ኅዳር 10 ፣ 2011

Brain-Washing (ህጽበተ-ኃልዮ)

ወቅታዊ ጉዳዮች

የመልክዓ ምድር ንድፍ ባለሙያው(Landscape Designer) ሚካኤል መላከ በጥቅምት 6፣ 2011 ዓ.ም. ቦሌ አካባቢ በሚገኝ አንድ ፕሮጀክቱ ሥራውን…

Brain-Washing (ህጽበተ-ኃልዮ)
የመልክዓ ምድር ንድፍ ባለሙያው(Landscape Designer) ሚካኤል መላከ በጥቅምት 6፣ 2011 ዓ.ም. ቦሌ አካባቢ በሚገኝ አንድ ፕሮጀክቱ ሥራውን ለማከናወን እየተጣደፈ ነበር፡፡ ሦስት የአዘቦት ልብሳቸውን የለበሱ ፖሊሶች ለጥያቄ አንደሚፈልጉት ይነግሩታል፡፡ ሚካኤል ትውልዱም፣ እድገቱም፣ ትምህርቱም፣ ሙያውም ከከተሞች ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የመብራቶች መጠገን፣ የሚሰሩት ግንባታዎች፣ የቆሻሻ አወጋገድ፣ ለነዋሪው ምቹነታቸው፣ ታሪካቸው እና ማኀበራዊ ሀብታቸው ትከረቱን የሚስቡ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ስለ ከተሞች ገፅታ እና አስተዳደር ተናግሮ አይጠግብም፡፡ ይህ መውደዱ በወንጀል አስጠርጥሮ ፖሊስ ዘንድ እንደሚያቀርበው አልገመተም ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ሲደርስ ግን የተረዳው ይህንን ነበር፡፡ሚካኤል ከህግ ባለሙያው ሔኖክ አክሊሉ እና ከሌሎች ወጣቶች ጋር የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የዜግነት መብቱን እንዲያውቅ ግንዛቤ ለመፍጠር እና ይህ መብቱ ደግሞ በመንግሥት ውሳኔዎች አትኩሮት እንዲያገኝ እንዴት እነሱን መሰል ዜጎች ማንቀሳቀስ እንደሚቻል የሚመክር ኢ-መደበኛ ውይይት ማካሄዳቸውን ያስታውሳል፡፡ ሔኖክ እንደሕግ ባለሙያነቱ አዲሱን የከተማዋን ምክትል ከንቲባ ለመሾም ሲባል የተፈጸመውን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ አካሄድ ያሳስበዋል፡፡ የሁለቱም ትኩረት አንድ አይነት ባይባል ተቀራራቢ በመሆኑ ይህንን ጉዳይ ሕጋዊ በሆነ መልኩ ለማንቀሳቀስ በማሰብ ነበር የሻይ ቡና ውይይት የተጀመረው፡፡ ይህ ግን አራት ቀናት በወህኒ እንዲሳልፉ አስገድዷቸዋል፡፡የሚካኤል እና የሔኖክ እስር እንዲሁም ወደጦላይ እና ሰንዳፋ የተጋዙት ወጣቶች ታሪክ ስለአሁኑ የኢትዮጵያ መንግሥት የህዝብ ግንኙነት ፖሊሲ ምስል የሚከስት ነው፡፡ የመንግስትን የህዝብ ግንኙነት ስራዎች የሚከታተሉ ባለሙያዎች በመንግስት ሚዲያዎች እና ከመንግስት ጋር ይፋዊ ያልሆነ ግንኙነት ባላቸው ሚዲያዎች የሚከተለው ሥልት ዜጎች በምክንያታዊነት በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ ከመጥራት ይልቅ ከነባራዊው ኹኔታ የተለየ ምስል በመፍጠር ጭፍን ድጋፍ ማሰባሰብ ነው ብለው ይከራከራሉ። የመንግሥትን የሕዝብ ግንኙነት ስራ አምልጦ እና በሚፈጠሩ ችግሮች ተደናግጦ ምክንያታዊ ነው የሚለውን አቋም ሲይዝ የሚወሰዱ የዜግነት ክብርን የሚገፍ እርምጃ ከመውሰድ እንደማይመለስም ያሰምሩበታል። ለዚህም በመዲናዋ የታየውን የዘፈቀደ እና ጅምላ እስር እንደአስረጅ ያቀርባሉ፡፡ ከፍተኛ በጀት የተመደበለት፣ ከሌሎች መንግሥታዊ ሥራዎች የማይተናነስ አንዳንዴም በሚበልጥ መልኩ የተደራጀ ኮሚኒስታዊ ስርዓቶች ያለ ማኀበረሰቡን በጅምላ እንደሚያጠምቁት