ኅዳር 29 ፣ 2011

Disruption/አንጓላይ

ኑሮማኪያቶ

እ.አ.አ የ1990ዎቹ መጨረሻና የ2000ዎቹ መጀመሪያ እንደ ስማርት ስልኮች፣ ፌስቡክ፣ የኮምፒዩተርና የስልክ መተግበሪያዎች (applications) ያሉ…

Disruption/አንጓላይ
እ.አ.አ የ1990ዎቹ መጨረሻና የ2000ዎቹ መጀመሪያ እንደ ስማርት ስልኮች፣ ፌስቡክ፣ የኮምፒዩተርና የስልክ መተግበሪያዎች (applications) ያሉ ኑሯችንን የለዋወጡ የአእምሮ ውጤቶች ለዓለም የተዋወቁባቸው ዓመታት ነበሩ። እነዚህ ፈጠራዎች ጥንስሳቸው በመኖሪያ ቤት፣ መኪና ማቆምያ (garages) እና በጓሮዎች የተጀመሩ የታዳጊ ወጣቶች የፈጠራ ጥረት ፍሬዎች፣ ገበያውን ሰብረው በመግባት የአሜሪካንንና ብሎም የዓለምን ቀልብና ኪስ የተቆጣጠሩባቸውም ዓመታት ነበሩ።በጊዜው ወጣቶቹ ወርሰው ሳይኾን ለፍተው ያቋቋሟቸው አዳዲስ ድርጅቶች አይነቃነቁም የተባሉትን ታላላቅ ግን ሽማግሌ ኩባንያዎችና ባለሀብቶችን እንዳልነበሩ አደረጓቸው። ገና በሃያዎቹ እና በሠላሳዎቹ ዕድሜ ውስጥ የነበሩ ወጣቶች የቀድሞውን የንግድ ሥርዓትና ልማድ አነቃንቀው ባለብዙ ሚሊዮን (ኋላ ቢሊየን) ዶላሮች ባለሀብት የሆኑበትን ክስተት፣ እንዲሁም ያመጡትን ማንም ያላለመውን ለውጥና ስኬት «ዲስረፕሽን» (disruption) ይሉታል። መንጓለል የ‹ዲስረፕሽን› ትርጉሙ ባይኾንም ውጤቱ ነውና ለዚህ ጽሑፍይመጥናል። የቃሉ ቀጥታ ትርጉም መተራመስ፣ መዛባት፣ መበጥበጥ፣ ቢኾንም አዳዲሶቹ ፈጠራዎችና ንግዶች ለበጎም ቢኾን ያደረጉት ያንኑ በመኾኑ ቃሉን ለመልካም ገለጻ ጥቅም ላይ አውለውታል።ይህ እንደ በጎ ክስተት የሚቆጠረው፣ ነባሩ የተበጠበጠበት ሂደት ባይኖር ዓለምን ወደ አንድ መንደርነት የቀየረው የንግድ፣ የኢኮኖሚ፣ የተግባቦት ምትሃታዊ መቀራረብ አይኖርም ነበር። ጉግል፣ ኔትፍሊክስ፣ ኡበር፣ ዩትዩብ ወ.ዘ.ተ... የ‹ዲስረፕሽን› ትልልቅ ተምሳሌቶች ናቸው። ሐሳቡን ቀድሞ ከነበረው ትርጓሜ በማውጣት እንደ አገባቡ (የሚባልበት አውድ ግልጽ ካልሆነ አሉታዊ ስለሚሆን) የፖለቲካ ሁኔታ መለዋወጥ (political disruption)፣ የኢኮኖሚ ሁኔታ መለዋወጥ (economic disruption)፣ የማኅበራዊ ሁኔታ መለዋወጥ (social disruption) እያሉ ይጠቀሙበታል። ዛሬ መውጣትና መውረድ የሌለበት ዘገምተኛ ዘርፍ ሲኖር «መተራመስ ያስፈልገዋል» (It needs disruption) ማለት እንደ በጎ ምኞት እንጂ እንደ ብጥብጥ ጥሪ አይቆጠርም። በተለይ በንግድ ፈጠራው ዓለም እንደዚህ ያሉ ልማድን የሚገለባብጡ ለውጦችን የሚያመጡ ትንታጎችን «ዲስረፕተርስ» (በጥባጮች) የሚል እንደ ማዕረግ የሚቆጠር ስም ይሰጧቸዋል።የኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ፖለቲካ «ዲስረፕተር» ቢባሉ ማጋነን አይኾንም። የእርሳቸውን መምጣት ተከትሎ የተወሰዱ እርምጃዎችንና፣ የመንግሥት ዘይቤ መሠረታዊ ለውጦችን መዘርዘር ከመደጋገሙ የተነሳ የነተበ ወሬ ሆኗል። ገና ባያቆምም የሆነውና ያየነው ብቻ ዐቢይን ‹ዲስረፕተር› ለማለት ይበቃል። የነበረው ሲበጠበጥ፣ የቀድሞ ኢ-ርትዓዊ የንግድ መረቦች እየተበጣጠሱ ነው፤ የቀድሞ የፖሊስ ያዥና አስያዥ እየተለዋወጡ ነው፤ የቀድሞ የጉምሩክ «ሳይፈትሽ አሳልፈው» እየሰለለ ነው፤ የቀድሞ የደጋፊ ጋዜጠኞች ምንጮች እየነጠፉ ነው……ግን ግን፤ እነዚያ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተን ሳለ ጓደኞቻችን ከመንግሥት ወታደሮችና ፖሊሶች በተተኮሰባቸው ጥይቶች ጎዳና ላይ ደማቸው ፈስሶ፣ እያለቀስን ወደቤት ስንመለስ በቴሌቭዥን ቀርበው «ባንክ ሊዘርፉ ሲሉ በፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት…» እያሉ ዜና ሲያነቡ የነበሩ «አንባቢዎች» አሁንም ሌላ የአድር ባይነት ዜና እያነበቡ ሊቀጥሉ ነው? ሀገር ታምሳ፣ ሕዝብ እያለቀ፣ በየጎጆው ደም እንባ እየተነባ «ሰላምና መረጋጋት ሰፍኗል» እያሉ የነገሩን «ጋዜጠኞች» አሁንም ባርኔጣ ቀይረው «መደመር፣ የለውጡ እንቅፋቶች…» እያሉን ሊቀጥሉ ነውን? ጋዜጠኝነትን ያዋረዱ፣ በሕዝብ ቁስል ላይ እንጨት የሰደዱ፣ ለትኩስ ሐዘንና ለቅሶ እንኳን የማይራሩ፣ በየምሽቱ ቀርበው ዓይኖቻችንን እያዩ በሚለፍፏቸው ውሸቶች ከገዳዮቻችን በላይ ያሰቃዩን «ጋዜጠኞች»ን አንጓላይ (ዲስረፕሽን) ዞር ሳያደርጋቸው ሊያልፍ ነውን?እነዚያ መለዮ ለብሰው በጉልበተኞች ትዕዛዝ ያዙ ሲባሉ የሚይዙ፣ ፍቱ ሲባሉ የሚፈቱ፣ የሕዝብ ጠላት የነበሩ «ሰላም አስከባሪ» ፖሊሶች ስያሜና ቦታቸውን እንደያዙ ሊቀጥሉ ነውን? ወንጀለኛ የሚወዳቸው፣ ንጹሕ የሚፈራቸው፣ ‹ዩኒፎርማቸው› የኢ-ፍትሐዊነትና የግፍ ማስታወሻ እስኪመስለን ድረስ እኛን (ሕዝብን) ከድተው ከአምባገነኖች ጋር የወገኑት ፖሊሶች እንደዘበት ሊቀጥሉ ነውን? አሁን እንኳ፣ ዛሬም እንኳ «የለውጡ እንቅፋቶች» ያሏቸውን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እያሰሩ፣ እያጋዙ፣ «ሥልጠና እየሰጡ» ለመቀጠል እንደማያቅማሙ ያረጋገጡልን ፖሊሶች «ሰላም እያስከበሩ» ሊዘልቁ ነውን?