You can paste your entire post in here, and yes it can get really really long.
ከዓለም አንደኛኢትዮጵያ በታሪኳ ዐይታ የማታውቀው የውስጥ መፈናቀል ገጥሟታል። የመፈናቀሉ ምክንያት የተለያዩ ምክንያቶችን ተከትሎ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ከተፈናቀሉት ውስጥ 79 በመቶ የሚሆኑት በማኅበረሰቦች መካከል በተፈጠረ ግጭት ምክንያት መኾኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት ያሳያል። ተ.መ.ድ በዚህ ወር ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ 2.2 ሚሊዮን የውስጥ ተፈናቃዎች አሉ።በጌዲኦ-ጉጂ እና በሶማሌ-ኦሮሚያ ክልል አካባቢ የተፈጠሩ ግጭቶችን ተከትሎ ከተፈጠረው የ1.4 ሚሊዮን ዜጎች መፈናቀል በኋላ እ.ኤ.አ በ2018 የመጀመሪያ ስድስት ወራት ኢትዮጵያ በውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር ሶርያን፣ የመንን እና ኮንጎን አስከንድታ በዓለም አንደኛ ኾናለች።በሀገር ውስጥ የሚደርሱ መፈናቀሎች የዓለምን ትኩረት መሳብ የጀመሩት በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ በነበሩ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የተፈጠረውን ሰፊ የውስጥ መፈናቀል ተከትሎ ነበር። የውስጥ መፈናቀል ጉዳይ በዋነኛነት የሀገራቱ መንግሥታት ኃላፊነት ቢኾንም የሀገራቱን ምላሽ ለማገዝ የዓለም አቀፍ ተቋማት የተለያዩ ማእቀፎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። የተ.መ.ድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በ1991 ዓ.ም. ሀገራት በውስጥ ለሚደርሱ መፈናቀሎች ስለሚወስዱት ምላሽ፣ ሕጋዊ አስገዳጅነት ባይኖረውም እጅጉን ተቀባይነት ያገኘ መመሪያ አውጥቷል።የአፍሪካ ኅብረት በበኩሉ ሕጋዊ አስገዳጅትን ያለው፣ በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የሚፈናቀሉ ሰዎችን ለመጠበቅ እና ለመርዳት የሚያግዝ ስምምነት -የካምፓላ ስምምነት - በጥቅምት 2002 ዓ.ም. ለሀገራት ፊርማ ክፍት አድርጓል። እስከ ዛሬ ስምምነቱን 27 የአፍሪካ ሀገራት ቢያጸድቁትም፣ ኢትዮጵያ ግን በጥቅምት 2002 ዓ.ም. ፈርማ በፓርላማዋ ሳታጸድቅ በይደር አስቀምጣዋለች።የ’The Emergence of Forced Displacement in Africa: Development and Implementation of Kampala Convention on Internal Displacement’ መጽሐፍ ጸሐፊ እና በአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ የኾኑት አቶ አለሆን ሙሉጌታ የዓለም አቀፍ ሕግ መርሖዎች እና ሀገራትም በስምምነቶቹ ውስጥ አባል መኾናቸው ያለውን ጥቅም ለአዲስ ዘይቤ ሲያስረዱ፣ «ሕግ እና የዓለም አቀፍ ስምምነት የውስጥ መፈናቀልን በራሳቸው ሊፈቱ አይችሉም። ነገር ግን የውስጥ መፈናቀል ችግሮችን ለመፍታት ሀገራት አቅጣጫዎችን እንዲያስቀምጡ ይረዳሉ። ለውስጥ መፈናቀል መፍትሔ መፈለግ በዋነኝነት ፓለቲካዊ ቁርጠኝነትን ይፈልጋል።