ኅዳር 10 ፣ 2011

የአሳዳጅና ተሳዳጅ አዙሪት

ኑሮማኪያቶ

ሰኞ ዕለት ጠቅላይ አቃቤ-ህጉ ለጋዜጠኞች የሰጡት መግለጫ ህወሓት/ኢህአዴግ በኢትዮጵያውያን ላይ ስለፈፀማቸው ለጆሮ የሚከብዱ በደሎች የሕግ ዕውቅና…

የአሳዳጅና ተሳዳጅ አዙሪት
ሰኞ ዕለት ጠቅላይ አቃቤ-ህጉ ለጋዜጠኞች የሰጡት መግለጫ ህወሓት/ኢህአዴግ በኢትዮጵያውያን ላይ ስለፈፀማቸው ለጆሮ የሚከብዱ በደሎች የሕግ ዕውቅና የሚያጎናፅፍ ነበር። ለተንገላቱ፣ ለተሰቃዩ፣ ለተዘረፉ…ፍትህ ያገኙበት ቀን ባይሆንም ፍትህ ደጃፍ የቆሙበት እንደሆነ አያጠራጥርም። አቃቤ-ህጉ ብርሃኑ ፀጋዬ ላለፉት አምስት ወራት ምርመራቸውን እያከናወኑ እንደነበር ገልፀው ሰውነትን የሚያንዘፈዝፉትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና፣ ዝርፊያዎች ዘክዝከዋል።በአዲስ አበባ ከመንግስት መዋቅር ወጪ የሚንቀሳቀሱ ማሰሪያና ማሰቃያ ቤቶች እንደነበሩ፣ ጨለማ ቤት ውስጥ ተጥለው ዓይኖቻቸው የታወሩ እንዳሉ፣ የተደፈሩ እንዳሉ፣ ጥፍሮቻቸው የተነቀሉ እንዳሉ፣ ጫካ ውስጥ በለሊት ከግንድ ጋር ታስረው የተተዉ፣ ከአውሬ ጋር ታስረው የነበሩ እንዳሉ ተነግሯል።የብረታብረት ኤንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ከመንግስት ተረክቦ ይሠራቸው በነበሩ ሥራዎችና፣ ይሳተፍባቸው በነበሩ ንግዶች በቢልዮኖች የሚቆጠሩ ብሮች እንደተመዘበሩ፣ አውሮፕላን ሁሉ እንደጠፋ፣ መርከብ እንደተሰወረ ተገልፆአል። ከአቃቤ-ህጉ መግለጫ በፊትና በኋላ ከስልሳ በላይ ተጠርጣሪዎች (የመከላከያ ሰራዊትና የደህንነት መ/ቤት አባላት እንዲሁም ተባባሪዎቻቸው) ስብሰባ ላይ ሳሉ፣ ከመኖሪያ ቤቶቻቸው፣ በሽሽት ላይ ሳሉም ተይዘዋል።ከነዚህ ውስጥ ከሁመራ ተይዘው ማክሰኞ ምሽት አዲስ አበባ በመድረስ፣ በመከላከያ ሰራዊትና በፌደራል ፓሊስ አባላት ታጅበው፣ እጆቻቸው በካቴና ታስረው ከቢጫ ሄሊኮፕተር ሲወርዱ የተነሳ ፎቷቸው በማሕበራዊ ሚዲያዎች የተበተነው የቀድሞም የሜቴክ ሥ/አስኪያጅ ጄነራል ክንፈ ዳኘው ምስል ትርጉሙ፣ ተምሳሌትነቱ፣ ምፀቱ፣ ፍትህ-አዘልነቱ ጥልቅ ነው።ወደ 1966 ዓ.ም እናጠንጥን። ደርግ ኢትዮጵያን የናጣትን አብዮት ሰርጎ ገብቶ፣ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴን ከቤተመንግስት አስወጥቶ፣ ቮልስዋገን መኪና ውስጥ ከትቶ በዚያው ከሸኘ በኋላ ዙፋኑን እንደተቆናጠጠ፣ ‘ኢትዮጵያን የዘረፉ፣ ድሃን የበደሉና ያሰቃዩ የቀድሞ ሥርዓት ሹማምንት ናቸው’ ያላቸውን ሥልሳዎቹን (በተለምዶ) መኳንንት በጠረጴዛ ዙሪያ የደቦ ፍርድ ፈጃቸው።አብዛኛዎቹ ባለሥልጣናት ከርቸሌ ተወስደው ጥይት ተርከፍክፎባቸው ሲያልቁ፣ ቀሪዎቹ በቤታቸው ሳሉ ‘እጅ አንሰጥም’ ብለው ተዋድቀው ሞቱ። መኳንንቱ የአፄው ሥርዓት እስር ቤት በነበረው ከርቸሌ ግቢ በጅምላ መገደላቸው እራሱ መራር ምፀትን ያዘለ ነበር።ሕወሓት/ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር በወታደራዊው ደርግ መንግስት ፈላጭ ቆራጭ የነበሩት ባለሥልጣናት ከአዲስ አበባ ለማምለጥ ሲራወጡ በጊዜው የደህንነት ኃላፊ የአዲስ አበባ መውጫዎች ሁሉ ክርችም ተደርጎ ተዘግቶባቸው፣ በመጨረሻም ከየተሸሸጉበትና ከመኖሪያ ቤቶቻቸው ተለቅመው፣ አንዳንዶቹም ድምበር ላይ ተይዘው ወህኒ ተወረወሩ። ጥቂቶቹ ኤምባሲ እንደተሸሸጉ እስካሁን አሉ፤ ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያምን ጨምሮ ሌሎቹ ጥቂቶች ደግሞ ከሀገር አመለጡ።እኛ የደረስንበት ኢቲቪ መመናቸክ የተለማመደው የደርግ ባለስልጣናትን የፍርድ ቤት ውሎ በማሳየት እንደነበር አይረሳም (ኢቲቪ ከዳኛ በፊት ፍርድ መስጠቱንም አሁንም ቀጥሏል)። ያኔ የቀይ ሽብር ሰለባዎች ተረሽነው የተቀበሩባቸው ጉድጓዶችና፣ በደርግ መንግስት የጅምላ ግድያ ተፈፅሞባቸዋል የተባሉ ስፍራዎች እየተጠቆሙ ተቆፍረው የሚወጡ ክምር አፅሞችን በፍርሃት ተሸብበን እንደ ተከታታይ ፊልም አይተናል።ዛሬ ደግሞ ከ40 በላይ የሜቴክ ከፍተኛ አመራሮችና የደህንነት አባላት አሞራው ሕንፃ (የቀድሞው ኢምፔርያል ሆቴል-የስሙን ምፀት እዩልኝ) ውስጥ ለስብሰባ በተገኙበት ተከብበው፣ ቀሪዎቹ በመኖሪያ ቤቶቻቸው፣ ሌሎቹ እግሬ-አውጪኝ ብለው በሽሽት ላይ ሳሉ ተይዘው ወደ ወህኒ ቤት ተወረወሩ።ይሄም ሳምንት እንደ 1966 ዓ.ም፣ እንደ 1983 ዓ.ም አሳዳጁ የተሳደደበት ሆኖ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ይወሳል። የብ/ጄነራል ክንፈ እጆች ላይ ካቴና ጠልቆ ከሂሊኮፕተር ሲወርዱ የተነሳው ምስልም በዚህ ትውልድ የሚረሳ እንደማይሆን ከወዲሁ መገመት ይቻላል።የሚደንቀው ነገር በ1966 ዓ.ም የነበሩት ተሳዳጆች በ1983 ዓ.ም ከነበሩት ተሳዳጆች፣ በ1983 ዓ.ም የነበሩት ተሳዳጆች በ2011 ዓ.ም ካሉት ተሳዳጆች ለሀገራቸው ያበረከቱት አስተፅኦ፣ የልምድና የዕውቀት ደረጃቸው፣ የስብዕና ከፍታቸው በእጅጉ እያነሰ፣ ግፍና ዝርፊያቸው እየጨመረ የመጣ መሆኑ ነው።