ታህሣሥ 2 ፣ 2011

የአዲስ አበባ ህንጻዎች ትላንት እና ዛሬ

ስለ እኛኑሮፊቸርታሪክ

አዛዉንቱ አቶ ታምሩ ደገፉ ከወጣትነት ት ዝታቸው ጋር የጥንት የጠዋቷን ሽገርን ቀበናን ከመሰሉ ኩልል ብለው ከሚፈሱ ንጹህ ወንዞቿና መልካም ከሚባል የጽዳት…

የአዲስ አበባ ህንጻዎች ትላንት እና ዛሬ
አዛዉንቱ አቶ ታምሩ ደገፉ ከወጣትነት ት ዝታቸው ጋር የጥንት የጠዋቷን ሽገርን ቀበናን ከመሰሉ ኩልል ብለው ከሚፈሱ ንጹህ ወንዞቿና መልካም ከሚባል የጽዳት ባህሏና የከተማ አኗኗር ዘይቤዋ ጋር አብረው ያስታዉሷታል። በአራት ኪሎ፣ በስድስት ኪሎ በሽሮ ሜዳ እና መሃል አራዳ ፒያሳ ላይ በወጣትነት እድሜዎቻቸው ሲምነሸነሹባት ህንጻዎቿ የተለየ አያያዝና አሰራር ዘዬ እንደነበራቸው ያስታዉሳሉ።ሁሉ እንደነበረ አይቆይምና የወጣትነት ወርቃማ ግዜያትን ያሳለፉባት አዲስ አበባ ከግዜ እና ሁኔታዎች አስገሳጅነት እየተቀያየረች መሆኗን ይገልፃሉ።  ዛሬ ቀበና ከወንዝነት ይልቅ ወደቁሻሻ መጣያነት ተቀይሮ በዘመን አመጣሹ የፕላስቲክ ኮዳ ተሞልቶ ሲያዩ “ድንቄም ስልጣኔ” ይላሉ። በከተማዋ ያስተዋሏቸው አንዳንድ ለዉጦችና ቅያሬዎች በዘመናዊነት ስም ቢደረጉም አግባብ እንዳልሆኑና ልብ እንደሚነኩ ይናገራሉ።አዲስ አበባ ምኗ ተቀየረ?“………(ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ) ከ1878 አመተ ምህረት ዠምሮ ከእንጦጦ ወርደው ከእቴጌ ጣይቱና እና ከመኳንንቶቻቸው ጋር ያዳመቁት የአዲስ አበባ ከተማ ከዕለት ወደዕለት እያማረበት ሄደ። ……… እንደዚሁም በቤተ መንግስቱ ራቅ ባለው አካባቢ በጉለሌ ንጉስ ተክለ ሃይማኖት፣ከእንጦጦ በታች ራስ ዳርጌ፣በጊሚራ ሰፈር እነ ራስ ሚካኤል፣ከዚያም እነ ራስ መኮንን ዙሪያውን እነ ንጉስ ወልደ ጊዮርጊስ እነ ራስ መንገሻ አቲከም ራስ አባተ እነ ፊታውራሪ ሃብተ ጊዮርጊስ…. በየስማቸው ልዩ ልዩ ያማረ ቤት ሰሩ። ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆነው የእንግሊዝ፣የመስኮብ፣የፈረንሳይ፣የኢጣልያና የጀርመን ሌጋሲዮኖች ተቋቋሙ …….” አፄምኒሊክ እና የኢትዮያ አንድነት በሚለው የበተክለ ፃዲቅ መኩሪያ መፅሃፍ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ መመስረትን እና የግንባታ ታሪክ አሃዱ ብሎ መጀመርን ያወሳሉ።ይህ ከአዲስ አበባ ከተማ መቆርቆር ጥቂት አመታት ቀድሞ የተጀመረው የግንባታ ታሪክ ግን በአፄ ምኒልክ የእንጦጦ ቤተ መንግስት አንድ ብሎ የጀመረ ነው። አፄ ምኒልክ በ1874 አመተ ምህረት 3200 ሜትሮች ከምድር ወለል ከፍ ብለው መናገሻቸውን እንጦጦ ላይ አደረጉ። ንጉሱም አልፍሬድ ኢልግ በተባላው የስዊዝ አማካሪያቸው ምክር አማካኝነት የእንጦጦ ቤተ-መንግስታቸው ታነፀ። በእዚህ መልኩ የተለያዩ የታሪክ መዛግብት ያሰፈሩት ቢሆንም ዛሬም የገዛ ራሱን ታሪክ ይዞ የሙዝየም ግልጋሎትን እየሠጠ የሚገኝ በመሆኑ ሙሉ ታሪኩን መዝግቦ ይዞ ይገኛል።