ጳጉሜ 4 ፣ 2012

“ጠቅላይ ሚንስትሩ ክልላዊ ምርጫውን ቢያዳንቁትም ቢያብጠለጥሉትም ፋይዳ የለውም” ፕሮፌሰር መረሳ ፀሐዬ

NewsCurrent Affairs

ለጷግሜ 4 ቀን 2012 ዓ.ም ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የትግራይ ክልላዊ ምርጫ በተያዘለት ቀንና ሰዓት በትግራይ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ከተሞችና ገጠራማ…

“ጠቅላይ ሚንስትሩ ክልላዊ ምርጫውን ቢያዳንቁትም ቢያብጠለጥሉትም ፋይዳ የለውም” ፕሮፌሰር መረሳ ፀሐዬ
ለጷግሜ 4 ቀን 2012 ዓ.ም ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የትግራይ ክልላዊ ምርጫ በተያዘለት ቀንና ሰዓት በትግራይ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ከተሞችና ገጠራማ ስፍራዎች ቀኑን ጠብቆ በመካሄድ ላይ ይገኛል። በአገሪቱ ህገ መንግስት ከፀደቀበት ነሐሴ ወር 1987 ዓ.ም ጀምሮ ከገጠሙት ከባድ ፈተናዎች አንዱ የሆነው ይህ ክልላዊ ምርጫ ህገ መንግስቱን በበላይ ለመጠበቅ ስልጣን በተሰጣቸው የመንግስት አካላት እውቅናን ቢነፈግም በተያዘለት ወቅትና ሰዓት በመካሄድ ላይ ይገኛል። አዲስ ዘይቤ ዛሬ ረፋድ ላይ ያናገረቻቸው የትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽን ማዕካላዊ ኮሚቴ አባል ፕሮፌሰር መረሳ ፀሐዬ እንደገለፁት ከሆነ በክልሉ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ምርጫ ያለምንም የሰላም ችግር በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ አክለውም “ምርጫው መካሄድ ከጀመረበት ወቅት አንስቶ ከመቀሌ አንስቶ ወደ አድዋ እና አክሱም በመጓዝ በተለያዩ ከተሞችና  ገጠራማ ክፍሎች የሚገኙ የተለያዩ የምርጫ ጣብያዎችን ለመጎብኘት ችያለው። ህዝቡ ከ12 ሰዓት አንስቶ ወደ ምርጫ ጣብያዎች በመሄድ ተሰልፎ ድምፁን በመስጠት ላይ ይገኛል።” በማለት በትግራይ ክልል እየተደረገ ስለሚገኘው ምርጫና በምርጫው ዙሪያ ስላሉ ጉዳዮች ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።ክልላዊ ምርጫው የህጋዊነት ጥያቄን አንግቦ ሊደረግ አንድ ቀን ሲቀረው ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ሊጠናቀቅ ሁለት ቀናት በቀሩት 2012 ዓመት ዙሪያ ባደረጉት ቆይታ በምርጫው ዙሪያ ስለተላለፉት መልዕክት አዲስ ዘይቤ ፕሮፌሰር መረሳን በጠየቃቸው ወቅት “በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም የምናገረው ነገር የለም። ጠቅላይ ሚንስትሩ ክልላዊ ምርጫውን ቢያዳንቁትም ቢያብጠለጥሉትም ፋይዳ የለውም።” በማለት መልሰዋል። አክለውም የትግራይ ህዝብ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ነፃነት እንኳን በደም የተዋጋና መብቱንም የሚያስከብር ህዝብ እንደሆነ በመግልፅ በምርጫው ዙሪያ ዶ/ር አብይ በሚድያ በተላለፈ ቃለ መጠይቅ ስለተናገሩት ነገር ምላሽ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ በሶስቱም የኮርፖሬሽኑ የቴሌቪዥን ቻናሎችና የኤፍኤም ጣቢያዎች በትላንትናው እለት በተላለፈው ቃለ መጠይቅ ላይ  በፌደራል መንግስትና በ ትግራይ ክልል መካከል ስላለው ቁርሾና ስለምርጫው ተጠይቀው ሲመልሱ “እኛ ከትግራይ ክልል ጋር ያለንን ግንኙነት የምናየውና የምናስበው በትግራይ ከሚገኘው ህዝባችን አንፃር ነው።” በማለት የጀመሩ ሲሆን በመልሳቸው ላይ “ትግራይ ክልል ላይ የሚደረገው