You can paste your entire post in here, and yes it can get really really long.
እንደሚገመተው ባይሆንም መጠነኛ ሊባሉ የጥላቻ ንግግሮች በኢትዮጵያውያን ዘንድ እየተስተዋሉ ነው።በተለይ ከማኀበራዊ ሚደያ ጠቃሚዎች ቁጥር መጨምር ጋር ተያይዞ ስጋቶች እየጨመሩ ነው። የሕግ መምህሩ ሚክያስ በቀለ ስለጥላቻ ንግግር ሕግ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዳሰሳ አድርጓል።መነሻየድህረ 1983 ዓ.ም. የኢትዮጲያ ፖለቲካ ዋነኛ መገለጫ ብሔር ሆኖአል። የተረገዘው በ60ቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ እንደሆነ የሚነገርለት የብሔር ፖለቲካ (ጥያቄ) ተቋሚዊ ቅርጽ ይዞ ኢትዮጲያን ማስተዳደር ከጀመረ አስርተ ዓመታትን አስቆጥሯል። በኢትዮጲያ ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝቦች “ስምምነት” የሀገሪቷን ሉአላዊ ባለቤትነታቸውን ያረጋገጠ ሕገ መንግስት በሕዳር 28 ቀን 1987 ዓ.ም ጸድቆአል። ሕገ መንግስቱ የአባላቱን የራስ እድል በራስ የመወሰን ስልጣን ለማጎናጸፍ አልሞም “የህዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ፈቃድን” መሠረት ያደረጉ ክልሎችን በመፍጠር የብሔር ተኮር ፌደራላዊ ስርዓት ገንብቷል። የብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት፣ በፌደራል መንግስቱ ውስጥ በአግባቡ የሚወከሉበት፣ ካሻቸውም ከፌደሬሽኑ ተለይተው የሚወጡበትን አካሄድም ለማስቀመጥ ሞክሯል።ይሄንንም ተከትሎ ሕገ መንግስቱን በሚደግፉ እና በሚቃወሙ መካከል ሙግቶች ሲካሄዱ ከርመዋል። የፖለቲካው ትርክት ሕዝቡን ከማቀራረብ፣ ሁሉን ያሳተፈ ስርዓት ወደ መመስረት ከመምጣጥ ይልቅ በሁለት ጉራ በተለዩ የፖለቲካ ሊሂቃን ተሸብቦ ከርሟል። በታሪክ አረዳድ እና የሀገሪቷ ቀጣይ አካሔድ ላይ ልዩነቱ ሰፍቷል። የፌደራል ስርዓቱ ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ የብሔር ግጭቶች በየቦታው ብቅ ጥፍት ሲሉ ቢከርሙም፣ አሁን ላይ ግን በሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት ከላይ ወደታች ሲፈስ የነበረው ጠንካራ የመንግስት የፖለቲካ አሰላለፍ ላይ ክፍተት መፈጠሩን ተከትሎ የብሔር ግጭቶቹ በስፋት መስተዋል ጀምረዋል። በብሔር ምክንያት የሚፈጠሩ ሞትና መፈናቀሎች የሀገሪቷ መደበኛ ዜናዎች መሆን ከጀመሩ ከራርመዋል፡፡የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደርም በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚተላለፉ መልእክቶች ለብሔር ግጭቶች መንስኤ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ተሰምቷል። ጠ/ሚ አብይ ፕሬዝዳንቱ የሁለቱ የፌደራል ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ የተናገሩትን ንግግር ባብራሩበት ወቅት መንግስታቸው የጥላቻ ንግግር ሕግን ለማውጣጥ ሀሳቡ እንዳለው ጠቁመዋል። ከዚህም ባሻገር የጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ፣ “ኢትዮጲያ፤ በአዲስ የተስፋ መንገድ ላይ” በሚል ርእስ ባወጣው የባለ 1 ገጽ የሀገሪቷ ተግዳሮቶች እና የ2 ዓመት ቀጣይ ስራዎች ምልከታ ላይ፣ በ2018 ዓ.