ኅዳር 10 ፣ 2011

የእርዳታና ብድር ፖለቲካ

ወቅታዊ ጉዳዮች

ከፉዎቹ ሳምራውያን(Bad Samaritans)የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ላይ እየሱስ ክርስቶስ የሚያወሳው አንድ ታሪክ አለ። አንድ የዚያ ዘመን ልግመኛ ህግ…

የእርዳታና ብድር ፖለቲካ
ከፉዎቹ ሳምራውያን(Bad Samaritans)የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ላይ እየሱስ ክርስቶስ የሚያወሳው አንድ ታሪክ አለ። አንድ የዚያ ዘመን ልግመኛ ህግ አዋቂ ኢየሱሰን “ የዘላለም ህይወት አገኝ እንደሁ ምን ላድርግ ? “ ብሎ ይጠይቀዋል። እየሱስም መልሶ “ የተጻፈውና አንተ ያነበብከው ምን ይሆን? “ ብሎ ቢጠይቀው “ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ” ይላል ልግመኛው። እየሱስስም “በቃ እሱን አድርግ” ቢለው እውነተኛ ባልንጀራዬንስ በምን አውቃለሁ ሲል ይጠይቃል ። ይህን ጊዜ ነው አየሱስ ስለደጉ ሳምራዊ የሚያነሳው። አንድ መንገደኛን ሽፍቶች ደብድበውና ዘርፈው በሞትና በመኖር መሃል ላይ እያለ ከመንገድ ጥለውት ይሄዳሉ። ይህ መንገደኛ ሲያቃስት የተመለከቱ የአይሁድ ካህንም ሆኑ የሌዋዊ ሰዎች እንዳላየ ጥለውት ሲያልፉ በመጫረሻ የመጣው ሳምራዊ ግን ያን መከረኛ ሰው ጥሎት መሄድ አልቻለም። ጠጋ ብሎ የተደበደውን መንገደኛ ቁስል በወይን ጠጅ አጥቦ የወይራ ዘይት አፍሶ ካሰረለት በኋላ በአህያው ጭኖ ወደማረፊያ ወስዶ ተንከባከቡልኝ ወጭውንም ሁሉ እኔ እሸፍናለሁ ይላል።ይህ ሰው በመጽኃፍ ቅዱስ ላይ ደጉ ሳምራዊ በመባል ይገለጻል።  እየሱስም የዚህ ሰው ባልንጀራ ይህ ሳምራዊ ነውና አንተም ይህን አድርግ ሲል ለህግ አዋቂው ያሰተምራል።የዚህ ታሪክ መልዕክት ጥሩ ስራህን ድጋፍህንና ወገንተኝነትህን ለወደቀና ያንተን እርዳታ የሚሻ ለማታውቀው መንገደኛ ብትዘረጋ በፈጣሪህ ፊት ባልንጀራህን እንደራስህ እንደወደድክ ተደርጎ ነው የሚታይልህ የሚል ነው።የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር፤ ደቡብ ኮሪያዊው ሃ ጁን ቻንግ ከዚህ በጎ ምግባር በተቃራኒ ሲነጉዱ ተመለከትኳችው ያላችውን ምዕራባዊያንን እና የነሱን ተልዕኮ አስፈጻሚ ብሎ የሚያምናቸውን ተቋማት ክፉዎቹ ሳምራዊያን (Bad Samaritans) ሲል 2014 ላይ ባሳተመው መጽሃፉ ይጠራችዋል። በዚህ ሳያበቃ ፕሮፌሰር ቻንግ አይ ኤም ኤፍ የዓለም የንግድ ድርጅትንና የዓለም ባንክን (IMF, World Trade Organization and World Bank)  ሰለስቱ እርኩሳን (Unholy trinity) ሲልም ሰይሟቸዋል።