ኅዳር 15 ፣ 2011

ከተሞች፣ ከተሜነት እና ሀገር ግንባታ (Urbans, Urbanization and Nation Building)

ኑሮ

ደራሲ አዳም ረታ እግዜር ባንዴ እንደማይሰራቸው የተናገራለቸውን ከተሞችን መኮንን ዛጋ በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ያላቸውን ሚና በዝርዝር…

ደራሲ አዳም ረታ እግዜር ባንዴ እንደማይሰራቸው የተናገራለቸውን ከተሞችን መኮንን ዛጋ በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ያላቸውን ሚና በዝርዝር ያስቃኘናል፡፡የመነሻ ሃሳቦች መዘርዝር- ከተማና ከተሜነት ስንል፡-የዛሬ ዓመት አካባቢ ጥር ወር ከመገናኛ ወደ የካ አባዶ በሚሄደዉ ሸገር ባስ ዉስጥ ከረጅም ጊዜ በኋላ መምህር አብዲሳን አገኘሁት። ታች ክፍል እያለን ከልጆቹ ጋር አብረን ተምረናል። ከተማ ይደናገራቸዋል ብሎ እንዳላምዳቸዉ አስቦ ነበር ከኔ ጋር ያወዳጃቸዉ። አሁን በልደታ መልሶ ልማት ተነስቶ የካ አባዶ ኮንዶሚነየም ዕጣ ደርሶት ገብቷል። ታሪኩን ለወላጆቼ ሲያጫዉት እንደተረዳሁት አብዲሳ የመምህራን ስልጠና መርሐግብር ትምህርቱን በ1970 ዓ.ም ከመምህራን ማሰልጠኛ እንዳጠናቀቀ የተመደበዉ በቀድሞዉ አጠራር ሲዳሞ ክፍለ ሀገር ይርጋ ጨፌ አዉራጃ ገርባ ከተማ (በአሁኑ ደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን) ገርባ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በህብረተሰብ ሳይንስ መምህርነት ነበር።አብዲሳ በማስተማር ላይ እያለ የጉጂ ተወላጅ ከሆነዉ አባቷና የአባቷ ሁለተኛ ሚስት ከሆነችዉ የጌዴኦ ተወላጅ ከሆነችዉ እናቷ ፋንታዬ ፈረንጄ ጋር በገርባ ከተማ የምትኖረዉን ወርቀቴን በሀገር ባህል አግብቶ መኖር ጀመረ። አብዲሳ አራት አመት ካስተማረ በኋላ በ1974 ዝዉዉር ጠይቆ ሚስቱን ወርቀቴን በመያዝ ህዝብ በብዛት ወደ ሚኖርባት ወደ ሐዋሳ ከተማ ታቦር የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ከዚያም ከሦስት ዓመት በኋላ አዲስ አበባ ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ማረፊያቸዉን አደረጉ። ወርቀቴና ባሏ አብዲሳ ባሁኑ ጊዜ ስድስት ልጆቻቸዉን ለወግ ማዕረግ ያደረሱ ሲሆን ለሥራቸው እንዲቀርባቸዉና ገንዘብን ለመቆጠብ እንዲመቻቸዉ በከተማው አነስተኛ ኪራይ በሚገኝበት አብነት ሰፈር በአንዱ የቀበሌ ቤት ጊቢ ውስጥ ተከራይተዉ ከተለያየ የአገራችን አካባቢ ከመጡ ከአስር በላይ ጎረቤቶቻቸዉ በመኖር ረጅም ጊዜ አሳልፈዋል። በየዕለቱ የኑሮ ትግል ቢያማርራቸውም በከተማ ውስጥ መኖራቸዉ ወደ መልካም አጋጣሚዎች እንደቀረቡ የሚሰማቸዉ ሲሆን ለስድስት ልጆቻቸው የወደፊት የዕድገት ተስፋ ሆኗቸዋል።ሁሌም በከተማዉ መኖራቸዉን እንደመልካም አጋጣሚ ይቆጥሩታል። ሁለቱም ማንነታቸዉን ረስተዉ በሚኖሩበት ማኅበረሰብ መስተጋብር ተዉጠዋል። ይህ አይነቱ ሁነት የብዙዎቻችን ታሪክ አንድ አካል ነዉ። ወርቀቴ ገጠር ከሚኖሩት ቤተሰቦችዋ በላቀ ጠዋት ገበያ የወጣችዉ የጎረቤትዋ ትርሀስ ደኀንነትና በሠላም ወጥቶ መግባት ያሳስባታል። ወርቀቴ እና ባሏ በአገራችን ልዩ ልዩ ከተሞችና በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ የከተማ ነዋሪዎች ውስጥ ከሚመደቡ ከ1.7 ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ዉስጥ ናቸው። አብዛኛዎቹ እነዚህን መሰል ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው የተሻለ ሥራ እና የኑሮ መሠረቶች ፍለጋ ወደ ከተሞች ፈልሰዋል።