ም ውስጥ የጥላቻ ንግግር ሕግን በማውጣጥ እና በማስፈጸም የብሔር ግጭትን የመቀነስ አላማ እንዳለ ተገልጾአል።አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው በአሜሪካን ኦሪገን ዮንቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ግንኙነት መምህር የሆኑት እንዳልካቸው ጫላ(ዶ/ር) ፤ ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኃላ የተፈጠረውን የተሻለ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት ቢያደንቁም “ለውጡ በሀገራችን ውስጥ ያሉ ታፍነው የቆዩ ተጻራሪ የሆኑ የታሪክ አረዳድ እና አተረጓጎሞችን እንዲሁም የማይታረቁ ሀገራዊ ህልሞችን ይዞ መጥቷል። ይህም በማኀበራዊ ሚዲያ በተለይ በፌስቡክ ካለንበት የፓለቲካ አውድ የተነሳ አደገኛ ከሕግ አንጻር ደግሞ የጥላቻ ንግግር ሊባሉ የሚችሉ ጽሑፎች፡ ቪዲዮዎች እና የፖለቲካ ሚሞች (ስእሎች) መበራከታቸውን“ ይናገራሉ፡፡የጥላቻ ንግግር - ሀሳብን በነጻ በመግለጽ እና በእኩልነት መብቶች መካከልሀሳብን የመግለጽ ነጻነት አመለካከትን የመያዝ፣ መረጃዎችን ወይም ማንኛውንም ሀሳብ የመጠየቅ፣ የመቀበል እና የማስተላለፍ መብቶችን ያካትታል። የእኩልነት መብት ደግሞ ማንኛውም ሰው በተለየ የማንነቱ መገለጫ ምክንያት ከተለያዩ ሀገራዊ ጥቅሞች ሊነፈግ እንደማይገባው፣ በሕግም ፊት አድሎ ሊደረግበት እንደማይገባ የሚያትት የመብት ጽንሰ ሃሳብ ነው። የጥላቻ ንግግርን በሁለቱ መካከል እናገኘዋልን። ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ገደብ አልባ አይደለም።እንደ አለም አቀፍ የፖለቲካ እና ሲቪል መብቶች ቃልኪዳን፤ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት ሊገደብባቸው የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች የሰዎችን መልካም ስም፣ የሀገር ደኀንነትን እና የማህበረሰቡን ጤናና ሞራል ለመጠብቅ ናቸው። እነዚህን በሰፊው የተቀመጡ ገደቦች ሀገራት በግልጽ እና ጠባብ በሆኑ ድንጋጌዎች፣ “በዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ውስጥ ጠቃሚ” ተብሎ ሊታሰብ በሚችልበት ደረጃ እንዲያስቀምጡ እና መልእክቱም ከአደጋው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ሲኖረው ብቻ እንዲቀጡ ስምምነቱ ያስገድዳል። ነገር ግን የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል ይህ በቂ ሆኖ አልተገኘም። በዚህም