You can paste your entire post in here, and yes it can get really really long.
የሁለቱ ተፈራዎች ወግበፍጹም አላመነም! ሹመት ስጠብቅ ሽረት፤ ከፍታ ስጠብቅ ውርደት፤ አዲስ አበባ ኢሰፓ ጽ/ቤት ተደላድዬ እቀመጣለኹ ስትል ጅንካ የሚያሽቀነጥር አብዮታዊ ርምጃ ሲወሰድብህ ምን ትላለህ?... ጓድ ተፈራ እንዳለው የገጠመው ዱብ እዳ ይሄው ነው፡፡ ሀዋሳ ውስጥ በ1978 ዓ.ም መኃል ፒያሳ፤ አሞራ የመሰለ አዳራሽ ሲገነባ ከዓሳ አጥማጅ እስከ ጋሪ ነጂ፤ ከአረብ ነጋዴ እስከ እርሻ ልማት ሰራተኞች ድረስ ጮቤ አስረግጦ ነበር፡፡ ከምርቃቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ኮለኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ተገኙ፡፡ ከተማዋ በእግሯ ቆመች፡፡ የደርጉ ሊቀመንበር ማምሻውን የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎበኙ፡፡ የውኃ እጥረት የብዙዎችን ወገብ አጉብጧል፤ የመንገድ ችግር አያሌ ጨጓራዎችን ልጧል፤ የመድሃኒት መጥፋት የትየሌሌ ነፍስ ሰርቋል፡፡ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ በጽሞና ተመልክተው ወደመኝታቸው አመሩ፡፡ሲነጋ እየተብሰለሰሉ ሁለት ዓመት የፈጀውን፣ 1428 ስኩዩር ሜትር ላይ ያረፈውንና 1080 ሰዎችን የሚይዘውን አዳራሽ በድምቀት(?) መረቁ፡፡ በወቅቱ የአዳራሹ አሰሪና በአካባቢው የደርጉ ተወካይ ጓድ ተፈራ እንዳለው ደስታው ጣራ ደርሶ ነበር አሉ፡፡ ምን ያደርጋል በሚቀጥለው ቀን በደስታ ፊቱ ላይ ሀዘን የሚለጥፍ ደብዳቤ ቢሮው ድረስ ከተፍ አለለት፡፡ "... ሰው በመጠጥ ውኃና ጤና እጦት ተሰቃይቶ አዳራሽ የሚሉት ፈሊጥ ምንድን ነው? ህብረተሰባዊነት ማለትስ ለመሆኑ እንዲህ ነው? ...ከሚቀጥለው ሰኞ ጀምሮ በቅጣት ወደ ጅንካ ተዛውረኸል" የማይነበብ ፊርማ፡፡ ከኢሰፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት፡፡ (መረጃውን የተገኘው ከሁለተኛ ደረጃ ምንጭ በሰሚ ሰሚ ነው፡፡)ይህ ለሆነ አመታት ካለፉ በኋላ የኢህአዴግ ጉባኤ በዚሁ መዘዘኛ አዳራሽ ተካሂዶ ነበር፡፡ በጊዜው ሌላኛው አቶ ተፈራ ዋልዋ ከዘውግ ፖለቲካ ላጥ ብለው ወጥተው የሸገርና ድሬ ወጣቶች ሊግ በከተማቸው ይደራጁ ብለው ከች አሉ፡፡ ካድሬው ሁሉ ግራ ተጋብቶ ጥፍሩን መቁረጥ ጀመረ፡፡ ጥቂት የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ረጅሙን ማብራሪያ ሲሰጡ ደግሞ መብራት ጠፋ፡፡ዛሬ ላይ ሁለቱ ተፈራዎች የት እንዳሉ አላውቅም፡፡ አሻራቸው ግን በጉልህ ይታያል፡፡ ሀዋሳ ላይ 'ሲዳማ ባህል አዳራሽ' ተብሎ አሁንም አለ፡፡ የአዲስ አበባ እና ድሬደዋ ወጣቶችም በየከተማቸው ቅርጽ ተደራጅተዋል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ 11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ በሀዋሳ ይካሄዳል፡፡ በዚህ መድረክ የአመራር፣ የአሰላለፍና የሀሳብ ብቻ ሳይሆን የአዳራሽም ለውጥ አለ፡፡ ደኢህዴን ከአንድም ሁለት ትላልቅ አዳራሾችን ገንብቷል፡፡ ዘንድሮስ ማን ኮከብ ተጨዋች ሆኖ ይወጣል? ማን ጎል አግብቶ ይጨፍራል? እነ ማንስ ፋወል ሰርተው ቢጫ ያያሉ? እነ ማንስ አብዶ ይሰራሉ? እነ ማነስ ተመልካችን ይሳደቡ ይሆን? ማንስ ዘመን ተሸጋሪ ነጥብ ያስቆጥራል?ሀዋሳ ላንጋኖ ለሽርሽር ሄጄ...ባለፉት አራት ወራቶች ጠ/ሚ አብይ አህመድ (ዶ/ር) በይፋ አራት ግዜ ወደ ሀዋሳ መጥተዋል፡፡ በሌላ የክልል ከተማ እንዲህ ስለመመላለሳቸው እግዜር ይወቅ፡፡ ሀዋሳ የማይታይ 'ማግኔት' አላት፡፡ አንድ ግዜ እጇ ላይ አይጣልህ እንጂ የዐይን ፍቅር እንደያዘው ጎረምሳ ታመላልስኃለች፡፡ በሀይቁ ብታሳብብ፣ በአሞራ ገደሉ ብታላክክ፣ በዘንባባዎቹ ብታመካኝ ያው የከተማ ፎንቃ ገብቶለኸል ማለት ነው፡፡ የሰው ፈገግታ አደናቅፎኝ ነው ብትል፣ የዓሳ ሾርባ አታሎኝ ነው ብትል፣ የመንገድ ላይ አናናሱ ሸውዶኝ ነው ብትል ሰሚ የለህም፤ ያው የሀዋሳ ፍቅር ጨምዷኸል ማለት ነው፡፡ ለነገሩ አንተ ብቻ አይደለህም አርቲስቱ፣ ነጋዴው፣ ስራ ፈላጊው፣ ፖለቲከኛው፣ ተማሪው... ሁሉ ነጋ ጠባ ወደ ከተማዋ እንደጎረፈ ነው፡፡ከሁለት ዓመታት በፊት የአጼ ዩሐንስ የልጅ-ልጅ-ልጅ የሆኑት ራስ መንገሻ ስዩም ወደ ሀዋሳ በመጡበት ወቅት የዚህ ጦማር ጸሐፊ ከጎናቸው ተቀምጦ በጥያቄ ከትዝታቸው የተወሰነውን ቃርሟል፡፡በዚህ ጨዋታ ራስ መንገሻ በአምስት አመታቸው እናታቸውን እንዴት እንዳጡ፣ በሰባት ዓመት ደጅአዝማችነት እንዳገኙ እና ከአምቦ ወደ ሲዳማ ጠቅላይ ግዛት ሲዛወሩ የ’አዳሬ’ን(የሀዋሳ የቀድሞ ስም) እንዴት እንደተነደፈ ተናግረዋል፡፡ ራስ መነገሻ ይናገራሉ እኔ አዳምጣለሁ፡፡ "ዋና ከተማውን ከይርጋለም ወደ ሀዋሳ ያመጣንው የወቅቱን ሁኔታ ብቻ ሳይሆን መጪውን ጊዜ ገምተን ነው፡፡ በ1960 ዓ.ም. ጃንሆይን ጋበዝኳቸው፡፡ እዚሁ ታቦር ተራራ ላይ ወጣን፤ ንግስቲቱም አብረው ነበሩ፡፡ ቀዳማዊ ኃ/ስላሴም 'የላክንህ እንዲህ አይነት በጎ ስራ እንድታከናውን ነው፤ ቀጥልበት' ብለው አበረታቱኝ፡፡ እንግዲህ ከዚያ በኃላ ነው የባህርዳር ማስተር ፕላን፣ የአሰብ ነዳጅ ማጣርያ፣ የቦሌ አየር ማረፍያ እና ሌሎችንም የሰራነው"፡፡የሀዋሳን ትናንትና ለማወቅ፤ የሀዋሳን የዛሬ ቀለም ለማየት፤ የሀዋሳን የነገን ጣዕም ለማጣጣም ራስ መንገሻ ትክክለኛው ሰው፤ ታቦር ተራራ ደግሞ ትክክለኛው ቦታ ነው፡፡ አረንጓዴ መልክ፣ ቀላል ስሜት እና የትላልቅ ዋርካዎች ሽቶ ያውዳል፡፡ Deborah Stevenson እንዲህ ትላለች "The city on the hill is a symbol of wisdom and balance, of the good life, and of democratic politics".