ነሐሴ 14 ፣ 2010

ኢህአዴግን ፍለጋ

ፖለቲካPoliticsአስተያየትምጣኔ ሀብት

ወይ ዘንድሮ!!የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተፈንቅሎ እንደገና አየተሰራ ነው ቢባል ማጋነን አይመስለኝም፡፡ ዘላለማዊ ንግስናን ሲያልም የነበረው (ህዝባዊ ወያኔ…

ኢህአዴግን ፍለጋ
ወይ ዘንድሮ!!የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተፈንቅሎ እንደገና አየተሰራ ነው ቢባል ማጋነን አይመስለኝም፡፡ ዘላለማዊ ንግስናን ሲያልም የነበረው (ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ) ህወሓት ወልጄ አሳደግኳቸው በሚላቸው፤ግን ደግሞ እነማን እንደሆኑ በውል ለተመልካች ለመለየት በሚስቸግሩ ሃይሎች ሃያልነቱን አጥቷል፡፡ በህወሓት ሲመራ የነበረው ኢህአዴግ ይኑር ይሙት ለመለየት በሚያሰቸግር መልኩ የርእዮተዓለም ዘይቱን ጨርሶ መንቃቃት ከጀመረ ውሎ አደረ፡፡ “ሁላችንም ያለን አማራጭ መደመር ብቻ ነው” በማለት ሰፊ ተቀባይነትን ያገኙት አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ተዋስኦ ያልጨመሩት ቡድንና ፓርቲ የለም፡፡ ከግራ እስከቀኝ፤ ከዘውግ ብሔረተኛ እስከ ኢትዮጵያዊ ብሔረተኛ፤ከጽንፍ እስከ ጽንፍ፤ ያልደባለቁት ሃይል የለም፡፡ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ያለውን መንግስት ሲሰድብና ሲያንጓጥጥ የሚታወቀው የአሜሪካ ዲያስፖራ ሳይቀር ፈጽሞ ባልተለመደ መልኩ “እኔንም ሀገሬንም የሚወክለን መሪዬ ይህ ነው ”ሲል ድምጹን ከፍ አድርጎ አዲሱን ጠቅላይ ሚንስትር በአደባባይ አሞግሷል፡፡ ዱር ቤቴ ብለው የሸፈቱ ቡድኖች ወደአገራቸው ገብተው በህዝብ መሃል ሲንጎማለሉ እየታዩ ነው፡፡ ስልጣን ላይ የነበረው መንግስት እድሜውን ሙሉ ማንም ከማን አልተጣላም እያለ ቢመጣም፤ አሁን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የብሔራዊ እርቅን እና ይቅርባይነትን እየሰበኩ ነው፡፡በዚህ ሁሉ መሃል “ለመሆኑ ኢህአዴግ አለ?“ የሚል ጥያቄን ብዙዎች ያነሳሉ፡፡ ለቀናት በቆየው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካን ጉብኝት መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ግንባር (ኢህአዴግ) መድከም እንደጥያቄ ቢነሳም ጠቅላይ ሚንስትሩ የሰጡት መልስ ህወአትን በጥፊ ከማጠናገር ባለፈ ስለኢህአዴግ ብዙ የሚናገር እንዳልነበረ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ “ኦሮሞ ሲመራው ነው ወይ የሚደክመው?