ኅዳር 10 ፣ 2011

“በ27 ዓመታት አንድም ቀን አሜሪካን አገር ኖሬ አላውቅም::” ዓለምፀሐይ ወዳጆ

ቃለመጠይቆች

የኢትዮጵያ ቴአትር ንግሥት የሆነችው ዓለምፀሐይ ወዳጆ ከብዙ አመታት ስደት በኋላ ወደ ወደሀገር ቤት ተመልሳ ነበር፡፡ ዓለምፀሐይ መራሔ ተውኔት፣ ጸሐፌ…

“በ27 ዓመታት አንድም ቀን አሜሪካን አገር ኖሬ አላውቅም::” ዓለምፀሐይ ወዳጆ
የኢትዮጵያ ቴአትር ንግሥት የሆነችው ዓለምፀሐይ ወዳጆ ከብዙ አመታት ስደት በኋላ ወደ ወደሀገር ቤት ተመልሳ ነበር፡፡ ዓለምፀሐይ መራሔ ተውኔት፣ ጸሐፌ ተውኔት፣ ተዋናይት፣ ገጣሚ ናት፡፡ ለብዙዎች የጽናት ተምሳሌት በመሆኗ ብርቱ እመቤት እያሉ ስለአይበገሬነቷ ይዘክራሉ፡፡ የአዲስ ዘይቤ ባልደረቦች ዳዊት ተስፋዬ እና አቤል ዋበላ ዓለምፀሐይን ወደ አሜሪካን ሀገር ልትመለስ በመትጣደፍበት የመጨረሻ ሰዓታት አግኝተዋታልአዲስ ዘይቤ፡ የየት ሰፈር ልጅ ነሽ?ዓለምፀሐይ፡ ትውልዴን ሲነግሩኝ ቀበና እንደተወለድኩ ይነግሩኛል፡፡ ያደገኩትና እኔ የማውቀው ግን ጉለሌን ነው፤ ጉለሌ ገፈርሳ አካባቢ ነው ያደገኩት። ከዚህ በተረፈ አያቶቼ አንድ ጊዜ ወደ ወለጋ መስመር ተመድበው ሔደው፤ ወዳጆ የአያቴ ስም ነው፤ ሲቡስሬ ወረዳ ገዢ ነበሩ፡፡ ለተወሰነ ጊዜ እዚያም ተቀምጫለሁ፡፡ ያደገኩትና የኖርኩት ግን ጉለሌ ገፈርሳ ነው፡፡ የጉለሌ ልጅ ነኝ፡፡ምን ትውስታዎች አሉሽ ስለ ጉለሌ?እንዴ በጣም ብዙ፡፡ መድኃኔዓለም ት/ቤት ነው የተማርኩት፡፡ ኤለመንተሪ ደግሞ ሁለት ዓመት ፊታውራሪ ኃ/ጊዮርጊስ ት/ቤት ነበር የተማርኩት፡፡ የሠፈሩ ገበያ፤ መንገዱ ጠቅላላ በጣም ከፍተኛ ትውስታ አለኝ፡፡ የመጀመሪያው መጽሐፌ ላይ እንዲያውም “ጉለሌ ገፈርሳ” የሚል ግጥም አለኝ፡፡ የዓለም ከበደ ዘፈንም ላይ ጉለሌን አነሳሳዋለሁ፡በጣም ብዙ ትዝታ አለኝ፡፡ የመጀመሪያ የግጥም ችሎታዬን፤ በዛ ዕድሜ አልችል ይሆናል ግን አራተኛ ክፍል፣ አምስተኛ ክፍል እያለሁ መምራኖቼ ግጥሜን ክፍል ውስጥ ቆሜ እንዳነብ ያደረጉበት ዕድሜዬ ነው፡፡ እና ብዕር እንዳልተው ያደረገኝ ዕድሜዬ ጉለሌ ነበር፡፡ መድሃኔዓለምም ስገባ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤትን ከሰባተኛ ጀምሮ እዛ ነው የጨረስኩት፡፡ የትምህርት ቤቴ ዳይሬክተርና መምህራኖቼም ናቸው፤ ቴአትርም ስጀምር፤ ግጥምም ስጀምር፤ ጭራሽ የስነ-ፅሁፍ ውድድርም ስገባ ይበልጥ ከክፍል [ውስጥ] ማንበብ ወደ ሰንደቅ ዓላማ መድረክ ላይ ፅሁፎቼን ማንበብ የደረስኩበት ነው፡፡ እና ያ ሁሉ ፅንሱ መሠረቱ ጉለሌ ገፈርሳ ነው፡፡ ትምህርት ቤት ውስጥ ደሞ በስቱደንት ሙቭመንትም በጣም እሳተፍ ስለነበር ስቱደንት ካውንስል ውሰጥ በመማክርት ጉባኤው ነበርኩበት፡፡ የፖለቲካ መነሻዬም ጉለሌ ነው፡፡ እና መነሻዬ ጥንስሱ ጉለሌ ነው፡፡ከተማን ስናይ የብሔር የሀይማኖት ስብጥሩ ይስበናል፡፡ አዲስ ዘይቤ በሀገር ደረጃ ያ እሴት ተዳክሟል ብሎ ታምናለች፡፡ አንቺ ልጅ እያለሽ ሰፈር ውስጥ ምን ዓይነት ገጽታ ነበር የነበረው፤ ከጎረቤቶቻችሁ ጋር እንዴት ነበራችሁ?የሚገርመው እሰከዛሬ የኔንም ዘር የሚያውቁ አይመስለኝም የነሱንም ዘር አላውቅም፡፡ አሁን እንዳውም ከስደት ዓለም ተመልሼ እንደገና ቤቴን ማየት ነበረብኝ፡፡ መጀመሪያ የቴአትር አዳራሽ ብዬ የወጣሁባት የት/ቤቴ አዳራሽ እሱን ለማየትም ሄድኩኝ፡፡ ዳይሬክተሩንም አናገርኩ፤ አብሬውም ሆንኩ፡፡ ሰፈሬም ሄድኩ፤ ሰፈረተኞቼን ሳገኝ አብዛኛው እዛ ሰፈር ያለው ያረጀም የደከመውንም ሰው አገኘሁ፡፡ እንደውም መጀመሪያ ከመኪና ስወርድ ያገኘኝ ያሲን ይባላል። የእስልምና ሐይማኖት ተከታይ ነው፡፡ ት/ቤቴ አብሮኝ የነበረ ልጅ ነው፡፡ ስሙ ያሲን ከመሆኑ በስተቀረ አንዳችም የምናውቀው ሌላ ነገር የለንም፡፡ በዘር ላይ የተመሠረተ ነገር አልነበረንም፡፡ እንኳን በዛ ዘመን ቴአትር ቤት ገብቼም አሁን ዓለሙ ገ/አብ ከትግራይ አካባቢ መወለዱን እንጂ ኤርትራዊ መሆኑንም አሁን በቅርቡ ነው የምሰማው፡፡ ምንም አይነት እንደዚህ ያለ ጥያቄና ቋንቋ ስላልነበረኝ እግዚአብሔርን በጣም አመሰግነዋለሁ፡፡ ሳላውቀው እንደኖርኩ ሳላውቀው እንድሞት ነው የምፈልገው። አሁንም ያ ችግር የለብኝም፤ አልወደውምም፤ አላምንበትምም፡፡ አገሬንም ለቅቄ እንደሄድ ያደረገኝ ደግሞ የዛ ወላፈን መምጣት ይታየኝ ስለነበር ነው፡፡ በዛ ውስጥ ደግሞ መጠመድም አልፈልግም፡፡ እንደጥበብ ሰውነቴ ደግሞ በተወሰነ ሕብረተሰብ ክፍል የምፅፈውም ነገርም ስለሌለኝ፤ ስፅፍም ለጠቅላላው ኢትዮጵያዊ፤ በጠቅላላው ሰው ስለሚባለው ነገር ስለሆነ፤ ሳላውቀው ወጣሁ፡፡ እዛም አሜሪካን ሀገር ዓለምፀሐይ የምትታውቀው በዚሁ ነው፡፡የ”ሀሁ በስድስት ወር” ተውኔት ሕትመት ውስጥ “እመት ጌኔ አምበርብር በዓለምፀሐይ ወዳጆ” ይላል፡፡ እሱ ቴአትር ሲሰራ የብሔራው ቴአትር ተቀጣሪ ነበርሽ ማለት ነው?