እነዚህ ቃለ መሀላ ፈጽመው፣ ጥቁር ካባ ለብሰው በዳኝነት ከተሰየሙ በኋላ፣ በመርማሪዎች ሰውነታቸው በድብደባ በተበላሹ፣ በተገረፉ፣ በተደፈሩ ኢትዮጵያውያን ላይ እያፌዙ፣ የታዘዙትን ቀጠሮና ፍርድ ይሰጡባቸው የነበሩ ኅሊና ቢሶች አሁንም ያን ጥቁር ካባ እንደለበሱ «ክቡር» ተብለው እየተጠሩ፣ ዳኛ እንደሆኑ ሊቀጥሉ ነው? ፍርድ ቤትን የግፍ አውደ ርእይ፣ ፍትሕን መሳለቂያ ያደረጉት ዳኞች አሁንም መዶሻቸውን እንደያዙ ሊሰየሙ ነውን? በንጹሐን ዜጎች ላይ ፈርደው የሰው ሕይወትን ያበላሹ፣ ሀገር ያሽመደመዱ፣ ቤተሰብ የበተኑ እነዚያ ቃለ መሀላቸውን ቅርጥፍ አድርገው የበሉ ዳኞች አሁንም ችሎት ላይ እያየናቸው ሕይወት ሊቀጥል ነውን?ሲሆን ሲሆን ማንም ጣቱን ሳይጠቁምባቸው ኅሊናቸው ወቅሷቸው ስለሰሯቸው ወንጀሎች፣ ስለፈጸሟቸው በደሎች ቀድመው ተናዘው «እኔ እዚህ ቦታ ላይ መቀጠል አልችልም» ሊሉ ይገባ ነበር። ያማ ለኛም ለነሱም ወጌሻ ሆኖ ያሸን ነበር። እስካሁን አንድም በአደባባይ ወጥቶ እንደዛ ያለን አላየንም፣ አልሰማንም። ግን ዝምታቸውና፣ ምንም እንዳልተፈጠረ መቀጠላቸው አያስደንቅም። እንዲያውም የይቅርታውን መንገድ ቢከተሉ ይደንቀናል። ቀድሞውኑ ማንጓለል (ዲስረፕሽን) የሚያስፈልገውስ ለዚሁ አይደል?ከቀበሌ እስከ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት፣ ከአስር አለቃ እስከ ጄነራል፤ ከግፍ ሥርዓት ጋር ተነካክተው የመንግሥትን በትር በመጠቀም በሕዝብና በሀገር ላይ በደል ያደረሱ እንቁጠር ቢባል ብዛታቸው አንድ ትልቅ ክልል ይመሠርታል (ምናልባት አንቀፅ 39ኝን ጠቅሰው እንገንጠል ሊሉ ይችላሉ)። ሁሉም እንዳደረሰው በደልና እንዳለው መረጃ መጠን ‹ዞር ቢልልን› የሚባለው ሚኒስትር፣ ኃላፊ፣ ባለስልጣን የትየለሌ ነው። አንዳንድ ባለስልጣኖችን ግን፣ አንዳንድ መስኮች (እንደ ዳኝነት) ላይ ያሉትን ግን፣ አንዳንድ በዳዮችን ግን ምስላቸውን ማየትና ድምጻቸውን መስማትም ያንገፈግፋል። የነበረው እንዳልነበር መለዋወጡ እነዚህን እያየ እንዳላየ ሊያልፍ ከኾነም ይጎዳል።ተበዳይ ይቅርታ አድርጎ እንዳይተዋቸው «ይቅርታ ማሩኝ» እንኳን አላሉትም። ከሶ ሕግ ፊት እንዳያቆማቸው ዳኞቹ እነሱው ናቸው። እርግፍ አድርጎ ትቶ እንዳይረሳቸው አሁንም በቴሌቭዥኑ፣ በጋዜጣው፣ በችሎቱ፣ በጣቢያው፣ በሰፈሩ፣ በሥራ ቦታው ሲወጣ ሲገባ ያያቸዋል። አንጓላይ ደ’ሞ ግማሹን ግፈኛ ንዶ፣ ግማሹን ግፈኛ ወዶ አያምርበትም። ፍትሕ አንዱን በዳይ ገላምጦ፣ አንዱን በዳይ ጠቅሶ ሲያልፍ ግማሽ ሙሉ ሳይሆን ግብዝ ይሆናል። ‹ዲስረፕሽን› ከወላወለ፣ ከመራረጠ፣ ከጠቃቀሰ ምኑን አተራመሰው፣ ምኑንስ አንጓለለው?  

አስተያየት