ኅዳር 10 ፣ 2011

የሜቴክ ቅስም ሰባሪ ተረክ

ወቅታዊ ጉዳዮች

ቀስ እያለ የተገለጠው የሜቴክ ነገር በዜጎች ላይ ብሔራዊ ውርደት እና መሸማቀቅን አስከትሏል፡፡ እንደዋዛ ከሚነገረው ሚሊዮኖች እና ቢሊየኖች ከሚቆጠረው…

የሜቴክ ቅስም ሰባሪ ተረክ
ቀስ እያለ የተገለጠው የሜቴክ ነገር በዜጎች ላይ ብሔራዊ ውርደት እና መሸማቀቅን አስከትሏል፡፡ እንደዋዛ ከሚነገረው ሚሊዮኖች እና ቢሊየኖች ከሚቆጠረው የባከነ የድሃ ሀገር ጥሪት ጀርባ ያለውን ተረክ ስንታየሁ ማሞ እና አቤል ዋበላ እንዲህ ቃኝተውታል፡፡ሻሸመኔ፡ራስ ኃይሉከአዲስ አበባ ወደ አርባምንጭ ጉዞ ጀመርን። ሻሸመኔ የሻይ እረፍት ማድረግ ፈልገን ቆም አልን ።እንዱ ወዳጃችን አንድ ለየት ያለ ቤት ላስጎብኛችሁ ብሎ ወሰደን። ከዋናው መንገድ 200 ሜትር እንደገባን አንድ ጭር ያለ ግቢ አንኳን። አንድ ቀጠን ያሉ ሽበት ጣል ጣል ያደረገባቸው ሰው በሩን ከፍተው በፈረንጅ አፍ አወሩን። ለጉብኝት እንደመጣን ስንነግራቸው ወደግቢያቸው ይዘውን ገቡ። ራስ ኃይሉ ይባላሉ። የጥበብ ሰው ናቸው። በሙዝ ቅጠል ላይ የተለያዩ ስዕሎችንና ቅርጾችን የሚሰሩ ጥበበኛ ። ካሳዩን ካስጎበኙን ነገሮች ሁሉ የገረመን በመስታወት በተከለለ መደርደሪያ ያስቀመጡት አንድ የገንዘብ ኖት ነው።ራስ ተፈሪያኑ ራስ ኃይሉ ወደብር ኖቱ በኖቱም ላይ ስላለው ምስል በኩራት አስረዱን። የህዳሴ ግድብ ዲዛይን ንጉስ ኃይለስላሴ በ1960ዎቹ አሰርተውት እንደነበር በገንዘብ ኖቱ ላይ ደመቅ ብሎ ይታያል። ይህንን እዉነታ አንድም የሃገራችን ሚዲያ ላይ አይተነዉም ሆነ ሰምተነዉ አናዉቅም። ያልተነገረውን ሃቅ በራስ ሃይሉ ቤት አገኘነው ።ስለ ሜቴክ ሲወራም ተመሳሳይ ነገር አለው። የመከላከያን ኢንዱስትሪ የጀመሩት ያጠናከሩት አጼ ኃይለስላሴና ኮሎኔል መንግስቱ እንደነበሩ አንዱም ቦታ ሲነገር አይሰማም። የታሪክ ተመራማሪው አየለ ፋንታሁን ልክ እንደራስ ሃይሉ የመከላከያ ኢንዱስትሪን መለስ ዜናዊ ሳይሆኑ በደርግ ዘመን መሰረት የተጣለለት ፕሮጀክት እንደሆነ “Ethiopian Army from victory to collapse 1977-1991” በተሰኘ መጽሐፋቸው ባሰፈሩት ጥናት ያረጋግጣሉ።ከነ መኮድ ወደ ሜቴክባለፉት መንግሥታት ስሙ ይለያይ እንጂ የሃገሪቱን የመከላከያ አቅም እንዲገነቡ ለመከላከያ ፍላጎት በሌሎች ላይ ጥገኛ መሆንን ለማስቀረት ዓላማ ያደረጉ ጥረቶች ሲደረጉ ነበር። ዘመናዊ የመከላከያ ኢንዱስትሪ ግንባታ ታሪክ በ1940ዎቹ መጨረሻ አጼ ኃይለስላሴ በቼኮዝሎቫኪያ መንግስት ትብብር በስማቸው ባቋቋሙት የጥይት ፋብሪካ ይጀምራል። ይህ ጥረት በደርግ ዘመንም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት የቀጠለ ሲሆን ደርግ ሰሜን ኮሪያን ከመሰሉ ሃገራት ጋር በመተባበር አምስት ያህል የመከላከያ ኢንዱስትሪዎችን መገንባት ችሏል። ዛሬ በሜቴክ ኢንዱስትሪ ዝርዝር ዉስጥ ከሚገኙት እንደ ጋፋት የመሳሪያ ፋብሪካ፣ሆርማት የመድፍና ሮኬት ፋብሪካ፣ሆሚቾ የፈንጂና ሮኬት ፋብሪካ ደብረዘይት የአውሮፕላን ፕላንት (አሁን ደጀን አቪዬሽን ተብሏል) መከላከያ ኮንስትራክሽን በተጨማሪ የፈጣን ጦር ጀልባ ፋብሪካ ፕሮጀክቶች ነበሩት። ልክ የህዳሴው ግድብ ሲነሳ የንጉሱ ስም እንደማይነሳው ሁሉ የሜቴክ ጉዳይ ሲነሳ መሰረቱ የ1970ዎቹ የሃገር መከላከያ መሰረቶች እንደሆኑ አንዱም ቦታ አይነገርም።ሜቴክ በደርግ ዘመን በተመሰረቱት የተወሰኑ የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ተቋማትን እንደእርሾ ይዞ በ2002 ዓ/ም በጸደቀው ደንብ 183/2002 እንደአዲስ ተቋም ተፈጠረ። መንግስት ለመነሻ 10 ቢሊዮን ብር የተፈቀደና 3.1 ሚሊዮን የተከፈል ካፒታል መደበለት። በማቋቋሚያ ደንቡ በዋነኛነት ከተጠቅሱት ዓላማዎች መካከል የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ዲዛይን ማድረግ፣ማምረት መትከልና ኮሚሽን በማድረግ ለምርት ማዘጋጀት፤ ኢንዱስትሪያል ማሽኖችን የካፒታል እቃዎችን የኢንዱስትሪ መለዋወጫዎች ዕቃዎችን የጦር መሳሪያዎችን አባሪ ዕቃዎቻቸውን ማምረትና መሸጥ በጥናትና ምርምር በመታገዝ የመከላከያዉን አቅም ማጎልበት የሚሉ ይገኙበታል። ብኢኮ በመካነ ድሩ ዓላማዬ ብሎ ካስቀመጣቸው አንዱ የህዝቡንና የግል ዘርፉን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ የሚችሉ የማምረቻ ፋሲሊቲዎችን መገንባት ይላል።