ኅዳር 10 ፣ 2011

የግጭት ትርክቶችና አንድምታዎቻቸው

ፖለቲካ

እንደ መግቢያክፍል አንድየአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በአህጉሪቱ ውስጥ ካሉ ቀጠናዎች ሁሉ በከፍተኛ ደረጃ ግጭት የሚከሰትበት ነው፡፡ በተጨማሪም በአፍሪካ ፖለቲካ…

የግጭት ትርክቶችና አንድምታዎቻቸው

እንደ መግቢያ

ክፍል አንድ

የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በአህጉሪቱ ውስጥ ካሉ ቀጠናዎች ሁሉ በከፍተኛ ደረጃ ግጭት የሚከሰትበት ነው፡፡ በተጨማሪም በአፍሪካ ፖለቲካ ውስጥም በበርካታ ግጭቶች፣ጦርነቶች እና ዘር እና ቀለም ተኮር ብጥብጦች በሚገባ የሚታወቅ በቀላሉ የማይተነበይ (ያልተረጋጋ) ሁኔታ ፣ ርስ በርሱ በጠላትነት የሚፈራረጅ ማኅበረሰብና በዚህም የተነሳ በዕድገትና ልማት ኋላቀርና ደካማ አካባቢ ነው፡፡ወደአገራችን ኢትዮጵያ ሁኔታ ስንመጣም ከአጠቃላይ የአህጉሪቱ ቀጠናዎች በተለየ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ በርካታ ቋንቋዎች ናነገዶች የሚሸፍን ማኅበረሰብ ያቀፈ በመሆኑ የተነሳ በበርካታ በመንግስታትና ግዛቶች መካከል የተካሄዱ ማኅበሰረባዊ አለመግባባቶችንና የርስበርስ ግጭቶችን ሲከፋም ደም አፋሳሽ ጦርነቶችን አስተናግዷል፡፡ ተቋቁሟልም፡፡ ምንም እንኳን ማኅበረሰባችን እርስበእርሱ በማኅበራዊ፣ ባሕላዊና ኢኮኖሚያዊ ድሮች በጥብቅ የተያያዘ ቢሆንም ግጭቶች በተለያዩ ደረጃዎች ማለትም ቀጥተኛ ክልላዊ ግጭቶች እና የጦር ግጭቶችን ጨምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍለ-ሀገሮች የእርስ በእርስ ጦርነቶች እና የመሬትና ሃብት ይገባኛል፣ የብሔር ማንነት ጥያቄዎች እና የልዩ ልዩ ማህበረሰቦች ግጭቶች ሲከሰቱ ቆይተዋል፡፡ የግጭቱን አውድ ሰፋ ባለ መልኩ ስናየው ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ በተለይም ኢትዮጵያ ካላት ጂኦ-ፖለቲካዊ ፋይዳ ለዩናይትድ ስቴትስ፣ አውሮፓ እና የአረቡ ዓለም የፖለቲካ አመክንዮነት የስበት ማዕከል በመሆኗ በተደጋጋሚ በሚፈጠሩ የግጭት ክስተቶች ምክንያት በግጭት ተሳትፎ አሊያም ሠላምን በማስከበር በዓለም ዙሪያ ትኩረት አግኝታለች፡፡በመሆኑም በአገራችን ለሚከሰቱት ግጭቶች የመፍትሔው ማዕቀፍ መታየት ያለበትአገሪቱ ከሌላው የአህጉሪቱና ዓለም ክፍል ጋር በታሪክ ፣በፖለቲካ ስርዓት፣ በሃይማኖት ቁርኝት እና በምጣኔ ሃብት ግንኙነት ረገድ ያላትን ትስስር ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን ይገባዋል፡፡ በአገራችን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በበርካታ አካባቢዎች ከፍተኛ ብሔር ተኮር የማንነት ማግለልና ግጭቶች፤ ደም አፋሳሽ አመጾች በተለያየ ጊዜና ጥልቅት እየተፈጸመ በማኅበረሰቡ መካከል መቃቃር ተፈጥሯል፡፡ ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ ማኅበረሰብ መካከል ያለው የቀድሞ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ እንዲሁም ምጣኔ-ሃብታዊ ትስስር፣ የአኗኗር ዘይቤና የአብሮነት ስነ-ልቦና ተሰበሯል ማለት አይደለም፡፡ በመካከላቸው ያለው ትስስር እየላላና እየቀነሰ ቢመስልም እንደ የውጭ ወረራና ጦርነት በመሳሰሉ በድንገተኛ አደጋ ጊዜያት ተመልሶ ሊጠነክር ይችላል፡፡ የአገራችን የረጅም ዘመን ታሪክ እንደሚያስረዳው ግጭቶች በተለያዩ ደረጃዎችና ማኅበራዊ መስተጋብሮች ተካሂደዋል-ክፍለሀገር፣ ክልል እና አካባቢያዊ እንዲሁም ግጭቱ የተለያዩ አካላትን አካቷል-መንግሥታት፣ ብሔራዊ ቡድኖች፣የሃይማኖት ቡድኖች እና የማህበረሰብ ወይም የጎሳ ማንነት ቡድኖች ሲሆኑ እነዚህ ግጭቶች ከውጭና ከውስጥ ኃይሎች ከፍተኛ ድጋፍ ያገኛሉ፡፡ ሆኖም የአገሪቱ ዜጎችን የአብሮነት ድር በጣጥሶ የመጣል አቅም ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡በአገራችን ውስጥ ግጭቶች በተደጋጋሚ በሚከሰትና አንዳንዴም ድንበር ዘለል በመሆን በአጎራባች አካባቢዎች ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ አቅም በማግኘት ውጤቱም በአጎራባች ክልሎች መካከል የኢኮኖሚና የንግድ ልውውጥ አለመረጋጋትን በመፍጠር፤ የዉስጥ-ስደተኞች ፍልሰት ያባብሳል፤ ለክልል ንዑስ ዞኖችና ወረዳዎች የደህንነት ስጋት ይፈጥራል፡፡ ስለሆነም ይህ ጽሑፍ በአገራችን ዉስጥ ያለውን የግጭት መንስኤ ከተለያየ አዉድ አንጻር በጥልቅ ማብራራትና በመተንተን የቢሆን ድምዳሜ ላይ ያተኩራል፡፡ በተጨማሪም ያለመረጋጋቱ ቀጣይ ሁኔታና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለመጠቆም ይሞክራል፡፡

የግጭት ብያኔ

ታዋቂዉ ሃንጋሪ-አሜሪካዊዉ የአካዳሚ፣ የሥነ-አእምሮ እና የሥነ-ሰብ ባለሙያ የሆነዉ ቶማስ እስቴፈን ስዛታዝ በአንድ አባባሉ እንዲህ ይላል፡- በእንስሳት ስርዓተ-መንግሥት ውስጥ የስርዓቱ ህግጋት መብላት ወይም መበላት ሲሆን በሰው ስርዓተ-መንግሥት ውስጥ ደግሞ መረዳት ወይም ማስረዳት ነዉ፡፡ ይህን አባባል የተጠቀምኩት ስለግጭት ብቁ ግንዛቤ እንዲኖረን ሃሳቡን ከሥሩ መረዳት አስፈላጊ መሆኑን ለማጠየቅ ነዉ፡፡ግጭት ምንድንነው? መነሻውስ? ግጭት እንዴት ይፈታል? ወዘተ ለሚሉ ጥያቄዎች ቀጥተኛና ወጥ መልስ መስጠት ቢያዳግትም በተለያዩ የግጭት መስኮች ጥናት የሰሩ ምሁራንን አጣቅሶ ስለጉዳዩ ማብራርያ መስጠት ይቻላል፡፡ የግጭት ምንነትን በተመለከተ በቀጥታ ወደ ባለሙያዎች ሙያዊ ብያኔ ከመግባት በፊት መዝገበ ቃላዊ ብያኔውን ማስቀደሙ የተሻለ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ተቋም ያዘጋጀው የአማርኛመዝገበ ቃላት ግጭትን ‹‹ጥል፣ ጠብ›› በሚል ይተረጉመዋል(1993፣ 510) የLeslu አማርኛ እንግሊዝኛ አውዳዊ መዝገበ ቃል ግጭትን ‹‹ትግል፣ ልዩነት፣ አለመስማማት፣ ጠብ፣ ውጊያ፣ ግጭት፣ አለመግባባት›› Lesiu (1973፣ 226)፡፡ በማለት ይበይነዋል፡፡ግጭት ሁለትና ከሁለት በላይ ተቃራኒ የሆኑ አስተያየቶችን ወይም መርሆዎችን በሚወክሉ ሰዎች፣ ተቋማት ወይም ቡድኖች መካከል የሚፈጠር አለመግባባት ነው፡፡ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ወገኖች ፍላጎቶቻቸው እርስበርስ የሚጣጣሙ ባለመሆናቸው ተቃውሞአቸዉን ለመግለጽ ወይም ሌሎች ተቃራኒ ወገኖችን በሚጎዱ ወይም በሚያገሉ እርምጃዎች ፍላጎቶቻቸውን ማሟላት ሲጀምሩ የሚፈጠር ነው፡፡ እነዚህ የግጭት ፓርቲዎች በተለያየ የማኅበረሰብ የትስስር ሰንሰለት የተዋቀሩ ግለሰቦች፣ አነስተኛ ወይም ትላልቅ ቡድኖች እና አገሮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ግጭት ፈርጀ ብዙ መግፍኤ ያለዉ በመሆኑ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች በተለያዩ መንገዶች እርስ በርስ ሊጋጩ ይችላሉ፡፡ እነዚህም፡-በሃብቶች፡- የአካባቢ፣ ገንዘብ፣ የኃይልምንጮች፣ ምግብ፣ ዉሃ፣ ማዕድንወዘተ….. ሐብት አስተዳደር እናእንዴትመከፋፈል እና መጠቀም እንዳለባቸው ባለመስማማት፤በስልጣን፡- በፖለቲካ ውሳኔ አሰጣጥ፣ የኃይል ቁጥጥርእናተሳትፎ አመዳደብ ላይ በሚፈጠር አለመግባባት፣በማንነት፡-ሰዎች እርስ በርስ የሚጣበቁበትን የብሔር፣ ባህላዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ የማንነት ማህበረሰቦችን በተመለከተ በሚፈጠር አተያይና ትርክት፣በማህበራዊ ደረጃ ከፍታ፡- ሰዎች በሰብዓዊነታቸዉ በአክብሮት እና በማዕረግ እንዴት መያዝ እንዳለባቸዉ እንዲሁም በባህላቸው እና በማህበራዊ አቋማቸው፣ ባላቸዉ አመለካከትና የክብር አያያዝ፤በእሴቶች፡- በተለይም በመንግስት፣ በሀይማኖት ወይም በርዕዮተ ዓለማዊ ስርዓቶች ውስጥ ባላቸዉ የአመለካከት እሴት ናቸው፡፡በሌላ በኩል ግን ግጭቶች በሃይል ግንኙነት መካከል በሚፈጠሩ ቅራኔዎች እና የተለያዩ አካላት እርስ በእርሳቸው በግለሰብ እና በቡድን ውስጥ በሚያደርጉት ግንኙነት እንዲሁም ከተፈጥሮ መሠረታዊ ውስንነት የተነሳ ሃብት ወይም ዕድሎች ፍለጋ ውስጥ የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ በአብዛኛዉ ጊዜ ግን ግጭት የሽግግርና ለዉጥ ማንቀሳቀሻ ሞተር ሲሆን ዉጤቱ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ይሆናል፡፡ እኩልነትን፣ ፍትሃዊነትን፣ ማኅበራዊ መሻሻል እና ስምምነትን ማረጋገጥ እንዲችል በብልሃት ሊለወጥ ይችላል አሊያም ወደ አስከፊ ሁኔታ ተለወጦ ከፍተኛ የጥቃት ስጋት ለመፍጠር አመቺ መንገድ ይሆናል፡፡

የግጭቶች ተፈጥሮአዊ ባህሪ

ታላቁ የሰላማዊ ትግል ስልት አባት ማኅተማ ጋንዲ ለግጭቶች አማራጭ መላ የምናበጅበትን መንገድ ሲጠቁም አይን ላጠፋ አይኑ ይጥፋ የሚለዉ ፍርደ-ገምድልነት ቢሰፍን መላዉ ዓለምን አይነስዉር ያደርጋል ይላል፡፡ ሌላኛዉ የሰላማዊ ትግል ፋና ወጊ አሜሪካዊዉ ማርቲን ሉተር ኪንግ (ጁኒየር) እንዲህ ይላል ለሁሉም ሰብዓዊ ግጭቶች የበቀል፣ የማጥቃት እና ትንኮሳ እርምጃዎችን የማይቀበሉ መፍቻ ዘዴዎችን በመጠቀም ረገድ የሰው ልጅ አስተሳሰቡ መሻሻል አለበት ለእንዲህ ዓይነቱ የግጭት መፍቻ ዘዴ መሠረቱ ደግሞ ፍቅር ነው፡፡በመሆኑም እርስበርስ የሚጋጩ ፍላጎቶች አካላዊና ስነልቦናዊ ጫና ወይም የኃይል ግፊት ሳይፈጽሙ ሊሟሉ ይችላሉ ምክንያቱም ሁሉም ግጭቶች አሰቃቂ አይደሉም፡፡ ግጭቶች ከተያዙ አዎንታዊ የለዉጥ መነሻ ክስተቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የአንዳንድ ወገኖች ተለዋዋጭ ፍላጎቶች ቀድመዉ ተለይተው በሚታወቁበት እና የግጭቱ ተዋናዮች ልዩነቶችን አክብረዉ በሚቀበሏቸው ጊዜያት እንደሚታወቀው ሁሉ የማህበረሰቦች ፍላጎትና የግጭት አስተሳሰቦች ሊለወጡ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ግጭቶች ሰላማዊና የአመጽ ግጭቶች በመሆን ሁለት መልክ ይይዛሉ፡፡

ሰላማዊ ግጭቶች

ተገዳዳሪ፣ ተመጣጣኝና ተወዳዳሪ ፍላጎቶችን ለማስተናገድ በሚያስችሉ የቁጥጥር ስልቶች ላይ መሰረት በማድረግ ይካሄዳሉ፡፡ ግጭቶችን መቆጣጠር የሚያስችሉ የተለያዩ መንገዶች ያሉ ሲሆን እነኚህም ብሔራዊሕገ-መንግሥቶችእናህጎች፣ የቤተሰብእናየጎሳ መዋቅሮች፣ የፍርድቤት የፍትሕ ስርዓቶች፣ የሃይማኖትሥነ-ሥርዓቶች እናባህላዊ ልምዶች፣ ክርክሮችእናውይይቶች (በሃገራችን እንደ አፈርሳታና አዉጫጭኝ) ከበርካታ የግጭት መፍቻ ስልቶች መካከል የተወሰኑት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በተጨማሪም ኢ-መደበኛ እና የዘልማድ ማህበራዊ ባህሎች እና ልማዶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሆኖም እነዚህ ኢ-መደበኛ ወግና ልማዶች በአንዳንድ ሃገራት ብሔራዊ የፅሑፍ ሕጎች ላይ እንደሚደረገው ሁሉ በተጨማሪነት መደበኛ እና ተቋማዊ አቋም ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ምርጫዎችና ሕዝብ ዉሳኔዎች ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱ ከሚችሉባቸዉ የተለመዱ አማራጭ መንገዶች ዉስጥ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ሰላማዊ የሆኑ የግጭት አፈታት መንገዶች ባህላዊ ወይም ዘመናዊ፤ አካባቢያዊ፣ አገር አቀፍ ወይም አለምአቀፍ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንደዚህ ያሉ ዘዴዎች የሚተገበሩባቸዉ በመላው ዓለም የሚገኙ ክልሎች እና ማህበረሰቦች “የሰላምቀጠናዎች” በመባል ይታወቃሉ። በአጠቃላይ እነዚህ ስልቶች እንደ እነዚህ ያሉ ማህበራዊ እና የብሔር ግጭቶች አጥፊ እና ጨካኝ ከመሆን እንዲቆጠቡ ይረዳሉ፡፡

የከረረ ግጭት

ሁለት ተጻጻሪ ወገኖች ተጨባጭ ግቦቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ለማሳካት ከሚፈልጉት በላይ በመሄድ ወይም በተጻራሪ ወገኖች ላይ የራሳቸውን ፍላጎት ጎን ለጎን ለማራመድ ከሚያስችላቸዉ መንገድ እላፊ በመሄድ ተቃራኒ ወገኖች ያላቸውን አቅም ለመቆጣጠር ወይም ለማጥፋት በሚሞክሩበት ወቅት የከረሩ ግጭቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡በዓለም ላይ በርካታ አመጽ በሚፈጠርበት ጊዜ አሰቃቂ ግጭት እና ማስገደድ  እንደ ተፈጥሮ ግዴታ ነው ብለን እናስብ ይሆናል ምክንያቱም ሰብአዊ ፍጡራን በተፈጥሮአቸዉ አይበገሬና ኃይለኛ ናቸው፤ እናም ጦርነቶች እና ግጭቶች የማይቀሩ የሕይወት ህልዎቶች ሆነዉ እስካለንበት ዘመን ዘልቀዋል፡፡በተቃራነዉ የሁላችንም ፍላጎት የተለያየ ቢሆንም እንኳን ሁሌም ሁከት ሊፈፀም አይችልም ማለትም ሁከት የማይቀር ሊሆን አይችልም፡፡ ጥቃቶች በአንዳንድ ሁኔታዎች መገኘት ወይም ያለመገኘት ላይ የተንጠለጠሉ ስለሆኑ መፍትሔዉን ከመፈለግ በላይ የግጭቶቹ መንስኤ፣ አያያዝና አስተዳደር ወሳኝነት አለዉ፡፡የከረሩ ግጭቶች የሚለዩበት የተለያዩ ፈርጆች አላቸዉ፡፡በዋና ዋናና ቋሚ ጉዳዮች ላይ አለመግባባት ወይም ፍላጎቶች መካከል በሚፈጠር ውጥረት፡- በተፈጥሮ ሀብት ውድድር፣ በመንግስት ሥልጣን ቁጥጥር፣ በክልል (አካባቢያዊ ቁጥጥር) ተፅዕኖ፣ የአገዛዝ ርዕዮተ ዓለሞች ወዘተ…..፣በሚሳተፉወገኖች፡- የጎሳ፣ የኃይማኖት ወይም ክልላዊ ማኅበረሰቦች፣ ክፍለ ሀገሮች ወይም የፖለቲካ አንጃዎች ወዘተ…..በሚጠቀሙት የኃይል ወይም የጭቆና አይነቶች፡- የኒዉክሌርጦርነት፣ መደበኛ ጦርነት፣ ሽብርተኝነት፣ አድማ፣ ጭቆና፣ የዘርማጥፋት፣ የሰብአዊመብትጥሰቶች፣ የዘርማጽዳት ወዘተ…..ስነምድራዊ ወሰን ወይም መድረክ ፡- ዓለም አቀፍ ግጭቶች፣ የዉስጠ-ኅብረተሰብ ግጭቶች፣ መንግስታዊ ሽብርተኝነት ወዘተ….በአጠቃላይ የግጭቶችደረጃዎች ባላቸዉ የትብብርወይምጥላቻ ደረጃ የተለያዩ ናቸው፡፡ አንዳንድግጭቶች በወዳጅነት መንፈስ ያለ ጭቆናና ኃይል በሰላም ሊፈቱሲችሉ ሌሎችደግሞከፍተኛግጭትእንዲፈጠር በማድረግ ወይምጭቆናእናአካላዊድብደባንያካትታሉ፡፡በግጭት ውስጥ በሚገኙ የተጋላጭነት ደረጃዎች መካከል ከመልካም ግንኙነት እስከ የጥላቻ ባሉ ግንኙነቶች መካከል - ከጓዳዊ ተፎካካሪነት እስከ ዘለቄታዊ ጦርነትድረስ፣ ይህ ቋሚነት በሰላም እና በጦርነት መካከል መደራደር እንዳለ ያሳያል፡፡ መደራደር በየ”ደረጃውጦርነት” “ቀዝቃዛ ጦርነት” “የጋራ መኖር” “የፉክክር” ዉዝግብ” “ትብብር,” “ልዩ ግንኙነት” “መግባባት” እና የመሳሰሉት በተመረጡ ቃላት ውስጥ የሚገለጥ ነው፡፡

ስለሃገራችን የግጭት መንስኤ ትርክታዊ ማብራሪያ

የአገራችን ፖለቲካ ግልብ ስሜትና የብሔር ማንነት ፖለቲካ እየተጫነው ከመጣ ሰነባብቷል፡፡ የብሔር ስሜት ስብዕናን እየሸረሸረ የሰዉን ልጅ ከምክንያታዊነት በማራቅ ወደ ደመነፍሳዊነት የሚገፋ ስስ ብልት ነዉ፡፡ የብሔር ፖለቲከኞችም በአመክንዮ የተጠናከረ ገዥ መወዳደሪያ ሃሳብ ማፍለቅ ሲያቅታቸው ያልተለፋበትን የብሔር ማንነት ትርክት ልቦለድ በመድረስ በወጣቱ ስስ ስሜት እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡ ስለዚህም ግጭቱን ከስሜት በጸዳ ጎኑ አንባቢን ለማስረዳት የግጭቱን ትርክታዊ መነሻ በዚህ ጽሑፌ ለመተንተን የሞከርኩት።በአገራችን ኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ አሳዛኝ የግጭት ሁኔታዎች እየተከሰቱ ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ የአመጽሃ ይሎች በተከታታይ የቋንቋ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ሰብዓዊ ጥቃቶች እና በተለያዩ የኢንቨስትመንት ተቋማት ንብረት ላይ የማቃጠልና የመዝረፍ አደጋ ሲፈጥሩ ቆይተዋል፡፡ ከ2 ሚሊዮን በላይ ኢትጵያውያን ከኢትዮጵያ ሶማሌ፤ ከኦሮሚያ፤ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ፤ ከአማራ ክልል ተፈናቅለዋል፡፡እነዚህ ክስተቶች አስከፊ ተጽእኖዎች ቢኖራቸውም በኢትዮጵያ ውስጥ በነባር የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች እና የቅርብ ጊዜ የኃይል ቡድን ለሆኑት ምንም አዲስ ነገር አይደለም፡፡ እነዚህ ቡድኖች በዲሞከራሲ ስርዓት ግንባታ አጀንዳ ማዕቀፍ ውስጥ በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች ሁከት በማስነሳት “ከገዥው ፓርቲ ተፅዕኖ” ለመላቀቅ በሚል መጠን ሰፊ ትግል እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም የችግሩን መሠረት ከተለያዩ የግጭትና አለመረጋጋት ነገረ-ምክንያቶች አንጻር ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡

የስዒረ-ነገር ትርክት - Conspiracy Theories

የሕዝባዊአመጹንመሠረታዊክስተቶች ለማብራራት በተለያዩ ተቋማትና ባለሙያዎች በርካታ የስዒረ-ነገር ንድፈ-ሐሳቦች በብዛት ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙ ሲሆን እነዚህም የሚከተሉትን ያካትታሉ:-(ሀ) የገዥዉ ፓርቲ ዝቅተኛ ካድሬዎችና ፖለቲከኞች የግል ስልጣናቸዉን ለማጠናከርና የፌዴራል መንግስቱን የቁጥጥር አቅም ለማዳከም ሆን ብለው አመጹን ይደግፋሉ ብሎም ያበረታታሉ ለአመጹ ተካፋይ ወጣቶችም የተለያዩ የገንዘብ፣ የሞራልና የሕግ ተጠያቂነት ከለላዎች ይሰጣሉ፡፡ይህን ትርክት በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍል በሚገኙ የፖለቲካ ተንታኞች እና አክቲቪስቶች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ከፌዴራላዊ አደረጃጀቱ አንጻርና ከሚከተለዉ ብሔር ተኮር ርዕዮተ ዓለም በተቃራኒ በቁጥር አናሳ በሆኑት አባላት የተፅዕኖ ደሴት ሥር ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ እንደ ንድፈ-ሐሳቡ አባባል ከሰሜን የመጡ በዋነኛነት የትግራይ ፖለቲከኞች (ማለትም ሰሜነኞች) በሀገሪቱ ላይ መስተዳድር መውረስ መብታቸው ነው ወይም መብት አለን ብለው ያምናሉ፡፡ እናም የሌሎች ክልል ልሒቃን፣ የፖለቲካ ካድሬዎችና የየአካባቢዉ ባለሥልጣናት ይህንን አመራር ላይ ያለን የተገቢነት ስነ-ልቦናና የቀደመ የመንግስት ልማድ ትርክት ለማኮላሸት አመጹን ለመርዳት ወሰኑ፡፡ ይህ አመጽ የመንግስትን አመራር ለማደናቀፍ እንደመሳሪያ እያገለገለ ቆይቷል አሁንም እንደ አንድ የጎሳ ተኮር ግጭቶች ማነሳሻ መሣሪያ ነው፡፡የዚህ ንድፈ-ሐሳብ ዋነኛው የምክንያታዊነት ድክመት የሚሆነዉ በአመጹ በአብዛኛው በአካልና በስነ-ልቦና እየተጠቁ ያሉት እነዚህ የዞንና ወረዳ ዝቅተኛ አመራሮችና ልሒቃን መሆናቸዉ ነዉ፡፡ እነዚህ የገዥዉ ፓርቲ የበታች ካድሬዎች ለገዥዉ የኢሕአዴግ አመራር አገሪቷ እንዳትመች ካደረጉ ለምን ከየክልላቸዉ ተወላጅ ሆኖ የወጣዉ አመራርን በማጥፋት ቡድኑን በመደገፍ አካባቢያቸዉን ለምን የአመጽ አዉድማ ያደርጋሉ? የሚለዉ ዋነኛ ጥያቄ ነዉ፡፡(ለ) የፌዴራል “የለውጡ” መንግስት አመጹን ይደግፋል፤ የአጋር ክልሎችን ድጋፍ ለመሰብሰብ ወይም ከ2012 የሀገራዊ ምርጫ በፊት ነባሩን “የለውጥ አደናቃፊ” አመራር ለማዳከም፣ሌላው የስዒረ-ነገርን ድፈ-ሐሳብ ቅኝት ደግሞ የፌዴራል መንግስት አመጹን በማራገብ የአካባቢዉ ነባር አመራር ለውጡን የማይደግፍ ነዉ በማለትና የፌዴራል መንግስቱ ራሱን በትክክል የለዉጡ ተንከባካቢ በማድረግ የክልል አመራሮች ደግሞ የለዉጡን ስሜትለማጥፋት ወይም የአገሪቱ አመራርእንዲወድቅ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን ለማስመሰል በፌዴራል መንግስትና በተወሰኑ የየክልሉ ከፍተኛው የለውጥ አመራር አስተዳደራዊና ሞራላዊ ድጋፍ እየተደረገ ያለ አመጽ ነው ለማሰኘት ነው፡፡ ይህ የፌዴራሉ መንግስት የእራሱንና የየክልል አጋሮችን “ከለውጥ አስተዳደሩ በስተጀርባ እንዲሰለፉና ድጋፍ እንዲያሰባስቡ የሚያስችል መንገድ ነው፡፡ሌላው የዚህ ስዒረ-ነገር ንዑስ ትርክት ወይም መላምት ደግሞ ከሁለት አመታት በኋላ በ2012 በሚካሄደዉ ምርጫ የለዉጡ ኃይል ወሳኝ አቅም እንዲያዳብርና የነባሩ አመራር የተፅዕኖ አድማስና የድጋፍ መሠረቱ እንዲዳከም፣ እንዲጠፋ ወይም እንዲቀንስ ይደግፋል የሚል ነው፡፡የዚህንንድፈ-ሃሳብ መሠረት ከሚያጠናክሩ ነገሮች አንዱ የተወሰኑ የፌዴራል መንግስቱ አካላት፣ በፌዴራል መንግስቱ ስር ያሉ የየክልሉ ልሒቃንና አመራሮች እንዲሁም አዲስ የተመረጡት የየክልሉ አመራሮችና የዞን መሪዎች ይህንን የለዉጥ ሥርዓት ቅቡልነት በይፋ በማስተጋባት የመርህ መሠረት ያለዉ መሆኑን ለማረጋገጥ መሞከር ነዉ፡፡በተቃራኒዉ የዚህ ንድፈ-ሃሳብ ዋነኛው ድክመት በአመጹ ተካፋይ የሆኑ አካላትና ወጣቶች እንዲሁም የአመጽ ቡድኑ መሪዎችና አባላት በቁጥጥር ስር ሲዉሉም ይህንን የሚያረጋግጥ ምንም አይነት መረጃና ማስረጃ አለመገኘቱ ነዉ፡፡ከዚህ በተጨማሪም ሁሉም የአካባቢዉ ነዋሪዎች በሃሰተኛ የብሔር መነቃቂያ የቅስቀሳ ዘመቻ በእራሳቸው ማንነት ላይ የሚያደርጉት ጉዳትና የራሳቸዉ ብሔር ሰዎችን በመግደል እንዴት እራሳቸውን በመጉዳት የሌላዉ መጠቀሚያ ይሆናሉ የሚለዉ ነው፡፡አሁንም ቢሆን የአመጹ አራማጅ ነን በሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች በሚተዳደሩ የተለያዩ የብዙሃንና የማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ ምስሎችና ቪዲዮዎች ይህንን አያረጋግጡም፡፡

የወደቁ አገራት ሙግት - The Failed State Argument

በተባበሩት  መንግስታት እና የአረብ ሊግ የአልጄሪያ ዲፕሎማት የሆነው ላክህዳር ብራሐሚ ባንድ ወቅት በተባበሩት መንግስታት ጉባኤ እንደተናገረው “የአገራት መዉደቅ የሌላ የማንም ኃላፊነት ሳይሆን የዚያው አገር አጠቃላይ ሕዝቦች ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት አስተዋጽኦ ውጤት ነው”፡፡ አንዳንድ ሰዎች ይህ አመጽና ሁከት የመንግስትና በአጠቃላይ የአገራችን የመዉደቅ አዝማሚያ ጅማሮ ወይም ገፋ ሲል ደግሞ የመንግስታዊ አመራር ስርዓት ዉድቀት ምልክት ሊሆን ይችላል ይላሉ፡፡ ችግሩ እዚህ ግብ ላይ የመድረስ መገለጫዎቹን ጨምሮ “የወደቀ ሃገር” ምንድነውየሚለው ጽንሰ-ሃሳብ ትርጉም ላይ መግባባት አለመኖሩ ነው፡፡የወደቀ አገር “Failed State” የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ ትርጓሜ ሌላዉ ችግር አንዳንድ ጊዜ እንደ ፖለቲካ አሻጥርና ማዕቀብ መጣያ መሣሪያ ጥቅም ላይ እየዋለ አስቸጋሪነቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡የወደቀ ሃገር ማለት የአንድ ሉዓላዊ ሀገር መንግሥት መሰረታዊ መዋቅሮች ሥራቸውን በሚገባ መተግበር ሲያቅታቸው ወይም መንግስት ህጋዊ ኃላፊነቶቹን አሟልቶ የማይሰራበት ደረጃ ሲደርስ የሚፈጠር ሁኔታ ነዉ፡፡ማንኛውም ሰው ወይም አካል የአንድን ሃገር የዜጎቿንና የብሔራዊ ደህንነት አጠባበቅ ሁኔታ፣ ወይም የዜጐቿን የኑሮ ደረጃን በማሻሻል ረገድ ያላትን አቋምና አፈጻጸም በማጤን “የወደቀ” ወይም “በመውደቅ ላይ ያለ-ደካማ” ሃገር ነው ብሎ መደምደም ይችላል፡፡የሕዝብ አመጽና ሁከት መበራከት፣ የግልና የመንግስት ንብረት ዉድመት ብሎም የሰዉ ሕይወት መጥፋት የአገራችንየመንግስትና ሀገር ስሪት ሂደት እንደወደቀ ማሳያ አንዱ አረጋጋጭ ማስረጃ ነዉ የሚለዉ ሙግትና ድምዳሜ የተጋነነ ይሆናል፤ ምክንያቱም እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ብራዚል ባሉ ስኬታማ አገሮች ዉስጥ እንኳ ተመሳሳይ አንገብጋቢ የደህንነት ችግሮች አሉ፡፡ምንም እንኳን አመጹና ሁከቱ በቀጣይነት ለሚኖረው ውድቀት የራሱ ተፅዕኖ ቢኖረውም የዚህ ትርክት ትንታኔ እንደእኛ ያለ ረጅም የመንግስታት ህዝብ ታሪክ፣ በመልከዓ ምድር ሰፊ ሃገርን ውስብስብ ሁኔታ በምሉዕ የማያሳይ ከመሆኑም በላይ ላለፉት ዓመታት በአማካይ በ8.7ከመቶ ያደገች ያለችን ሀገር”የወደቀ ሀገር” ለማለት የሚያስችል ምንም አይነት ነባራዊ ሁኔታ የለም፡፡

