You can paste your entire post in here, and yes it can get really really long.
አዲስ አበባ ከተቆረቆረች በወርሃ ሕዳር መቶ ሠላሳ ሁለተኛ ዓመቷን ይዛለች፡፡ ታሪኳን በወፍ በረር የቃኙት ታምሩ ሁሊሶ እና አቤል ዋበላ ያናገሯቸው ሰዎች የከተማዋ የወደፊት እጣ ፈንታ የሰመረ እንዲሆን የነዋሪዎቿ የሰለጠነ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡ትውልድና እድገቷ-ህዳር 1879ንጉሱ ለዘመቻ ወደ አርሲ ወርደዋል። ጥቅምትን ተንተርሶ የሚመጣው ሕዳር ወር ብርድ አያጣም፤ እንጦጦም እንጦጦ ነው። በዚህ መሃል ከእንጦጦ ፍልውሃ ድረስ ለሙቅ ጠበሉ መለስ ቀለስ ማለቱ የሰለቻቸው ንግስት ጣይቱ፤ እዚያው ፍልውሃው አቅራቢያ መክረሙን መረጡና በዚያው መኖሪያቸውን ቀለሱ። ቦታዋንም በአቅራቢያቸው ባገኟት ትኩስ አበባ መስለው አዲስ አበባ ሲሉ ሰየሟት ይላሉ የታሪክ ሰዎች። ይህ የሆነበትን ቀን በትክክል ለማግኘት ለብዙ የታሪክ ባለሙያዎች ቸግር ነው። ያም ሆኖ ንጉስ ምነሊክ በአርሲ አድርገው ወደ ሃረር እንደሄዱ የባለቤታችው ደብዳቤ ደረሳቸው-እነሆ አዲስ አበባን መሰረትናት የሚል።ንጉስ ምንሊክ ጉዳያቸውን ፈጻጽመው እንደተመለሱም ወዲያውኑ መናገሻ ከታማቸውን ከእንጦጦ ወደ አዲስ አበባ አላመጡትም ። ቢያንስ ስድስት ዓመታትን እዚያው እንጦጦ ላይ ከራርመው ነው ኋላ ላይ አዲስ አበባ ላይ ሙሉ ለሙሉ የለመደኑት። ከእንጦጦ ወደ አዲስ አበባ ለመውረድ መጀመሪያ የዛሬው አዲስ አበባ ላይ የሚገኘው ቤተመንግሰት (በተለምዶ ጊቢ ይሉታል) ተሰርቶ መጠናቅቅ ነበረበት።ባህሩ ዘውዴ የዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ ሲሉ በሰየሙት መጽሐፋቸው ላይ፤ የአዲስ አበባን ምስረታ ከአክሱምና ጎንደር ምስረታ ቀጥሎ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቁ ፋይዳ ያለው ነገር ሲሉ ይገልጹታል።በ1979 ዓም የአዲስ አበባ መቶኛ ዓመት ልደት ሲከበር ፤በወቅቱ በነበረው የከተማው አስተዳደር ድጋፍ አለም አቀፍ ሲምፖዚየም ላይ የሚቀርቡ በርካታ ጽሁፎች በእንግሊዘኛ ቀርበው ነበር። ክጹሁፎቹ አንዱ የባህሩ ዘውዴ የጥንቱ የአዲስ አበባ ስፈሮች (Early Safars of Addis Ababa: Patterns of Evolution) ነበር። በዚህ ጽፉ እንድሚገልጸው ለአዲስ አበባ መመስረት ሌላኛው ምክንያት የሰሜኑ ገደላ ገደል መልክአምድር ለመንገድ ስራ አለመመቸቱም ነው።በወቅቱ ንጉስ ምኒሊክ ክጅቡቲ ጋር በባቡር ለመገናኘት የነበራቸው ፍላጎት ከእንጦጦ ቁልቁል ወደምትታየው የዛሬይቱ አዲስ አበባ እንዲመለከቱ እንዳደረጋቸው ተጽፏል። የምንሊክን ጊቢ ዙሪያ መኳንንቶቹ ሲሰፍሩበት፤ ልነግድ ያለው ደግሞ ከፍ ብሎ የጥንቷን አራዳ ያዘ። ንጉሱ ከጊቢው አጠገብ የግቢ ገብርኤልን ቤተክርስትያን አስሩ። በነገራችን ላይ የግቢ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የህንጻ ንድፍና ግንባታ ላይ በስፋት ተሳትፎ ያደረገውና ለፍጻሜ ያበቃው ሙስሊሙና የህንድ ተወላጁ ዋሊ ሞሃመድ ነው። በአዲስ አበባም የመጀመሪያው መስኪድም በዚሁ ዋሊ ሞሃመድ ስም ከገብርኤል ብዙም ሳይርቅ የተሰራው መስኪድ እንደሆነ የታሪክ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።