ኅዳር 6 ፣ 2011

የኢትዮጲያ ወደ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የመቀላቀል ሩጫ- ተስፋ እና ስጋቶች

ወቅታዊ ጉዳዮችፊቸር

የአስተዳደር ለውጡ የሀገሪቱን የፖለቲካዊ ምጣኔ ሀብት ላይ ተጽእኖውን በማሳደር ላይ ያለ ይመስላል። በዚህ ሂደት ውስጥ ሀገሪቱ የዓለም የንግድ ድርጅትን…

የኢትዮጲያ ወደ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የመቀላቀል ሩጫ- ተስፋ እና ስጋቶች
የአስተዳደር ለውጡ የሀገሪቱን የፖለቲካዊ ምጣኔ ሀብት ላይ ተጽእኖውን በማሳደር ላይ ያለ ይመስላል። በዚህ ሂደት ውስጥ ሀገሪቱ የዓለም የንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል እየተጣፈች መሆኑን በመንተራስ ሚኪያስ በቀለ የቅልቅሉን ተስፋ እና ስጋት እንዲህ አቅርቦታል።እንደ መንደርደሪያጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኃላ ሀገሪቷ ወደ አዲስ የፖለቲካ ኢኮኖሚ አቅጣጫ እያመራች ይመስላል። የልማታዊ መንግስት ርእዮተ ዓለም የሚፈተንበት አካሄዶች እየታዩ ነው። በፊት የነበረው ረጅም የመንግስት እጅ ከኢኮኖሚው ገለል ሊደረግ ይመስላል። ለዚህም ማሳያ ጠቅላይ ሚንስትሩ የስልጣን በትሩን በያዙ አጭር ጊዜ ውስጥ ፓርቲያቸው ሀገሪቷ የገባችበትን እዳ ለማቃለል በሚል የሀገሪቷን ትላልቅ ለትርፍ የተቋቋሙ የመንግስት ድርጅቶች ወደ ግል ለማዘዋወር መወሰኑን ማሳወቁ ነው። ኢትዮጲያ ወደ አለም ንግድ ድርጅት (World Trade Organization) በሁለተኛው የልማትና ትራንስፎርሜሽን ማብቂያ(2012 ዓ.ም) ላይ ትቀላቀላለች የተባለውን እቅድም የዐቢይ አስተዳደር ለማስፈጸም አላማው እንዳለው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የ2011 የሁለቱን ምክር ቤቶች የስራ ዘመን በከፈቱበት የጋራ ስብሰባ ላይ “…ተገቢውን ድርድር በማቅረብ፣ በፓለቲካ አመራሩ ቅርብ ድጋፍ፣ ያገራችንን ባስጠበቀ ሁኔታ እና በተቀናጀ አሠራር [በሚቀጥለው ዓመት ወደ አለም ንግድ ድርጅት የመቀላቀል] ሒደቱን ከግብ ለማድረስ ይሠራል” በሚል ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት ስለ ዓለም አቀፍ ንግድ ግንኙነቶች፣ ስለድርጅቱ ምንነት፣ ወደ ድርጅቱ ለመቀላቀል ስለሚኖረው ሒደት እና ኢትዮጲያ ድርጅቱን በመቀላቀሏ ስለሚገጥማት ስጋት እና ተስፋ የመወያያው ጊዜ አሁን ነው።የአለም ንግድ ድርጅት አመጣጥየአለም ንግድ ድርጅት (WTO) የተቋቋመው በታህሳስ 23 ቀን 1987 ዓ.