አዲስ አበባ በዚህ ወርኃ ህዳር 132ኛ ዓመት ልደቷን ስታከብር ብዚህ ረጅም እድሜዋ ለዉጧ ፈርጀ ብዙ ቢሆንም አዲስ ዘይቤ የከተማይቱን የጥንት ቀደምት ያሉ የህንጻ አሻራዎቿን ተከትላ ምን በምን ተለወጠ። የትኛው ህንጻዋ ታደሰ የትኛዉስ ግልጋሎቱን ቀየረ የቱስ እስከመኖሩ እስከነ ታሪካዊ ፋይዳዉ እንደትራ ነገር ተረሳ በሚል መዲናዋን በጥንት ታሪካዊ ህንጻዎቿ መነጽር ለመቃኘት ሞክራለች ። ታምሩ እንደሚሉት አግባብ ያልሆኑ ለዉጦች ይኖሩ ይሆን ብላም ጠይቃለች ።የአዲስ አበባ ሙዝየምየአሁኑ የአዲስ አበባ ሙዚየም የአዲስ አበባን እና የኢትዮጲያን ታሪክ እና ባህሎችን በተለያዩ ስዕሎች፣ታሪካዊ ፎቶዎች እና ቁሳቁሶች አካቶ ታሪክን ለትውልድ ሰብስቦ በመያዝ መስቀል አደባባይ ወረድ ብሎ ይገኛል። ይህንን ሙዚየም በዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ትእዛዝ ለጥይት ቤት ይሆን ዘንድ በ1880ዎቹ ሃጂ ቀዋስ በተባሉ ሰው ተገነባ። ለጥይት ቤት ተብሎ የተሰራው ህንጻ ከዚያ ብኋል ባሉት ዓመታት ለበርካታ እይነት ግልጋሎቶች ዉሏል።መኖሪያ ቤት፡ክሊኒክ ቀበሌ ጽ/ቤት ትምህርት ቤት ሆቴልም ሆኖ ያዉቃል።አፄ ምኒልክ ይህን ህንፃ ለራስ ብሩ ወልደ ገብርኤል መኖሪያ ቤት እንዲሆን ወይዘሮ አማከለች አሊን ሲያገቡ በጋብቻቸው ቀን በስጦታ ሰጡአቸው።በጣለያን የኢትዮጲያ ወረራ ዘመኑም እንደ ክሊኒክ አድረገው ጣሊያኖች ሲጠቀሙበት ከቆየ በኃላ በ1928 ዓመተ ምህረት ሃገር ከጠላት ወረራ ነፃ ስትሆን ራስ ብሩ ወልደ ገብርኤል ተመልሰው መኖሪያቸው አደረጉት። አሁን በቤተ መዘክሩ የመጀመርያ የጉብኝት አዳራሽ ተፅፎ በተለጠፈው የህንፃው ታሪክ አጭር ገለፃ እንደሚያስረዳው ከራስ ብሩ ሕልፈተ ህይወት በኃላ ልጆቻቸው ወይዘሮ ፍቅርተ ብሩ እና በወይዘሮ ዘነበወርቅ ብሩ ለሁለት ተከፍሎ ለመኖሪያ ቤትነት ውሎም ነበር። በ1960ዎቹ ማገባደጃ አካባቢ ደግሞ ቀበሌ ፅህፈት ቤት፣ትምህርት ቤት እና የሹራብ ማምረቻ አገልግሎቶችን ሰጥቷል። በ1979 ዓመተ ምህረት ወደ ቤተ መዘክር ከመቀየሩ በፊት ደግሞ ማሩ ደምቢያ ሆቴል ተሰኝቶ ተስተናጋጆችን ተቀብሎ አስተናብሯል።ይህን ሁሉ የአገልግሎት አይነቶችን ያፈራረቀው የአዲስ አበባ ቤተ መዘክር ህንፃ ዛሬ ላይ የአዲስ አበባ ቤተ መዘክር በመሆን በአማካኝ በአንድ ወር እስከ አንድ ሺህ ሰዎች በቦታው በመገኘት ታሪክን እንደሚማሩበት ከቤተ መዘክሩ አስጎብኚ መቅደስ አባቡ ለመረዳት ተችሏል። ይህ ህንፃ ከግድግዳዎቹ በስተቀር በተለይ ፎቁ ሙሉ በሙሉ ከእንጨት እና መስታወት የተሰራ ማራኪ ገፅታ ያለው ሲሆን ስድስት ቋሚ የአውደ ርዕይ አዳራሾች እና አንድ ጊዚያዊ የስእል አውደ ርዕይ የሚያስተናግዱ አዳራሾችም ያሉት ታሪክን ተራኪ ቤተ መዘክር ነው።ሼክ ሆጀሌ ቤተ መንግሥትዛሬ ስያሜው አጥሮ ሸጎሌ ሜዳ ወይም ሸጎሌ እየተባለ የሚጠራው አካባቢ ይገኛል ይህ ታሪካዊ የሼህ ሆጀሌ ቤተ-መንግስት። ሼክ ሆጀሌ አል ሃሰን ይባላሉ። ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ያስተዳድሩ የነበሩ እና ለሃገር የተለያዩ ውለታዎችን የዋሉት እኚህው የአፄ ሚኒሊክ ቅርበት ያላቸው ባላባት ነበሩ። አዲስ አበባ ውስጥም በነበራቸው ይዞታ ይህን ቤተ መንግስት የገነቡ ሲሆን 1890ዎቹ ተገንብቶ እንደተጠናቀቀ ይነገራል። ከሼህ ሆጀሌ መኖሪያ ቤትነት በኋላም የልጅ እና የልጅ ልጆቻቸው መኖሪያነት በተጨማሪም በትምህረት ቤትነት ጭምር ያገለገለው ይህ ሕንፃ በአሁኑ ሰአት ደግሞ ያለ አንዳች ስራ በቦታው ይገኛል።ህንፃዎችን ሲገነቡ ከታሰበላቸው የመጠቀም አላማ ወይም ግልጋሎት ውጪ ስንጠቀማቸው ስለሚገጥሙ ጉዳዮች የስነ ህንፃ ባለሞያ  የሆኑት አቶ ክንፈ ፅጌ ሲያብራሩ፡- “…….በህንፃው መሰረታዊ የስትራክቸራል ችግር ይፈጥራል። ይህም የስትራክቸራል ጥናት በዋነኝነት የሚያተኩረው የህንፃውን የመነሻ አገልግሎትን መሰረት በማድረግ ነው። ይህ ሲቀየር ግን በህንፃው ላይ የሰትራክቸር ችግር በህንፃው ላይ ይፈጥራል።ለምሳሌ ለመኖሪያ አገልግሎት የታቀደ ህንፃ ወደ ንግድ ብንለውጠው በህንፃው የሚኖረው የእንቅስቃሴ መጠን በሙያዊ ቋንቋ (Live Load) ላይ ለውጥ ይፈጥራል። ህንፃውም ሊያናጋ የሚችል ይሆናል” ያሉ ሲሆን ህንፃው ላይም በሚኖሩ ለውጦች እና ማሻሻያዎች ምክንያት የህንፃው አገልግሎት አድሜ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ይጠቁማሉ። ፖስታ ቤትሌላው ደግሞ አፄ ሚኒሊክ በ1894 ዓመተ ምህረት ለሃገሪቱ የፖስታ አገልግሎት ተዋወቀ። የፖስታ አገልግሎት ይሠጥ ዘንድ የተሰራው ይህ ህንፃ አሁን አሮጌው ፖስታ ቤት በመባል የሚጠራው ነው።ይህ ህንፃ በ1908 የተገነባ ሲሆን እስከ ጣሊያን ወረራ ግዜ ድረስ በፖስታ ቤትነት ያገለግልም ነበረ። በጣልያን ግዜም “ሲኒማ ኢጣሊያ” ተብሎ በሲኒማ ቤትነት አገልግሏል።በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሲኒማ ኢትዮጲያ በሚል መጠሪያ ፒያሳ ይገኛል። ተፈሪ መኮንን ት/ቤት“…. ለኢትዮጲያ ነፃነትና ፅናት ወሰንዋን ጠብቆ አሳፍሮ አስከብሮ ለማኩራትና የሕዝቧ ልብ የታመነ ኃይል እንዲኖረው ለማድረግ መሣሪያው ትምህርት መማር ነው።………..”ይህ ንግግር ቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ምርቃት አስመልክተው ከአረጉት ንግግር የተወሰደ ነው።አምሳለ ገነት ቤተ መንግስት የቀድሞ መጠሪያው ነበረ። በኋላ ደግሞ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እና አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ግቢ የህግ ትምህርት ክፍል ነው።