“ ነበር መልሳቸው፡፡ ወደአሜሪካ ከማቅናታቸው ቀናት ቀደም ብሎ አገር ውስጥ ካሉ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይትም ኢህአዴግ ተዳክሟል ብላችሁ ፈጽሞ እንዳትዘናጉ ሲሉ ተወዳዳሪዎቹን መክረዋል፡፡የኢህአዴግ አጭር የህይወት ታሪክኢህአዴግ ዘንድሮ ግንቦት የ30 ዓመት ጎልማሳ በሆነ ነበር፡፡ በ1982 ጥቅምት ላይ የተፃፈና በበይነ-መረብ ላይ እንዲሁ ግርድፉን ያለ አንድ ዶክመነት እንደሚያመለክተው ኢህአዴግ ውልደቱ በወቅቱ የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኝቅናቄ (ኢህዴን) እና በህወሓት መካከል በነበረ ጋብቻ ነው፡፡ የተወለደውም በግንቦት 1980 ዓ.ም. ነበር፡፡ ኢህአዴግ በሁለት ዓመቱ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትን (ኦህዴድን) ደራ ላይ ወለደ፡፡ ደርግን ከስልጣን ካስወገደ በኋላ ደግሞ በ1984 ዓ.ም. ወደ ደቡብ ወርዶ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን (ደኢህዴግ) እንዲሁ ደገመ፡፡ ደኢህዴግ የብዙ ፓርቲዎች ግንባር ነበር፤ ኋላ ላይ ለቁጥጥር እንዲመች ይመስላል ፓርቲዎቹ ፈርሰው ግንባሩ ወደ ንቅናቄ ተቀየረ፡፡ የተቀሩትን አካባቢዎች (በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ክልሎች ይሏቸው ነበር በወቅቱ) ይወክላሉ ያላቸውን ፓርቲዎችም ከየመንገዱ እያነሳ የማደጎ ልጆች አደረገ፡፡ኢህአዴግ ራሱን የአራት ፓርቲዎች ግንባር ነኝ እያለ ነው የሚጠራው፡፡ እንደኢህአዴግ ከሆነ ሁሉም ራሱን ችሎ ፤ አንዱ አንዱን ሳያዘው፤ ለአንድ አላማ የተሰለፈ የአራት ፓርቲዎች ድምር ነው፡፡ እያንዳንዱ ፓርቲም የክልል ወይም የብሔር ውክልና ይዞ ራሱን ችሎ የቆመ መሆኑ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ኢህአዴግ መርሐ ግብሩንና ህገመንግስት ያለውን ሰነድ ሲያረቅ ኦህዴድና ደኢህዴን ጭራሽ አልተረገዙም ነበር፡፡  ከምስረታቸው በኋላ ይህንኑ ዶክመነት በየቋንቋቸው እያባዛ ክልላችሁን ምሩበት ብሎ ሰጣቸው፡፡ ይህ እንግዲህ የሚያሳየን ኢህአዴግ ከአመሰራረቱም ዴሞክራሲያዊ ያልሆነና ግንባሩን የፈጠሩት ሃይሎች ከኢህዴን በስተቀር (በወቅቱ የአማራ የስም ውክልና እንኳን ያልያዘ ነበር) እዚህ ግባ የሚባል የትግልና የርእዮተዓለም አስተዋጽኦ ያላበረከቱ መንገደኞች እንደነበሩ ነው፡፡ያለፉትን ሦስት አስርት ዓመታት ህወሓት የኢህአዴግ ሩህያ (ነፍስያ) ነበረች፡፡ ህወሓት እንደጭንቅላት ስትወሰድ የተቀሩት ደግሞ እጅና እግሮች ነበሩ-በህወሓት ፍላጎት ተንቀሳቃሾች፡፡ ለወትሮው ህወሓት ከሌለች ኢህአዴግ የለም ነበር፡፡ ይህን ጠንቅቀው የሚያውቁት ሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር በ1993 የህወሓት ‘እንፍሽፍሽ’ ወቅት እነ ስዬ አብርሃን በግፍ ሲያባርሩ፤ ሶስቱን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እንደመሳሪያ ተጠቅመውባቸዋል፡፡ በወቅቱ አቶ መለስ ከእሳቸው በተቃራኒ የቆሙ የኢህአዴግ ምክር ቤት ያሉ የህወሓት ተወካዮችን ወደምክር ቤቱ ስብሰባ ድርሽ እንዳይሉ እንዲደረግላቸው፤ ይህ ካልሆነ ግን ህወሓትን ከኢህአዴግ እንደሚያስወጡ ዛቱ ( የአቶ ገብሩን አስራት መጽሐፍን መመልከት  ይቻላል)፡፡  ኢህአዴግ ከሌለ ደግሞ ሶሰቱ ማህበርተኞች (ብሃዴን፤ኦህዴድና ደህዴን) የሉም፡፡በመሆኑም እነስዬን ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከምክር ቤቱ ስብሰባ ከለከሉ፡፡  ዛሬ ህወሓት የለችም-ኢህአዴግም ተዳክሟል፡፡ኢህአዴግን ማን አዳከመው?በርካታው ሰው ቢያንስ የሁለት ትውልድን እድሜ ስልጣን ላይ ለመኖር እቅድ የነበረው ኢህአዴግ የደከመውና ሊወድቅ የቀረበው በኦሮሚያና አማራ ክልል በተነሱ (ቄሮና ፋኖ ይሏቸዋል) ወጣቶች ተቃውሞ ብቻ ነው ብሎ ያስባል፡፡ የህዝብ ምሬቱና ተቃውሞው እንዳለ ቢሆንም፤ ኢህአዴግ ግን ከተቃውሞው ቀደም ብሎ ራሱን የሚበላ ደዌ እንደተቆራኘው የተዘነጋም ይመስላል፡፡በምርጫ 97 የደነገጠው ኢህአዴግ የሚያደርገውን አያውቅም ነበር፡፡ ከግንባሩ አባል ፓርቲዎች በሚሊዮን የሚቆጠር አባላትን ወደ ድርጅቱ አመጣ፡፡ የኣባላት ብዛት ያድኑኛል በሚል ታሪካዊ የሚባል የፖለቲካ ስሌት ስህተት ሰራ፡፡ አብይ ተክለማሪያም በ2001 ዓ.ም. ይህ አይነቱ በገፍ አባላትን የማምጣት አካሄድ (co-option)  ውሰን የሆነውን ሃብት ወደ ሽሚያ ሊወስደውና ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል አዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ በስፋት ቃኝቶት ነበር፡፡  በ2002 ምርጫ 99.6 በመቶ አሸንፎ አለምን ጉድ ያሰኘው ኢህአዴግ በጊዜ የችግሩን መፍትሄ መፈለግ ሣይሆን የያዘው የሁለት ምርጫዎች ወግ በሚል ይህን አደጋና መፍትሄውንም ያስቡበታል የሚባሉት የድርጅቱ ፈላጭ ቆራጭም በድንገተኛ ሞት አለፉ፡፡ ብዙው በወቅቱ የፈራው በሚፈጠረው የስልጣን ክፍተት ሊመጣ የሚችለውን ግጭት ቢሆንም፤ እንደታሰበው ሳይሆን ኢህአዴግ የቡድን አመራር (Collective leadership ) በሚል ዘዬ የመከራውን ወቅት የተሻገረ መሰለ፡፡ ሽግግሩ መልካም መምሰሉ ኢህአዴግን፤ በተለይም ጭንቅላት የነበሩ መሪዋን ሞት የነጠቃትን ህወሓትን፤ ለከት ወዳለፈ ልፍያ ውስጥ ከተተ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ለሃብትና ለስልጣን ሲሉ ቀን ጠብቀው ሊባሉ የሚችሉ አዳዲስ አባላቶቹን ረሳቸው፡፡ በ 2007 ዓ.ም. የ100% እጅግ አሳፋሪ የምርጫ ውጤትም የእነዚህ አባላቱ ሽሚያና ልፊያ ጅማሬ ታየ፡፡ ለይሉኝታና እንዲሁም ለአንጻራዊ ተዓማኒነት ብሎ እንኳን አንዲት ወንበር ለመልቀቅ ፈቃደኛ የሚሆን አባል ማግኘት አዳጋች ሆነበት፡፡ ይህ ለኢህአዴግ የጅማሬው ፍፃሜ ነበር፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግና ደጋፊዎቹ ግን ይህ የገባቸውም አይመስሉም ነበር፡፡ በ “ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ” ያገኘነውን የህዝቡን ሉአላዊ ድምጽ ለምንድነው ለተቃዋሚዎች የምናካፍለው እያሉ ይቀልዱ ጀመር፡፡ የፓርላማ ይሁን የክልል ምክር ቤት መቀመጫ ግን በሚሊዮን ለተቆጠሩ አባላት ሽሚያ በቂ አልነበረምና ፍትጊያው ቀጥሎ ላለፉት 3 ዓመታት ያየነውን የፓርቲ ውስጥ ጦርነት አስከተለ፡፡ ኢህአዴግንም ለሞት ሩብ ጉዳይ ላይ አስቀመጠው፡፡ኦህዴድና ብሔረ ዐማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብዐዴን) በአንድ ጎራ ህወሓት በሌላው በቆሙበት በኢህአዴግ የውስጥ ሽኩቻና ቡጢ ኦህዴዶች ከውጭ (በተለምዶ ህወሓት/ኢህአዴግ ጠላት ከሚላቸው ቡድኖች) ሳይቀር ድጋፍ ያገኙትን ሚስጥርም ወደውጭ ሲያወጡ እንደነበር የሚያሳዩ ነገሮች እየታዩ ነው፡፡ከሁለት ሳምንታት በፊት በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ አንዲት ምስልበድምጽ የብዙዎችን ትኩረት ስባ ነበር፡፡ የመንግስት ሚዲያዎች ታዋቂውን የማኀበራዊ ሚዲያ የኦሮሞ አክቲቪስት ጃዋር መሃመድን ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ጉብኝት እየጠየቁት ይታያል፡፡ ከሰጠው መልስ ውስጥ የብዙዎቹን ቀልብ ስቦ የነበረው ኢህአዴግ ውስጥ ስላሉ፤ አሁን የሚታየው ለውጥ ደጋፊዎች በአጠቃላይ፤ ስለኦህዴድ ሰዎች ደግሞ በተለይ የሰጠው አስተያየቱ ነው፡፡ ጃዋር የአሁኖቹን አመራሮች አሞግሶ ሲያበቃ ያው እንደሚጠረጠረው ከነዚህ ሰዎች ጋር ለረጅም ጊዜ ሰርተናል፤ እንተዋወቃለን የትግሉም አካል ነበሩ ሲል ጨመረበት፡፡ኢህአዴግ በህይወት ቢኖር ኖሮ ይሄ የጃዋር አንድ መስመር ዐረፍተ ነገር ብቻ ሊያፈርሰው በተገባ ነበር ፡፡ ምክንያቱን  ከአራት ወራት በፊት ጃዋርና እሱን መሰል ሰዎችና ቡድኖች በወቅቱ በኢትዮጵያ መንግስት በሽብር (በሃሰትም ቢሆን) ተከሰውና  ተወግዘው የነበረበት ወቅት ነው፡፡ እንደጃዋር ከሆነ ደግሞ የኢህአዴግ አባል የነበረውን ኦህዴድን የሚመሩት ሰዎች የሽብር ወንጀል ክስ ከነበረበት ቡድን ጋር ከህወሓት ጀርባ ሆነው ሲሰሩ ነበር ማለት ነው፡፡ በዚህ ሳያበቃ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያው የአሜሪካ ጉብኝታቸው ወቅት አዲሱን የለውጥ ሃይል ባሞገሱበት ንግግራቸው ከአዋሳ እስከ ባህርዳር የግለሰቦችን ስም ሲያነሱ ወደመቀሌ ዞር ማለትንም አልፈለጉም፡፡ዛሬ ኢህአዴግ ተፈረካክሶ የወደቀ ይመስላል፡፡ በህዝቡ ዘንድ በኢህአዴግ ውስጥ የህወሓት መልዕክተኞች ናቸው ተብለው ሲታመኑ የነበሩት ደካማዎቹ ፓርቲዎች (በተለይም ብዐዴንና ኦህዴድ) አሁንም ገና ወፌ ቆመች እያሉ እንጂ ጠንክረው መቆም አልቻሉም፡፡ እንኳንስ በኢህአዴግና በፌደራል መንግስት ደረጃ በክልላቸው ውስጥም ጠንክረው ህግና ሥርዓት ማስከበር አቅቷቸው ሲንቧቸሩ ይታያል፡፡ በዚህም የተለመደው ዴሞክራሲያዊ ማእከላዊነቱ እጅጉን