ከተሜነት የብሔር ማንነትን ሳይሆን የሥራ፣ የአስተሳሰብና የችግር ተካፋይነት መስተጋብርን ግቡ ያደርጋል። ይሁን እንጂ የከተማ ድንበር በፍጥነት እየተስፋፋ በሄደ መጠን ነዋሪዎች ለአዳዲስ ማንነቶች ተጋላጭ በመሆን የአስተሳሰብ አድማሳቸዉን በማስፋት ዘልቀዋል። ለወርቀቴ፣ አብዲሳና እና በቢሊዮኖች ለሚቆጠሩ የከተማ ነዋሪዎች ይህ ማለት የከተሜነት አካታች ባህሪን ተላብሰዉ የኑሮ ዘዬዉን ባወቁት ልክ የኑሮ መሰረታቸዉን የሚደግፉበት መሣሪያ ነዉ።እግዜር ባንዴ አልሰራትም!አዳም ረታ በስንብት ቀለማት መጽሐፉ መግቢያ ላይ ማንኛዉም ከተማ የሠዉ ልጅ የሥራ ዉጤት ናት (እንስት ብትሆን)። ፈጣሪ እንደ ተራራ ፣ እንደ ወንዝ፣ እንደ ሎሚና እንደ ሰላጣ፣ እንደ እግሮቻችን፣ እንደ ጡት ባንዴ አልሰራትም ይላል።ከተማ የሠዉ ልጅ በዘመናት ሂደት የሚያበጃት የክሱት ግብሩ ዉጤት ብቻ ሳትሆን የድብቅ ነፍሱ የሃርነት ንቅናቄ ዓርማም ናት። የሕልሙ ማኅተም መድመቂያ ጌጡ እንደማለት ነዉ። ከተሜነት የድርጊትና የአስተሳሰብ ብልጽግና ሽግግር የሚለካበት የሰዉ ልጅ የድርጊት አሻራ ነዉ።ከተሜነት ከገጠር ወደ ከተማ ቀመስ ቦታዎች ነዋሪነት በሚደረግ ፍልሰት የሚፈጠር የሕዝብ ቁጥር መለወጥ ወይም በከተሞች አካባቢ የሚኖሩና የተወለዱ ሰዎች ቁጥር ቀስ በቀስ የመጨመር ሂደት የሚከሰት አዲስ የማንነት ለዉጥ ሲሆን ከዚህ የዲሞግራፊክ ስሪት ጋር ተያይዞ እያንዳንዱ የከተማዉ ነዋሪ ማኅበረሰብ ከዚህ ለውጥ ጋር የሚጣጣምበትን የሃሳብ ዘይቤ የሚያበጅበት መራሄ ፍኖት ነው።ከተሜነት የራሱ ቀለምከተሜነት የራሱ ቀለም አለዉ። የተለያየ ማኅበረሰባዊ ማንነት ቀልጦ እንደአዲስ የሚሰራበት የማንነት ማቅለጫ ገንቦ-Melting Pot ነዉ። በመሆኑም ከተሜነት የሰዉ ልጅ የማደግ፣ የመረዳዳት፣ የመወያየት ሰብዓዊ ግብር መገለጫ ነዉ ማለት ይቻላል። በአብዛኛው ከተሞች የሚመሰረቱትና የሚያድጉት የተለያየ ማንነት ያላቸዉ እጅግ በርካታ ሰዎች ለመኖር በሚያደርጉት ትግል በሚፈጠር እንቅስቃሴ እና በአማካይ ዉስን ቦታዎች ላይ ለኑሮ መደጎሚያነት በመሥራታቸው ነዉ። ከተማ ከሌላዉ የአገር አካባቢ የሚለይበት አንዱ መገለጫዉ ደግሞ አካታችነቱ ነው።በገጠራማ አካባቢዎች ማኅበራዊ ትስስር ባብዛኛዉ የደም (የትዉልድ)፣ የዘር ሐረግ መስመርን ሲከተል በከተሞች ግን የሰዎች ርስ-በርስ መስተጋብር የአስተሳሰብ፣ የመደብ፣ የኑሮ ደረጃ ተመሳስሎሽ ዉጤት ነዉ። የከተማ ሥልጣኔ የሰው ልጅ ሁሉ ድምር ሥልጣኔ መገለጫ ነው። በከተማና ከተሜነት የእገሌ ወገን የሚባል በጠባብ ማንነት ላይ የተለጠፈ የሥልጣኔ ማማ የለም። የከተማ የሥልጣኔ መርሕ ኑሮን ለማሸነፍ ለሚሠራ ሁሉ በሩን ክፍት አድርጎ መጪን መቀበል እንዲያም ሲል ኑሮን መቋቋመ ያቃተዉ መልሶ ሂያጅን መሸኘት ነው። ሆኖም ከተማ ሂያጅን አያበረታታም የኗሪዉ ትብብር፣ የሽሮ በርበሬ ብድር ተቸግሮ መኖርን መልመድ ያስችላል። ከተማ በሰው ልጅ የዕውቀትና የላብ ጭማቂ እንደምታድግና እንደምትደምቅ ገብቶት ይህንን በትጋት ለመፈጸም የቻለ፣ በዉድድሩ ማዕበል ራስን ለማኖር በሚደረግ ትግል አሸናፊ የሆነ ያ ስኬታማ ሰዉ ከተሜ ይሆናል።ከተሞች ከየአራቱም ማዕዘናት የተሻለ ሕይወት በመሻት፣ ጥበብና ዕውቀት ፍለጋ የመጡ፣ ለንግድና ለጥቅም የተሰባሰቡ፣ በተለያየ ደረጃ ባለ በመንግሥታዊና ኢ-መንግስታዊ መዋቅር ሚና የነበራቸው ዜጎች የፈጠሯቸዉ የጋራ ሥልጣኔ ዕሴቶች ማሳያ ናቸው። ከተማነት ዘር የለውም። የከተማ ሰዉ ገጠር ካለ ዘመዱ ይልቅ የከተማው ልጅ ጎረቤቱ ወገኑ ነው።የከተማና ከተሜነት ወግ ሲነሳ የከተማ ልማትና ከተሜነት የተሰኙት ሁለት ወሳኝ ጽንሰ-ሐሳቦች አንዳንድ ጊዜ በተለዋዋጭነት ጥቅም ላይ ስለሚዉሉ በግልጽ መለየት ይኖርባቸዋል። ከተሜነት ማለት ከገጠር ወደ ከተማ ነዋሪነት በሚደረግ የሕዝብ ፍልሰት የሚከሰት የኗሪ ቁጥር መጨመር፤ በከተሞች አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በመዋለድ የቁጥር ቀስ በቀስ ዕድገት እንዲሁም እያንዳንዱ ህብረተሰብ ከዚህ ለውጥ ጋር ራሱን የሚስማማበትን የሐሳብ መንገድ የሚያመለክት ነው። በሌላ በኩል ከተሜነት ከተሞች የሚመሰረቱበት ሂደትና እጅግ በርካታ ሰዎች በጊዜ ቅብብሎች ለመኖር ሲመርጧቸዉ እና በአማካይ የሚመች ቦታ ሆነው ለመሥራት ሲጠቀሙባቸዉ ይሁነኝ ተብሎ የሚከወን የመለስተኛና ትላልቅ ከተሞች የዘመናት ሥሪት ዉጤት ነዉ።