ዛሬ እነዚህ ተቋማትና ባለጸጋ ሃገራት፤  ድሃዎቸን ይህን ብድርና እርዳታ ለማግኘት ከፈለጋችሁ ፤ይህን አድርጉ ይህን አታድርጉ እያሉ ሲመክሩ ይታያል። ለድሃ አገሮች ከሚያስቀምጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከልም የመንግስት ንብረቶችንና ተቋማትን ወደግል ይዞታ በፍጥነት አዙሩ፤ገበያችሁንም ክፈቱ፤ የመንግስትንም ሚና ከገበያ ውስጥ ቀንሱ፤ የሚሉት ይገኙበታል። ይህንን ፕ/ር ቻንግ የበሉበትን ወጪት መስበርና አዙሮ አለማየት ይለዋል። እነዚህ አገሮች በአንድ ወቅት የራሳቸውን ገበያ ከውጨ ተጽዕኖ ለመጠበቅ የሚችሉትን ሁሉ ሲያደርጉ እንድነበር የሚያስታውሰው ቻንግ፤ እነሱ ሽቅብ የወጡበትን መሰላል ሌሎች እንዳይጠቀሙበት ዛሬ በሾኬ እየጣሉትነው ይላል። (they are kicking away the ladder they used to climb up)ዶር በፈቃዱ ደግፌ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ መምህራን መጽሄት-ውይይት ላይ በ1984 ዓም ባሳተሙት “የዓለም ባንክ ኢኮኖሚን የማቅናት ዘዴ ለኢትዮጵያ ያዋጣል?” ሲሉ ባቀረቡት ጽሁፍ ሲገልጹ ብዙዎቹ ለጋሽ አገሮች ለኢተዮጵያ መሪዎች፤ የአለም ባንክንና የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (በአጭሩ አባ/አገድ ይሉታል ዶሩ) የሚሰጧችሁን አሰራርና የመዋቅር ማስተካከያ ስትቀበሉ፤ የበለጠ እርዳታ እነሰጣችኋለን ይሉ ነበር። እንደዶር በፈቃዱ ከሆነ የአባ/አገድ የመዋቅር ማስተካከያ ግፊት ተቀባይነት ባገኙባቸው አገሮች እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ያለማምጣታቸው ነበር በዙ ታዳጊ አገሮቸን የማሰተካከያ ሃሳቡን በስጋት እንዲያዩት ያደረጋቸው። ” አባ/አገድ የአለም ኢኮኖሚ ነጻ አውጭ ግንባር ነው። ታዲያ እንደማንኛውም ነጻ አውጭ ግንባር የሚያተኩረው በአላማው መሳካት ላይ እንጂ በሚጠቀምበት ዘዴ ድክመትና ጥረቱ ሊያስከትል በሚችለው ችግር መፍትሄ ላይ አደለም” ይላሉ ዶር በፍቃዱ።ኢትዮጵያ እርዳታና ብድርጠ/ሚ ዶር አብይ ስልጣን ከያዙ ወዲህ መካከለኛው ምስራቅ አንስቶ እስከ ቅርቡ የአውሮፓ የጉብኝት ጉዟቸው ድረስ ትልቁ ሰኬታችው ተብሎ ከሚጠቀሱላቸው ጉዳዮች አንዱ ብድርና ዕርዳታ ነው።የዩናይትድ አረብ ኤሜሬት ልዑል ለኢትዮጰያ የሶስት ቢሊዮን ዶላር የእርዳታና ኢንቨስትመንት ድጋፍ ማድረጋቸው የዚያ ሰሞን ትልቅ ስኬትና ደስታ ተደርጎ ተወስዷል።ብድርና እርዳታ ላኢትዮጵያ አዲስ አደሉም። የዘመናዊት ኢትዮጵያ ካዝና ከመነሻው አንስቶ የብድርና እርዳታ ሰነዶችን አጥቶ አያውቅም።ማርጀሪ ፕርሃም የኢትዮጵያ መንግስት (The Government of Ethiopia) በሚል ሰይማው ኖርዝ ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ 1969 ላይ ባሳተመላት መጽሃፏ እንደጠቀሰችው፤ሃጼ ሃይለስላሴ ከስደት መልስ ጥር 23 1934 ዓም ከእንግሊዝ መንግስት ጋር ወታደራዊና ሌሎች ጉዳዮችን የተመለከተ አንድ ስምምነት ፈረሙ። የዚሀ ሰምምነት አራተኛ አንቀጽ እንደሚገልጸው፤ንጉሱ የእንግሊዝን መንግስት በጠየቁት መሰረት፤መንግስታቸውን መልሰው የሚያቋቁሙበት ቢበዛ ለአራት ዓመታት የሚቆይና ለመነሻ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የእንግሊዝ ፓውንድ እርዳታ እንዲስጣችው ይላል።