ሐምሌ 28 ፣ 2014

አወዛጋቢው የአዳማ የትራንስፖርት ታሪፍ እና የሹፌሮች ቅሬታ

City: AdamaEconomyCurrent Affairs

“ነዳጅ በሊትር 37 ብር ሲገባ የተጨመረ ታሪፍ አሁን ነዳጅ 42 ብር ሲገባ እንዴት ይቀንሳል?” ስትል ትጠይቃለች ሳራ አደም።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

 አወዛጋቢው የአዳማ የትራንስፖርት ታሪፍ እና የሹፌሮች ቅሬታ
Camera Icon

ፎቶ፤ በተስፋልደት ብዙወርቅ (አዲስ ዘይቤ)

ከሰሞኑ በአዳማ ከተማ የተከሰተውን የትራንስፖርት መስተጓጎል እና የተሽከርካሪዎችን እስር መዘገባችን ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ ከቀናት በኋላ የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች የታሪፍ ቅናሽ መደረጉን ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል።  የአዲስ ዘይቤ የአዳማ ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ ማጣራት አካሂዶ እንደሚከተለው ዘግቦታል።

ከዚህ ቀደም በአዳማ ለመጨረሻ ጊዜ የታሪፍ ማስተካከያ የተደረገው የሚያዚያ 30 የተደረገውን የነዳጅ ዋጋ ክለሳን መሠረት በማድረግ በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። በወቅቱ የተሰራው የታሪፍ ዝርዝር አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎችን በሚኒባስ እና ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች "ባጃጆች"፣ የከተማዋን የአስፓልት እና በኮብል መንገዶች ደረጃ መሰረት አድርጎል። የመንገዶችም ርቀት በአራት ምድቦች ውስጥ ያስቀምጣል። 

ለሚኒባስ ታክሲዎች በታሪፍ አከፋፈል ከመነሻ እስከ 2.5 ኪሜ በ 3 ብር ከ20 ሳንቲም፣ ከ2.6 ኪሜ እስከ 5 ኪሜ በ6 ብር ከ45 ሳንቲም፣ ከ5.1 ኪሜ እስከ 7.5 ኪሜ በ9 ብር ከ 65 ሳንቲም  እና ከ7.5 እስከ 10 ኪሜ በ12 ብር ከ90 ሳንቲም ነበር። ይህም በአማካኝ በ 1 ኪሎ ሜትር 1 ብር ከ 28 ሳንቲም የሚያስከፍል ነበር።

“ከዚህ ቀደም የተሰራው ታሪፍ የወጣው ቤንዚን በሊትር 37 ብር መግባቱን ተከትሎ ነበር” የምትለው ሳራ አደም አሁን ቤንዚን በድጎማ 42 ብር መሆኑን ትናገራለች። አስታያየቷን በመቀጥልም “ነዳጅ በሊትር 37 ብር ሲገባ የተጨመረ ታሪፍ አሁን ነዳጅ 42 ብር ሲገባ እንዴት ይቀንሳል?” ስትል ትጠይቃለች።

የግንቦቱ ታሪፍ ባለበት ቢቆይ ከስራው ጋር የሚያዋጣን እሱ ነው የምትለው ሳራ “አዲሱ ታሪፍ ተፈጻሚ መሆን የለበትም። ከታሪፍ ውጪ  የሚያስከፍሉ ደግሞ ኃላፊነቱ የመንገድ ትራንስፖርት ስለሆነ እርሱ ላይ ቁጥጥር ያድርግ” ስትል ሀሳቧን ትገልጻለች። የታሪፍ ማስተካከያው ነዳጅን ብቻ ሳይሆን የመኪና መለዋወጫዎችንም ታሳቢ ሊያደርግ ይገባው እንደነበር ሃሳቧን ገልጻለች።

አቶ አህመድ መሐመድ የንብ የታክሲ ባለንብረቶች ማህበር ሊቀመንበር ነው። በአሽከርካሪነት እና በታክሲ ስራ ዘርፍ ከ30 ዓመት በላይ መስራቱን ይናገራል። በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ ይህንን መሠል የታሪፍ አወጣጥ አይቶ እንደማያውቅ ይናገራል።

የትራንስፖርት ታሪፍ ማስተካከያው የተደረገው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ እንደሆነ የሚናገረው አህመድ “መንግስት የነዳጅ ድጎማ አድርጎልን የበቃ ስላልመሠለው ነው የታሪፍ ጭማሪ ያደረገልን” ይላል።

