ታህሣሥ 2 ፣ 2011

የአቶ በረከት አገር አቀፋዊ የፖለቲካ መዋቅር ትሥሥር ከሰመ

ዜናዎች

አቶ በረከት ስምዖን (በሚንስትር ማዕረግ) ይመሩት የነበረው የፌዴራል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት፣ በሀገር ውስጥ ወደ ታች እና ወደ ጎን የዘረጋው ፖለቲካዊ…

የአቶ በረከት አገር አቀፋዊ የፖለቲካ መዋቅር ትሥሥር ከሰመ
 አቶ በረከት ስምዖን (በሚንስትር ማዕረግ) ይመሩት የነበረው የፌዴራል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት፣ በሀገር ውስጥ ወደ ታች እና ወደ ጎን የዘረጋው ፖለቲካዊ የትሥሥር መዋቅር፣ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ውሳኔ፣ ከአናቱ ጀምሮ ወደ ጎን እና እስከ ታች (ወረዳ) ድረስ ከአገልግሎት ውጪ ኾኖ እንዲከስም መደረጉን ምንጮች ለዘጋቢያችን አስታወቁ።የጽ/ቤቱ ሠራተኞች ወደ አራት የመንግሥት ተቋማት የተመደቡ ሲኾን፣ ሁሉም ተቋማት ለተመደቡት ሠራተኞች ተቋማቸውንና አሰራራቸውን ለማስተዋወቅ የሁለት ቀን ሙያዊ ሥልጠና (ኦረንቴሽን) እንደሰጡ ለማረጋገጥ ተችሏል። በቀጣይም፣ በየተቋማቱ ያለ ሥራ የተቀመጠው የኮሙኒኬሽን መዋቅር ሙሉ ለሙሉ ይከስማል ተብሏል።የኮሙንኬሽን ጽ/ቤት ሠራተኞች አጠቃላይ የንብረት ርክክብ ዓርብ፣ ቅዳሜ፣ እሁድ፣ ሰኞ እና ረቡዕ ኅዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም. አከናውነዋል። ሐሙስና አርብ ሙያዊ ሥልጠናቸውን እንደጨረሱ አዲሱን ሥራቸውን ሰኞ እንደሚጀምሩ ታውቋል።አቶ በረከት ስምዖን በሚንስትር ማዕረግ ይመሩት የነበረው የፌዴራል ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ወደ ጎን የክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮዎችን፣ በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱና ድርጅቶች ያሉ የኮሙኒኬሽን መዋቅሮችን በዳይሬክቶሬት ደረጃ የሚሾሙ ዳይሬክተሮችን በፖለቲካዊ ታማኝነት ብቻ ከየትኛውም ሙያ በመመልመል፣ በመሾምና ፖለቲካዊ አቅጣጫ በመስጠት ለፕሮፓጋንዳ ያሰማሩ እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል።ወደ ታች በሚገኝ የቀጥታ የፖለቲካ መዋቅር ደግሞ የዞን ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት፣ የወረዳ ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት እና የቀበሌ የኮሙኒኬሽን የሥራ ሂደት መሪ ለተባሉ ካድሬዎች የቀጥታ የፕሮፓጋንዳና የፖለቲካ ትእዛዞችንና አቅጣጫ በማውረድ በፈለጉት ቀን 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መፈክር አስጽፈው፣ ባነር አሳትመው፣ መሪ ቃል ሰይመው ትልቅ የድጋፍ ሰልፍ ማከናወን ይችሉ ነበር ሲሉ የውስጥ ምንጮች ለዘጋቢያችን አስረድተዋል።ጽ/ቤቱ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የመንግሥትና የሕዝብ ብዙሐን መገናኛዎችን (የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢ.ዜ.አ)፣ ፕሬስ ድርጅት፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣና መጽሔት፣ ኢትዮጵያን ሔራልድ እንግሊዝኛ ጋዜጣ፣ ዓል አለም ዐረብኛ ጋዜጣ፣ በሪሳ አፋን ኦሮሞ ጋዜጣ) የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን ይመራል፤ አቅጣጫ ሰጥቶ ያሰራል።በአቶ በረከት የተቀየሰው የሀገሪቱ የሚዲያ ሥርዓት በገዢው ፓርቲ ርእዮተ ዓለም የተቃኘ እንዲኾን እና የፕሮፓጋንዳ አመንጪና መሣሪያ ኾኖ እንዲሠራ የተደራጀ ሲኾን፣ ዋልታ እና ራዲዮ ፋናም በተዘዋዋሪና በቀጥታ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ርእዮተ ዓለም አስፈጻሚዎች ነበሩ ሲሉ ምንጮች ለዘጋቢያችን አብራርተዋል።