መርስዔ ሃዘን ወልደ ቂርቆስ የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፡የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ካየሁትና ከሰማሁት በተሰኘው የታሪክ መፅሃፍ ላይ ስለ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት መከፈት እንዲህ ሲሉ ያወሳሉ፡- “ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን ከጃንሜዳ በስተ ሰሜን በኩል በሚገኝና የወይራ ዛፍ በሞላበት በአንድ ቦታ ላይ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ለማሰራት ስላሰቡ ከሁለት አመት በፊት ህንፃውን አስጀምረው ነበር። በዚህም አመት ሕንፃው ተጠናቆ ስላለቀ በስማቸው የሰየሙትን ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ሚያዝያ 19 ቀን 1917 ዓ.ም ሰኞ መርቀው ከፈቱት”ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥትየገነተ ልዑል ቤተ መንግስት በጀርመናዊው ኪነ ሕንፃ ባለሞያ ካሜዝ ንድፉ ተሰርቶ ግንባታው ደግሞ በ1927 ዓመተ ምህረት የተጠናቀቀ ሕንፃ ነው።ይህ ሕንፃ በ1900 ራስ መኮንን ለልጃቸው ራስ ተፈሪ (በኋላ ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ) በውርስ የተሰጠ ይዞታ ነበር። በጣልያን ወረራ ግዜም ለኢጣሊኑ “ምክትል ንጉስ” መኖሪያ ቤትነት አገልግሏል። በአሁኑ ሰአት ደግሞ የአዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጲያ ጥናት ተቋም ሆኖ እያገለገለ የሚገኝ አንጋፋ የአዲስ አበባ ጌጥ ነው።ብሔራዊ ሙዚየምሙዚሞችንስ ለመገንባት እንዴት ያሉ የስነ ህንፃ ንድፍ መርሆችን መከተል አለባቸው? አቶ ክንፈ ፅጌ በተለያዩ የህንፃ ዲዛይን ስራዎች ላይ ለረጂም አመታት አገልግለዋል። በአሁኑም ሰዓት በሙያው እያገለገሉ ሲሆን የአርክቴክቸር ማህበር የኮሚቴ አባልም ናቸው። አቶ ክንፈ ስለ ሙዚየም የንድፍ ስራ ሲያብራሩም  እንዲህ ይላሉ፡- “ለብዙሃን ተደራሽ የሆነ እና ከሙዚየሙ አላማ ጋር በትርጉም የሚጣጣም ቦታን መምረጥ። የኤግዚቢቶቹን አይነት፣ባህሪ፣እና ሌሎች ይዞታቸውን ማወቅ እና መረዳት ያስፈልጋል። ንድፉ የኤግዚቢቶቹን አካላዊ ሆነ አካባቢያዊ ሆኑ አላስፈላጊ ችግሮችን እንዲስወገድ ባስቻለ መልኩ መታቀድ አለበት። ለታዳሚዎችም ምቹ፣ያማረ፣እና ቅርሶቹን በቀላሉ ለመመልከት ብሎም ያላቸውንታሪካዊ ሆነ ባህላዊ ይዞታቸውን በቀላሉ ለመረዳት የሚያስችል እና ሌሎችን ተቸማሪ ነገሮች ያሟላ መሆን ይኖርበታል፡”የኢትዮጲያ ብሄራዊ ሙዚየም ሃገሪቱ ብሔራዊ ቤተ መፃሃፍት አካል ሆኖ በ1937 አመተ ምህረት ተመሰረተ።ለመጀመሪያ ግዜም አውደ ርዕይ ሲያቀርብ ከንጉሳውያን ቤተሰቦች የተለያዩ አልባሳትን በስጦታነት አግኝቷል።