“ታክሲ አገልግሎት እንደሀገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች ወጥ ጉዞ አይደለም የሚያደርገው። በዚህም ምክንያት በየኪሎ ሜትሩ መነሻ አለው” የሚለው አህመድ፤ በአሁን ወቅት በተሰራው የትራንስፓርት ታሪፍ ማሻሻያ በፊት የነበረው የጉዞ መነሻ ቀመር አሰራርን መቅረቱን ይናገራል።

ለምሳሌ በግንቦት ወር የተሻሻለውን የታሪፍ ዋጋ ያነሳው አህመድ በወቅቱ በነበረው ቀመር መነሻው እስከ 2.5 ኪሜ ርቀት ያላቸው ጉዞዎች 3 ብር ከ20 እንዲሁም ለባጃጅ 3 ብር ከ50 እንደነበር፤ ይህም በኪሎ ሜትር 1 ብር ከ28 ሳንቲም እንደነበር ያስረዳል። አሁን ደግሞ ጭማሪውን ተከትሎ መንግስት ይህንን ታሳቢ በማድረግ በኪሎ ሜትር 1 ብር ከ36 ሳንቲም እንዳደረገ ይገልጻል።

አህመድ መሃመድ የደረሰኝ መረጃ ብሎ እንዳካፈለን “አሁን የተደረገው ጭማሪ 7.5 በመቶ ድረስ ነው ብሎናል።  መንግስት ያደረገው ጭማሪ 25 በመቶ ሲሆን ከዚህ ላይ 10 በመቶ በነዳጅ በድጎማ ተካክሶ ቀሪውን 15 በመቶ ደግሞ ለአሽከርካሪ እና ተሳፋሪ ለሁለት ሲካፈሉት የእያንዳንዳቸው ድርሻ 7.5 በመቶ ይሆናል። 

“ሁሉም እንደ አንድ ኪሎ ሜትር ነው የተወሰደው” የሚለው አህመድ “አንድ ሰው አንድ ኪሜ ሄዶ በ1 ብር ከ36 ሳንቲም ይከፍላል። ይሄ ለአሰራርም አይመችም” በማለት አዲሱ የትራንስፖርት ታሪፍ  የቀድሞ ቀመር ማስቀረት ያልተቀበለበትን ምክንያት ይገልጻል።

“ከኦዳ አባ ገዳ በተለምዶ ዋርካ እስከ ቦሌ ኮብል ጫፍ ድረስ 5 ነጥብ 1 ኪሜ ነው።  በቀድሞው ታሪፍ 9ብር ከ65 ሳንቲም ነበር” የሚለው አህመድ በአሁኑ ታሪፍ ግን 6 ብር ከ45 ሳንቲም መሆኑን በመናገር “ጨመረልን ነው፤ ቀነሰብን ነው የምንለው?” ሲል ይጠይቃል። “በየመሀሉ ብዙ የማይሰጡን ታሪፎች አሉ” የሚለው አህመድ “ግንቦት ላይ የተሰጠን ታሪፍ  በፊት ተሰጥቶን በድጋሚ ተሰብስቦብን የተሰጠን  ነው" ሲል ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።

ፎቶ፤ በተስፋልደት ብዙወርቅ (አዲስ ዘይቤ)

በአዳማ ከተማ ከፍተኛ የሆነ የትራንስፖርት ታሪፍ አክብሮ ያለመስራት ይታያል። በቀድሞ አሰራር መሠረት ከመነሻ እስከ 2.5 ኪሜ ድረስ የተጓዘ ሰው 3 ብር ከ20 ሳንቲም ይከፍል ነበር። ለአብነት ያህል እንኳን በተለምዶ መብራት ኃይል እስከ ፖስታ ቤት ደራርቱ አደባባይ ርቀቱ ከ1 ኪሜ ባይበልጥም የሚኒባስ ታክሲም ሆነ የባለሦስት እግር አሽከርካሪዎች 5 ብርን በራሳቸው እንደታሪፍ ደንግገው ይጠቀማሉ። መልስ ለሚጠይቅ ሰው ከትችት እስከ ስድብ ከፍ ሲልም አምባጓሮ መፈጠር ለአዳማ ታክሲ ተጠቃሚ የሁልጊዜ ትዕይንት ነው።

ወጣት ዮሴፍ የአዳማ ኗሪ ነው። የአዳማ የከተማ ታክሲ አገልግሎት ብዙ ችግሮች አሉበት የሚለው ዮሴፍ “ከታሪፍ በላይ እጥፍ ማስከፈል፣ ረዳቶች መልስ ሲጠየቁ ላለመመለስ 'ሳንቲም የለንም' ወዘተ ምላሽ መስጠት እየተለመደ ነው” ሲል ይገልጻል።

