ሰኔ 11 ፣ 2012

የአምባሳደር ፓርክ የእድሳት ስራ ተጠናቀቀ

ቃለመጠይቆችNewsCurrent Affairsወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

በአራዳ ክፍለ ከተማ ራስ ዳምጠው ጎዳና ላይ የሚገኘው የአምባሳደር ፓርክ እድሳት መጠናቀቁን መልከዐ ምድር ንድፉን እና እድሳቱን የሰራው ዛና ላንድስኬፒንግ…

የአምባሳደር ፓርክ የእድሳት ስራ ተጠናቀቀ
በአራዳ ክፍለ ከተማ ራስ ዳምጠው ጎዳና ላይ የሚገኘው የአምባሳደር ፓርክ እድሳት መጠናቀቁን መልከዐ ምድር ንድፉን እና እድሳቱን የሰራው ዛና ላንድስኬፒንግ ኃላ.የተ.የግል ማኅበር አስታወቀ። ድርጅት በትላንትናው ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ እንዳስታወቀው በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም በ42 ሚልዮን ብር አጠቃላይ በጀት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወንዝ ዳርቻና የአረንጓዴ አካባቢዎች ኤጀንሲ ባለቤትነት የተጀመረው የአምባሳደር ፓርክ የእድሳት ፕርጀክት ይፈጸማል ተብሎ ከነበረው ጊዜ በጥቂቱ ቢዘገይም ፤ በስኬት ተጠናቋል ሲል አስረድቷል፡፡ ወደ አስር ሺ  ካሬ ሜትር የሚጠጋ መሬት ላይ ያረፈው አምባሳደር ፓርክ የሚገኝበት አካባቢ ለብዙኃኑ ተስማሚ ከመሆኑ በተጨማሪ ፤ በወቅቱ አበባ ከተማ አስተዳደር የወንዝ ዳርቻና የአረንጓዴ አካባቢዎች ኤጀንሲ ስር እየተሰራ ከሚገኘው የከተማ ማስዋብ ስራ አካል ስለመሆኑ በፕሮጀክቱ ጅማሬ ወቅት ተገልጾ እንደነበር ይታወሳል። የአምባሳደር ፓርክ በከተማችን ከሚገኙት አስራ አምስት ዋና ዋና ፓርኮች መካከል አንዱ ሲሆን የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ከአንድነት እንዲሁም ከእንጦጦ ፓርኮች ቀጥሎ ስራው የተጠናቀቀ ሶስተኛው ፓርክም ያደርገዋል። የፓርኩ የእድሳት ስራ በኮንስትራክሽን ስራ ዘርፍ በተሰማራው ናሄድ ቢዝነስ ሃ/የግ/ማ እና በዛና ላንድስኬፒንግን ሃ/የግ/ማ የተከናወነ መሆኑንም ባደረግነው ማጣራት ለመረዳት ችለናል።አዲስ ዘይቤ ዛና ላንድስኬፒንግን ከመሰረቱት አባላት አንዱ ከሆኑት አቶ ሙሉቀን ነጋ ጋር ባደረገችው ቆይታ መረዳት እንደቻለችው ፕሮጀክቱ በከፊሉ ቢዘገይም ከሞላ ጎደል በተመደበለት በጀት እና ወቅት ተጠናቋል። ፕሮጀክቱ በአንፃራዊነት ከሌሎች የፓርክ እድሳት ስራዎች በተሻለ ቴክኒካዊ ጥራት ስለመጠናቀቁም ይናገራሉ። ለዚህም እንደ ምክንያትነት ኤጀንሲው ተገቢውን ትብብር በወቅቱ ማደረጉን እንዲሁም ከዚህ ቀደም እንደተለመደው ለኮንስትራክሽን ድርጅቶች ብቻ ሳይሆን በመልክዐ ምድር ንድፍ ሙያ ቴክኒካዊ እውቀትና ልምድ ያለውን ድርጅት ማሳተፉን እንደ ምክንያትነት አቅርበዋል። በተጨማሪም ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ የእድሳቱ ፕሮጀክት ንድፍ የሰራው ባለሙያ በአማካሪነት በኤጀንሲው ውስጥ መቀጠሉ ፕሮጀክቱን ከዚህ ቀደም በስራ ዘርፉ ከሚስተዋለው የጊዜና የሀብት ብክነት መታደጉን ገልፀዋል። ፓርኩ በውስጡ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል መፅሕፍት ቤት፣ ካፌዎችና የህፃናት መዘናኛዎች ይገኙበታል። ፕሮጀክቱ መጠናቀቁን ተከትሎ የዋጋ ትመናንና የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ድርጅቶችን የማወዳደር ስራ ቀጣዩ የኤጀንሲው ቀጣይ ተግባር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም የአምባሳደር አካባቢ አዲስ ድምቀት ይሆናል ተብሎ ሚጠበቀው ፓርክ በኮሮና ቫይረስ አማካኝነት ከተገደቡት መብቶችና ድርጊቶች አንጻር ቫይረሱ በቁጥጥር ስር ከመዋሉ በፊት ለህዝብ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም። ሆኖም ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት እንደሚሆን የጎላ ግምት ተሰጥቷል።

አስተያየት