ምክንያትም ይሄው ስምምነት የሆነ ቡድን አባል ላይ አድሎ እንዲፈጸም ወይም አደጋ እንዲደርስ የሚነሳሱ ንግግሮች ሀገራት እንዲከለክሉ መብት ይሰጣል። ይሄንን ድንጋጌም አስመልክቶ የተባበሩት መንግስታት ድርጅተ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የጥላቻ ንግግር ክልከላ ሀሳብን የመግለጽ እና የነጻነት መብቶችን እንዳይጻረር በማሰብ፣ ጠበባ በሆነና የማህበረሱን ጥያቄም ለመመለስ ብቻ በሆነ፣ ቅጣቱም ተመጣጣኝ እንዲሆን በማሰብ ሀገራት የጥላቻ ንግግርን ለመቆጣጠር የሚያወጧቸው ሕግጋት ምንን መሰረት አድረገው መረቀቅ እንደሚገባቸው በዝርዝር አስቀምጧል።ስለ ጥላቻ ንግግር ክልከላ የምናገኘው በአለም አቀፍ የሲቪል እና ፖለቲካዊ መብቶች ቃልኪዳን ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በ1953 ዓ.ም ላይ በጸደቀ እራሱን የቻለ ማንነትን መሰረት ያደረጉ አድሎዎችን ለማጥፋት በተቋቋመ ስምምነት ላይም ነው። ስምምነቱ ለአባላቱ ካካተታቸው ኃላፊነቶች ውስጥ ዋነኛው ሀገራት አድሎን እና ግጭቶችን የሚያነሳሱ የጥላቻ ንግግሮች መከላከል እንደሚገባቸው የሚያትተው ድንጋጌ፣ አንቀጽ 4 ነው። ድንጋጌው በሰፊ የተቀመጠ እንደመሆኑ ሀገራት ይህንን በሕግጋታቸው ውስጥ ሲያካትቱ እና ሲያስፈጽሙ ትኩረት ሊሰጡባቸው የሚገቡ ጉዳዮች በባለሙያዎች እንዲተነተኑ ተደርጓል። የባለሙያ ስብስቦቹ 18 አባላት ሲኖሩት ኃላፊነቱም የስምምነቱን ድንጋጌዎቹን ከመተርጎም ባሻገር አባል ሀገራት ግዴታቸውን እየተወጡ መሆኑን ማጣራትም ነው። በዚህም መሰረት የባለሙያዎቹ ኮሜቴ “የጥላቻ ንግግር ስለመዋጋት” በሚል ስለ ጥላቻ ንግግር ሕግ ጥልቅ ትርጓሜ ሰጥቶበታል። ኢትዮጲያም የጥላቻ ንግግርን ለመቆጣጠር ሕግ ለማውጣጥ በዝግጅት ላይ እንደመሆኗ እነዚህ በተ.መ.ድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና በ18ቱ ባለሙያዎች የተቀመጡትን ሁኔታዎችን አጣምሮ መመልከቱ አስፈላጊ ነው፡፡የጥላቻ ንግግር የሚያስቀጣው መቼ ነው?የጥላቻ ንግግር ወንጀል የሚሆነው እና የሚያስቀጣው በሚል በሁለቱም ተቋማት የቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎች ተጠቃለው ሲታዩ በስድስት መሰረታዊ ነገሮች ላይ ተገድበው እናገኛቸዋለን - 1) መልእክቱ የተላለፈበት ከባቢ (Context)፣ 2) የተናጋሪው ማንነት፣ 3) የተናጋሪው የወንጀል ሀሳብ (intent)፣ 4) የንግግሩ ይዘት፣ 5) የንግግሩ ተደራሽነት እና 6) የንግግሩ ውጤት። አንድ የጥላቻ ንግግር እንዲያስቀጣ ንግግሩ የተደረገበትን ጊዜ እና ሁኔታ መመልከት ይስፈልጋል።