You can paste your entire post in here, and yes it can get really really long.
“መብራት ሠራተኞቹ የጎዳና ተዳዳሪዎች”“በአንድ በተረገመ ቀን መብራት ጠፍቶ ነበር፤ ቤት ውስጥ ማንም ስላልነበረ ጨለማውን ለመግፈፍ ሻማ ለኮስኩኝ። ብዙም ሳልቆይ እንቅልፍ ወሰደኝ። በሕልሜ ይኹን በእውኔ የማላውቀው የሰዎች ጩኸት ከእሳቱ እንዳመልጥ እየነገሩኝ ነበር፤ በድንጋጤ ወደውጨ ወጣሁኝ፤ እያየሁት ቤታችን እንዳልነበረ ኾነ፤ በሕልም እንዳልኾነ የተረዳሁትም በዚህ ጊዜ ነበር። ከቀድሞው ይልቅ የባሰ ድቅድቅ ጨለማ ዋጠኝ፤ ከምኖርበት ለገጣፉ እግሬ እንደመራኝ ተጓዝኩ። ከቤት እንደወጣሁ ቀረሁኝ።” በማለት በጸጸትና በእልህ ይናገራል።የ14 ዓመቱ ያሬድ (ባቡጄ) የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በጥሩ ውጤት አጠናቅቆ ለመሰናዶ ትምህርት ቢዘጋጅም የአዲስ ዓመት ብሩህ ተስፋው እንደጨለመ ግን አምኗል። የጎዳናን ሕይወት ከጀመረም አንድ ወር አካባቢ እንዳስቆጠረ ይናገራል። ስሜቱ ምን ያህል እንደተጎዳ ከአነጋገሩ በላይ የፊቱ መቋጠርና የሚነበበው የሐዘን ድባብ በቂ ማስረጃ ነው። የለበሰው ልብስ ንጹሕ መኾን (ከሌሎች መሰሎቹ አንጻር ሲወዳደር) እና የፊቱ ወዘና የጎዳና ሕወትን በቅርቡ እንደተቀላቅለ እማኝ ናቸው። ሲናገር ማቀርቀሩ የአዲሱ ጉዞ ጅማሬው በስጋት እንደተከበበ ያስብቃል። እንደ ያሬድ ዓይነት ተስፋን ሰንቀው ግን እንደ ጉም የተነነባቸው ምን ያህል ይኾኑ? መረጃዎች ምን ይላሉ ?ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በዓለም ላይ 100 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች ኑሯቸውን በመንገድ ያደረጉ ናቸው፤ ከነዚህም ውስጥ 10 ሚሊዮኑ አፍሪቃውያን ናቸው። በ2012 ዩኒሴፍ ባወጣው ጥናት በኢትዮጵያ 600, 000 የሚጠጉ የጎዳና ተዳዳሪዎች አሉ። (የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቁጥሩን ወደ 150, 000 ዝቅ ያደርገዋል።) በዘርፉ የተደረጉ ምርምሮች እንደሚያሳዩት አዲስ አበባ 74.8 ከመቶ ፣ባሕር ዳር 71.9 እንዲሁም ናዝሬት 77.5 በመቶ በመያዝ ከፍተኛውን ቁጥር ያስመዘገቡ ከተሞች ናቸው።ሁለት ዓይነት የጎዳና ሕይወት አለ፤ ውሎና አዳራቸው ሙሉ ለሙሉ በጎዳና ያደረጉና ቀን ቀን በጎዳና ውለው (የመብራት ሠራተኞች) ማደሪያ ተከራይተው የሚኖሩ ተብለው ይከፈላሉ። ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ኑሮአቸውን በጎዳና ያደረጉት ናቸው። (በተመረጡ የኢትዮጵያ አራት ከተሞች ላይ የተደረገ ጥናት፣ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ከአየርላንዱ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኮርክና ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ጋር በመሆን 1993) ::እንደ ዩኒሴፍ መረጃ 150, 000ዎቹ በአዲስ አበባ ይኖራሉ የተባሉት ልጆች እድሜያቸው ከ6 እስከ 16 እንደሆኑ ይገመታል። ከነዚህ ታዳጊዎች መካከል 29 በመቶ የሚኾኑት ብቻ ልጆችን ከጎዳና በማንሳት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዳሉ ያውቃሉ። የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገረቻቸው ልጆችም ምንም እንደማያውቁ ገልጸዋል።በአፍሪካ ዋና ከተሞች ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች እንደሚገኙ በ2012 የተሠራው የዩኒሴፍ ጥናት ያመለክታል። በተለይም በግብጽ (በካይሮና አሌክሳድሪያ) ፣ በጋና (አክራ) እና በተለያዩ ዋና ከተሞች ይኖራሉ። ለዚህም እንደምክንያት የሚጠቀሰው በከተማ አካባቢ የተሻለ የሥራ እድል ለማግኘት እንደሆነ ጥናቶች ያትታሉ፤ ሌላው የቤተሰብ ፍቺ፣ የአቻ ግፊት እንዲሁም የገንዘብ አቅም ማነስ (ዝቅተኛ ገቢ ) ናቸው። ገፊና ሳቢ ምክንያቶችየ9 ዓመቱ አቤል ፒያሳ አካባቢ ጎዳና ላይ መኖር ከጀመረ ሦስት ወራት አስቆጥሯል፤ ወላጆቹ በፍቺ በመለያየታቸው ምክንያት ከሁለት ወንድምና እኅቶቹ ጋር ከአባታቸው ጋር መኖር ቢጀምሩም የአባቱ በየቀኑ መስከርና ልጆቹን መደብደብ ለዚህ ሕይወት እንደዳረገው በሐዘን ይናገራል። ደቃቃ ሰውነቱ እና በላዩ ላይ ያለቀው ልብሱ የጎዳና ሕይወት አስከፊነት ማሳያ ናቸው። እነዚህ ሕፃናት የምግብ አቅርቦት ከአንድ በጎ አድራጊ ግለሰብ ቢያገኙም ማደሪያቸውን ግን የሰው ፊት ገርፏቸው በየቀኑ 15 ብር እየከፈሉ በየቪዲዮ ቤት እንደሚያድሩ ይናገራሉ።አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች እንደሚሉት አብዛኞቹ በሚባል ደረጃ በቤተሰብ ፍቺ ምክንያት የጎዳና ሕይወት ሰለባ ሆነዋል፤ ሁሉም ወደቤተሰባቸው መመለስ እንደሚፈልጉ ቢናገሩም ምንያህል ቤተሰብ ለመቀበል ፍቃደኛ እንደኾነ ስጋት እንዳላቸው ግን መሸሸግ አልቻሉም። ልጆችን ወደቤተሰብ የመመለስ ሥራ በምግባረ ሰናይ ድርጅቶች ጥረት ቢደረግም ብዙም ውጤታማ እንዳልኾነ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሞያዎች ይናገራሉ። የቤተሰብ የገቢ መጠን ዝቅተኛ መኾንና የልጆቹ በተለያዩ ሱሶች መዘፈቅ እንደመንስኤ ይጠቀሳል።የፍልሰቱ አቅጣጫ ከወዴት?እንደ ዶምቦስኮ ልጆች ት/ቤት ዲን እንዳልካቸው ባዩ የልጆቹ ፍልስት ወቅትን መሠረት ያደረገ (seasonal) ነው፤ አንዳንዴ በርካታ ሰዎች ከአማራ ክልል ሲመጡ በሌላ ጊዜ ደግሞ ከደቡብ አካባቢ እንደሚመጡ ባደረጉት ተከታታይ ምርመራ እንዳውቁ ይናገራሉ።