የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ግድያን በተመለከተ የተጠረጠሩ የመንግስት ኃላፊዎች በምርመራ ሂደቱ ላይ ጫና እያደረሱ ወይም በቂ ትብብር እያደረጉ አይደለም አለ።
ኮሚሽኑ በግድያው ዙሪያ የምርመራ ሪፖርት ጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ማውጣቱን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፖሊስ ኮሚሽን ጉዳዩን እንደሚመረምር አስታውቆ ነበር።
ኮሚሽኑ ተጠርጣሪዎችን በተመለከተ ከታማኝ የመረጃ ምንጮቼ አገኘሁት ባለዉ መረጃ መሰረት ግድያውን ለማጣራት ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የተውጣጣ መርማሪ ቡድን መቋቋሙን አረጋግጫለሁ ያለው ኢሰመኮ፤ እስከ መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን በህግ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን አስታውቋል።
ኢሰመኮ መጋቢት 14 ቀን 2014 በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው በአካባቢው ማህበረሰብ በግድያው ተሳትፎ አላቸው ተብለው የተጠቆሙ ሰዎች ሆነው በቁጥጥር ስር ያልዋሉ መኖራቸዉን ገለጾ የክልሉ መንግስት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጿል።
ከወንጀል ምርመራው ጎን ለጎን በአባገዳዎች ምክር ቤት አስተባባሪነት በኦሮሚያ ክልል መንግስት እና በከረዩ ማህበረሰብ የሀገር ሽማግሌዎች መካከል ሽምግልና እየተካሄደ ነው። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን “የእርቅ ሂደቱ የወንጀል ተጠያቂነትን መተካት ወይም ማስተጓጎል የለበትም” ሲል አሳስቧል።
በመግለጫዉ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) “የተጎዱትን መካስ፣ ዕርቅና ሰላም፣ ፍትሕና ተጠያቂነት በአንድነት ሊተገበሩ የሚችሉና የሚገቡ በመሆናቸው፣ የመንግሥት ኃላፊዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ለዚህ አይነት የተሟላ ዕርቅ፣ ሰላምና ፍትሕ በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።
የወንጀል ምርመራ እርምጃዎችን በአካባቢዎች ባህልና ልማድ መደገፍ የተለመደ ቢሆንም ይህ አሰራር በተጎጂዎች፣ በተጎጂ ቤተሰቦች እና በአካባቢው ማህበረሰብ ሙሉ ፈቃድ እንዲሁም ተሳትፎ ሊሆን ይገባል ብሏል ኮሚሽኑ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት የክልሉ ልዩ ኃይል እና ፖሊስ አባላትን ጨምሮ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች 39 የጅላ አባላትን ከአካባቢያቸው ወስደው 16 የሚሆኑት በአንድ ጊዜ ሲገደሉ 23ቱ ወደ ሌላ ቦታ መወሰዳቸው ተገልጾ ነበር።