የላላበትና የርዕዮተ-ዓለም እስትንፋሱን ያጣው ኢህአዴግን፤ ነፍሱ አለ ወይስ ሞቷል ብለው እየጠየቁ አጎንብሰው የልብ ትርታውን የሚያዳምጡ ሰዎች በርክተዋል፡፡ኢህአዴግ ቢሞትስ? ኢሀአዴግን አቁሞት የነበረው የጠራና ሁሉም አባላቱ የሚያምኑበት ርዕዮት አልነበረም፤ ዴሞክራሲያዊ ማእከላዊነትና ይህ የሚፈጥረው ጠንካራ መንግስት እንጂ፡፡ የስልጣን ቁንጮ ላይ የነበሩት ሰዎቹ በወጣትነታቸው እንደማንኛውም የወቅቱ ተማሪ ማርክሲሰት ሊኒንዝም ቢማርካቸውም፤ ስልጣን ከያዙ በኋላ ይህ አይነቱ አስተሳሰብ ከውስጣቸው ተንጠፍጥፎ ባይወጣም የሚይዙት የሚጨብጡትን እንደጠፋቸው ያስተውቃል፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ የሚለይበት ነገር ቢኖር የዘውግ ፌደራሊዝሙ ነው፡፡ ወደውስጥ ጠልቆ ለተመለከተውም ከዚህ ያለፈ ርዕዮተዓለም እንደሌለው ይረዳዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን መለያው የሆነውን የዘውግ ፌደራሊዝም የሚችለውን ያህል የርዕዮት ቅባት ሊቀባው፤ የአስገዳጅ ነባራዊ ሃቅ ምላሽ እንደነበር ሊያስረዳ ሲጥር ቆይቷል፡፡ ለዚህ ማሳያም ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አስራ-ሰባት የሚሆኑ ነፍጥ ያነገቱ የዘውግ ሃይሎች እያፋጠጡን ሳለ ከዘውግ ፌደራሊዝምና መገንጠልን መብት ከሚያረገው የህገ-መንግስት አንቀጽ ውጭ አገሪቱን ሊያተርፍ የሚችል ሃይል እንዳልነበር ሲናገሩ ኖረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ህወሓት ከላይ የተጠቀሰው ጽሁፍ ላይ እንደተገለጸው ገና የትጥቅ ትግሉን በሚያካሂድበት ወቅት ምን አይነት ስርዓት ለኢትዮጵያ እንደሚያስፈልግና ደካማ ኢትዮጵያንና ጠንካራ መንግስትን (የፖሊስ፤ የመከላከያና የደህንነት አገርን ሳይሆን ፓርቲን እንዲጠብቁ) እንደሚሻ በፖለቲካ ፕሮግራሙ ላይ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ይህን ወደተግባር የሚቀየሩ የተለያዩ ቡድኖችንም ህወሓት በአምሳያው እንዲያመልኩት ፈጠረ እንጂ አዲስ ነገር አላመጣም፡፡የኢህአዴግ ሞት ለሀገሪቱ ሞት የሚበጅ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ሌላ ተተኪ የሚሆን ሃይል እንዳይወጣ ሌት ተቀን ሲታትር የነበረው ኢህአዴግ ቢሞት አገሪቱ ወደቀውስ መግባቷ የታወቀ ነበርና፡፡ ይህን የተረዳው ኢህአዴግ ለሚቃወሙት ዘውጌዎችም ይሁን የአንድነት ሃይሎች ክፉ የነበረ ቢሆንም፤ የአንድነት ሃይሎች ላይ ግን የበለጠ ጨካኝ ነበር፡፡ በምርጫ 97 ከተደናገጠ ወዲያ የአንድነት ሃይሉ ላይ የፈሪ በትር ነበር ያሳረፈው፡፡ ስለሆነም እንዲህ በደከመበት ሰዓት የአንድነት ሃይሎች በፍጥነት አገግመው ሊመጡና ሊያዩት አልቻሉም፡፡በአመለካከት የሚቀርቡት የዘውጌ ሃይሎችም የደረሰባቸው ጉዳት ኢህአዴግን ለመተካት የሚያስችል አቅም የነሳቸው በመሆኑ እስኪጠናከሩ ድረስ እና ስልጣኑን እስኪቀበሉት ድረስ ሞቱን አይፈልጉትም፡፡ ለዚህም ነው ኢህአዴግ ጠንካራ ነው አሁንም አገሪቱን እየመራ ነው በማለት እተኛበት አልጋ ላይ ነፍስ ሊዘሩበት እየጣሩ ያሉት፡፡ ኢህአዴግን ነፍስ ሊዘሩለት እየጣሩ ካሉት ሰዎች መሃል ጃዋር አንዱ መሆኑ ነው፡፡ የዚህን ሰሞን የአገር ውስጥ ጉዞዎቹን ማየት መልካም ነው፡፡ ይሳካለት ይሆን?