ሃገሪቱ ከነበረችበት ሁኔታ ከምትከተለው ርዕዮተ ዓለም አንጻር የሃገር መከላከያ ተቋማትን በሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ዉስጥ የሚሳተፉበት ሁኔታ፤ የተሳትፎው መጠን ይለያይ እንጂ በብዙ የአለም ሃገራት የተለመደ ነው። ወታደሩን ወደዚህ ሲያስገባ ግን የእያንዳንዱ ሃገር መንግስት የራሱ ምክንያት ይኖረዋል።ሜቴክ የተቋቋመበት ዓላማ እንደኢትዮጵያ ላለ ታዳጊ ሃገርና በልማታዊ መንግስት ጽንሰ ሀሳብ ለተቃኘ ኢኮኖሚ አስፈላጊና ዓላማዉም ግልጽ ቢመስልም የሚተዳደርበት መንገድ ግን ከጥያቄ ነጻ ሆኖ አያዉቅም።ሜቴክና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብጨርቆስ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አጸደ የስልሳ ሶሰት ዓመት ድሃ አሮጊት ናቸው። በመንገድ ጽዳት ሥራ ይተዳደሩ የነበሩ ሲሆን አሁን ጉልበታቸው ደክሞ በጡረታ ከቤት ውለዋል። አሁን የጡረታ የተጣራ ወርሃዊ ገቢያቸው ከአራት ምቶ አምሳ ብር አይበልጥም። ከሰባት ዓመታት በፊት በሥራቸው ላይ እያሉ ከደመወዛችው በየወሩ እየተቆረጠ ለሁለት ዓመታት የሚቆይ የአንድ ሺህ አራት መቶ ብር የቦንድ ግዥ ፈጽመው ነበር። ይህ የገዙት ቦንድ አምስት ዓመቱ በማለፉ ከነ ወለዱ ታሰቦ ሊክፈላቸው ይገባ ነበር። “አምና ይሁን ካቻምና የቦንድ ገንዝብ ይሰጣል ብለው ሰምቼ ነበር፤የትም እንደምሄድ ግራ ገብቶኝ ይዤው ቁጭ ብያለሁ” ሲሉ ቢያንስ ገንዘባቸውን ቢያገኙ ምን ያህል ደስተኛ እንደሚሆኑ ይገልጻሉ።ሌላው የሦስት ሺህ ብር ዋጋ ያለው ቦንድ ባለቤት ም/አ አለቃ ታምራት ነጋሽ (ስሙ ተቀይሯል) ነው። አስር አለቃ ታምራት ከሰሞኑ እየሰማ ያለው የዘረፋ ዜና ራስ ምታት ሁሉ እንዳስያዘው ይናገራል። በመልካም ስራ አፈጻጸሙ እንኳን የተሸለመው ሁለት ባለአምስት መቶ ብር ቦንዶች እጁ ላይ አሉ። ግድቡ በጊዜው አልቆ የአገሩን ትንሳኤ ማየት ነበር ጉጉቱ። ሰሞኑን እንቅልፍ መተኛት እንዳልቻለ ይናገራል።እንደ ወ/ሮ አጸደና አስር አለቃ ታምራት ዓይነቱ ታሪክ ያላቸው ብዙዎች ናቸው። በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ድሆችና ገበሬዎች ላለፉት 7 ዓመታት ወደውም ሳይወዱም፤ ልጆቻቸውን እያስራቡም፤ መቀነታቸውን እየፈቱ የህዳሴ ግድብ ቦንድን ሲገዙ ኖረዋል።የህዳሴ ግድቡ ከተጀመረ አንስቶ በርካታ የሆነ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የገንዘብ ምንጩን ሰፊው ሀዝብ አድርጎት ቆይቷል። በወቅቱ የግድቡን ሥራ ያስጀመሩት ሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ “የግድቡ የገንዘብ ምንጮችም እኛው፤መሃንዲሶችም እኛው።” በማለት ተናግረው ነበር። የራሳችን መሃንዲስ ተብሎ የቀረበው፤ አመራሮቹ ከመከላከያ ሠራዊት የተውጣጡለትና በሽግግሩ ወቅት የወጣውን የመንግስት ልማት ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 25/1984 መሰረት በማድረግ በድንብ ቁጥር 183/2002 የተቋቋመው ብኢኮ የሚባለው ድርጅት ነው።የህዳሴው ግድብ ግንባታ ሲጀመር የግድቡን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች እንዲሰራ ኮንትራት የተሰጠው ለሜቴክ ነበር። ድርጅቱ ያለምንም ልምድ እንዲህ ያለ ትልቅ ዋጋ ያለው ሃገራዊ ፕሮጀክት ለመስራት መወሰኑ ብዙዎችን ባያሳምንም ወደ ስራው በወታደራዊ ድፍረት ገብቶበታል። ስራዉን በተሰጠው ጊዜ ባለመጨረሱ ሳሊኒ የተባለው ኩባንያ የራሱን የስራ ድርሻ በሚቴክ አፈጻጸም ምክንያት መጨረስ እንዳልቻለ አቤቱታ አቅርቦ ነበር። በዚህም ምክንያት ለደርሰበት ኪሳራ ሳሊኒ መንግስትን ከ380 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ካሳ መጠየቁ ተወስቷል። እንደ ዘገባዎች ከሆነ ሜቴክ የህዳሴው ግድብ ላይ ከሚኖረው ጠቅላላ የሥራ ኮንትራት ውስጥ 90% ያህሉን አስቀድሞ ተቀብሏል፤ የስራው መጠን ከ25% ባይበልጥም።ጀብደኝነት በቀላቀለ እቅድ ሲጀመር በአምስት ዓመታት ውስጥ ያልቃል የተባለው የህዳሴው ግድብ ከሰባት ዓመታት በኋላ ዛሬ መቼ እንድሚጠናቀቅ በአግባቡ ሊታወቅ የማይችልበት ደረጃ ላይ ይገኛል። የሌሎቹም ሜቴክ የገባባቸው ፕሮጀክቶች ታሪክም ከህዳሴው ግድብ ፕሮጀከት የተለየ አይደለም።