ያለ የሚዲያ ሥራ በዋነኛነት የሚከወን ነው፡፡ ይህንን ጥምቀት በመቃወም መንግሥት የሰራውን የሕዝብ ግንኙት ስራ በሚያፈርስ መልኩ የተንቀሳቀሰውን ደግሞ ከተቻለ በቡድን እና በግለሰብ ደረጃ ኅጽበተ-ኃልዮ(brainwashing)፤ አልያም መታሰር እና እንግልት ፈርቶ ቤቱ እንዲቀመጥ የሚደርግ የሚዲያ ስትራቴጂ ነው፡፡አሜሪካዊው  ኤድዋርድ ሀንት ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ከዘገቡ ስመጥር ጋዜጠኞች አንዱ ነው። ሀንት በፋስሽታዊው የጣሊያን መንግስት እና በኢትዮጰያ መካከል የተካሄደውን ውጊያም ዘግቧል።  ስሙ ይበልጥ ተያይዞ የሚነሳው በጦርነት ወቅት ባለጋራዎች ከሚጠቀሟቸው ስነ-ልቦናዊ የጦር መሣሪያዎች ጋር ነው። በ1950ዎቹ የቻይና ኮሚኒስታዊ መንግሥት ድጋፍ ሰሜን ኮርያ፣ የደቡብ ኮርያ ግዛት ላይ ወረራ አካሂዳ ነበር። ይህንን ለመቀልበስ በተባበሩት መንግሥታት አስተባባሪነት ኢትዮጵያን እና አሜሪካንን ያካተተ ሕብረ-ብሔራዊ ጦር ተሰማርቶ እንደነበር ይታወሳል። በውጊያው በሰሜን ኮርያ የተማረኩ የአሜሪካን ወታደሮች አስተሳሰባቸውቸው እየተቀየረ የኮሚኒስታዊው ሥርዓት አወዳሽ አሜሪካን እና ካፒታሊዝምን ወቃሽ ሆነው ብቅ ማለት ጀመሩ። የሚገርመው እዚህ ምርኮኞች ከእስር ተለቀው ከኮሚኒስታዊው ስርዓት አስተዳደር ክልል ውጪ ሆነውም በዚህ አስተሳሰባቸው አክራሪ አቀንቃኝ ሆነው መቀጠላቸው ነው። ይህ በአጭር ጊዜ የሚደረግ ውልጠት እንግዳ ነበር። ኤድዋርድ ሐንት በወቅቱ ይህንን ስነ ልቦናዊ ጫና የሚፈጥር ሂደት የሚያጋልጡ ዘገባዎችን ሲያደርስ ነበር። በዚህም ምክንያት የአሜሪካን ሸንጎ ዘንድ ቀርቦ ምስክርነቱን እስከመስጠትም ደርሷል። ይህንን ድርጊት Brain-Washing በተሰኘ አዲስ የእንግሊዘኛ ጥምር ቃል ይጠራዋል።ኅጽበተ-ኃልዮ (Brainwashing) የተለያዩ ስነ ልቦናዊ ስልቶችን በመጠቀም የሰውን ልጅ አእምሮ መቆጣጠር እና መቀየር ይቻላል ከሚል ንደፈ ሀሳብ የሚነሳ ነው። እነዚህን ስልቶች በመጠቀም የሰው ልጅን ስሜት እና አስተሳሰብ ያለ ሰውየው ፍቃድ ለሚፈልጉት ዓላማ መግራት፣ ማጣመም ይቻላል ከሚል መነሻ ይጀምራል።  አንድን ሰው የሚበጀውን የተሻለ ነገር ስነ ልቦናዊ ጫና በመፍጠር ማስተካከል ምን ነውር አለው የሚል ጥያቄን ያስነሳል።ይህ የሞራል ጥያቄ ዕድሜው እንደሰው ልጅ የአብርኆት ታሪክ የረዘመ ነው። ሐንት  ሐሳቡን ከቻይናው szu-hsiang-kai-tsao ጋር ቢያገናኘውም፤ ከእርሱ ሁለት ክፍለ ዘመን የቀደሙ ጸሐፊያን ይህ አእምሮን ማጥብ እና ልብን ማደስ ጋር የተያያዘውን አስፍረውት ነበር። የምእራቡን ዓለም የሞራል መደላድል ከሰሩት ልሂቃን አንዱ የሆነው ቶማስ ሙር ዮቱፒያ ላይ እንዳሰፈረው የሰው ልጅ የመለኮት ጥበቃ እና የነፍስ ኢ-መዋቲነት ስለሚከተለው  እውነትን ከመንገር በቀር ምንም አይነት ጫና ሊደረግበት አይገባም ብሎ ይከራከራል። ሰው ለራሱ ጥቅም እንኳን በምክንያት ህሊናን ለመግዛት ከመሞከር በቀር መንግስትም ሆነ ሌላ አካል አካላዊው ሆነ ስነ ልቦናዊ ጫና ሊፈጥርበት አይገባም። ይህ ትርጓሜው ብዙዎች የሚስማሙበት ነው። ለአብነት የኦክስፎርድ እንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት ኅጽበተ-ኃልዮ ላይ የሰጠው የትርጉም ብይንና የአማርኛ ትርጉም እንመልከት።