የኢህአዴግ ጉባኤም የዚሁ መዓዛ ሰለባ መሆኑ አይቀርም፡፡ ይህ ስብሰባ መቐሌ ወይም ጎንደር፤ ነቀምት ወይም አዋሽ ሰባት፤ አሶሳ ወይም ጅግጅጋ ቢካሄድ ድባቡ እና ውጤቱ የተለየ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዴት? እንዴት ማለት ጥሩ፡፡ በማኀበራዊ ሳይንስ የትምህርት መስኮች በተለይም በስነ-ሰብዕ (Anthropology) የአከባቢ ብይን እና የባህል ብይን (Environmental determinism and Cultural determinism) የተሰኙ ሁለት ህልዮቶች አሉ፡፡ ማህበራዊ ህይወታችን በተፈጥሮ (አካባቢ) ወይም በባህል ተጽዕኖ ውስጥ ነው፡፡ በምሳሌ ላስረዳ፤ አንድ በሰመራ የሚኖር ሰው ለከፍተኛ ሙቀት የተጋለጠ ነው፡፡ ይህ ክስተት በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አማካኝነት ሊመጣ ይችላል፡፡ በመሆኑም በአካባቢው ነዋሪዎች የአለባበስና አመጋገብ ባህል ላይ የራሱን አሻራ ያሳርፋል፡፡ ስስ የሆኑ ልብሶችን እንዲለብሱና ፈሳሽ የሆኑ ምግቦችን እንዲያዘወትሩ ያስገድዳል፡፡In traditional societies, the cultural system one is born into tends to be more influenced by the natural environment. In industrialized cultures, the environment tends to be much more socioeconomic, with class and income (access to resources) being the major environmental difference between individuals. (Dobzhansky, 1972)በሌላ በኩል ባህል በቀን ተቀን ህይወታችን ውስጥ ያለውን ውጣ ውረድ፤ ከሌሎች ጋር ያለንን ህብረት እና ግንኙነት በመሞረድ እና ቅርጽ በማስያዝ የራሱን ድርሻ ያበረክታል፡፡ በተጨማሪም ጆ. ኩበር እና ኢ. ቴይለርን የመሰለ የመስኩ ሊሂቃን ባህል የሰው ልጅ ምክኒያታዊ ፍጡር እንዲሆን ያስቻሉት ወይም ከሌሎች ፍጡራን ለመለየት ያበቁትን ሙሑራዊ፣ ስነ-ምግባራዊ፣ አካላዊ እና ቴክኒካዊ እውቀቶችን የሚያጠቃልል ጽንሰ-ሀሳብ ነው፡፡ ይብዛም ይነስም አንዳንድ ባህሎች ለልማት መፋጠን፤ ለእድገት መቀላጠፍ የራሳቸው አወንታዊ ሚና አላቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ ለልማት መጓተት የራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡ ባህል ከሰው ልጅ የእድገት ህልም ጋር ያለው ቁርኝት የጠበቀ ነው፡፡ ሁሉም የመለወጥ እና የመበልጸግ ሀሳቦች የሚፈጥሩት በሰው አዕምሮ ውስጥ ነውና፡፡ሀዋሳ ለሁለቱም ሀሳቦች የተጋለጠች ከተማ ነች፡፡ ሐይቅ፣ ፓርክ እና በአንጻራዊነት ምቹ የመሰረተ ልማቶች ባለቤት በመሆኗ የደስተኝነት እና የፈጠራ ስሜትን ትለግሳለች፡፡ በተጨማሪም የብዘሀ ቋንቋ፣ ሀይማኖት እና እሴት መነሀርያ ስለሆነች ለአዳዲስ ሀሳቦችና መፍትሄዎች በሯ ክፍት ነው፡፡ ከአመታት በፊት በዚችው ከተማ በተከናወነ የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ እጁን ጉንጩ ላይ ያልጫነ ካድሬ አልነበረም፡፡ አቶ ተፈራ ዋልዋ አዳራሹን የሚነቀንቅ ሀሳብ ይዘው ከተፍ አሉ፡፡ "የአዲስ አበባና ድሬድዋ ወጣቶች መደራጀት