የሰው ልጅ ፍላጎት ዕድገትና የብልሹ አስተዳደር ትርክቶች The Human Needs and Poor Governance Theories

እንደጆን በርተን እና አብርሃም ማስሎው ያሉ የሰው ልጅ ፍላጎት ንድፈ-ሃሳብ ቀማሪዎች ጽሁፎችን መነሻ በማድረግ በሚቀርቡ ትንታኔዎች በመመሠረት የግጭቱን አውድ ለመተንተን ስንሞክር በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ላለፉት 27 ዓመታት በዋናነት ላለፉት 4 ዓመታት ለተፈጠረው ግጭት መንስኤ ከሆኑት ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች መካከል አንዱ የዜጎች ምናባዊ ወይም ያልተጨበጠ የዕድገት ተስፋና በሚባለው ዕድገት ልክ ያልተሟላ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት መፈለጋቸው ነው ወደ ሚል ድምዳሜ ያደርሳል፡፡በዚህ መላምት መዋቅራዊ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነን ላለፉት 3 ዓመታት በሃገራችን የታየውን የብጥብጥ ክስተት ለማብራራት ስንሻ በሃገራችን ዜጎች በተለያዩ የአገዛዙ መገናኛ ብዙሃን መግለጫዎች በጠቅላላ የነፍስ ወከፍ ገቢ መሻሻል ቢኖረዉም (ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገሪቱ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት ከማሳየቱ በፊት) እና ላለፉት ስምንት ዓመታት ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት አለ ቢባልም በርካታ የሃገሪቱ አካባቢዎች በከፍተኛ ድህነት የተጠቁ ናቸዉ፡፡ዓመጹ በተቀጣጠለባቸዉ በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ያለውየዜጎቻችን የኑሮ ሁኔታ እንደፍራንዝፋነን አገላለጽ “የምድር ገሃነም” ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ የሚኖሩ አብዛኛዎቹምርታማ ሊሆኑ የሚችሉ ወጣቶች ተምረው ሥራ የሌላቸው ወይም በከፊል ሥራ አጥ የሆኑ ናቸው፡፡ እንደ ቴድጉርተር አሰያየም በተለያየ ምክንያት “በአንጻራዊ እጦት” ውስጥ የተዘፈቁ ናቸው፡፡ የሥራ ዕድል ለሰዎች ባህሪ ቁልፍ መገለጫ በመሆን ለዕለት ተዕለት ኑሮ ድርጅታዊ ቅርጽ ይሰጣል፤ በተቃራኒው ሥራ አጥ ግለሰቦች ለሥነ ልቦናዊ እና ማህበራዊ ጫና በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ናቸዉ፡፡ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ሥራ አጥነት ከአእምሮ ጤና ችግሮች ጋር የተቆራኘ ነው፡፡እንደ አንዳንድተንታኞች አስተሳሰብ ከሆነ ለሃገሪቱ የድህነትሁኔታ መባባስና የመልካም አስተደዳር ዕጦት (ብልሹ አስተዳደር) ዋነኛዉ መነሻ ለክልሎች የልማት ሥራዎች የሚመደበዉን በጀት የክልሉ አስተዳዳሪዎች ክልላቸዉን ብሎም ሀገሪቱን ለማልማት ማዋል ሲኖርባቸዉ ገንዘቡን በማጭበርበር ወይም በመዝረፍ ለግል ጥቅማቸዉ እንዳዋሉ የሚያሳዩ ክሶች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ አመራሮች ደረጃ ከፍተኛ በጀትን የማስተዳደር አቅም ማነስ ተጠቃሽ ነዉ፡፡በሰብአዊ ፍላጎቶች እና በብልሹ አስተዳደር መካከል በሚኖር የትስስሮሽ መጠን ላይ ያነጣጠሩ የግጭት መንስኤ ክርክሮች ቢኖሩም ግን የግጭቶቹን አነሳስ፣ መስፋፋትና ቀጣይ ድርጊቶችን ሙሉ በሙሉ ማብራራት አልቻሉም ወይም ተመሳሳይ የሆነ የአመጽ ቡድን በሌሎች ዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ባላቸዉ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ለምን እንዳልወጣ መግለጽ አልቻሉም፡፡ ከዚህም በላይ ይህ የአመጽ ሁኔታ በአገሪቱ የአመጹ ማዕከላዊ የሥዕበት ቦታዎች ያለዉን ደካማ መስተዳድር ብቻ የሚገልጽ አይደለም ምክንያቱም አንጻራዊ ሠላም ባለባቸዉ በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ የተሻለ አስተዳደር እንዳላቸው የሚያሳይ ምንም አይነት ተጨባጭ ማስረጃ የለም፡፡ ይህ ማለት በዚህ ትርክት ላይ ተመስርቶ የሚቀርብ ትንተና ሙሉ በሙሉ የግጭቱን መሠረታዊ መንስኤ አይገልጽም እንጂ ተደማሪ አስተዋጽኦ አላደረገም ማለት ግን አይደለም፡፡

ተስፋ መቁረጥ-ጠብ አጫሪነት መላምት The Frustration-Aggression Hypothesis

በዚህ መላምት አገላለጽ ከሆነ ተስፋመቁረጥ የጠብ አጫሪነት መንስኤ ይሆናል፡፡ ሰዎች የያዙት አንድዓላማ ከስኬት ሲታገድ ብዙውን ጊዜ ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ የዚያ ተስፋ መቁረጥ ምንጭ በሆነዉ ጉዳይ በጣምየተቆጡ ከሆነ የብስጭት ርምጃ መዉሰድ ይጀምራሉ፡፡ የተስፋ መቁረጥ-ጠበኝነት ጽንሰ-ሐሳብ እንደሚያሳየው ብስጭት ብዙውን ጊዜ ወደ ጠበኛ ባህሪ ይመራል፡፡ ይህንን ንድፈ-ሃሳብ የተቀመረው በ1930ዎቹ ሲሆን ምሁራኑም ዶላርድ፣ ዱብ፣ ሚለር፣ ሞወርና ሲርስ የተባሉ የማኅበራዊ ሳይንስ  ናቸው፡፡

የተስፋ መቁረጡ መንስኤ በግልጽ ታውቆና ተጠንቶ ሁነኛና ወቅታዊ መፍትሔ ሊገኝለት ወይም ሊሰጠዉ የማይችልከሆነ ጠብ አጫሪነቱ ንጹሃን ሰዎችን፣ ኢንቨስትመንትንና ሌሎች ማኅበረሰባዊና ቁሳዊ ሃብትን ዒላማ ወደማድረግ ይሸጋገራል፡፡ በአገራችን የሚታዩ ብዙዎቹ የቅርብጊዜ የግጭት ክስተቶች ከዚህንድፈ-ሐሳብ ጋር በእጅጉ የሚስማሙይመስላሉ፡፡ለምሳሌ በቅርብ ጊዜ ከፌዴራል መንግስት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያስረዱት ለግጭቱ መንስዔና መባባስ ምክንያት ከሆኑ ነገሮች አንዱ በፌዴራል መንግስቱ የሚገኙ የተለያዩ ገቢዎች የሚከፋፈሉበት የበጀት ቀመርና ክፍፍል አግባብ ከክልሎች ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ አለመሆንና አድሎአዊነት አንዱ ነው፡፡እንደወጡት መረጃዎች ከሆነ የበጀት ክፍፍሉ ህዳግና የሚወከልበት ሽንሻኖ ትኩረት የሚከናወነዉ ባብዛኛዉ ለአንድ ክልል ባደላና ሌሎቹን ከቁጥር በማያስገባና ጉዳት በሚያስከትል መንገድ ነው የሚል ትርክት አለ፡፡ በሃገሪቱ የሃብቶች (የመጠን፣ የአይነትና የአቅጣጫ) ስርጭት ኢ-ፍትሐዊነትና እየጨመረ በሚሄደው የአመጽ ኃይል ስበት መካከል ግልጽ የሆነ ቀጥተኛ ግንኙነት አለ፡፡ይህ ክርክር በከፊል ትክክለኛ ሊሆን ቢችልም ብጥብጡ መሠል እጣ ፈንታ በሚጋሩ የሰሜን ምዕራብና ደቡብ ምስራቅ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለምን እንዳልተፈጠረ ወይም ደግሞ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በደቡብ ክልል ያለመከሰቱ ስለምን በቂ ማስረጃ አያቀርብም፡፡ሌላው ለተከሰቱ ግጭቶች ተስፋ መቁረጥ ጠብ አጫሪነት መላምት ሁነኛ ምላሽነት በከፍል ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባዉ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በአጠቃላይ የለዉጥ መንፈስ ተንሰራፍቷል በሚባልበትና ለዉጡ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ከሞላ ጎደል በሥራ ላይ ከዋለና በስፋትም እየተተገበረ ነዉ በተባለበት ሁኔታ የአካባቢዉ ወጣቶችና ነዋሪዎች በተመሳሳይ ተስፋ መቁረጥ ዉስጥ መሆናቸዉና ጥፋቱ ተባብሶ መቀጠሉ ነው፡፡ሌላው በዚህ የመላምት ብ ማዕቀፍ ውስጥ ሊታይ የሚገባዉ ነጥብ በቅርብ ጊዜያት እየገነገነ የመጣዉ የሃገራችን የፖለቲካልምድ እንደሚያሳየን “አንድ ሰው ፍየል ወይም ከዚያ ያነሰ ዝቅተኛ ስርቆት ፈጽሞ ከባድ ቅጣት ሲቀጣ አንድ በማንኛዉም ርከን ላይ ያለ አመራር በቢሊዮኖች የሚቆጠር የሕዝብ ሃብትና ንብረት ዘርፎ ሳይቀጣ ነጻ ይሆናል፡፡” ይህም ወጣቱን በፍትሕ ስርዓቱ ላይ መተማመን በማሳጣት ወደ መንጋ ፍትሕ እንዲሸጋገር አድርጎታል፡፡