አዲስ አበባን የሁልጊዜ መናገሻ አድርጎ ያቆማት ግን የ1988 የአድዋ ድል ነበር።ይህ ድል እጃችውን አፋቸው ላይ ያስጫናቸው በርካታ ምዕራባውያን የቆንስላ ጽህፈት ቤታቸውን ለመክፈት የአዲስ አበባን በር መቆርቆር ጀመሩ። አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የታሪክ ተመራማሪ እንደሚሉት የአድዋ ድል ባይኖር ኖሮ አዲስ አበባ እንደሌሎቹ እንደ አዲስ አለምና እንጦጦ ሁሉ ተንቀሳቃሽ መናገሻ (Roving Capital) የመሆን እድል ነበራት። ብዙዎቹ የምዕራብ አገራት ቆንሰላዎቻቸውን ከፈቱ። በ1900 የመጀመሪያው የከተማ መሬት አዋጅ “የመሃንዲስ ስዕል” በሚል ታወጀ። የመኖሪያና የንግድ ህንጻዎች ተገነቡ።እንዲህ እንዲህ እያለች ነበር ያደገችውና የሞቀችው።ይሁንና በአድዋ ድል ሽንፈቱ አዲስ አበባን አለም እንዲያውቃት ምክንያት የነበረው ጣልያን በ1928 ኃይሉን አጠንክሮ መጥቶ አዲስ አበባን አፈራረሳት፤አቃጠላት፤አስዘረፋት። የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን መውጣት ተከትሎና መጪው ክረምት እንዳይቀድመው ሲዋከብ የነበረው ጣልያን አዲስ አበባን በሚያዝያ ማለቂያ 1928 ዓ.ም ሲቆጣጣራት በርካታ ህንጻዎችን አራዳ ላይ በእሳት አወደማቸው።ከንቲባዎቿአዲስ አበባ እስከ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ድረስ 30 የሚሆኑ ሰዎች አስተዳድረዋታል። ከላይ የተነሳው የባህሩ ዘውዴ ጽሑፍ የመጀመሪያውን ከንቲባ የ1908ቱ አዛዥ መታፈሪያ ቢያደርጋቸውም፤ የአዲስ አበባ መስተዳድር መካነ ድር ላይ ግን የመጀመሪያው የከተማዋ ከንቲባ አድርጎ የሚያሳየው የ1892ቱን ከንቲባ ወልድጻዲቅ ጎሹን ነው። አዲስ አበባ በአጠቃላይ ታሪኳም የራሴ ብላ የሾመችው ከንቲባ ኖሯት አያውቅም።በ1997 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ የከተማዋን ወንበሮች ሙሉ በሙሉ ያሸነፈው ቅንጅትን ሲመሩ ከነበሩት አንዱ ብርሃኑ ነጋ(ዶ/ር) የከተማዋ ተመራጭ ከንቲባ ለመሆን ጫፍ ላይ ደርሰው ነበር። አልሆነም። የቀድሞው አስተዳደር ምክንያት ፈልጎ ብዙኃኑን የቅንጅት አመራሮች እስር ቤት አጎረና አምባሳድር ብርሃኑ ደሬሳን በባለአደራነት አስቀመጠላት። ከ1997 ወዲህም የከተማዋ ምክር ቤት ምርጫ ከሌሎቹ ቦታዎች በሁለት ዓመታት የሚዘገይ ሆነ።