈጠር አደጋ ደሞ ለጥገና ድርጅቶች ከፍተኛ የስራና የገቢ ምንጭ ይፈጥራል። ለምሳሌ የቀድሞዋ የባህል ቱሪዝም ሃላፊ አደገኛውን መጠለያ ለማንሳት ሃያ ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብለው ነበር። በቅርቡ ደሞ የቅርስ ጥበቃ ሃላፊ ሶስት መቶ ሺህ ብር ያስፈልጋል ብለዋል። ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የጊዜአዊ መጠለያ የሰሩትን ኩባንያዎች የሰሩበትን የማፍረሻ ዲዛይን ተቀብሎ መጠለያው እንዴት እንደሚነሳ ዕቅድ እና ገንዘብ አዘጋጅቶ ስራ ቢጀምር ኖሮ ችግር አይኖርም ነበር። ዝርዝር ጥናት ሳይደረግ የገንዘቡ ስሌት በዚህ ፍጥነት ይህን ያህል ልዩነት ፈጥሮ እንዴት እንደመጣ ሌላ እንቆቅልሽ ነው። ይህ ሁሉ የሚያሳየው ላሊበላ አሳካሚና አስታማሚ እንደሌለው በሽተኛ እነዚህ ተቋማት ለራሳቸው ስራ እንዲመች የፈለጉትን እንዲያደርጉ የተተወላቸው ሃብት መሆኑን ነው። ይህ የሆነው ግን ላሊበላ ሰው ስለሌለው ሳይሆን የላሊበላ ሰው ሰውን ስላመነ ብቻ ነው።ስለላሊበላ ጥገና ሲናገሩ አንዳንድ አዋቂ ነን የሚሉ ሰዎች የሚያተኩሩበት ነጥብ የአካባቢው ሰው አያውቀዉም ብለው የሚያስቡትን ሳይንሳዊ እና ሞያዊ ሃሳብ በማጉላት እንጅ በተግባር ከሚሰራው ስራ ላይ በማተኮር አይደለም። በተግባር ምን ተሰራ የሚለውን ከመመርመር ይልቅ በወሬ ምን ታቀደ የሚለዉን ትኩረት አድርገው ያወራሉ። እነዚህ ሰዎች ሳይንሳዊ እውቀትን የተግባር መለኪያ ሳይሆን የወሬ ማደናገሪያ እያደረጉት ነው። ህዝቡ በተግባር የተሰራውን መሰረት ያደረገ መልስ ያስፈልገዋል።የቅዱስ ላሊበላ መቅደሶች የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሃብቶች ናቸው። ንጉስ ላሊበላ በዘመኑ በአሁኑ አከላለል በአማራ ብቻ ሳይሆን በትግራይ፣ በኦሮሚያና ሌሎም ቦታዎች የጥበብ አሻራውን ትቶ አልፏል።ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዚህ ብርቅ የመንፈሳዊና ታሪካዊ ውርስ ተወክሏል። ስለዚህ እየተሰራ ያለውን መጠየቅና መንግስትም ጉዳዩን አጣርቶ እርምጃ መውሰድ ይገባዋል። የችግሩ ምንጭ ታማኝ የሆነ ተቋም አለመኖር ነው። እውቀት የጥቅም አገልጋይ በሆነበት ባሁኑ ጊዜላሊበላን ላዋቂነን ባዮች ብቻ መተው ማለት ጊደርን በጅብ ማስጠበቅ ማለት ነው። በህንጻው ላይ ከዚህ በህዋላ የሚደረጉ ጥገናዎችን እና ተያያዥ ተግባራትን የሚከታተሉ የአካባቢዉ ተወላጆችና የሃይማኖት አባቶች ከመንግስት ነጻ የሆኑ ባለሞያዎች ሊሳተፉ ይገባል:: ሁሉም ህዝብ ጥበቃውንና ድጋፉን ከላሊባላ ማራቅ የለበትም:: 