ሀሁ በስድስት ወር’ ልክ ሊጀምር ሲል እጩ ተዋናይ ሆነን ሄድን፤ ወደ ሦስት መቶ አስራ ሁለት ተማሪዎችን አወዳደረና ጋሽ ፀጋዬ[የዓለም ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን] የመጀመሪያውን የትአትር ት/ቤት ያኔ የትአትር አርትስ ዲፓርትመንትም የለም፤ የቴአትር ት/ቤትም በኢትዮጵያ አይታወቅም። ስለዚህ አስራ ሁለት ተዋንያኖችን አስተምራለሁ ብሎ ወሰደ፡፡ ሲወስድ ከአስራ ሁለቱ እኔ አንዷ ነበርኩ፡፡ ሀሁ በስድስት ወር ተከፍቶ መታየት ጀምሯል፡፡ እነ ወጋየሁ፤ እነ እትዬ ጠለላ፤ እነ ጋሽ ጌታቸው ደባልቄ፤ እነ አውላቸው ደጀኔ፤ ጃይንት የምትላቸው አክተሮች ነበረ የሚሰሩት፡፡ እኛ ደግሞ እኔ፤ ተክሌ ደስታ፤ ሲራክ፤ ዓለሙ ገ/አብ፤ እና ሌሎችም በእጩ ተዋናይነት እዛ ስንገባ ደብል ካስት ተደርገን የወጋየሁን ተክሌ፤ ዓለሙ ገ/አብ፣ የጋሽ ተስፋዬ ሳህሉን፤ ሲራክ ታደሰ፣ የአውላቸው ደጀኔ እና እኔ የእትዬ ጠለላን እንድናጠና ተደርገን ክፍለ-ሀገር እንድንጓዝ ማለት ነው፤ እንደ ሁለተኛ ቡድን ተቆጥረን ስናጠና እያለን እትዬ ጠለላ ከፀጋዬ ጋር በነበረ ችግር ቴአትሩን አቋረጣ ወጣች። ስወጣ ዋናው ቡድን ውስጥ እኔ ገባሁ ማለት ነው በዚያ እድሜዬ፡፡ ከባድ ነበር፤ ቀላልም አልነበረም፡፡ ቡድኑ እኔን ለመቀበል የነበረበት ፈተና ነበረ፤ እንደ አንድ ጀማሪ ሕጻን ነው የምታየው፡፡ እና ጌኔ አምበርብርን ተጫውቻለሁ፡፡ከፀጋዬ ገ/መድኅን ጋር ሰርተሻል፡፡ እና ፀጋዬን እንዴት ታስታውሺዋለሽ?ፀጋዬ ከሙያ አባቶቼ አንዱ ነው፡፡ መጀመሪያ ቴአትር ያስጀመረኝ መላኩ አሻግሬ ነው፤ ጋሽ መላኩ የመዝሙር አስተማሪዬ ነበር፡፡ በመዝሙር አስተማሪነት ት/ቤቴ ውስጥ ሲያየኝ የወላጆች ቀን ላይ፤ በት/ቤት በማደርገው እንቅስቃሴ ለትወና ያጨኝ ጋሽ መላኩ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ አገር ፍቅር ሄጄ የተወሰኑ ቴአትሮችን ሰራሁ፡፡ ጋሽ ፀጋዬ ደግሞ አገር ፍቅር መድረክ ላይ አየኝ ማለት ነው፡፡ ከዛ በኋላ ነው ወደ እጩ ተዋናይነት ያመጣን፡፡ በመሃል ደግሞ ቴአትር እደገት ክበብ የሚባልም ነበረ። ተማሪዎችን ከት/ቤት ስንጨርስና ስንመጣ ክበብ ነገር ነበረን፡፡ ያንን ክበብ ደግሞ የሚመራው ተስፋዬ አበበ ስለነበር የሱም እጅ አርፎብኛል፡፡ ከዛ በኋላ ነው ጋሽ ፀጋዬ ያገኘን፡፡ ጋሽ ፀጋዬ ደግሞ እንገዲህ ለየት የሚያደርገው፤ አንደኛ በውጫ ስታንዳርድ ነው የሚያስበው። እና የብሔራዊ ቴአትርን ከቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴአትር ቤትነት፣ ብሔራዊ ቴአትር ብሎ አስሰይሞ ተዋንያኖችን ዘመናዊነት በታከለበት በአዲስ ስልጠና እንደ አዲስ ትምህርት እንድንማር አደረገን፡፡ መምህራኖችን ከየቦታው አመጣ፡፡ እነዛ መምህራኖች እነስብሃት ከራሽያ ተምረው ነው የመጡት፤ ማስተርሳቸውን በቴአትር ይዘው፤ እነ ጋሽ ተስፋዬ ገሠሠ አሉ፤ እርሱም ማስተርሱን አሜርካ ሰርቶ ነው የመጣው፤ ኃይማኖት ዓለሙ፤ እርሱም ማስተርሱን አሜሪካን ሰርቶ ነው የመጣው፤ ደበበና ወጋየውን ጨምሮ እነዛ ትልልቅ ባለሙያዎች ቴአትር ምን እንደሆነ እንድንማር አደረገን፡፡ ጋሽ ፀጋዬ በተለይ አገር ፍቅር ቴአትር ስሰራ መጥቶ ከመድረክ ጀርባ “ጋሽ  ፀጋዬ  መጥቷል፤ ጋሽ ፀጋዬ መጥቷል” ተብለን እንርበደበዳለን፤ ስወጣ “አጨበጨቡልሽ? ደስ አለሽ?” አለኝ፤ እኔም “አዎ! ጭብጨባ ታድያ ደስ አይልም እንዴ?” አልኩት፡፡ እንግዲህ ውሎ አድሮ ነው የሚገባኝ፡፡ እሱ “ጭብጨባ እንዳይሰርቅሽ ፈራለሁ” የሚል ነገር ነበረው፤ ከጭብጨባ በላይ እንድሆን ይፈልጋል፡፡ እና ዛሬ አንዳንዴ በትንሽ ቴአትር ወይም በትንሽ ሙያ ዝና የሚሰብራቸውን ሰዎች ሳይ የጋሽ ፀጋዬ ያ ምክር ወጥሮ እንደያዘኝ አያለሁ። ለምን? ለጭብጨባ አልተሰበርኩም፤ ወይም ለእንደዛ ዓይነት ነገር እጄን አልሰጠሁም፡፡ በአንዳንድ የአስተዳደር ጉድለቶች ላይ በነበሩ የቴአትር ቤቱ ችግሮችና ሰላማዊ ሰልፎች ውስጥ ከአርቲስቶች ጋር የነበረው ችግር ነበር ጋሽ ፀጋዬ፡፡ እንደፀሐፊ፤ እንደብዕር ሰው ግን ባሕሪ አጎልብቶ በማውጣት፤ ሼክስፒር አማርኛ ተናጋሪ ነበር ወይ እሰኪባል ድረስ ነው ሲተረጉምም የሚተረጉመው። ቋንቋው፤ ሐምሌት ላይ ስጫወተው ራሱ የነበረው ክብደትና ግዝፈት፤ ስደት ዓለም ደግሞ ሄጄ ማክቤዝን ሳዘጋጀው ማክቤዝ ውስጥ ያሉት የጥንቁልና ባሕሪያት ውስጥ ኦሮምኛ ሳይቀር ይከታል ጋሽ ፀጋዬ ድርሰትና ትርጉሙ ውስጥ፡፡ እንዴት ወደኛ አምጥቶ እንደሚከታቸው እነዛን የጥንቆላ ባሕሪያት፤ ድቤ መቺዎች፤ የኢትዮጵያ ደንበኛ ቃልቻዎች አድርጎ ስለሚሰራቸው በጣም ኢትዮጵያዊ ያደርጋቸዋል፤ እና እውነት ይሄ ነገር ሼክስፒር ነው ፀጋዬ ነው? እስክትል ድረስነው የሚሰራው፡፡ ያ ጉልበቱ በጣም ይገዝፍብኛል፡፡ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ የተለያዩ ማሕበረሰቦች ባሕሎችን ማስተዋወቅ እኛ ነን የጀመርነው የሚሉ አሉ፡፡ ይሄም ትውልድ እሱን ሲሰማ ነው ያደግነው፡፡ ያኔ ስትሰሩ የተለያዩ የኢትዮጵያ ማሕበረሰቦች ባሕሎችን ለማስተዋወቅ ጥረቶች አይደረጉም ነበር?ምንድነው መሰለህ? እንዲያውም ጋሽ ፀጋዬ የሰራቸውንና ሌሎችም ስራዎችን ስታይ ብዙ ግዜ የእንግሊዝ አገር ታሪኮች ናቸው፤ እነ ሀምሌት፤ እነ ማክቤዝ፤ ሌሎቹም ትርጉሞች እነ የፌዝ ዶክተር፤ ወይም ሞሊየርንም፤ ሌሎች ነገሮችንም በምንሰራበት ሰዓት ላንዳንዱ ተመልካች ጭራሽ ትርጉምነቱም አይገባውም ባሕሉን ሲጠብቅ፡፡ ቅድም እንዳልኩት የኦሮምኛ ቃሎችን መጠቀም የምንፈልገበት ቦታ ላይ እንጠቀመዋለን፤ ግጥሙ ውስጥ ይከተዋል፡፡ የዛም ጉልበቱ ነው የጋሽ ፀጋዬ ኃይለኝነቱ፡፡ የኢትዮጵያን፤ ዛሬ ብሔር ብሔረሰቦች የሚባሉትን የሚያካትትበት ባሕርያቶች አሉት፡፡ እንዳልኩት፤ አሁን የነጌኔ አምበርብርም በለው፤ ከስም ሳይቀር የነሃምሳለቃ ጣሴም በለው ይከት ነበር፤ ምንም ችግር አልነበረበትም፡፡ እሱ አንዱ ነው፡፡ሌላው በኛ ግዜ ልዩነት ስላለ ሳይሆን፤ ወይም ፈርተን ሳይሆን፤ ወይም “እንትና አልተጠቀሰም፤ የእንትና ብሔረሰብ ይከፋዋል” ከሚል ሳይሆን የእውነተኛ ፍቅርና አቅርቦት፤ የእውነተኛ ታሪክ ትረካ ነበር የሚሰራው፡፡ ሌላው እንደነ ጋሽ አውላቸው ደጀኔ ያየህ እንደሆነ፤ መቼም ጋሽ አውላቸው ደጀኔ ያልተነገረለት ትልቅ ባለሙያ ነው፡፡ ቴአትር ትወናውን ያነሳኸው እንደሆነ፤ በባሕል ስራዎቹ ያነሳህ እንደው፤ ጋሽ አውላቸው ማለት እያንዳንዷ የክፍለ-ሀገር ወረዳ እየሄዱ በቴፕ ቀርፀው ሙዚቃውን፤ ፎቶግራፍ አንስተው፤ ያኔ ቪዲዮም ምንም የለም፤ አምጥተው “የእከሌ ባሕል እንዲህ ነው፤ ፀጉሩ፤ ዕቃዎቹ፤ ቁሳቁሱ፤ የወግ እቃቸው ይሄን ይመስላል፤ ጌጣቸው እንደዚህ ነው” ተብሎ ቆዳው ተፈልጎ፤ ጨሌው ተፈልጎ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ያን ሁሉ የባሕል ጨዋታ ሲያቀርብ የዛ ስጋት ስላለ ሳይሆን እውነተኛይቱን ኢትዮጵያ ከማቅረብ አንፃር ነው፡፡ ውበቷን፤ ልዩነቱን፤ ጌጡ ብዛቱ፤ የወግ ዕቃዎቹ፤ የፀጉር ስራዎቹ እራሱ፤ የዜማው፤ የጭፈራው ልዩነት ውበታችንን፤ ጉልበታችንን እናወጣው ነበር፡፡ ዛሬ ያንን ጉልበት ነው መጣያችን ያደረግነው እንጂ ውበቱ ይወጣ ነበር በብሔራዊ ቴአትር ቤት፡፡ባለቤትነቱ ነበር ማለት ነው?አዎ የኛ የጥበብ ስራችን ነበር፡፡ እሱንም ነው በዓለም አቀፍ ደረጃ ይዘውት የሄዱ የነበረው፡፡ እኔ በጣም ልጅ ብሆንም፤ ሌጎስ በ1977 ዓ.ም ነው ዓለም አቀፍ የጥቁር ሕዝቦች የአርት ፌስቲቫል ነበር፡፡ እዛ ፌስቲቫል ላይ ከሁለት መቶ በላይ የኢትዮጵያ አርቲስቶች የተገኙበት ነው፡፡ ያንን ክብደት ያለውን የኢትዮጵያን ባሕል ነው ወስደን ያቀረብነው፤ እና ዓለም ነው አፉን ከፍቶ የሚያየው፡፡ ምክንያቱም እኛ ከውጪ የሚያስቀላውጠን ምንም ነገር የለም በእውነት ለመናገር፤ ውጪው ነው ወደኛ የሚያየው፡፡ ይሄንን መጣያችን ስታደርገው ነው የሚያሳዝነው እንጂ ውበታችን ያ ነው፤ ልዩነቱ፡፡ በዛ ውስጥ ነው ያደግነው እኛ፡፡ አሁን ያለው ነገር ግራ ነው የሚገባው፡፡ ብዙ ሰው እዚህ አገር ገብቼ “መንገዱን አየሽው? ሕንፃውን አየሽው? የተሰራውን አየሽው?” ይሉኛል፤ አዎ ግን ሰው ላይ አልተሰራም፡፡ ሰው ላይ መሰራት ነበረበት፤ ለዚህ ነው ችግሩም የሚመጣው፡፡ከ27 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰሽ ሰነባበትሽ፤ ታዲያ ምን አስደነቀሽ?ያሳዘነኝም ያስደሰተኝም ነገር አለ፡፡ ያስደነቀኝ ሕዝቡ አሁንም በጣም ጥሩ ሕዝብ ነው፤ ከእውነት፡፡ ለምን? ዘይት፤ ዳቦ ወይም ገበያው ዋጋው ቀንሶ ሳይሆን እኛንና የሌሎች መምጣት እያስለቀሰው ሲቀበለን ሳይ ዛሬም የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬም የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚገርም ሕዝብ ነው፡፡ በኛ ደስታ እሱ ሲደሰት አየዋለሁ፤ በኛ ሀገራችን መግባት ተስፋን ማየት መቻሉ በጣም ይደንቃል፡፡ እነሱ በሞቱ፤ እነሱ በቆሰሉ፤ እነሱ በታሰሩ ነው እኛ የመጣነው፡፡ ግን በሱ ስቃይ መጥተንም እሱ ነው የሚደሰተው፤ እኛን ማምጣቱን ራሱ እንደድል ቆጥሮ ማለት ነው፡፡ እንጂ ኑሮው ተለውጦ አይደለም፤ ያው ነው ኑሮው፡፡ የሕዝቡን ደግነትና ጥሩነት ባላገሩም ውስጥ ስሄድ የሚደንቅ ሕዝብ ነው፡፡ እና ጥቂቱ ከግንዛቤ ጉድለትም ይሁን ከማጣመም ፍላጎት ያንን ያለውን የሕዝብ ፍቅር ለማጥፋት የሚፈልገው ሰው ያሳዝነኛል፡፡ በተረፈ በጣም ብዙ ሕንፃ ተሰርቷል፤ ብዙ መንገድ ተሰርቷል፤ ብዙ የማላውቃቸው ነገሮች አይቻለሁ፡፡ በዛው መጠን ያዘንኩበት ነገር አለ፡፡ እንዳልኩት ያልተሰራበት የሰው አዕምሮ፤ ፍቅር ላይ ያልተደረገው ያልተሞከረው ሙከራ፤ ለማፍረስ የተደረገው፤ በመሀላችን ልዩነታችን እንዲሰፋ የተደረገውና የደከሙበት ድካም አሳዝኖኛል፡፡ሌላው ብዙ ግዜ በፖለቲካ ባሕል እጦትም እንደሁ አላውቅም ሰዎች ከፖለቲካ ወንበር ላይ ስለተነሱና የፖለቲካ ወንበር ላይ አዳዲስ ሰዎች ስለተቀመጡ ሀገር የምትቀየር እየመሰለን የምናስበው አስተሳሰብ ያሳሰበኛል፡፡ ሀገር የሚቀየረው ሕበረተሰቡ በሙሉ አስተሳሰቡ ሲለወጥ ነው፡፡ ያኔ ነው የሚለወጠው እንጂ የተወሰነ ጥቂት ሰው ወንበር ስለቀየረ አገር አትቀየርም፡፡ በስደት ዓለምም አሁን አንድ በሀገሪቷ ይመጥናል ተብሎ የማይታመን መሪ ነው አሜሪካንን እየመራት ያለው፡፡ ያንን መሪ ግን ገትሮ የያዘው ያ የተለወጠ አሰተሳሰብ ያለው ሕዝብ ነው፡፡ “አትችልም፤ ይሄን ስደተኛ እንዲህ ልታደርግ አትችልም፤ ይሄንን ዘር እንዲህ ልታደርግ አትችልም፤ ይሄንን ዕምነት እንዲህ ልታደርገው አትችልም” የሚለው ሕዝብ ነው፡፡ እና ያንን የሚል፤ “እምቢ ልትከፍለን አይገባም፤ እምቢ በዚህ ዘር ላይ ይሄንን አታደርግም” የሚል ሕዝብ ስላልሰራን እዛ ላይ ሚዲያና የጥበብ ሰው በግንባር ቀደምትነት ብዙ ስራ የሚጠበቅበት ይምስለኛል፡፡ ኃላፊነት አለብን፤ ሕብረተሰብን በአስተሳሰቡ የመቀየር፡፡ ወጣቱንም ሳይ አንዳንዴ አዝናለሁ፤ እንዲህ አይነት ችግር ውስጥ በማለፉ ልናዝንለት የሚገባ ወጣት አለ፡፡ ያም ሆኖ አጠገቡ ሌላ ባለሕንፃ ቁጭ ብሎ ከታች ሲያዝን ሲለምን ታየዋለህ፡፡ የኛ ባሕል ቀላል ባሕል አይደለም፤ እና እሱ እሱንም አያለሁ፡፡ በጥበቡም በሌላውም መስክ እየተከታተልኩ ምን እንዳለ የተገነዘብኳቸው ነገሮች አሉ፡፡ የሰራ ባሕልና የተጠያቂነት መጥፋት ደሞ አለ፡፡ የተጠያቂነት መጥፋት ከመንግስት ጋር የተገናኘ ነገር አይደለም፡፡ ለምን? አንድ ሰው የመኖሪያ ግቢው ውስጥ ያለውን ዛፉን የመጠበቅ፤ ቦታውን ንፁሕ አድርጎ የመያዝ ተጠያቂነት የግለሰብ ነው፡፡ ሃኪሞች በበሽተኞቻቸው ላይ፤ ዳኞች በፍትሕ ጥያቄ ላይ፤ መምህራን በተማሪዎቻቸው ላይ፤ የጥበብ ሰው በጥበብ ግቢ ውስጥ ባለው ሁኔታ ተጠያቂነት ሊኖርበት ይገባል፡፡ እና የዛ ንዝህላልነት ውጤት ጠቅላላ እንዲጠፋ ያደረገው ብዙ ነገር ይታየኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከመንግስት ፖለቲካም ውጪ የሆነ ነገር ነው ይሄ፡፡ እና የተጠያቂነት ባሕል መጥፋቱም ያሳስበኛል፡፡በተለይ በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ በጣም የሚታወቅ አንቺ፤ ወጋየሁ ንጋቱ፤ እና ጥላሁን ገሰሰ ደጅ ላይ አብራችሁ ተቀምጣችሁ የምትታዩበት ፎቶ አለ፡፡ ስለዛ ፎቶ ምን ትውስታ አለሽ?