እንደ ምሳሌ ግጭት መኖሩን፣ የጥላቻ ንግግሩ ያነጣጠረበት ቡድን በፊት የአድሎዋዊ አካሄዶች ተጠቂ መሆኑን፣ የጥላቻ ንግግሩን የሚመክት በቂ አማራጭ ሚዲያ ስላለመኖሩ፣ እና የፖለቲካው ሁኔታ በማንነት ላይ የተቃኘ መሆኑ ግምት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ያለውን አጠቃላይ ታሪካዊ እና ማህበረሰባዊ ሁኔታዎች መመልከትም አንድን መልእክት በጥላቻ ንግግሩ አውድ ውስጥ ለመክተት መሰረታዊ ሁኔታ ነው። የተናጋሪው ማንነትም ወሳኝ ነው። መልእክቱን ያስተላለፈው ሰው በማህበረሰቡ ውስጥ ያለው ድርሻ እና ተደማጭነት ግምት ውስጥ መግባቱ መልእክቱ አድሎን ወይም ግጭትን ለመፍጠር ያለውን ኃይል ለመገንዘብ ይረዳል። ግለሰቡ ተደማጭነት ያለው ፖለቲከኛ ወይም የማህበረሰብን አስተያየት የመቅረጽ አቅም ካለው የጥላቻ ንግግር ላይ ለሚኖር ተሳትፎ ተጋላጭ ያደርገዋል።ሌላው ተናጋሪው ጥላቻን ወይም አድሎን ለማነሳሳት ሀሳቡ ሊኖረው ይገባል። ዝም ብሎ ሀሳብ መግለጽ የጥላቻ ንግግር ሊባል አይችልም። የተናጋሪውን ሀሳብ ለመለየት መልእክቱን ያስተላለፈው እና የጥላቻ ንግግሩ ያነጣጠረውን ቡድን ልዩነት፣ በሁለቱ መካከል ያለውንም ቁርሾ ማየት ይቻላል። መልእክቱን ያስተላለፈው ሰው ሀሳቡ ባይኖረው እንኳ በአስተላለፈው መልእክት ምክንያት አድሎ ወይም ጥላቻ ሊፈጠር እንደሚችል እውቀቱ ሊኖረው ይገባል። ይሄም በተለያዩ ሁኔታዎች ሊጣራ ይችላል - በተጠቀመው ቋንቋ፣ የንግግሩ ድግግሞሽ እና የመልእክቱ ዓላማ። ስለዚህ በግድ የለሽነት ወይም ሀሳቡን ለማስተላለፍ በማሻት ብቻ የሚተላለፉ መልእክቶች የሚያስቀጡ የጥላቻ ንግግሮች ለማለት አይቻልም። የመልእክቱን ይዘት፣ ከቀጥተኛው ገላጻ ባሻገር የአጻጻፉን/አነጋገሩን እና የተጠቀመው ዘዴ ግምት ውስጥ ማስገባት ያሻል። የመልእክቱ ተደራሽነት ሲባል በቁጥር ላይ የተመሰረተ፣ ለብዙሃን መዳረሱ ብቻ ሳይሆን አድማጩ/አንባቢው መልእክቱን አንብቦ የመረዳት ችሎታም መታየት አለበት እንደማለት ነው። መልእክቱ የጥላቻ ንግግር እንዲሆን በንግግሩ ምክንያት የአድሎ ወይም ጥላቻ የመፈጠር አጋጣሚው ከፍ ያለ ሊሆን ይገባል። ይሄ ማለት ግዴታ የመልእክቱ ውጤት - አድሎ፣ ጥላቻ ወይም ግጭት - መፈጠር አለበት ማለት አይደለም። ነገር ግን አድማጩ/አንባቢው በመልእክቱ ጫና ሊያድርብት የሚችልበት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመልእክቱ ምክንያት የጥላቻ ወይም አድሎ አቋም ሊይዝ የመቻሉ አጋጣሚ ሊመረመርም ይገባል እንደማለት ነው፡፡ኢትዮጲያም የሚያስቀጡ የጥላቻ ንግግሮች ከእነዚህ አኳያ በጥንቃቄ መለየት፣ ከፖሊስ፣ እሰከ ዓቃቢ ሕግ እና ፍርድ ቤት ያለውን የወንጀል ስርዓቷንም በብቁ እና ነጻ ግለሰቦች ማስታጠቅ ይኖርባታል። የጋዜጠኝነት እና ግንኙነት ባለሙያው ዶ/ር እንዳልካቸው በዚህ ይስማማሉ። እንደ ባለሙያ አገላለጽ “[የጥላቻ ንግግር] ሕጉ የሚወጣ ከሆነ አሁን የተጀመረው ፍርድ ቤቶችን ከፓርቲ ፖለቲካ ነጻ (non-partisan) በሆነ መንገድ ማደረጀት በሰፋት እና በፍጥነት መቀጠል አለበት። በተጨማሪም እንደ ጸረ ሽብር ሕጉ ጊዜ መንግስት የተለየ የፓለቲካ አመለካከት ያላቸውን ተቃዋሚዎችን፣ ጋዜጠኞችን እና አክቲቪስቶች በጥላቻ ንግግር እያሳበበ እንዳያስር ያሰጋኛል። እና አንድን ንግግር (text) የጥላቻ ንግግር ነው ብሎ መወሰን ያለበት ፖለቲከኞች ሳይሆኑ ፍርድ ቤቶች መሆን አለባቸው። ከሁሉ በፊት ግን ስለ ሚወጣው ህግ ምሁራዊ ውይይት ያስፈልጋል”፡፡የማኀበራዊ ሚዲያ ሚናየማኀበራዊ ሚዲያ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዱብዳ ነው። መልእክቶች በማንኛውም ሰው እና ከየትኛውም የአለማችን ክፍል በሰኮንዶች ልዩነት ውስጥ እንዲሰራጩ አጋጣሚን ይፈጥራል። ኢትዮጲያ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ብዛት የጨመረባት ሀገር ነች። ቁጥሩ በተለያዩ ምንጮች ላይ አወዛጋቢ ቢሆንም፣ እንደ የአለም አቀፍ የቴሌኮሚኒኬሽን ማህበር ገለጻ በኢትዮጲያ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ቁጥር 15.37 በመቶ ደርሷል፡፡ማኀበራዊ ሚዲያ በተለያዩ ምክንያቶች ለጥላቻ ንግግሮች ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። በመጀመሪያ በማኀበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ መልእክቶች ከተለመዱ የመገናኛ ብዙሃን (ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ጋዜጣ) በበለጠ የመቆየት፣ በተደጋጋሚም የመታየት አዝማሚያ አላቸው። የጥላቻ መልእክቶች ለረዥም ጊዜ መቀመጣቸው ደግሞ የመልእክቶቹን ዉጤታማነት ከፍ ያደርገዋል። ከዚህ ባሻገር መልእክቱ እንደሌሎቹ የመገናኛ ብዙሃን አንድ ቦታ ላይ ብቻ የሚገኙ ሳይሆኑ በተለያዩ ቦታዎች ላይ እንዲሰራጩ እና እንዲገኙ ይሆናል። የማኀበራዊ ሚዲያ የግለሰብ ማንነት ሳይታወቅ መልእክቱን እንዲተላለፍ እድሉን መስጠቱ ግለሰቡ የጥላቻ መልእክቱን በምቾት፣ “ተጠያቂነት የለብኝም” በሚል መንፈስ እንደልቡ እንዲያስተላለፍ ምክንያት ይሆናል። በሕግ ወደ ሚኖረው ቁጥጥርም ስንመጣ ግለሰቡ በተለያዩ ሀገራት ስለሚኖር የአደጋው ተጋላጭ የሆነው ሀገር መንግስት አጥፊውን ለመቅጣትም ሆነ ለማስቆም የስልጣን እና የተደራሽነት ገደብ ይኖርበታል፡፡የጥላቻ ንግግሮች አስከፊ ውጤት - የዘር ማጥፋትየጥላቻ ንግግር አስከፊውና ከፍተኛው ውጤቱ የዘር ማጥፋት ወንጀል ማነሳሳት እና ማበረታታት ነው። የዘር ማጥፋት የተለየ ቡድንን አባላት በከፊል በሙሉ ለማጥፋት በማሰብ የሚደረግ አጸያፊ እና አደገኛ የወንጀል ድርጊት ነው። ወንጀለኛው ይህን አላማውን ለማስፈጸም በግድያ ብቻ ሳይሆን የተለመደ ኑሮን ለማካሄድ የሚያዳግት የአካል ወይም የአእምሮ ጉዳት በማድረስ፣ የወሊድ ሒደትን በመቆጣጠር፣ ለመኖር የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮችን በመከልከል የሰውን አድሜ በመገደብ፣ ወይም የአንዱን ቡድን አባል ወደ ሌላው እንዲካተት በማስገደደ ሊፈጽም እንደሚችል የአለም አቀፍ የወንጅል ፍ/ቤት መመሰረቻ ስምምነት ያስረዳል። እሰከ 6 ሚሊዮን የሚገመቱ የአይሁድ ዘር አባላትን የጨረሰውን የናዚ የዘር ማጥፋትን ተከትሎ የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ በዘር ማጥፋት ላይ ቆራጥ አቋም ለመያዝ ሞክሯል። በዚህም በጥር 1943 ዓ.