ኅዳር 6 ፣ 2011

በግንባታ ላይ የሚደርሱ አደጋዎች

ወቅታዊ ጉዳዮችፊቸር

ከሁለት ቀናት በፊት፣ ረቡዕ ጥቅምት 28 የቀን ሠራተኛ የሆነው ማስረሻ የተባለ ወጣት መገናኛ አካባቢ በመሠራት ላይ ከሚገኘው የ40/60 ኮንዶሚኒየም ሕንፃ…

በግንባታ ላይ የሚደርሱ አደጋዎች
ከሁለት ቀናት በፊት፣ ረቡዕ ጥቅምት 28 የቀን ሠራተኛ የሆነው ማስረሻ የተባለ ወጣት መገናኛ አካባቢ በመሠራት ላይ ከሚገኘው የ40/60 ኮንዶሚኒየም ሕንፃ ላይ ከ17ኛ ፎቅ ላይ ወድቆ ሕይወቱ አልፏል። የረቡዕ የመገናኛ አሳዛኝ ክስተት በርካታ የቅርብና የሩቅ ጊዜ የግንባታ ላይ አደጋዎችን ያስታውሰናል። ከሦሥት ወራት በፊትሐምሌ 18 ቀን በባህዳር ከተማ የህንፃ መወጣጫ ተደርምሶበግንባታ ላይ የነበሩ 20ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው የቅርብ ትውስታ ነው። በአዲስ አበባ የሚገነቡት ሕንፃዎች ቁጥር ከሌሎች ከተሞች በእጅጉ እንደመብለጣቸው አደጋዎቹም ቢበዙም፤ በሁሉም የኢትዮጵያ ከተሞች ላይ በሕንፃ ግንባታ ላይ የሚደርሱ አደጋዎች ያለማቋረጥ ይሰማሉ። አዲስ አበባችንም ረጃጅም ህንፃዎቿን በላይ በላይ ከመገንባት ቦዝና አታውቅም። ቀን ቀን ለወትሮው ከምናያቸው የቤት አውቶሞቢሎች ጋር የግንባታ (ኮንስትራክሽን) ተሸከርካሪዎች እንቅስቃሴን ማየትም እንግዳ ትዕይንት አይደለም።በመዲናችን አዲስ አበባ፣ በአራዳ ክፍለ-ከተማ የሚገኝ በተለምዶ እሪ በከንቱ የሚባል ሰፈርአለ። ዳገታማና ቁልቁለታማ የሆነው ይሄ ሰፈር ለስያሜው መነሾ የሆኑ ከአስርተ ዓመታት በፊትየተፈፀሙ የዝርፊያና የሌብነት ታሪኮች አሁንም ድረስ በአካባቢው ነዋሪዎች ይተረካሉ። እሪ በከንቱ ዛሬም ቢሆን እንደድሮው በዝርፊያ ሳይሆን በግንባታ ላይ በደረሱ አደጋዎች ዋይታ ስሙ ይነሳል። ከአስራ አምስት ቀናት በፊት ሰኞ ጥቅምት 12 ማለዳ ላይ የደረሰው አስደንጋጭ አደጋ ከነዚህ አንዱ ነው። በአከባቢው ላይ እየተገነባ ያለ አንድ የህንፃ መወጣጫ ደረጃተደርምሶ በ8 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል። አደጋዎቹ እየቀነሱ አይደለም።በፍጥነት እየጨመሩና እየተስፋፉ የመጡት ግንባታዎቹ ለከተማዋና ለሀገር ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋፅዖና የሚኖራቸው ምጣኔ-ሃብታዊ ሚና ትልቅ ቢሆንም፤ የግንባታ ዘርፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያሻው የተዘነጋ ለመሆኑ በየዕለቱ የሚደርሱት አደጋዎች ማስረጃ ናቸው። ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያ ባለስልጣን የተገኘ መረጃ እንደሚያመለከተው በ2008ዓ.ም በግንባታ ወቅት 8 ሰዎች ላይ የሞት እናበ8 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሷል። በ2009 ዓ.