የአዲስ አበባ ዋጋ-የጠፋው ትውልድ(The missing generation)አዲስ አበባ የ132 ዓመታት ታሪኳን እያቋረጠች እዚህ ስትደርስ ብዙ ተከፍሎባታል። የቅርቡን የ1997 መርጫን ተከትሎ የመጣውን እና በመቶ የሚቆጠሩ ልጆቿን የፈጀባትን እልቂት ትተን ውደኋላ ብንሄድ ብዙ እናገኛለን።ባህሩ ዘውዴ የጠፋው ትውልድ ሲሉ ይገልጹታል። የመጀመሪያው ጠላት እንከት አርጎ የበላው የኢትዮጰያ የተማረ ትውልድ። የካቲት 12 1929 ዓ.ም በሞገስ አስገዶምና አብርሃም ደቦጭ በማርሻል ግራዚያኒ ላይ በገነተ ልኡል ቤተ-መንግሥት የግድያ ሙከራ ተድረገ። ይህን ተከትሎ ጣልያን ከተማዋን የሞት ዝናብ አወረደባት። በተለይም የተማሩና የነቁ ያላቸውን ወጣቶች በባለ ጥቁር ሸሚዝ ፋሽሽት ወታደሮቹ እያደነ አረዳቸው።አንዳንዶችንም በአውሮፕላን እየጫነ ለሌላው መቀጣጫ ይሁኑ በሎ ከሰማይ ቁልቁል ከሰከሳቸው። በሶስት ቀናት ውስጥ ብቻ ወደ 30 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ሳይለዩ ተጨፈጨፉ። ይህም አዲስ አበቤ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ በቻ የከፈለው የመጀመሪያው ትልቁ ዋጋው አድርጎ ታሪክ መዝግቦታል።ሌላኛው ቀይ ሽብር ነው። የኢትዮጵያ ቀይ ሽብር ሲል በሰየመው መጣጥፉ ጆን አቢንክ ከ1969 እስከ 1970 ብቻ አዲስ አበባ እስክ 20 ሺህ የሚደርሱ ልጆቿ በጥይት አልቀዋል። የአዲስ አበባ እናቶች ወደውስጣቸው እያለቀሱ ልጆቻቸውን የቀበሩበት አስከፊ ዘመን።ባለቤት ያጣችው ከተማአዲስ አበባ ማንንም አትገፋም። ዶር ሽመልስ ቦንሳ ለሶስተኛ ዲግሪ ማሟያ አገርን ማዘመን (Urbanizing a nation) በሚል በጻፈው መጽሐፍ ላይ አዲስ አበባ ከምስረታዋ ማግስት አንስቶ ህንዶች አርምኖችና ግሪኮች የንግድ ሱቆቿን እያሞቁ ከብረው ኖረውባታል። አውሮፓውያንም ማምሻ ቤቶቿን፤ ዘመናዊ ምግብና ሆቴል ቤቶቿን በመገንባት ውበትን ሲፈጥሩላት ኖረዋል።ዛሬ አዲስ አበባን የኔ ነች እያለ የሚጎትታት ብዙ ነው። ሲጓተቱ ጨርቋ ቢቀደድ፤ ውበቷ ቢበላሽ ግድ የማይስጣቸው በርክተዋል። ልጆቿ የመጫወቻ ሜዳ፤አዛውንቶቿ ማረፊያ ጥላ የማያገኙባት ሆናለች።ዛሬ አዲስ አበባ በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፋ መንታ መንገድ ላይ ትገኛለች። ብዙ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ትኩሳት የሚከታተሉ ሰዎች አዲስ አበባ በምርጫ ዘጠና ሰባት ከገዢው አስበልጣ ተቃዋሚውን ፓርቲ መምረጧ ብዙ ዋጋ እንዳስከፈላት ይስማሙበታል።የከተማዋን ነዋሪዎች ፍላጎቶች ግምት ውስጥ ያላስገቡ ፖለቲካዊ ግብ የተጫናቸው የአስተዳደር እና የመልሶ ልማት ሥራዎች በመሠራታቸው የከተማዋ ቅርፅ ተቀይሯል። በተለይ በከተማ የነበሩ ነባር ሰፈሮች ፈርሰው ነዋሪዎቿ በከተማዋ ጥጋጥግ መሥፈራቸው ብዙ እንዳጎደላት ብዙዎች ይስማማሉ ።በዚህ ሂደት የከተማው ነዋሪ የኑሮ ደረጃ ወረዶ ነዋሪው በብዙ ችግር ውስጥ አልቀዋል። በከተማዋ ፍልሰት፣ ስራ አጥነት፣ ድህነት፣ የመኖሪያ ቤት፣ የመሰረታዊ ፍላጎቶች፣ የሞራል መዳሸቅ ከተማዋን በመሳሰሉት ችግሮች ውስጥ እንዲዳክር አድርገውታል።