ም ላይ ተፈጻሚ የሆነ፣ ሀገራት በውስጥ ሕጎቻቸው የዘር ማጥፋት ክልክላን እንዲደነግጉ የሚያስገድድ ስምምነት እንመሰረት ሆኖአል። በዚሁ ስምምነት ላይ የዘር ማጥፋት ማነሳሳት ተካትቷል። ድንጋጌው ለማህበረሰቡ ሊደርስ በሚችል ሁኔታ ቀጥተኛ፣ አድማጩ/አንባቢው ሊደራ በሚችልበት አካኋን፣ የዘር ማጥፋት ለማነሳሳት ወይም መልእክቱ የዘር ማጥፋን ሊያነሳሳት የሚችልበት አጋጣሚ መኖሩን እያወቀ የሚተላለፍ መልእክት የዘር ማጥፋት ማነሳሳት እንደሚሆን እና ሊያስቀጣም እንደሚገባ ይገልጻል፡፡ሕግ እና ቅጣት ብቻ አያስጥለንም!የጥላቻ ንግግርን እና የሚስከትለውንም ውጤት ለመዋጋት የወንጀል ሕግ ማውጣት ብቻውን መፍትሔ ሊሆን አይችልም። የጥላቻ ንግግርን መቅጣት ችግሩን ሊያስታግስ እንጂ ሊያክም አይችልም። ይልቁንም መንግስት በተለያዩ አጋጣሚዎች ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ እና የእኩልነት መብቶችን አብረው የሚሄዱበትን ሁኔታዎች ማበረታት ይኖርበታል። መንግስት በማኀበረሰቦች መካከል ጥላቻ የሚፈጥሩትን ሁኔታዎች ስረ መሰረት መመርመር እና መፍትሔ ለመስጠጥ መሞከር አለበት። ልዩነቶችን የሚፈጥሩ እና ተግባቦቶችን የሚሸረሽሩ የፖሊሲ፣ የሕግ እና ተቋማዊ ማእቀፎች በጥልቅ መመርመር ይኖርባቸዋል።የማህበረሰቡን መረጃ የማግኘት መብት በሰፊው በመፍቀድ የጥላቻ ንግግሮች የሀሳብ መለዋወጫ ገበያውን እንዳይቆጣጠሩት ማድረግ ያስፈልጋል። ተመዝግበው ለሚሰሩ ጋዜጠኞች በጥንቃቄ የተቀረጸ የሥነ ምግባር መመሪያ ሊሰናዳላቸው፣ የሚዲያዎቹም ባለቤቶች በግልጽ የሚታወቁበትን ሁኔታ መፍጠር ይገባል። ሚዲያዎች ገለልተኛ እና እውነተኛ መረጃዎች በማውጣጥ ብቻ ሳይሆን፤ ከኩነት ዘገባዎች ዘለል ብለው ትንታኔዎችን በመስጠት እና ለልዩነት መንስኤ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ክርክር የሚደረግበትን መድረክ በማመቻቸት ገንቢ ወይይቶችን ማበረታታት እና የጥላቻ ንግግሮችንም መመከት ይችላሉ። ተከታታይነት ያለው እና ገንቢ ውይይት የመፍትሔው ወሳኝ አካል ነው።የጋዜጠኝነት እና ግንኙነት ባለሙያው ዶ/ር እንዳልካቸውም ከሕግ በላይ መፍትሔው “ተጻራሪ የሆኑ የታሪክ አረዳድ እና አተረጓጎሞችን እንዲሁም የማይታረቁ የሚመስሉ ሀገራዊ ህልሞችን የሚያቀራርቡ እና የሚያስታርቁ ተቋማት መገንባት፣ ሕግጋትን ማርቀቅ፣ በመረጃ ላይ የተመሰረቱ የሰከኑ ውይይቶችን ማካሄድ” እንደሚመስላቸው ይገልጻሉ። የትምህርት ካሪኩለሞችን አብሮነት እና ተግባቦትን የሚያጎሉ ሆነው መቀረጽ ይኖርባቸዋል። የየትኛውም ቡድን አባል፣ የጥላቻ ንግግር ሰለባ ለሚሆኑ ቡድኖች ድምጽ መሆን ይገባዋል። ማኀበረሰቡ፣ በተለይ ወጣቱ መረጃዎችን እያጣራ በመቀበል ብቻ ሳይሆን የሀሰት መረጃዎችን ባገኘው አጋጣሚ በማጋለጥ፣ ተሰሚምነት ማሳጣት አለበት። መንግስታዊ ያልሆነ የሚዲያ ተቆጣጣሪ ተቋማት (media monitoring institutions) መመስረትም ለግጭቶች መንስኤ የሚሆኑ መልእክቶች ቀድመው እንዲታወቁ፣ የጥላቻ መልእክት የሚያስላልፈው ግለሰብ/ተቋምም የሚከታተለው እንዳለ በማወቁ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