ንጉሱም ይህንን ገንዘብ ተጠቅመው ከስደት መልስ የመንግስትን ካዝና ሊሞሉ ቻሉ። መጠኑ እንደየጊዜው ይለያይ እንጂ እስክዛሬ ድረስ ከውጭ ብድርና እርዳታ የተላቀቅንበት ጊዜ የለም። በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ ከአገር ውስጥና ከውጭ በብድር የወሰደችው ወደ 47 ቢሊዮን ዶላር ሲያናጥርባት፤ ከዚህ ውስጥ 24 ቢሊዮኑ የውጭ ብድር ነው።የእርዳታ ዋጋ (Cost of Aid)የሃብታሞች እርዳታ በብዙዎች እንደሚታሰበው በነጻ የሚገኝ የሃብታሞች እርዳታ በብዙዎች እንደሚታሰበው በነጻ የሚገኝ ነገር አደለም። ክፍያ አለው። በምዕራቡ አለም ውስጥ የምትካሄድ እያንዳንዷ ፖለቲካዊ ውሳኔ፤ የዶላር  ምጣኔዋ ይሰላል። ትርፍና ኪሳራዋ በገንዘብ ይተመናል። ከነዚህ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ውስጥ ደግሞ የውጭ እርዳታ (Foreign Aid ) አንዱ ነው። የውጭ እርዳታ ለማን፤ በምን ያህል ዋጋ ቢሰጡት፤ የሚያመጣው ትርፍስ ምን ያህል ነው የሚለውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሰራትኞች  እንቅልፍ አጥተው ሲያሰሉት የሚያድሩት ጉዳይ ነው። ይህንን ነው ጁን ቻንግ የክፉ ሳምራዊያን ምግባር የሚለው።ብሩስ ቡኖ እና አላስቴር ሰሚዝ በ2011 ባሳተሙት Dictator’s handbook በተሰኘ መጽኃፋቸው የ“ለጋሽ” አገሮች የውጭ  እርዳታ ሂሳብ እንዴት እንደሚሰላ ይተነትናሉ። እንደፀሃፊዎቹ ከሆነ የእርዳታ ዋጋ ሲሰላ ሶስት ነገሮች ከግምት ይገባሉ።
  1. የእርዳታ ፈላጊዋ አገር የመንግስት ባህሪ (Democratic Vs Undemocratic government)
የአሜሪካ የእርዳታ ገንዘብ ብዙውን ጊዜ ወደአምባገነኖች እንደሚፈስ የሚናገረው ይህ መጽሃፍ፤የቅርብ ምሳሌ ብሎም ግብጽና ፓኪስታንን እንዲሁም የ1980ዋን ላይቤሪያ ያነሳል። አሜሪካ ለምን አምባገነኖችን የእርዳታ ምርጫዋ አደረገች የሚለውን ጥያቄ መጽኃፉ፤ ምክንያቱም ይላል፤ምክንያቱም አምባገነኖች የሚመሯቸው አገሮች የእርዳታ ዋጋቸው (cost of aid) አዋጪና ርካሽ ስለሆነ ነው ይለናል። ይህንን በምሳሌ ሲያስረዳ አምባገነናዊ ሥርዓት ውስጥ ያሉ አገራት መንግስት የሚቆመው በጥቂት ስልጣን አካባቢ በማይጠፉ የአምበገነን አጫፋሪዎች ነው። በመሆኑም በእነዚህ አገራት መንገስታት የስልጣን ምንጫቸውና የስልጣናቸው ባለቤት መጠን (winning coalition size) ብዙሃኑ ዜጋ ሳይሆን እነዚሁ ጥቂት አጫፋሪዎችና የስልጣን ጥቅም ተጋሪዎች (State privileged) ናቸው። ስለዚህ አምባገነን መንግሰታት ማንኛውንም ውሳኔ ሲወስኑ፤ ሰፊውን ህዝብ ይርሱት እንጂ፤ አጠገባቸው ያሉትን የስልጣናቸውን ጠባቂዎች ሊዘነጉ አይችሉም-ካለነሱ ጥበቃ መንገስታቸው ሊጸና አይችልምና።