ም ነው። መቀመጫውን በጄኔቫ፣ ሲዊዘርላንድ ያደረገው የአለም ንግድ ድርጅት የተቋቋመው የእቃዎች(goods) ንግድ ግንኙነቶችን በሚያስተዳደር የሕግ ማእቀፍ ውስጥ በተደረጉ ድርድሮች ነበር። ለሕግ ማዕቀፉ መሠረት የሆነው ደግሞ በሀገራት መካከል የሚደረጉ የንግድ ግንኑነቶች በሁለትዮሽ ስምምነቶች ላይ ብቻ የተመሰረቱ በመሆናቸው፣ ሀገራት በተመረጡ ሀገራት እና እቃዎች ላይ አድሎዋዊ የማስገቢያ ቀረጦችን(ታሪፍ) በመጣል፣ የመጠን ገደብ (ኮታ) በማድረግ እና የተወሳሰቡ የፍቃድ አወጣጥ አካሄዶችን በማስቀመጣቸው ምክንያት የተፈጠረውን የአለም አቀፍ ንግድ መዛባት ተከትሎ ነበር።አድሎዋዊ የሆነው የአለም አቀፍ ንግድ ሂደት በተለየ፤ በ1930ዎቹ አሜሪካ የደረሰባትን ከፍተኛ የንግድ መቀዛቀዝ (Great Depression) ተከትሎ ባወጣችው የታሪፍ ሕግ (US Tariff Act) በበለጠ እንዲጋጋል ሆኖአል። ይህ የተዛባ፣ አግላይ እና አድሎአዊ የንግድ ሂደት፣ በአውሮፓ እያበበ ከመጣው የፋሺዝማዊ አስተዳደሮች ጋር ተቀላቅሎ ለሁለተኛው የአለም ጦርነት ምክንያት መሆኑ ይነገራል። የሁለተኛው የአለም ጦርነትን መገባደድ ተከትሎ የአለም አቀፍ እቃዎችን ንግድ የሚያስተዳድር ስምምነት(General Agreement on Tariffs and Trade/GATT) በመስከረም 19 ቀን 1940 ዓ.ም በ23 ሀገራት እንዲፈረም እና በታህሳስ 22 ቀን 1940 ዓ.ም ተፈጻሚ እንዲሆን ተደርጓል። ይህንን ስምምነት የሚያስፈጽም ድርጅታዊ ተቋም ለመመስረት የተደረገው ሙከራ ግን በአሜሪካ ምክር ቤት ጣልቃ ገብነት ሳይሳካ ቀርቷል። ነገር ግን በሕግ ማእቀፉ ላይ በተመሰረተ ጊዜያዊ ተቋም ስር ስምንት የተለያዩ ድርድሮች ተካሄደዋል። ድርድሮቹ በተለየ ታሪፍ ላይ ትኩረት ያደረጉ ሲሆኑ፣ በኡራጋይ የተካሄደው 8ኛው ድርድር ግን እንደሌሎቹ በታሪፍ ላይ ብቻ የተገደበ እንዲሆን ጊዜው አልፈቀደም። የቀዝቃዛው ጦርነት መገባደድ እና የቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት መበታተን፣ የአእምሮአዊ ንብረቶች ጉዳይ ወደ ንግዱ ዓለም መምጣት እና በአፍሪካ ሀገራት እየታየ የመጣው የገበያ ተኮር ኢኮኖሚ ድርድሮች መሻት፤ ሀገራቱ ቋሚ የሆነ የዓለም ንግድ ድርጅት እንዲመሰረቱ እና ከቁሳዊ እቃዎች ንግድ ባሻገር የአገልግሎት ንግድን እና የአእምሮአዊ ንብረቶችን ጉዳይ ያካተተ የሕግና ተቋማዊ ማእቀፍ እንዲመሰርቱ ምክንያት ሆኖአል።ስለ አለም ንግድ ድርጅት በጥቂቱየዓለም ንግድ ድርጅት ከቁሳዊ እቃዎች ንግድ ባሻገር የአገልግሎት እና አእምሮዋዊ ንብረቶችን የሚመለከቱ እና ሌሎች ሰፋፊ ስምምነቶች አካትቶ፣ አንዱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተለየ ክፍል (Specialized Agency) ሆኖ በ1987 ዓ.ም ተመሰረተ።ድርጅቱ ሶስት ዋና መዋቅራዊ ክፍሎች አሉት - የድርጅቱ ከፍተኛ አካል የሆነውና ሁሉም ሀገራት የሚወከሉበት የሚንስትሮች ካውንስል፣ የሙያዊ ስራዎችን የሚሰራ አጠቃላይ ካውንስል እና የድርጅቱን የቀን ተቀን አስተዳደራዊ ስራ የሚሰራ ሴክሬታሪያት። የድርጅቱ ጥቅም በጠቅላላው፤ የሀገራት የንግድ ስምምነቶችን ማስተዳደር፣ ለንግድ ድርድሮች ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ በአገራት ንግድ ዙሪያ የሚነሱ አለመግባባቶችን መፍታት እና የሀገራትን የንግድ ፖሊሲ መመርመር ነው።