You can paste your entire post in here, and yes it can get really really long.
ለምን የኮሌጅ ትምህርቴን አቋርጬ ወጣኹኝ ብዬ የማማርር ወመኔ ነበርኩኝ፤ የዛሬን አያድርገውና። ዛሬማ ነገር ተቀይሯል። የሰው አናት ላይ መሽከርከር እና አብዶ መሥራት ለምጄ ህይወት ቀሽት ሆናልኛለች። እንደቀልድ የለመድኳት የጸጉር አስተካካይነት ሙያ ሕይወቴን አንዴ ላይመለስ ቀይራዋለች። አሁንማ ስሜ ራሱ ተረስቷል። ትንሽ ትልቁ ሚዶ፣ ሚዶው፣ ሚዶዬ፣ ሚዶካ ነው የሚለኝ። ሁሌ ሳቄን አፍኜ “ወዬ” እያልኩኝ እመልሳለኹ። የወጣልኝ ቅጽል ስም ሁሌ ለእኔ ባዕድ ነው። ግን አላስጠጣም ምክንያቱም የስኬቴ ብራንድ ነው።ትዝ ይለኛል ያኔ ችስታ እያለኹ ቅፈላ ያማረረው ወዳጄ እስኪ ሰርተህ ብላ፤ እስኪ እኛን ምሰል ብሎ መቀስ እና ሚዶ አስጨበጠኝ። መጀመሪያ ደብሮኝ ነበር በኋላ ግን ችግሬን ከምቆጥር የሰው ጸጉር ብመነጥር የሚሻል መሰለኝ። ተመሰጥኩበት። ብዙ ደንበኞች አፈራኹኝ። ሚዶ ከደረት ኪሴ አይለይም። መቁረጥ ከመጀመሬ በፊት የሰውየው አናት ላይ እንደሚባርክ ቄስ በሚዶዬ እያሰመርኩኝ፣ የሐሳብ መስመሮች እየሰራኹኝ እመትራለኹ። ስራዬን በዕቅድ ነው የምመራው። የማሾፍ እየመሰላቸው በእኔ እና በሚዶዬ መሳለቅ ያዙ። እኔ ግን ደንበኞቼን እና አናታቸውን ማክበሬ ነው። ዋዛ ከበዛበት ሕይወቴ ውስጥ ጨልፌ አስር እና አስራ አምስት ደቂቃ ቁም ነገር ልስራበት ብዬ ነው።ከዚያማ ደንበኛዬ በዛ፤ ስሜም ተቀየረ። ሁሉም ሚዶ ካልቆረጠኝ ሞቼ እገኛለኹ ማለት ጀመረ። ከደንበኞቼ አንደኛው ቋሚ ተሰላፊ ሆነ። ቶሎ ቶሎ መምጣቱ፤ በዚያ ላይ ቲፕ አገፈታተሩ። ሚኒስተር ዴታ ነው ይሉኛል፣ ዴታ ምንድን ነው? ብዬ ጠይቃለኹኝ የሚመልስልኝ የለም። ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር ነው ይሉኛል፣ እኔ ደግሞ ለምን ይደጋግሙታል አንድ ዳይሬክተር አይበቃውም? ብዬ ጠይቃለኹኝ። ሁሉም አትፈላሰፍ አትፈላሰፍ ይለኛል።መጀመሪያ ጸጉር ከምታጥበው ቆንጅዬ ልጅ ጋር ፍቅር የያዘው መስሎኝ ነበር። እኔ ከርክሜ እስክጨርስ አንዳንዴ ጸጉር ቤት ውስጥ፣ ሌላ ጊዜ የዴታው መኪና ውስጥ ቁጭ ብለው የሚጠብቁትን ቆነጃጅት ሳይ ግምቴ ስህተት መሆኑ ገባኝ። ላለመሸነፍ በቃ እርሷ ናት ከእርሱ ፍቅር የያዛት ብዬ ደመደምኩኝ።ዴታዬ ይጠይቃል። “ስራ እንዴት ነው? ጥሩ ገቢ ታገኛለህ ወይ?” እያለ ያደክመኛል። ከአገር ውስጥ ገቢ የመጣ ስለሚመስለኝ “ምንም አይልም በቀን አራት አምስት አናት ብፈነክት ነው” እለዋለኹ። ቀልዴ ደስ ይለዋል። አንድ ቀን ውጪ ቆመና ክላስክ አድርጎ ሚዶን ጥሩልኝ አለ። በመስኮት የሚመጣበትን ሰዓት ልጠይቅ ጠጋ ስል ከኋላ እንድገባ ምልክት ሰጠኝ። ፈራ ተባ እያልኩኝ ስገባ አንድ ጠቆር ያለ ሰው ጋቢና ተቀምጧል። “ሚዶ፣ ተዋወቀው” አለኝ “ቀላል ሰው እንዳይመስልህ የመለስ ቀብር ዕለት ነጭ ሸሚዝ ለብሶ የሄደ ጀግና ነው።” ባይገባኝም ፈገግ ብዬ እጄን ዘረጋኹኝ። ሰውየውም በአክብሮት ጨበጠኝ።ዴታዬ መናገሩን ቀጠለ። “አንድ ጥሩ ህንጻ ላይ ጸጉር ቤት ብንከፍት ምን ይመስለሃል? ለእኛም እዚህ ሰፈር መምጣት አይመችም፤ በዚያ ላይ ይሄ ጸጉር ቤት አርጅቷል:: ወጪውን አታስብ እኔ ከዱባይ እቃዎች እንዲመጡ አዝዣለኹ። የሚከራይ ቦታ እንደተገኘ ወዲያውኑ ትጀምራለህ። የደንበኛም ጉዳይ አያሳስብህ፣ እኛን መሰል ሰዎች ቤተኛ እንዲሆኑ እናደርጋለን።”