“The systematic and often forcible elimination from a person’s mind of more established ideas, especially political ones, so that another set of ideas may take their place; this process regarded as the kind of coercive conversion practiced by certain totalitarian states on political dissidents.”“ስልታዊ እና አብዛኛውን ጊዜ በኃይል በሚደረግ፤ በአንድ ሰው አእምሮ ውስጥ ያለ የረጋ ሐሳብን በተለይ ፖለቲካዊ የሆነውን ጠርጎ በማውጣት፣  ምንአልባት ሌላ ሐሳብን በቦታው  ማስገባት ነው። ይህ ሂደት አምባገነን መንግሥታት የፖለቲካ ተቃዋሚዎቻቸውን አስተሳሰብ በጉልበት ለመቀየር እንደሚደረግ ሂደት ይፈረጃል።”ከዚህ በተጨማሪ የሰውን አእምሮ የሚጠመዝዙ እኩያን ኅጽበተ-ኃልዮው እንዲሰምርላቸው የተለያዩ የማሰቃየት ተግባራትን(torture) እንደመሳሪያ ስለሚጠቀሙ ኅጽበተ-ኃልዮ በራሱ ከማሰቃየት ተግባራት እንደ አንዱ ይቆጠራል በማለት የሚከራከሩም አሉ።ከኅጽበተ-ኃልዮ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የማሰቃየት ተግባር አይነቶች አንዱ እንቅልፍ መንፈግ ነው። በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራን እንቅልፍ ማጣት ሰውን የሀሰት ትውስታ እንዲኖረውን እና በነባራዊው ዓለም ከሚያስተውለው ዉጪ የሆነ ምናባዊ ነገር በአእምሮው እንዲቀረጽ የሚያደርግ ነው። ለመኖር ምቹ ባልሆነ ቦታ፣ መሠረታዊ ፍላጎቶች ባልተሟሉበት ሁኔታ የሚደረግ ማጎሳቆል ከማሰቃየት ተግባሩ እና የኅጽበተ-ኃልዮ ጋር መሳ ለመሳ የሚሄድ ነው።ምንአልባት ይህ ጉዳይ ከአንድ አመት በፊት ተከስቶ ቢሆን ኖሮ ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው መወትወት እና ስለ ኀሊና አጠባ(brainwashing) ምንነት ማወቅ ባላስፈለገ ነበር።  ምክንያቱም በዜጎች ላይ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጫናን በማሳደር በሚደረግ ጥምዘዛ የኢትዮጵያ መንግስት ጥሩ ስም አልነበረውም። ከሀገር ወስጥ እስከ ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይህንን የመብት ጥሰቶች እና አረመኔያዊ ተግባራት የሚዘረዝሩ ሪፖርቶች ሲያወጡ ኖረዋል።በተለይ ከዚህ የማሰቃየት ተግባር ጋር ስሙ ተያይዞ የሚጠራው የፌደራል ወንጀል መከላከል እና ምርመራ ዘርፍ በተለምዶ ማዕከላዊ ተብሎ የሚጠራው ነው። በማዕከላዊ እና በሌሎች በግልጽ በሚታወቁ እና በማይታወቁ ስፍራዎች ዜጎች አካላዊ እና ስነ ልቦና የማሰቃየት ተግባር ሲፈጸምባቸው መኖሩ አሌ አይባልም። መንግሥት ለበርካታ ጊዜያት ይህንን በዜጎች ላይ የሚደርስ የመብት ጥሰት ሲያስተባብል ሰንብቷል።ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስተር ወደ ሥልጣን መምጣት ጋር ተያይዞ፣ መንግሥት እንደበፊቱ መካዱን በመተው ዜጎቹን ማሰቃየቱ አምኗል። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም መንግሥታቸውን ወክለው ይቅርታ ጠይቀዋል።