በሀገር ግንባታ ሂደት የሚፈጠር ግጭት Crisis in Nation Building

ስለ አገራችን የረብሻና አመጽ ክስተትየተሻለናሰፊእይታ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው መላምትበአገር-ግንባታ ሂደቶች ላይ የተፈጠረን ቀውስ እንደ ማሳያ በመጠቀም ነው፡፡ምንም እንኳን እነዚህ በአገሪቱውስጥ ለሽብርተኝነት፣ ንብረት መጥፋት እና ሞትም ክንያት የሆኑ በርካታ ቡድኖች ተግባር የሚወገዝ ቢሆንም የእነዚህ ቡድኖች አስተዋጽኦ አንደኛው እንጂ ብቸኛዉ አይደለም፡፡ ይህ ስለመሆኑ ለማሳየት ቡድኖቹ ቢጠፉ እንኳ ዘር ተኮር ድብደባዎች፣ እስሮች እና ሌሎች አግባብነት የጎደላቸው ድርጊቶች ብሎም የደህንነት ዕጦት ሊወገዱ ይችላሉ ወይ? ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡እንደ እውነታዎች ከሆነ በአገሪቱ ውስጥ በሁሉም ክልል ውስጥ ያለው ችግር መንስኤው የጀርመን-አሜሪካዊቷ ፖለቲካዊ ንድፈ-ሃሳብ ተንታኝ አና አርደንት እንደምትጠራዉ “የእኩያን ተራ” በመሆኑ ነዉ፡፡ በአገራችንም የብሔር እኩያኑ ሥፍራውን በስፋት መቆጣጠራቸውን ያመለክታል፡፡ የክርክሯ ጭብጥም የሚያተኩረው በታሪክ ውስጥ የታዩት ታላላቅ ግጭቶችና ማኅበረሰባዊ ጥፋቶች የተፈጸሙት በአክራሪ ብሔረተኞች ወይም አእምሮአቸዉ በዚህ ስነ-ልቦና በተቀየደ ተከታዮቻቸው ሳይሆን የድርጊቶቻቸውን መነሻ እንደቅቡል በሚመለከቱ ተራሰዎች ሲሆን እነዚህ አሰቃቂ ድርጊቶችም የተለመዱ ናቸው በሚል መነሻ በግጭቱ ውስጥ በጉልህ ይሳተፋሉ፡፡ ይህ አካሄድ “በህሊና የማይታሰበውን ነገር መደበኛ” ወይም ክፋትን መለማመጃ መንገድ ተብሎ የሚጠራው ነው፡፡ይህ የስነ-ሃሳብ ሙግት በመላው ሃገራችን እየተከሰተ ያለውን ወሳኝ ሃቅ በሚገባ ይገልጻል ይኽዉም በመላዉ ሀገሪቱ ላይ የጭካኔ ድርጊትን የተላበሱ ግድያዎችና ዝርፊያዎች፣ በተለይም በኦሮሚያና አማራ እንዲሁም በጥቂት በደቡብ ክልል አካባቢዎች (በተለይምበደቡብምስራቅ) የሰዎችና ንብረት ዕገታና ወረራዎች እንዲሁም ዘረፋ፣ በአነስተኛ ደረጃ በታጠቁ ሽፍቶች እና አጥቂ ቡድኖች (በሰሜን ጎንደር እንዲሁም ቀደም ሲል አርባ ምንጭ ዙሪያ ውስጥ) ትናንሽ የመንደር ጦርነቶች፣ በጎሳና ጎሳ እንዲሁም በንዑስ ጎሳዎች መካከል መርህ አልባ ግጭቶች በስፋት እየተፋፋሙ መገኘቱ አንዱ ነው፡፡ ሌላው በኢትዮጵያ ሀገረ-ምስረታ ሂደት የተፈጠረው ቀውስ ከዝቅተኛ የዕድገት (ልማት) ምጣኔ ጋር ተቀላቅሎ ለብዙዜጎች ስጋትና የዳበረ ዘላቂ ነባራዊ ቀውስ ወደ መፍጠር ተሸጋግሯል፡፡በርካታ የሃገራችን ወጣቶች ከአጠቃላዩ የአገሪቱ ልማት የመገለል የባይተዋርነት ስሜታቸውን ለማስወገድ የመፍትሔ መንገድ ብለው የያዙት ገዥው ፓርቲ ከሚከተለው ብሔር ተኮር ርዕዮት ጋር በማዳቀል ከ”ሃገረ-ኢትዮጵያ ግንባታ ፕሮጀክት” ራስን ማግለል ሲሆን በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ከተለያዩብሔር ብሔረሰቦች አዳዲስ ወረዳዎች፣ ዞኖች ወይም ክልሎችን የመመስረት አዲስ ዘዬ ማምጣት ከዚህ ገፋ ሲልም ከቀደምት የጎሳ ማንነቶች በመነሳት ከነባሩ ፌዴራላዊ ስርዓት የተቃርኖ ሀሳቦችንማዘጋጀትና ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊ ማንነትን እንደጠላትአድርጎመቁጠር ነው፡፡ ወጣቶች በተለያዩ የፖለቲካ ተዋናዮች የሚቀነቀኑ የቅድመ-ታሪክ ትርክቶችን እንደ እውነት በመቀበል የራሳቸውን የብሔር ጀግና ወደ መፍጠር ገብተዋል፡፡ ይህም የአገር ግንባታ ሂደቱን እያስተጓጎለው ይገኛል፡፡ከላይ በተጠቀሰው ሃሳብ መሰረት መንግስት በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶችንና ስርዓት አልበኝነትን ከሥሩ ለማጥፋትና ምንጫቸውን ለማድረቅ እንዲያስችለው ሊከተለው የሚገባ ዋነኛው (መሠረታዊ) ስልትበኢትዮጵያ አገር-ግንባታ ሂደቶች ላይ ያሉትን ችግሮች መፍታትና ያላለቁ የአገር ግንባታ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ነው፡፡ ይህ ማለት አገር-መገንባት ጊዜ ስለሚወስድ ችግሩን ለመቀነስ ከተቻለም ለማስወገድ የረጅም ጊዜ ዕቅዶችና መፍትሄዎች ማዘጋጀት ያስፈልጋል ተብሎ ይታመናል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በእነዚህ ጽንፈኛ ቡድኖችና የተለያየ የፖለቲካ አስተሳሰብ በያዙ አካላት/ፖርቲዎች ያጋጠሙትን ፈታኝ ችግሮች ለመፍታት የሚያግዝ በተከታታይ የሚተገበሩ የአጭርና የረጅም ጊዜ የሀገር ግንባታ ስልቶች ሊኖሩት ይገባል፡፡

ክፍል ሁለት

በዚህኛው ክፍል አመጽ እና ግጭቶችን ስለሚወስኑ ሁኔታዎች እና የረጅም እና የአጭር ጊዜ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ያስረዳል።

የግጭቱ ቀጣይ ተጨባጭ ሁኔታ ታሳቢዎች

በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ባህሪያት፣ ተያያዥ መነሻዎችና መግፍኤዎች አሏቸው። ለውጥ መጥቷል ከተባለ በኋላ ቢሆን በሃገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረገው ግጭት እየጨመረ የሄደ ሲሆን ቀደም ሲል በአገሪቱ ደቡባዊ ምሥራቅ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በሚገኘው የጅግጅጋ ከተማ ላይ በአካባቢው ወጣቶች ጥቃት በተሰነዘረበት ወቅት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፤ እንዲሁም በብዙ ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ጠፍቷል። ይህ ጥፋት ግጭቶቹ ለደረሱበት ደረጃ እንደ አንድ ዋቢ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።እንዲሁም በዚህ ሳምንት ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ የተወሰኑ የአውሮፓ አገራት ለኢትዮጵያ መንግስት የደህንነት ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት እያሳዩ ነው። ሆኖም ግን ይህ አመጽ ማዕከሉ የት ነው? ባህሪው እንዴት ነው የሚለው ባግባቡ መጠናት አለበት። ሌሎች ታዛቢዎችና ተንታኞች ደግሞ የአሁኑ ጊዜ የብጥብጡ ማብቂያ ጅማሮ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ ሌሎች ተቺዎች ደግሞ የውጪ ጣልቃ ገብነት እሳቱን እንዲቀጣጠል እንዳያደርገው ያስጠነቅቃሉ።ሥለ ግጭት ያሉ ትርክቶችንና ያሉዋቸውን አንድምታዎች ይህን ያህል ዝርዝር ሀተታ ማቅረቡን እዚህ ላይ በማቆም ስለግጭቶቹ ቀጣይ አዝማሚያዎች ለማብራራት እሞክራለሁ። ግጭቱ ይቀንሳል? የአሁኑ የአመጹ ቅርጾች ቋሚ ይሆኑ ይሆን? ወይስ ዓመፅ ይበልጥ እየተፋፋመ ይሆን? ለምን?