ሜቴክና ያዩ የማዳበሪያ ፋብሪካ11 ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ የተገመተውና ኋላ ግን 23 ቢሊዮን የደረሰው የግንባታው ውል ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተሰጠው ያዩ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ አጠቃላይ የግንባታው አፈጻጸምም 42.3 በመቶ ላይ ሆኖ የውሉ 60 በመቶ ለሥራ ተቋራጩ፣ሜቴክ ተከፍሏል። የፕሮጀክቱ ባለቤት ኬሚካል ኮርፖሬሽን ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ለተበደረው ገንዘብ በየወሩ 70 ሚሊዮን ብር የባንክ ወለድ ይክፍላል። ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ፣ የፋብሪካው ባለቤት የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ለፕሮጀክቱ ከባንክ ለተበደረው ብድር እስከ የካቲት 2008 ዓ.ም. ድረስ ብቻ 1,825,513,172 ብር ወለድ መክፈሉ ዋና ኦዲተር አረጋግጧል። በመጨረሻም የኬሚካል ኮርፖሬሽን ከሜቴክ ጋር ያለው የስራ ዉል እንዲቋረጥ ተደረጓል።ሰባቱ ስኳር ፋብሪካዎችየስኳር ኮርፖሬሽን 77 ቢሊዮን ብር ተበድሮ ሰባት የስኳር ፋብሪካ ባንድ ዓመት ከግማሽ እገነባለሁ ብሎ አቀደ። እቅዱን ለማሳካት የግንባታ ኮንትራቱን ለሜቴክ ሰጥቶ ቢጠብቅም ከሰባት ዓመታት በኋላም አንዱንም ፋብሪካ መረከብ አልቻለም፣ ይሁን እንጂ የግንባታውን 23 በመቶ ብቻ ላጠናቀቀባቸው አንዳንድ ፕሮጀክቶች ሜቴክ የግንባታውን እስከ 90 በመቶ ክፍያ ተቀብሏል። ይህንም የስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ተናግረው ነበር። በመጨረሻም ሁሉንም ሊያሳካቸው ባለመቻሉ ፕሮጀክቶቹን ተነጥቋል። ለክፋቱ ሜቴክ እነዚህን በርካታ የሰኳር ፕሮጀከቶች ተቀብሎ ሲንከባለልባቸው በነበሩ ዓመታት፤ በአገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የስኳር ዕጥረት በማጋጠሙ ምከንያት አገሪቱ በዓመት እስከ 600 ሚሊዮን ዶላር ለስኳር ግዢ ስታወጣ ቆይታለች።መጀመር እንጂ መጨረስ የተሳነው ሜቴክብዙ ትላልቅ ሃገራዊ ፕሮጀክቶችን ኮንትራክት ሲወስድ እንጂ አጠናቅቆ ሲያስረክብ ያልታየው ሜቴክ “የወሰዳችሁት አንዱም ፕሮጀክት አልተጠናቀቀም” ብሎ ህግ አዉጪው አካል ጥያቄ ሲያቀርብ “እየሰራን እንማራለን እየተማርን እንሰራለን“ በሚለው አባባላቸው የሚታወቁት ወታደሮቹ የሜቴክ ስራ አስፈጻሚዎች ከፓርላማ ጥያቄና መልስ አልፈው ዛሬ ወደህግ ተጠያቂነት ተሸጋግረዋል። ኮርፖሬሽኑ የሚቀርብበት ክስና ወቀሳ ብዙ ቢሆንም ዋነኛ የሚባሉትና መንግስትን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳሰቡት የህዳሴ ግድብ፡ የያዩ የማዳበሪያ ፋብሪካና የስኳር ፕሮጀክቶች ናቸው። በነዚህ ፕሮጀክቶች ሃገር በቢሊዮኖች የሚቆጠር ከስራለች። በአጭር ጊዜ የማትወጣው የብድር ማጥ ውስጥ ተዘፍቃለች። ከሜጋ ፕሮጀክቶቹ ዉጪም ያለ በቂ የገበያ ጥናት የሚያመርታቸው የእርሻ ትራክተሮች፣ መሣሪያዎችና የመለዋወጫ ዕቃዎች በቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ የተለያዩ መለዋወጫዎች በጥቅሉ ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ንብረቶች መጋዘን ውስጥ ተከማችተዋል።ሜቴክ ለምን ተቋቋመ? እንዲያመርት ወይስ እንዲሸምት?ሰሞኑን የጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ለሚዲያ በሰጠው መግለጫ መረዳት የሚቻለው የማምረቻ ማሽነሪዎችን በማምረት የሃገርን ኢኮኖሚ ይደግፋል የተባለው ተቋም ትኩረቱ ሁሉ ግዢ ላይ መክረሙን ያመለክታል። በሸመታ የተጠመደው ተቋም ከቻይና አምራቾች ጥራታቸው ጥያቄ ውስጥ የወደቀ እቃዎችን ሲሸምት እንደከረመ ትላንት ዋዜማ ሬዲዮ ይፋ ያደረገችው 5 ሺህ የሚደርሱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተገኙ የግብይት እንቅስቃሴ አመላካቾች (Transactions) ያሳያሉ። ከዚህም በላይ ሰሞኑን የመገናኛ ብዙሃን እንዳሳዩት አሮጌ መርከብና አዉሮፕላን ሁሉ እያሳደደ ሲገዛ እንደከረመ ይታያል። የማምረቻ ማሽኖች በመስራት ሃገሪቷ ከዉጪ የምታስገባቸውን በርካታ ቁሳቁሶች በሃገር ዉስጥ የማምረት አቅም ይፈጥራል ተብሎ ተስፋ የተደረገበት ተቋም የቢሊዮን ዶላሮች ሸማች ሆኖ አረፈው።ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካን አጠናቅቆ እንዲያስረክብ ሲጠበቅ የነበረው ሜቴክ ፕሮጀክቱን በወቅቱ አጠናቆ ለአሰሪው የኬሚካል ኮርፖሬሽን ማስረከብ ሲገባው በፕሮጀክቱ አካባቢ የድንጋይ ከሰል በማምረት መሸጥ ላይ ተሰማርቶ እንደነበር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠይቆ የድንጋይ ከሰሉን አምርቶ መሸጡን ይህን ያደረገው ግን ከጠቅላይ ሚነስትሩ አማካሪ አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) ተማክሬ ነው በማለት ሲገልጽም ነበር።ማን ይጠየቅ?የሜቴክ የበላይ ተቆጣጣሪ አካል የፕራይቬታይዜሽንና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ነው።ይህ ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 412/1996 የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲንና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለስልጣንን በማዋሃድ የተቋቋመ ነው። ይህ ባለስልጣን ደግሞ ተጠሪነቱ ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ነው።በአዋጁ ከተጠቀሱት የባለስልጣኑ ተግባርና ኃላፊነት መካከል የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የውጭ ኦዲተሮች ምደባ ይፀድቃል፤ በውጭ ኦዲተሮች የተመረመሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የሂሳብ ሪፖርት ያፀድቃል፤የሚሉ ይገኙበታል። ባለስልጣኑ እንዲህ ያለ ስልጣንና ሃላፊነት ቢኖርበትም የፌዴራል ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ የሚቴክን ኦዲት በተመለከተ ሚቴክ እንደ አንድ የመንግስት የልማት ድርጅት በአዋጅ መሰረትም ኦዲት መደረግ የነበረበት ቢሆንም ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ኦዲት እንዳልተደረገ በአደባባይ ተናግረዋል። ከ2003 ጀምሮም መ/ቤቱ ሂሳቡን ዘግቶ ማቅረብ ባለመቻሉ በኢንዱስትሪ ሚኒስትር ስር ያሉ ፕሮጀክቶችን የክዋኔ ኦዲት በቀጥታም ባይሆን የመጨረሻው ከሜቴክ ጋር የተገናኘ የኦዲት ሥራ እንደሆነ ተናግረዋል። ለህግ አውጪው አካልም ባቀረቡት ሪፖርት ይህንኑ አካተዋል።በማንኛውም ተቋም ውስጥ ተቋሙን በበላይነት የሚመራው ተቆጣጣሪ ቦርድ ከተለመዱት መሰረታዊ የቦርድ ኃላፊነቶች መካከል የድርጅቱን ሃብት መጠበቅ አንዱ ኃላፊነት ነው። መንግስት የቦርድ አባላትን ሲሰይም እንደእኔ ሆናችሁ ሃብቴን አስተዳድሩ ማለቱ ነው። ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ በይፋ ከገለጻቸው ጥፋቶችና ለዓመታት የኦዲት ሪፖርት ሳይቀርብለት በጀት ሲያጸድቅ ትላልቅ ስትራቴጂክ ሊባሉ የሚችሉ ዉሳኔዎች ሲያሳልፍና ሲያጸድቅ የቆየው የሚቴክ ቦርድ ተጠያቂነትን በተመለከተ አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው የህግ ባለሙያው አቶ አመሃ መኮንን ቦርዱም ሆነ የመንስግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ከተሰጣቸው ሃላፊነት አንጻር ከህግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ አስረግጠው ይናገራሉ። የአዋጅ ቁጥር 412/1996 ሆነ የአዋጅ ቁጥር 25/1996 ይህንኑ የተጠያቂነት ልክ ያረጋግጣሉ።የሚሊዮን ዜጎች ንብረት ናቸው የሚባሉትን ፕሮጀክቶች በዋናነት ይሰራል ስለተባለው ሜቴክ እዚህ ግባ የሚባል የሂሳብም ይሁን የአፈጻጸም ሂደቱን የሚያሳይ ይፋዊ መግለጫ ማግኘት እጅጉን ከባድ ነው። የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የ2006/2007 ኦዲት ዓመት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርት አጠቃላይ ዘገባ ለተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን በኦዲት ከተጠቀሰው የበጀት ዓመት በሁለት ዓመት ወደኋላ እንደሚቀር ገልጾ ነበር። ከዚህም አልፎ ከሁለት ዓመታት በፊት ተደረገ የተባለው ኦዲትም ቢሆን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን በአጠቃላይ የሂሳብ መግለጫው ፈጽሞ ተቀባይነት ባለው መንገድ የተሰራ ባለመሆኑ የኦዲት አስተያየት ለመስጠትም አዳጋች እንደሆነበት ገልጾ ነበር።