ያለባቸው በብሄራቸው ሳይሆን በከተማቸው ነው" አሉ ባለ ግራጫው ኮት ሰውዬ፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስተር አቀርቅረው በቢክ እስኪርቢቶ እየጻፉ ነው፡፡ በረከት ስምኦን 'ምን ሲደረግ' ብሎ አዲስ መከራከርያ ሀሳብ አመጣ፡፡ እነርሱም በብሄራቸው መደራጀት አለባቸው፤ ይህ የኢህአዴግ የቀድሞ ባህልና ወግ ነው፡፡ "ከዚህ የሊግ አደረጃጃት ሸርተት ማለት ለቀድሞ ስረዓት ናፋቂዎች መጫወቻ ሜዳ በነጻ እንደመልቀቅ ነው፡፡ የላይ አርማጭሆ አርሶ አደር አንዲት ድንቅ አባባል አላቸው ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል የምትል" (ተረቷ ለጨዋታ የተሰነቀረች ናት)፡፡ አዳራሹ በሳቅ አውካካ፡፡ ከብዙ ክርክር በኃላ ጓድ መለስ ውሳኔው በሚቀጥለው ጉባኤ እንደሚተላለፍና እስከዚያ በጉዳዩ ላይ ጥናት እንዲካሄድ አዘዘ፡፡እንደ ድሬደዋ፣ አዲስ አበባ ሀዋሳ እና መሰል Cosmopolitan ከተሞች ለዘውጌ ትርክት አቀንቃኞች አይመቹም፡፡ መሰረተ ልማት መስፋፋቱ፣ የእርስ በርስ ግንኙነት መቅለሉና የአዳዲስ ልምዶች ሽግግር መቀላጠፉ የጋራ እሴቶች አንዲበቅሉ ያስችላል፡፡ እንዲሁም ብቸኝነት የሚፈጥረውን ፍርሃት ለመሸሽ በሚደረግ ቀና-ፍትጊያ የጋራ ትወፊቶች ያብባሉ፡፡ በጊዜ ሂደትም የጋራ የሆኑ ትዝታዎች (Collective memories) ፍሬ ያፈራሉ፡፡ የተለያዩ ባህሎች ቀልጠው (Melting pot) የከተሜ ማንነት ያቆጠቁጣል፡፡ ስለሆነም በእንደነዚህ አይነት ውስብስብ ከተሞች የምታካሂደው ኮንሰርት በለው ኮንፈረንስ፤ ስብሰባ በለው ግምገማ የከተሞቹ ጥላ ያርፍበታል፤ የነዋሪዎቿ ትካሻ ይወድቅበታል፡፡ልዩው ድምጽቴዲ አፍሮ እንኳን ለክፍለ ሀገር ልጆች ለአዲስ አበቤዎችም ብርቅ ነው፡፡ በቀላሉ አይገኝም፤ በየካፌው አይታይም፤ በየኤፍ ኤ ሙ አይጣድም፡፡ ለሀዋሳ ግን እንግዳ አይደለም፤ በብዛት ይመጣል፡፡ የ'ፍቅር ቡና' ወሳኝ ደንበኛ ነው፤ ዋቢ ሸበሌ ቁጥር ሁለት ሆቴል ደግሞ ቤተኛ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ከጀርመን ድምጽ ሬድዩ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ስለ ሀዋሳ ሚስጢራዊ ድምጽ እንዲህ ብሏል፡፡ዶቼ ቨሌ- ስለ ፍቅር ሲባል ስለ ጸብ ካወራን በሚለው ሙዚቃህ ላይ የምትጀምረው በምን ቋንቋ ነው?ቴዲ አፍሮ- ይህን ሙዚቃ ስንሰራ ሀዋሳ ነበርን፡፡ የአካባቢው ኢነርጂ አለ፡፡ በስሜት የመጣ፤ የራሱ ትርጉም ያለውና ድንገት የሆነ ነገር ነውዶቼ ቨሌ- ሌላ ቋንቋ ነው?ቴዲ አፍሮ- አዎ! ስሜቱ ነው እዛጋ ያለው... አዲስ ቋንቋ ነው... እነዚህ ደግሞ በራሳቸው የተዋቡ ናቸው፡፡የባህል ብይን ይሉኸል እንዲህ ነው፡፡ ካንተ ቁጥጥር ውጭ በሆኑ እሴቶች ስር ትወድቃለህ፤ ካንተ በፊት በተቀመሩ ስሌቶች መኃል ትዋልላለህ፤ ሌሎች አካላት ባሰመሩልህ የትውፊት መንገድ ትጓዛለህ፡፡ ሀዋሳ እንዲህ አይነት የባህል ሀብት (Cultural capital) አላት፡፡ ለስራ የሚያነሳሱ፣ ለለውጥ የሚያጓጉ እና