የኤልሻዳይ ሪልፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን የሚዲያ ዳይሬክተር ነጋሽ በዳዳ በበኩላቸው በርካታ ቁጥር ያላቸው ልጆች ፍልሰት ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ከደቡብ ፣ ከትግራይና ከኦሮሚያ ክልል (በተለይ ከአዲስ አበባ ዙሪያ) እንደሚመጡ ይናገራሉ። የዝግጅት ክፍላችን ባደረገችው ዳሰሳም በርካታ ታዳጊዎች ከደቡብ እና ከአዲስ አበባ ዙሪያ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።በተለይ በፒያሳ አካባቢ ልጅ ያዘሉ ወጣት ሴቶች፣ ለመውለድ የደረሱ እርጉዞች ፣ ጥግ ይዘው የሚቅሙና የሚያጨሱ እንዲሁም መጻሕፍትና ጌጣጌጦችን በመሸጥ የሚተዳደሩ አሉ። ሌሎቹ ደግሞ ሰው መለመን ታክቷቸው አሊያ ያሉበት ኹኔታ አስመርሯቸው በትካዜ ተቀምጠዋል። የሁሉም እድሜ በአማካይ ከ16 አይበልጥም።ሔዋን (ስሟ የተቀየረ) በሚያሳዝን ገፅታና ልብን በሚነካ ድምፀት ታጅባ የእለት ጉርሷን ለመሙላት አላፊ አግዳሚውን ትማጸናለች። በጀርባዋም ጨቅላ ሕፃን አዝላለች። በእንዲህ ዓይነት ኹኔታ ላለፉት ስምንት ዓመታት በጎድዳና ላይ ኑሮዋን እየገፋች ትገኛለች ። የወላጆቿ ፍቺ እና የአባቷ ዱላ አስመርሯት ወደ ጎዳና እንደወጥች ትናገራለች፤ ተመልሳ ከቤተሰብ የመቀላቀሉን ሐሳብ ግን በፍፁም እንደማትፈልገው ነገር ግን ለወለደቻት ሕፃን የወደፊት ስኬት እንደሚያስስባት እንዲህ በማለት ትናገራለች “መንግሥት ድጋፍ አድርጎልን እኛም ተደራጅተን ብንሠራ ከዚህ ሕይወት መላቀቅ እንችላለን፤ ልጆቻችንም ይሄን ሕይወት እንዳይደግሙት ያደርጋቸዋል። የሚረዳን አካል ካለ እዚህ ያለነው በሙሉ ለመለወጥ ዝግጁ ነን። አዲስ ለሚመጡ ልጆም ወደቤተሰባቸው እንዲመለሱ እንመክራቸዋለን። ምክንያቱም እዚህ መኖር ምን ያህል አስከፊ እንደኾነ ከእኛ በላይ ምስክር የለም።”በማለት በምሬት ትናገራለች።ነጋሽ በበኩሉ “ሌላው አስገራሚ ኹኔታ ወንዶች በእህል በመሰብሰቢያ ወቅት ወደከተማ በመምጣት በልመና ላይ ይሰማራሉ፣ ሴቶቹ ደግሞ በእርሻ ወቅት ተመሳሳይ ድርጊት ይፈጽማሉ፤ ይህም የሚሠሩት የማንሳት ሥራዎች ውጤታማ እንዳይኾኑ አድርጓቸዋል።” በማለት የችግሩን ተለዋዋጭነት ያስረዳሉ።ሱሰኝነት፣ የጎዳና ሕይወትና የቁጥጥር ማነስቸርችል አደባባይ፣ስታዲየም፣ለገሀርና አምባሳደር አካባቢ ያሉት ታዳጊዎች በማስቲሽ መሳብ ሱስ ውስጥ የተዘፈቁ ልጆች በብዛት የሚገኙባቸው ሥፍራዎች ናቸው። በፊት በልብሳቸው ሸፍነው ይጠቀሙት የነበረው ድርጊት አሁን ሃላል (በገሀድ) መመልከት የየእለት ትእይንት መሆን ከጀመረ ሰንበት ብሏል። ይህም በሕግ አስከባሪዎች ዘንድ ያለውን ቸልተኝነት በግልፅ ያሳያል።እንዳልካቸው ባዩ እንደሚሉት “ይሄን ሥራ የሚሰሩት ፈርጣማ ክንዶች ያሏቸው ነጋዴዎች በጎዳና ላይ ካሉና በዚሁ ሱስ ምርኮኛ ኾነው ከሚያሻሽጡ ልጆች ጋር በመተባበር ያከፋፍላሉ። ችግሩ በግልፅ እንዳለ ቢታወቅም ፤ ይህን ለማስቆምም የሚተባበሩ የፀጥታ አካላት ማግኘት ከባድ ነው።” ይላሉ።