ከዚያ ወዲህ የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሰለ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ያነሳበት ቦታ የለም። ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ማን ነው ለሚለው ጥያቄ አሁንም ከተለያዩ ባለሙያዎች የተለያዩ መልሶች ይሰጣሉ።አቶ ቢሰጥ በየነ የህግ አማካሪና ጠበቃ ናቸው። “ሜቴክ የተቋቋመው ከመከላከያ ሚንስትር በተለየ መልኩ ልክ እንደ አንድ የልማት ደርጅት ነው፤ እንደማንኛውም የልማት ድርጅት ሂሳቡን ሰርቶ ኦዲት የማስደረግ ግዴታ ነበረበት” ይላሉ። “ማንኛውም ሜቴክን የሚመራ አካል ስልጣኑ የሚመነጨው ከልማት ድርጅቶች አዋጅና ከሜቴክ ማቋቋሚያ ደንብ ነው “ሲሉ ይጨምራሉ። የዚህ ሁሉ ቀውስ መነሻና መድረሻ ግን የሜቴክ አመራር ላይ ብቻ የሚወድቅ አይደለም የሚሉት አቶ ቢሰጥ በየደረጃው ተጠያቂነቱ ሊኖር ይገባል ባይ ናቸው። ሜቴክ በቦርድ የሚተዳደር ድርጅት እንደመሆኑ የቦርዱ አባላት በየጊዜው እየተገናኙ ከፍተኛ የሚባሉ ውጪዎችን ምክንያት፤ ያልተገባ ምዝበራን እንዲሁም ኦዲት ሪፖርት ላይ ካለተወያዩ ምን ላይ ሊወያዩ ነው? “ሲሉም ይጠይቃሉ። በዚህ ሳያበቁ ይህን ያህል ከፍተኛ የሆነ የአገር ሃብት ሲባክንና የፌዴራል ኦዲተር “ሜቴክ ሂሳቡን በአግባቡ እየያዘ አይደለም” የሚል ሪፖርት ሲያወጣ ከፍተኛ የሚባለውም የስልጣን አካል፤የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ ጣልቃ ሊገባ ይገባው ነበር፤ ይህ ባለመሆኑም ይህም አካል ከመጠየቅ አይድንም ሲሉ ይደመድማሉ።ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ በአደባባይ ሲዘረዝራቸው የነበሩ ሃጢያቶች ሁሉ ሲፈጸሙ የሜቴክ ቦርድ ሊቀመንበር ሲራጅ ፈርጌሳ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ደግሞ አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ነበሩ። የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ አመሃ መኮንን የተጠያቂነትን ጉዳይ በተመለከተ ዋና ኦዲተር ለፓርላማው የኦዲት አለመደረጉን በተመለከተ ሪፖርት አድርጎ ከሆነ ተጠያቂነቱ ከሜቴክ ቦርድ ጀምሮ በስልጣን እርከኑ መሰረት እስከህዝብ ተወካዮች እንደሚደርስ ይናገራሉ። እነዚህ አካላት በአዋጅ በተሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት መጠየቅ ያለባቸውን ጥያቄ ጠይቀዋል? ጠይቀው ከሆነስ ምን እርምጃ ወስደዋል? የሚለው መመለስ ያለበትና እነዚህን አካላትም ለተጠያቂነት የሚዳርግ እንደሆነ ይናገራሉ።መንግስት በአደባባይ እንደመሰከረው የህዝብ ሃብት በግለሰቦች ዉሳኔ ያለተጠያቂነት እንዲባክን ተደርጓል። ይሄን ያመጣው ምንድነው ለሚለው ጥያቄ የህግ ባለሙያው አቶ አማሃ “ደርግን አሸንፎ ስልጣን የተቆጣጠረው ቡድን የቡድን ፍላጎቱን ለማሟላት የመንግስትን አደረጃጀት በመጠቀም የፈጠረው ነው ይላሉ። ይሄ የዝርፊያ ሁኔታ የተጋለጠው ግለሰቦች ስላጋለጡት ሳይሆን ይሄ የራሱን ጥቅም ለማስከበር የመንግስትን ስርዐት ይጠቀም የነበረ ስርዓት ስለወደቀና በሌላ ኃይል ስለተበለጠ ነው በማለት ያክሉበታል።ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድና ሜቴክጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ ሜቴክን በአዲስ መልክ ለማዋቀር ታስቦ የህግ ደንብ እየተዘጋጀ እንደሆነ ተሰምቷል።ሜቴክ በስሩ በተለያዩ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ 14 ኢንዱስትሪዎችና 93 ፋብሪካዎችን ያቀፈ ነው። በዚህ መሰረት ወታደራዊ እቃዎችን ከሚያመርቱትን የንግድና የሲቪል ነክ ምርቶችን ከሚያመርቱት ካምፓኒዎች ተለይተው በመከላክያ ስር እንዲጠቃለሉ ታስቧል።እነዚህ በመከላከያ ስር እንዲሆኑ የተፈለጉት ድርጅቶች ሆሚቾ ጥይት ማምረቻ፣ ደጀን አቪዬሽን ፣ጋፋት አርማሜንት ኢንጂነሪንግና ሃይ ቴክ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ናቸው።ከአደረጃጀት ለውጡ በተጨማሪ ሜቴክ በስሩ የሚገኙ ፕሮጀክት አፈጻጸም የሚወቀስባቸው ፕሮጀክቶችን እንዲያስረክብ ታዟል።የስኳር ፕሮጀክቶችን ለስኳር ኮርፖሬሽን የማዳበሪያ ፋብሪካን ለኬሚካልና ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን ሌሎቹንም ለፕሮጀክቱ ባለቤቶች እንዲያስረክብ ታዟል።