ለአዲስ ነገር የሚገፋፉ Symbolic capital (the look and feel of cities [which] reflect decisions about what – and who –should be visible and what should not, concepts of order and disorder, and on uses of aesthetic power’ (Zukin, 1995: 7) የቋጠረች ከተማ ናት፡፡ ስለሆነም ከመስከረም 23 እስከ 25 በሚካሄደው የኢህአዴግ ጉባኤ ከአዳራሹ ውጭ በሚነፍሰው ነፋስ፤ በሚለቀቀው ድብልቅ ዜማ እና በከተሜነት አዚም በመጠኑም ቢሆን ጣዕሙ፣ ሂደቱ እና ውጤቱ ሊለወጥ ይችላል፡፡ለምሳሌ: ጉባኤተኞቹ በሀዋሳ የምሽት ህይወት ተንፈስ ማለት ስለሚሹ ለአሰልቺና መንቻካ ስብሰባ እጅ አይሰጡም፡፡ አዳዲስ እና ወጣት አመራሮች ስለሚበዙ በጉባኤው ጠቃሚ እና ያልተደጋጋሙ ሀሳቦች ይነሳሉ፡፡ ሽማግሌዎቹ በጊዜና በቦታ ስለተከዱ ወንበሩ ይቆረቁራቸዋል፡፡ ከአዳራሹ ውጭ ያለው ብዘሀ ባህል ለዐቢይ ትረካ የማርያም በር ይሰጠዋል፡፡ አጅሬም ሀገረኛ ምሳሌ ያቀርባል፤ የተለያዩ ቋንቋዎችን ይጠቀማል፤ አስቂኝ አባባሎችን ያዘንባል፤ ታዳሚውን በቁልምጫ እየጠራ ልባቸውን ይሰርቃል፤ ኢትዮጵያ ማህጸነ ለምለም ስለመሆኗ እናንተ ምስክር ናችሁ እያለ ይሰብካል፡፡ ካድሬው ሁሉ 'አጃኢብ ነው' እያለ ያዳምጣል፡፡በዚህ ምክንያት በዐቢይ አህመድ አስተዳደር ተስፋ ላሳደሩ ሰዎች ሰርግና ምላሽ ሊሆን ይችላል፡፡ ኢህአዴግ ከቆረበበት የግራ ጥግ ወደ መኃል ይመጣ ይሆናል፤ ቅድምያ ለ'ሰው'ነት (ተለዋዋጩ የቡድን ማንነት ከዚህ በኃላ የሚመጣ ትርክት ነው) እና ከዚህ እውነትነት ለሚመነጨው ሀሳብ የሚቆረቆሩ ቦታ ያገኛል፤ በዘውግ ፖለቲካ የጎረመሱ ሆኖም ፈጣኑን ዓለም ተረድተው ኢትጵያዊነት ሁሉንም ማቀፍ እንደሚትችል የተረዱ ወጣቶች ወደ ፊት ብቅ ይላሉ፤ መሐል ሰፋሪዎቹ ነፋሱን ተከትለው ኳሷን ለጠሚው ያቀብላሉ፤ አብይ የመጨረሻዋን ጎል በመጨረሻ ሰዓት ያስቆጥራል፡፡ ይህ ካልሆነስ?ዳኤ ቡሹየሲዳማ ባህል አዳራሽ (Sidaamu Woga Hara) በ1999 ዓ.ም እድሳት ስለተደረገለት አሁን በአንጻራዊነት ምቹና ውብ ሆኗል፡፡ ቦታው ለኔና ለእኩዮቼ ብዙ የማይረሱ ትዝታዎች አሉት፡፡ እንዲህ የፓለቲካና መሰል ጉዳዮች ማስተናገጃ ከመሆኑ በፊት የህንድ ፊልም አይተንበታል፡፡ በMother India አልቅሰንበታል፡፡ በሸዋዚንገር ኮማንዶ ቡጢ ተሳቀናል፡፡ በቡርስሊ ካራቴ ተደንቀናል:: በቀበሌ ቲያትር ፈንድቀንበታል፡፡ የጊዜ ጉዳይ ሆነና ነገ ደግሞ የኢህአዴግን ጉባኤ በውስጡ ሳይሆን እንደኛ ከውጭ ይመለከታል፡፡እናም ሀዋሳና ነዋሪዎቿ እንግዶቻቸውን በሁለት የተለያዩ ስሜቶች ውስጥ ሆነው እየጠበቁ ነው፡፡ በተለይ ሰሞኑን በአንዳንድ መኖርያ ቤቶች ምልክት መደረጉ የተወሰነ ስጋት ፈጥሯል፡፡ በሌላ በኩል በሆቴልና መሰል ዘርፍ ለተሰማሩ ነጋዴዎች አጋጣሚው አሪፍ ገበያ ነው፡፡ እንደ ሀገር እኛ ኢትዮጵያውያንስ ምን እናተርፍ ይሆን? ለማንኛውም የፖለቲካው ዓለም መሪ ተዋንያኖቻችንን 'DAAE BUSHSHU!' ብለናል፡፡