አላማውም በሀገራት መካከል ያልተገደበ፣ ነጻ የንግድ ግንኙነቶች መፍጠር የሆነው የአለም ንግድ ድርጅት፤ ይህን አላማውን የሚያስፈጽምባቸው አራት መርሆዎች አሉት - አድሎአዊ የሆኑ ንግዶችን መከልከል(trade without discrimination)፣ ግልጽነት እና ተገማችነት (transparency and predictable) ያላቸው የንግድ ሂደቶችን ማበረታታት፣ ሚዛናዊ የንግድ ውድድርን (fair competition) ማበረታታትእና የሀገራትን የልማት እና የኢኮኖሚ ማሻሻሎችን(development and economic reform)ማገዝ።አድሎአዊ ንግዶች ለመከልከል ሁለት መሰረታዊ አካሄዶች ሲኖሩት፤ የመጀመሪያው ከተለያዩ ውጪ ሀገራት የሚገቡ ተመሳሳይ እቃዎች ላይ የተለያየ የማስገቢያ ቀረጥ ከመጣልና የማስገቢያ ሂደቶች ከማስቀመጥ እና ወደ ሀገር ውስጥ ከገቡም በኃላ አድሎአዊ መመሪያዎችን ከመጠቀም መቆጠብ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከውጪ በገቡና በሀገር ውስጥ የተመረቱ እቃዎችን ላይ የተለያዩ የውስጥ አስተዳደርያዊ አካሄዶች አለመከተል ነው። ግልጽነት እና ተገማችነት ያላቸው የንግድ ፖሊሲ እና አካሄዶችን ሀገራት እንዲኖራቸው ሀገራት የውስጥ የንግድ ሕጎቻቸውን እና ፖሊሲዎቻቸውን መለወጥ/ማሻሻል የሚችሉት በድርጅቱ ስር በሚደረግ ድርድር ብቻ ይሆናል። ሚዛናዊ የንግድ ውድድሮች የሚበረታተቱት ሀገራት በአለም አቀፍ ገበያ የሚቀርቧቸውንእቃዎች ከመደጎም እንዲቆጠበ በመከልከል ነው። ድርጅቱ ከዚህ ባሻገር በተለያዩ አጋጣሚዎች ሀገራት የውስጥ ሕጋቸውን እና ፖሊሲያቸው ነጻ ገበያን እና ፍትሃዊ ተወዳዳሪነትን የሚያበረታቱ እንዲሆኑ እና ከድርጅቱ ሕግጋትም ጋር እንዲጣጣሙ ሆነው እንዲያሻሻሉ ያግዛል።የአለም ንግድ ድርጅትን የመቀላቀል ሒደት - የኢትዮጲያ አካሄድ በተለየበዓለም ንግድ ድርጅት መመስረቻ ስምምነት አንቀጽ 12 መሠረት ሀገራት ወደ ድርጅቱ መቀላቀል የሚችሉት፤ የድርጅቱን ሕግጋት ለመፈጸም ፍቃደኛ ሲሆኑ እና ከድርጅቱ አባል ሀገራት ጋር በሚደረግ ስምምነት ነው። ሀገራት ወደ የዓለም ንግድ ድርጅት ለመቀለቀል የሚያደረጉት ሒደት እንደሌሎቹ የአለም አቀፍ ድርጅቶች ቀላል አይደለም። ይልቁንም እራሱን የቻለ ዝርዝር እና ውስብስብ ሂደቶች ያሉት ሲሆን የመቀላቀል ሂደቱ የሚፈጸመው ከአባል ሀገራቱ ጋር በሚኖር ተከታታይ ድርድር ነው።