ምርጫ የጨረቃ ምርጫ ነው። የጨረቃ ምርጫ ደግሞ እንደጨረቃ ቤት ነው።” በማለት ምርጫው ህጋዊ እንዳልሆነ በግልፅ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ከ“ጨረቃ ቤት” በተጨማሪ እንደ “የቁራ ጩኸት”፣“የእድር ስብሰባ”ና “የእቁብ ስብሰባ” የመሳሰሉ ቃላትን በመጠቀም የምርጫው ህጋዊነት በቃለ መጠይቁ ላይ የተቃረኑ ሲሆን “ምርጫው ህጋዊ አይደለም። ምክንያቱም ህጋዊ ምርጫ የሚካሄደው በምርጫ ቦርድ ብቻ ነው” በማለት በክልሉ የሚካሄደው ምርጫ የፌደራል መንግስትም ሆነ የኢትዮጵያውያን ራስ ምታት ሊሆን አይገባም በማለት በምርጫው ዙሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል። ዶ/ር ዐቢይ “እኔ የምፈልገው ለትግራይ አንድ ጥይት ሳይሆን የኮሮና አፍ መሸፈኛ መላክ ነው” በማለት ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለኢትዮጵያውያን ጦርነት ያስፈልጋል ብለው እንደማያምኑ በቃለ መጠይቁ የገለፁ ቢሆንም በአንፃሩ “ብልፅናና ልማቱን  የሚያቆም አቅም ደግሞ ህውሓት የለውም” በማለት የትግራይ ምርጫም ሆነ ህውሓት የሚወስዷቸው እርምጃዎች ብዙም አስጨናቂ እንዳልሆኑ በቃለ መጠይቁ ተናግረው ነበረ።ምርጫው ከሚካሄድበት የዛሬው ቀን በአራት ቀናት ቀደም ብሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ ያነሳውን የህጋዊነት ጥያቄ ከዚህ ቀደም ባደረግነው ቆይታ እንደገለፅኩት ነው ያሉት ፕሮፌሰር መረሳ በተጨማሪም አዲስ ዘይቤ ፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ካነሳችው ነጥቦች አንዱ በሆነው የወልቃይት ጉዳይ ላይ ከአዲስ ዘይቤ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ለወልቃይት ተቆርቋሪ ነን የሚሉ  አካላት በመሬት ላይ ያለውን ነገር የተረዱት አይመስለኝም። እኔ እስከአሁን ተደውሎ የተነገረኝም በሌላ መልኩ የሰማሁትም የፀጥታ ችግር በአካባቢው ላይ የለም። ምርጫው በተያዘለት መልኩ በመካሄድ ላይ ይገኛል።” በማለት በአወዛጋቢው የወልቃይት ዞን ከምርጫው ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ችግር እንዳልተፈጠረ ተናግረዋል። የምርጫው ውጤት በመጪው አዲስ አመት መስከረም ሦስት እንደሚወጣ የገለፁት ፕሮፌሰር መረሳ “በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች  ምርጫው በመራዘሙ ምክንያት 38 የምርጫ ጣቢያዎችን ብቻ ስለሆነ የምንቆጥረው የምርጫው ውጤት ከተያዘለት ቀን ቀደም ብሎ ይፋ ሊሆን ይችላል” በማለት በምርጫው ውጤት ዙሪያ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። ይህም መስከረም ሦስትን ገና ካልተወሰነው የኢትዮጵያ ብሄራዊና ክልላዊ ምርጫ ከሚካሄድበት ቀን ባልተናነሰ የትግራይ ክልልን ከፌደራል መንግስት ጋር የሚፋጠጥባት ሌላ ቀን ያደርጋታል። ለ6ኛ ጊዜ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የትግራይ ክልላዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ከ2.7 ሚልዮን በላይ ህዝቦች እንደተመዘገቡ አዲስ ዘይቤ ከዚህ ቀደም የዘገበ ሲሆን ፕሮፌሰር መረሳ በክልሉ መንግስትና በክልሉ በሚገኙ ባለሃብቶች ድጋፍ የምርጫ ኮምሽኑ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚረዱ የተለያዩ ቁሳዉሶችን ወደ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች እንደላከ ገልፀዋል። 

አስተያየት