ናይጄርያ ሌጎስ ነው፤ በ1977 ዓ.ም ለዓለም የጥቁሮች ፌስቲቫል ሄድንና ናይጄሪያ ሌጎስ በጣም ይሞቃል፤ የሚደንቀው ትልልቅ ቢዩልዲንግ ነው የተሰራው የአርቲስቶች ቪሌጅ ተብሎ፡፡ እና የቪሌጁ መሐል መንገድ አለ፤ ከመንገዱ ባሻገር የሴቶች ማረፊያ ነው፡፡ እኔ ሴቶቹ ሰፈር ጫጫታ ሲያስቸገረኝ ወደዚህ [ወደ ወንዶቹ ማረፊያ] መጣሁና እነጥላሁን ክፍል ማደር ጀመርኩ፡፡ እኔ፤ የመጀመሪያው ባለቤቴ ታዴ፤ ወጋየሁ፤ እና ደበበ አራታችን አንድ ክፍል ነበረ የምናደረው፤ ተደራራቢ አልጋ ላይ ነው፡፡ እና ቀን ቀን ውጪ እንሆናለን፡፡ በዛ ሙቀት ጥላሁንም ልብሱን ከፍቷል፤ እኔ በፒጃማ ነኝ፤ ወጋየሁ በቱታ ነው፡፡ እና ይሄን ፎቶ ለሪታ ወጋየሁ ከአልበሜ ላይ በስልኬ ፎቶ አነሳሁና የድሮ ፎቶ ነው እዪው ብዬ ስልክላት እሷ ደሞ ፌስቡክ ላይ ላከችው፡፡ ከዛ ዓለም ላይ ተበተነ ማለት ነው (ሳቅ)፡፡ ለሪታ እንዳውም ውይ ሪታ ይሄ እኮ ሰው የሚያየው ፎቶ አይደለም፤ አለባበሳችንን እዪው በረንዳ ላይ በፒጃማና በቱታ እኮ ነን፤ ጥላሁን እራሱ ልብሱ እንኳን ክፍት ነው አልኳት (ሳቅ)፡፡ እና  ሳየው በጣም እሰቀቃለሁ (ሳቅ)፡፡ለ27 ዓመት በስደት ስትኖሪ እንደሁ የመጣው ይምጣ ብለሽ፤ ሻንጣሽን ሸክፈሽ ወደሀገሬ እመለሳለሁ ያለሽባቸው ጊዚያቶች አሉ?ዓለምፀሐይ፡ ውይ ነበሩ፡፡ እንግዲህ እናቴን አልቀበርኩም፡፡ ተመልከት እናቴ የሞተች እንደሄድኩ ነው፡፡ ቀጥሎ ባለቤቴ ሞተ፤ ኡ (በጩኸት) አልኩኝ፤ መቅበር አለብኝ ባሌን በቃ የመጣ ይምጣ ብዬ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ አባቴ ሞተ፤ እና በነዚህ ሀዘኖች ግዜ በጣም ተጎድቻለሁ፡፡ ስደት እንደ ለቅሶ ጊዜ ደግሞ የሚቀጣህ ጊዜ የለም፡፡ ወይ በዚህ ባህል ውስጥ ስላደገኩ ይሆናል፤ ጮኸህ በማለቀስ፤ አብሮ ተቃቅፎ ማልቀስ ነው ያደግኩበት ባህል እና ያም ፍላጎትም ሊሆን ይችላል፡፡ አስቤም ነበረ፡፡ መንግስትም በቃ ትምጣ ተብለሻል፤ ተብለሻል ነው የምባለው። ለምንድነው ተብለሻል የምባለው? ለምን ህግ አይኖርም አገሬ ውስጥ? የሰራሁት ወንጀል ካለ በሰራሁት ልጠየቅ፤ ያጠፋሁት ጥፋት ካለ፡፡ አለበለዚያ ግን እንደማንኛውም ስደተኛ ህግ ይውጣልንና በህግ አትፈለጉም መባል አለብን፡፡ ምክንያቱም ሃምሳ ሎሚ የሚባል የቴሌቭዥን ፕሮግራም ነበር ታውቁታላችሁ፤ አሜሪካን አገር መጥቶ የኔን የጣይቱ ማዕከልን የምሽት ዝግጅት ቀረፀና፤ ብዙ ፕሮግራሞች ሰርተዋል ልጆቹ ጎበዝ ጎበዝ ጋዜጠኞች ናቸው፤ ከዛ እኔን ኢንተርቪው አደረጉኝ፡፡ ምንም ፖለቲካ ነገርም አልገባበትም ግን ስለ ጥበቡ ምሽት “እንዴት እዚህ ሆነሽ በስደት ዓለም የገጣሚያኑን ታሪክ እንዲህ እያቀረብሽ የኢትዮጵያን ግጥም ልታስተዋውቂ ቻልሽ?” በሚል ጠየቁኝ፡፡ ኤፍሬም ስዩም ነበረ የምሽቱ የክብር እንግዳችን፤ ያው እሱ አሜሪካን አገር የለም፡፡ ስራዎቹን፤ ታሪኩን ለቅሜ አቅርቤ ነበር፡፡ እሱን የሰጠሁትን ኢንተርቪው በቴሌቭዥን ለቀቃችሁ ተብሎ ፕሮግራማቸው ታገደ፤ እና ከስራ ተባረሩ፡፡ እሱን እሱን ሳይ እነዚህ ሰዎች አሁንም ያው ናቸው ብዬ ተወዋለሁ እንጂ በሃያ ሰባት ዓመታት አንድም ቀን አሜሪካን አገር ኖሬ አላውቅም፡፡ ሁሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ነኝ ያለሁት፤ ሁሉ ሰው ያውቃል፡፡ “ኧረ ዓለም ተይ አሜሪካ ውስጥ ኑሪ፤ ግቢ” ነው የምባለው፡፡ ልቤ እዚህ ነው ያለው በቃ፡፡ ምን ተባለ የምለው እዚህ፤ ደውዬ የተነበበውን፤ የተሰራውን ቴአትር ጠይቃለሁ “ዛሬ ይሄን ቴአትር ከፈታችሁ አይደል?”፤ እንዲሁ ነኝ እዚሁ ነበር የነበርኩት፡፡ ስመጣም ወዲያው ግንኙነቱ የተጠበቀበት ምክንያት የገጣሚዎችን መፀሐፍ ሰብስቤ አምጥቼ አነባለሁ፤ ስራቸውን እከታተላለሁ፤ ዘፈን ሲወጣ እከታተላለሁ፤ ቴአትር ሲከፈት እከታተላለሁ፤ እና ድልድዩን ሳልሰብረው ኖርኩኝ፡፡ እና እዚህ ነው የኖረኩት፤ በእውነት፡፡የሲኒማ ጥበብ ብዙ አንጋፋ የቴአትር ተዋንያንን አባብሏል፤ አሸፍቷል፡፡ እንደሁ ሲኒማ አንቺንስ አሽኮርምሞሽ እንኳን አያውቅም?ልዩነቱን የማያውቅ ሰው ነው የሚሸነፍ፡፡ አሁን አሜሪካን አገር ቴአትር ገቢ የሌለው ሙያ ነው፤ አቅመ ደካማ ሙያ ነው፡፡ በዚያው መጠን ደግሞ የተከበረ ሙያ ነው፡፡ አሜሪካን አገር አንዲት የፊልም አክትረስ ለቴአትር ብሮደዌይ ብትጋበዝ ወይም የሼክስፒር ቴአትር ውስጥ ብትጋበዝ “እንዴት እንደምወጣው አላውቅም ግን ቴአትር እንድጫወት ተጋብዣለሁ” ብላ መፍራቷን ማክበሯን ነው የምትናገረው፡፡ ለምን? ቴክኖሎጂ የማያግዝህ፤ ትንፋሽህን ሳይቀር ተመልካች የሚያይህ፤ ዓይንህ እጅህ ሙቀትህ ከሙቀቱ ጋር የሚገናኝበት ከባዱ ሙያ ተውኔት ነው፡፡ ፊልምማ [ሲሰራ] ተመልካች የለህ፤ የሚፈርድህ የለ፤ የምትፈራው ነገር የለህ፤ ስክሪፕትህን እያየህ እያነበብክ፤ እየተቆረጠ እየተገጠመ በቴክኖሎጂ ታግዘህ የምትሰራው ስራ ነው፡፡ ክብደቱን ስለማውቅ ቴአትርን ምንግዜም አከብረዋለሁ፡፡ እንዲያውም