ለመከላከያ ሚኒስትርም ሆነ ለሜቴክ አዲስ ስራ አስፈጻሚና ቦርድ ተሹሞለታል።ሜጀር ጀኔራሉከሁለት ዓመታት በፊት በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ምላሽ የሰጡት የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣ ኮርፖሬሽኑ ላይ ለሚመጣ ተጠያቂነት እርሳቸው ብቻ ተጠያቂ መሆን እንደሚፈልጉ እንዲህ ብለው ነበር “በግሌ የማምነው ለዚህ አገር ልማት እየወደቅንና እየተሰዋን እንደምንሠራ ነው። መጠየቅ ካለብኝ እኔ ልጠየቅ። ከእኔ ውጪ ማንም እንዲጠየቅ አልፈልግም። እኔ የሚፀፅተኝ ነገር የለም። መታወቅ የተፈለገው ይህ ከሆነ ለዚህ ዝግጁ ነኝ፤” ብለዋል። ይህን ይበሉ እንጂ ጄኔራሉ መቀመጫቸውን መቀሌ ላይ በማድረግ ባገኙት የሚዲያ አጋጣሚ ሁሉ ያሳለፏቸውን ዉሳኔዎች ከረር ባሉ ቃላት ሲከላከሉ ቆይተዋል። እኔ ልጠየቅበት ያሉትን ተቋም ቀርቶ ሃገሪቷንም ጥለው ሊወጡ ሲሉ መንግስት ድንበር ላይ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ገልጿል። የመሩት ተቋም እሳቸው በሚሉት መጠን ትክክለኛና ህጋዊ ስራ ካከናወነ እሳቸውን ሃገር ጥሎ የሚያስፈረጥጥ ምን ተገኘ በማለት ብዙዎች ይጠይቃሉ።ልማታዊነትልማታዊ መንግስት የሚያቀነቅኑ ሰዎች ድሃ ሀገራት ለማኀበረሰቡ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማቅረብ የመንግሥትን በልማት ሥራዎች መሳተፍ ይደግፋሉ። ምክንያቱም የግሉ ዘርፍ የራሱ ምርጫዎች ስለሚኖሩት ለመሰረተ ልማት ግንባታዎች እንደልብ የሚታዘዝ እና የሚተጋ አይሆንም። ይህንን መሠረታዊ ችግር ለመፍታት እንደመፍትሔ የተወሰደው የግሉ ሴክተር ለማልማት በሚያመነታባቸው ዘርፎች ውስጥ የሚሳተፉ ግዙፍ ኩባንያዎችን ልማታዊ መንግሥት ያቋቁማል። መሠረተ ልማቱን እነዚህ ድርጅቶች ሲገነቡ የግሉ ዘርፍ የተፈጠረውን የገበያ ዕድል በማየት ለመሳተፍ ፍላጎት ይኖረዋል።የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ብስራት ተሾመ ይህንን የፖሊሲ አቅጣጫ መንግሥት መከተሉ በራሱ ችግር የለውም ብሎ ይከራከራል። “ከልማታዊ መንግሥት አኳያ ካየነው አንድ አገር ልማቱን በተለይ የመሠረተ ልማት ግንባታዉን አንደኛ እና ዋና አቅጣጫ ለማድረግ ግዙፍ መንግሥታዊ ድርጅት ያስፈልገዋል። ሜቴክ የቴክኒክ አቅሞችን (technical ability) ከውጭ በማስመጣት አሟልቶ የተሰጡትን ፕሮጀክቶች በአግባቡ ቢያጠናቅቅ ኖሮ ዕድሉ ወርቃማ ነበር። የቁጥጥር አቅማችን የወረደ መሆን፣ የቁርጠኝነት መጥፋት እና የተጠናወተን የዘራፊነት ችግር፣ የሰዎቹ ሌብነት ይህንን ዕድል አባክኖታል።” ሲል ይናገራል።አዲስ ዘይቤ ያናገረችው ሌላው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው መንግሥቱ በስር ልማታዊ መንግሥትን በተመለከተ የተለየ ሀሳብ አለው። እንደመንግሥቱ አንድ መንግሥት ለማኀበረሰቡ መልካም የሚሰራ፣ ልማታዊ ለመባል በህዝብ ዘንድ ቅቡልነት ሊኖረው ይገባል። ቅቡልነት ከሌለ ግን ህዝብን ለዝርፊያ የሚያጋልጥ ነው። “ኢትዮጵያ ውስጥ ማን ነው ለመንግሥት ውክልናውን የሰጠው? ህዝቡ መንግሥትን ተቀብሎታል ወይ? ያምነዋል ወይ? መንግሥትስ የምር የህዝቡን ጥያቄ መመለስ ይችላል ወይ? ይህ በሌለበት ሁኔታ መንግሥትን አምኜ ልማታዊ ሁን ልለው አልችልም።” በማለት ይከራከራል።ሌላው የመንግሥቱ በሲር ስጋት የመንግሥት እና ወታደር መተባበር ነው። መንግሥት በራሱ ስኬታማ የሆነባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ሁሉ ጥሩ ያልሆነባቸው ጉዳዮችም አሉ። መንግሥት እና መከላከያ አንድ ላይ ሲሆኑ ግን በብዙ ሀገሮች ስኬታማ አይደሉም። የዝርፊያ መሣሪያ ነው የሚሆነው፤ የተወሰኑ ልሂቃንን ማበልጸጊያ ነው የሚሆነው። የሁለቱ ጥምረት ውጤቱ ብዙውን እንደሜቴክ አደገኛ ነው የሚሆነው በማለት ይከራከራል።ብስራት ከፖሊሲ ክርክሩ በዘለለ የሜቴክ ውድቀት የሚጀምረው ንድፈሐሳቡ ከፖለቲካ ልሂቃን ወደ የቴክኒክ ሰዎች ሲሄድ እንደሆነ ይናገራል። “የሀሳቡ አመንጪዎች አስበው ሰርተው ባስቀመጡት ልክ ላይሆን ይችላል የሜቴክ ኃላፊዎች የተረዱት። እንደሜቴክ አይነት ድርጅት ለሀገር እድገት ያለውን ድርሻ ያልተረዱ ዘራፊዎች ስልጣን ላይ ሲቀመጡ ይመስለኛል ስህተቱን የሚጀመረው።” በማለት የግል አስተያየቱን ያስቀምጣል።