«ልጄ ሆይ ይህ አገር ላንተ አይሆንህም! እንቅልፍ ያለው ከተማ ነው። እዚያ ሂድ፤ ተማርና በደንብ ትተኛለህ!»
አደይ በለሆሳስ ድምፅ ተናግረው ሲያበቁ የልጃቸውን ጸጉር ማሻሸት ያዙ። ፀሐይ ቀጥቅጦትና አቧራ ቦሎበት እንኳ እንደ ተልባ ይለሰልሳል። የ10 ዓመቱ ብላቴና በናፍቆትና በተስፋ መሀል ዋለለ። የቀይ ዳማው ታዳጊ በዛሬና በነገ አካፋይ መንገድ ላይ ቆመ። ጸጥታ ከነአሰስ ገሰሱ ሰፈረባቸው። የ‹ርባ ገረድ› አንጀት እንደዚያ ቀን ውሏ ተፈቶባት፣ ቀጠሮዋ ላልቶባት፣ መቀነቷ ተንሸራቶባት አያቅም።
እርሱ ቸር እረኛ ነበር፤ ከብትና ፍየሎችን ከፊት ኾኖ የሚነዳ። ተራራሮቹን የመዳፉ ያህል፤ ጭራሮዎቹን የጣቶቹ ያህል፤ የበለስ ቁልቋሎችን የአባቱን ዳዊት ያህል ያውቃቸዋል። የልጅነቱ የትዝታ ድንግል የተገረሰሰው እዚችው ሰፈር ነው። የሕፃንነቱ የሕልም ዓለም ጉዞ ንድፍ የተወሰደው ከዚች ቀዬ - ርባ ገረድ - አድዋ - ትግራይ ነው።
መምህር ገብረ እግዚአብሔር ገ/ዮሐንስ እና ወ/ሮ መዓዛ ተ/መድኅን የመጀመርያ ትዳር አጋሮቻቸውን ሞት ነጥቋቸዋል። ሁለተኛው አብሮ የመኖር ‹ለ ሉ› ሞቅ ሞቅ ማለት ሲጀምር ደግሞ ጣልያን መጣ። ባገር ምድሩ ላይ የሐዘን ጢስ ለቀቀበት፤ የሞት እሳት አነደደበት። ቢኾንም አንድ ‹አብዮተኛ› ልጅን ከነቃጭሉ ለመውለድ ትንፋሽ፣ ጊዜና ቦታ አላጡም።
ሚያዚያ 27፣ 1928 ዓ.ም. የተወለደው ጨቅላ ሙሉ ስም ስብሐት ለአብ ገ/እግዚአብሔር ይባላል። በ1938 ዓ.ም. አዱ ገነትን ሲረግጥ ግን ስሙን ብቻ ሳይኾን ፍላጎቱን፣ እምነቱን እና የኑሮ ይትበሃሉን አሳጥሮ ‹እንግዳ› ሰው ኾኗል። ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ በ2000 ዓ.ም. ባሳተመው ጥናት ቀመስ መጽሐፉ «...የስም ዘልዛላ በቅጡ ካተሸከፈ ከሸክም በላይ ያስቸግራል። ስለዚህ ስሙን ከርክሞ ለአጠራር እንዲመች አደረገው።
እንግዲህ ልብ ካልነው ሰውየው በቀጣይነት በአኗኗሩ ውስጥ የሚያጋጥሙትን የተንዛዙ ምኞቶችና ተስፋዎች ሁሉ እየቆረጠ በመጣል ጣጣ ፈንጣጣ የማያውቅ የብሕትውና ዓይነት ድባብ እንዲኖረው አድርጓል፤» ሲል አዲስ አበባና ስብሐት እንዴት እንደተዋሐዱ ያስረዳል። የአራዳ ልጆች ዝርዝር ኪስ ይቀዳል የሚሉት ለካስ ወደው አይደልም።
ከተማ እንዲህ ነው! ለሁሉም ክፍት ስለኾነ ከሁሉም ይቀበላል፤ ከሁሉም ስለሚቀበል ለሁሉም ለመስጠት ወደ ኋላ አይልም። ከተማ ይህን ይመስላል! ትላንት ቀድመህ ብትመጣ ጉዳዩ አይደለም፤ ዛሬ ዘግይትህ ከች ብትልም ከቁብ አይቆጥርህም። ጨዋታው ያለው የእሴት ተፈላጊነት እና ትውልድ ተሻጋሪነት ላይ ነው። ደግሞ እንዲህ ስልህ ሩጫው ቀላል እንዳይመስልህ፤ ፉክክሩ የዋዛ አይደለም፤ ጥሎ ማለፉም ወኔ ይፈትናል። የእብድ ገበያ ልትለው ትችላለህ።
ዋጋው በሻጩ አይወሰንም፤ ጥራቱ በቦታ አይለካም፤ ብዛቱ በቀኑ አይታይም። በዚያ ላይ ጥድፊያው እረፍት አይሰጥም፤ ትንፋሽ ይጠይቃል። ዳር ቆመህ አትታዘበውም፤ ያለህ አማራጭ ገብተህ መዋኘትና ለብዙሐኑ የሚተርፈውን የባህል አቅምህን (Cultural capital) ማሳየት አለብህ። ከዚያ ማስተዋወቅ፤ ከዚያ ማበልጸግ፤ ከዚያ ማስተላለፍ፤ በመጨረሻም የጋራ እሴት (Shared value) አድረገኸው እርፍ።
Sennet R. (1970) የከተማ አየር ነዋሪውን ነጻ ያደርጋል (city air makes people free) ይላል። በርግጥ እርሱ አየሩ ሲል የምንስበው አየር ማለቱ አይደልም፤ ከዚያ ራቅ ይላል። ይሄኛው ነጻነት ለፈጠራ የሚያነሳሳ ነው፤ ለአዲስ ነገር የሚያደፋፍር ነው፤ ወደ ምርምር የሚያንደረድር ነው፤ ለልዩ ልዩ ዘይቤዎች በር የሚከፍት ነው።
Redfield እና Singer የተባሉ የማኅበራዊ ሳይንስ አጥኝዎች በበኩላቸው ከተሞች የባህል እና የማኅበረ-ፖለቲካ ለውጥ መፈትፈቻ ድስት ናቸው ሲሉ ይከራከራሉ። In addition to maintaining tradition and transmitting it, cities are also centers of change. Much of the change that occurs in the great tradition and become the new orthodox takes place in the city.
በዚህ የፍትፈታ ትርምስ ላይ ተጠርተህ ልትመጣ ትችላለህ፣ በእንግድነት ዱቅ ልትልም ትችላለህ ወይም እግር ጥሎህ ዘው ብለህም ይኾናል። የድርሻህን ከጎረስክ በኋላ ግን ታመሰግናለህ (‹ሼም› የምታውቅ ከሆነ ማለቴ ነው)። ከዚያም የጎደለውን ሞልተህ፤ የበዛውን ቀንሰህ፤ የሚያጣፍጠውን ጨምረህ የተሻለ ፍትፍት ለማሰናዳት ታስባለህ።
በዚህ ውለታ ስር የወደቁት ስብሐት፣ በዓሉ ግርማ፣ ጸጋዬ ገ/መድኅንና ሌሎች ታላላቅ ባለ-ሀገሮች ዘመን ተሻጋሪ የጥበብ ሥራዎችን አበርክተውልን አልፈዋል። ከገጠር ኮብልልው ከተማ ከች ቢሉም አሪፎች ስለነበሩ የፒያሳን ሙድ ባነውበታል፤ የአራዳነትን ልክ ነቅተውበታል፤ የጭስነትን መልክ ቀድመው ሹፈውታል።
እንደመታደል ወይም እንዳለመታደል የኔ ዘመን መንፈሱ ከዚያ ይለያል። እጅጋየሁ ሽባባው ‹ጉድ ፈላ› በተሰኘ አልበሟ «አንተ ያገሬ ልጅ መዋያህ ከማማ፤ መጣሁ ካንተ ላድር ሰለቸኝ ከተማ» ትላለች። በጊዜው እየቀለደች መስሎኝ ነበር። ዛሬ ላይ ባለቅኔዋ ትክክል ትኾን እንዴ ስል መጠየቅ ጀምሬያለሁ።
ከተሜነት የፍርሐት ጋቢ ተከናንቧል። የከተማው ትርክት የሽሽት ዳዋ ወርሶታል። Philip Mayer (1961) ይህንን ውጥንቅጥ ‹የአፍሪካ ከተሞች ተቃርኖ› ይለዋል። እኔ ደግሞ ‹ገተሜ› እለዋለሁ። ወይ የገጠሩን (anti-city or folk society) እሴት ወርሶ ቁጭ አላለ፤ ወይ የUrbanization መንገድ አልተከተለ፤ አለበለዚያም ሀገር በቀል የከተሜነት ርእዮት አልፈጠረ። መደናገር ብቻ!