ጎድተውብኝ ስለቆዩ እዚህም በጣም ብዙ ሰዎች ጋር ተነጋግሬበታለሁ፤ ባለስልጣንም ሳይቀር፡፡ የቴአትር ሙያ እንዲህ መሆን አልነበረበትም፡፡ ጊዜያዊ ገቢን፤ ጊዜያዊ ሩጫን፤ ጊዜያዊ ጥቅምን፤ ወይም ጊዜያዊ ስልጣኔን ተከትሎ የሚመጡ ነገሮች አሉ፡፡ ከዚህ ወደ አሜሪካን የሚመጡ የፊልም ሰዎች አሉ፤ “ዓለም ምንም አንፈልግም፤ መንገዱን ብቻ አቋረጪና ስምሽን ስክሪን ላይ እንፃፈው ያሉኝ አሉ”፤ እኔ ሙያዬ ደግሞ መንገድ ማቋረጥ አይደለም (ሳቅ) ስለዚህ አላቋርጥም፡፡ ስክሪፕታቸውንም ሳይ የማይመጥነኝን ነገር አልሰራም ብዬ ተቀምጬ ነው የምኖረው፡፡ ግን አሜሪካን አገር አንድ ትልቅ ቆንጆ ፊልም ስክሪፕቱን ወድጄው የሰራሁት አለ፤ “ዎቭን” የሚባል በደንብ የተዘጋጀ ፊልም አለ፡፡ ሴት ነች ዳይሬክት ያደረገችው፡፡ እንጂ ድሮ “ሦስት ሺህ ሁለት” የሚል እንደዚሁ ጎበዝ ሰዎች የተሳተፉበት እንደነ ተፈሪ ብዙአየሁ፣ ታደሰ ወይም ደስታ ስሙ ጠፋኝ፣ ተፈሪ ዓለሙ እነሱ እነሱ የሰሩት እሱም ፊልም ላይ ተሳትፌ ነበር፤ ሦሥት ሺህ ሁለት የሚልበት ምክንያት ሦሥት ሺህ የኢትዮጵያ ዘመንና ሁለተኛው የአብዮት በዓል እሱን ብለው ተከፍቶ ነበረ፡፡ ጄነራል ተፈሪ በንቲ ስለነበሩበት ደርግ ከለከለው ፊልሙም በዛው ቀረ፤ ከዛ ሌላ የሰራሁት የለም፡፡ የቴሌቭዥን ተውኔቶች ነው የሰራሁት፡፡ ግን የቴአትርን ክቡርነት ስለማውቅ አስደንግጦኝም አያውቅ፤ አስበርግጎኝም አያውቅ፡፡ የምወደውም ሙያዬም የመድረኩን ቴአትር ነው፡፡ከትወናው፣ ከዝግጅቱ እኩል አንቺ የምትታወቂባቸው የዘፈን ግጥሞች አሉ፤ ከአስር ዓመት ወዲህ ግን የዘፈን ግጥሙ ላይ ጠፍተሻል፡፡ ምነው?እፅፋለሁ፤ ባታይ ነው እንጂ የነግርማ ተፈራ “እኔ አይደለሁማ” የአልበም ርዕሱ እራሱ የኔ ስራ ነው፤ ጎሳዬ አሁን የሚያወጣው ላይ ፅፌያለሁ፤ እነዳዊት፤ እነፀሐዬ የሚያወጡት ሲዲ ላይ ሁልጊዜ አለሁ፡፡ ዘፈን እራሱ ስራው ደክሟል እንጂ የኔ ግጥም አልቆመም፤ ዘፈንም ቢቆም ደግሞ ግጥም መፃፌን አላቆምም፡፡ እፅፋለሁ፡፡የዘፈን ግጥሞችሽ ዘመን ተሻጋሪ ናቸው፤ ከመደበኛው ግጥም እንዴት ነው የምትለዪው?የዘፈን ግጥሞች በሁለት ሦሥት የተለያዩ ዓይነቶች ነው የምሰራው፡፡ አሁን ሰርፀ [ሰርፀ ፍሬስብሃት] የኔን የዘፈን ግጥሞች ሲገልፅ ገጣሚ ሁሉ የዘፈን ግጥም መፃፍ አይችልም ብሎ ይገልፃል፡፡ ወይም በውቀቱ ስዩም “እንዴት ነው የሚዋጣልሽ ዓለምዬ?” ይለኛል፡፡ የቴአትር ስራዬ፤ ኦብዘርቭ የማድረግ ባሕሪዬ ረድቶኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን እዚህ ቤት ገብቼ፤ እናነተን ሰላም ብዬ ስቀመጥ “እዛ ጋር ያለው ሰው፤ ምን ይዟል? ምን እየጠጣ ነው?” ብለህ ብትጠይቀኝ አስተውዬዋለሁ፡፡ ይሄን በትወና ሙያ ላይ የምትሰለጥንበት ነው፡፡ በመሰረቱ ለስለላ ስራም ይሆናል አይደል? (ሳቅ)፡፡ ሁለተኛ ደግሞ አነባለሁ፤ ማንበቤ ደግሞ በጣም ይረዳኛል፡፡ ለሁሉ ሰው የምነግረው መፃፍ ከፈለጋችሁ አንብቡ ነው፡፡ ያነበበ ሰው ምንም ጊዜ ባዶ አይሆንም፤ አለው፡፡ ቃልም አይቸግረው፤ ዓረፍተ ነገርም አይቸገረው፤ ሀሳብም አይቸገረውም፡፡ ሦስተኛ ሰው በጣም አዳምጣለኹ፤ ማዳመጥ ወዳለኹ፡፡ እና ጓደኞቼ ቢወዱም፤ ቢያፈቀሩም፤ ቢከዱም፤ ቢጣሉም አዳምጣቸዋለሁ፡፡ እና እነዛ ነገሮች ደግሞ ሀብት ናቸው፡፡ እሱ ራሱ የሚረዳኝ ይመስለኛል፡፡ በተረፈ ዜማዎቹን እንደመነሻ አድርገው ሲሰጡኝ በዛ ዜማ መነሻነት የምፅፋቸው ፅሁፎች አሉ፡፡ አንዳንድ ግዜ ደግሞ ከራሴ ድንገት፤ አሁን የሆነ ዘፈን ስሰማ ሌላ ነገር ውስጥ ከገባሁ ፈንጠር ብዬ ሄጄ የራሴን ሀሳብ ፅፌ የተቀመጡ ፅሁፎቼም፤ የተዘፈኑ ፅሁፎቼም አሉ፡፡ አሁን ቅድም ስንሰማው የነበረው[የሙሉቀን መለሰን] “ምነው ከረፈደን” ከራሴ ነው የሆነች ካርድ ላይ አንድ ሀሳብ አግኝቼ ነው “is it not too late” የምትል፤ ሌላ ነገር የለም እና ከዛ ላይ ተነስቼ ሀሳብ አደረግኳት ማለት ነው፡፡ አንዳንዶቹን ደግሞ ከሚመጡት ዜማዎች ስሜት ላይ ተነስቼ ሰራለሁ፡፡ ሳዳምጥ ደሞ አሁን የማዝንበት አለኝ፡፡ ለምሳሌ እንደሁ እስክሰታ በሚያስወርድ ዜማ ስለመለየት ቢፃፍ ልክ አይደለም አይደል? ለእሱ እሱ ደግሞ እጠነቀቃለሁ፤ ይገባኛል፡፡ እሱ እሱም የረዳኝ ይመስለኛል፡፡ ከዛ ውጪ ዘፋኞቹ ሲዘፍኑት ጉልበት የሚሰጡት አሰጣጥ፣ የቋንቋ እውቀታቸው፣ አማርኛ የቱጋ እንደሚነሳና እንደሚወርድ ማወቃቸው ለኔም ግጥም አስዋፀኦ አድርጓል፡፡ ዜማዎቹ፣ ሙዚቃዎቹን ያቀናበሯቸው ሰዎች በኢትዮጵያ እነዚህ አይደነቁም እንጂ በእውነት ከጀርባ ያሉት ባለሙያዎችም ሊከበሩ እንደሚገባና ጉልበት ሊሰጡት እንደቻሉ መናገር ፈልጋለሁ፡፡ አሁን ጥላሁን [ገሠሠ] በጣም የደከመ ግጥም ሰጥተኸው፣ ፅፈህ ብታነበው ኤጭ የምትለውን ግጥም ግጥም አድርጎ ዋው ብለህ የምትሰማው ዜማ ያደርገዋል፡፡ የሱ ጉልበት ነው ያንን ያደረገው፡፡ ወይ ሌላ ዘፋኝ ቢዘፍነው ላትሰማው የምትችለው ነገር ይሆናል፡፡ ብዙ ሳይሰሙ የወደቁ ድንቅ ግጥሞች አሉኝ በዘፋኙ ድክመት ምክንያት፡፡ ሙሉቀን [መለሰ] እራሱ አሁን የፕሮቴስታንት አማኝ ከሆነ ጀምሮ ዘፈን ስለማይሰማ አንዴ “ያለም ሰው መኪና ውስጥ ሆኜ አንድ ያንቺን ዘፈን ሰማሁ፤ ገሎብሻል ገሎብሻል” ብሎኛል፡፡ እና የዘፋኙም ጉልበት አለ፤ የዜማው ጉልበት አለ፤ የሙዚቃ አቀናባሪዎቹ ጉልበት አለ፤ የሙዚቀኞቹ ጉልበት አለ፤ እና መታደልም ነው፡፡ ጥሩ ጥሩ ነገሮች እንዲቀርቡልኝ ያደረገው ያም ያም ሳይሆን አይቀርም፡፡የዘፈን ግጥሞችሽን ግን አንጎራጉረሻቸው ታውቂያለሽ?