እኛም ከትውልድ ትውልድ ግፈኞች ሲታሰሩ “እልል ፍትህ ተገኘ” እያልን፣ ግፈኞችን ያሰረው የባሰ ግፈኛ ሲሆን ተሸማቅቀን አንገታችንን ደፍተን እየተራገምን 2011 ዓ.ም ላይ ደርሰን አሁንም “እልል ፍትህ ታየ” ብለናል።የቀድሞዎቹ የመከላከያና የደህንነት አባላት የሠሩትን ግፍ ስንሰማ ደም እንባ ቢያስነባንም፣ ሰውነታችን በድንጋጤና በሀዘን አልታዘዝ ቢለንም፣ በድጋሚ ፍትህ ደጃፍ መድረሳችን የዐቢይን መንግስት እንድናመሰግን ቢያስገድደንም፤ አሁንም ተረኛ አሳሪ፣ ተረኛ ገራፊ፣ ተረኛ ደፋሪ፣ ተረኛ መዝባሪ፣ ተረኛ መሬት ቸብቻቢ ለመሆን ያኮበከቡ አላየንም ብለን አንዋሽም።አሁንም ከዚህ የግፍ አዙሪት እንደምንወጣ ሕጋዊ፣ ተቋማዊ፣ እና መዋቅራዊ ማረጋገጫ አግኝተናል ማለትም አንችልም። በእርግጥም ይኼ መንግስት ላይ ብቻ የሚጣል ኃላፊነት ሳይሆን ዜጎችም ክፍተቶችን በመሙላት፣ የመንግስትን መተላለፎችና ስህተቶች በማጋለጥ፣ ተጠያቂነትን በማጠንከር ጭምር የሚሰምር ውጥን ነው።‘ይኸው አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነሳ፣ አሁንስ አይበቃም? ይኸው እነ’ገሌ ተፈቱ፣ ይኸው እነ’ገሌ ታሰሩ፣ ከዚህ በላይ ምን ትፈልጋለህ? ይኸው እነ’ገሌ ተሸሙ፣ አሁንስ ምን ቀረ?’ እያሉ የሕግ የበላይነትንና የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትን ጥያቄ ወደ ‘ቲፎዞነት’ ክርክር ወለል የሚያወርዱት ሁሉ ሊገነዘቡት የሚያሻው፣ በኢትዮጵያ የመንግስት ግፍ እንዳይደገም ማረጋገጥ ዐቢይ ጉዳያችን ሊሆን እንደሚገባ ነው።በሦሥት መንግስታት ግፈኞች ሲታሰሩ፣ ግፍን ግን እንዳይመለስ አድርገን ማሰር ተስኖናል።በሦሥት መንግስታት በሥልጣን የባለጉ ወህኒ ሲወረወሩ፣ ብልግናን ግን አሽቀንጥሮ መጣል አቅቶናል። በዳዮች ተሳደዱ እንጂ፣ በደልን የምር አሳድደን አናውቅም። የሕግ የበላይነት ሰፍኖ፣ ለሥልጣን ልጓም ተበጅቶ፣ የፍትሕና የደህንነት ተቋማት ጠንካራና ገለልተኛ ሆነው፣ ሕዝብ የሀገሩ ባለቤት ከሆነ ብ/ጄነራል ክንፈ በካቴና ታስረው ከሂሊኮፕተር ሲወርዱ የተነሳውና የተሰራጨው ምስል በኢትዮጵያ የፍትህ መጀመሪያ ሆኖ ይታወሳል። ካልሆነ ምስሉ የሌላ ዙር ግፍ መጀመሪያ ምልክት ሆኖ ይቀመጣል።ባለስልጣናት በሥልጣናቸው ዘመን እንዳይገድሉ፣ እንዳያሰቃዩ፣ እንዳይዘርፉ ሕግ እየተቆጣጠራቸው፤ የአሁንም ባለሥልጣናትም የዛሬ አሳዳጆች የነገ ተሳዳጆች ከመሆን ተርፈው፣ የሥልጣናቸውን ዘመን ጨርሰው ሲሰናበቱ፣ በኢትዮጵያ መሬት ላይ በክብር የሚዘዋወሩበት ቀን ሊመጣ ይሆን?

አስተያየት