ሌላዋ ያነጋገርናት የአዳማ ኗሪ ሰናይት መኖሪያዋ አዳማ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ሲሆን የስራ ቦታዋ ዋርካ ሰፈር ነው። “የታሪፍ ለውጥ መኖሩን ሰምቻለሁ ግን 10 ብር ከፍዬ ነው ወደ ስራ የምገባው" ትላለች። በአዳማ የታክሲ አገልግሎት ላይ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል የተለመደ ነው የምትለው ሰናይት “የሚያስፈጽም አካል ባለመኖሩ ረዳቶችም እንደመብታቸው ነው የሚቆጥሩት። መልስ መጠየቅህን እንደነውር ነው የሚያዩት” ትላለች።

ትርፍ መጫን ሌላው በአዳማ ታክሲ አገልግሎት ላይ የታዘበችው ህገወጥ ተግባር መሆኑን ሰናይት ገልጻለች። ከስምሪት መስመር ውጪ መሄድ እና መንገድ ሲዘጋ አማራጭ መንገድ አለመጠቀም እንዲሁም ተሳፊፋሪን ማንገላታት እንደሚገጥማት ለአዲስ ዘይቤ ትናገራለች።

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የታክሲ አሽከርካሪ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለጹት “መንግስት አስር በመቶ ድጎማዎች ያደርጋል ነገር ግን የታክሲ አሽከርካሪውም ድርሻ 2 በመቶ አለበት ዋጋ አለውና ይህም መጠቀስ አለበት” ይላሉ። መንግስት ይህንን ልፋታቸውን አልረሳውም የሚሉት አስተያየት ሰጪው በከተማው የሚያስፈጽመው አካል ላይ ግን በአሰራሩ ላይ ቅሬታ እንዳላቸው ይናገራሉ። ይህም “መነሻችን የነበረውን የቀመር አሰራር አንስቶ የትራንስፖርት ታሪፋችን እንዲቀንስ አድርጓል” ይላሉ።

መንግስት በሰጠው የነዳጅ ድጎማ መሠረት አንድ ተሽከርካሪ ከ7 እስከ 25 ሊትር ድረስ ድጎማ ያገኛል ይላሉ አሽከሪካሪዎች። አንድ ታክሲ በቀን ከ20 እስከ 25 ሊትር ይጠቀማል። እንደ ታክሲው እድሜ እና የሞተር ሁኔታ በሊትር ከ5 እስከ 8 ኪሜ ይጓዛል ሲሉም ይገልጻሉ። 

አንድ ታክሲ በቀን ውስጥ ከጎማ ፍተሻ፣ የተራ አስከባሪ ክፍያ፣ የሹፌር እና የረዳትን አበል፣ የባለንብረት ገቢና የነዳጅ ክፍያ ውጪ በየእለቱ 1 ሺህ 4 መቶ ብር ውጪ አለበት ይላሉ አሽከርካሪዎች። የነዳጅ ዋጋ ሲጨመር እስከ 1 ሺህ ብር ድረስ ይሆናል ይላሉ። እንደ አስተያየት ሰጪያች ገለጻ አንድ ታክሲ ያለብልሽት እና ያለተጨማሪ ወጪ ሰርቶ ለመግባት ከ2 ሺህ 4 መቶ ያወጣል ይላሉ። 

በድጎማው መሰረት ከተሰላ አንድ ታክሲ በቀን 25 ሊትር ነዳጅ አግኝቶ ቢሰራ፤ በአማካኝ  በሊትር በ6 ኪሜ ቢጓዝናም 11 ሰው የሚጭን ሚኒባስ ታክሲ ገቢው 2244 ይሆናል ይላሉ። ይህም ከወጪው ጋር እስከ 100ብር ልዩነት እንዳለው ይገልጻሉ።

ከተሳፋሪ ለሚነሳው ቅሬታ ምላሽ የጠየቅነው አህመድ መሐመድ እንደሚለው “ሁሌም ታሪፍ ስንሰጥ ለባለቤቶቹ በታሪፉ እንዲሰሩ አስፈርመን ነው” ይለል። አክሎም “በተሰጠን ታሪፍ ላይ ባለመስማማታችን

ለአዳማ መንገድ ትራንስፖርት ኤጀንሲ ሶስት የሚኒባስ ታክሲ ማህበራት ሆነን ቅሬታ አስገብተን እየጠበቅን ነበር” የሚለው አህመድ የህግ ጥሰት ያለባቸው አሽከርካሪዎች ላይ አርብ እለት የተጀመረው ቁጥጥር ወደ ታሪፍ ጥያቄና የመንጃ ፍቃድ መቀበል በመግባቱ ውዥንብር መፈጠሩን ይናገራል። 