እርዳታ ተቀባይ አገር የመንግስት ፖሊሲን የልዋጭ እቃ (Policy concession) አድርጎ ማቅረብ ይኖርበታል። የሚከተለውን ፖሊሲ ይቀይራል፤ይተዋል ወይም ደግሞ አዲስ ፖሊሲ ያሰተዋውቃል። ይህም የፖሊሲ ለውጥ (Policy Concession) ይባላል።እንደ መጽሃፉ አምባገነን መንግስታት ይህንን የፖሊሲ ለውጥ (Policy Concession) በቀላሉ ይቀበሉታል። የፖሊሲ ለውጣቸውን በርካሽ  ይሽጡታል። በእንዲህ ዓይነቱ ሥርዓት ከእርዳታው የሚገኘው ገቢ (Aid Revenue) ለጥቂት የአምባገነን አሸርጋጆች (Essential backers) ሲካፈል በነፍስ ወከፍ የሚገኘው ጥቅም ከፍ ያለ ነው። መጽኃፉ ይህንን በምሳሌ ሲያስረዳ አንድ በአምባገነን ስርኣት ስር ያለች አገር 100 ዜጎች ቢኖራትና የመንግስቱን ስልጣን የሚጠብቁት አሸርጋጆች (Essential backers) 10 ፐርሰንት ወይም 10 ብቻ ቢሆኑ ሲል ይጀምራል። ለዚህች አገር የ100 ሺህ የአሜሪካን ዶላር እርዳታ አግኝታ ፖሊሲዋን ለመቀየር፤ የእርዳታ ገቢዋን ለ10 ሰዎች ብቻ አካፍላ የስልጣን ጠባቂዎቿን ይሁንታ ማግኘት በቂዋ ነው። የስልጣን ጠባቂዎቹ የነፍስ ወከፍ ገቢም 10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ነው።  የፖሊሲ ለውጡ ሀዝብን ጠቀመም ጎዳ ተቀባይነት ያገኛል።ይችው አገር ዴሞክራሲያዊ መንግስት ቢኖራትና ቅቡልነቱ የቆመው ቢያንስ በ50 ሰዎች ቢሆን ግን ተመሳሳዩ የእርዳታ ገንዘብ የነፍስ ወከፍ ጥቅም ከ2 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በታች ነው። ይህ አይነቱ መንግስት ዜጎቹን አሳታፊና፤ቅቡልነቱም ዜጎቹ ላይ የወደቀ በመሆኑ የእርዳታውን መጠንና በምላሹ የሚጠበቀውን የፖሊሲ ለውጥ ለመቀበል ወይም ለመተው የመደራደሪያ አቅሙ ትልቅ ነው። የስልጣን ዋስትናዎቹን  ዜጎቹን ከሚያስቀይም እርዳታው ይቅርብኝ ሊል ይችላል ወይም ደግሞ የእርዳታውን መጠን አሳድጉልኝ ብሎ ይደራደራል።  በመሆኑም የዴሞክራሲያዊ ሃገራት የእርዳታ ዋጋ ለለጋሾች ከፍተኛ ነው።የምጣኔ ሃብት ባለሙያውና በድቡብ አፍሪካ ለሚገኝ አንድ አፍሪካ አቀፍ የምጣኔ ሃብት ተቋም የሚሰሩት ዶር ቢኒያም በዳሶ ይህን  በሃልዮት ደረጃ የምቀበለው ነው ይላሉ። ወደአገራችን ስንምጣም የኢትዮጰያን ከውጭ እርዳታ ጋር የተያያዘ የፖሊሲ ለውጥ የሚወሰኑት ቢበዛ በኢህሃዴግ ስራ አስፈጻሚ አባላት ናቸው ባይ ናችው።የብዙውን ዜጋ ጥቅም ተከበረ አለተከበረ ግድ የሚለው የለም ሲሉ ይጨምራሉ። “ቢሆንም የፖሊሲ ለውጡ ጥያቄ ከጠነከረና ከስልጣን ጋር ከተገናኘ ገን፤ሰራ አስፍጻሚውም ቢሆን ላይቀበለው ይችላል ሲሉ ያከላሉ። “ለምሳሌ ኢህአዴግ መሬትን የግል አድርግ ቢባል ከስልጣኑ ጋር ቀጥታ የሚገናኝ ጉዳይ በመሆኑ ጥያቄውን ላይቀበል ይችላል” ይላሉ።