ም ከ83 በላይ ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሷል። በ2010 ዓ.ም በ20 ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል። የ2011 ዓ.ም ከተጀመረበ 3 ሰዎች ላይ የሞትና በ12 ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል።ግርማ ገንዘቤ (ስሙ የተቀየረ)በግንባታ ዘርፍ ከተሰማሩት ወጣቶች አንዱ ነው። በሥራ ላይ እያለ የደረሰበትን አደጋ “የዛሬ ስምንት ወር ገደማ በተለምዶ ቱሉ ዲምቱ አካባቢ የማህበር ቤቶች ግንባታ ውስጥ የቀን ስራ በምሰራበት ግዜ፣ ከጠዋቱ አራት ሠዓት ገደማ ለመሰረት የሚሆን እንጨት እኔና የሥራ አጋሬ ወደ መሬት ውስጥ በማስገባት ላይ ባለንበት ወቅት የስራ አጋሬ በትልቅ መራጃ እንጨቱን ስቶ እጄን መትቶኝ በደረሰብኝ አደጋ አውራ ጣቴ ከጥቅም ውጭ ሆናል” ሲል የደረሰበትን አደጋ ያስታውሳል።በግንባታ ላይ የሚደርሱት አደጋዎቹ ሁሉ ተመሳሳይ አይደሉም። ለአደጋዎቹ በርካታ መንስኤዎች ቢኖሩም የደህንነት አጠባበቅና መሠረታዊ የግንባታ ቅድመ-ሁኔታዎች ቁጥጥር ማነስ ለአደጋዎቹ መከሰት ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው። እ.አ.አ በ2013 ዓ.ም የዓለም የሥራ ድርጅት ባወጣው ጥናታዊ ሪፖርት መሠረት 2.34 ሚሊዮን ሠራተኞች በሥራ ላይ እያሉ በሚደርሱ አደጋዎች ሳቢያ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ አመልክቷል። ሪፖርቱ በአማካኝ በየአስራ አምስት ሰከንድ የአንድ ሠራተኛ ሕይወት በሥራ ላይ በሚደርስ አደጋ ሳቢያ እንደሚቀጠፍም አስገንዝቧል።የኢትዮጲያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌድሬሽን ዋና ፀሀፊ የነበሩት አቶ ብርሃኑ ደሬሳ እንደገለፁት በግንባታ(ኮንስትራክሽን) ዘርፍ ላይ ያለው የሙያ ደህንነት አጠባበቅ ደረጃ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው። በተለይም የአሠሪዎች(ኮንትራክተሮች) በመንግስት የወጡ መመሪያዎች ተፈፃሚ አለማድረግ ለችግሩ መስፋፋት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አቶ ብርሃኑ ይጠቁማሉ።የቀን ሠራተኞች ስንክሳርበሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሙያ ደህንት ጤንነት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ መስፍን ይልማ እንደሚሉት በሀገራችን የግንባታ ኢንዱስትሪ ከ850 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥሯል። ነገር ግን በ2020ዓ.