ሟቹ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የልማታዊ መንግሥት አስፈላጊነት ተከራካሪ ነበሩ። መለስ በበርካታ መድረኮች ኒዎሊበራሊዝምን ነቅፈው ልማታዊ መንግሥትን ደግፈው ቢከራከሩም እ.ኤ.አ. 2007 በአሜሪካን ሀገር በኮሎምቢያ የኒቨርሲቲ እንዳቀረቡት ‘African Development: Dead Ends & New Beginnings’ የሚል ርዕስ ያለው ባለ51 ገጽ ጅምር መጽሐፍ ተጠቃሽ ጽሑፍ የላቸውም። በዚህ ክታብ አቶ መለስ ልማት የኢኮኖሚያዊ እና ማኀበራዊ ሂደት ከመሆኑ በፊት ፖለቲካዊ ሂደት መሆኑን ያሰምሩበታል። ስለዚህ የመንግሥት ድርሻ ይህንን ፖለቲካዊ ሂደቱን እንዲወጣ ማስቻል ነው።እንደ አቶ መለስ ኒዎሊበራሎች መንግሥት በንቃት እና በግዝፈት በልማት ስራዎች መሳተፍ የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋን ያስከትላል የሚለው ስጋት የመንግሥትን የተለያዩ አይነት ያላቸው ሱታፌዎች የለየ አይደለም። The neo-liberal paradigm states that socially wasteful rent-seeking is the result of government activity and of the size of government activism. It does not distinguish between different types of state activism.(Page 09) መንግስት ንቁ ሆኖ መሳተፉ ኪራይ ሰብሳቢነትን በማስወገድ ሁሉም አይነት ልማቶች ያለ ምንም ሳንካ እንዲከናወኑ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ያስችለዋል ባይ ናቸው፤ አቶ መለስ። በኢትዮጵያ በሜቴክ አማካኝነት የሆነው ግን አቶ መለስ ኒዎሊበራሎች ያሏቸው ኃይሎች እንዳስቀመጡት ያለ በመንግሥት እጅግ የበዛ ተሳትፎ የተፈጠረ መረን የለሽ ኪራይ ሰብሳቢነት ነው።ሌብነትና ዘረፋ እንዳይደገም?መንግሥቱ በልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ አዋጭነት ላይ እምነት ባይኖረውም የደረሰውን ኪሳራ መቀነስ ይቻል እንደነበር ያምናል። እንደመንግሥቱ የባለሙያ አስተያየት ሜቴክ መውደቅ የጀመረው የአስተዳዳር መዋቅር፣ የቢዝነስ ዕቅድ እና ቅርጽ ሳይኖረው ወደተግባር በመግባቱ ነው። አስተዳደራዊ መዋቅር፣ ቅርጽ እና ዕቅድ ተሰርቶለት እንደሌሎች የመንግስት የልማት ድርጅቶች በቢዝነስ መርሕ ቢመራ ኖሮ ምንአልባት የተለየ ውጤት ሊኖረው ይችል እንደነበር ይገምታል። የአቶ መለስ ዜናዊ ሞትም የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች እንደአለቃ የሚያከብሩት ሰው መጥፋትም ለብክነቱ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይገምታል።አቶ አመሃ እንዲህ ያለ በህዝብ ላይ የደረሰ ከፍተኛ ጉዳት ዳግም እንዳይፈጸም ዋስትናው የዜጎች ነጻነት ብቻ ነው ይላሉ። ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጽ መብት ሲኖራቸው የመንግስትን አሰራር ይተቻሉ ይጠይቃሉ። ሲቪል ማህበራት የተለያዩ የህዝቡን ጥቅሞች ይዘው በነጻነት መደራጀት ሲችሉ ጋዜጠኞች ነጻ ሆነው የምርመራ ጋዜጠኝነትን መስራት ሲችሉና ጠንካራ የፍትህ አስከባሪና የፍትህ ስርዐት መፍጠር ሲቻል ብቻ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በአሃዝ ካስቀመጠው በላይ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ብዙ እንደከሰረች ብዙዎችን ያስማማል። መንግሥቱ በስር ይህንን ለማስላት ብሩ ወዴት ነው የሚሄደው ሲል ይጠይቃል። ብሩ ተመዝብሮ ግለሰቦች እጅ በመግባቱ የተነሳ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ከሀገር ይወጣል። ይህ ከሀገር የሚወጣ ገንዘብ (Capital flight) ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ያስከትላል ሲል ያስረዳል። ሁለተኛው ሜቴክ በተሰማራባቸው ዘርፎች ሊሰማሩ ይችሉ የነበሩ የንግድ ሥራዎችን በማጨናነቅ ከገበያ አስወጥቷል።