ኅዳር 10 ፣ 2011

የሕግ የበላይነት ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር

ርዕሰ ዕንቀጽ

አዲሱ አስተዳደር በትረ-ሥልጣኑን ከጨበጠ ወዲህ እንደ አድናቂዎቹ ባይበዙም በርካታ ተቺዎች አጋጥመውታል። መንግሥት የሚታማው በብዙ ጉዳዮች ነው። ከእኒዚህ…

አዲሱ አስተዳደር በትረ-ሥልጣኑን ከጨበጠ ወዲህ እንደ አድናቂዎቹ ባይበዙም በርካታ ተቺዎች አጋጥመውታል። መንግሥት የሚታማው በብዙ ጉዳዮች ነው። ከእኒዚህ ጩኸት ከበረታባቸው ጉዳዮች መካከል የሕግ የበላይነትን ማስከበር አንዱና ዋናው ነው ቢባል። ጠቅላይ ሚኒስተሩ አብዝተው ስለፍቅር፣ ስለመደመር ማውራታቸው በብዙዎች ዘንድ እንደገራገር እና የዋኅ አስቆጥሯቸው ነበር። አስተዳደራቸውም በሀገሪቱ ታሪክ ከታዩ ልፍስፍስ መንግሥታት ጋር እስከማወዳደር የደረሱ ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።ከሰሞኑ በተለያዩ ዜና ማሰራጫዎች የተላለፉት የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንቅስቃሴዎች ይህንን መረዳት የሚፈትኑ ሆነዋል። የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ህዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም. በጽ/ቤታቸው ለተገኙ ጋዜጠኞች እና በቀጥታ ስርጭት ለሚከታተሉ ዜጎች በሰጡት መግለጫ መንግሥት በከፍተኛ የሙስና ወንጀሎች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ወራት የፈጀ ምርመራ በማድረግ ተጠርጣሪዎችን ማሰሩን ገልጸዋል።መግለጫው ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮችን ይዟል። የመጀመሪያው ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር የተያያዘ ነው። ተጠርጣሪዎች ወደ መደበኛው የወንጀል ምርመራ ሂደት ውስጥ ከመግባታቸው በፊት  በብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አመራሮች እና አባላት በስውር እስር ቤቶች፣ እንዲሁም መደበኛው ምርመራ በፖሊስ ጣቢያ፣ በማረሚያ ቤቶች ማሰር እና የማሰቃት ተግባር መፈጸም፣ ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት እራሳቸውን እንዲያገሉ ማድረግ እና ማሰቃየት፣ በአንቡላንስ እያፈኑ ሰዎችን መሰወር፣ ህገወጥ መሳሪያዎችን የራሴ ነው ብሎ እንዲፈርሙ ማድረግ፣ የብልት ቆዳዎችን በፒንሳ መሳብ፣ ጫካ ማሳደር፣ ከአውሬ ጋር ማሰር፣ አፍንጫ ውስጥ እስክርቢቶ መክተት፣ ግብረሰዶማዊ ጥቃት መፈፀም፣ ሴቶችን መድፈር የመሳሰሉ ድርጊቶች መፈጸማቸውን ገልጸዋል።  ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጽ/ቤቱ ባሉት ማስረጃዎች እነዚህን ድርጊቶች ሲፈጽሙ ነበሩ ያላቸውን ከሠላሳ በላይ ባለሙያዎችን እና ኃላፊዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል።ሁለተኛው “ለውጥን እንደገፍ፣ ዴሞክራሲን እናበርታ”  በሚል መርሕ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድን ለመደገፍ በተደረገው ሰልፍ ላይ ፈንድቶ የዜጎችን ህይወት የቀጠፈው የቦንብ ጥቃት በቀድሞው ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ኃላፊ መቀናበሩን የገለጹበት ነው።ሦስተኛው ከፍተኛ የሆነ የሙስናና የምዝበራ ወንጀል ነው። ይህም የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በስድስት አመት ውስጥ በተፈጸሙ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ግዢዎች ጋር በተያያዘ የሀገርን ሀብት አባክነዋል ያላቸውን ከፍተኛ የኮርፖሬሽኑን አመራሮች እና ሠራተኞች (የኮርፖሬሽኑን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ) በቁጥጥር ማዋሉ ነው።