ከፀጥታ አካላት በተጨማሪ ይሄን ችግር ለመቅረፍ ዓላማዬ ብሎ የተነሳው የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚንስቴር መ/ቤት አቅራቢያ ድርጊቱ መከናወኑ ያስገርማል። ከላይ በተጠቀሱት ስፍራዎች ረፋድ 4፡00 አካባቢ ሽያጩ እንደሚከናወን የአደባባይ ምሥጢር ነው።” በማለት ያለበትን እሳሳቢ ደረጃ ነጋሽ በዳዳ በምሬት ይናገራሉ።ይህንን እውነታም በፒያሳ አካባቢ የሚኖሩ ታዳጊዎች ያረጋግጣሉ “ምንም እንኳ እኛ ባንጠቀምም በማስቲሽ ሱስ የተጠቁ ልጆች ለመግዛት ሲመጡ እንደሚመለከቱ ይናገራሉ። ሔዋን በበኩሏ “አንዲት ጓደኛችን በብዛት ተጠቅማ ለሕልፈት ከበቃች በኋላ ተጠቃሚዎች ማቆማቸውን እና አዳዲስ ልጆች ሲስቡ ካየን በመገሰጽ እንዲተው እናደርጋለን።”” ትላለች። አዲስ ዘይቤ ባካባቢው ባደረገችው ቅኝትም እውነታውን አረጋግጣለች።ከተሜውና የመብራት ሠራተኞቹበስታዲየም አካባቢ የትራፊክ መብራት የለቀቃቸውን መኪኖች በሩጫ ተሽሎክልኮ ያለፈን ታዳጊ ከመግጨት ለጥቂት ያተረፈውን አሽከርካሪ ጨምሮ በርካታ ተሳፋሪዎች በአንድ ቃል ተስማምተዋል “ማስቲሽ ስቦ እንጂ በጤናው እንደዚህ አይሆንም። “ በማለት።ይሄንን የሚያረጋግጠው ሌላኛው እውነት ፤ ማስቲሽ በመሳብ ላይ የነበሩ ልጆች ድንገት የትራፊክ መብራት ያስቆማቸውን ባለመኪናዎችንና ተሳፋሪዎችን ገንዘብ የሚጠይቁበት ኹኔታ ከማሳዘን ይልቅ ወደ መፍራትና መጠራጠር እንደሚያደላ የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ። እንደ አስመረት ወልዳይ አገላለጽ “ገና ሳያቸው ደኅንነት አይሰማኝም ፤ አንዳንዴም የታክሲ ረዳቶች መስኮት ከፍተው ተንቀሳቃሽ ስልክ ለሚያናግሩ ሰዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ስለሚነግሩ መስኮቱን በፍጥነት እዘጋዋለሁ።” ትላለች።መገናኛ አካባቢ የገጠመውን ደግሞ ዳንኤል ከበደ እንዲህ ያጫውተናል። “ከሥራ ወጥቼ ወደቤት እየተጓዝኩኝ ነበር፤ ከመገናኛ ወደ የካ አባዶ በሚወስደው የፍጥነት መንገድ ላይ ነኝ ። በተወሰነ መልኩ መንገዱ ተጭናንቋል፤ በዚህ ጊዜ አንድ የተጎሳቆለ ምስኪን ታዳጊ ወደ መስኮቴ ተጠግቶ እርዳታ ጠየቀኝ ። በድካምና መሰላቸት ውስጥ ሆኜ ‹ፈጣሪ ይስጥልኝ› አልኩት፤ እሱ ግን ፍንክች አላለም እኔም ጉዳዬ ብዬ ትኩረት አልሰጠሁትም።ጭንቅንቁ ጋብ ብሎ መንቀሳስ ስንጀም ግን ያ ሲቅለስለስና ሲማፀን የነበረ ታዳጊ ስልኬን አንስቶ ሮጠ ፤ እኔም ባለኝ ፍጥነት ተቃራኒውን በር ከፍቼ ተከተልኩት ያጋጣሚ ነገር ልጁ ላይ ደርሼ ንብረቴን አስመለስኩኝ። “ከዚያ ወዲያ ግን በተለይ የጎዳና ተዳዳሪዎች በሚበዙበት አካባቢ በተቻለው መጠን መስኮት ከፍቶ እንደማያሽክረክር እንዲሁም ልጆቹን በጥርጣሬና በንቃት እንደሚከታተላቸው ይናገራል። በዚህ ጊዜ አደጋ ቢደርስ ኖሮ ማን ተጠያቂ ይኾን ነበር? የፀጥታ አካል በአካባቢው አለመኖር በራሱ ትልቅ ክፍተት ነው።” ሲል ሐሳቡን ያጠቃልላል።