የካምፓላ ስምምነት የውስጥ መፈናቀል መኖሩን ሀገራት በግልጽ እውቅና እንዲሰጡ ይረዳል። የስምምነቱ አባል በመኾን መንግሥታት በአፍሪካ ውስጥ ያለውን ሰፊ የውስጥ መፈናቀል ምላሽ ለመስጠት ብቻ ሳይኾን ወደ ፊት የሚኖረውን ለመቆጣጠር ያላቸውን ተነሳሽነት ያሳያሉ። ወደ ስምምነቱ መቀላቀል ሀገራት በውስጥ መፈናቀል ላይ ስለሚያወጧቸው ሕጎች እና ፖሊሲዮች ግልጽ አካሔድ ያስቀምጥላቸዋል። በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ማን ምን ኃላፊነት እንዳለበትም ግልጽ መመሪያ ያስቀምጣል። ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የሚኖሩ ግንኙነቶችንም ያመቻቻል፣ የውስጥ ተፈናቃዎችን ኃላፊነት እና ተሳታፊነትም ግልጽ ያደርጋል።»ከመደበኛው ጊዜ የተለየ ምላሽየውስጥ መፈናቀሎች የሚፈጠሩት ድንገተኛ በኾነ አጋጣሚ ምክንያት ነው። የውስጥ መፈናቀል በተለያየ ጊዜ በሚፈጠር የእርስ በርስ ጦርነት፣ የማኅበረሰብ ግጭት፣ የተቀናጀና ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወይም በተፈጥሮአዊ አደጋ ምክንያት ሊፈጠር ይችላል። የውስጥ መፈናቀል ተፈጥሯል ለማለት ሁለት ኹኔታዎች መሟላት አለባቸው፡- በመኖሪያ ቦታ ላይ በአስገዳጅነት/ያለፍቃድ የሚደረግ እንቅስቃሴ እና እንቅስቃሴውም በአንድ ሀገር ድንበር ውስጥ ብቻ የተገደበ መኾኑ።ይህ የውስጥ መፈናቀል በተለየና ባልታሰበ ጊዜ መፈጠሩ፣ እና የተለየ ችግርን ይዞ መምጣቱ መንግሥታት ችግሩን ለመፍታት በመደበኛ ጊዜ ከነበረው አሠራራቸው ወጣ ያለ አካሔድን እንዲከተሉ ያስገድዳቸዋል። ኹኔታዉን ያገናዘበ የፖሊሲ እና የሕግ ለውጥ ያስፈልጋል። ይህም ማለት የውስጥ መፈናቀል በሚፈጠርበት ጊዜ መንግሥታት ኹኔታውን ያገናዘበ እና የመፈናቀል ችግሩን በየደረጃው የሚመልስ የሕግ ማእቀፍና ተቋማዊ ቅንጅቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊመሠርቱ እና ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጡ ይገባል።መንግሥታት በሀገር ውስጥ የሚኖርን መፈናቀል መፍትሔ ለመስጠት የሚወስዷቸው እርምጃዎች በሦስት ደረጃዎች ሊቀመጡ ይችላሉ፡- መፈናቀሉን ማቆም ወይም አደጋውን መቀነስ፣ በመፈናቀሉ ጊዜ የተለያዩ እርዳታዎችን ማቅረብ እና ተፈናቃዮች በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ኹኔታ ማመቻቸት።መፈናቀልን ወይ ማስቆም፣ ካልኾነ አደጋውን መቀነስዜጎች በየትኛውም ቦታ የመዘዋወር እና የመኖሪያ ቦታቸውን የመምረጥ መብት አላቸው። መንግሥታትም ይህን የዜጎች የሰብዓዊ መብት የማክበር እና የማስከበር ግዴታ አለባቸው። ስለሆነም መንግሥት ዜጎች እንዳይፈናቀሉ ጥበቃ ማድረግ አለበት። ዜጎችን በኃይል ማፈናቀል ከባድ ወንጀል ነው። ይህ ወንጀል በጥልቅ የሚጣራበት፣ ድርጊቱን የፈጸመው አካልም በግልጽ ሕዝብ እንዲያውቀው የሚደረግበት አካሔድ ያስፈልጋል።ዜጋን በማፈናቀል ድርጊት የሚሳተፉ ሁሉ ተገቢው የወንጀል ቅጣት እንዲተላለፍባቸው መንግሥት መሥራት አለበት። በማፈናቀል የተሳተፉ ብቻ ሳይኾኑ፣ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ምክንያትም ከኃላፊነት እስከመነሳት የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው፣ የወንጀል ተጠያቂነትም ሊኖርባቸው ይገባል። ቅጣት፣ አጥፊውን በእስር በማስቀመጥ እና ሌላው እንዲጠነቀቅ መልእክት በማስተላለፍ ወንጀሉ ዳግመኛ እንዳይደገም ያደርጋል።የመፈናቀል አደጋዎችን ለመቀነስ እና ቀድሞ ለማወቅ የሚያግዝ ተቋም (Early warning system) ማቋቋም፣ ካለም ማጠናከር የመፍትሔው ዋነኛ አካል ነው። ተቋሙ ኃላፊነቱን እንዲፈጽም ግልጽ የሆነ ተቋማዊ ቅርጽ ያስፈልገዋል። በጉዳዩ ላይ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎችን ማካተት፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና የሲቪክ ማኅበራት ጋርም ግንኙነት መፍጠር አለበት። መዋቅሩ ከማዕከላዊ መንግሥት ወደ ክልሎች የሚወርድበትን እና ክልሎች ስለኹኔታው ያላቸውን የተሻለ እውቀት መጠቀም እና አደጋዎች ከመድረሳቸው በፊት ለመቆጣጠር ያላቸውን ተደራሽነት መጠቀም ያሻል።ኢትዮጵያ በ1997 ዓ.ም. የተቋቋመ «የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚሽን» ቢኖራትም፣ አደጋ ከደረሰ በኋላ በሚካሄዱ እርዳታ የማቅረብ ሥራዎች ላይ እንጂ፣ አደጋዎችን ከመድረሳቸው በፊት ቀድሞ በማወቅ እና በመከላከል ረገድ እምብዛም ስሙ አይነሳም። አደጋዎችን ቀድሞ ለማወቅ በአፍሪካ ኅብረት ስር የተቋቋመው ክፍል ዋና ቢሮ (situation room) መቀመጫ እዚሁ አዲስ አበባ ቢኾንም፣ አፍንጫው ስር የሚደርሱ አደጋዎችን ቀድሞ ከማወቅ አኳያ ብዙም እየተጠቀምንበት አይደለም።ድኅረ መፈናቀልዜጎች በሀገር ውስጥ በመፈናቀላቸው ምክንያት ለብዙ አደጋዎች ይጋለጣሉ፣ ሰብዓዊ መብታቸውም በሰፊው ይገፈፋል። መሠረታዊ ለኾኑ ፍላጎቶቻቸው፡- ለመጠለያ፣ ምግብ እና ውኃ ጥገኛ፣ የሌላውን እጅ ጠባቂ ይኾናሉ። ደክመው ያፈሩትን ንብረታቸውን፣ ቤታቸውን እና መሬታቸውን ያጣሉ። ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይለያያሉ፣ ከኖሩበት ቀዬና ማኅበረሰብ ይነጠላሉ።መሠረታዊ የጤና፣ የትምህርት እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ይነፈጋሉ። በሀገራቸው ፖለቲካ ውስጥ እንዳይሳተፉ፣ መምረጥም ሆነ መመረጥ እንዳይችሉ ይኾናሉ። ተፈናቅለው በሚመጡበት መንገድም ሆነ ተፈናቅለው ባረፉበት አካባቢ ለወሲብ ጥቃት ይጋለጣሉ። ስለዚህ መንግሥታት ከበፊቱ፣ በመደበኛ ጊዜ ከሚሔዱበት አቅጣጫ ወጣ ብለው የተለየ አቅጣጫ በማስቀመጥ የተፈናቃዮችን መብት እና ጥቅም ለማስጠበቅ መሥራት ይኖርባቸዋል።