የሞት ቅጣት ሊፈፀምበት ሦስት ቀናት ቀርተውታል። ወንጀሉን አልፈፀመም፣ እሱ ልቦናው ያውቃል፣ ዓለም ግን አያውቅም፤ምሎ ይገዘታል ራሱን ግን ከሞት ፍርድ ማዳን አልተቻለውም። የፖሊስ ባልደረባን ገድለሃል ተብሎ 12 ዓመት ታስሯል። ተስፋ ቆርጦ በተቀመጠበት ነበር ቀድሞ የግል መርማሪ የነበረው፣ የኋላው ዘጋቢ ፊልም(Documentary) ያን ኤሪስ ሞረል ጉዳዩን የሰማው። ሰምቶ ዝም አላለም ‹thin blue line› የተሰኘ የምርመራ ዘጋቢ ፊልም በዚህ ሰው ሕይወት ዙሪያ ሰራ።
ራንዳል ዴል አዳምስ በዚህ ታሪኩን በሚዘግብ ፊልም ምክንያት የፍትሕን ብርሃን አየ። ዘጋቢ ፊልም ው እውነቱን ፍንትው አድርጎ አሳይቶለታልና በአደባባይ ብዙዎች ጮሁለት። ዳግም ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ተመለሰ፣በሀቤየር ኮርፐስ ታየለትና ነጻ ወጣ።
ይህ ከሆነ 30 ዓመት አልፎታል፤ የአዳምስ ጉዳይ ግን ዛሬም ዘጋቢ ፊልሞች ፍርድን ማስቀየር ስለመቻላቸው ማስረጃ ኾኖ በድግግሞሽ ይጠቀሳል።
ሰሞነኛ የኛ አገር ጭቅጭቅም በዚሁ ርእሰ ጉዳይ ላይ እየተሽከረከረ አይተነዋል። በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዙሪያ በታዩ ምዝበራ እና ብክነት ተግባራት ላይ የቀረበው ዘጋቢ ፊልም አገሪቷን ከዳር ዳር አነቃንቋታል። ብዙዎቻችን አዝነናል፣ተቆጥተናል። ነገሮቹን ቀድመን ያወቅናቸው ቢኾንም እንኳ የዘጋቢ ፊልም ኃይል ግን ስሜታችንን በጥልቅ ነክቶታል። በእርግጥም በታሰበው ልክ ሁላችንን በአንድነት ነገሩን ለመኮነን አብቅቶናል። የታለመትን በጉዳዩ ላይ የሕዝብን አመለካከት የመቅረፅ ዓላማ በማሳካቱ የካፌ ጠረጴዛዎችን፣የግሮሰሪ ባንኮኒዎችን እና የማኅበራዊ ሚዲያ ገፆችን አጨናንቆ ሰንብቷል። መንግሥት ለወሰዳቸው እርምጃዎች ሰፊ ድጋፍ አስገኝቶለታል።
ነገረ ዘጋቢ ፊልም በኛይቱ ምድር
በኢትዮጵያ ከአንዳች ውሳኔና ክስተት አስቀድሞ በዘጋቢ ፊልም ፊልም የሕዝብን አመለካከት ለመቅረጽ መሞከር ዛሬ ላይ አልጀመረም። በተለይ ከፀረ ሽብር ሕጉ መጽደቅ ወዲህ ባሉ ዓመታት ፖለቲከኞችን፣ጋዜጠኞችን ጦማሪያንና የሃይማኖት ሰዎችን ለመወንጀል በሰፊው ጥቅም ላይ ውሏል።
በቅርቡ ከታዩት ለውጦች መካከል የኢንጂነር ስመኘውን አሟሟት ፖሊስ የነገረን ሰሞን እና አሁን በሜቴክ ጉዳይ ተመሳሳይ ኹኔታዎች ተስተውለዋል።
ዘጋቢ ፊልም ን ለፖለቲካዊ ዓላማ ማዋልን ግን ከኢሕአዴግም በፊት ደርግ በተሰካ ኹኔታ ተጠቅሞበታል። መስከረም 1፣1967 በአዲስ ዓመት ምሽት የቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴን የተቀናጣ የ80ኛ ዓመት ልደት አከባበር ከሰሜን ኢትዮጵያ ረሃብ ጋር እያስተያየ የቀረበው ዘጋቢ ፊልም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።”ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ” ብሎ ለሺህ ዓመታት የኖረ ሕዝብ ይህ ዘጋቢ ፊልም በታየ ማግስት ግልብጥ ብሎ አደባባይ ወጣ። ንጉሡ ከሥልጣን ወርደው በዚያች ታሪከኛ ቮልስ ተጭነው ሲሄዱ ለዘመናት አንቀጥቅጠው የገዙትን ንጉሥ በመንገዱ ግራና ቀኝ ተሰልፎ «ሌባ! ሌባ!» እያለ ሰደበ።
