You can paste your entire post in here, and yes it can get really really long.
እዚህ ደርሰናል፡፡ ከረዥም ውጥረት፤ ከሺዎች ሕይወት መጥፋትና አካል መጉደል፤ እንዲሁም ከሚሊዮኖች መፈናቀል በኋላ እዚህ ደርሰናል፡፡ ከገዢው ፓርቲ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር መቀየር፤ ከተከታታይ የካቢኔ ሹም ሽር መካሄድ፤ከፖለቲካ እስረኞች መፈታት፤ ከኢትዮጵያ ኤርትራ እርቅ፤ በስደትና በበረሃ ለዓመታት ሲባዝኑ የነበሩ ተፋላሚዎች ወደ አገር ቤት መግባት በኋላ እዚህ ደርሰናል፡፡ በፍቅር ከመተቃቀፍና በጸያፍ ቃላት ከመነቃቀፍ፤ ከአንጀት ከመተሳሰብና በተንኮል ከመጠላለፍ፤ ከልብ ከመተጋገዝና በረባው ባልረባው ጉዳይ ተፎካክሮ ከመገዳደል፤ እንዲሁም ከኦሕዴድ ሥያሜና መዝሙር ለውጥ በኋላ እዚህ ደርሰናል፡፡ በተለይ የፌደራልና የክልል መንግሥታት “አለን” ብለው በሚከራከሩባት ኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ብዛት በሚሊዮኖች ከተቆጠሩ በኋላ እዚህ ደርሰናል፡፡አዎ እዚህ ደርሰናል፡፡አሁን ተጠቂዎች ያሉት ሩቅ ያሉ ሳይሆን በአፍሪካ መዲና፤ በዓለም አራተኛዋ የዲፕሎማቲክ ከተማ በፌደራል መንግሥቱ መቀመጫ፤ የኢትዮጵያውያን ቤት በሆነችው በአዲስ አበባ ነው፡፡ እድሜ ለአገም ጠቀም የፖለቲካ ሥልት አራማጆች፤ እዚህ ከደረስን በኋላ ቀጣዮቹ ተፈናቃዮች የሚጠለሉት በውጭ ኤምባሲዎች ውስጥ ሊሆን ይችላል! አዝማሚያውን በጥሞና ለተከታተለው ይህ የማይሆንበት ምክንያት እምብዛም የለም፡፡ታዲያ ከእንግዲህ ብዙዎች ወደ ሚፈልጉት መልካም አቅጣጫ ለመሄድ ምን ይደረግ? በመሠረቱ የወደፊቱ አቅጣጫ እስካሁን ከተመጣበት ሁኔታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ እናም የለውጡን ተፈጥሮ በቅድሚያ ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው፡፡ለውጡ በውስጣዊ ቅራኔና ውጫዊ ጫና ስለመምጣቱአሁን በኢትዮጵያና በመላው የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ውስጥ እየታየ ያለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ በአንድ በኩል በሚስጥረኛው የኢህአዴግ ድርጅትና መንግሥት ጓዳ እየከረረ የመጣው ውስጣዊ ቅራኔ ጡዘት ላይ በመድረሱ ምክንያት የተፈጠረ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ምንግዜም ክስና ወቀሳ ጠባዩ የሆነው የሕዝብ ተቃውሞ ውጫዊ ጫና ሆኖ የወለደው እንደሆነ አምናለሁ፡፡ እዚህ ላይ የውስጣዊ ቅራኔውም ሆነ የውጫዊ ጫናው ግንኙነት ከተመለከትን ተመጋጋቢ እንደሆኑ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ውስጣዊ የድርጅት ቅራኔውስጣዊ ቅራኔው የአይቀሬው የኢህአዴግ ፓርቲ እጣ ፈንታ እንደሆነ መረዳት አስተዋይነት ነው፡፡ ግንባሩ በ1980ዎቹ በነበረበት ቁመና በ2010 እንዲቀጥል መጠበቅ ተፈጥሯዊ ከሆነው የለውጥ ሕግጋት ጋር መላተም ነው፡፡ በግንባሩ ከቁጥር ወደ አይነት፤ ከአይነትም ወደ ቁጥር ለውጦች መስተናገዳቸው አይቀሬ ነበር፡፡ ለምሳሌ የ1980ዎቹ አብዮታውያን ወደ 2010 ባለአክሲዮን ባለሀብትነት ሲሸጋገሩ የባህርይ ለውጥ ማምጣታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡አሁን የድርጅት የኦዲት ኮሚሽን ሪፖርት ከማዳመጥ ይልቅ፤ የቤተሰብ ሀብት ሰነድን ከጉድፍ የሚያጸዳ የፋይናስ ኦዲተር ፍለጋ መሯሯጥ አዋጭ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ያወጧቸው የንግድ ፈቃዶች የየፓርቲያቸውን ደንብና መመሪያ እንዳስረሳቸው ግልጽ ነው፡፡ውጫዊ የሕዝብ ተቃውሞ ጫናወደ ውጭ ጫና ሲመጣ ደግሞ፤ በርግጥ በለውጡ ሠሪ ፈጣሪነት ላይ በተለይ በተለይ ወጣቶች የሌሎችም ማህበራዊ ኃይሎች ሚና ብዙ ተብሎለታል፡፡ ይሁንና አሁን መንግስታዊ ሥልጣንን ተቆጣጥሮ ያለው አዲሱ የኢህአዴግ አመራር ለአመታት በአራት ኪሎ ግቢ ውስጥ ሲንተከተክ የቆየውን ውስጣዊ የድርጅት ቅራኔ በወጣቶች በሚመራው ውጫዊ ጫና ጋር በመለወስና በመደቆስ በለውጥ ጎዳና ላይ እየተጓዘ እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡ ታሪካዊ ለውጥም ሆነ ሂደት የብዙ ሰሪ ፈጣሪዎች ድምር ውጤት መሆኑን መገንዘብ ከፍ ሲል በመንግስት ባለሥልጣናትና የአገም ጠቀም ፖለቲካ በሚያራምዱ አክቲቪስቶች መካከል ያለው የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ መንፈስ በሳይንሳዊ መንገድ እንዲገራ ይረዳል፤ ዝቅ ሲል ደግሞ በሜዳሊያ ሽልማት ወቅት ከሚፈጠር የይገባኛል ውዝግብ ያድናል፡፡የብዙዎች የስራ ውጤት የሆነውን ለውጥ በበጎ መልኩ ወደፊት እንዲጓዝ ከማን ምን ይጠበቃል የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ ሥልጣኑን በአዲስ መልክ ከቀጠለው አዲሱ የኢህአዴግ ኃይል ልጀምር፡፡ሀ. የኢህአዴግ ውስጣዊ ቅራኔ ይፈታመጀመሪያ ፉክክሩንና እሰጥ እገባውን ተውት፡፡ ሁሉም የግንባሩ አባል ድርጅቶች የፓርቲ እና የመንግስትን ሥራ በትርፍ ሰዓቱ ሲሰራ ነው የቆየው፡፡ እያንዳንዱ የኢህአዴግ አባል ድርጅት የተዳከመውና የተሸነፈው በገዛ ራሱ ንቅዘት ነው፡፡ አንዱ አንዱ ላይ ማላከኩ የብሳናን ተረት ወደራስ መጋበዝ ይሆናል፡፡ “ ‘ለመሆኑ ብሳና ይነቅዛል ብለው ቢጠይቁት ዛፉን ሁሉ መንቀዝ ያስተማረው ማን ሆነና?’ አለ፡፡” እያንዳንዱ የኢህአዴግ አባል ድርጅት ወሬ የሚያበዙ እንጂ አንድ የረባ የርዕዮተ ዓለም ተንታኝና ፖሊሲ አመንጪ ባለፉት 27 ዓመታት እንኳን ማፍራት ያልቻሉ ናቸው፡፡ ማን ነበር “ኢህአዴግነት ድንቁርናን ያበረታታል” ያለው? አሁን ሚኒስቴርና ሚኒስቴር ዲኤታ ሁሉ የፈረደበትን የዓለም ባንክ እቅድ ከውሎ አበል ጋር ተቀብሎ ሲተረተር ይውላል፡፡ ለመሆኑ ብአዴን ምን አድርጎ ነው ሕወሃትን ወይም ኦህዴድ/ኦዲፓን ያዳከመው? የትኛው ድርጅት ነው የአገሪቱ ሕዝብ ብዛት በአስደንጋጭ መጠን እያደገ ከእውቀትና ከሥራ ጋር የእድሜ ልክ ደመኛ የሆኑ ደረጃ አንድ ዘራፊዎችን በአመራርነት ያልሰበሰበው? ወልቃይት፤ ፊንፊኔ፤ የሲዳማ ክልልነት ምንትስ ንትርክ የመጣው ሥራ ተበላሽቶና ዝርፊያ በርትቶ ነገር ሲበላሽ አይደለም እንዴ? ሳጠቃልል ውስጣዊ ቅራኔው ብሔር የለውም፡፡ የህወሃትን ቆሻሻ ከብአዴን፤ የብአዴንን ጭቅቅት ከደህዴን፤ የደህዴን እድፍ ከኦህዴድ/ኦዲፓ፤ የኦህዴድ/ኦዲፓን ፎሮፎር ከሶሕዴፓ ማበላለጡና የቋንቋ ሽፋን መስጠቱ የቅራኔውን ተፈጥሮ ከመደበቅ ውጭ መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡ በቅድሚያ ግንባሩ የገባባትን ውስጣዊ ቅራኔ ይፍታ!ለ. ጉልበት የተሰማችሁ ኃይሎች ከአገም ጠቀም ፖለቲካ ውጡ!ኢትዮጵያ መቶ ሚሊዮን ሕዝቦች የሚኖሩባት አገር ነች፡፡ ኢትዮጵያ እልፍ አእላፍ የነፍስ ወከፍ ጦር መሳሪያዎችን ያነገቱ ዜጎች የሞሉባት አገር ነች፡፡ ኢትዮጵያ ደመናው ዞር ሲል በረሀብና በጠኔ የሚንገላቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ያሉባት አገር ነች፡፡ ኢትዮጵያ በአረቦችና በነጮች ምጽዋት የምትደዳር አገር ነች፡፡ ኢትዮጵያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿ በስደት ምክንያት የበረሀ አሞራ ሲሳይ፤ የዓሳ ነባሪ ራት የሚሆኑባት አገር ነች፡፡ ኢትዮጵያ ቀን ከሌሊት ለውድቀቷ የሚሰሩ ጠላቶች በቀጠናው ያሉባት አገር ነች፡፡ እናም ፈተናው ውስብስብ፤ ቀወሱም ማባሪያ የለውምና፤ በትላንት ድል ጉልበት የተሰማችሁ፤ ጉልበቱም ወደ ሥካር የወሰዳችሁ ኃይሎች ከማን አለብኝነት ይልቅ ሆደ ሰፊነት ጥበብ መሆኑን ተረድታችሁ ከአገም ጠቀም ፖለቲካ ውጡ!ሐ. “ወሬ ሩዝ አይቀቅልም”፤ እየሰራን ለውጡን እናስቀጥል!የመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ማኀበራዊና ባህላዊ ፍላጎቶችን ለማርካት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ጠንካራ ሰራተኛ ይፈልጋል፡፡ ክልሎች በዚህ ረገድ ከፍተኛ ፈተና ላይ ወድቀዋል፡፡ በምናየውና በምንሰማው ከቀበሌ እስከ ዞን ተገቢው የመንግስት ስራ ቆሟል፡፡ ሁሉም ፖለቲከኛ፤ ሁሉም ተንታኝ፤ ሁሉም አክቲቪስት ሆኖ ባለቤት ያጣውን የህዝብና የመንግስት ሀብት ተቀራምቶ ወደቤት ይገባል፡፡ቻይናውያን “ወሬ ሩዝ አይቀቅልም” ይላሉ፡፡ እውነታቸውን ነው፡፡ መሪዎቻችን በዚህ ጉዳይ ላይ ቢጎተጉቱም ሰሚ ያገኙ አይመስልም፡፡ ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል ከላይ አቶ ለማ “የስራ ያለህ!” እያሉ ሲጮሁ ቆይተዋል፤ ከታች ያለው የወረዳ ካቢኔ ሀሜትና አሉባልታ ሲነዛ ውሎ ደሞዙን ወስዶ ወደቤት ይገባል፡፡ በሌላውም ክልል ያው ነው፡፡ ደቡብ ክልል ልዩ ወረዳነትና ክልልነት ዋና አጀንዳ ሆኖ አሉባልታ መሰለቅ መተዳደሪያ ሆኗል፡፡ የማህበራዊ ድረ-ገጽ አክቲቪስቶች ገበያ ደርቶላቸዋል፡፡ የ“ዩኒቨርሲቲ”“ምሁራንን” ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ጉዳዩ ቢመለከተውም ባይመለከተውም ተንቀሳቃሽ ስልኩን በየሰከንዱ እንደ እንጀራ ምጣድ ሲያስስ ይውላል፡፡ በደፈናው ብዙ ኢትዮጵያዊ ወጣት አሻንጉሊት መጫወቻው ተስማምቶት ከትምህርት ቤት የቀረ ሕጻን መስሏል፡፡ ወሬ ነግሷል፤ ሥንፍና እስከ አጥንታችን ድረስ ዘልቆ ገብቷል፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ ፌስ ቡክ፤ ብሎግና መድረክ አስተናባሪነት ለሹመት እያበቃ ስለሆነ የብሎግ ሹመኞች በዝተዋል፡፡ መፍትሔው አንድ ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በጊዜ ወደ ቢሮ ሥራ እንግባ፡፡ ( እባክዎትን የውጭ ግንኙነት ሥራውን ለሌሎች ያካፍሉት) ሰሞኑን እንዳደረጉት የሰሜንና የደቡብ ሱዳን ጉዳይን በተለመደ ቅንነትዎ ከማሸማገልዎ በፊት ጉለሌና አውቶቡስ ተራ ግጭት እንዳይነሳ በንቃት መስራት ነበረብዎት፡፡ አክቲቪስቶችም ብትሆኑ ሥራና የህዝብ ኃላፊነት ያለባቸውን ተከታዮቻችሁን ወደ ሥራ ግቡ በሏቸው፡፡ ወሬ እንጀራ አይጋግርም!መ.በመጪዎች ሳምንታት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስለሚከፈቱ ሰዶ ማሳደድ እንዳይሆን!አሮጌው ኢህአዴግ ለዚህ ውድቀት የተዳረገው በተለይ ዝርፊያ በወለደው ውስጣዊ ቅራኔው ነው ብያለሁ፡፡ በዚህም ምክንያት ጠንካራ ሠራተኛን ማንቀሳቀስም ሆነ መቆጣጠር እንደማይችል መገመት ይቻላል፡፡ እንዲሁም በብዙ የክልል መንግስት ተቋማት ሥራ እንደተዳከመ፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ወጣቱ ሞባይሉን በጣቶቹ ሲዳብስ እንደሚውል ጠቁሚያለሁ፡፡ ታዲያ አፈር ድሜ በበላ ደካማ የመንግስት መዋቅር እንዴት ተደርጎ 27 ሚሊዮን ገደማ ተማሪ በሰላም ትምህርቱን እየተከታተለ ከወር ወር ይዘልቃል? በትምህርት ተቋማት የብሔርና የሀይማኖት ግጭት እንዳይነሳ ከወዲሁ ዝግጅት ቢደረግ መልካም ይመስለኛል፡፡ ሽባ የመንግስት ትምህርታዊና አስተዳደራዊ ተቋማትን እሹሩሩ እያሉ ችግር ቢፈጠር በማንም ላይ ጣት መቀሰር ተገቢ አይሆንም፡፡ አንዳንድ ባለአጀንዳዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መከፈትን ለጉዳያቸው ማስፈጸሚያ በእጅጉ መሻታቸው አይቀርም፡፡ ፖለቲከኞች “በኢቲቪ ብቅ ብለን እናረጋጋለን” ስላሉ ተማሪዎች አይረጋጉም፡፡ ጠንካራ መዋቅር ከሌለ ማንም ቀስቃሽ ሳያስፈልጋቸው ብዙ ወጣቶች በገዛ ራሳቸው ዳተኝነትና በአቋራጭ የመኖር ዝንባሌ ለሥርዓተ አልበኝነት ያጋልጣቸዋል፡፡ መዘንጋት የሌለበት ቁልፍ ጉዳይ ከአሮጌው ኢህአዴግ ውድቀት ጀርባ አንድም የመዋቅር መበስበስ መኖሩ ነው፡፡ ተማሪው ተረጋግቶ እንዲማር፤ ከተሞችም ሰላም እንዳይርቃቸው፤ በየትምህርት ተቋሙ ጠንካራ ፕሬዚዳንቶች፤ ዲኖች፤ ዳይሬክተሮችና ኃላፊዎች፤ በየከተሞችም ኃላፊነት የሚሰማቸው ከንቲባዎችና አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ታታሪ ሰራተኞች ሊኖራቸው ይገባል፡፡ አለበለዚያ ችግር በተፈጠረ ቁጥር አክቲቪስቶች ጋር አማላጅ እየላኩ አገር ማስተዳደር አይቻልም፡፡ከእንግዲህ እንዲህ ይደረግ ዘንድ ጊዜው ያስገድዳል፡፡