ነቄዎቹ ተወልደዋልን?
አክሱም ላይ መቆም ራስ ያዞራል። ሐውልቶቹ ስር ቁጭ ማለት አንጀት ያላውሳል። በከተማዋ ስዞርም ዘንቢል ሙሉ ጥያቄ፣ ኩንታል ሙሉ እንቆቅልሽ ተሸክሜ ነው። የትላንቷ አክሱም በሦስት ቋንቋ (ግዕዝ፣ግሪክ፣ ሳባ) የምትጽፍ፣ ከሦስት ቋንቋ በላይ የምታወራ ነበረች። ዶረሴ (1957)፣ፓንክረስት (1961)፣ኪርዋን (1972a, 1972b)፣ ስርግው (1972) እና ሽመልስ (2010) እንደሚያስታውሱን የትላንቷ አክሱም በብዝሐ ባህል የምታጌጥ ግብፃውያን፣ ሱዳኖች፣ የመናውያን፣ የምስራቅ ሜድትራንያን (ፊንቄያውያን፣ ግሪኮች፣ የጥንት ሶሪያውያን) ሞልተው የፈሰሱባት እንዲሁም ህንዶችና ቻይናውያን የቀን እንጀራቸውን የሚያበስሉባት የፈካች ከተማ ነበረች።
በዛሬዋ አክሱም የኮብል ስቶን መንገዶች ሳዘግም እንደ ታሪክ ባለዕዳ ተሳቅቄ ነው። በደረቁ ዛፎች መሀል እና አንገት በደፉ ቤቶች በር ፊት መጓዝም ቁጭት ያስታቅፋል። በርግጥ ልቡ አንደ ቄጠማ ርጥብና ገር የሆነው ነዋሪ ያን ጭንቀት ያስረሳል።
በኢትዮጵያ የከተሞች ታሪክ ውስጥ አክሱም ከቀዳሚዎቹ ተርታ ትሰለፋለች። እድሜ ለአዱሊስ ወደብ ይኹንና ከተማዋ የደራና የሞቀ ገበያ ነበራት። በዚህ ገበያዋ ሻጩን ከገዢ፤ ነጩን ከጥቁሩ፤ዐረቡን ከኤሽያው ታገናኛለች። በዚህ የመተዋወቅ አጋጣሚ ባህል፣ የመቀባበልና የመለማመድ ድግግሞሽ ውስጥ አዳዲስ የኪነ ሕንጻ፣ የንግድና የአስተዳዳር እውቀቶች እንዲበለፅጉ አስችሏል።
በርግጥ ዘመናዊ ከተማ በአስተዳደር፣ በመሠረተ ልማትና ከሌሎች ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ ሲታይ በኢትዮጵያ የተጀመረው በ19ኛው መ/ክ/ዘመን እንደኾነ ይታመናል። በዋነኝነት ከተሞቹ አመሠራረታቸው በወታደራዊ ካምፕነት (ጎንደር፣ አንኮበር)፤ በፖለቲካ አስተዳደር ማዕከልነት (መቀሌ)፤ በኢኮኖሚ ክስተት ደግሞ በምድር ባቡር ዝርጋታ የተመሠረቱ (ድሬድዋ፣ ሀረር) ናቸው።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከዛሬ 52 ዓመት በፊት (በ1959 ዓ.ም.) የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን እንዳስታወቀው የዛሬዋን ኤርትራ ጨምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ 248 ከተሞች የነበሩ ሲኾን የከተማው ሕዝብ ብዛትም ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ሕዝብ 8 በመቶውን ብቻ ይይዝ ነበር።
በ2004 ዓ.ም. በወጣው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን መረጃ መሠረት ደግሞ በመላ ሀገሪቱ 973 ከተሞች ያሉ ሲኾን ከአጠቃላይ ሕዝቡም 17 በመቶ የሚሆነው በነዚህ ከተሞች ውስጥ ይኖራል። ይህም ማለት ቀሪው 83 በመቶው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁንም ገጠሬ ነው ማለት ነው። በቅርብ ግዜያት የሚወጡ መረጃዎች ደግሞ 20 በመቶ ኢትዮጵያዊ በከተማ እንደሚኖር ያሳያሉ።
የከተማ እድገት እንዲህ እያነከሰም እንኳ ከገጠር ወደ መሀል አገር የሚደርገው ፍልሰት እንደ ጉድ ነው። ፖለቲካው ተቦክቶ የሚጋገረው ከተማ ነው፤ ትምህርት ተጠብሶ የሚበላው እዚያው ከተማ ነው፤ ንግዱ የሚደራው የከተማውን ሙቀት ተከትሎ ነው። በ1970 ዎቹ ለሥራ ፍለጋ ወደ ሀዋሳ የሚተሙ ወጣቶች አንዲት መዝሙር ነበረቻቸው፡-
«ጉዞዬ ወደ ሀዋሳ
ሀዋሳ ብር ባካፋ
ዱቄት በጣሳ»
ይሉ ነበር። በሌላ በኩል ሥነ ጥበቡም ተጠንስሶ የሚጠመቀው ከተማን ታኮ አድርጎ ነው።
«ካራዳ ልጆች ጋር አብረው ቢሰደዱ
ቢያገኝ ያበላል ቢያጣም ያዝናል ሆዱ» ያለው ዘፋኝ የከተሜነት ጣዕም ቀምሶ ይመስለኛል።
ዛሬ ዛሬ የሀገሬ ከተሞች ቅርጽና ጸባይ እየተለወጠ ነው። መንግሥት በሚያከናውናቸው የመሠረተልማት ማስፋፋት ሳቢያ ከተሞች በአንጻራዊነት ለኑሮ ምቹ ሆነዋል። ባለሀብቱ በበኩሉ መሠረተ ልማቱ በፈጠረለት አጋጣሚ የንግድ ተቋማትን አስፋፍቷል። በዚህም ምክንያት በከተሞች የሚኖረው የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። ይህም የማኅበራዊ
ሕይወት አደረጃጀት፣ አሰላለፍና አካሄድ ላይ የሚታይ ለውጥ ፈጥሯል። አብሮነት፣ የላይ የላይ ግንኙነት፣ኢ-መደበኛ እና መልኮቻቸው የተውሶ እየኾኑ ይገኛሉ። ማቀፍን ሳይኾን መግፋትን እየተከተሉ ነው። ይህም እንኳን ከሩቅ የመጣውን ሊያለምዱ ይቅርና ለራሳቸውም ሰው የነጻነት አየር መንፈግ ጀምረዋል።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከተሞች የሥልጣኔ ማሳያ መስታወት ናቸው፤ የሀገራዊ እውቀት ከፍታና ዝቅታ መለኪያም በከተሞች እየተወሰነ መጥቷል። እናም የመንገዱ ዳር ሁሉ በካፌና በፔንስዩን ከተወረረ፤ ካንጀት ጠብ በማይል የታሪክ ሽሚያ ላይ ጉልበትህን ከጨረስክ፤ ለጎረቤትህ ጀርባ ሰጥተህ ማኅበረሰቡ ለፈበረከው ዘውግ ፊትህን ካሳየህ፤ ብዝሐ ቀለማትን ማየት
ተስኖህ ‹አንድ አምፖል አንድ መብራት› እያልክ ካላዘንክ፤ አደባባዮችህን ከፈጠራ ማሳያነት ወደ ኃይል ማሳያነት ከቀየርክ... ወዳጄ የከተሜነት ጀምበር እያዘቀዘቀች መሆኑን ተረዳ።
City of Fear?
ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የአሜሪካዋ የንግድ ከተማ ኒው ዩርክ በፈላስፎች ቁጥር ቁንጮ ኾነች የሚል ዜና ተሰምቶ ነበር። በወቅቱ መረጃውን ለየት ያደረገው ከሌላኛዋ የትምህርት ተቋማት ማዕከል ከኾነችው ቦስተን ደረጃውን መንጠቋ ነበር። የብዝሐ ባህል፣ እሴትና ታሪክ መናኽርያ የሆነችው ኒው ዩርክ በሰፋፊ የእግር መንገዶቿና ማሰላሰያ ቦታዎቿ አማካኝነት የፈጠራ ቋት እንድትኾን አስችሎታል።
በሌላ በኩል እንደ ኬንያዋ ናይሮቢ የሚያስጨንቁ፣ እንደ ብራዚሏ ሳኦ ፖሎ የሚያስፈሩ ከተሞችም አሉ። ሥርዓት አልበኝነት፣ ሥራ አጥነትና ሌብነት ሲጎመራ ከተሞቹ በሕገ ወጦች ይታመሳሉ። የሀገሬ ከተሞች በሁለቱ ተቃርኖ መካከል ዥዋዥዌ እየተጫወቱ ነው። የችግሩ ምንጭ ብዙ ቢኾንም ከማኅበረሰብ ጥናት (Sociology) አስተምሕሮ አንጻር በሦስት ዋና ዋና ሐሳቦች ላይ ልናስቀምጠው እንችላለን።
- የማኅበራዊ ትስስሩ መላላት (Social network የሚባለው)። ወጪና ወራጅ በበዛበት ከተማ ባህሉን፣ ኢኮኖሚውንና ሃይማኖቱን ተጠልለው የሚገመዱሉ ማኅበራዊ ትስስሮች እንደሚኖሩ እሙን ነው። Michel (1996) እና Bolsevic (1974) እንደሚያስረዱት እነዚህ ገመዶች የጊዜ ፈተናን ከተቋቋሙና በለውጥ ውስጥ ራሳቸውን እያከሙ ከሄዱ ውለው አድረው ጠንካራ የአንድነት መቀነት መሸመናቸው አይቀሬ ነው። ታክሲ ውስጥ የምንጋራት ወንበር፤ ት/ቤት ውስጥ የምንካፈላት ፓስቲ፤ ከቀብር መልስ የምንጋራው ንፍሮ፤ ሥራ ላይ የምንካፈላት ‹ትሪደንት› ማስቲካ፤ መስጊድ ውስጥ የምንሰጣጣት ውኃ፤ ሰፈር ውስጥ የምንዋሳት ጭልፋ ሁሉ ትርጉም አላት። ይኹን እንጂ ለማኅበራዊ ግንኙነቱ መጠናከር የሚረዱ ግብአቶች እጥረት ሲገጥም ማለትም የኢኮኖሚ ልዩነቱ ሲሰፋ፣ ፍትሕ በአፍጢሟ ስትደፋ፣ ነዋሪውን እንቁልጭጭ የሚል አስተዳደር ሲሰፍን፣ የብሽሽቅ ፖለቲካው እስከ ጓዳ ገብቶ ሰላም ሲነሳ የጋራ ትዝታዎችና የጋራ ተስፋዎች እየመነመኑ ይመጣሉ።
- የማኅበራዊ ተቋማት መዳከም (Social organization የሚባለው)። እኔን ያሳደጉኝ ቤተሰቦቼ ብቻ አልነበሩም፤ የሰፈሩ እናቶች፣ አባቶችና መላው አድባር ጭምር እንጂ። እናም ጸባይ፣ አስተምህሮ እና አመለካከት ላይ ዘመን አመጣሽ ባህል ለመጫንም ሆነ ለማውረድ ያው አስተዳደጋችን እና አዋዋላችን ጉልህ ሚና አለው። ዛሬ የሀገሬ ዋና ዋና ከተሞች ትላልቆቹን ከትናንሾቹ፣ ፍንዳታዎቹን ከጎልማሳዎች፣ ባልቴቶቹን ከነብር ጣቶቹ ጋር የሚያገናኝ ድልድይ አጥተዋል። በዚህም የእውቀት ቅብበሎሹ፣ የተሞክሮ ልውውጡ እና የሞራል ውርርሱ ተመናምኖ - ተመናምኖ አንድ ሐሙስ ቀርቶታል። መንደሮቹ ባለቤት እያጡ ነው። ከተሞቹ የሥነ ምግባር መሪ እያጡ ነው። ባለፉት ጊዜያት የኛነታችንን መልክ የቀረጹት ተቋማት (ቤተሰብ፣ ት/ቤት፣ ሃይማኖት) እንኳን ለሌሎች ሊተርፉ ራሳቸውን ማነጽ ከብዷቸዋል።
- የማኅበራዊ ሀብት ማጣት (Social capital የሚባለው)። በርግጥ በከሰረ ማኅበራዊ ተቋምና በተበጣጠሰ ማኅበራዊ ትስስር ውስጥ ኾኖ የጋራ የሆነ ማኅበራዊ ሀብት አተርፋለሁ ማለት የዋህነት ነው።
እናስ መንገዱ ወዴት ይወስዳል?