ትላልቅ ከተሞች፣ መለስተኛ ከተማ ቀመስ መኖሪያ አካባቢዎች ሌላው ቀርቶ ትንንሽ መንደሮች እንኳን በአንድ ሌሊት ተሰርተዉ አያድሩም። እነዚህ ከተሞች የሲቪል እና የዲዛይን ምህንድስና ባለሙያዎች፣ የፕሮጀክት አስተዳዳሪዎች፣ አርክቴክቶች፣ የአካባቢ ዕቅድ አውጪዎች እና ቀያሾች ጥንቃቄ የተሞላበት ዕቅድና የተግባር ድምር ውጤቶች ናቸው። እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን መርሆዎችና ተግባራትን በማዋሃድ የሚተገበር ሥርዓት የከተማ ልማት (Urban Development) ተብሎ ይጠራል። የከተማ ልማት ማለት ከተማና የከተሜነት አኗኗር ዘዬን ለመፍጠር የሚያስችል የመኖሪያ ቤቶችና ተያያዥ መሠረት ልማት ግንባታ ማስፋፊያ ስልት ሲሆን ይህም ማለት የመኖሪያ አካባቢዎች የከተማ ልማት ዋነኛ መሠረቶች ናቸው። የከተማ ልማት የሚከናወነዉ ነዋሪ ወደሌለባቸዉ (ሠዎች ወዳልሰፈሩባቸዉ) አካባቢዎች በመስፋፋት እና / ወይም ያረጁ አካባቢዎችን መልሶ በማደስ ነዉ። በመሆኑም የከተማ ልማት ረጅም ጊዜና ከፍተኛ ወጪን የሚፈጅ የግንባታ ሂደት ነዉ። በድርጅቶች፣ በተቋማት እና በግለሰቦች መካከል የተቀናጀ የጋራ ጥረት እንዲሁም ከመንግስታት፣ ትላልቅ ኮርፖሬሽኖች እና ባለሀብቶችና ግለሰቦች በዋናነት የገንዘብ ድጋፍ ይጠይቃል።እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትንበያ ከሆነ በ2050 በማደግ ላይ ካሉ አገራት 64 በመቶ የሚሆኑት እንዲሁም ካደጉት ሀገራት ደግሞ 86 በመቶዎቹ በከተሞች እንደሚሸፈኑ ይገመታል። ይህ ማለት እ.ኤ.አ በ2050 እስከ 3 ቢሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ የከተማ ነዋሪ ይሆናል ማለት ነዉ። ይህም በአብዛኛው በአፍሪካ እና በእስያ አህጉራት ይከሰታል ተብሎ የሚገመት ነዉ። በተለይም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቅርቡ ከተሞችን አስመልክቶ ባዘጋጀዉ ተመሳሳይ ሪፖርት ከ2017 እስከ 2030 ባለው ጊዜ ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚፈጠረዉ የህዝብ ቁጥር መጨመር በከተሞች ዉስጥ የሚዋጥ ሲሆን ወደ 1.1 ቢሊዮን የሚደርሱ አዳዲስ የከተማ ነዋሪዎች በሚቀጥሉት 13 ዓመታት ውስጥ እንደሚጨመሩ አስነብቧል። እነዚህ ተስፋፊ ከተሞችና ከተሜነት ታዲያ የጋራ ርዕዮትን በመፍጠር ለአገር ግንባታ ጉልህ ድርሻ እንደሚጫወቱ ሳይታለም የተፈታ ነዉ።አገር ግንባታ ስንልበዘመናዊው ማኅበረሰብ ውስጥ ሀገራት መሠረታዊ የፖለቲካ መዋቅር አካል ናቸው። ወደ ሰዉ ልጅ የኋልዮሽ ታሪክ ስንመለስ ዓለም በግዛተ-አጼዎች እና በጎሳ ስርወ-መንግሥታት የተከፋፈለች እንደነበር እናያለን። ይሁን እንጂ በዘመናችን እነዚህ አጼያዊ መዋቅሮች በሉአላዊ ሀገራት ወይም ዲሞክራሲያዊ መራሄ መንግስታት እንደ አንድ የፖለቲካ አሃድ ተደርገው መዋቀር ጀመሩ። አገራችን ኢትዮጵያም የዘመናዊው ዓለም አካል እንደመሆኗ መጠን ዜጎቿ ስለሀገረ-ኢትዮጵያ ግንባታና ዉቅር አብዝተን መጨነቅ አለብን። ሆኖም ግን አገራት በድንገተኛ ታሪካዊ ሁኔታ ሊከሰቱ እንደማይችሉ ይታወቃል። ይልቁንም ሃገር-ግንባታ የዜጎች የራዕይና የድርጊት መስተጋብር ድምር ዉጤቶች ናቸው።