የጎዳና ልጆችን በሁለት መንገድ ነው የምመለከታቸው፤ ምግብ ሲሰጣቸው ተፋቅረው መብላታቸውና አመስግነው መቀበላቸው ያስደስታል፤ ገንዘቡን ለሱስ ሲያውሉት ደግሞ በጣም ያበሳጫል። አንዳንዴ በአራዳ ቋንቋ የለኝም (ወፍ የለም፣ ጨላ የለኝ (ገንዘብ የለኝም) ሲባሉ እንደሚሄዱ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲሳደቡ እንዳጋጠመው ይናገራል።ከልጁ ጋር በተሽከርካሪ ሲጓዙ የልጁን የማያባራ ጥያቄ ለመመለስ ከመቸገር አንስቶ በአእምሮው እያውጠነጠነ፤ የሀገሪቱ መጻኢ እድል ምን ይኾን ይኾን? የሚሉት ጥያቄዎች ዘወትር እንደሚያሳስቡት ዓለምሰገድ ኃይሉ ይናገራል። “ሲለምኑ አለመስጠት አይቻልም ነገር ግን ጥንቃቄ በታከለበት መንገድ (ሌሎች መስኮቶችን ዘግቼ፤ በእኔ በኩል ያለውን ደግሞ በግማሽ ከፍቼ) ለምን ማስቲሽ ትስባላችሁ? ለጤና ጎጂ ነው። በማለት የዜግነቴን ለመወጣት ጥረት አደርጋለሁ። በአንጻሩ ለልጄም ጥያቄ ‹ትምህርትን በአግባቡ አለመከታተል፣ ወላጅ የሚለውን አለመስማት እንደዚህ ያደርጋል› በማለት ለማስረዳት እሞክራለሁ ።” ይለናል።ዓለምሰገድን ጨምሮ አንዳንድ አሽከርካሪዎች በበኩላቸው ልጆቻቸው እንደዚህ ዓይነቱን ትእይንት እንዳይመለከቱ መንገድ ከመቀየር ጀምሮ ትኩረታቸውን ወደሌላ ነገር ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉ ይናገራሉ ፤ ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ አይስካላቸውም ። የእኔስ ልጅ ብትኾን እንደዚህ የኾነችው? የሚለው ጥያቄ እንደሚያስጨንቃቸው ይናገራሉ። ሁሉም ዜጋ ግን በእነዚህ ልጆች ላይ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይናገራሉ።መፍትሔውስ ምንድር ነው ?“አሁን ባለንበት ወቅት የጎዳና ልጆችን መሰብሰብ ከባድ ነው።” የሚሉት ነጋሽ ምክንያታቸውን ደግሞ እንደዚህ ያስቀምጡታል። “ልጆቹን ሰብስበን የሕይወት ክህሎት ለመስጠት ስናናግራቸው የሚሰጡን ምላሽ ‹እኛ የመብራት ሠራተኞች እንጂ የጎዳና ተዳዳሪ አይደለንም› ይላሉ። የትራፊክ መብራት ላይ ለምኖ አዳሪ ነን ማለታቸው ነው። አንድ ክፍል ውስጥ እስከ 20 ሆነው ተከራይተው መኖራቸው እንደ ተጨማሪ ምክንያት ያቀርባሉ።” ነገር ግን ይሄ አኗኗራቸው ግን ለተላላፊ በሽታ፣ ላልተፈለገ እርግዝናና በተመሳሳይ ፆታ መደፈርን እንደሚያስከትል ባለሞያው የሚያመጣውን ማኅበራዊ ቀውስ ያስቀምጣሉ።እርግጥ ነው የተለያዩ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች የጎዳና ልጆች በማንሳት የተሻለ ሕይወት እንዲመሩና ብቁ ዜጋ ለመፍጠር እየደከሙ ያሉ፤ ውጤታማ ሥራዎችን እየሠሩም ይገኛሉ። በተጨማሪም የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚንስቴርም በየጊዜው የሚያደርገው እንቅስቃሴ ይበል የሚያሰኝ ነው።“በመጀመሪያ ደረጃ ከመንግሥት በኩል ተገቢውን እውቅና መስጠትና ድጋፍ በማድረግ በጋራ የሚሰሩበት መተዳደሪያ ቢነደፍ የተፈለገው ውጤት ማምጣት ይቻላል።” የሚሉት ነጋሽ በዳዳ ናቸው።