ያ ዘጋቢ ፊልም በፊልም ቋንቋ ሞንታዥ (በሁለት የተለያዩ የተከወኑ ድርጊቶችን በንፅፅር በማቀናበር) ዘዴ የሕዝብ ብሶትን በመቀስቀስ ያለምንም ኮሽታ ደርግ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥትን መቋጨት አስችሎታል።
መንግሥታት በዓለም ዙሪያ ለአንዳች በጎ ወይ እኩይ ዓላማ ሕዝባቸውን ለማደራጀትና ለማንቃት ዘጋቢ ፊልም ን ሲጠቀሙ ኖረዋል፡፡ በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብርት ሶሻሊዝም ተሰብኮበታል፤ በናዚ ጀርመን በአንድ የአርያን ዘርነት ጀርመናውያንን ለማሰባሰብ አስችሏል፤በኢራን-ኢራቅ ጦርነት ሕዝብን ለጦርነት ለማስታጠቅ ዓላማ ውሏል፡፡
ዘጋቢ ፊልም እውነት ወይስ የእውነታ ምትሐት
ዘጋቢ ፊልምን አደገኛ የሚያደርገው ከመሠረታዊ ብያኔው ማለትም ዘጋቢ ፊልም ተግባሩ እውነትን መዘገብ ነው ከሚል ግንዛቤ በመነሳት ሰዎች በቀላሉ እውነት ነው ብለው የሚቀበሉት መሆኑ ነው። ይህን ተፈጥሮውን የተረዱ መንግሥታትና አንባገነኖች በዘመናት ውስጥ ለበጎም ሆነ ለክፉ ዓላማቸው ሲጠቀሙበት ቆይተዋል።
እንኳንስ አንዳች ግብ ተቀምጦለት ለፕሮፓጋንዳና ሌላ ዓላማ ውሎ ይቅርና ዘጋቢ ፊልም ማለት ከእውነት ጋር እኩያ ነው የሚለው ብያኔ ምሁራንን ከጅምሩ እስካሁን ያከራክራል፡፡ «እውነት በካሜራ ውስጥ ሲያልፍ የሠሪውን ትርጓሜ እንጂ ተፈጥሯዊ ማንነቱን ይዞ አይወጣም፡፡ ዘጋቢ ፊልም ያን ምን ለማሳየትና ምን ላለማሳየት ሲወስን እውነትን እየተረጎመ ነው» ብለው የሚከረከሩ ምሁራን ብዙ ናቸው፡፡
ጉምጉምታ ከወደ ትግራይ
የተመዘበረውን ብቻ ሳይሆን የባከነውን፣ ሊወገድ የተዘጋጀውን እና በየሜዳው የተዝረከረከውን የአገር ሀብት ማየት ለብዙዎቻችን አንዳች ሆድ የሚያም ነገር ነበረው። በዚህች ደሀ አገር አቅም ይህን ሁሉ መቋቋም እንዴት ተቻለ ሲሉ ብዙዎች ጠይቀዋል። ማኅበራዊ ሚዲያውም ይህንኑ ሲያንፀባርቅ አንዳንድ የትግራይ አክቲቪስቶች ብቻ የተለየ አቋም ይዘው ብቅ አሉ። ዘጋቢ ፊልም ው የተጠርጣሪዎችን መብት የሚጥስ መሆኑን አጥብቀው ሞገቱ።
እንግዲህ በዚህ ሁሉ መሀል ነው የዚህ ሳምንቱ አወዛጋቢ የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል መግለጫ የወጣው። በዚህ መግለጫ ላይ ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ «በቁጥጥር ስር እየዋሉ ያሉት አካላት በመገናኛ ብዙኃን ጥፋተኛና ወንጀለኛ ተደርገው እየቀረቡ መሆኑ የሕግ ልእልና ጉዳዮችን ለማጣራትና ለመፍረድ የተቋቋሙትን ፍርድ ቤቶችና የፖሊስ ተቋማት ተግባር ያለአግባብ እየሰሩ መሆናቸውን
ይህም ፍትሕን ከማስከበር እሳቤ ጋር የሚጣረስና የተጠርጣሪዎችን ሰብዓዊ መብት የሚጋፋ ነው» ማለታቸው ተዘግቧል።
ይህን ስንሰማ ብዙዎቻችን በሽብር ሕጉ ስም እነዚያ ሁሉ ዘጋቢ ፊልሞች ሲፈበረኩ፣ዜጎች በሕግ ሥርዓቱ ፊት እስኪፈረድባቸው ንጹሕ ሆነው የመታየት መብታቸው ሲገፈፍ፣ፍትሕ በጉልበተኞች እግር ስር ወድቃ ስትረጋገጥ እኝህ ሰው የት ነበሩ ብለናል።
እነዚህ ሰዎች በሰፈሩት ቁና ነው የተሰፈሩት፣በንጹሐን ላይ ሲፈጽሙት የነበሩት ዞሮ በነሱ ላይ ሆኗል። የካርማ ነገር ብለን ከማለፍ ውጪ ምን ሊባል ይቻላል። በፍፁም ክፋት አገርና ወገን ሲበድሉ ሲገርፉና ሲዘርፉ የኖሩ ሰዎች ላይ ይህ ሆነ ብለን አናዝንም። የነገሩ አያያዝ ግን ያሳስበናል። ዛሬ እኛን ደስ ባሰኘን ጉዳይ ላይ እንዲህ ያለ የፍትሕ ሥርዓቱን የሚፈታተን ዘጋቢ ፊልም ሲታይ በዝምታ ማለፍ፣ ነገ ዳግም በሌላ የማናምንበት ጉዳይ ላይ ይኸው ሲፈፀም ለመናገር ይልጎመጉመናል፣ ለኅሊናችን ስንል እንዲህ ያለው ነገር ይቅር እንላለን።
የዘጋቢ ፊልሙ ግድፈት
ማንኛውም የሚዲያ ተቋም የምርመራ ሥራ ሰርቶ በጎዳዩ ላይ ዘጋቢ ፊልም የመስራት ሙሉ መብት አለው። ይህን ማድረግ የሚነቀፍ ሳይሆን የሚደነቅና የሚያሸለም ባለሙያዎቻችንም እንዲከተሉት የምንጓጓለት ነገር ነው። እንዲህ ያለውን ዘጋቢ ፊልም ከሚዲያዎቻችን የምንጠብቀው ዛሬ አቃቤ ሕግ በራሱ መንገድ ምርመራውን አገባዶ ተጠርጣሪዎችን ከያሉበት መልቀም ሲጀምር አልነበረም። በራሱ ተነሳሽነት መርምሮ የደረሰበትን ሐቅ የሚያሰራጭና መንግሥትን፣ ትልልቅ ኮርፖሬሽኖችን እና ግዙፍ ወንጀለኞችን የሚያጋልጥ ሚዲያ እና የዘጋቢ ፊልም ሠሪ ነው የሚናፍቀን።
አሁን የሆነው ግን ከዚህ ለየቅል ነው። ዐቃቤ ሕግ ተጠርጣሪዎችን ማሰር በጀመረ እና በተቃዋሚ ሚዲያ ስንሰማቸው የነበሩ የዘረፋ እና ሰቅጣጭ የመብት ጥሰት ተግባራት በመንግሥት ደረጃ በአቃቤ ሕጉ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ መግለጫ ተካተው በሰማን ማግስት የመንግሥትን እንቅስቃሴ ለመደገፍ ነው ዘጋቢ ፊልሙ የቀረበልን።
እንዲህ ያሉት ዘጋቢ ፊልም ዎች ችግራቸው ከአንድ የፕሮፓጋንዳ ማዕከል ለሦስት ሚዲያ የታደሉ መምሰላቸው ነው። ሙሉ በሙሉ አንድ ዓይነት የሆነ ዘጋቢ ፊልም ሦስት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሊሰሩ ይችላሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው እና ይህን መነሻ አድርገን ስንነሳ ዘጋቢ ፊልም ው የተሰራው በጣቢያዎቹ አይደለም ወደሚል ድምዳሜ ያደርሰናል።