በቀደመዉ ወቅት ሃገራት የተመሰረቱት “በደምና በብረት” ጫና እንደነበር በርካታ የዓለም የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። በዚህ ዘመን በመላው ዓለም አለመግባባትን በመፍታት፣ በባለብዙ ግንኙነት አካላት ድጋፍ፣ በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እና በነፃ ምርጫዎች በኩል በመጠቀም አገርን መገንባት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ይሁን እንጂ ይህ የሠለጠነና የተራቀቀ የአገር ግንባታ አሠራር እምብዛም ስኬቶች ሲያጎናጽፍ አይታይም። ዉጤታማ የሀገር ግንባታ ተግባር ለማከናወን ወታደራዊ ግፊትን እንዳስፈላጊነቱ መጠቀም የተገባ ሲሆን ዲሞክራሲያዊ ስልት ግን ሁሌም ብቸኛና አዋጭ መንገድ አይደለም። ምክንያቱም አገር-ግንባታ ማለት ለተለያዩ አካላት የተለያዩ ትርጉም አለዉ። እንደዘመናዊ የአገር ግንባታ ጽንሰ-ሀሳቦች ትንታኔ ከሆነ ዋና ዋናዎቹ የሃገር ግንባታ መርሃግብሮች በሀገሪቱ ውስጥ አብዛኛዉን ማኅበረሰብ የሚያካትት የጋራ ማንነት፣ የተቀናጀ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ ሁሉን አቀፍ የሲቪል ማህበረሰብ አቅምን ማጎለበት፣ ባህላዊና ዘመናዊ የግጭት አፈታት ስልቶች መንደፍና መተግበር እንዲሁም የጋራ የኢኮኖሚ ዕቅዶችን በመንደፍ የአገራት ነባራዊ የማስተዳደር አቋምን በመደገፍ የአብሮነት መሠረት ማኖር ነዉ።በሌላ በኩል አገር ግንባታ አጠቃላይ ማኅበረሰቡ ወይም የሆነ አንድ አካል እነጻዉን በዘመናት ሂደት ሆን ብሎ የሚያካሄደው ነዉ ተብሎ ይታሰብ እንጂ የአገር ግንባታ ንድፈ ሐሳቦችን በዕድገት ዝግመተ ለዉጥ ሂደት ውስጥ በመተንተን እና በዘርፉ በተካተቱ ሌሎች ጽንሰ-ሀሳቦች ላይ በመመርኮዝ መመርመር አስፈላጊ ነው። በርካታ ሰዎች አገር መገንባት ቅጽበታዊ ግኝት ሳይሆን አዝጋሚ የለውጥ ሂደት ነው ብለው ያምናሉ፤ ይህም ረጅም ጊዜ የሚወስድ እና እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ ከውጭ መጀመር የማይችል ማህበራዊ ሂደት ነው። የጣሊያን የከተማ ክፍለ-ግዛቶች ወደ አንድ ሀገር፣ የጀርመን ብትንትን-ግዛቶች ወደ ዞልቮሪን የጋራ ንግድ ማህበር ከዚያም በኋላ ወደ አንድ አገር፣ በፈረንሣይ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ቋንቋዎች እና ባህላዊ ቡድኖች ወደ አንድ ፈረንሣይቷ አገር፣ ከየጦር አበጋዞች የአውራጃ ሰፈሮች የቻይና ግንባታ፣ እነዚህ ሁሉ የአገር ግንባታ ትርክቶች የተፈጠሩት በፖለቲካ አመራር ላይ ብቻ ተመስርተዉ ሳይሆን በቴክኖሎጂ እና በኢኮኖሚያዊ ሂደት (የግብርና እና የኢንዱስትሪ አብዮት) ለውጦች፣ እንዲሁም የርስ-በርስ ግንኙነቶች፣ ባህል እና የሲቪል ማህበራት እና በሌሎች ብዙ ምክንያቶች ነዉ።በዚህም ሀገር ግንባታ(Nation-building) ማለት ሆን ተብሎና ታቅዶበት በአገራት አስተዳደራዊ መዋቅር ስሪት ማዕቀፍ ዉስጥ በሚተገበር ተከታታይ ሥራ የሚገኝ ዉጤት እንጂ የዕድል ክስተት ውጤት አይደለም። ሀገር ግንባታ ዘወትር በተከታታይነት የሚከወን የማኅበረሰብ ግንባታ ትግበራ ሲሆን ሁልጊዜ የሚዳብር እና አፈጻጸሙም በጥናት ላይ የተመሰረተ እና ቀጣይነት ያለው መሆን አለበት። ሀገር ግንባታ ፈጽሞ አይቆምም እናም እውነተኛ ሀገር-ገንቢ አያርፍም ምክንያቱም በርካቶቹ የዓለም አገራት ሀገራት ሁልጊዜ በአዳዲስ ፈተናዎች የመጠመድና ተግዳሮቶችን በመፍታት ሂደት ላይ ይገኛሉ።አገር-ግንባታ ብዙ ጠቃሚ ገፅታዎች አሉት። ሁለት ፈርጆች ያሉት ሲሆን በመጀመሪያ ደረጃ በአጠቃላይ ማኅበረሰቡ ተቀባይነት ባላቸው ሕግጋት፣ ደንቦች እና መርሆዎች እንዲሁም የዜጎች የጋራ የአመለካከትና ማንነት ላይ በመመስረት ከግዛት ዳር ድንበር ጋር የተያያዘ አንድ የፖለቲካ ተቋም መገንባት ነው። ሁለተኛው ደግሞ የፖለቲካ ተቋሙን የሚወክሉ ተቋማትን በመገንባት፡- እንደ የመንግስት ቢሮክራሲ፣ ኢኮኖሚ፣ የፍትህ አካላት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሲቪል ሰርቪስ እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የመሳሰሉትን የሚያመለክቱ ተቋማትን መገንባት ነው።