በውስጥ ላሉ ተፈናቃዮች የሚደረግ ምላሽ በዋነኝነት ከእኩልነት መርሕ - ተፈናቃዮች ተፈናቅለው ከሄዱበት ማኅበረሰብ ጋር በእኩል እንዲታዩ የታለመ ነው። ይሄም ማለት ተፈናቃዮች ከተለየ ቦታ እንደመምጣታቸው የመጡበት አካባቢ ሕግ/ተቋም ሊያገላቸው፣ አድሎ ሊያደርግባቸው ይችላል። በዚህም ምክንያት የውስጥ ተፈናቃዮች ከአካባቢው ነዋሪ የተለየ ጥበቃ እንዲደረግላቸው፣ ተጠቃሚም እንዲኾኑ እና ከአካባቢው ነዋሪ ጋር እኩል የሚሆኑበትን ምቹ ኹኔታ መፍጠር ያሻል።በአደጋ ጊዜ ለተፈናቃዎች መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ማሟላት የመንግሥት አዲስ ኃላፊነት ኾኖ ብቅ ይላል። ስለዚህ መንግሥታት በአፋጣኝ የሚያስፈልገውን የእርዳታ መጠን እና ዓይነት ማጥናት፣ የውጪ ለጋሾችን እርዳታ ከመጠየቅ አንስቶ በሀገር ውስጥ መዋዕለ ንዋይ ማፈላለግ እና ሟሟላት ይጠበቅባቸዋል። መንግሥት እርዳታ ለማዳረስ እንዲያስችለው ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ሕግን እና ፖሊሲን ማስፈጸም እንዲችል፤ የተፈናቃዎችን ቁጥር፣ ቦታ፣ የተፈናቀሉበትን ምክንያት ያካተተ ትክክለኛ መረጃ መሰብሰብ እና አጠናቅሮ ማስቀመጥ አለበት።የምዝገባው ሒደትም ግልጽ በኾነ ቅድመ ኹኔታ፣ አድሎአዊ ባልኾነ፣ በጊዜ እና ቦታ ባልተገደበ እና ፈጣን በኾነ አሠራር መከናወን ይኖርበታል። ተፈናቃዮች የተጠቃሚነት ካርድ እንዲኖራቸውም ማድረግ ያሻል። የሚወጣው ካርድ ግን «የተፈናቃይነት ቦታ» ለመስጠጥ ሳይኾን ለአስተዳደር እንዲያመች፣ ከሚኖረው አነስተኛ እርዳት ለመጠቀም የሚፈጸሙ ማጭበርበሮችን ለመቆጣጠር መኾን ይኖርበታል። እንደ የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ አለሆን ሙሉጌታ አገላለጽ «[የውስጥ ተፈናቃዮችን] እንደተለዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ልናያቸው አይገባም። የውስጥ ተፈናቃዮች እንደማንኛው ሰው ናቸው፣ የተፈናቀሉበት ሀገር ዜጋም ናቸው።»ከእርዳታ ጋር ግንኙነት ያላቸው የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት (በተለይ ቀይ መስቀል) አብረው የሚሠሩበትን አካሔድ ማመቻቸት ያስፈልጋል። ከፌደራል መንግሥት ወደ ክልል ትዕዛዝ የሚወርድበትና በአስቸኳይ የሚፈጸምበት ብቻ ሳይኾን፣ ስለ ሁኔታው ክትትል የሚካሄድበት እና መረጃ ልውውጥ የሚደረግበት የጎንዮሽ ግንኙነቶች የሚካሄዱበትን መዋቅር ማኖር ያስፈልጋል። በእርዳታ ሒደት ውስጥ የሚሳተፉ እያንዳንዳቸው ተቋማት የተለየ እና ግልጽ ሥልጣን እና ኃላፊነት ሊቀመጥላቸው ይገባል።ከተፈናቃዮች ጋር ተያይዞ የሚኖረው ኃላፊነት አዲስ ስለሚሆን፣ በየደረጃው የሚሳተፉ የመንግሥት ኃላፊዎች ስለ የውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች፣ ከሌሎቹ ነዋሪዎች በተለየ ስለሚሰጣቸው ጥቅም እና ሥራቸውንም እንዴት መሥራት እንዳለባቸው ሊሰለጥኑ ይገባል። ይህም ተፈናቃዎቹን በሚመለከት የሚሠሩ ሥራዎች በዘፈቀደ እና ከሌላ አካባቢ ጋር የተዛቡ/የተለያዩ እንዳይኾኑ፣ አስቸጋሪ የሆኑ የቢሮክራሲ አካሔዶችንም ለማስወገድ ያግዛል። ከተፈናቃዮች ጋር አንድነት፣ መተጋገዝ እንዲፈጠር እና አድሎም እንዳይኖር ሰፊው ማኅበረሰብ ላይ ያነጣጠረ ግንዛቤን የማሳደግ ፕሮጀክቶች ያስፈልጋሉ።