ጥር 22 ፣ 2011

በድሬዳዋ የተነሳን ተቃውሞ ተከትሎ ነዋሪዎች እየታሰሩ መሆናቸው ተነገረ

Politics

በድሬዳዋ የተነሳን ተቃውሞ ተከትሎ ነዋሪዎች እየታሰሩ መሆናቸው ተነገረ

በድሬዳዋ ከተማ የተነሳው አለመረጋጋት ቀጥሏል፡፡ በርካታ ወጣቶች መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ በመጠየቃቸው ምክንያት ከየቤታቸው እየታፈሱ ለእስር ተዳርገዋል ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡

ጥር 13፣2011 ዓ.ም የእግዚአብሔርአብ ታቦት አስገብተው ሲመለሱ የነበሩ ምእመናን ላይ ድንጋይ በመወርወር የተነሳው አለመረጋጋት ቅርጹን ቀይሮ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ መጓደል ጥያቄዎች እንዲሁም የታሰሩ ወጣቶች ይለቀቁ በሚል አለመረጋጋቱ ቀጥሏል፡፡ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ እና ሐሙስ የከተማው ከንቲባ ህዝቡን ያናግራሉ ቢባልም ኃላፊው ፖሊስ ሜዳ (አሸዋ) የተባለው ስፍራ ባለመምጣታቸው አመፁ እንዲባባስ መንስኤ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

ለችግሩ መቀስቀስ ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን 84 ተጠርጣሪዎች ፖሊስ በቁጥጥር ስር ቢያውልም በአንጻሩ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡትን ጨምሮ እያፈሰ እንደሚገኝ ከአካባቢው የሚወጡት መረጃዎች ይገልጻሉ፡፤፡

የድሬዳዋ ነዋሪ ጌትነት ታደሰ የተነሳውን ረብሻ ሃይማኖታዊ መነሻ ምክንያት ይኑረው እንጂ ለረጅም ጊዜ ሲንከባለል የቆየው "ድሬዳዋ የሁላችንም ነች" የሚለው የህዝብ ጥያቄ ገንፍሎ የወጣበት መሆኑን ገልጸው፤ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ሁኔታውን ለማረጋጋት ጠንካራ ስራ እየሰሩ እንደሆነም አያይዞ ጠቁሟል፡፡

ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ የድሬዳዋ ነዋሪና የህግ ባለሞያም “የተነሳው ተቃውሞ ዘርፈ-ብዙ ነው፡፡  ከነዚህም መካከል የኃላፊዎች ቸልተኝነት ዋነኛው ጉዳይ ነው፡፡” ሲያብራሩም “የተጠራቀመ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ከሌሎች ክልሎች በተለየ ድሬዳዋ ላይ ለውጥ አለመታየቱ እና የ40-40-20 የፖለቲካ ቀመር ዋነኛ መንስኤ ናቸው፡፡” ይላሉ፡፡

40-40-20 ቀመር ማለት ከተማውን የማስተዳደር ድርሻ አርባ በመቶ ከሱማሌ ብሔር ተወላጅ፣ አርባ በመቶ ከኦሮሞ ብሔር ተወላጅ እና ቀሪው ደግሞ ከሌላ ብሔር የተወለዱ ኢትዮጵያውያን ይወስዳሉ የሚል ነው፡፡

በርካታ ምሁራን እና የአካባቢው ተወላጆች ቀመሩን ምንም አይነት የህግ ድጋፍ እንደሌለው ይገልጻሉ፡፡ እንዲሁ ለፖለቲካ ፍጆታ የቀረበ ማሸማገያ (ማስታረቂያ) እንጂ ከዚህ አሰራ የተጠቀመ አንድም የሶማሊያም ሆነ የኦሮሞ ተወላጅ እንደሌለ ያስረዳሉ፡፡