በከተማዋ ተወልዶ ያደገውና የምጣኔ ሀብት እና የሰው ኃይል አስተዳደር ባለሙያው ናትናኤል ፈለቀ ከከተማዋች ችግሮች ውስጥ የወጣቱ ሥራ አጥንት ያሳስበዋል። ከቴክኔክ ሙያ እና ከሌሎች የትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ተቀጥረው ወይም በራሳቸው መስራት የሚችሉበት ዕድል ማነስ እጅግ ያሳስበዋል።በሀገረ እንግሊዝ በማንችስተር ከተማ፣ የከተማ ልማት ትምህርቱን በመከታተል ላይ ለሚገኘው ኢዛና ሐዲስ ከሁሉም ችግሮቿ በላይ የነዋሪዎች መኖሪያ ቦታዎች ያሳስበዋል። መሠረታዊ ፍላጎቶች ያልተሟሉባቸው፣ የተፋፈጉ፣ ዝናብ የሚያፈሱ፣ በርካታ ሰው የሚኖርባቸው፣ መጸዳጃ ቤቶች የሌላቸው የመኖሪያ ስፍራዎች የአዲስ አበባ እጅግ አንገብጋቢ ችግሮቿ ናቸው።ባለፉት አስር ዓመታት ወደሁለት መቶ ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተገንገብተዋል። ኢዛና “ነዳጅ በሌለበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ ድሃ ሀገር እንዲህ መስራት ለእኔ ይሄ እጅግ ተዓምራዊ ነገር ነው። ይህ የተደረገው ደግሞ ከከተማ ጉዳዮች ቅድሚያ ተሰጥቶት ከፍተኛ በጀት ተመድቦለት ነው።” በማለት የነዋሪውን ችግር ለመፍታት የተደረጉ ሙከራዎችን ያደንቃል። ነገር ግን ይህ ሂደት የነበሩበትን ችግሮች ከመግለጽ አልተቆጠበም። በሁሉም የኢኮኖሚ ደረጃ ላሉ ዜጎች ተደራሽ አለመሆኑ፣ መንግሥት በራሱ የከተማዋን ችግሮች በሙሉ ራሴ ፈታለኹ ማለቱ፣ የቤትን ችግር ብቻ ነጥሎ ለመፍታት መሞከሩ ኢዛና ከሚጠቅሳቸው ችግሮች ውስጥ ግንባር ቀደምቶቹ ናቸው።ነዋሪዎቹ ከሚኖሩበት ስፍራ ወደሌላ ቦታ ሲዘዋወሩ ከማኀበራዊ እና ምጣኔ ሀብት መሠረታቸው ተነቅለው ስለሚሄዱ እንደመፍትሔ የታሰበው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ የብዙዎችን ህይወት አስቸጋሪ አድርጎታል።አዲስ አበባ ዛሬለአዲስ አበባ ህዳር ወር ልደቷ ነው። ከተቆረቆረች መቶ ሠላሳ ሁለት ዓመት ሞላት። ልደቷ ትዝ ያላቸው የማይመስሉት የሀገሪቱ ርዐሰ መንግሥት እና የከተማዋ ምክትል ከንቲባ የድንገቴ ስጦታ አቅርበውላታል። ነዋሪዎቿ በግርታ ባለሙያዎች በጥርጣሪ የሚመለከቱት የቢሊየን ዶላሮች ግንባታ ከተማዋ እምብርት ላይ ሊጀመር ፊሽካ ተነፍቷል።በለገሀር እና አከባቢው እንደሚገነባ የተነገረለት 360 ሺህ ሜትር ስኩዌር ላይ የሚያርፈው እና መሰረቱን አቡዳቢ ባደረገውና ኤግል ሂልስ በተባለው የግል የሪልስቴት አልሚ ድርጅት የሚገነባው ይህ ፕሮጀክት ለመኖሪያ፤ ለንግድ፤ ለመዝናኛና ለሎችም አገልግሎቶች የሚውሉ ተቋማትን እንደሚያካትት ተነግሯል። የለገሃርን የቆየ ታሪካዊና አካባቢያዊ እሴቶች ጠብቆ የነዋሪዎችን ትዝታዎች ለማቆየት በልማት ተነሺ የሚሆኑትን የአካባቢው ነዋሪዎችን መልሶ የሚያሰፍርና ተጠቃሚ የሚያደርግ የተነገረለት ይህ ግንባታ በማኀበረሰቡ ውስጥ የተደባለቀ ስሜትን ፈጥሯል።