ከሁሉ በላይ ግን ሀገር-መገንባት ማለት የዜጎችን የጋራ ዓላማዎች፣ የጋራ ዕጣ ፈንታ ስሜት፣ የጋርዮሽ ኅብረትና የኔነት ስሜት መገንባት ነዉ። ስለሆነም አገር-ግንባታ ስንል የፖለቲካ ተቋሙን (አገር) ባንድ አስተሳስረዉ የሚይዙና ተጨባጭ የአብሮነት ስሜት የሚያጎለብቱ የሚታዩና የማይታዩ የአብሮነት ማሰሪያ ድሮችን መፍተልና መሸመን ነዉ።በዚህ ዓለም አቀፋዊነት በተንሰራፋበት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን የሰዎች ዝዉዉር እንዲሁም የሀሳቦች ቅጽበታዊ እንቅስቃሴ በሚታይበት ክስተት የጋራ ዕጣ ፈንታ የሚጋሩ ፣ የጋራ ማንነት ያላቸዉ በአንድ አገር ዉስጥ የታቀፈ ማኅበረሰብ (One-nation State) መኖር የብልጽግና መገለጫ ከመሆኑም በላይ በራሱ ዘመናዊነት ነዉ። በተጨማሪም አገር መገንባት ማለት በዚህ ዘመናዊ ዓለም እና የቴክኖሎጂ ዕድገት ወቅት የጋራ ማኅበረሰብን ኅልዉና እና አብሮነት የሚደግፉ ተቋማትንና እሴቶችን ማቋቋም ነው።የከተሜነት ስለምን?ቀደም ሲል ጀምሮ በአገራችን ያሉ ከተሞችም እንደ ሌሎቹ የዓለም አገራት ከተሞች በገጠሪቱ የአገራችን ክፍል ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል። እያሳደሩም ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል ገጠር ቀመስ አካባቢ ያሉ ከተሞች በአጎራባች አካባቢያቸዉ ካሉ መንደሮች ውስጥ የሰዎች ስርጭትን እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን በማቃናት ዋነኛ ሚና ይጫወታሉ።በኢትዮጵያ እና በአብዛኛው የአፍሪካ አገሮች ከ1980 ዎቹ እስከ አሁን ድረስ በገጠር እና በከተማ አካባቢ ከተፈጠሩ በጣም አስፈላጊ ግንኙነቶች ዉስጥ ዋነኛዉ ከገጠር አካባቢ ወደ ከተማ በሚደረግ ፍልሰት የተነሳ የህዝብ ብዛትና የከተሜነት አኗኗር ተፅዕኖዎች መፈጠር አንዱ ነዉ።ከተሜነት በተለያየ የጥናት ዘርፎች እንደ ጂኦግራፊ፣ ስነ-ህብረተሰብ፣ ምጣኔ ሃብት እና ህዝባዊ ጤናን ጨምሮ ባሉ ዲሲፕሊኖች ሲታይ የተለየ ማንነት የሚንጸባረቅበት የሰዉ ልጅ የአስተሳሰብ አብሮነት የሚጎላበት ቅይጥ ማንነት ነዉ። ይህ የከተሜነት ክስተት በአንጻራዊነት ዘመናዊነትን የተላበሰ፣ የመሥራት (ኢንዱስትሪስነስ) ባህልን የሚያጎለበት እና ከማህበረሰብ ዕድገት ሂደት ጋር ከሚያያዝ የምክንያታዊነት አስተሳሰብ ጋር የሚቆራኝ ነዉ።ስለሆነም ከተሜነት የራስ ማንነነትን ሳይለቁ የሌላዉን ባህል ወግ ልማድና አስተሳሰብ እየተጋሩ እኩላዊ ህብረት የሚፈጠርበት የአገረ-ግንባታ አንድ አእማድ ነዉ። ለአገረ-ግንባታ ሂደት ዋነኛዉ ግብዓት የጋራ ማንነት አንዱ መሆኑ ግልጽ ነዉ። ስለሆነም ከተሜነት ሃገራዊ ሃብትን ይበልጥ ውጤታማና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም፣ ዘላቂ የመሬትን አጠቃቀም ለመፍጠርና ተፈጥሮአዊ ስነ-ምህዳሮችን ለመጠበቅ እንዲሁም የሀሳብ ብዝሃነትና የማንነት ክብር ለመጠበቅ የሚያስችል “ዘላቂነት ያለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ለውጦች የትስስር ዉጤት ነዉ። በሌላ በኩል ከተሞች ከፍተኛ የማኅበረሰብ አለመረጋጋት ሁኔታ ሲከሰት እንኳ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል፣ ዕድገትን ለማጎልበትና ዘላቂ የሆነ አቅም ለመገንባት የታደሰና ሰፊ የእድገት ምንጮችን ያበረክታሉ።እንደ ዓለም ባንክ ጥናት ከሆነ ከተሞች በሶስት ወሳኝ ገዢ መርሆዎች ለአገር ግንባታ ከፍተኛ ድርሻ አላቸዉ። የማኅበረሰብ ተግባቦት ግንባታ መነሾ፣ የዕድገትና ልማት አንቀሳቃሾች እና የፖለቲካ ለዉጥ ማቆሚያ መልህቆች በመሆን ለህዝብ እና ለአገር ሁለንተናዊ ብልጽግናና ልዕልና ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።