ብዙኃኑ እንደሚስማሙት ድሬዳዋ የሁሉም እንጂ የተወሰነ ብሔር ብቻ የሚኖርባት ሳይሆን በርካቶች በከተማዋ ተወልደው ልጆች አፍርተው የሚኖሩባት ህብረ-ብሄር በአንድ የምታስተናግድ ከተማ ነች፡፡

አስናቀ ከፋለ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስና በዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል Ethnic Decentralization and the Challenges of Inclusive Governance in Multiethnic Cities: The Case of Dire Dawa, Ethiopia በሚል ርዕስ የሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ ባዘጋጁት ጥናታዊ ፅሑፋቸው ላይ ድሬዳዋ የሁሉም ብሔሮች ተዋፅኦ ብቻ ሳትሆን የውጪ ሀገራት ዜጎች የሚኖሩባት ከተማ እንደሆነች ይገልጻሉ፡፡ “…ድሬዳዋ ከአመሰራረቷ ጀምሮ የተለያዩ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መገናኛ ናት፡፡ በተጨማሪም ፈረንሳውያን፣ የመናዊያን፣ ህንዳዊያንና ኢትዮጵያውያን በአንድነት የሚኖሩባት ከተማ ናት፡፡” በማለት ያስረዳሉ፡፡

ቀመሩ የህገ መንግስት ድጋፍ የሌለውና ድሬዳዋ እንደ ፌዴራል ከተማ የቀረበውን የፖለቲካ አሰራር የህግን አግባብ የተከተለ እንዳልሆነ፤ በተጨማሪ የማንን ይሁንታ እንዳገኘ እንኳን የሚገልፅ ምንም ማስረጃ እንዳላገኙ የህግ ባለሞያው ባደረጉት ፍተሻ ማወቃቸውን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡

በየጊዜው በአባላቱ መካከል የሚነሱት ግጭቶች ዋነኛ ምክንያት ግልጽ የሆነ ፖሊሲ (አሰራር) አለመኖርና የፌዴራል መንግስት አቅጣጫ አለማስቀመጥ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በኢኮኖሚው ረገድ ደካማ ውጤት እንዲያስመዘግብ ምክንያት ነው ሲሉ ባለሙያዎች ይከራከራሉ፡፡

“የማዕከላዊው መንግስት በ1985 ዓ.ም ያቋቋመው የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ምንም አይነት ህጋዊ መሰረት እንደሌለው፡፡ ነገር ግን አምስት አባላት ማለትም ሁለት ሁለት ከሶማሌ እና ከኦሮሞ የተቀረው አንዱ የአማራ ተወካይን ያቀፈ ነው፡፡” የሚሉት አስናቀ ከፋለ በዚህ ማእቀፍ ውስጥ አብላጫ ቁጥር የያዙትን የሁለቱን አባላት ግራ ለማጋባት እና ማንኛቸው የአስተዳደሩ ሹመኛ መሆን እንደሚገባቸው የአማራ ተወካይ የዋና አስተዳደሩ ተቀዳሚ ተወካይ እንዲሆን ተደርጓል፡፡” ይላሉ ፡፡  

ሁለተኛ ሳምንቱን የያዘው ተቃውሞ በህዝቡ ውስጥ ታፍኖ የቆየው ኢ-ፍትሃዊ አሰራር ውጤት ነው፡፡ በርካታ የእድሜ ባለፀጎች ተቃውሞውን መቀላቀላቸውም ጉዳዩ የሰሞኑን አጀንዳ ብቻ ያነገበ አለመሆኑ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡

አስናቀ በጥናታው ጽሑፋቸው እንደሚያብራሩት ከ1983 ዓ.ም በኃላ በተደረገው ለውጥ የፌዴራል መንግስትን፣ የኦሮሞ እና የሶማሌ ክልል ተወላጆችን ጨምሮ በከተማ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቡድኖች ያቀፈ ሰላማዊ የሽግግር ሂደትን ይፋ አድርጎ የነበር ቢሆንም ከተማዋ ለኦሮሞ እና ሶማሌ ተወላጆች ቀረቤታ አላት በማለት በሁለቱ ቡድኖች መሀል የእኔ እበልጥ ሽኩቻ ማስነሳቱን ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ከሁለት አመታት በኃላ ሌላ ክስተት ተፈጥሮ ቁርሾውን የበለጠ እንዳባባሰው አስናቀ ከፋለ ሲያሰፍሩ “በ1985 አዲሱ የሱማሌ ክልላዊ መንግስት ሲቋቋም ዋና ከተማውን ድሬዳዋ ማድረጉ በኦሮሞ ተወላጆች ዘንድ ተቃውሞ አስነሳ፡፡ የፌዴራል መግስትም ይሄን ለመፍታት ተጠሪነቷ ለራሱ እንዲሆን አደረጋት፡፡ ከተማን የማስተዳደር ስራም የሁለቱ ብሔር ተወካይ ፓርቲዎች ኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት(ኦህዴድ) እና የሶማሌ ህዝቦች ዴሞክሲያዊ ፓርቲ(ሶህዴፓ) እንዲያስተዳድሩ የማስማሚያ ሀሳብ አቀረበ፡፡”

ታዲያ ይሄ ስርዓት ልሂቃኑ በየፊናቸው ህዝቡን በቀላሉ እንደፈለጉት እንዲያሾሩት፣ በፍቅና በመተሳሰብ አብሮ የኖረ ህዝብ እንዲጋጭ መንገድ እንደከፈተ ከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ቀደም ወጣቶች በጋራ መስጊድ እና ቤተክርስቲያን ሲሰሩ ነበር፤ ነገር ግን አሁን የተፈለገው እርስ በእርስ ህዝቡን ለማጋጨት እንደሆነ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡

ፋሲካ ታሪኩ ተወልዶ ያደረገው ድሬዳዋ ነው፤ ያለውን አለመረጋጋት አስመልክቶ ሲናገር “ያለው አሰራር የድሬዳዋ ተወላጆችን ያገለለ ነው፡፡ አሁን እየተነሱ ያሉት ጥያቄዎች እንደ መንስኤ እንጂ ዋነኛው የህዝቡ ጥያቄ 40-40-20 የሚባለውን የብሔር አሰራርን በመቃወም ነው፡፡” በማለት ያስረዳል፡፡

ይሄ አሰራር ወጣቱን ያገለለ እና ስራ-አጥ እንዲሆን ዳርጎታል፡፡ እንዲሁም የአስተዳደሩ ቸልተኝነት ህዝቡ ቁጣውን እንዲያሰማ እንዳደረገው ተገልጿል፡፡

“ቢሮክራሲው ሶማሊያንና የኦሮሚያን ተወላጆች እንኳን ተጠቃሚ ያደረገ አይደለም፤ ይልቁንም ከተማዋን ለማጥፋት አላማ ያደረገ ነው፡፡” በማለት ከጥቅሙ አደገኛነቱ እንደሚመዝን የከተማዋ ነዋሪ ጌትነት ታደሰ ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል፡፡

ተቃዉሞው ሰላማዊ መሆኑ እና የመንግስትም ሆነ የግለሰብ ንብረት አለመውደሙን የአይን እማኞች ተናግረው መንገዱ የተዘጋበት ምክንያት የሆኑት የፀጥታ አካላቱ የአብዲ ኢሌ ቀኝ እጅ በመሆናቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

“ሰሞኑን የተቀሰቀሰውን ረብሻ ያስነሱት “ሄጎ” በሚል ስያሜ የሚታወቁት ወጣቶች በቀድሞው የሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳደር አብዲ ኢሌ የተደራጁ ናቸው፡፡ ሙስሊሙንም ክርስትያኑንም የድሬዳዋ ወጣት የሚወክሉም አይደሉም፡፡” በማለት ጌትነት ታደሰ ይናገራሉ፡፡