ይህንን ንግግራቸው ከተሜው አጣጥሞ ሳይጨርስ ነው አዲስ አበባ በወጣቶቹ ጅምላ እስር መታወክ የጀመረችው። ጠቅላይ ሚኒስተሩ “በእኔ የሥልጣን ዘመን የሚታሰር፣ የሚሳደድ አንድም ሰው አይኖርም፡፡” ብለው በአደባባይ ቢለፍፉም እስራቱ አልቀረም። በፊት በነበረው አስተዳደር የሚደረጉ የመሸፋፈኛ ስልቶች እንኳን ተግባራዊ ሳይደረጉ ዜጎች ታፍሰዋል። እንደቀድሞው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንኳን ሳይታወጅ ዜጎች ሕገ መንግስታዊ መብታቸው ተጥሶ በዘፈቀደ ታስረዋል።በመዲናችን አዲስ አበባ በፖሊስ መታፍስን ተከትሎ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት፣ የአሁኑ የሰላም ሚኒስተር ዴዕታ አቶ ዘይኑ ጀማል ለፋና ቴሌቪዥን በስልክ በሰጡት ቃለመጠይቅ ለስለስ አድርገው በእስር ላይ ያሉት ወጣቶች የኅጽበተ-ኃልዮ (Brainwashing)  ስራዎች ከተሰሩባቸው በኋላ እንደሚለቀቁ ተናገረዋል። ኮሚሽነሩ እንዲህ እንደዋዛ ይናገሩት እንጂ ጉዳዩስ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም።በወንጀል የተጠረጠረ ሰው ሊያልፍባቸው የሚገቡ የሕግ ስነ ሥርዓቶች አንዳቸውም አልተከበሩም። የታሳሪዎቹ ቤተሰብ ሰለ ልጆቻቸው ደኅንነት ምንም አይነት መረጃ አልደረሳቸውም። አዲስ ዘይቤ ከወጣቶቹ መረዳት እንደቻለችው በተፋፈገ ኹኔታ ከመታሰራቸው በላይ ለጤና ተስማሚ የሆነ ምግብ እና መኝታ አልቀረበላቸውም።በዚሁ ሁኔታ ያሉ ወጣቶች ናቸው በኮሚሽነሩ ቃለ መጠይቅ እንደሰማነው የኅጽበተ-ኃልዮ ስራ የተሰራባቸው። ከላይ ለማሰየት እንደተሞረው ኅጽበተ-ኃልዮ ከማሰቃየት ተግባሮች አንዱ ነው። ከኮሚሽነሩ ንግግር እና ጦላይ ሰንብተው ከመጡ ወጣቶች ምስክርነት የምንረዳው ነገሮቹ በአጋጣሚ የተከሰቱ ሳይሆኑ በዕቅድ እንደተደረጉ ለመደምደም የሚያስገድዱ ናቸው። አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው ወጣቶች የነበሩበት ኹኔታ አስተሳሰብን የመለወጥ ጥረት የተደረገበት እንደሆነ ገልጸዋል።አንድ የፖለቲካ ፓርቲ የራሱን ሀብት በመጠቀም የዜጎችን ሰብዓዊ ክብር ሳይጥስ ያዋጣኛል የሚለውን ስልት መከተል ይችላል፡፡ የሀገር ሀብት እና መንግሥታዊ መዋቅር እየተጠቀሙ እና የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብት እየጣሱ ዓላማን ለማሳከት መንቀሳቀስ ግን በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም፡፡ በተለይ ምንም አይነት ሕጋዊ ቅቡልነት  በሌለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት እንዲሁ ሀገሪቱን ወደ ዴሞከራሲያዊ ስርዓት አሸጋግራለኹ በማለት ለተለያዩ አካላት በተሰጠ ቃል ብቻ የጸና ዙፋን ይዞ ይህንን ስልት መከተል ብዙ ዋጋ ያስከፍላል፡፡እነ ሚካኤል፣ በየጦር ካምፑ ሥልጠና የተሰጣቸው ወጣቶች፣ የእነርሱ ቤተሰቦች፣ ይህ ዜና ወደ ጆሯቸው የገባ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵውያን በኮርያ ጦርነት ወቅት በቻይናውያን ሥልጠና እንደተሰጣቸው የአሜሪካ ወታደሮች የባለጋራዎቻቸውን ርዕዮት ያቀነቅኑ ይሆን? መልሱ ለቀባሪው እንደማርዳት የቀለለ ነው።

አስተያየት