ም ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ እንድትሰለፍ የተቀመጠው ራዕይ እንዲሳካ የግንባታ (ኮንስትራክሽን) ተሳትፎ ትልቅ ሚና ቢኖረውም አሁን ባለውሁኔታ ግን በዘርፉ ላይ ያለው ችግር አስጊ ነው ብለዋል። በዘርፉ የተሰማሩት አብዛኛዎቹ ዕድሜያቸው ከ30 በታች ዓመት ሲሆን በተለያዩ የቅጥር ሁኔታ የሚሠሩ ሲሆን በጊዜያዊነት (በኮንትራክት) ለተወሰነ ጊዜ ወይም ለተወሰነ ሥራ የሚቀጠሩት ይበዛሉ። በዚህ መልክ የተቀጠሩ በርካታ የኮንስትራክሽን ሠራተኞች ከቀጣሪ ድርጅቶቻቸው ጋር በሚመሠርቱት የቃል/ የፁሑፍ ውል መሰረት በቀን ፤ በሳምንት ፤ በሁለት ሳምንት ወይም በወር (26 የስራ ቀናት) የታሰበ ወይም በቁርጥ ሥራ የተሰላ የደሞዝ ክፍያ ያገኛሉ።የሠራተኛና እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አዲስ ምዕራፍ በተሰኘው መጽሄቱ ላይ እንዳሰፈረው በግንባታ ዘርፍ ከተሰማራው የሰው ኃይል ከ54 በመቶ በላይ የሚገመተው አነስተኛ ወይም መካከለኛ ዕውቀት ያለው ሲሆን ከ10 በመቶ በታች የሚሆነው ደግሞ ከፍተኛ ሙያተኛ ተብሎ የሚመደብ ነው። እንዲሁም ከ28-30 በመቶ ያለው ሠራተኛደግሞ ማንበብና መፃፍ የሚችል ሲሆን በዋናነት የጉልበት ሥራ ተቀጣሪ ነው። የኮንስትራክሽን ዘርፍ አደጋ ስለባዎች አምራች ወጣቶች መሆናቸውሁኔታውን የበለጠ አሳሳቢ ከመሆኑም አልፎ በቤተሰብና በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖም ብርቱ እንዲሆን ያደርጋል። የሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የሙያ ደህንነትና ጤና ቡድን መሪ የሆኑት አቶ መስፍን ይልማምለሠራተኞች ደህንነት የተሠጠው ትኩረት አናሳ መሆኑንና ጠንካራ ተቆጣጣሪ አካልምማጣቱ አሳሳቢእንደሆነ ይገልፃሉ።በዘርፉ የተሠማሩት የጉልበት ሠራተኞች በየጊዜው የሚደርሱት አደጋዎች ቢያሰጋቸውም ለደህንነቶቻቸው ዋስትና የማስገኘት የድርድር ጉልበቱ ያላቸው አይደሉም። ከዚህ በተጨማሪም ለሕይወታቸው ስለሚሰጉ የግንባታ ሥራ ዘርፍን በመተው ወደ ሌሎች የሥራ መስኮች ለመቀላቀል ዕድሉ ያላቸው ሠራተኞች አይደሉም። ካዛንቺስ አካባቢ ለሆቴል አገልግሎት ለሚውል ባ15 ወለል ህንፃ ግንባታ ላይበጉልበት ሠራተኛነት ሲሠሩ ነው ያገኘናቸው ወ/ሮ አስናቀች ለገሠ እንደሚሉት “በቀን 70 ብር ቢከፈለኝም ለዕለት ቀለብ እንጂ ለቤት ኪራይ እንኳ ፈጽሞ አይበቃኝም። አልተማርኩም የተለየ ሙያም የለኝም፤ ስለዚህ የማገኘውን ክፍያ እንደ ጥሩ አመራጭ ይዠዋለሁ። ”የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በግንባታ ዘርፍ ላይ የተለያዩ ህግና ደንብ እንዲወጣ ያደረገ ሲሆን በዋናነት ትኩረቱን በደህንነትና ጤንነት ላይ ያደረገ አዋጅ ቁጥር 724/2001 መኖሩ ይታወቃል። በአዲስ አበባ አስተዳደር የሰራተኞችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በተለያዩ ጊዜያቶች የወጡየግንባታ ህጎች ቢኖሩም በተገቢ ሁኔታ ተግባሪዊ ባለመደረጋቸው አደጋዎቹየከፉእንዲሆኑአድርጓል። አሠሪዎች (ኮንትራክተር)እና የመንግስት አካላት ተጠያቂነታቸው ሙሉ በሙሉ አለመረጋገጡም አደጋው እንዲቀጥልና እንዲጨምር ከመፍቀዱም በላይ ሠራተኞቹ ዋስትና እንዳይኖራቸውም አድርጓል። በተጨማሪም አሠሪዎች የጥንቃቄ መሳሪያዎች አሟልተው አለማቅረባቸውየአደጋው መጠን እንዳይቀነስ፤ እንዲሁም ሊከላከሏቸው የሚችሉአደጋዎች ሞትና ከባድ የአካል ጉዳቶችእንዲደርሱ እየዳረጉ ነው። “አሠሪው ወደ ሥራ ከማስገባቱ በፊት የጥንቃቄ ቁሳቁስን ማሟላት አለበት የሚል ህግ አለ”የሚሉት የቢሮው ኃላፊ ዋነኛ ችግሩ የሕግ አለመተግበር መሆኑንይገልፃሉ። “ሕጉ ተግባራዊ አለመሆኑ ሰራተኞችን ለአካልጉዳትና ሞት እየዳረጋቸው ይገኛል” ሲሉምክፍተቱን ያሰረዳሉ። ሠራተኞችምቢሆኑ የጥንቃቄ ቁሳቁስ ሲቀርብላቸውስራውን ለምደነዋል፣ ምንም አንሆንም በሚል እንደማይጠቀሙበግንባታ ዘርፍ ላይ ያሉአሠሪዎች ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል።የችግሩን ዋነኛ ምክንያት ለማወቅ በርካታ ጥናቶች ቢካሄዱም፣ የተካሄዱት ጥናቶች ውጤቶችና ምክሮች ትግበራላይ የዋሉ አይደሉም። ከተካሄዱት የዳሰሳ ጥናቶች አንዱ በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተጠና ሲሆን የተካሄደውም በዋነኛነት በግንባታሥራዎች እየተስፋፉ ያሉበትን መጠን ለማወቅ ነበር። የሰራተኛ እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው አዲስ ምዕራፍ መጽሔት ቅጽ 7 ቁጥር18 የካቲት 2018 እንደዘገበውበጊዜያዊና በዋናነት የጉልበት ስራ እያገለገሉ ያሉ የግንባታ ሠራተኞች ቁጥር በዘርፉ ከተሰማሩ ሠራተኞች 89 በመቶውን እንደሚይዙ ተጠቁሟል። በኢንዱስትሪው የሚታየው የ“ሰብ-ኮንትራክቲንግ” (sub-contracting) አሰራር የቅጥር ግንኙነቶችን ውስብስብ እንዲሆኑ፤ በህግ መሰረት የስራ ላይ መብቶንች ከማስጠበቅ አኳያ ብርቱ ፈተናዎች እንዲገጥሙ ምክንያት እየሆነ ነው። ዘርፉ ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቅና በየጊዜው እያደገ ከሚሄደው የቴክኖሎጂ አሰራር ጋር ራሱን በማደራጀት የዘመናዊ መሣሪያዎች አጠቃቀምን የሚያስገድድቢሆንም ከሠራተኞች ደህንነት መጠበቅ እኩል የሠራተኞች ጤና እና መሠረታዊ ፍላጎቶች መሟላት ላይ በርካታ ችግሮች መኖራቸው ይገለፃል። አብዛኛዎቹየግንባታሥራዎች በውጭ(outdoor) የሚሠሩና ለተለያዩ የዓየር ንብረት ሁኔታዎች (ፀሀይ፤ ሙቀት፤ ብርድ፡ ዝናብ) የሚያጋልጡ ናቸው። ከከተማ ወጣ ብለው የሚካሄዱ የኮንስትራክሽን ስራዎች