አላውቅም፡፡ ዘፈን አይሆንልኝም (ሳቅ)፤ ዜማ አላውቅም፤ ድምፄ አያምርም (ሳቅ)፡፡እንዳንቺ በቴአትር ዝግጅት፤ በተዋናይነት፤ በግጥም፤ በዘፈን ግጥም፤ በትወና፤ የጥበብ ተቋም በመመስረት የላቀች ኢትዮጵያዊት ሴት የለችም ብንል አያወዛግብም፡፡ ባንቺ መንገድ መጓዝ ለሚፈልጉ ሴቶች ምንድነው የምትመክሪያቸው?እንቅልፍ የለኝም፡፡ ቀላል አይደለም፤ ረጀም ሰዓት ነው የምሰራው፡፡ ይታረፋል ወደሚባልበት ኢትዮጵያም መጥቼ ይኸው አልተኛሁም እስካሁን ድረስ፡፡ ከሦስት ሰዓት ከአራት ሰዓት በላይ አልተኛም በሕይወቴ ውስጥ፡፡ አንዳንድ ጊዜ መቶ ዓመት የኖርኩ እስኪመስለኝ ድረስ እኔ ራሱ ይሄን ሁሉ ሰርቼዋለሁ የምለው፡፡ በዝግጅትም እንዳጋጣሚ የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት አዘጋጅ መሆኔ ይገርመኛል፡፡ አላውቅም ነበር ያኔ፡፡ ብቻ ትግል ነው፤ ላለማረፍ በማደርጋቸው ነገሮችው ውስጥ ብዙ ነገሮችን ነክቼ ዳስሼ ሰርቼአለሁ፡፡ ሰለምፀናና ስለምጥር ይመስለኛል ውጤቴ፡፡ እንደዘበት አልሰራም፡፡ ብርጭቆም ቢሆን ማጠብ ካለብኝ በደንብ መታጠቡን አረጋግጣለሁ፡፡ እና አንዳንዴ ይሄ ፐርፌክሽኒስት የሚሉት ዓይነት ነኝ መሰለኝ፡፡ ችግርም እኮ ነው በሽታም ነው፤ ግን እንደዛ ነው የምሰራው፡፡ በጣም ጥርት ያለ ሥራ መስራት ስለምፈልግ ይመስለኛል፡፡ ስተወው ከአስር ዓመት ከሃያ ዓመት በኋላ ትልቅ ነገር ሆኖ አየዋለሁ፡፡ ስሰራው የደከምኩበት ወይም ያፈሰስኩበት ጉልበት ውጤት ነው፡፡ በሕፃናት ቴአትርም በኩል፤ በግጥሞቼም በኩል፤ በትወናዬም በኩል፤ በዝግጅቴም በኩል የሰራሁትን ስራ ስሰራው በደንብ ጥንቅቅ አድርጌ፤ ደክሜበት ስለምሰራው ነው፡፡ እውነት ለመናገር ያከበርከው ነገር ምንግዜም አይጥልህም፡፡ በምንም ሙያ በደንብ ከደከምክበትና አክብረህ ከያዝከው መልሶ እንደሚያስከብርህ፤ እንደሚከፍልህ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ እና ፅናት፣ ተስፋ አለመቁረጥ፣ እኔ ተስፋ ቆርጬ አላውቅም፡፡ አይቻልምን ደግሞ አላውቅም፡፡ እኔ አሜሪካን አገር የግጥም ምሽት ስጀምር “እንዴ አሞሻል እንዴ፤ እዚህ ሕዝብ መሐል አሁን ሰው መጥቶ ግጥም ያዳምጣል ብለሽ ነው?”ሲሉኝ እኛ ማዳመጥ የምንወደው ሰዎች እናዳምጣለን ብዬ ነው የጀመርኩት፡፡ አይቻልምን አልቀበልም፤ በቃ አይቀበልም ሰውነቴ፡፡ ይቻላል ብዬ ነው የምሰራው፡፡ በሀገሬም ሆነ በምኞትና ሕልሞቼ ላይ ተስፋ ቆርጬ አላውቀወም፡፡ ለምን አይቻልም? ብዬ ስለምል ነው ምንም በሌለበት ሰዓት ብሔራዊ ቴአትር ቤት የኃላፊነት ቦታዎችን በምይዝበት ሠዓት ይቻላል ብዬ የሰራኋቸው ነገሮች ዛሬ ቀርተው እንደዚህ የማያቸው፡፡ በዛ ላይ ሴት ሆነህ፤ በእውነት ብዙ ፈተና አለ ሴት መሆን ላይ፡፡ በዛ ላይ ስደት፡፡ ስደት ዓለም ውስጥ ዓይኖች ሁሉ ድፍን ልቦች ሁሉ ባዳ የምለው ውሸት አይምሰልህ፡፡ እና በቋንቋ የማይግባባህ ሕዝብ፤ ግጥሞቼ ላይ እንደምለው በቁልምጫ የማይጠራ ሕዝብ መሐል፤ ስሜን አያቁትም እንኳን በቁልምጫ ሊጠሩኝ፡፡ ማንነቴም በማይታወቅበት አገር ውስጥ ወጥቼ የሴናተርም ይሁን፤ የኮንግረስማንም ይሁን፤ የሜየርም ይሁን ከአርባ ሁለት በላይ ሽልማቶች ነው ያገኘሁት፡፡ ፅናት ይከፍላል፤ የምትሰራውን ስራ ካላቆምክ፤ ተስፋ ካልቆረጥክና ከጠነከርክ፤ ደሞም ጥራቱንም ይዘህ መሆን አለበት፡፡ ግን እኔን ጎድቻለሁ፤ ቤተሰቦቼን ጎድቻለሁ፤ የሚወዱኝን ሰዎች ጊዜ ወስጄባቸዋለሁ፤ አቅሜን አጥቻለሁ፡፡ ባለሕንጻ አይደለሁም፤ ባለንብረት አይደለሁም፤ ብዙ ጓደኞቼ ሀብታም ናቸው (ሳቅ)፤ አሁንም መንግስት ስለጋበዘኝ እንጂ ማረፊያ ኖሮኝ አልመጣሁም፡፡ ስለዚህ የሚጎዳህ፤ የሚነጥቅህ ነገር አለው፡፡ ብዙ ነገር ይነጥቅሀል፡፡ ጤናዬን ወስዶብኛል፤ ይጎዳኛል፡፡ ያ ከእንቅልፎቼ የወሰድኩት ጊዜም ስላለ ነው፡፡ እና እንዲፀኑ ነው የምመክራቸው፡፡ ተስፋ እንዳይቆርጡ፤ እንዲያልሙ፡፡አዲስ አበባ ላይ አንቺ የምትሳተፊበት የሙሉ ጊዜ ቴአትር ልናይ እንችላለን?በጣም! እንዴ በጣም፡፡ ዋናው ነገሬ እሱ ነው፡፡ በተለይ የእቴጌ ጣይቱን ቴአትር በጥር ከፍታለሁ ብዬ ነው የመጣሁት፡፡ ኢትዮጵያም ሁኔታዋም ተመቻችቶ፤ እግዚአብሔር ደግ ነው፤ ያ ነገር እንደሚከፈት ተስፋ አለኝ፡፡ ሌሎችም ቴአትሮች ቢሆኑ ችግር የለብኝም፡፡ እኔ ግን ከመድረኬም አልነጠል፤ ድሮም መድረኬን ነው የምወደው፡፡ ከመሬቴ አልለቅም፤ የኔ ዙፋን ያለው እዛ ላይ ነው።ወደ ኢትዮጵያ ጠቅልለሽ ትመለሺ ይሆን?እሱን አላውቅም፡፡ ለምንድነው የማላውቀው? እዛም ስደት ዓለም ውስጥ በኔ መውጣት በጣም ስጋት አለው፡፡ እዛ አካባቢ ብዙ የኢትዮጵያ ሕፃናትንም፤ ብዙ ወጣትንም፤ ከጥበብ የሚያገናኝ ስራ ሰራለሁ፡፡ ችግር አለ፤ ተቋምን አክብሮ የመያዝና የመቀጠል ችግር አለ፡፡ እንደ ድርጅት የመቀበል፤ በጎ ፈቃደኛ ሆኖ የመስራት ነገር ባህላችን ውስጥ ደካማ ነው፡፡ እና እዛም ያቋቋምኩትና አስራ ስምንት ዓመት የደከምኩበት ድርጅት በዚህች በመጣሁበት ጊዜ እንኳን ሲንገዳገድ ነው የማየው፡፡ በጣም አዝናለሁ፤ ዓለምም ባትኖር ይሄ ነገር መቀጠል አለበት መባል አለበት፡፡ እና እዛም ያለው ሕብረተሰብ ደሞ ከጥበብ ውጪ እንዳይሆን ፈልጋለሁ፡፡ ልጆቹ በማንነት ቀውስ ውስጥ እንዲገቡ አልፈልግም፡፡ ከጥሩ ሕዝብ፣ ከጥሩ ባሕል፣ ከጥሩ ታሪክ እንደወጡ አፅንተን ነው የያዝናቸው፡፡ ቀላል አይደለም፡፡ በስነ-ፅሁፍ፣ በቴአትር፣ እና ኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ ዎርክሾፕ እንሰጣቸዋለን፡፡ የመጀመሪያውን ቤተ-መፅሐፍቷን ስከፍት