የአንድ ከተማ ዋነኛ መገለጫና ሃብት የባህል፣ አኗኗር ተመሳስሎና የጋራ ማንነት አንዱ ነው። ግዙፋዊ ህልዎት ያላቸዉ የማኅበረሰብ የጋራ ማንነት ግንባታዎች እና አዕምሯዊ ውርሶች ለጎብኝዎች ብቻ ሳይሆን ለጋራ አካባቢያዊ ማንነት እና ለፈጠራ ስራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። የከተሜነት ባህል ለሀገር ግንባታ ስትራቴጂያዊ ዘርፍ ነው። ይኽዉም ባህላዊ መሠረት ያላቸው የከተማ ልማቶችና የከተሜነት አስተሳሰቦች እንደ አንድ ዘላቂ የከተማ ልማት አካል ሆነው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አገራዊ የማንነት ችግሮችን በወሳኝነት ለመፍታትና ግጭቶችን ለማብረድ የሚችሉ መንገዶች መሆናቸው በተደጋጋሚ ታይቷል። እንደ አብነት በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት የሚገኙ ማራኪ የታሪክ ማእከላት፣ የባህል ተቋማት፡ ሙዚየሞች፣ ጋለሪዎች፣ ፌስቲቫሎች ወይም ቤተ መዛግብትና ቤተ-መጻህፍት ለየት ላሉ ሐሳቦችና የጋራ ማንነቶች የመገናኛ ማዕከል እየሆኑ ይገኛሉ።ከተሜነት እና የአገር ግንባታ አስተዋጾኦውከተሜነት የራሱ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩትም እንኳ ተያይዘዉ የሚመጡት በርካታ እድሎች አሉት። ከተሞች ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን፣ ሲቪል ማሕበራት እና የግል ባለሀብቶችን በማሰባሰብ፣ በማገናኘት እና የገንዘብ ፍሰትን በማጠናከር ዘላቂ የሃገር ግንባታና የሠዉ ኃይል ልማት በማምጣትም ውጤታማ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። ከተሞች በውስጣቸዉ እና በአጎራባች ዙሪያ አካባቢዎቻቸዉ በአገር ግንባታ ረገድ የሚጫወቱት ሦስት ወሳኝ ሚናዎች አሏቸዉ። ማለትም፡-እንደማህበራዊ መስተጋብር አቀጣጣዮች፣የኢኮኖሚ ትስስር መስመሮች እናየፖለቲካዊ አብሮነት መልህቆች (ማለትም በህዝቦች መካከል) በመሆን የአገር ግንባታ መሠረትን በላቀ ሁኔታ ለማጽናት ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።እነዚህ ሚናዎች ምን ያስከትላሉ? ከተማዎች ዘላቂ ዕድገትን ለማረጋገጥ እና ሁሉን የሚያካትት ጠንካራ አገር ለመገንባት፣ የወደፊት አስጊ ችግሮችን ለመቅረፍ የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ ይችላሉ?1. የተለያየ ማንነት ያላቸዉ ማኅበረሰቦችን በማስተሳሰር የማህበራዊ መስተጋብር መቀጠያ ድሮች በመሆን ያገለግላሉ።የኢትዮጵያን ጨምሮ ሁሉም ከተሞች ከአጎራባች አካባቢዎች ማኅብረሰብ ጋር ያላቸዉ ግንኙነት ጠንካራ ነዉ።መንግስት ከተማና ከተሜነት በአገር ግንባታ ረገድ የሚኖረዉን ጉልህ አስተዋጽኦ በዉል ተገንዝቦ ዘላቂ የከተሞች ልማት፣ የመሬት አስተዳደርና ለከተሞች ሃብት አያያዝ ቅድሚያ በመስጠት ስርዓት ማበጀት አለበት።እንደዚሁም “የአፍሪካ ከተሞች:- ወደ ዓለም የተከፈተ በር” የሚል ርዕስ በቀረበ ዘገባ እንደተገለጸዉ የከተማ ኗሪዎችን የሕይወት ዉጣ ዉረድ በማቅለል፣ የኑሮ ሁኔታዎች በማሻሻል እና ከሥራ ዕድል በመፍጠር ጥብቅ ማኅበራዊ መስተጋብር በማጎልበት ለኅንጸተ- አገረ ፕሮጀክት (Nation Building Project) ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ ይቻላል።ለዚህ የአገር ግንባታ ፕሮጀክት ከተሞች ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል ሪፖርቱ ባለሁለት ፈርጅ መፍትሔዎችን ያስቀምጣል። አንደኛ የከተማ መሬትና ሌሎች ሀብቶች ገበያዎችን ህጋዊ መስመርን እንዲከተሉ ማድረግና መስመር ማስያዝ፣ የከተሞችና ሀብቶችን የባለቤትነት መብት በግልጽ ማስቀመጥ፣ እንዲሁም የማኅበረሰቡን የአኗኗር ዘይቤ ያገናዘበ የከተሞች ፕላን ማዘጋጀትና መተግበር ናቸዉ። ሁለተኛዉ ደግሞ በተጠና ዕቅድ ላይ የተመሠረተ የተቀናጀ የመሠረተ ልማት፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድገት ናቸዉ።