ከመጠጥ ውሀ ጀምሮ ለቢሮ አገልግሎት፣ ለግንባታ ሰራተኞች የመኖርያ አገልግሎት አቅርቦቶች፤ የመመገቢያ ፤ የመታጠቢያና የመፀዳጃ አገልግሎት፣ የጤና አገልግሎት መስጫ፣ የሸቀጣሸቀጥ መደብርና እንዲሁም የመዝናኛ ክበብ በማደራጀት ለሠራተኞች የተሟላ ማህበራዊ አገልግሎት የመስጠት ሀላፊነት አለባቸው። እነዚህ መሠረታዊ ፍላጎቶች ካለመሟላታቸው አልፎ በቂ እና ተመጣጣኝ ምግብ እንደማያገኙ የሚናገሩት የቀን ሰራተኞች፣ የጉልበት ሰራተኞች እንደመሆናቸው ከአንዱ ወለል ወደ ሌላ ወለል ሲሚንቶ፣ አሸዋና ሌሎች ቁሳቁሶች በመሸከም የሚያሳልፉት የስራ ውሎ እጅግ አድካሚና አታካች ከመሆኑ በተጨማሪ የሰውነት ጉዳት (የወገብ፣ የእግር መሸማቀቅ) እንደሚደርስባቸው ይናገራሉ።የሠራተኛና ማህበሪዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ የሙያ ደህንነት እና ጤና ቡድን መሪ አቶ መስፍን ይልማ እንደሚሉት ደህንነትን እንደ ሥራቸው አካል ቆጥረው በማያሠሩ አሠሪዎች ምክንያት የሚጠፋው የሰው ህይወት፣ እና የሚወድመው ንብረት እየጨመረ መሆኑን ይናገራሉ። የግንባታ (ኮንስትራክሽን) ዘርፍ ጥራት ያላቸው የግንባታ ግብአቶች ተጠቅሞ ደረጃውን በጠበቀና ህግ በሚፈቅደው መሰረት መወጣጫዎቹን ከብረት አዘጋጅተው፣ ሌሎች ለደህንነት የሚረዱ የጥንቃቄ አልባሳትን ተሟልቶ ወደ ሥራ ባለመግባቱ በሚደረሰውአደጋ አሠሪው ብቻ በዓመት የገቢውን 4 በመቶ ያጣል፤ ወይም ኪሳራ ይገጥመዋል። ይህ ኪሳራ ጉዳት በደረሰው ልክ ለማሳከም የሚወጣውን የህክምና ወጭ እንደማይጨምር ጠቅሰው፤ጠቅላላ ወጪው ሲደመር ኪሳራው ከዚያም በላይ መሆኑን ያመለክታሉ። አደጋውን ዜሮ ማድረስ ባይቻልም የተለያዩ የግንዛቤና የቁጥጥር ስራዎች በመስራት መጠኑን መቀነስ እንደሚቻል ግን አበክረው ይገልፃሉ።አሁንም በግንባታ መስክ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው የቀን ሠራተኛሁሉንም ስጋቶችና በደሎች ችሎ፣ ብሶቱን ዋጥ አድርጎ ኑሮውን ለማሸነፍ መጣጣሩን አላቆመም። ግንባታን ዋነኛ ትኩረቱ ላደረገው ኢንቨስትመንት ትልቅ ቦታ ቢሰጠውም ዛሬም የግንባታ አካሄዳችን ሰውን እንደዘነጋ እየተጓዘ ነው። በእሪ በከንቱም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች እየደረሱ ያሉት አደጋዎችም ቀጥለዋል። ማስረሻ በተባለው ወጣት ላይ ከሰሞኑ መገናኛ አካባቢ የደረሰው የሞት አደጋ ገና ሦሥት ቀኑ ነው። የጉልበት ሠራተኞቹ ስጋት ባያቋርጥም ከእጅ ወደ አፍ የሆነው ሥራቸውን ጥለው መሄድ ግን አይችሉም። የአደጋዎቹ ቁጥር ማሻቀብና የጉልበት ሠራተኞቹ የማያባራ ጥያቄ፣ የግንባታ ቁጥጥሮቹን በማጥበቅም ሆነ የጤናና የደህንነት ሁኔታዎቹን በማሻሻል ረገድ እምብዛም ለውጥ አለማምጣቱ የግንባታ ላይ ሠራተኞችን ዋይታ እሪ በከንቱ አድርጎታል።

አስተያየት