ሕዳር 10፣ 2011 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመዲናዋ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ስፍራ ወደ የምትገኘው ለገሀር መንደር አቅንተው ነበር፡፡ ምንአልባትም በታሪክ ከረጅም ጊዜ በኋላ ለገሃር ባቡር ጣቢያን የረገጡ የሀገሪቱ መሪ ያደርጋቸዋል፡፡ ባዶ እጃቸውንም አይደለም የሄዱት፡፡ ‘ኤግል ሂልስ’ የተሰኘውን መነሻው የተባበሩት አረብ ኢመሬትሷ አቡዳቢ የሆነውን የሪል ስቴት ቤቶች የሚገነባ ድርጅትን ይዘው ነው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የተቀናጀ የማህበረሰብ ልማት አምባ ፕሮጀክት ተብሎ የሚጠራው ግዙፉ የመኖሪያ መንደር 36 ሄክታር፣ ከቫቲካን በጥቂቱ የሚያንስ ሲሆን 4000 መኖሪያ ቤቶችን እና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጡ ግንባታዎች እንደሚካሄድበት ጠቅሰዋል፡፡
ይህ ዜና ቻርቲ ዋተርኤይድ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚያክብረውን ዓለም አቀፍ የመጸዳጃ ቤት ቀንን ምክንያት በማድረግ ከለቀቀው ሪፖርት ጋር ገጥሟል፡፡ በዚህ ሪፖርት 93 በመቶ ኢትዮጵያውያን እዚህ ግባ የሚባል ሽንት ቤት እንደሌላቸው ጠቅሶ ምንአልባትም ኢትዮጵያውን ከየትኛውም ሀገር ዜጎች በጽዱ ሽንት ቤት መጠን እንደሚያንሱ ይናገራል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስተሩ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር የገለጹት ጸዳ ያለ ስፍራ አስፈላጊነት ከላይ ከጠቀስነው ሪፖርት ጋር ተደምሮ የፕሮጀክቱን በጎ ጎን አጉልቶታል፡፡ ይህም የከተማዋን መዘመን አጥብቀው ለሚጠይቁ በከፊል ምላሽ የሰጠ ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም የግንባታው መልካም ገጽታ፡፡ ከዚህ ቀደም የከተማው አስተዳደር የመልሶ ማልማት ሥራዎችን እያከናወንኩኝ ሲል በከተማው ነዋሪዎች ላይ ያደርስ የነበረውን ጉዳት ለመቅረፍ እንደታሰበበት መገለጹ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በሚገነባበት ስፍራ የነበሩ ቀደምት ነዋሪዎች እንደከዚህ ቀደሙ እድር፣ ማኀበራቸው ተበትኖ፣ የእንጀራ ገመዳቸው ተበጥሶ የከተማ ጥግ እንደማይወረወሩ እንዲያውም በዚያው በሰፈራቸው፣ በቀያቸው የሚገነባው መኖሪያ ቤት እንደሚሰጣቸው መገለጹ ነው፡፡ ሌላው የዚህ ፕሮጀክት በጤናማነት የሚገለጸው የስፍራውን የታሪክ አሻራዎች እና ማኀበራዊ ትውስታዎች በማያጠፋ መልኩ እንደተነደፈ መገለጹ ነው፡፡
ይህ የ50 ቢሊየን የኢትዮጵያ ብር ፕሮጀክት መልካም ጎኑ እንዳለ ሆኖ ጥርጣሬን የሚያጭሩ እና ስኬታማነቱንም ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ገጽታዎች አሉት፡፡ የከተማዋ አስተዳደር የአገልግሎት ዘመኑን በጨረሰ ምክር ቤት ላይ የተሾሙ ናቸው፡፡ ሀገሪቱም መጠኑ ከፍ ያለ ወደ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት የሚደረግ ጥረት ላይ ናት፡፡ በዚህ ወቅት እንደዚህ ከፍ ባለ መጠን የማኀበረሰቡን እጣ ፈንታ ለመዋሰን የሚያስችል ህጋዊ ቅቡልነት አለመኖሩ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ የከተማው ማኀበረሰብ ያልመረጠውን አስተዳደር መቆጣጠር እና ቃሉን እንዲጠብቅ መጠየቅ አይችልም፡፡ ከዚህ እና ከፕሮጀክቱ ግዙፍነት አንጻር ለሙስና እና ለብልሹ አሰራር የመጋለጥ እድሉ ሰፉ መሆኑን ከመገንዘብ የሚመነጭ ስጋትን አዲስ ዘይቤ ትጋራለች፡፡