ኢህአዴግ ያገግም ይሆን?የምናውቀው ኢህአዴግ የሚያገግመው ህወሓት ስታገግም ብቻ ነው፡፡ ህወሓት ታገግማለች ወይ?ብዙ የኢትዮጵያ ፖለቲካን የሚያብሰከስኩ ሰዎች አንድ ነገር ስተው የሚታዩ ይመስላሉ፡፡ ፖለቲካ ከኢኮኖሚ ተነጥሎ ብቻውን የሚቆም ይመስላቸዋል፡፡ ፖለቲካ ብቻውን የማይቆምና ከኢኮኖሚ ጋር የተጣመረ ወይም እህልና ውሃ (Political Economy) የበለጠ እንዳለው መዘንጋት ይታይባቸዋል፡፡፡ ለዚህ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፤ታሪካችን፤ ሃይማኖትና ባህላችን ትልቁን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ ሃይማኖታችን ሰማያዊ ነው፤ ባህላችን ከምእራባዊያን እኔነት የራቀ ነው፤ ታሪካችን የእጅ የማንሰጥ አሸናፊዎች ነው፤ ርዕዮተ ዓለማችን ብሔረተኝነት ነው፡፡ በዚህም የፖለቲካ ምልከታችን ወደሃይማኖትና ከዚያ ውስጥ ወደሚጠበቅ ፍትሃዊነት፤ እንዲሁም ስሜታዊነት ያደላል፡፡ይህን የተለመደ ለፖለቲካ ያለንን አመለካከት በግላጭ ወደጎን አድርጋ እህልና ውሃን ፖለቲካችን ውስጥ ያስተዋወቀችውና ድርጅታዊና ካድሬያዊ ዘረፋ ላይ ያተኮረችው ለመጀመሪያ ጊዜ ህወሓት ነች ማለት ይቻላል፡፡ እድሜ ለቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት ህወሓት የምእራቡና የምስራቁን አለም ርዳታና ገንዘብ በአንድ ላይ በአግባቡ ቃርማለች፡፡ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታትም በዓለም አቀፉ ከባቢ ለውጥ ምክንያት በአገሪቱ ውስጥ ከተፈጠረው የኢኮኖሚ መነቃቃት ዋነኛ ተጠቃሚ ሆና ቆይታለች፡፡ዛሬ ላይ ግን ህወሓትን የሚመሩ ሰዎች ድንገት በደረሰባቸው ህዝባዊና ፖለቲካዊ ዱላ ከመሃል አገር ፖለቲካ ሸሽተው መቀሌ ከትመዋል፡፡ ያም ሆኖ የህወሓት አመራሮች ከመሃል አገር ፖለቲካ በፍጥነት ሸሽተው ሊያመልጡ አይችሉም፡፡ ሳያስቡት ድንገት የወረደባቸው ናዳ በመሃል አገር አለን የሚሉትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የጥቅም ጅራታቸውን ረግጦባቸው እየተወራጩ ይታያል፡፡ በርግጥ ናዳው ቢለቃቸውም እነሱ በቀላሉ የማይለቁት ብዙ ጉዳይ ማሃልና ዳርዳሩን አላቸው፡፡ህወሓቶችና ተከታዮቻቸው አሁን ላለው ህገ-መንግስታዊ ሥርዓትና የፌደራል አስተዳደር ከአቅም በላይ አዋጥተናል ባዮች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ፈጠርናት የሚሏት ፌደራላዊት ኢትዮጵያ እውነተኛ ፌደራላዊነትን በተግባር ከማየት እጅጉን የራቀች ነች፡፡ በብሔሮች ሙሉ ፈቃደኝነት የተመሰረተች እያሉ የሚለፍፉላት አገር፤ አይደለም ከ24 ዓመታት በፊት የፌደራል መንግስቱ ሲመሰረት፤ ዛሬ እንኳን ሁሉም ዘውጎች በእኩልነት ተደራድረው ጥቅማቸውን ሊያስከብሩ የሚችሉበት አቅም ላይ እንዳልሆኑ ብዙ መገለጫዎች አሉ፡፡ (የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ እርግጥ ግለሰቦች እንጂ ዘውጎች ወይም ቡድኖች እኩል ናቸው ወይም እኩል ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ አያምንም)፡፡የብሔር ፌደራሊዝም ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ይምራው ማን እውነተኛ ሊሆን አይችልም (It has been fake and it will remain so)፡፡ ህወሓት የብሔር ፌደራሊዝም ኢትዮጵያ ውስጥ ስታስተዋውቅ እውነተኛ እንደማይሆን ታውቀዋለች፡፡ ክልል አይደለም መንደር መምራት የሚችል የሰው ሃይል የሌለውን ቤንሻንጉልንና ጋምቤላን የመሳሰሉትን ክልሎች ናችሁ ብሎ ማወጅ ጨዋታ እንደሆነ አይጠፋትም፡፡ ግን ራስህን አስተዳድር ተብሎ የሚቀመጠው ጋምቤላና ቤንሻንጉል ኣማራና ኦሮሞን ከማዳከሙ በላይ፤ህወሓትን እንደፈጣሪ እያመሰገነ የሚኖር አመራር እንደሚኖር ገምታለች፡፡ እንደፈጣሪ የሚያዩዋቸውን የህወሓት ደጋፊዎች ደግሞ በአካባቢው የሚገኙ ሃብቶችን በር በደንብ በርግደው እንደሚሰጡ ይታወቃል፡፡ ብዙ ጊዜ የህወሓት አፈቀላጤዎች እነዚህን ክልሎች እንዳበቋቸውና በሁለት እግራቸው እንዳቆሟቸው ከመናገር ቦዝነው አያውቁም፡፡ በዚህም ሳያበቁ እነዚህ ክልሎች የፌደራሊዝሙ ማገሮች እንደሆኑና እነሱን መነካካት፤ አገሪቱን እላያችን ላይ መናድ ነው በማለት ያስፈራራሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የፌደራል መንግስት ስልጣን ከክልሎች ተሸራርፎ የመጣና ክልሎች የማዕከላዊ መንግስት አለቆች እንደሆኑ በቃላት ሽንገላ ይገልፅ ነበር፡፡ይህን ትርክት የማይቀበሉት ሰዎች ነገሩ ወዲህ ነው ይላሉ፡፡ ነገሩ ህወሓት ፌደራሊዝሙን ስትመሰረት የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተጽዕኖዋን ለረጅም ጊዜ ያቀደችባቸው አካባቢዎች እነዚህ ክልሎች ይመስላሉ፡፡ ምክንያቱም የእነዚህ ክልሎች ልሂቃን ህወሓት ባመጣችው ስርዓት የህብረተሰባቸውን ህይወት ባይቀይሩም የየአካባቢያቸው ፈላጭ ቆራጮች (Local Chiefs) ስለሆኑና የስርዓቱ እህልና ውሃ (Political Economy) ተጠቃሚዎች በመሆናቸው ለህወሓት የበላይነት ምንጊዜም ዘብ የሚቆሙ ተደርገው ተወስደዋል፡፡  ኮንትሮባንዲሰቶች የነገሱበት የኢትዮጵያ ሶማሊ ክልልና፤ የጋምቤላ የእርሻ ልማቶችን ማየት ለዚህ አይነተኛ ግብኣት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ታዳጊ ክልሎች ዛሬም የማእከላዊ መንግስትን ድጋፍ የሚሹ ናቸው፡፡ የሶማሊ ክልልን ሲያማክር ቆይቶ ወደፌደራል መንግስት መጥቶ የመሬት ዘረፋ ቁንጮ ተብሎ ተከሶ ሲያበቃ በቅርቡ የተለቀቀውን የቀድሞ የገቢዎች ሚንስትር አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስን ልብ ይሏል፡፡እነዚህ ክልሎች በማዕከላዊ መንግስት ውስጥ የህወሓትን ጉልበትና መደራደሪያ ከመጨመር ያለፈ ሚና እንዳይኖራቸውና፤ ከመነሻውም እውነተኛ የሆነ ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ እንዳይቻል አድርገዋል፡፡አሁን ህወሓት በጣና ታማለች፡፡ በታዳጊ ወይም ተላጣፊ ክልሎቿ ተጽእኖ ፈጥራ ልታስፈራራ ሞክራም እየተሳካላት አይመስልም፡፡ ከፖለቲካ-ኢኮኖሚው ተነጥላለች ማለት ይቻላል፡፡ እህል ውሃ አጥታ ደግሞ ብዙ እድሜ አትቆይም፡፡ ህወሓት ከሌለች ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትሩ ባይዋጥላቸውም ጠንካራው ኢህአዴግ አይኖርም፡፡ ኦህዴድና ብዐዴን ኢህአዴግን ለማጠነከር፤ ካድሬውን ቀንና ሌሊት የሚያስሮጥ ርዕየተ-ዓለም ሊፈጥሩ የሚችሉበት ታሪካዊ እርሾ ጓዳቸው ውስጥ የለም፡፡ ከፖለቲካ ኢኮኖሚው በአንፃራዊነት ተገልለው ስለቆዩና አገሪቱም ላለፉት ሶስት ዓመታት የግጭት ፍራሽ ሜዳ ሆና ቆይታ ሃብት የመፍጠር ጉልበቷ ስለዛለ ”እድሜ ለኔ …ለዚህ አበቃኋችሁ “ እያለ ለሚያጉረጠርጥባቸው በሚሊዮን የሚቆጠር ጎረምሳ የሚያቃምሱት ይሄ ነው የሚባል ጥሪትም የላቸውም፡፡ደኢህዴን ብዙ ፍላጎት በውሰጡ የያዘ ተፈጥሮው ሁልጊዜ አዳክሞ ስላሚያቆየው ከጠነከረው ጋር ከመጓዝ ውጭ ይሄ ነው የሚባል ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ኦህዴድና ብዐዴንም ያለቸው አማራጭ በየክልሎቻቸው ያሉ ተቃዋሚ የብሄር ፓርቲዎችን መቀላቀል ይመስላል፡፡ ለምሳሌ ኦህዴድ በይፋ ስያሜውን ሊቀይር እንደሆነ ሲነገር፤ አንዳንድ ምንጮች ደግሞ ከሌሎች በክልሉ ከሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ሊዋሃድ ነው በማለት ይገልፃሉ፡፡ ብዐዴንም የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) የተባለ ትኩስ ብሔርተኛን ጉያው ስር ታቅፎ ከኦህዴድ የተለየ እድል አይጠብቀውም፡፡ ይህ ደግሞ ኢህአዴግን  ከውስጥም ከውጭም ቀይሮት ለወትሮው የሚታወቀውን ኢህአዴግነቱን ከማጥፋቱም በላይ ህወሓትን ሙሉ ለሙሉ ቆርጦ የመጣል እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህም ኢህአዴግ በተአምር ተርፎ ካልሞተ እንኳን አገግሞ ለመነሳት ብዙ ጊዜ ይፈጅበታል፡፡ኢትዮጵያ ኢህአዴግን አሳክማ ለማዳን፤ ወይም አስታምማ ለመቅበር አቅምና ጊዜስ ታገኝ ይሆን?? ትልቁ ቁምነገር ይህ ነው፡፡ ለጊዜው ግን ኢህአዴግ ያልሻረ ቁስሉን እንደያዘ የደረሰበትን ፈልጎ ማግኘት የሚቻል አይመስልም፡፡

አስተያየት