  1. በእርዳታው ምላሽ የሚገኘው ጥቅም (What the Policy Concessions are worth)
ሌላኛው የእርዳታ ዋጋ መወሰኛ ከእርዳታ ተቀባዩ የፖሊሲ ለውጥ የሚገኘው ጥቅም ረብ ያለው ነው ወይ የሚለው ነው። መጽኃፉ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ አድርጎ ግብጽን ይጠቅሳል። ግብጽ ከ1979 የካምፕ ዴቪድ ስምምነት አንስቶ ከፍተኛ የሚባለውን የአሜሪካን እርዳታ የምታገኝ አገር ናት። ግብጽ በህዝብ ብዛቷና ባላት  የአረቡ ዓለም ተሰሚነት እስራኤልን እንደመንግስት እውቅና መስጠቷ ለአሜሪካ እጅጉን ትልቅ የሆነ እርባና ያለው የፖሊሲ ጉዳይ ነበር። ለዚህም አሜሪካ ብዙ ብትከፍል ያዋጣታል።ዶር ቢኒያም ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያም ትልቅ አገርና በምዕራባውያን ዘንድ ከፍ ያለ የፖለቲካ መልከአ ምድር (Geo-poltical) ጉልበት ያላት አገር በመሆኗ፤የተድራዳሪነት አቅሟ ጥሩ ነዉ ይላሉ።አሜሪካዊያን ታክስ ከፋዮች ልጆቻቸው በሶማሊያ በረሃ በ1993 በመኪና ታስረው ሲጎተቱ ካዩ በኋላ ወታደሮቻቸው ወደ አፍሪካ እንኳን ሊዘምቱ ፊታቸውን አዙረው እንዲተኙ አይፈልጉም። የሶማሊያ መንግስት ፈራርሶ ህንድ ውቅያኖስ በባህር ላይ ዘራፊዎች በተወረረ ወቅት፤ እንዲሁም አልሸባብ ምስራቅ አፍሪካና ይህንኑ የባህር ላይ የንግድ መስመር አደጋ ውስጥ በከተተበት ወቅት፤ አሜሪካ በውክልና የሚሞትላት ብታገኝ ለዚህም ሳትሰስት እርዳታ ብትዘግን አዋጪ ነበር። በዚህ ጉዳይ ሌላ የሚያዋጣት ገበያ እንደሌለ የተገነዘቡት የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊም ኒኦሊበራሊስቶች እያሉ አሜሪካኖችንና መሰሎቻቸውን ከመተቸት አልፈው፤የሚሰጡን እርዳታ የእኛ ሉአላዊነት (Policy Autonomous) ካላከበረ እርዳታቸውን ይዘው ገደል መግባት ይችላሉ እያሉ ደጋግመው ይገልጹ ነበር። ይህ የአቶ መለስ የአቋም ጽኑ መስሎ መታየት የማይዋጠላቸው የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩንቨርሲቲ የታሪክ መምህሩና ተመራማሪው ዶር ታምራት ሃይሌኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከእርዳት ሰጪ የመደራደር አቅሟ መድክሙን ያንሳሉ። አጼ ሃይለስላሴ ከእንግሊዞች የሚመጣባቸውን ተጽዕኖ ለመቀነስ የቻሉትን ሁሉ ያደርጉና የተማሩ ኢትዮጵያውያንን የፖሊሲ ማውጣትና መተግበር ላይ ከውጭ ሃይሎች ተጽዕኖ ለማላቀቅ ይጥሩ ነበር። ደርግ በሶቭየቶች ተጽዕኖ ስር የውደቀ ሲሆን፤ኢህ አዴግ ደግሞ ከዚያም ብሶ በብዙ ዘርፎች ላይ በተለይም ትምህርትና ጤና ላይ የውጭ ሃይሎች ፖሊሲ እስከምቅርጽና የራሳችውን ይሰው ሃይልም በየሚንስትር መስሪያ ቤቱ ሲሰግስጉ ይታያል ባይ ናችው። በዚህ ጉዳይ የሚስማሙት ዶር ቢኒያም፤ በተለይም የቻይና የውጭ ጉዳይና ዕርዳታ ወይም ብድር አላማ ያመረተችውን መሸጫ ቦታ ማግኘትና የሰው ሃይሏን የምታሰማራበት አገር ፍለጋ በመሆኑ ከዕርዳታ ወይም ብድራቸው ጋር አብረው በርካታ የሰው ሃይልን ይለካሉ።