እንደ ድሬዳዋ ነዋሪዎች እምነት ወጣቶቹን ካደራጁት ውስጥ አሁን በስራ ኃላፊነት ላይ የሚገኙት የካቢኔ አባላት  እንዳሉበት ገልጸው፤ እነዚህ አካላት ደግሞ ከአዲሱ የለውጥ ኃይል ጋር አብረው መስራት የማይፈልጉ ናቸው፡፡ ለዚህ ማሳያ ሰሞኑን በከንቲባው ጽ/ቤት ፊት ለፊት የጦር መሳሪያ የያዘ የጭነት ተሸከርካሪ መያዙን ያስረዳሉ፡፡

እንደ ህግ ባለሞያው አገላለፅ “ይሄ ቀመር የሶማሌውንም የኦሮሞውንም ህዝብ ተጠቃሚ ያደረገ አይደለም፡፡ ይልቁንም የፖለቲካ አባላቱ ተጠቃሚነት የሚስተዋልበት ነው፡፡ ለአብነት የሶማሌ ተወላጆች ራሳቸው ለሁለት የተከፈሉ መሆናቸው ከዚህ አሰራር ምንም ጥቅም እንዳላገኙ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡” ብለዋል፡፡

በአዲሱ የመንግስት ለውጥ አማካይነት 76 ባለስልጣናት ሲቀየሩ 24 የሚሆኑት ደግሞ ተሸጋሽገዋል፡፡ በተጨባጭ የሚታየው ግን ምንም አይነት ለውጥ አለመካሄዱን እንደሆነ የነዋሪው ሌላኛው ጥያቄ ነው፤ በዚህም ምክንያት ጥያቄያችን በተገቢው መንገድ እየተመለሰ አይደለም፡፡ ተቃውሟችን ከሰዎቹ ሳይሆን ከብልሹ አሰራሩ ነው ሲሉ ተናግዋል፡፡

የህብረተሰቡን ችግር ያነገበ ከመምህራን፣ ከተማሪዎች እና ወጣቶች የተውጣጣ “ሳተናው” የተባለው ቡድን “ስለድሬዳዋ ያገባናል” ብሎ በመነሳቱ እየተሳደደ ይገኛል፡፡ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፡፡ ከባለፈው ሃሙስ ምሽት ጀምሮ ወጣቶች ለምን ተቃውሞ አሰማችሁ ተብለው እየታፈሱ ከከተማው ወጣ ብሎ በሚገኘው የኢንዱስትሪ መንደር እየታሰሩ መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡

የአካባቢው ተወላጆች እንደሚናገሩት ማንም አይነት የፖለቲካ ቀመር ደጋፊ አይደለም፡፡ ህዝቡ የሚፈልገው ከየትም ይምጣ ድሬዳዋን እንደሌሎች ክልሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

“በጥናት ላይ የተደገፈ ማንኛውም አሰራር ህብረተሰቡ ይቀበላል፡፡ ነገር ግን የተወሰኑ አካላትን ለመጥቀም ሲባል የሚታይን ብልሹ አሰራር ደግሞ ይቃወማል፡፡” በማለት የህግ ባለሞያው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

ያሉት አስተዳደሮች በብቃት ማነስ ምክንያት የመምራት አቅም የላቸውም፤ ድሬዳዋ የባለቤትነት ጥያቄዋ ሊመለስላት ይገባል፣ እንዲሁም ህዝቡ የሚተማመንበት እና ተቀባይት ያለው አስተዳደር እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል ፡፡

በከተማዋ የኢንተርኔት አገልግሎት በበቂ ሁኔታ እየሰራ አለመሆኑን ነዋሪዎች ገልፀው አደጋ ሲደርስ ብቸኛ የመገናኛ አማራጫችን የማኀበራዊ ሚዲያ ነው በማለት ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ የድሬዳዋ ከተማ የፀጥታ አካላት እና አስተዳደሩ የሕዝብ ግንኙት ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡

አስተያየት