በ2007 ዓ.ም. ለሕትመት የበቃውን ‹ሰልፍ ሜዳ› የተባለ መጽሐፍ ባነበቡኩት ቁጥር ትላንት ተጽፎ ዛሬ ለንባብ የበቃ ይመስለኛል። ደራሲው ግርማ ተስፋው በአንዲት ጭርንቁስ ሰፈር (ሰልፍ ሜዳ) አማካኝነት የከተማን ድብልቅልቅል ሕይወት (ቀበሌ 29ና 30 ልብ ይሏል)፣ ንግድ (የአብዱላ ሻሂ ቤት)፣ ፖለቲካ (የሙዚቃ መምህሩ አሽኔ)፣ ተስፋ (ወፍጮ ፈጪው ንጉሤ)፣ ፍቅር (ለዓለም)…እና ሌሎች አይረሴ የከተማ ታሪኮችን አጋርቶናል። የአብሮ መኖር ትርጉሙ ጥልቅ ነው፤ ክፉና ደጉን በጋራ ማሳለፍ ረቂቅ ነው። ይኹን እንጂ አብሮ መኖርም የሚፈተንበት ቀን ይመጣል። ግርማ ከአብዮት በኋላ ላለው የብቸኝነት ኑሮ ተዘጋጁ ይላል።
«በጋራ ማበድ ትተን፤
ከአብዮት ማዶ፣ ከድል ማዶ፣ ከሽንፈት ማዶ ወዳለ ብቸኝነት መጣን
በየዋሻችን ልንከተት፤ የህልውናችንን ጭነት ልንሸከም»… (ገጽ 78)
ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የማኅበረሰቡ ገመና ታይቷል፤ ባህሉ ተጠይቋል፤ ሰውነቱ ተፈትኗል። ከተሞች ለችግሮች መፍትሔና ለጋራ ነገ አዋጭ መፍትሔ የሚቀረጽባቸው አደባባዮች ናቸው። ይህ ተዘንግቶ የልዩነት እና የንትርክ ምንጭ ወደ መሆን ካዘነበለ አደጋ አለው። Nik Hanita bt Nik Mohamad እና Lar. Zulkefle bin Hj Ayob (2013) ‘Urban Life and the Changing City’ በተሰኘ የጥናት ወረቀታቸው እንደሚመክሩት ከተሞች የትላንት ትዝታዎች ማስታወሻ፣ የዛሬ መኖሪያ ብቻ ሳይኾኑ የነገ ሕልሞች መፍቻ ቁልፍ የያዙ ናቸው።
ስለኾነም ወደ ሰውነታችን እንመለስ፣ ማኅበራዊ ሕይወታችንን እናስቀጥል፣ ጊዜ አመጣሽ አጥሮችን እናፍርስ። ምክንያቱም ይህን የመራራቅ ጊዜ የምንሻገረው በመተዋወቅ ነው፤ ይህን የመናናቅ ጊዜ የምናመልጠው በመከባበር ነው፤ ይህንን የመነጣጠል ጊዜ የምናልፈው በፍቅር ነው። «ከወረስነው ቂም ይልቅ የምናወርሰው ፍቅር ይበልጣል» እንዲል ቴዲ አፍሮ። ተስፋ አለኝ፤ አዎ እናልፈዋለን!