ከአንድ ወር በኋላ ራሴን በዘመናዊ የጸጉር ማስተካከያ መሣሪያዎች በተሞላ፣ ጓዳ ያለው ጸጉር ቤት ውስጥ አገኘኹት። ‘ሚዶ ባርበር ሾፕ’ የሚለውን ሳይ ሁሌ ሳቄ ያመልጠኛል። ደንበኞቼ ተቀየሩ። የሚቀር ባለስልጣን፣ ባለሀብት እና አርቲስት የለም። ሚኒስተሩ ሰላጸደቀው በጀት ሲነግረኝ፣ ባለሀብቱ ስለሚረከበው መሬት፣ አርቲስቱ ደግሞ ስለሚቀጥለው ፊልሙ ይተነትንልኛል። ሐሳብ እሰጣለኹ፣ ይስቃሉ። የሚከፋው የለም። ሁሉም እንደ የልብ ዳጁ ነው የሚያኝ። በዚያ ላይ ከድሮ ጸጉር ቤት አስኮብልዬ ያመጣኋት አመለ ጓዳ ሆና ስክራፕ የሚቀባ፣ አናቱን ማሳጅ የሚሠራ ሰው ከመጠበቅ በቀር አንገቷን ደፍታ ልብወለዷን ስለምታነብ ሚስጢር ለማውራት ይመቻል። የጓዳቸውም የቢሯቸውም ሚስጢር ለእኔ ጆሮ ቅርብ ነው።የመለስ ቀብር ዕለት ነጭ ሸሚዝ ለብሶ የሄደው ሰውዬም ደንበኛዬ ሆነ። ብዙ ወሬ የማያበዛ ቁጥብ ሰው ነው። ጓደኞቹ ሲሽቆጠቆጡለት ለጉድ ነው። ለምን እንዲህ እንደሚከብሩት የተገለጸለኝ እየቆየ ነው። ፖለቲካ እንደ ጸጉር ማስተካከል በሚዶዬ የምማርከው ነገር አልሆነልኝም። በነጭ ሸሚዝ የተጀመረችው ትዕቢት ነበረች ዶክተሩን አራት ኪሎ ያስቀመጠችው። እየቆየ ሲገባኝ ያ ሰውዬ እና ጓደኞቹ ነበሩ ተጋዳላዮቹ ላይ ማመጽ የጀመሩት። ፊቱ የማይታወቀው ሰውዬ በንዴት በቴስታ እንደሳተው ዴታዬ የነገረኝን እያስታወስኩኝ ሳምንት ስቄያለኹ።አሁን ከተማው የሚነጋገርበትን ጉድ ሰምቼ የማካፍለው ሰው አጥቼ ነበር። አንድ ቀን ዴታዬ አንድ ረጅም ቀላ ወፈር ያለ ሰው እና ሌሎች ኹለት ጎልማሶች ይዘው ሚዶ ባርበርሾፕ ከች አሉ። ጓዳ ገብተው ከዴታዬ ጋር በሚስጢር ተነጋግረው ወጡ። ሸኝቷቸው እንደተመሰለ ማቆጥቆጥ የጀመረውን ጺሙን እንዳነሳለት ማስተካከያው ወንበር ላይ ተቀመጠ። ዴታዬ እና ዶክተሩ ጺም ማሳደግ አይወዱም።“የአሁኑን ሰውዬ አየኸው አውሬ ነው።” ዝም አልኩኝ ማለት ማብራሪያ እፈልጋለኹ ማለት ነው። ዴታዬ ይህንን ስለሚያውቅ ንግግሩን ቀጠለ “ማዕከላዊ ቶርች ሲያስደርግ፣ ሴቶችን ሲያስደፍር፣ ጥፍር ሲያስነቅል፣ ብልት ላይ ውሃ በኮዳ ሲያንጠልጥል ነው የኖረው::” እኔም “ታዲያ በመደመር ዘመን ምን ያደርጋል?” ብዬ ጠየኩት። “ሚዶ ደግሞ ታሪክ አለማወቅህ ትንሽ ዘገም ያደርግሃል። ተስፋዬ ወልደሥላሴ የደርግ ደኅንነት ነበር። ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ የወያኔው ደኅንነት ክንፈ ገብረመድኅን ሁለት ወር ሙሉ ሳይታሰር ሚስጢር ሲያቀብል ነው የቆየው። በቂ መረጃ ካቀበለ በኋላ ነው ወደ ጓደኞቹ የተቀላቀለው። ይሄም በተራው የሚያውቀውን በሙሉ እየተናዘዘ ነው” አለኝ።ሰኞ ዕለት ዐቃቤ ህግ ደኅንነቶች ማሰሩን ሲገልጽ ዴታዬን “ያ ሰውዬ ታሰረ እንዴ?” ብይ ጠየኩት። “ባክህ አለቆች በእርሱ ጉዳይ አልተስማሙም። ሁሉም ቶርች ያደረገ አልታሰረም፤ ያኔ ዐቢይ የተመረጠ ጊዜ የለውጡን ኃይል ለማሰር የተባበረው ብቻ ነው የተቀፈደደው። ያንተ ሰውዬም አንደኛው ረድቶት ወደ እስካንዴኒቪያ ሄዷል።” መናደዴን መደበቅ አልቻልኩም።ዴታዬ ይህንን ሲያይ ሌላ መረጃ ጨመረልኝ “ከእስር ቢያመልጥም ከእግዜሩ ቁጣ አላመለጠም፣ እዚያ ፓራላይዝ ሆኗል እየተባለ ነው።”