“ለቅሬታው መልስ እየጠበቅን አሽከርካሪዎቻችን ታሪፍ ራሱ እየተጠየቁ ነበር” የሚለው አህመድ “ጎዳዩ 'ታክሲ ማህበራት አድማ አደረጉ' እስከመባል ደርሶ ነበር” የሚለው አህመድ ማህበራቱም ሆነ ታክሲዎች ይህንን እንዳላደረጉ ይስረዳል።

“የእኛ ጥያቄ የታሪፍ አሰራሩ ወደ ቀድሞ የመነሻ ቀመር አሰራር ይመለስልን የሚል ነው። የኪሎ ሜትሩ አሰራር እኛ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል” ሲል የንብ ታክሲ ባለንብረቶች ማህበር ሊቀመንበሩ አህመድ መሐመድ ሀሳቡ አጋርቶናል።

የነዳጅ ድጎማው ብዙ ሊስተካከሉ የሚገቡ ነገሮች አሉት የሚለው አህመድ “ግማሹ የታክሲ አሽከርካሪዎች ያለድጎማ ነው የሚሰሩ ነው። የድጎማው ተጠቃሚ የሆነ አሽከርካሪም አንድ ቀን በድጎማ አንድ ቀን ደግሞ ያለ ድጎማ ነው የሚንቀሳቀሱት” የሚለው አህመድ የአቅርቦት ችግሩ ይህንን እንዳመጣ ይናገራል። 

የአዳማ መንገድ ትራንስፖርትን ኤጀንሲ በመወከል የከተማ ትራንስፖርት ዘርፍ ባልደረባ ከሆኑት ከአቶ ቱሉ መሀመድ ጋር የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ቆይታ አድርጓል። “ከነዳጅ ዋጋ ጋር በተገናኘ የትራንስፖርት ታሪፍ ማሻሻያ ተደርጓል” የሚሉት አቶ ቱሉ መሀመድ “መንግስት በነዳጅ ዋጋ ላይ ድጎማ በማድረጉ ለተሳፋሪውም ነዳጁ እንዲቀንስ አድርጓል” ይላሉ። ይህንንም ሲያስረዱ “በ1 ኪሜ ለሚኒባስ ታክሲ 1 ብር ከ36 ሳንቲም ሆኗል” ብለዋል። 

አዲሱ ታሪፍ ምን አዲስ ነገር አለው ? ያልናቸው አቶ ቱሉ መሀመድ ቀድሞ የነበረውን ቀመር ማስቀረቱን ከበፊቱም ታሪፍ ዋጋው ከ1 ብር እስከ 1 ብር ከ50 ሳንቲም ቅናሽ አለው ሲሉ ተግረውናል።

ከአሽከርካሪዎች የቀረበውን ቅሬታ አንስተን የጠየቅናቸው አቶ ቱሉ ሙሀመድ ሲመልሱ “ከአሽከርካሪዎች ጋር መወያየታቸውን እና አሽከርካሪዎች በቴሌ ብር ላይ ቅሬታ አቅርበዋል። መንግስት ለታክሲዎቾ የነዳጅ ድጎማ ካደረገ እነርሱ ደግሞ ህዝቡን ሲያስከፍሉት የነበረው ከፍተኛ ታሪፍ እንዲቀንሱ በሚል ነው።" ሲሉ የትራንስፖርት ኤጀንሲው ባልደረባ ስለተወሰደው ማስተካከያ ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል።

አዲስ ዘይቤ ከምንጮቿ እንዳገኘችው መረጃ የኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ኤጀንሲ የወጣው የትራንስፖርት ታሪፍ በርቀት የተከፋፋለ ቀመር ያለው ሲሆን በታክሲ አገልግሎት ዘርፍ ከመነሻ እስከ 30 ኪሜ ያሉ ርቀቶችን የዋጋ ዝርዝር ይገልጻል። ታሪፉ በውስጡ ከዘረዘራቸው ነገሮች ውስጥ ከመነሻ እስከ 2.5 ኪሜ ከ3 ብር ከ20 እስከ 3 ብር ከ80 ሳንቲም ታሪፍ ማውጣቱን ማረጋገጥ ችላለች።

ከአዳማ ከተማ መንገድ ትራንስፖርት ኤጀንሲ የተገኘውን መረጃ እንደሚያሳየው 11,810 ተሽከርካሪዎች የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚዎች ናቸው። ከዚህ በመነሳት ይህ የአገልግሎት ዘርፍ 11,810 አሽከርካሪዎችን፣ ረዳቶቻቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን በቀጥታ የስራና የኑሮ መሰረት በመሆኑ ተኩረት ሊሰጠው ይገባል። 

አስተያየት