በእርዳታው አሰጣጥ አካሔድ ላይ ተፈናቃዮችን ብቻ ሳይኾን ተፈናቃዮች በሰፈሩበት አካባቢ ያሉ ማኀበረሰቦችን ማሳተፍ፣ ፍላጎታቸው ማየት ያስፈልጋል። ተፈናቃዮችን ማሳተፍ መንግሥት የገጠማቸውን አደጋ፣ የወደፊት ፍላጎታቸውን እንዲረዳ ተፈናቃዮቹም አደጋውን ለመቀነስ/ለማጥፋት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እድል ይሰጣል።ስለዚህ መንግሥት ለተፈጠረው የመፈናቀል አደጋ ምን ዓይነት ምላሽ ሊሰጥ እንዳሰበ፣ ስለ እርዳታው መጠን እና የማከፋፈል ሂደት ለተፈናቃዮች ማሳወቅ እና ሐሳባቸውን ማድመጥ ይኖርበታል። ይሄም ብቻ ሳይሆን ተፈናቃዮችን ማሳተፍ በተለይ ተጋላጭ የሆኑ (በተለይ ሴቶች) ተፈናቅለው በሰፈሩበት ቦታ የሚገጥማቸውን አደጋ የሚያሳውቁበት እና ተገቢውን ጥበቃ የሚያገኙበትን አጋጣሚ ይፈጥራል።እርዳታዎች እንዳይባክኑ፣ በአግባቡ እየተከፋፈሉ መኾኑን ለማረጋገጥ እና በሚያስፈልገው የእርዳታ መጠን ላይ በየጊዜው የሚኖረውን ለውጥ፣ ክፍትቱንም ለማወቅ ተከታታይነት ያለው የክትትል እና ኦዲት ማድረጊያ ስልት ማኖርም ያስፈልጋል። ይህ ክትትል የሚካሔደው እንደ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ባሉ መንግሥታዊ ተቋማት ቢኾንም፣ ገለልተኝነቱን ለማረጋገጥ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችን ማካተት ይገባል። የእርዳታው ሒደትም ዓላማው ተፈናቃዮች በዘላቂነት እራሳቸውን የሚችሉበትን ኹኔታ ለመፍጠር እንዲኾን አልሞ መሥራት ያሻል።…ወደ ዘላቂ መፍትሔተፈናቃዮች በእርዳታ ሊቆዩ የሚገባው በዘላቂነት መፍትሔ እስከሚገኝላቸው፣ የፖለቲካው እና ማኅበረሰባዊ ኹኔታው እስከሚስተካከል ጊዜ ድረስ ብቻ ነው። ተፈናቃዮች በዘላቂነት ስለሚቋቋሙበት ኹኔታ ሦስት አማራጮች አሉ፡- በፍቃደኝነት ወደ መጡበት መመለስ፣ ተሰደው የመጡበት ቦታ ላይ መቀጠል እና ሌላ ሦስተኛ ቦታ ላይ ሄደው መስፈር። በዚህ ጉዳይ መንግሥታት በዋነኛነት የተፈናቃዮችን ፍላጎት ማየት ይኖርባቸዋል።ዜጎች (ተገደው ከቀያቸው የተፈናቀሉትን ጨምሮ) በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የመንቀሳቀስ፣ የመኖሪያ ቦታም የመምረጥ መብት አላቸው። መንግሥት ይሄንን ሊያሟላ የሚችለው ደግሞ ለነዋሪነታቸው ማረጋገጫ ሰነድ በማቅረብ እና ደኅንነታቸውንም በመጠበቅ ነው። ስለዚህ የተፈናቀሉ ሰዎች በካምፖች ውስጥ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቀመጡ መኾን የለባቸውም።የተፈናቀሉ ዜጎች በዘላቂነት የሚኖሩበትን ቦታ እንዲመርጡ መፈቀድ አለበት። ተፈናቃዮች ወደ መጡበት ቀያቸው መመለሳቸው የሚበረታታ አማራጭ ቢኾንም ማስገደድ ግን በጭራሽ አይገባም። ለዚህም መንግሥት ተፈናቃዮቹን «ወደ መጣችሁበት ተመለሱ» ከማለት ይልቅ፣ የተፈናቀሉበትን ቦታ የደኅንነት ኹኔታ እና ቢመለሱ የሚያገኙትን እርዳት በግልጽ ሊያሳውቃቸው ይገባል።