ራሱ ደስታ አለ፡፡ ሰመር ላይ ደሞ ለሕፃናቱ ጭምር የምንሰጣቸው ነፃ ትምህርቶች አሉ፡፡ ያ ነገር ጥፍት እንዳይል ስጋት አለኝ፡፡ ያ መሠረት ከያዘ እኔ ከዚህ ዕድሜ በኋላ ስደት ዓለም መኖር ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ ወደ ሀገሬ ብመለስ የበለጠ ብዙ እዚህ ሰራለሁ፡፡ ብዙ መስጠት የምችለውን ሳልሰጥ አልፌአለሁ እዚህ ሀገር፡፡ እኔም ብዙ ከሕዝቤ ተምሬ የማሳድገውን ጥበቤን ተነጥቄአለሁ፤ ተነፍጌያለሁ ብዬ አስባለሁና እዚህ ብኖር ደስ ይለኛል፡፡ የዛን ግን እርግጠኛ መሆን ፈልጋለሁ፤ ያም መቅረት አይችልም፡፡የብሔር ፅንፈኝነት አንቺም ወዳጆችሽም የደከማችሁበትን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በብርቱ እየፈተነ ያለበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ መድሃኒቱ ምንደነው ትያለሽ?አንዱ ቅድም ያልኩት ማስተማር ነው፡፡ ማስተማር፤ ማስተማር፤ ያለመታከት ማስተማር ነው፡፡ ይሄንን ነገር ያሰፉት የግንዛቤ ችግሮች ናቸው፡፡ ሰዎች በሰለጠኑ ቁጥር፤ ባወቁ ቁጥር ከጎጆ ማለፍ፤ ከሀገር ማለፍ፤ ከአህጉር ማለፍ መጥቷል ሌላው አለም ላይ፡፡ ዛሬ አውሮፓ አንድ ላይ ሆኖ ባንድ ፓስፖርት፤ ባንድ ከረንሲ የሚጠቀምበት ሀገር እየሆነ ነው፡፡ እነዛን የሚያካክሉ ትልልቅ አገራት እየተዋሃዱ፡፡ እኛ አሁን ትንንሽ ጎጆዎች ውስጥ ነው የምንጣላው፡፡ ያ እንደማይሆን መረዳት የሚቻለው ከመማር፣ ከማወቅ፣ ከመገንዘብ ነው፡፡ ትምህርት ሲባል ደግሞ ምናልባትም መደበኛ ቋንቋን እውቀት ትምህርት አይደለም ብዬ እስባለሁ፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ቅፀል ያላቸው፣ ዲግሪያቸውን የምሰማ ሰዎችም ሲሳሳቱ ስለማይ ከዛ ጋራ ብቻ የሚያያዝ ነገር አይመስለኝም፡፡ ሁለተኛው ነገር ሕግ ነው፡፡ ሕጎች በሀገሪቷ ውስጥ መደንገጋቸውና የሕግ የበላይነት መኖሩ እራሱ ያሻል፡፡ እኔ አንተን መንካት እንደማልችል፤ መጉዳት እንደማልችል መደንገግ አለባቸው፡፡ ሦስተኛ እኔ ያደገኩበት ሕብረተሰብ በኃይማኖትም ቢሆን በጣም ጠንካራ ነው፡፡ እስልምናም ይሁን ክርስትናም ይሁን፤ ምንም ዓይነት እምነት ላይ የምንማራቸው ድንጋጌዎች አሉ፡፡ በነዛ ድንጋጌዎች መሠረት ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ነብስ ሊነጥቅ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው አይደለ? በግብረገብ እንኳን የምንማራቸው ቀላል ትምህርቶች አልነበሩም፡፡ እንደ ሕብረተሰብ ደግሞ ከትምህርት ቤትም፣ ከኃይማኖትም ወጪ ወንዶችም ብይ ይጫወቱ እኔም ገመድ ልዝለል ስንጫውት የነበርናቸው ጨዋታዎችና እንማራቸው የነበርናቸው ትምህርቶች እነሱም ተፅእኖ አላቸው፡፡ ስለዚህ የቤተሰብ፣ የሕብረተሰቡ፣ የአካባቢህ፣ የመምህራኖችህ፤ የመንግስት፣ እነዚህ ሁሉ ተቋማት የራሳቸውን ጥንካሬ እየፈጠሩ ከሄዱ መሻሻል የሚችሉ ነገሮች ናቸው፡፡ ሌላው መቼስ እግዚአብሔር እዚህ የተስፋ ጭላንጨል ውስጥ አድርሶናል፤ ኢትዮጵያ ቆኝጆ መንገድ ላይ ነው ያለችው፡፡ ያቺን ጭላንጭል ማስፋት ደግሞ የሁላችንንም ሚና ይፈልጋል፤ ግዴታም ነው፡፡አንቺ የክብር እንግዳ በሆንሽበት የራስ ሆቴል የግጥም ምሽት ላይ ጌትነት እንየው “ዓለምዬ እንዳንቺ ማን አለ፤ እኮ የታለ…” የሚሉ ስንኞችን የያዝ በስሜት የሚንጥ ግጥም አቅርቧል፡፡ እኛ ደሞ የምር እንጠይቅሻለን፡፡ በአእምሮና በመንፈስ ልዕለና የላቀ አንድ ሰው ጥሪ ብትባዪ ማንን ትጠሪያሽ?(ዝምታ) ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ ጌትነት ይሄንን ሊል የቻለበትን ምክንያት ሳስበው ገና ልጅ እያለ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ከመጣ ጀምሮ፤ ብሔራዊ ቴአትር በጣም መድከሜን ወይም ከዚህ ሙያ ጋር ተጣብቄ ያሳለፍኩትን ሕይወት ስለሚያውቅ ነው፡፡ ስደት ላይ ደግሞ የሱን ሙያ ወይም የሱን የጥበብ ውጤት አስመጥቼ አሜሪካን አገር ሃያ ሰባት ስቴቶች ዞረን ነበር፤ የቴውድሮስ ራዕይን ሳሳይ፡፡ ከዛ እሱም እራሱ ኖሮ አውሮፓ አንድ ዘጠኝ አገሮችን ዞርን፡፡ ያየኛል እንዴት እንቅልፍ እንደማጣ፣ መድረክ ጎትቼ፣ ጠረጴዛ አቅርቤ፣ ወንበር ሰርቼ፣ ተዋናይ አሰልጥኜ፣ አልባሳት ተሸክሜ፣ ሜካፕ ሰርቼ ስለሚያይ ምንድነው ነው የሚለው፡፡ “በቃ ከዚህ ዕድሜም በኋላ እንደዚህ ናት?” እያለ ያየኛል፡፡ እና ይሄ ነገሬ ከዛ ገና ድሮ የሱ ድርሰት የሆነውን በላይ ዘለቀን ሳዘጋጅ ከሚያውቀኝ ጊዜ ጀምሮ ያለ ነገር ስለሆነ ይመስለኛል፡፡ ብዙ የኔ ሀገር ሙያተኞች ያሳለፉት ብዙ ስቃይ፤ ትግልና፤ መከራ አለ፡፡ ከዚህ በፊትም የከፈሉ አሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ እነ አስናቀች ወርቁን አስታውሳለሁ፤ እነወጋየሁን አስባለሁ፤ እነአውላቸውን አያለሁ፤ እነእትዬ አስካለ አመነሸዋን አያለሁ፤ እነየሺ ተክለወልድ ከአገር ፍቅር፤ እነሱ እነሱንም አያለሁ፡፡ አንዳንዴ ከኔ በፊት ከነበሩት የመገነዣ ከፈን እንኳን የሌለው እንደነበር አውቃለሁ፡፡ እነ ጋሽ ፍቅር አየለ አሉ፤ ሰማለሁ ታሪካቸውን፡፡ የተጎዱና ያለፉ ሰዎች አሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አንድ ቴአትር ከሰራ ወይም አንደ ዘፈን ከዘፈነ የጨረሰ የሚመስለውንም ሰው አይቼአለሁ፡፡ ግን በዚህች በመጣሁባት አንድ ወር ውስጥም