በዚህ ሂደት መንግሥት እውቅና ሊሰጣቸው የሚገቡ በርካታ ሥራዎች እንዳከናወነ እናምናለን። የመጀመሪያው ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የዋሉበት ሂደት ነው። ከዚህ ቀደም በብዙ ክሶች እንደታየው መንግሥት ወንጀል የሚፈልገው እና ማስረጃዎቹን የሚያደራጀው ተጠርጣሪዎችን ከያዘ በኋላ ነበር።በርካታ ዜጎች የማያውቁት ወንጀል ፈጽመናል ብለው እንዲያምኑ በማስገደድ የማሰቃየት ተግባር መፈጸም የተለመደ ነበር። ከዚህ በተቃራኒው በዚህ ወቅት በባለሙያዎች ወራት የፈጀ ምርመራ ከተካሄደ በኋላ ተጠርጣሪዎችን እንደተያዙ መነገሩ በራሱ ትልቅ እርምጃ ነው። ይህ የንፁኃንን እንግልት የሚቀንስ፣ የሀገርን ሀብት ከኪሳራ የሚያድን እና ማኀበረሰቡ በፍትሕ ተቋማት ዘንድ ያለውን ተቀባይነት የሚያሳድግ ነው።ሌላው ተጠርጣሪዎቹ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከመሆናቸው በላይ በደኅንነት እና መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ባላቸው ኃላፊነት ምክንያት የማይነኩ ተደርገው ይቆጠሩ የነበረውን ግምት ያስቀረ እርምጃ መሆኑ ነው። ይህም ሕግ ዜጎችን ትንሽ ትልቅ ሳይል ሁሉንም እኩል ማየት እንደሚገባው የሚገልጸውን መርሕ በተግባር የሚያረጋግጥ ነው።ሌላው ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ባላቸው የፖለቲካ አመለካከት እና ማንነት ሳይሆን ፖሊስ ማስረጃ ሰብሰቤባቸዋሁ ባለው ወንጀሎች መሆኑ ሌላ እውቅና የሚገባው ጉዳይ ነው። እስካሁን ድረስ እንደታዘብነው አንድን ዘውግ ለይቶ ጥቃት የመፈጸም አዝማሚያ አለመኖሩ ይበል የሚያሰኝ ነው። ከመንግሥት የዜና አውታሮች እንደሰማነው የትግራይ ልዩ ፖሊስ የኮርፖሬሽኑን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፈን ይዞ ማስረከቡም ሊበረታታ የሚገባው ነው።በሌላ በኩል የመንግሥት የህዝብ ግንኑነት እንቅስቃሴ እንደወትሮው የሚያስገምት ሆኖም አግኝተነዋል። የመንግሥት ሚዲያዎች በዘመቻ መልክ የተጠርጣሪዎችን ሐጥያት አጉልተው ለማሳየት ተረባርበዋል። በቀድሞው አስተዳደር የተለመደው መንግሥት በሐሰት ክስ ሲመሰርት እንደሚያደርገው የዘጋቢ ፊልም ተሠርቶ ወደ ሕዝብ ደርሷል።ይህም ተጠርጣሪዎቹ አስተያየታቸውን ሳይጠየቅ ወይም በሕግ አማካሪያቸው በኩል ምላሽ ሳይሰጡ የአንድ ወገን ብቻ ትርክት ማቅረቡ የክስ ሂደቱ ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀርም። ይህም በለውጥ ሂደት ላይ እንዳለ የተዘገበለት የፍትህ ስርዓት ማጥራት ያለበት ነገር ነው። የማኀበረሰብ አስተያየት (public opinion) እና የፍርድ ቤት አስተያየት (judicial opinion) መናበብ ቢገባቸውም፣ ተጠርጣሪን በሕግ ፊት እንደነጻ ሰው የመታየት መብት በማያጣብብ መልኩ እንዲሆን መተማመን መፍጠር ያስፈልጋል። ይህ ከአሁን በኋላም በስፋት በሚዘገበው የፍርድ ቤት ውሎ ላይ ጥላውን ስለሚጥል ከወዲኹ ሊታሰብበት ይገባል።ጠቅላይ ሚኒስተሩ መንግሥት በዜጎች ላይ ላደረሰው በደል በደፈናው ይቅርታ መጠየቃቸው አይዘነጋም። ይሁንና ይህ ይቅርታ የመንግሥት ባለስልጣናት ለሠሩት ወንጀል በህግ ፊት ቀርቦ ከመጠየቅ የሚያድን ነው? ለይቶ የሚያድን ከሆነ የሚያድናቸው እና የማያድናቸው እነማን ናቸው?መለያ መስፈርቱ የተሠራው ጥፋት ወንጀልን የሚያቋቁም በመሆኑ እና ባለመሆኑ ነው ወይስ ተጸጽቶ ንስሐ በመግባት እና ባለመግባት ነው የሚወሰነው? እነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚሹ፣ ሀገሪቱ ወደ ዴሞክራሲ ልታደርገው ካለመችው ሽግግር ጋር በእጅጉ የተቆራኙ እና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ዐቢይ ሚና የሚጫወቱ ናቸው።

አስተያየት