ሌሎች ተመሳሳይ ግዙፍ ለመኖሪያ እና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ግንባታዎች በከተማዋ ሊከናወኑ በሂደት ላይ መሆናቸውን ሌሎች የዜና ማሰራጫዎች አክለው ተናግረዋል።ከፊሉ የከተማዋ ገጽታ መዘመን እና ለነዋሪውም ሆነ ለሀገሪቱ የሚፈጥረውን ዕድል ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በበጎ ተመልክተውታል። ከተማ ትደግ፣ የነዋሪውም የኑሮ ዘይቤ ይዘምን ከተባለ ሀገሪቱ ካለችበት ድኅነት አንጻር በውጭ መንግሥታት ድጋፍም ቢሆን ግንባታው ማካሄድ እንደኢትዮጵያ ላሉ ድሃ ሀገሮች አማራጭ የላቸውም ብለው ይከራከራሉ።ናትናኤል ፈለቀ መንግሥት እንደታቀደው የዜጎችን ማኀበራዊ መሠረት ሲያናጋ፣ ነዋሪዎቹ ሳይፈናቁሉ እና ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት በመዘርጋት ካከናወነው ለከተማዋ ትልቅ ዕድል ነው በማለት ይናገራል። ነገር ግን የአሁኑን አስተዳደር ጨምሮ በከተማዋ የነበሩት ኃላፊዎች ከፍተኛ ነገሮች በባለሙያ የመፈጸም ችግር እንዳለበቸው እና በዚህ ዕቅድ ላይ ይህ ድክመት ጥላ እንዳያጠላበት ስጋቱን ይገልጻል። “በሀገር ውስጥ በቂ ሊባል የሚችሉ የአስተዳደር እና የቁጥጥሩን ሥራዎችን ማከናወን የሚችሉ ባለሙያዎች አሉ። እነርሱ ሥራውን እንዲመሩት ሊደረግ ይገባዋል።” በማለት ይመክራል። በናትናኤል ፈለቀ ግምገማ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ ባለሙያዎችን ለማሰራት እንደማይቸግራቸው ተስፋ አድርጓል።ይህ ለ25, 000 ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር የታመነበት ሰፊ የከተማ ክፍል የሚሸፍን ግንባታ ነቃፊዎች አላጣም። ግንባታው የሚካሄደው በከተማዋ መሪ ፕላን ለአዲስ አበባ ማዕከላዊ ፓርክ (City Center Park) ተብሎ የታሰበበት ስፍራ ላይ እንዳሳሰበው በሊንክድኢን ገጹ ያሰፈረው የከተማ ልማት ዕቅድ ባለሙያ የሆነው ታምራት እሸቱ ነው። እንደ ታምራት መሪ ፕላኑን የሚቀይሩ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ሲመጡ ጥቅም እና ጉዳቱ በመመዘን ማስተካከል ያልቻሉት የከተማዋ ፕላን ኮሚሽን እና ሌሎች የሚመለከታቸዉ አካላት መተቸት ይኖርባቸዋል::“መሪ ፕላን ማለት ህግ ማለት ነዉ። የተለያዩ የመንግስት አካላት እንዲያስፈጽሙት ግደታ አለባቸዉ ከፍተኛ የመንግስት አካለት ሲያከብሩት ሲያስፈፅሙት አርአያ ስለሚሆኑ በዝቅተኛ ኢኮኖሚ ደረጃ የሚገኘዉም የህብረተሰብ ክፍል ሊያስፈፅመዉ ይችላል::”ኢዛና ሐዲስ በበኩሉ ስልጣኔን ከብዙ ፎቆች እና ተደራራቢ መንገዶች ጋር የማገናኘት ችግር አለብን በማለት ግዙፍ ግንባታዎች መሠረታዊ የንድፈ ሀሳብ ግድፈት እንዳለባቸው ያስረዳል። “ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች የብልጽግና ምልክት ናቸው ወይ? ሌሎች ችግሮቻችንን እየሸፈኑብን አይደሉም ወይ” በማለት ይጠይቃል።