የድሮ ባለሙያዎች ቤት ሄጃለሁ፡፡ የሞቱተም ጋር፤ በሕየወትም ኖረው የደከሙት እነምበሬ በላይ፣ እትዬ አስካለ ጋር ገብቼ ያው እነሱም እኔም መላቀስ ነው፤ ንግግር ቋንቋ የለንም፤ በቃ እንላቀሳለን፡፡ እና አያለሁ ኑሮአቸውን፡፡ እነዚህ ሰዎች ለቴአትር ጥበብ ያለምንም ክፍያ ብለው ይሻለኛል ሃያ ሃያ አምስት ብር ሊሆን ይችላል ደሞዛቸው፤ ያለምንም ክፍያ ብዙ ስቃይ አሳልፈው ነው ይሄን ጥበብ ደሞ ለኔ የሰጡኝ፡፡ እኔም ደግሞ ያቅሜን ያህል ወደታች እንዲወርድ ነው የሞከርኩት፡፡ ግን በጋለው ምጣድ ላይ ቻቻቻቻ ብለው ደግሞ የተንጣለለ ኑሮ ውስጥ የኖሩትንም አያለሁ፡፡ ለሕብረተሰቡ መልሶ ያለከፈለውንም ሰው አያለሁ፡፡ እንጂ ብዙ ተሰቃይተው ያለፉ፤ ብዙ ተቸግረው ያለፉ ባለሙያዎች፤ ጉልበተኞች አሉ፡፡ እንዲሁ እገሌና እገሌ ባልልም ብዙ ደክመውበታል፡፡ አሁን እትዬ አስካለን ሳነሳ ሁሌ ትዝ የሚለኝ ነገር እትዬ አስካለ እኮ ማንበብና መፃፍ አይችሉም ሼክስፒርን ሲጫወቱ፡፡ እንድትጠይቋቸው ሄዳችሁ፡፡ ምናልባት የማስታወስ አቅማቸው ደከም ብሎ ሊሆን ይችላል ግን ጎበዝ ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ ምልስ ያደርጋቸዋል፡፡ አሁን 92 መሰለኝ ዕድሜያቸው፡፡ እና ልጆቻቸው ነበር የሚያነቡላቸው፤ ሼክሰፒርን ያህል ቴአትር እያደመጡ እያሉት እያዳመጡ እያሉት፡፡ ባለሳሳት “midsummer night dreams”ን ነው “የበጋ ለሊት ራዕይ” በሚል ነው በአማርኛ ተተርጉሞ የነበረው፡፡ እሱን የተጫወቱ ሰው ናቸው፡፡ የአዛውንቶች ክበብ መሪ ተዋናይ ማለት ናቸው እትዬ አስካለ አመነሸዋ፡፡ አያምንም ሰው እሳቸው ማንበብና መፃፍ አይችሉም ብትለው፡፡ ያንን ሁሉ ትግል ገትረው የቴአትር ጥበብን በኢትዮጵያ ያቆዩ ትልልቅ ሰዎች ናቸው፡፡ እነሱ ያቅማቸውን ያህል ከፍለዋል፡፡ የኔ አቅም ከበድ ብሎ ሊሆን የችላል፤ አነበብኩ አወቅኩ፤ ዘመናዊ ነገርም ቀሰምኩ፡፡ እሳቸው ግን በዛ አቅማቸው ያን አደረጉ፡፡ እንደ አቅማችን ነው የከፈልነው፤ እንደየዘመናችን፡፡ እነሱን እነሱን የላቁ አይደሉም ልል አልችልም፤ ለኔ በጣም ናቸው፡፡ አውላቸው ደጀኔን ማን የተካዋል በፈጣሪ አምላክ!? አንዳንዴ አሜሪካን አገር ቴአትር ገባለሁ፡፡ አይና አሁን ኦቴሎን ከናንተ የበለጠ ሰርተነዋል ብል ማን ያምነኛል እላለሁ፡፡ ኢትዮጵያ? ብለው የሚስቁ ነው የሚመስለኝ፡፡ እውነቱ ግና ያ ነው፡፡ እያጎን ተስፋዬ ሳህሉ ሲጫወት ያየ ሰው፤ አውላቸው ኦቴሎን የተጫወተበትን አቅም፤ እነዛን ትልልቅ ሰዎች አናውቅም፡፡ እንጂ የደበበ [እሸቱ] ራሱ ሻይሎክን ሲጫወት “የቬኑሱ ነጋዴ”፤ እኔ ራሱ ከሱ ጋራ ዕድል ደርሶኝ ተጫውቻለሁ፤ አይታመንም፡፡ ትልቅ ቦታ አድርሰውታል፡፡ እርግጥ ዛሬ ቴአትር ቤቶች ደክመው አያለሁ፡፡ ግን የድሮዎቹ ትልልቅ ባለሙያዎች አንድ ሁለት አይደሉም፤ መዓት ናቸው፡፡የእቴጌ ጣይቱ ሃውልት አዲስ አበባ ላይ ይተከላል?አዎ፤ አትጠራጠር፡፡ እሳቸው ትልቋ ብሔራዊ ሀብታችን፤ ኮሎያሊዝም ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይገባ ያደረጉ፤ የበታች እንዳንሆን ያደረጉ፤ ጥቁርነታችን እንዳያሳንሰን ያደረጉ ኩሩ ኢትዮጵያዊ እንድንሆን ቀርፀው ያሳደጉን ናቸው እቴጌ ጣይቱ፡፡ ይሄንን ነው የማያውቀው ሰዉ፤ እንጂ የብሔረሰብ ጀግና አይደሉም፡፡ የአንድ ብሔር አርበኛ አይደሉም፡፡ እንኳን ለእሳቸው ከአንድ አካባቢ የወጣ አርበኛም ቢሆን፤ ለኢትዮጵያና ለወገኖቹ መጠነኛ ስራ ያደረገም ቢሆን፤ ወይም ትልቅ ስራ የሰራ ሰው፤ እንደ ጄነራል ጃገማ ኬሎ፤ ገረሱ ዱኪ፤ ዘርዓይ ደረስ፤ አሉላ አባነጋ ላሉ በየሰፈሩ ቢሰራ ምን አለ? ደስታውን አልችለውም፡፡ እቴጌ ጣይቱን የማይበት ዓይን ግን ይለያል፡፡ ትልቅ የኢትዮጵያ አርበኛ ናቸው፤ ኢትዮጵያን ነው አንደ ያደረጉት፤ ለኢትዮጵያ ነው የደከሙት፤ ውጫሌ 17 ውሉን ነው ያስቀደዱት፡፡ ምኒሊክ የፈረሙትን ውል ነው ያስቀደዱት፡፡ አድዋ ሲኬድ ውሃ ያዝ ብለው ነው ሰራዊቱ በዘዴአቸው ያሸነፈው፡፡ ያንን የሚያክል ትልቅ የጣልያን ጦር የኢትዮጵያ ሰራዊት ድል እንዲያደርግ ያስቻሉ እናት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ትምህርት ከባህል ትምህርት ነው መጀመር ያለበት ብለው ዛሬ የደረሰውን ችግራ ያኔ የተናገሩ ናቸው፡፡ አነስተኛ ኢንዱስትሪን የጀመሩ ናቸው፡፡ የመንግስት አስተዳደር አንድ ቦታ መቀመጥ አለበት፤ ሕዝቡን ተጉላላ ብለው አንኮበር፤ አክሱም፤ ጎንደር ይሄድ የነበረውን ሰብስበው ማዕከላዊ መንግስት የመሠረቱ ናቸው፡፡ ይሄን አይደለም የሚል ካለ ያሸንፈኝ፤ ነው ካልን መሰራት አለበት፡፡ ይሄ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ደግሞ የመላው አርበኞቻችን ሃውልት ይመስለኛል፤ መሆንም አለበት፡፡ በምንም መስክ በጦርነትና በውትድርና ብቻ ሳይሆን በጥበቡ፤ በመምህርነቱ፤ በሳይንሱ፤ በፍልስፍና ለምንወደውንና ትልቅ ነው ለምንለው ሰው ለምን አናሰራም፡፡ ይሄማ አድናቆት መንፈግ ስስታምነት ካልሆነ ካልሆነ በስተቀር፤ ጀግኖቻችንን የማደነቅ ባህል ያስፈልገናል፡፡ እኔ በስደት በቆየሁበት አሜሪካን ሀገር የራሱን ጀግኖች አይደለም የእንግሊዞችን፤ የጀርመኖችን ሁሉ ሀውልት ያሰራሉ በየአደባባዩ፡፡ ለምን ተብሎ ነው ይህቺን የመሰለች ንግስት ሃውልት የማይሰራላት፡፡ እንዲያውም በቅርቡ ይኸው እንደሚሉኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ እና ይሠራል፡፡ 

አስተያየት