ኅዳር 24 ፣ 2013

አሶሳ፡ ለመንገድ ግንባታ 400 ሚሊዮን ብር ብድር ተፈቀደ

ቃለመጠይቆችወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግስት አሶሳ ከተማ ለከፍተኛ ጉዳት የተጋለጠ አስፋልት ለመጠገን፣ ለማስፋፋትና አዲስ ለመገንባት የሚያስችል 412 ሚሊዮን ብር…

አሶሳ፡ ለመንገድ ግንባታ 400 ሚሊዮን ብር  ብድር ተፈቀደ

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግስት አሶሳ ከተማ ለከፍተኛ ጉዳት የተጋለጠ አስፋልት ለመጠገን፣ ለማስፋፋትና አዲስ ለመገንባት የሚያስችል 412 ሚሊዮን ብር ብድር ከልማት ባንክ ተመቻቸ፡፡ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የከተማ ልማት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ቢፍቱ ጎሹ ከአጠቃላይ ብድሩ ላይ በዚህ ዓመት ለሥራ ማስጀመሪያ የሚሆን 100 ሚሊዮን ብር መፈቀዱን ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል፡፡

በዚህም 5.5 ኪሎ ሜትር አዲስ ግንባታ፣ 6.82 ኪሎ ሜትር የደረጃ ማሻሻያ እንዲሁም 8.6 ኪሎ ሜትር የነባሩ አስፓልት ጥገና ሥራ ይከናወናል፡፡ የክልሉ ዋና ከተማ ለሆነችው አሶሳ እድገት በ2003 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ  ትልቅ ዕድል ይዞ ቢመጣም ለዓመታት ያለዕድሳት ያገለገለው መንገዱ በከተማዋ ገጽታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ነዋሪዎች ይገልፃሉ፡፡

«መንገዱ ከጅማሮው ተገቢውን ጥራት ጠብቆ ካለመሠራቱም ባሻገር በወቅቱ ጥገና ባለመደረጉ አብዛኛው መንገድ ክፉኛ ተጎደድቷል፡፡ መንግስት ለከተማው የመንገድ መሠረተ-ልማት የሠጠው ግምት ዝቅተኛ ነው» ያሉት አቶ ሰለሞን አየነው የተባሉት ነዋሪ ተገቢው ጥገናና ማሻሻያ በአፋጣኝ እንዲደረግለትም ጠይቀዋል፡፡

የባጃጅ አሽከርካሪ የሆነችው አይናለም ተሠማ በበኩሏ«የከተማው አስፓልት ለከፍተኛ ብልሽት መዳረጉን ተከትሎ መኪና ለማሽከርከር ተቸግረናል፡፡ የመንገዱ መበላሸት በተሸከርካሪዎቻችን ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ለከፍተኛ ወጪ እየዳረገን ነው፡፡ ለእግረኛም ሆነ ለተሸከርካሪ እጅግ አስቸጋሪ ደረጃ በመድረሱ አስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል፡፡» ስትል ለአዲስ ዘይቤ ቅሬታዋን ገልፃለች።


የከተማውን የመንገድ ብልሽት ያመነው የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ በበኩሉ የአስፋልት ጥገና ማስፋፊያና አዲስ ግንባታ ለማካሄድ ድርጅቶች ከወዲሁ መለየታቸውን ገልጸዋል፡፡ በግንባታው የሚሳተፉ ጥሩ አፈጻጸም ያላቸውን ተቋራጮች በጨረታ የመለየት ሥራ እንደተጀመረም አክለዋል፡፡ የአሶሳ ከተማ ከ30 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ እንዳላት ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

አስተያየት