አመጹና ግጭቱ በቀጣይ ይቀንሳል

በተለያዩ አካላትና አካባቢዎች የሚነሱ አመጾችና ግጭቶች በቀጣይ እንዲቀንሱማድረግይቻላል። ሆኖም ግን ይህተስፋበአጭርጊዜውስጥ የሚፈጸም አይመስልም። እንዲያውም በተለያዩ ቡድኖች ላይ የተጠናከረ ከፊል-ወታደራዊ (Para-military) ዘመቻ እና በተወሰኑ አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚመስል ነገር ቢታወጅም ባንዳንድ አካባቢዎች ሰዎችን ማገት፣ ንብረት ዘረፋና የመሳሰሉ ጥቃቶችን ለማስፈፀም የሚችል አቅም ያላቸው ኃይሎች በመኖራቸው በተደጋጋሚ ብዙ ሰዎች እንዲሞቱና ንብረት እንዲዘረፉ እያደረጋቸው ነው፤ነበሩም።በገሀድ እንደሚታየዉ በቅርብ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች በየደረጃዉ ያሉ አመራሮች አማካኝነት ከሕዝቡ ጋር ተከታታይ ዉይይቶች ከተደረጉ በኋላም ቢሆን ሁኔታዎች እንደሚያሳዩት አደጋና ተያያዥ ስጋቶቹ እያደዱ እንጂ እየቀነሱ አይደለም። በቀጣይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችና የአመጽ ድርጊቶች ቢረጋጉም ሊቀንሱ የሚችሉት ከቀጣዩ የ2012 አገር አቀፍ ምርጫ መደምደሚያ ላይ ሊሆን ይችላል። ምንም እንኳን በተለያየ አካባቢ፣ መልክና ቅርጽ የሚፈጠሩት እነዚህ የአመጽ ድርጊቶች በብሔር ማንነት መነቃቃትና የብሔር ጭቆና ትርክት ላይ መሠረታቸውን ቢያኖሩም (ቢቆጥሩም) ቅርጻቸውን ቀይረው በአካባቢው ነዋሪዎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ላይ ሊያነጣጠሩ ይችላሉ።ለዚህ የመረጋጋት ተጨባጭ ተስፋ ከሰነቁት ምክንያቶች መካከል አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት በቀጣዩ የ2012 የሚካሄደዉ ሃገራዊ ምርጫ የአገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሁሉንም ተቃዋሚዎችን ያሳተፈ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ መሆኑ ነው።በኢሕአዴግ የሥልጣን ክፍፍል እና የኃይል ቅንብር አቀማመጥ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ከኦሮሞ ዉጪ መሆኑ ማብቃት አለበት የሚለዉ ሌላዉ ልልና መሬት ያልረገጠ ትርክት ነዉ።በ2012 በሚደረገው ሃገራዊ ምርጫ ላይ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ኢሕአዴግ ቢያሸነፍ ወይም የምርጫ አሰራሩ ተቀይሮ ከተቃዋሚዎች ጋር የጥምር መንግስት ቢመሰርት እነዚህ ተቃዋሚዎች ሕዝቡን ከሚመገቡትየተስፋ ፖለቲካና ከሚጭሩት አለመረጋጋት በሰላማዊው የለዉጥ ሽግግር ምክንያት በሂደት ሊከስሙ እንዲያም ሲል ሊወገዱ ይችላሉ።ለዚህም በተወሰነ መልኩ በኦሮሚያ በአመጽ ሲንቀሳቀስ የነበረዉ የኦሮሞ ነጻ አዉጪ ግንባር እንዲሁም አርበኞች ግንቦት 7 የአንድነትና ፍትሕ ፓርቲ ወደ አገር ቤት ሲገቡ በክልሉ የተፈጠረዉ ጊዜያዊ አንጻራዊ ሠላም እንደማሳያ ሊቆጠር ይችላል። እንዲያውምእነዚህ ኃይላት ከኤርትራ ጋር በተፈጠረዉ ስምምነትና በሁለቱ መንግስታት መካከል በሚደረገው ድርድር ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል።በሌላ በኩል በአገሪቱ በተከሰተዉ አመጽና ግጭት ትልቁ ተዋናይ የነበረዉ የኦሮሞ ክልል ሕዝብና ወጣት (በተጨማሪም በሌሎች ክልሎች የነበሩ እንደ ፋኖ፣ ዘርማና ሌሎች) ሲሆን ከራሳቸዉ ከሕዝቡ የወጣዉ የኦህዴድ አመራር የፌዴራል አመራሩን በተቆጣጠረበት በዚህ ወቅት ለእነዚህ ተቃዋሚዎች የኃይል እርምጃቸዉንና ብጥብጣቸውን ለማደስ አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል ምክንያቱም እነዚህ እርምጃዎች በአካባቢያቸው ካለው ህብረተሰብ የራሳቸውን አንድ አካል እያወደሙ እንደሆነ በማስረገጥ ሙግትና ተግዳሮት ስለሚገጥማቸዉ ነዉ።ከዚህ በተቃራኒዉ በኦህዴድ የሚመራዉ ገዥዉ ፓርቲ በምርጫ 2012 ድምጽ ካጣበክልሉ ብሎም በአገሪቱ ላይ አመጽና የኃይል እርምጃን እንደገና ለመጨመር ይችላል። አመጽና ሽብርተኝነት ላይ ሊቀነስ የሚችልበት ሌላኛው መንገድ የፌዴራል መንግስቱ በጣም የተጎዱትን ክልላዊ መንግስታት በመለየት በአማራና በአሮሚያ ክልሎች እንደታየዉ የጸጥታ አስተዳዳሪዎችን ሚሊታሪ ቀመስ በሆነ ጠንካራ አመራር እየተካ መሆኑ ነው። ጦር ቀመስ አመራሮች በአካባቢዎቻቸው የሚከሰትን አመጽና ግጭት ለመቀነስ የሚያስችል የቅድመ-ትንበያና ቴክኒካዊ አቅም አላቸው።በሌላ በኩል ደግሞ ይህ እርምጃ በከፍተኛ የሥልጣን ደረጃ ያሉ ወታደራዊ ተስፈኛ መኮንኖች ያላቸዉን አቅም ተጠቅመዉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሥልጣን መቆየት የሚችሉበትን አጋጣሚ በመፍጠር በኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲ ደረጃ ማሽቆልቆልን ሊያስከትል ይችላል። እንደሚታወቀዉ የአገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጅማሮ ገና እንጭጭና ከግንቦት 1983 የሚልቅ እድሜ የሌለዉ ነዉ። ኢትዮጵያ ለሺህ ዓመታት የዘለቀ የረጅም ጊዜ የሃገረ-መንግስት ስርዓት ቢኖራትም በ1967 የጥቂት ወታደሮች ቡድን (ደርግ) ስልጣንን በቁጥጥር ስር አውለው አምባገነንነትን ያመጡ ሲሆን ከ17 ዓመታት መራር ጦርነት በኋላ ሙሉ ባይሆንም የዲሞክራሲ ጽንሰ-ሃሳብ ጅምር ታይቷል። እንደገናም በ1997 በሀገሪቱ ውስጥ ፍትሐዊ ምርጫ በማድረግ ዲሞክራሲን በድጋሚ ለመመስረት የተደረገው ሙከራ በወታደራዊና ሲቪል ዕመቃ እንደገና ወደ ኋላ ሊመለስ ችሏል።በሃገሪቱ ውስጥ የሚፈጸሙ የኃይልና አመጽ ድርጊቶች እንዲገደቡ የሚያደርገው ሦስተኛ ነገር በተለያዩ ክልሎች በሚኖሩ ሌሎች ብሔሮች ላይ የሚደርሰዉ ተደጋጋሚ አደጋ ኢሰብዓዊነት እና ድርጊቱን አስመልክቶ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ከየአጥቂዉ ብሄር ተደጋጋሚና ጠንከር ያለ ዉግዘት መበራከቱነው። በየአካባቢዉም ድርጊቱን በመንቀፍ ተደጋጋሚ የተቃዉሞ ሰልፍ እየተካሄደ መገኘቱ ናቸዉ።በተጨማሪም መንግስት ሁሉን አቀፍ አቅሙን አቀናጅቶና ከሕዝቡ ጋር ስምምነት ፈጥሮ የአመጹን መሪዎችና በገንዘብና በሞራል ድጋፍ የሚሰጡ ተቋማትንና ግለሰቦችን በተቻለዉ መንገድ ሁሉ አደብ ማስያዝ ከቻለና ህጋዊ ርምጃ መዉሰድ ከጀመረ አመጹ በአስተማማኝ መልኩ ሊቀንስ ይችላል።አመጾቹ /ጥቃቱ/ ጠባያቸውን እና ጥንካሬያቸውን ጠብቀው ሊቆዩ ይችላሉበዚህ ሁኔታ ኦሮሚያ፣ አማራና ሶማሌ ክልሎች የአመጹ/ሁከቱ/ የግለት መሠረት ሲሆኑ በሌሎች እንደ ደቡብ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉልና ጋምቤላ ባሉ ክልሎች ወቅት እየጠበቁ በድንገት የመቀስቀስ እድሎች ይከሰታሉ።ከነባራዊ የግጭት አድማሳዊ ሙግቶች እንደምንረዳዉ ይህ ሁኔታ ሊከሰት የማይችል ነው ምክንያቱም ግጭቱ ከጥቂት ወራትና ዓመታት በፊት ከነበረበት ጡዘት ቀንሶ የተሻለ ደረጃ ላይ በመሆኑ ቀጣይ ቅቡል አዝማሚያዉ መረጋጋት መሆኑ ነዉ። በሶማሌና ቤንሻንጉል ክልሎች እንዲሁም በደቡብ ክልል ቴፒና ዳዉሮ ዞኖች በተፈጠሩ የቅርብ ጊዜ ጥቃቶች ላይ ከተለያዩ አካላት እንዲሁም ከራሱ ከአካባቢዉ ማኅበረሰብ በተሰነዘረዉ ጠንካራ ዉግዘት እንደተገለፀው ለግጭቱና ሁከቱ ያለዉ ተቃዉሞዉ እያየለ መጥቷል።ይህም ባለበት እንዲቆም ያደርገዋል።ለምሳሌም ወደ ሃገር ዉስጥ በሕጋዊ መንገድ ለመታገል የገቡትን ተፎካካሪዎች በመጠቀም የግጭት ሽፋኑን ማረጋጋት ይቻላል። ስለዚህ ግጭቱ በባህሪዉና እንደሁኔታዉ አያያዙ አይለወጥም የሚለዉ አስተሳሰብ የማይሆን ትርክት ነዉ። ከዚህ በላይ ከተጠቀሰው የመጀመሪያዉ መነሻ አቅጣጫ ጋር የሚጣጣም ካልሆነ በስተቀር ግጭቱ እየጠነከረ ይሄዳል።የግጭቱ አደጋ በፍጥነት ይጨመራል፤በአገሪቱ የሚታዩት ግጭቶች አሁን ካለው ሁኔታ እጅግ በከፋ ሁኔታ ሊጨምር ይችላል። ይህ አዝማሚያ ቢያንስ ቢያንስ በአራት ተገቢ ሁኔታዎች ውስጥ ሊከሰት ይችላል።የግጭቱ ማዕከላዊ (የስበት) አካባቢ አሁን ካለበት መልከዓ-ምድራዊ ስፋት በየትኛዉም አቅጣጫ እየጨመረ ከመጣና ወደ ሌሎች ክልሎች ከተዛመተ ግጭቱ በስፋትና በጥልቀት ይጨምራል። እንዲሁም የሚሰነዘረዉ ጥቃት ወደ ሌሎች ዋና ዋና ክልሎች በቤንሻንጉል፣ ጋምቤላና አፋር እንዲሁም በደቡብ ሁሉም ዞኖች ከተዛመተ በጣምሰፊ የሆነ አመፅ ሊገጥም ይችላል። ይህ ከተከሰተ ደግሞ ጠርዝ አልባ ሽብርተኝነትን በማስፋፋት ከጽንፈኛ ብሔረተኝነት፣ ከሃይማኖት አክራሪነት እና ከጠባብ ክልላዊነት አስተሳሰብ ጋር ይቀላቀላል። ከሚያስከትላቸው ውጤቶች አንዱ በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ተቃራኒ ቡድኖች ተከታታይ የአጸፋ ምላሽ እርምጃዎች ሊሆን ይችላል። ዙረቱ ይቀጥላል።እነዚህ የተቃዉሞ ኃይሎች ሁከቱን በተለያየ መልኩ ወደ ሌሎች ብሔሮችና ሃይማኖቶች እንዲዛመት ለማድረግ ቢመርጡ ወይም ወደጥቃቱ ሰርገዉ ከገቡ አመጹ ወደሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ሊሰራጭ ይችላል። አሁንም ነሐሴ 9 ቀን 2010 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ምስራቅሐረርጌ በግጭቱ የተጠለሉ ከ50 በላይ ዜጎች እንደተገደሉ ሪፖርት ተደርጓል። በርካታ የክርስትና እምነት ተከታይ ህዝቦች ባሉባቸው ክፍለ ሀገራት ተመሳሳይ ግጭቶች ተከስተዋል። በእነዚህ አሳዛኝ ክስተቶች የአመጽ ኃይሉ ተሳታፊ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ ፈጥረዋል። እነዚህ ጥርጣሬዎች እውነት መሆናቸውን ከተረጋገጡ በጥቃቶቹ የተጎዱት አካባቢዎች በቀላሉ ለበቀል ሊነሳሱ ይችላሉ።ሌሎች ኃይሎች በአመጹ ከተሳተፉ በተለይም ይህ ጣልቃ ገብነት በነባሩ የአመራር ቡድን እና በሙስና የተጨማለቁ አመራሮች ተጣምረዉ አመጾችን እንዲደግፉ በማድረግ በርካታ ሰዎች አሸባሪዎቹን ለመደገፍ ይንቀሳቀሳሉ። ለተጨማሪ አባላት ምልመላም ይረዳል።በቀጣይ በ2012 በሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ኢሕአዴግ ብቻ አሸናፊ ከሆነ በሃገሪቱ ከሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የሚኖሩ አለመግባባቶች ጠንካራ እና ለአማጺዎች ተጨማሪ እሳት ማቀጣጠያ ይሰጣሉ። ይህ ጉዳይ በተለይ በሀገሪቱ የኦሮሚያ ክልል ያለዉ ተቃዋሚ ሃይል ኦነግና ግንቦት 7 ኃይሎች በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ፓርቲዎች ይበልጥ አስፈሪ አቅም ያላቸዉ ናቸዉ። እንደአገራችን የፖለቲካ ታሪክ በተለይም በ1997 በተካሄደዉ ምርጫ እንደታየዉ ተቃዋሚዉ ኃይል ምርጫውን ካጣና ገዥው ፓርቲ የመጫን ርምጃ ከወሰደ ተጨባጭ ፖለቲካዊ ቅሬታዎችን የሚያባብስ ይሆናል።

ቀጣይ መንገድ ምን ይሆን- The Way Forward

በየአካባቢዉ የሚነሱ ቅሬታዎችን በእልህና በመለዮ ለባሽ ሃይል ለመፍታት መሞከር ግጭቱ ላይ ቤንዚን እንደ ማርከፍከፍ ይቆጠራል።ይሁን እንጂ በሃገራችን ያሉት አሳዛኝ ክስተቶች እና ተያያዥ ግጭቶች እንደ ሽብርተኝነት ድርጊቶች እየታዩ ብቻ ተመሳሳይ ምላሽ አያስፈልጋቸውም። በአሁኑ ጊዜ የውጭ መንግስታት የደኅንነት እና ክትትል ድጋፍ እያደረጉ ቢሆንም ግጭቱ ለረዥም ጊዜ እና ጥልቅ የሆኑ ቅሬታዎች እስከሚወገዱ ድረስ አይጠፋም። በመንግሥት የሚወሰዱ ስልቶች በቡድን እና በአሸናፊነት ላይ ለማነጣጠር የታቀዱትን የአጭር እና የረጅም ጊዜ ተብለዉ መለየት አለባቸዉ።ቀውሱን ለመግታት የረጅም ጊዜ መፍትሔዎች:-በአገር ግንባታ ሂደት ላይ የተከሰተውን ቀውስ መፍታት-Resolving the Crisis in Ethiopia’s Nation Buildingከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካሀገሮችእና በአጠቃላይ በአህጉሪቱ ዉስጥ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ዉስጥ የምትገኘዉና ከናይጄሪያ ቀጥሎ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት ሀገራችን በሃገር ግንባታ ሂደት ዉስጥ ከፍተኛ የሆነ ቀውስ እያጋጠማት ነው። ከሞላ ጎደል በያንዳንዱ የኢትዮጵያ ክፍል ዉስጥ የሚገኝ የብሔር ስብስብ “ተገልያለሁ” የሚል ነው።የተወሰኑ የአንድነት ቡድኖች ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ሕዝብ በአንድነት ጥላ ሥር ለመኖር ይፈልጋሉ ወይስ አይፈልጉም የሚለዉን ለመወሰን ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ጉባዔ ተጠርቶ ዉይይት እንዲደረግ ጥሪ እያደረጉ ናቸው። “እኩል ኢትዮጵያዊነትን” ለመፍጠር የሚደረገዉ ጥረት ጠንካራ ተግዳሮቶች እየገጠሙ ይገኛሉ። ይኽዉም ኢትዮጵያውያን ከሌላ ማንነታቸዉ በበለጠ ኢትዮጵያዊ መለያዎችን እንደ ማንነት እንዲጠቀሙና እንዲያስቀድሙ ለማስቻል ያለዉ ተቃርኖ ከፍተኛ ችግር ሆኗል። ስለሆነም አንዳንድ ሰዎች አሁንም ኢትዮጵያ “እንዲሁ የመልከዓ-ምድር መገለጫ ቦታ ብቻ” እንጂ ከዛ የዘለለ መገለጫ የሌላት “በጣም የጥቂቶች ኢትዮጵያውያን” ንብረት ብቻ እንደሆነች ያምናሉ።የጋራ ሃገር ግንባታ ትግሉ ከድህነት፣ ኢ-እኩልነት፣ ኢ-ፍትሐዊነት፣ ከማኅበረሰብ የንቃተ ህሊና ማነስ እናየልማት እጦት ጋር ተቀላቅሎ በብዙ ኢትዮጵያውያን መካከል ነባራዊ ቁዉስ ፈጥሯል። በሕዝብ መካከል ያለው አለመተማመንም እንዲጎለበት አድርጓል።ናይጄሪያዊዉ ዓለም አቀፍ የሰላምና ልማት አማካሪና የ“wealth For All” መጽሐፍ ደራሲ ኢዶዉ ኮይንካ በአንድ ወቅት በአገርህ ዉስጥ ያሉ ወጣቶች የሚያከብሩትን ጀግና ንገረኝና የአገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ እነግርሃለዉ ብሏል።በብዙ ወጣቶች ላይ የሚታየዉ የባዕድነት (የመገለል) ስሜት የመፍቻዉ መንገድከ “ሃገረ-ኢትዮጵያ ግንባታ ፕሮጀክት” ራስን ማግለል ሲሆን - በአገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ በርካታ ወካይ ብሔር ብሔረሰቦች አባት አገርን አምጦ መዉለድን እንደ መጤ ፋሽን (ዘመናዊ ሀሳብ) መዉሰድ ነው። እናም ከቀደመ የተመረጠ ማንነት (የብሔር፣ጎሳ፣ ቋንቋወዘተ…) ሥር የተለየ መለያ ግንባታ ላይ በመጠመድ ኢትዮጵያን እንደጠላት መመልከት እና ተቃራኒ ትርጉም መስጠት ነው።ይህንን ክስተት «የኢ-ኢትዮጵያዊነት ሂደት» በማለት ትርጉም ሰጥቼያለሁ። በኢትዮጵያ በተለያዩ ግለሰቦች፣ ጎሳዎች፣ ክልሎች እና ሃይማኖታዊ ቡድኖች መካከል ያልተፈቱ ከፍተኛ የቁርሾ፣ የፍትሕ መዛባት፣ ያለመተማመን እና እንዲያም ሲል ሥር የሰደዱ የመበቃቀል ጠጣር ስሜቶች አሉ። ከዚህ አንጻር ሲለካ ባብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን ባህልና ወግ እንደአሰቃቂ የሚታዩ ድርጊቶች በጥቂት አክራሪ ብሔርተኞች የተለመዱ አልፎ ተርፎም የጀግንነት መለኪያ ተደርገዉ ይታያሉ። ይህ የ”ኢ-ኢትዮጵያዊነት ሂደት” እየጠነከረ እና በፍጥነት እያሻቀበ መሆኑን የሚያመለከት ስሜት አለ።አሁን ባለዉ ነባራዊ ሁኔታ ማንም ግለሰብም ሆነ የፖለቲካ ባለሥልጣን በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ሁሉን አቀፋዊ ቅቡልነት የሌለዉ በመሆኑ አገሪቷ የበለጠ ፍትሐዊና “እውነተኛ ኢትዮጵያ/ኢትዮጵያውያንን” የመፍጠር ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው። ይህ አዝማሚያ በዚሁ ከቀጠለ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ግለሰቦች እና ቡድኖች የሚፈጽሙት ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያን መንግሥትና የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም የመጉዳትና የማጥቃት ስጋት ይጨምራል።አሁንም ቢሆን የአገሪቱን የጋራ ብሔራዊ ጥቅምና ሉአላዊነት የማስከበር ኃላፊነት ከተሰጣቸው አካላት መካከል አንዳንዶቹ መሰማት አልቻሉም፣ ራሳቸዉም ሆነ ብለዉ የፌዴራል መንግስቱን ትዕዛዝ ባግባቡ አይተገብሩም፣ አንዳንድ የህግ አስከባሪ አካላት ትንሽ ጥንካሬና የመወሰን ነጻነት ሲሰጣቸዉ ሌላውን የተቃራኒ ጥፋት መንገድ ይከተላሉ፣ የተደራጁ አካላት መምህራንን ጨምሮ አንዳንድ ጊዜ ባልተጨበጠ ተስፋ የረጅም አመጽ ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ፣ ተማሪዎች የራስን ስብዕና የማጉላት እና የብሔር ግጭቶችን ማነሳሳት ላይ ማተኮር እና ሠራተኞች ብዙ ጊዜ በሥራ ላይ እጅና እግሮቻቸውን መጎተት (ማልመጥ) ፣ በሙሉ አቅማቸው ያለመጠቀም እና የትርፍ ሥራ ክፍያ እንዲኖር ማድረግ ወዘተ… እየተከሰቱ ይገኛሉ። ሁሉም ሰዉ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በአገሪቱ አገዛዝና በተቋማቱ ላይ ያጉረመርማል።የሁሉንም የአመጽ ኃይሎች መሠረታቸዉን ለመናድ እናሌሎች የዉጭ ሰርጎ ገብ ቡድኖችን ለማጥፋትና የተረጋጋች ሀገር ለመገንባት የረዥም ጊዜ መፍትሔ የሚሆነዉ በሀገር ግንባታሂደት ዉስጥ የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በብልሃት መፍታት ብቻ ነዉ። ኢትዮጵያውያን እራሳቸውን እንደ አንድ ህዝብ አድርገዉ መመልከት ሲጀምሩ የአመጽና ሁከት ድርጊት ያበቃል እናም ቤኔዲክት አንደርሰን “imagined communities- አንድ ወጥ ምናባዊ ማህበረሰቦች” በማለት የሚጠራውን ስሜት በሚያንፀባርቅበት ጊዜ ሁሉ ነገር ያበቃል።ለአንደርሰን አንድ ሃገር ማለት በኅብረተሰቡ ህሊናዊ ማንነት ውስጥ በጥልቅ የተገነባ እና ኅብረተሰቡም ራሱን የቡድኑ አካል እንደሆነ የሚሰማውና የሚኮራበት ሲሆን ነው።ለእርሱ አገር ማለት “በሁሉም ዜጎች ህሊና ዉስጥ ግዙፍ ማንነት ያለዉ ዜጎች በጠባብ የብሔር ማንነት አስተሳሰብ ላላቸዉ ወገኖቻቸዉ ዕዉቅና የማይሰጡበት እንዲያም ሲል ብዙሃኑንእንኳን የማያውቋቸዉ፣ የማይቀበሏቸው ወይም የማይሰሟቸዉ በእያንዳንዱ ዜጋ ዉስጥ ያለዉን የኅብረት ስሜታቸውን ብቻ ነዉ የሚያቁዉት ሲሆን ነዉ።የሆነ ቦታ ተንገራግጮ የቆመውን የአገር-ግንባታ ሂደትን እንደገና ማስጀመር በአንድ ምሽት ላይ አይከሰትም ነገር ግን ቀጥሎ የተዘረዘሩት እርምጃዎች ግን ጥሩ ተስፋ አላቸው:-(ሀ) በሀገሪቱ ውስጥ ለሚታዩት በርካታ ችግሮች መፍትሔ እንዲሰጥ ታስቦ በተለያዩ ኃይሎች የቀረበውን የአገር አቀፍየዕርቅ፣ የይቅርታና የመግባባት ብሔራዊ ጉባዔ ባጠረ ጊዜ ሁሉንም የአገሪቱ ጉዳይ ያገባኛል/ይገባኛል የሚሉ አካላትን በማሳተፍ ማካሄድ ወሳኝ ነዉ። ሆኖም ግን በዚህ ጉባዔ ስኬት ላይ ያለኝ አንድ ጥርጣሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ግለሰቦችና ቡድኖች መካከል ከፍተኛ ጥልቀት ያለዉ ያለመተማመን በመኖሩ ነዉ። ሆኖም ስብሰባውና ዉይይቱ ባግባቡ ከተደራጀና ሁሉን በነጻነት ካሳተፈ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት በሃገረ-ኢትዮጵያ ግንባታ ፕሮጀክት ላይ የደረሰባቸዉን ቅሬታ እና ተስፋ መቁረጥ በማስተጋባት ወደ በጎ መንገድ እንዲመለሱ ተፅዕኖ ማሳደር የሚያስችል ታሳቢ መድረክ ሊሆን ይችላል። አገሪቷ ለመሠረታዊ የሀገር ግንባታ ችግሮች የረጅም ጊዜና ስር-ነቀል መፍትሔዎችን የምትፈልግ እንደመሆኗ መጠን የቀደሙ ቁስሎችን አዉጥቶ በግልጽ መነጋገሩ ተጠቃሽ ጠቀሜታ አለዉ። በተመሳሳይ መልኩ ከስብሰባው የተገኙ ምክረ-ሃሳቦችና በዉይይቱ የሚወሰኑ የውሳኔ ሃሳቦች በፍጥነትና ሳይቀናነሱ በቀናነት ከተተገበሩ ቅሬታ ያለባቸዉን ቡድኖች ለማበረታታትና ለማለዘብ ሊረዱ ይችላሉ።(ለ) ለዚህ ተፈታታኝ የሆነ አመጽና ሁከት የረጅም ጊዜ መፍትሔ በሁኔታዎችና ጊዜ ለዉጥ በሂደት ሊመጣ ይችላል። እየጨመረ የሚሄደው “የጎረቤት አገራት ትስስርና የጋራ ተጠቃሚነት አመለካከት ተስፋ” መጎልበት የአመጹን ማዕከላዊ ስበት ሀይል ለማለዘብ ይረዳል። ይህም በሀገሪቱ የኢኮኖሚዕድገትናበጎረቤት አገራት ርስ-በርስ ትስስርና የጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ የታየዉ የተስፋጭላንጭል፤ በምስራቅ አፍሪካ አገራት ኢኮኖሚ ትብብር ላይያተኮሩ አዳዲስ ኢኮኖሚያዊ ስምምነቶች የጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት(ጂዲፒ) ዕድገት በመጨመር በአፍሪካ ትልቅ ክፍለ-አህጉራዊ ኢኮኖሚን ለመፍጠር ያስችላል። በመሆኑም ሰዎች በባህሪያቸዉ ከስኬታማነት መለየት ስለማይፈልጉ ኢኮኖሚያዊዉ ዕድገት በተለይም ከፍትሃዊ የሃብት ስርጭት እና ሕዝብ ተኮር ዕድገት ጋር ተመጣጣኝ ከሆነ ከፋፋይ ጫናዎችን መቋቋም ያስችላል ምክንያቱም እነዚህ የግጭት ኃይላት ከሀገሪቱ በሚለዩበት ጊዜ ለወደፊቱ የሚመጣዉን ታላቅ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት በማሰብ የመልቀቅ ፍራቻ ያድርባቸዋል።(ሐ) አጠቃላዩ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ ሲመጣ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እርስ-በርስ የሚደረጉ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን በማጎልበት የሃገር ግንባታ ሂደቱን በአዎንታዊ መልኩ ማፋጠን ይችላሉ። ለምሳሌ በሰሜናዊው ክልል የሚመረተዉ ሰብል ወደ ደቡብ፤ ከደቡብ የሚመረተዉ አትክልት ወደ ሰሜን እየሄደ የጁስ መጠጦችን ለማምረት ጥቅም ላይ ይውላል። እንደነዚህ ያሉ ኢኮኖሚያዊ ትስስሮች ለየአካባቢው ነዋሪዎች ጥላቻን በማስታገስ የብሄራዊ አንድነት ለመመሥረት ምክንያት ይሆናሉ።(መ) ከተሜነትንና ኢንቨስትመንትን በፈጣን ሁኔታ ማስፋፋት፣(ሠ)”በብሔራዊ- ሃገር ግንባታ የመጀመሪያውና በጣም አስፈላጊው አካል የሕግ ስርዓት ነው። ምክንያቱም ሕግ የብሔራዊ ትስስር ምንጭ ነው። መንግስት ህጋዊ ስርዓቱን በጥንካሬና ያለማወላወል እንዲሁም ያለምንም አድልኦ መተግበር አለበት።