  1. እርዳታ ፈላጊዋ አገር ምን ይህል ተቸግራለች? (Needier countries are likely to get less aid)
ምእራባውያን ሆኑ ማንም ባልጸጋ ሀገር እርዳታ ሊሰጥ ሲል የእርዳታ ፈላጊዋን አገር ጓዳ ያያል፤ካዝናዋ ባዶ እንደሆነ ያረጋግጣል። ካዝናዋ ተራቁቶ የተገኘች እርዳታ ጠያቂ አገር ለማንኛዋም ተጨማሪ የእርዳታ ዶላር ያላት ጉጉት፤ የመደራደር አቅሟን፤ይሄን አላደረግም አደረጋለሁ የምትልበት ሃሞቷን ይሟጥጠዋል። ጠቅላይ ሚንስትር አብይም ሆኑ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ደጋግመው  “ ድሃ ምን ሉኣላዊነት አለው?” ሲሉ ተሰምተዋል። ድሃ አገር በቀውስ ማግስት ካዝናው ባዶ ነው። አዲሱ ጠቅላይ ሚንስተር 27 ዓመታት ከቆየው ዘረፋና ሶሰት ዓመታት ኢትዮጵያን ሲንጣት ከከረመው አለመረጋጋት ማግስት የተረከቡት ካዝና ባዶ ነበር፤ በተለይ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አገሪቱን አዙሮ ሊደፋት የደረሰበት ወቅት ነበር። በዚህ ወቅት የእኛ የእርዳታ ዋጋ (Cost of Aid) ለለጋሾች ርካሽ ነው። መንግስት ይህን ፖሊሲ ለውጥ ይህንን ፖሊሲ አምጣ ቢባል አሻፈረኝ ማለት ይከብደዋል። ከእከሌ ጋር ታረቅ ከእንትና ጋር ደሞ ተጣላ ቢባል መግደርደር ይሳነዋል።ዶር ቢኒያም እንደሚሉት ምዕራባውያንም ሆኑ ተቋሞቻቸው አሁን የተፈጠረውን ክፍተት ሊጠቀሙበት ይፈልጋሉ። አባ/አገድ ኢትዮጵያን በሯን ለገበያ ስርዓት እንድትከፍት ደጋግመው ሲጠይቁ ኖረዋል። ከዚህ በመነሳትና ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ የታየውን መለሳለስና የድርድር አቅም መዳከም አይተው የጠነከረ ግፊት (Too far push) ሊያደርጉ ይችላሉ።  ይህንን መቋቋም ያስፈልጋል። ካለበለዚያ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የብድር አዙሪት (Debt Cancellation circle) ውስጥ ይገባና ወደ ሌላ ቀውስ ያመራናል ይላሉ።የእርዳታ ፋይዳየምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ሳሙኤል ሙሉጌታ ምንም እንኳን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የማርሻል እቅድ ብዙ የአውሮፓ አገሮችን ወደ ብልጽግና ቢቀይርም፤ እርዳታ ብቻውን የእድገት ምንጭ ሊሆን አይችልም ይላሉ። እድገት ካስፈለገ የፖለቲካ መረጋጋት፣የምጣኔ ሃብት መብቶችን (Economic