የዶምቦስኮው እንዳልካቸው በበኩላቸው “የሚከናወነው ሥራ እልህ አስጨራሽ በመሆኑ በጥበብ ሊሰራ ይገባዋል።” እንደምሳሌ በእርሳቸው ማዕከል የሚሰጠውን ሥልጠና ሲያብራሩ “ሥልጠናችን በአራት ዙር የተከፋፈለ ነው። መጀመሪያ ጉብኝት በማድረግ ፍላጎት ያላቸውን እንመርጣለን፤ በመቀጠል መጥተው እንዲጎበኙን ካደረግን በኋላ አሁንም ፍላጎት ያላቸውን በማያሰለች መልኩ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጠን በተመላላሽ ለአንድ ወር እናስተምራለን፤ በመጨረሻም በት/ቤታችን በማስገባት የአራት ወር መሠረታዊ ሥልጠና ከመስጠት በተጨማሪ ትምህርታቸውን ያቋረጡትን እንዲቀጥሉ እናደርጋለን፤ ወላጆቻቸው በሕይወት ያሉትን ስለልጆቻቸው የማወቅ መብት ስላላቸው በየጊዜው የደረሱበትን ደረጃ በማሳወቅ ተጭባጭ ለውጦችን አምጥተናል፤ ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ ስኬታማ ነው ባንልም። ሁለት፣ ሦስት ልጆች ስልጠና አቋርጠው በመውጣት ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው የሚመለሱ አሉ ፤ ነገር ግን የመለወጥ አላማ ካላቸው ሁሌም ደጃችን ክፍት ስለሆነ መምጣት እንደሚችሉ እንነግራቸዋለን።”በቅርቡ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ባስቀመጠው የ100 ቀናት እቅድ ውስጥ ሕፃናትን ከጎዳና ማንሳትና ወደቤተሰባቸው መመለስ ዋነኛው ጉዳይ እንደሆነ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፤ እንደዚህ ዓይነት የዘመቻ ሥራዎች በየጊዜው ቢከናወኑም ውጤታማ እንዳልኾኑ ግን ባለሞያዎች ይናገራሉ። አቶ አበበ አቡሽ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የጥናትና ፕሮጀክት ኃላፊ ናቸው፤ “በየጊዜው በዘመቻ ከመሥራት ይልቅ በችግሩ ላይ በጥልቀት የተሠሩ ምርምሮችን መሠረት በማድረግ ቀጣይነት ያለው ሥልጠና መሰጠት አለበት።” ይላሉ።የሕፃናት ድጋፍና ክትትል ኃላፊ ገነት ውሂብ በበኩላቸው “የሚሰጠው ሥልጠና ያለውን ተጨባጭ ኹኔታ ከግምት ያስገባ ካለመኾኑ በተጨማሪ የሚሠራው ሥራ ሁሉን በኃላፊነት ያቀፈ መሆን አለበት።” ጨምረውም ሚንስቴር መ/ቤቱ ብቻውን መሥራቱ ስኬታማ ያልሆነ ፕሮጀክት እንዲኾን አድርጎታል ይላሉ።የኤልሻዳዩ ነጋሽ የሚመጡትን አስተያየቶች ተቀብለው ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ነገር ግን ድርጅታቸው ከአቅሙ በላይ ጥረት በማድረግ ላለፉት 30 ዓመታት እየሠራ እንደሚገኝና በርካታ ልጆችን ለውጤት ማብቃታቸውንም ተናግረዋል።ከተሜነት የአንዲት ሀገር ሁለንተና ገፅታ እንደመሆኑ መንግሥት ፣ማኅብረሰብ፣ ተቋማትና እያንዳንዱ ግለሰብ የዜግነት ግዴታውን መወጣት እንዳለበት ባለሞያዎች ጠቅሰው ይሄም የዘመናዊነት መገለጫም መሆኑ ታስቦ መሠራት አለበት ይላሉ።