ከወር በፊት ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሚንስትር መሥሪያ ቤቶችን እንደ አዲስ ባዋቀሩበትና ባጣመሩበት ወቅት የፌዴራል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት እንዲከስም ውሳኔ አሳልፈው በጽ/ቤታቸው ስር የፕሬስ ሴክሬቴሪያት እንዲቋቋም አድርገዋል። በአሁኑ ወቅት ቀደም ሲል የመንግሥት አቋም የሚገለጽበት የአቶ በረከት አሰራር ተቀይሮ፣ በፕሬስ ሴክሬቴሬያት አማካኝነት በሀገሪቱ የሚከወኑ ጉዳዮች ላይ ተንተርሶ መረጃ የሚሰጥ ሆኗል ብለዋል።አዲሱ የተግባቦት አሰራር የየተቋማቱን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት መዋቅርን ይቀይራል፤ የአሰራር ሥርዓቱ ይለወጣል፤ የሰው ኃይሉንም ሊለውጥ እንደሚችል ፍንጮች አሉ ብለዋል።ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ፣ የቀድሞው ማስታወቂያ ሚንስቴር ከሕዝብ ጋር ምንም ዓይነት የሠመረ የተግባቦትና የፕሮፓጋንዳ ሥራ አላከናወነም በሚል በአቶ መለስ ዜናዊ የያኔው (ጠ/ሚ) ፖለቲካዊ ውሳኔ መሠረት አቶ በረከት ስምዖን በሚንስትር ማዕረግ የፌዴራል ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤትን ማቋቋማቸውን እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን (ኢ.ዜ.አ) ደግሞ ተጠሪነቱን ለአቋቋሙት ጽ/ቤታቸው በማድረጋቸው ኢ.ዜ.አ እንደተዳከመ እና ከሁለት ዓመት በፊት ግን መልሶ በቦርድ መዋቀሩን የዜና አገልግሎት ሠራተኞች ይናገራሉ።የፌዴራል ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሲከስም በሥራ ሂደት ውስጥ ከነበሩት ከሁለት መቶ አርባ ሰባት (247) በላይ ሠራተኞች፡- ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት 31 ዓላማ ፈፃሚ የሰው ኃይል፣ 35 ድጋፍ ሰጪ የሰው ኃይል፤ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን 27 ዓላማ ፈፃሚ የሰው ኃይል፣ 31 ድጋፍ ሰጪ የሰው ኃይል፤ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት 27 ዓላማ ፈፃሚ የሰው ኃይል፣ 33 ድጋፍ ሰጪ የሰው ኃይል፤ ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን 30 ዓላማ ፈፃሚ የሰው ኃይል፣ 33 ድጋፍ ሰጪ የሰው ኃይል መመደባቸውን ለማረጋገጥ ችለናል።ከጽ/ቤቱ ሠራተኞች ውስጥ የተወሰኑ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው ካድሬ የፖለቲካ ተሿሚዎች በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የመንግሥት (የሕዝብ)፣ የግል እና የማኅበረሰብ ብዙኋን መገናኛዎችን (የሕትመት፣ ኤሌክትሮኒክስ እና ማኅበራዊ ሚዲያዎች)ን በተለይ የግል ሚዲያውን በብሮድካስት ባለሥልጣን በኩል በትሥሥር በመከታተል (ሞኒተሪንግ) እና ለመንግሥት ተስማሚ፣ ተቃዋሚ እና ተቺ የሚል ብያኔ በመስጠት በግሉ ሚዲያም ሆነ በመንግሥት ሚዲያ ለሚታሰሩና ለሚሰደዱ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን፣ ከወረዳ ካድሬዎች ጋር በመቀናጀት የተወሰኑ ጋዜጦች፣ መጽሔቶችና ድረ-ገፆች ማተሚያ ቤት ሕትመት እንዲከለከሉና እንዲዘጉ ምክረ-ሃሳብ አቅራቢዎች ናቸው፣ አሁን ሙያዊ ሥራ ለመሥራት ድንጋጤ ውስጥ ገቡ ሲሉ ምንጮች ለዘጋቢያችን ገልጸዋል።ከሁለት ዓመት በፊት በዚህ የክትትል መስክ ላይ የነበሩ 98 ተሿሚ ካድሬዎች (ጋዜጠኞች ተብለው) በኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት በሞኒተሪንግ፣ ሪሰርች እና በኃላፊነት ተሹመው ይሰሩ የነበሩ ሲኾን፣ የተወሰኑትም በዝውውር ወደ ፕሬስ ድርጅት፣ ኢ.ዜ.አ፣ ኢ.ቢ.ሲ እና ብሮድካስት ኤጀንሲ ውስጥ ኾነው ነበር ብዙሐን መገናኛውን የሚጠረንፉት ብለዋል- ምንጮቻችን።  

አስተያየት