rights) የሚያስጠብቁ ተቋማትን ማጠናከር ወሳኙ ጉዳይ እንደሆነ ያውሳሉ። ዶር ቢኒያም በበኩላችውብዙ ጊዜ የዕርዳታና ብድር አስፈላጊነትን ለመግለጽ ሰዎች እንደምሳሌ የማርሻል እቅድን ያነሱና አፍሪካም እንዲሁ በዕርዳታና ብድር የምትለውጥ ይመስላችዋል። አውሮፓ በተለወጠችበት መንገድ ግን አፍሪካን መለወጥ ከባድ ነው ይላሉ። አቶ ሳሙኤልም ሆኑ ዶር ቢኒያም ለኢትዮጵያ ከዕርዳታ ጋር የተገናኙ የፖሊሲ ለውጦችን በተመለከተ የአባ/አገድን ሆነ የምዕራባዊያንን “ ጨርሶ ተከፈቱ፤ሁሉንም ለገበያ ፍርድ ተውት “ የሚለውን አከራሪ ( dogma) አመለካከት መገዳደር፤ሁሉንም ነገር መንግስት ይወጣዋል የሚለውንም የቆየ የመንግስት አስተሳሰብን ትቶ ወደ መሃል መመጣትን ይመክራሉ።ዶር ቢኒያም በተለይ እንደሚሉት እርዳታ በብዛት ወደ አንድ አገር መምጣቱ የራሱ የሆነ ጉዳቶችም አሉት ። የመጀመሪያው ሳይሰራ በዕርዳታ በሚመጣው ገንዘብ ምክንያት የአገልግሎት ዘርፍ ካልቅጥ ማደግ (Dutch disease) ሲሆን ይህም ሌላውን ዘርፍ በመጉዳት የምጣኔ ሃብት ቀውስ ውስጥ ሊከት ይችላል። ሌላኛው የዕርዳታ ኢኮኖሚ ላይ መንጠላጠል የሚኖረው አሉታዊ ተጽዕኖ ተጠያቂነት ነው። ዜጎች ታክስ ከከፈሉ መንግስትን ተጠያቂ ለማድረግ ይሞክራሉ። ነገር ግን በዕርዳታ የተገኘ ገንዘብ ላይ ባለስልጣናት የመጠየቅ ዕድላቸው አንስተኛ ይሆናል።ዶር ቢኒያም ዕርዳታ ሌላም  የጎንዮሽ ክፍትቶች አሉት ባይ ናችው። ዕርዳታ ከዴሞክራሲያዊ ቅቡልነት(Democratic legitimacy) ይልቅ የአፈጻጸም ቅቡልነትን (Performance Legitimacy) ያመጣል። ኢህአዴግ ብዙ ጊዜ የመሰረተ ልማት አፈጻጸሜ እጅግ የተዋጣ ነው፤በዚህም ዋነኛ ጠላታችንን ድህነትን እያደባየሁት ነው ሲል ይሰማ ነበር። እንደ ዶር ቢኒያም ይህ ባትመርጡኝም የአፈጻጸም ቅቡልነት ስጡኝ እንደ ማለት ነው። ይህ አስተሳሰቡ ኢህአዴግን ወደለየለት አምባገነንነት ወስደውት ነበር።ከወራቶች በፊት ጠቅላይ ሚንስትር ዶር አብይ ከሳኡዲ ጉብኝታቸው መልስ በሚሊኒየም አዳራሽ ተገኝተው ለበርካታ ህዝብ የማነቃቂያ ንግግር ባደርጉበት ወቅትም፤ስለጉብኝታቸው ስኬት አነሱና “ በነበርንበት ሃገር ምን ትፈልጋላቸሁ ስንባል፤ገንዘብ ሳይሆን፤ዜጎቻችችንን ፍቱልን ነበር ያልነው። የሚገርመው ነገር ግን ዜጎቻችንን ስናከብር፤ዜጎቻችን ሲፈቱ ያልጠየቅነው ሁሉ ይሰጣል” በማለት ከፍተኛ የሆነ ብድርና እርዳታ ቃል እንድተገባላችው ሲገልጹ ነበር።ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት ዜጎቻችውን እያክበሩ ያልጠየቁትን እንደተሰጣቸው ይቀጥላሉ ወይስ እንደ መለስ ዜናዊ ዜጎችን እያዋረዱ የአፈጻጸም ቅቡልነትን( Performance legitimacy ) በመጠየቅ  “ ዋነኛው ጠላታችን ድህነት ነው “ ወደማለት ይመለሳሉ?ለሁሉም ጊዜ አለው። ያም ሆኖ ጊዜ ከፉዎቹን ሳምራዊያንስ ደግ ያደርጋቸው ይሆን?

አስተያየት