ተፈናቃዮቹ ትክክለኛ ፍላጎታቸውን ሊያውቁ የሚችሉት መጀመሪያ ስለመጡበት ቦታ ኹኔታ ሲያውቁ፣ ወደ ሌላ ቦታ ቢሰፍሩም የሚኖራቸውን ተጠቃሚነት በግልጽ ሲያውቁ ነው። መንግሥት በኃይል በማስገደድ ብቻ ሳይሆን፣ እርዳታን እንደመሳሪያ ተጠቅሞ የተፈናቃዮች ምርጫ ላይ ተጽእኖ ከማድረግ መታቀብ ይኖርበታል። በሚመርጡበት ቦታ ላይ ዳግመኛ ደኅንነታቸው አደጋ ውስጥ እንደማይገባ ማረጋገጥ መቻልም አለበት።የመጡበትን ቦታ ደኅንነት፣ ንብረታቸው ያለበትን ኹኔታ እንዲያጣሩ እና ሰብል እንዲሰበስቡም ለአጭር ጊዜ ሄደው የሚመለሱበትን ኹኔታ መፍቀድ፣ ማመቻቸት ይገባል። በዚህም በተፈናቃይነታቸው የሚያገኟቸውን ጥቅሞች መነፈግ የለባቸውም። ወደ መጡበት ቦታ ለመመለስ የሚመርጡ ተፈናቃዮች የትራንስፖርት አገልግሎት ሊሟላላቸው፣ በመንገዳቸውም ላይ ደኅንነታቸው ሊረጋገጥላቸው ያሻል።ተፈናቃዎች በዘላቂነት በሚቋቋሙበት ወቅት የተወሰዳባቸው ንብረት ካለ መንግሥት ንብረታቸውን መልሰው እንዲያገኙ ሊያደርግ ይገባል። ንብረታቸው (በተለይ ቤትና መሬታቸው) የተወሰደ/የተቃጠለ ከኾነ ተገቢውን ካሣ፤ አጥፊዎች የሚከፍሉበትን፣ ይህ ካልሆነ መንግሥት እራሱ የሚከፍልበትን (ወይም ንብረቱ በሌላ የሚተካበትን) አካሔድ ማመቻቸት ያስፈልጋል። እዛው የተሰደዱበት ወይም ሌላ ሦስተኛቦታ ላይ ለመስፈር የሚፈልጉ ከኾነም የተፈናቃዮችን ብቻ ሳይኾን፣ የሚሰፍሩበት ማኅበረሰብ ፍላጎት እና ጥቅም የማይጎዳበት ኹኔታም ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል። ወደ ሌላ ቦታ በሚሄዱበት ወቅት የሚያስፈልጋቸው የነዋሪነት ሰነድ የሚሟላበት፣ ወደ ማኅበረሰቡ ውስጥ የሚቀላቀሉበት፣ ከሚሰፍሩበት ማኅበረሰብ ጋር እኩል የኢኮኖሚ ተጠቃሚትን የሚያገኙበት፣ በሀገራቸው ፖለቲካ ውስጥም የሚሳተፉበትን ኹኔታ ማመቻቸት ይገባል።የጠ/ሚ ዐቢይ አስተዳደር የጉዳዩን አንገብጋቢነት መረዳቱን እና ዘላቂ መፍትሔም ለማፈላለግ ያለውን ቁርጠኝነት የካምፓላ ስምምነትን በማጽደቅ ሊያረጋግጥ ይገባዋል። ጉዳዩ በዋነኝነት በውስጣዊ መዋቅራችን የሚፈታ ቢኾንም በስምምነቱ አባልነታችን የምናገኛቸውን፣ በተለይ የሙያዊ ምክር ጥቅሞች ወደ ጎን መተው የለብንም። የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ አቶ አለሆን እንደሚሉት «በብዙ [የካምፓላ ስምምነት አባል] ሀገራት ካሉ ልምዶች፣ መንግሥታት በሕጋቸው እና ተቋማዊ መዋቅሮች ውስጥ ያሉ ክፍተቶች ላይ በሚኖር ምርመራ እና ኦዲት ተጠቃሚ ይኾናሉ።ኢትዮጵያ ደግሞ በሁለቱም የሕግና ተቋሞቿ አቅም ውስጥ ያሉትን ክፍተቶች ለማወቅ ጥልቅ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋታል።» ከሁሉም በላይ ለመፈናቀል ምክንያት የሆነውን ዋነኛ ሥረ መሠረት ማጥናት እና ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ፣ በማኅበረሰቡ መካከል ግጭት የሚፈጥሩ ትርክቶችን ማስታረቅ፣ የልዩነት መንስኤ የሆኑ ፖሊሲዎችን እና ሕጎችን ማረም፣ ዳግመኛም የዜጎች ደኅንነት አደጋ ውስጥ የማይገባበትን ከባቢ መፍጠር፣ ሁሉም ለአገር ያገባኛል የሚል አካል ዋነኛ ኃላፊነት ነው።