አመጹን ለማርገብ የአጭር ጊዜ መፍትሔዎች

በአጭር ጊዜ እና በረጅም ጊዜ ውስጥ መንግስት ሲሆን ሲሆን በአነስተኛ አርጩሜ ገረፍ-ገረፍ በማድረግ ህግና ስርዓትን ማስከበር ገፋ ሲል “ከብሔራዊ ኬክ የድርሻቸዉን ቁራጮች በመስጠት” ወይም “ወደ ውስጥ ጠልቀዉ እንዲገቡ በማበረታታት” መቀራረብን መፍጠር አለበት። በምዕራቡ ዓለም ይህ የካሮት እና ዱላ ስትራቴጂ ይባላል። መንግስት ሊወስዳቸው ከሚችሏቸው የአጭር ጊዜ እርምጃዎች ውስጥ አንዳንዶቹ:-የክልል መንግስታትን አቅም በማጠናከር ለደረሰዉ ጉዳትና ኪሣራ ክስ እንዲመሠረቱ በማድረግ ህግና ስርዓትን እንዲያስከብሩ ማድረግ እና አመጹን ለማረጋጋት በሚካሄደው እንቅስቃሴ የመሪነት ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ። በስዒረ-ነገር ትንታኔዉ መሠረት ምናልባት የክልል መንግስታት (የዞንና ወረዳ አመራሮች) አመጹን በገንዘብ በመደገፍም ሆነ የሞራል ትብብር በማድረግ እጃቸዉ ካለበት በ 2012 የሚካሄደውን ምርጫ ከአመጸኞች ለመለየት እንዲረዳው በማድረግ የተቃዋሚዉን የአመጽ ጽንሰ ሃሳብ ሊቀንስ ይችላል። በዚህ አጋጣሚ በአመጽ ኃይሎች ላይ የጋራ ተቃዉሞን ለማነሳሳት የስዒረ-ነገር ጽንሰ-ሀሳቦች ህግና ስርዓት የማስከበር እንቅስቃሴዉን የበለጠ አስቸጋሪ እንደሚያደርጉት ማመልከት አስፈላጊ ነው።በሃገሪቱ ውስጥ ያሉትን ድህነት፣ ሥራአጥነት፣ ከፍተኛና መደበኛ እንዲሁም የጎልማሶች ትምህርት እና የመሳሰሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ጨምሮ በሃገሪቱ ውስጥ ያሉ በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ለመፍታት የመፍትሔ ሃሳብ የሚያቀርብ በኢኮኖሚ፣ማህበራዊ፣ ቴክኖሎጂያዊና ፖለቲካዉ ባለሙያዎች የተደራጀ አንድ ተቋም መፍጠር ነዉ። ይህ መድረክ በአካባቢው የሚኖሩትን ሰዎች ልብ እና አእምሮ በማለስለስ እና የአመጽ ሃይሎች የሚመገቡትን የአካባቢው ቅሬታዎች ለማሸነፍ አንዱ መንገድ ነው።የአመጽ ኃይሉ ተሟጋቾች ወይም የገንዘብ ደጋፊዎች ተብለው በሚታወቁ ግለሰቦችና አካላት ላይ ክስ መመሥረት እና ፍርድቤቶች ሙሉ ስልጣን እንዲኖራቸው በማድረግ በሂደቶቹ ውስጥ ፈጣን እና ፍትሐዊ የፍርድ ዉሳኔዎችን ማካሄድ። ተጠርጣሪዎች ለብዙ ወራት ወይም ለዓመታት በፍርድ ችሎት የሚቆዩ መሆኑ ተቃውሞ ይፈጥራል ብዙውን ጊዜም ለተጠርጣሪዎች አላግባብ እንደተበደሉ ተደርጎ የርህራሄ ስሜት ለማሳደግ መንገድ ይከፍታል። እነዚህ የአመጽ ቡድኖች በፌዴራል መንግስቱ የፍትህ ስርዓት ላይግልጽ ተቃውሟቸውንና አድሎአዊነቱን እየገለጹ በመሆኑ ወንጀሉ በተፈጸመበት አካባቢ ባሉ የፍርድ ተቋማት በግልጽ ችሎትና የፍርድ ትችት በማሰጠት ተጠርጣሪዎችን ለፍትሕ ማቅረብ ስልታዊ ዘዴ ሊሆን ይችላል። በእነዚህ የአካባቢ ፍርድ ቤቶች በግልጽ የአሰራር ስርዓት መሠረት የሚሰጡት ቅጣት የፌዴራሉ መንግስት በብሔሩ ላይ እንደ ማሴር ተደርጎ አይቆጠርም።በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ወይም የተጎዱ ተብለዉ በተለዩ አካባቢዎች የሚገኙ የአካባቢው ህዝቦች ልብ እና አእምሮ ለማሸነፍ የታቀደ እንደ ማርሻል ፕላን አይነት ማቋቋም፤ ፕላኑም ጥራት ያለው ትምህርት መስጠት፣ የአካባቢያዊ አቅምመገንባትእና የሥራ ዕድል መፍጠር ላይ ማተኮር ይኖርበታል፣ ከብሔረተኛ ቡድኑ ዉስጥ ለዘብተኛ የሆኑ ሰላማዊ ግለሰቦችን በሃገር ባህልና ወግ በሽምግልና ይቅርታ እንዲያገኙ በማድረግ አክራሪ ኃይሎችን በመለየት ለማጥፋት አማራጮችን ማፈላለግ እና ይህንኑ ለመፈፀምና ለማፅደቅ የሚረዱ ዘዴዎችን ማፈላለግ።

አስተያየት