በተመሣሣይ ሁኔታ በፍጥነት እያደጉ ባሉ የአገራችን ከተሞች የሚገኙ የከተማ ፕላነሮች እና የመንግስት ውሳኔ ሰጪ አካላት የመሬት፣ የቤት እና ሌሎች የአገልግሎት አቅርቦቶችን በማሻሻል እንዲሁም ለአዳዲስ ነዋሪዎች የሀብት ተደራሽነትን በመፍጠር የርስ-በርስ መገናኘትን ማሻሻል አለባቸው። በመሆኑም በርካታ መካከለኛና አነስተኛ የከተማ ማዕከላት መፈጠር ለነዋሪዎች የጋራ የማንነት ቅርጽ በመስጠት ርስ-በርሳቸዉ በማገናኘት በአስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ መስተጋብር እንዲፈጠርና የታላቅ አገር ግንባታ ሂደትን ያፋጥናሉ። መቀጠያ ድርም ይሆናሉ።2. ፍትሐዊና አካታች የኢኮኖሚ ዕድገት በማምጣት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ከተሞችን እንደገፊ ምክንያት፤ከላይ በመግቢያዬ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የከተማ ሥልጣኔ መርሕ ኑሮን ለማሸነፍ ለሚሠራ ሁሉ በሩን ክፍት አድርጎ መጪን መቀበልና ኑሮን መቋቋመ ያቃተዉ ሂያጅን መሸኘት ነው። ሆኖም ከተማ ሂያጅን አያበረታታም የኗሪዉ ትብብር ተቸግሮ መኖርን መልመድ ያስችላል። ስለሆነም ከተሞች ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማምጣት ከጫፍ ጫፍ ርስበርሱ የተሳሰረ አንድ የኢኮኖሚ ማኅረበሰብ በመፍጠር ለአገር ግንባታ የበኩላቸዉን ጠጠር ይጥላሉ። የአገር ግንባታ መነሻዉ ከተማና ከተሜነት ነዉ የሚባለዉ ለዚህ ነዉ።በአንድ አካባቢ የሚመረት ምርት ወደ ሌላ አካባቢ ገብቶ ሲሸጥ፣ ባንድ አካባቢ ለሚመረት ምርት ከሌላ አካባቢ ግብዓት ሲመጣ ትስስሩ ይበልጥ ይጠናከራል።እ.ኤ.አ ከ2000 ዎቹ ዓመታት ጀምሮ ተቀራራቢ የዕድገት ደረጃ ላይ በሚገኙና ተወዳዳሪ በሆኑ ከ750 በላይ የዓለም ከተሞች ውስጥ በተካሄደዉ ጥናት ከተሞች በብሔራዊ ኢኮኖሚ ከተመዘገበዉ ዕድገት ከሦስት አራተኛ በላይ ፈጥነዉ ማደግ ችለዋል። ይሁን እንጂ በታዳጊ አገሮች ውስጥ ከሚገኙ ከሦስት የከተማ ነዋሪዎች መካከል አንዱ/ዷ አሁንም በአሰቃቂ የኑሮ ደረጃዎች ውስጥ ይኖራል። ይህም ለበርካታ ጊዜ ከተሞች የወንጀልና የብጥብጥ መነሻ የስጋት ቀጠና ሆነዉ ዘልቀዋል።ከተማዎች በቀጣይ ለሁሉም ነዋሪዎቻቸዉ ዘላቂ የኑሮ ዕድገትና ፍትሐዊ ዕድል እንዲሰጡ ለማድረግ ባለሶስት አቅጣጫ “የአካታች ከተማዎች” ስልት መንደፍ ያስፈልጋል። ይህ ስልት በአንድ ላይ ተጣምሮ የሚተገበር ሲሆን የሁሉንም የአገሪቱ ከባቢ ዜጎችና ባህላዊ ማንነት አካታችነት፣ ማህበራዊ ተሳትፎ/አካታችነት እና ኢኮኖሚያዊ አካታችነት ናቸዉ። እንዲሁም ተጠያቂነትና ጠንካራ አቋም ያላቸው አካባቢያዊ አስተዳደራዊ ተቋማት በመገንባት እና የከተማዉን ማህበረሰብ አቅም በማጠናከርና በማብቃት ከተሞችም በጋራ ደህንነት ቦታዎች ማድረግ ይቻላል።3. ከተሞችና ከተማ ቀመስ አካባቢዎች የፖለቲካና የዘር ግጭት አደጋዎች እየጨመሩ ሲሄዱ የአገራዊ (ብሔራዊ) ማንነት አንድነትን ለማረጋገጥ እንደ መሠረት ተደርገው ይቆጠራሉ፣ሃገራት ከተሞቻቸዉን በበለጠ ሁኔታ በማስፋፋትና በማሳደግ የጎሳ ግጭቶችን የመቋቋም አቅም እንዲኖራቸው በማድረግ አገራዊ አንድነትን እና አገራዊ ማንነትን ጠብቀዉ እንዲቆዩ ማድረግ ይችላሉ። ዘር ተኮር የፖለቲካ ቀዉሶችና የጎሳ ግጭቶች ዜጎችን በድህነት ውስጥ እንዲገቡ ሊያደርግ ይችላል።