ብሄራዊ ቤተ መዘክሩ እስከ ድረስም በብሄራዊ ባንክ ሰራተኞች ክበብ ቅጥር ግቢ ውስጥ የነበረ ሲሆን አሁን ያለበት ቦታ አራት ኪሎ እና አምሰት ኪሎ መሃል ባለ ቦታ 1959 አመተ ምህረት ተዛወረ።በዚህ ግዜ የተዛወረበት ህንፃም ይዞታነቱ የአንድ ኢጣሊያዊ የጦር መኮንን መኖሪያ የነበረ ቢሆንም በኃላ ላይ በኢጣሊያን መንግስት  የአዲስ አበባ አስተዳደሪ ሰው መኖሪያ ቤት ሆኖ አገልግሏል። ፋሽስት ኢጣሊያን ከሃገሪቱ ከተባረረ በኃላ ለንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ ልጅ መኖሪያ ቤትነት ተሠጥቶ ከቆየ በኃላ ከአመታት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሆኖ አገልግሏል።በመጨረሻም በ1960 ዓመተ ምህረት ለብሄራዊ ቤተ መዘክርነት ስራ እንዲያገለግል ተሰጠ። ለበርካታ አመታትም በቤተ መዘክርነት ከአገለገለ በኋላ በ1994 ዓመተ ምህረት አዲስ የሙዚየም ህንፃ በመገንባቱ ቤተ መዘክሩ ወደዚያው የተሸጋገረ መሆኑን ብሄራዊ ሙዚየሙ ያሰናዳው አጭር ፅሁፍ ያስረዳል። በአሁኑ ሰዕት ደግሞ ይሄው እድሜ ጠገብ ህንፃ ለአዲሱ የሙዘየም ህንፃ ስራውን አስረክቦ በእድሳት ላይ ይገኛል።በተለይ ታሪካዊ እና እድሜ ጠገብ ህንፃዎችን በተለያየ ወቅት ለተለያየ ትቅም ላይ ማዋል በአንድ ማህበረሰብ ብሎም በአንድ ሃገር ላይ የተለያዩ ተፅዕኖዎች እንዳሉአቸው የሚናገሩት የኪነ ህንፃ ባለሞያው አቶ ክንፈ ፅጌ ከእነዚህም አሉታዊ ጎኖች መካከል አንዱ ማህበረሰቡ  ማለትም ባለቤቱ ታሪኩን እና ቅርሱን ተረክቦ እና ጠብቆ በተገቢው መልኩለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ይቸገራል። ሁለተኛው እና ባለሞያው ያነሱት ነጥብ ህንፃዎቹ ታሪካዊ ይዘታቸውን ጠብቀው ሃገር በቱሪዝም ዘርፍ ልታገኝ የሚገባውን ጥቅም ያሳጣል ይላሉ።በስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲው ዋናዉ ግቢ ትምህርታቸውን ለጥቂት ግዜ ተከታትለው ባህር ማዶ የተሸጋገሩት አቶ ታምሩ በአሁኑ ሰአት ሃገራቸውን በበጎ ምግባር ስራዎች ላይ በማተኮር እየተሳተፉ ነው። ከተማዋ ብዙ ነገሮችዋ ቢቀያየሩም እሳቸው ግን አዕምሮቸው በአዲስነት ይዞ ያቆየውን ትዝታ አሁን ያለበት ሁኔታ እንዳያደበዝዝባቸው ከማይሄዱባቸው ቦታዎች አንዱ የስድስት ኪሎ ዩኑቨርሲቲው ደጃፍ ነው።በዚያ ያዩት ነገር እንደማያስደስታቸው ይናገራሉ። በሰማዕታት ሃዉልት ትይዩ የግቢዉን አጥር ተጠግተው የተሰሩ አዲስ ህንጻዎችን የዘመኑ ስህተቶች ይሏቸዋል።ያኔ የተለየ ግርማ ሞገስ የነበረው ዉብ ግቢ በአዲስ ተብዬዎቹ ህንጻዎች ዉበቱንም ሞገሱንም እንደተነጠቀ በቁጭት ይናገራሉ።ጥንት የግቢው ማማር ብቻ ሳይሆን  የዩኒቨርሲቲው ደጃፍ በዛፎች ውበት ያጌጠ፣ውስጥ ደግሞ በገነተ ልዑል ቤተመንግስት ፍክት ያለ የጥበብ እፁብነት የተነሳ አረፍ ብለን እንድንዝናና ያደርገን ነበረ። የሁልግዜም ትውስታዬም እሱ እንዲሆን እፈልጋለሁ” ይላሉ።

አስተያየት