በጠቅላላው ወደ አለም ንግድ ድርጅት የመቀላቀል ሂደት በ4 ደረጃ ይቀመጣሉ - 1) በመጀመሪያ መቀላቀል የሚፈልገው ሀገር ለድርጅቱ ሀላፊ ያመለክታል፣ ይህንንም ተከትሎ የባለሙያዎች ስብስብ(ኮሚቴ)ይቋቋማል፣ 2) የኩነቶችን የማጣራት ደረጃ በሚለው ላይ ደግሞ ሀገራቱ በንግድ ግንኙነት ዙሪያ ያላቸውን ሕግጋት እና ፖሊሲዎች ለተቋቋመው የባለሙያ ስብስብ እንዲያቀርቡና ከድርጅቱ ሕግጋት ጋር የሚጣጣምበትን ሁኔታ እንዲጠና ይሆናል፣ ከድርጅቱ አባል ሀገራትም ተከታታይነት ያላቸው የጥያቄ እና መልስ ሂደቶች ይኖራሉ 3) የሁለትዮሽ እና የብዙሃን ድርድሮች እና ስምምነቶች በሚፈጸሙበት ሂደት ላይ ወደ ድርጅቱ ለመቀላቀል የሚፈልገው ሀገር ለአባል ሀገራቱ ገበያውን ክፍት የሚያደርግበት አካሄድ ላይ ስምምነት የሚፈጽምበት እና የድርጅቱ ሕግጋት እና መመሪያዎችለመፈጸም ያለውን ፍቃደኝነትየሚያሳይበት ደረጃ ነው 4) በመጨረሻም ሀገራቱ ወደ ድርጅቱ እንዲቀላቀሉ የሚደርግበት አካሄድ ሲሆን፣ በዚህም የተቋቋመው የባለሙያዎች ኮሚቴ መቀላቀል የሚፍልገው ሀገር ድርጅቱን ለመቀላቀል የሚጠበቅበትን ሁኔታዎች እንዳሟላ በመግለጽ ለሚንስትሮች ካውንስል የሚያቀርብበት እና አባል ሀገራቶቹም በሁለት ሦስተኛ አብላጫ ድምጽ ሀገሩ ወደ ድርጅቱ እንዲቀላቀል የሚወሰንበት አካሄድ ነው።ኢትዮጲያ ወደ አለም ንግድ ድርጅት ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረበችው በታህሳስ 1995 ዓ.ም ነበር። ይህንንም ተከትሎ የባለሙያዎቹ ስብስብ ኮሚቴ ከአንድ ወር በኃላ ተቋቁሟል። በንግድ ግንኑነት ዙሪያ ያላትን ሕግጋት እና ፖሊሲዎች እንዲጣራ አጠናቅራ ያስገባቸው ደግሞ በሕዳር 1999 ዓ.ም ነበር። ከዚህ በኃላም ከሚያዚያ 1999 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 2004 ዓ.ም ድረስ ከአባል ሀገራቱ፤ በተለየ ከአሜሪካ፣ ካናዳና የአውሮፓ ህብረት ሀገራት አራት ዙር ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን ኢትዮጲያም ለመጀመሪያዎቹ ሦስቱ ምላሽ አቅርባ፣ በሚያዚያ 2004 ዓ.ም ላይ ለቀረበው የአራተኛ ዙር ጥያቄ ግን ምላሽ አላቀረበችም።ኢትዮጲያ ወደ ድርጅቱ ለመቀላቀል የሚጠበቅባትን ሁኔታዎች ማሟላቷን የሚያጣራው የባለሙያዎቹ ኮሚቴም ሦስት ጊዜያት ተገናኝቷል። ሒደቱ ላለፉት 6 ዓመታት የቆመ ሲሆን አሁን ላይ ግን ኢትዮጲያ እንዲቀጥል ጥያቄ ማቅረቧን ሪፖርተር የተባለው የሀገር ውስጥ ጋዜጣ የዓለም ባንክ የመረጃና የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተሩን አቶ ኪዝሮልዌል ጠቅሶ ዘግቧል።የኢትዮጲያ ወደ አለም ንግድ ድርጅት የመቀላቀል ተስፋ እና ስጋቶችኢትዮጲያ የአለም ንግድ ድርጅትን በመቀላቀሏ ምክንያት የሚገጥሟት፣ በጥልቀትና ሙያዊ ትንታኔዎች መታየት የሚኖርባቸው፣ በዚህ ጽሁፍም ሊጠቃለሉ የማይችሉ ተስፋ እና ስጋቶች አሉባት። ውይይት እንዲጀመር በማሰብ ይህ ጽሑፍ ከብዙ በጥቂቱ ለማየት ይሞከራል።በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ኢትዮጲያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሻለና ያልተገደበ የገበያ አማራጭ ልታገኝ ትችላለች። ነገር ግን ኢትዮጲያ ካላት የምርት መጠን ትንሽነት አንጻር ተጠቃሚነቷ እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም።አሁንም አባል ሳትሆን ኢትዮጲያን ጨምሮ በተለዩ እቃዎች ላይ ያለምንም ወይም በቅናሽ ታሪፍ እቃ ለመላክ የተዘጋጀውን በአሜሪካ የቀረበውን የአፍሪካ እድገት እና እድል አካሄድ (Africa Growth and Opportunity Act/AGOA) እና በአውሮፓ ሕብረት የተሰጠውን ከጦር መሳሪያ ውጪ የቁሳዊ እቃዎችን የማስገባት (Everything But Arms/EBA ) አካሄድ ኢትዮጲያ ከሌሎች ሀገራት አንጻር ተጠቃሚነቷ አነስተኛ ነው።በድርጅቱ የሚቀመጡ የጥራት እና የማሸጊያ ስታንዳርዶችም ለኢትዮጲያን የውጪ ንግድ ገደብ ናቸው። የኢትዮጲያ አባልነት የንግድ ፖሊሲዋን ግልጽ እና ተገማች ስለሚያደርገው በውጪ ነጋዴዎች ዘንድ እምነት እንዲያድርና የውጪ ንግድን በብዛት የመሳብ ትልሟን ሊያበረታታ ይችላል።ኢትዮጲያ ካለችበት የኢኮኖሚ ደረጃ በንግድ ምክንያት የሚነሱ አለመግባባቶችንም ከተቋም ውጪ ለመፍታት በቂ የመከራከሪያ አቅም ስለማይኖራት በአለም ንግድ ድርጅት መቀላቀሏ ፍትሃዊ የፍርድ ሂደት የምታገኝነትን አጋጣሚ ይፈጥርላታል።ከውጪ የሚገቡ እቃዎች ላይ ከፍተኛ ግብር በመጣል እና ወደ ውጪ የሚላኩ እቃዎች ላይ ዝቅተኛ ግብር በመጣል፣ ኢትዮጲያ የወደውጪ እቃ ላኪዮችን ንግድ ለማበረታታት እና ከውጪ የሚላኩ እቃዎችንም በአገር ውስጥ በሚመረቱ ለመተካት የምታደርገውን ጥረት ይገታባት። የአለም ንግድ ድርጅት አባልነት በንግድ ዘርፎች ላይ አድሎን ስለሚከለክል፣ ኢትዮጲያ ለተለዩ፣ ለሀገሪቷ ቀዳሚ ለምትላቸው ንግዶች የውጪ ምንዛሬ የምታቀርብበትን አካሄድም እንድታቆም ትገደዳለች። ኢትዮጲያ ከውጪ የሚገቡ እቃዎች ላይ የሚጣሉ ግብሮችን(ታሪፍ) የመቀነስ/የማጥፋት ኃላፊነት ስለሚኖርባት በሀገር ውስጥ ያሉ ትናንሽ አምራች ድርጅቶች መወዳዳር እንዲያቅታቸው፣ ከገበያውም እንዲወጡ ምክንያት ይሆናል። በአገልግሎት ንግድ ዙሪያም ኢትዮጲያ በዜጎቿና በመንግስት ብቻ እንዲሰሩ የተተዉ ዘርፎችን እድትከፍት መገደዷ የሀገር ውስጥ የአገልግሎት ተቋማት ካላቸው ተወዳዳሪነት አንጻር፣ በተለይ ለዜጎች ብቻ የተተዉ የፋይናንስ የአገልግሎት ዘርፎችን ተወዳዳሪነት አደጋ ውስጥ ሊከትና ከገበያም ሊያወጣቸው ይችላል።አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው በለንድን የኢኮኖሚክስ እና ፖለቲካ ሳይንስ ት/ቤት ፌሎ የሆኑት ዶ/ር እዮብ ባልቻ ኢትዮጲያ ወደ ወደ አለም ንግድ ድርጅት መቀላቀሏ “በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኘው አብዛኛው የሀገራችን የገጠርና የከተማ ህዝብ የትኛውንም ዓይነት የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ምርትን አምርቶ እንዳይገበያይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል። በቆሎና ስንዴ አምርተው የሚኖሩ ኢትዮጲያዊ አርሶአደሮች በአውሮፓና በአሜሪካ በከፍተኛ ቴክኖሎጂና የገንዘብ ድጋፍ ታግዘው ምርታቸውን በገፍ እና በርካሽ በሚያቀርቡ አምራቾች ይዋጣሉ። ይህንን ምሳሌ ይዘን ሌሎችም የምርትና የአገልግሎት ዘርፎችን ብናይ ተመሳሳይ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ማንሳት ይቻላል” ይላሉ።ወደ ሀገር ውስጥ እቃዎች ሲገቡ የሚከፈሉ ግብሮች መቀነሳቸው በመንግስት ሀብት ላይምየሚኖረው አሉታዊ አስተዋጾ ከፍተኛ ነው። ኢትዮጲያ ካለባት የጠንካራ ተቋማት እና ብቁ የንግድና ኢኮኖሚ ባለሙያዎች እጥረት አንጻር እንደ ድርጅቱ አባል ለሚደረጉ ድርድሮች ዝግጁነቷም አጠያያቂ ነው። በአእምሮዊ ንብረት ዘርፉም ኢትዮጲያ በውጪ የተሰሩና የአእምሮአዊ ፍቃድ ያገኙ ንብረቶች ወደ ሀገሯ አስገባታ እንድታመርት እገዳ ስለሚጥል ኢትዮጲያ የያዘችውን የቴክኖሎጂ ልውውጥ ስራ ይገድባል።በፖለቲካው ዘርፍ ኢትዮጲያ የምትከተለውን የልማታዊ መንግስት የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ አካሄድ እንደትከልስ የምትገደድበት አጋጣሚም ይፈጠራል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚቀረጹ የንግድ ተኮር ፖሊሲዎችም ይገደባሉ። እንደ ዶ/ር እዮብ አገላለጽ “የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን ማለት የመንግስትንና የህዝብን በልማት ላይ ያላቸውን ቀጥተኛና ወሳኝ ውሳኔ ሰጪነት ማጣት ብቻ ሳይሆን ሉዓላዊነትን ማስረከብም ጭምር ማለት ነው። ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ከሚያስከትላቸው አሉታዊ ተጽዕኖዎች አንዱ ሉዓላዊነትን መሸርሸር (ትርጉም ማሳጣት)ነው።” ኢትዮጲያ ሕግጋቶቿን፣ ተቋሞቿን እና ፖሊሲዎቿን ከድርጅቱ ጋር ለማጣጣም፣ የአገልግሎት ንግዶችን ነጻ ለማድረግ፣ የተለያዩ የደረጃ፣ ንጽህና፣ እና የግብር አካሄዶችን የሚከታተሉ ተቋማት ለማቋቋም እና ከአባላትነት በኃላ በሚኖሩ ተከታታይ ድርድሮች ውስጥም ለመሳተፍ የምታወጣው የገንዘብ ወጪም ቀላል የሚባል አይደለም።በአጠቃላይ የዶ/ር አብይ አስተዳደር ወደ አለም ንግድ ድርጀት ለመቀላቀል ከመቻኮሉ በፊት ሀገሪቷ አሁን ካለችበት ኢኮኖሚ አንጻር ስጋቶቹን እና ተስፋዎቹን በጥልቅ መመርመር እንደሚኖርበት የዘርፉ ባለሙያዎች ያሰፍሩበታል። የሀገሪቷን ጥቅም ለማስጠበቅም ሆነ አባል ከሆነች በኃላ ኃላፊነቶችን በቀላሉ ለመወጣጥ እንዲቻል የእውቁልኝ ሳይሆን ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት፣ ማለትም የመንግስት ተቋማት ተወካዮችን፣የሕግ ባለሙያዎች፣ ምሁራን እና የግሉ ንግድ ዘርፍ እውነተኛ ተሳትፎ በሒደቱ ውሰጥ መኖር አስፈላጊነት አያጠያይቅም።

አስተያየት