በሁለተኛነት ለከተማ ልማት ጥናት ተማሪ ለሆነው ኢዛና ለገሃር አካባቢ የሚገነባውን የተቀናጀ የማህበረሰብ ልማት አምባ ፕሮጀክት ላይ ጥርጣሬውን እንዲያሳድር የሚያደርገው ምክንያት የውጭ ሐገር ባለሀብቶች በቤቶች ልማት እንዳይሳተፉ የተከለከለበት ሕግ መጣሱ ነው።ይህ አዋጭ የሆነ እና ብዙም የዕውቀት ሽግግር የማይደረግበት የንግድ ዘርፍ ተለይቶ በሀገር ውስጥ ዜጎች ብቻ እንዲያዝ የተደረገበት ሕጋዊ ምክንያት በሕግ ሳይሻሻል እንዲህ ማድረጉ ተገቢ መስሎ አልታየውም።ሌላው ኢዛና የሚያነሳው የወቅታዊነት ጥያቄ ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ከተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ የያገኘችውን የሁለት ቢሊየን ብር የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት በቤቶች ልማት ላይ መዋል ቀደሚ አጀንዳ መሆን አልነበረበትም ባይ ነው።የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ይህንን ድጋፍ በፋብሪካዎች ወይም የኢንዱስተሪ ፓርክ እንዲሆን ቢያደርጉ የተሻለ የስራ ዕድል እና የእውቀት ሽግግር ስለሚፈጥር የተሻለ ነበር በማለት ይከራከራል። በዚህ ፕሮጀክት ላይ የተጠቀሰው የስራ ዕድል ጊዚያዊ ይሁን ቋሚ መሆኑን ያልታወቀ የሚያምታታ ነው። “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእንግዲህ የመገበያያ ማዕከላት ፍለጋ(shopping malls) ወደ ዱባይ መሄድ ላይጠበቅብን ይችላል ብለው ነበር። እሺ የገበያ ማዕከላቱን ሰራናቸው ምን አይነት ምርት ነው የምንሸጥባቸው ከቻይና ወይስ ከባንግላዴሽ የገዛነውን የውጭ ምርት?” በማለት ይጠይቃል።ባለሙያዎቹ የዕቅዱ ድንገቴ መሆን እና በንድፍ ሂደቱ የኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ተሳትፎን የሚያሳይ መረጃ አለመኖር የከተማውን ቅርጽ የሚቀይሩ ፕሮጀክቶች የከተማውን ነዋሪ እጣ ፈንታ አሳሳቢ ያደርገዋል።አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው ሰዎች ወቅቱ ሙሉ በሙሉ ተስፋ የሚያስቆርጥ እንዳልሆነ ይናገራሉ። በተለይ በሀገሪቱ ከሚካሄደው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ጅማሮ ጋር በተያያዘ የፌደራል መንግሥትም ሆነ የከተማው አስተዳደር በሰለጠነ መልኩ ለሚደረጉ ማኀበረሰባዊ እንቅስቃሴዎች ጆሮ ዳባ የማለት ዝንባሌ እንደማይኖራቸው ይናገራሉ። የነዋሪነት ጥያቄዎች በተደራጀ መልኩ ማቅረብ የለገሃሩንም ሆነ ሌሎች ሥራዎች የነዋሪውን ጥቅም ታሳቢ በማድረግ እንዲከናወኑ ያግዛል በማለት ይመክራሉ። ከተሞች የሰለጠነ የነዋሪነት የመብት ጥያቄዎች ማዕከልነታቸውን እንደገና ማድስ እንደሚገባቸው ያስምሩበታል።