በመሆኑም አንዳንድ አገራት ከፖለቲካ ቀዉስ ለመዉጣትና መልሶ ለማገገም ለሚያደርጉት እልህ አስጨራሽ ትግል የከተማና የከተሜነት በድርድርና ዉይይት ላይ የተመሰረተ አኗኗር ዘይቤን ቀዉስን ተቋቁሞ አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር እንደአስፈላጊነቱ በአማራጭነት ሊጠቀሙበት ይገባል። እነዚህ የከተሞችን ጠቀሜታና ከተሞች የአገራትን የወደፊት ሁኔታ ለመቅረፅ ከሚሰጡት አገልግሎትና በርካታ ትልልቅ ሀሳቦች ዉስጥ ጥቂቶቹ ናቸው።4. እናስ ምን ይበጃልከተሞች የጋራ ማንነትን እንዲያጸባርቁ አድርጎ መከተምከተሞች ምንም እንኳ በተለያየ አካባቢዎች ቢኖሩም የንግድ፣ የመንግስት እንዲሁም ከድርጅት ስያሜዎቻቸዉ ጀምሮ እንዲሁ መሠረተ ልማታቸዉ አገራዊ ማንነት በሚያንጸባርቁ መጠሪያዎች እንዲሰየሙ ማድረግ፣ዘላቂ እና ለማኅበረሰብ ብቹና ተስማሚ ከተሞች መገንባትየአገራችን አብዛኞቹ ከተሞች የተለያዩ ማንነቶች ስብጥር መሆናቸዉን በመገንዘብ እንዲሁም መንግሥት ሰዎች የማንነት አደጋ ስጋት ውስጥ መኖር እንደሌለባቸው በማሰብ የጋራ አገራዊ ማንነት ጥበቃ የሚያስፈልጋቸውን ከተሞች በመለየት ዘመናዊ የልማትና እድገት ዘዴዎችን መተግበር አለበት። መንግስት የመጀመሪያ ደረጃ ከተሞችን በመለየት የፖለቲካ አስተዳደር ስርዓታቸዉን በፌዴሬል መንግስቱ ሥር ማዋቀር፣ ዓላማውም የተሻሉ የከተማ አካባቢዎችን እና የተለያዩ የከተማ ኗሪ ህዝቦችን ያካተተ ዘመናዊ የከተሞችን አስተዳደራዊ ቅርጽ ማቋቋም ነው። መንግሥታት ቀጣይነት ያለውን የከተማ ሀብት ፍሰት ለማበረታታት እንዲሁም በአረንጓዴ የመሰረተ ልማት፣ ዘላቂ ኢንዱስትሪዎች እና አካባቢያዊ የልማት ዘመቻዎች፣ የአየር ብክለት አስተዳደር፣ ታዳሽ ኃይል፣ የሕዝብ ትራንስፖርት፣ እና የንጹህ ውሃ አቅርቦት ማሻሻያ እና የልማት መዋዕለ ንዋይ ማፈላለግን የመሳሰሉ ቀጣይ አካባቢያዊ ኢኮኖሚያዊ ድጋፍን ማበረታታት አለበት።አስፈላጊ አገልግሎቶችን መስጠትሁሉም የከተማ ባለድርሻ አካላት በከተሞች ውስጥ ለሚገኙ ሁሉም ህዝቦች በቂ ማህበራዊ አገልግሎቶች መስጠት አለባቸዉ። ማለትም ትምህርት፣ ጤና፣ የንጽህና እና ንጹህ ውሃ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኤሌክትሪክ እና በቂ ምግብ ማግኘት አለባቸው። በእዚህ ረገድ በዋነኛነት የሚቀመጠው ዓላማ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እና ሀብትን ለማፍራት የሚያስችሉ ሥራዎችን ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት ነው። መሠረታዊ የጤና ጥበቃ፣ መሠረታዊ ትምህርት፣ የኃይል አቅርቦት፣ ትምህርት፣ የህዝብ ትራንስፖርት፣ የባህል ግንኙነት ሥርዓቶች እና ቴክኖሎጂ ወጪዎች ለመቀነስ የመንግስት ጽኑ ድጋፍ ሊኖር ይገባል።ተጨማሪ ሥራዎች መፍጠርፈጣን የሆነ የከተማ እድገትን አሉታዊ ተፅዕኖ ለማቃለል በተመሳሳይ ጊዜ የተፈጥሮ ሥርዓተ-ምህዳርን ለመጠበቅ የግል ኢንቨስትመንቶችን ለማስፋፋት የተፈጥሮ ሀብት ባግባቡ በመጠቀም እና ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር የግል ባለሀብቶችን ማበረታታት ያስፈልጋል። የቱሪዝም መስህቦችን ማስተዋወቅ እና የተፈጥሮ ሀብቶችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ማጎልበት ለከተማው ሰዎች ተጨማሪ የስራ እድል ይፈጥራል።የሕዝብ ቁጥጥርና ሞዴል ከተሞችከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት መቀነስን ለማገዝ በከተሞች ውስጥ የሚገኙ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት የቤተሰብ ምጣኔ ዘመቻዎች እና ምክር መስጠት አለባቸው። የበሽታዎችን መዛመት እና የህዝብ ቁጥር መጨመርን ለመቆጣጠር በሁሉም የከተማ ክልል ውስጥ የቤተሰብ ምጣኔ አማራጮች ላይ የሚያተኩር የሕክምና ክሊኒኮች መዘጋጀት አለባቸው።በተጨማሪም የህዝብ ወደ ከተማ ፍልሰትን ለመከላለከል በአነሰተኛ መንደሮች የሞዴል ከተሞች አሰራርን መተግበር ይገባል።

አስተያየት