አሁን ጥያቄው «ማን ሊሰራው ይችላል?» የሚለው ይሆናል። ጤነኛ ጥርጣሬ ሊሆን የሚችለው መንግሥት ከነዚህ ጣቢያዎች የአንዱን ባለሙያዎችና ቁሳቁስ ተጠቅሞ አልያም በመንግሥታዊ መዋቅሩ ውስጥ ከሚገኙ የኦዲዮ ቪዥዋል ማዕከሎች በአንዱ እንዲሰራ አድርጓል ማለት ነው።
መንግሥት በውስጡ ያሉት ሦስት አካላት (ሕግ አውጪ ፣ተርጓሚ እና አስፈጻሚ) እርስ በርስ ሳይደበላለቁ መሄድ እንዳለባቸው ሁሉ መንግሥትና ሚዲያም ሚናቸው መለየት አለበት። የመንግሥት ሚና ማንም ሰው ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት ነጻ ኾኖ የመቆጠር መብቱን ማስከበር ሲኾን የዘጋቢ ፊልም ሠሪዎች/የሚዲያው ድርሻ ደግሞ በየትኛውም መንገድ መረጃን ማድረስ ነው።
ሁለቱ አካላት ሥራቸውን ለመስራት በሚያደርጉት ጥረትና ፍትጊያ መሀል ሚዛን ይጠበቃል፣እውነት አትዳፈንም፣የሰዎች መብት አይገሰሰም። ሁለቱ ሲደበላለቁ ግን ይህ ሚዛን ይፋለሳል። ኃይል አንድ ቦታ ተሰብስቦ የሥልጣን ብልግናን ይፈጥራል።
ይህን ሁሉ የምለው አሁን ያለውን የኃይል አሰላለፍ፣ የርስበርስ ትግል እና የሚጠይቀውንም ዋጋ ስለማልረዳ፣ ለዚህም የሚከፈል ዋጋ መኖሩን ስለምክድ አይደለም። ጥረታችን የቀደመውን ሕገወጥ ምዕራፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዘግተን የሕግ የበላይነትን ማሰከበር እንደሆነ እንዳንዘነጋ በመመኘት ነው። በተሳሳተ መንገድ ተጉዘን ትክክለኛ ቦታ እንደርሳለን ብዬ ባለማመንም ነው።
እንደው በአጋጣሚ በሜቴክ ዙሪያ ከተያዙት ሰዎች መሀል ምን አልባት አንዱ እንኳ በፍርድ ቤት ሂደት ነጻ ቢወጣ በመልካም ስሙ ላይ የማይቀለበስ ጉዳት ደርሷል። ወደፊትም አያርግበትና መንግሥታችን ተቀናቃኞቹን ለማጥቃት ሊጠቀምበት እንዳያስብ ካሁኑ ማሳሰብ ይገባል፡፡
ኤሪስ ሞረን ‹Thin blue line›ን ሰርቶ ለፍትሕ መስፈን ሲታገል ከጀርባው የመንግሥት መግፍኤ አልነበረውም። በራሱ ገንዘብ የሰራው ፊልም ያለፍትሕ 12 ዓመት የታሰረውን ሰው ነጻ ቢያወጣውም እሱን ግን ለገንዘብ ኪሳራ ዳርጎታል። ባልሰራው ወንጀል የሞት ቅጣትን ከመቀበል የተረፈው ራንዳል ዴል አዳምስ ከእስር ከወጣ ወዲያ የሕይወት ታሪክ መብቴ ይከበርልኝ ብሎ በአደባባይ ሞግቶታል። ዘጋቢ ፊልም ሠሪው ግን የሚቆመው ለእውነት ነውና ለእውነት እነዚህን ሁሉ ዋጋዎች ከፍሏል። የሱ ክፍያው በሱ ሥራ ፍትሕ መስፈኑ ነበር ይህንን አድርጎታል። ከዚህ መለስ አሜሪካ በየዓመቱ በቅርስነት ከምትመዘግባቸውና ጥበቃ ከምታደርግላቸው 25 ፊልሞች ዝርዝር ውስጥ መካተቱ በሥራው ካገኘው እውቅናና ሽልማት ውስጥ ተጠቃሽ ነው።
በተረፈ እንደ ሰሞነኞቹ ያገራችን ዘጋቢ ፊልም ዎች ያሉቱ ሥራዎች ለፕሮፓጋንዳ (የሕዝብን አመለካከት በአንዳች መስመር ለመቃኘት) የሚሰሩ እንደመሆናቸው ማንም ራሱን ከምር የሚወስድ የዘጋቢ ፊልም ባለሙያ በፍጹም እንዲህ ባለው ሥራ እጁን አይከትም። ባለሙያ ነኝ ባዮችም ለመርሕ መቆም መጀመር ይገባቸዋል፡፡