መንግሥቱም ብስራትም የግሉን ዘርፍ በማቀጨጭ ተወዳዳሪነቱን በመግደል ከፍተኛ አሉታዊ ሚናን እንደተጫወተ የሚናገሩት ባለሙያዎቹ በመርካቶ እና በሌሎች ስፍራዎች የሚንቀሳቀሱ ትንንሽ የንግድ ሥራዎችን ሳይቀር ጉዳቱ እንደተሰማቸው ያሰምሩበታል። ሀገሪቷ የዘውግ ፖለቲካዊ መዋቅር መከተሏ ለሜቴክ ውድቀት አስተዋጽኦ ማስርከቱን የሚናገረው መንግሥቱ በስር ይህም በዘውግ የተደራጁ ሊሂቃን በኮርፖሬሽኑ አከባቢ እንዲሰባሰቡ እንዳደረገ ይገልጻል። በአጋርነት አብረው የሚሰሩ ድርጅቶች ጋር የሚሰሩ ድርጅቶች ከብቃት ይልቅ የአንድ አከባቢ ልጅነት መሰባሰባቸው ለውድቀቱ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይገልጻል። መንግሥቱ ይህ በዘውግ እና በወንዝ ልጅነት የሚደረግ ቁርኝነት በሜቴክ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የሀገሪቱ መስተጋብሮች ላይ እንደሚታይ ይገልጻል። “በአጠቃላይ የዘውግ ፌዴራሊዝም ላይ ያለኝ አስተያየት ዜጎች የሚያደርጉት የንግድ ግንኙነት ከምርት እና አገልግሎት ጥራት፣ ቅልጥፍና እና ሌሎች የተወዳዳሪነት መለኪያዎች ይልቅ በሰፈር ልጅነት እንዲሆኑ ማድረጉ ትልቅ ውድቀት ነው። ለሜቴክም ውድቀት አስተዋጽኦ ካደረጉ ጉዳዮች አንዱ ይሄ ነው።”ብስራት ተሾመ በበኩሉ የድርጅቱ ኃላፊዎች ከአንድ ዘውግ ሊመጡ እንደሚችሉ ቢገምትም በሙስና የሚታባበራቸው ካገኙ በተበላሸ አሰራራቸው ካገኙት እንደሚቀጥሉ ይናገራል። ብቃትን መሠረት ያላደረገ በመሆኑ በደምብ አስማማለሁ። የዘውግ አደረጃጀቱ ምን ያህል እንዳጠላበት ለማወቅ ሜቴክ ኮንትራቱን ለነማን ነው የሰጠው የሚለውን መገምገም እንደሚገባ ይገልጻል።ሦስተኛው የሜቴክ ፕሮጀክቶች ብዙ የውጭ ምንዛሬ ወጥቶባቸው ከፍተኛ ወለድ እየተከፈለባቸው ነገር ግን አልቀው ወደገበያ ባለመግባታቸው ሀገሪቱ ልታገኝ ትችል የነበረው ጥቅም (Opportunity cost) ሌላው ኪሳራዋ ነው። ሌላው ጉዳት ለሜቴክ ፕሮጀክቶች ሀገሪቱ የተበደረችው ገንዘብ ከፍተኛ የዕዳ ጫና ሆኖ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ ማዳከሙ ሌላው ከፍተኛ ጉዳት ነው።የሜቴክ የወደፊት እጣ ፈንታ ምን ይሁን የሚለው ላይ መንግሥቱ በዶ/ር ዐቢይ በተጀመረው የሜቴክ ሥራዎችን ለሁለት መከፈል ይስማማል። ከሀገሪቱ ደኅንነት እና ራስን መከላከል ጋር ቁርኝት ያላቸው እንደጥይት ፋብሪካ እና ወታደራዊ ማሽነሪዎችን ማምረት የመሳሰሉት ጉዳዮች ራሱ ሜቴክ እንዲሰራቸው እንዲደረግ ቦርዱን ላይ ብቻ የፖለቲካ ሹማምንትን በማሳተፍ አስተዳደሩ ግን የንግድ ሥራ ዕቅድ እና መዋቅር ወጥቶሎት በንግድ ሕግ እና በባለሙያ እንዲመራ ማድረግ እንደሚገባ ይገልጻል።ሌሎቹን ደግሞ መንግሥት ውስጣዊ አሰራርን በማስተካከል፣ ተጠያቂነት ያለው በእውቀት እና ልምድ የሚመረጥ ባለሙያ በመሾም ማስተካከል ተገቢ ነው። እነዚህን ሥራዎች መንግሥት እንደልማታዊ መንግሥትነቴ ራሴ ሰራቸዋለው ቢል እንኳን ዕድሜ ልክ እየሰራ ለመኖር ማሰብ እንደሌለበት መንግሥቱ ይመክራል። መንግሥት መከተል ያለበት ገንብቶ እንዴት እንደሚሰራ አሳይቶ ለግሉ ዘርፍ አስተላለፎ የመውጣት Build–Operate–Transfer ሞዴልን መከተል ይገባዋል ባይ ነው።ብስራት ተሾመ ስለኮርፖሬሽኑ የወደፊት እጣ ፈንታ ሲናገር ሜቴክ ላይ የፈሰሰው የሀገር ሀብት ያሳስበዋል። ስለዚህ ሜቴክን ከማፍረስ ይልቅ አሁን በእጁ ያለውን ሀብት ወደ ጠቃሚ ምርትነት የሚቀይርበት ሁኔታዎች ቢመቻቹ እና በሜቴክ አቅም መሠራት የሚችሉ ሥራዎችን እየሰራ ቢቆይ የተሻለ ነው በማለት ያስረዳል።ብስራት ወደፊት ተመሳሳይ የሆነ ኪሳራ በሜቴክም ሆነ ሌሎች የሀገሪቱ ድርጅቶች ላይ እንዳይከሰት ሕገ መንግሥቱ በአግባቡ እንዲከበር፣ የፍትህ አካላት በገለልተኝነት እንዲሰሩ ማድረግ፣ የነጻ ሚዲያ እና ሲቪክ ማኅበራት መኖር ላይ ተስፋ አድርጓል። “የፖለቲካ ምህዳሩ ካልሰፋ፣ የሕግ የበላይነት ካልተከበረ፣ ሚዲያው እና ሲቪክ ማኀበራት በነጻነት መስራት እስካልጀመሩ ድረስ እንደዚህ አይነት ኪሳራ ላይ በድጋሚ የማንወድቅበት ምንም ምክንያት የለም” ሲል ስጋቱን ያስቀምጣል።የዘውግ ነገር መኖሩ መቼም ቢሆን ሌላ መንግሥት ቢመጣም ነገሮችን ከባድ እንደሚያደርግ የሚናገረው መንግሥቱ በስር ጉዳቱን ለመቀነስ ጠንካራ የሆነ ውስጣዊ የቢዝነስ አስተዳደር መዘርጋት፣ የሂሳብ እና ኦዲት አሰራርን ማዘመን፣ ተጠያቂነትን መፍጠር የአጭር ጊዜ፣ የሽግግር ወቅት መፍትሔ አድርጎ ያስቀምጣል። ፖለቲካዊ መፍትሔ እስኪኖረው ድረስ ቢዝነስ አስተዳደሩን በባለሙያ በመምራት የፖለቲካ ሹማምንትን ግን በቦርድ ብቻ እንዲወሰኑ ማድረግ ጉዳቱን ለመቀነስ እንደሚያስችል ይናገራል።ዘላቂና አሰሪ የሚባል መፍትሄና አሰራር ካልተዘረጋ በቀር ዛሬም ነገም የዘርፉትን ማሳደድ ለደሃዋ እናት ወ/ሮ አጸደም ይሁን ለጭቁኑ ወታደር አስር አለቃ ታምራት የራስ ምታት መድሃኒትነቱ አጠያያቂ ነው።

አስተያየት