ሌላው አሳሳቢ ነገር ሰማይ ጠቅስ ህንጻዎችን እና ግዙፍ የመገበያያ ስፍራዎችን መገንባት ለአዲስ አበባ ነዋሪ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው? ብሎ ከመጠየቅ ይመነጫል፡፡ ብልጽግናና ስልጣኔ እነዚህን ግንባታዎች በማካሄድ ይመጣል ወይ የሚለው ስጋት በከተማ ልማት ዘርፍ ባለሙያዎች ዘንድ የሚያከራክር ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡
ሦስተኛው በዚህ ፕሮጀክት አዋጭነት ላይ የሚነሳው በከተማዋ መሪ ፕላን ለአዲስ አበባ ማዕከላዊ ፓርክ ( City Center Park) በተከለለ ቦታ መገንባቱ ነው፡፡ እንደዘርፉ ባለሙያዎች ትንታኔ መሪ ፕላን በሳይንሳዊ ቀመር የሚዘጋጅ ከተማዋ የላትን አቀማመጥ እና የመሬት ሀብት ግምት ውስጥ በማስገባት ለነዋሪው ምች እንድትሆን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በሙሉ ባካተተ ሁኔታ የሚዘጋጅ ነው፡፡ መንግሥትም ሆነ ነዋሪዎች የሚካሄዷቸው ግንባታዎች ይህንን ግምት ውስጥ ያስገቡ መሆን ይኑርባቸዋል፡፡ በተለይ አስተዳደሩ ግንባታዎች ከመሪ ፕላኑ ውጪ እንዳይካሄዱ የመጠበቅ ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡
ሌሎች በርካታ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ዐቢይ ጉዳይ በከተማው አስተዳደር እና ነዋሪዎች መካከል ያለው መስተጋብር ነው፡፡ ይህ ግንኙነት የሰመረ እንዲሆን ሁለቱም አካላት የሚጠበቅባቸው ኃላፊነቶች አሉ፡፡ በመጀመሪያ አስተዳደሩ የሞግዚትነት ሳይሆን የአገልጋይነት መንፈስ ሊኖረው ይገባል፡፡ በተቀመጠለት የህግ አግባብ የከተማው ነዋሪ ለኑሮው ምቹ የሆነ የመኖሪያ ስፍራ ተጋጅተውለት፣ መሠረታዊ ፍላጎቶቹ ተሟልተውለት፣ በነጻነት እና በሰላም እንዲኖር ማስቻል በዋናነት የሚጠበቁ አገልግሎች ናቸው፡፡ አገልጋይነት መነሻው ይህ ስለሚያስፈልግህ እንካ ሳይሆን ምን ልታዘዝ ከሚል ጥያቄ ይጀምራል፡፡
ነዋሪው የከተማውን አስተዳደር ከመምረጥ ጀምሮ በአስተዳደሩ የሚሰሩ ስራዎችን የመምረጥ፣ ቅደም ተከተል የማስያዝ፣ የማገዝ እና የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት፡፡ መሠረታዊ የዴሞክራሲ መርኆች ከየትኛውም ስፍራ በበለጠ መተግበር የሚገባቸው በከተሞች ነው፡፡ የዴሞክራሲ መነሻውን ሀሳብ ያመነጩት የጥንት ግሪካውያን እንዴት ከተማቸውን ማስተዳደር እንዳለባቸው ሲያሰላስሉ ነው፡፡ ከተሞች ላይ ያልተተገበረ ዴሞክራሲ በሀገር ደረጃ ይከበራል ማለት ዘበት ነው፡፡ ከተሞች ጥያቄያቸው በአብዛኛው መሠረታዊ ከኑሮ ጋር የተቆራኙ እና ሁሉም ሰው ያለ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ርዕዮት ልዩነት ሊስማማባቸው የሚችሉ ናቸው፡፡ ያልተማከለ አሰራር መዘርጋቱ የሚረጋገጠው ቀበሌዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆነ ከከንቲባው አስተዳደር ይልቅ ለቀበሌው ነዋሪ ቅርብ ሲሆኑ ነው፡፡ ከተማው የሚጸናው ነዋሪው የከተማዋ ባለቤት ሲሆን ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል የግሪኩ ፈላስፋ አፍላጦን ‘ይህች ከተማ የሆነችው፣ እኛ ዜጎች ስለሆንን ነው’ ሲል በሪፐብሊክ የጻፈው፡፡
“This City is what it is, because our citizens are what they are.” Plato