መጋቢት 15 ፣ 2014

የ12ኛ ክፍል ውጤት ድጋሚ ዕንዲታይ የሚጠይቀው የተቃውሞ ሰልፍ በሌሎች ከተሞችም ይቀጥላል ተባለ

City: Gonderዜና

መምህራን እና ተማሪዎችን ጨምሮ የተማሪዎቹ ቤተሰቦች በተሳተፉበት ሰልፍ የዚህ ዓመት 12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ድጋሚ ዕንዲታይ ተጠይቋል።

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የ12ኛ ክፍል ውጤት ድጋሚ ዕንዲታይ የሚጠይቀው የተቃውሞ ሰልፍ በሌሎች ከተሞችም ይቀጥላል ተባለ
Camera Icon

ፎቶ፡ PCMag

የትምህርት ሚንስትር በያዝነው ወር መጀመርያ ይፋ ያደረገውን የ12ኛ ከፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ተከትሎ በልዩ ልዩ አካባቢዎች ተቃውሞዎች ተሰምተዋል። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮን ጨምሮ መንግሥታዊ ያልሆኑ የሲቪክ ማኅበራት እና የሐይማኖት ተቋማት ተቃውሟቸውን የሚገልጽ እና ውሳኔው ድጋሚ እንዲታይ የሚጠይቁ መግለጫዎች አውጥተዋል።

ይህንን ተከትሎ መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም. በደብረማርቆስ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ መካሄዱ ተሰምቷል። መምህራን እና ተማሪዎችን ጨምሮ የተማሪዎቹ ቤተሰቦች በተሳተፉበት ሰልፍ የዚህ ዓመት 12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ድጋሚ ዕንዲታይ ተጠይቋል።

በተያያዘ ዜና መጋቢት 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በሁሉም የአማራ ክልል ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ እንዲካሄድ ጥሪ ቀርቧል፡፡ ሰላማዊ ሰልፉን የጠሩት የአማራ ተማሪዎች ማኅበር (አተማ) እና የአማራ ወጣቶች ማህበር (አወማ) ናቸው፡፡  

“በጠራነው ሰልፍ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እርማቱ ድጋሚ ዕንዲታይ እንጠይቃለን” የሚሉት የአማራ ተማሪዎች ማኅበር አፈ ጉባኤ አቶ መኳንንት ሙላት ናቸው፡፡

በተለይ በጦር ቀጠና አካባቢ የነበሩ ተማሪዎች በጦርነቱ ተሳትፎ ሲያደርጉ መቆየታቸውን፣ በጦርነቱ ምክንያት ስነ-ልቦናዊ ጉዳት መዳረጋቸውን ያነሳው አቶ መኳንንት ተማሪዎቹን ያላገናዘበው የውጤት አሰጣጥ ሊታረም ይገባል ብሏል፡፡  በተጨማሪም “የትምህርት ቁሳቁሶች በጦርነቱ ሙሉ ለሙሉ በወደሙበት ሁኔታ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ሳይኖሩ ፈተና ላይ የተቀመጡ ተማሪዎችን በተረጋጋ መንገድ ለፈተና ከተዘጋጁ ተማሪዎች ጋር መመዘን ፍርደ ገምድልነት ነው” ብሏል፡፡

እርማቱ በገለልተኛ አካል በድጋሚ እንዲካሄድ የሚጠይቁበት ምክንያት ቅሬታ አስገብተው ውጤታቸው የተስተካከለ ተማሪዎች በፊት ከነበረው ጋር የተጋነነ መሆኑ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ መኮንን ማብራሪያ 150፣ 140 እና 162 እንዳመጡ የተነገራቸው 9 ተማሪዎች ከ500 በላይ አምጥተዋል፡፡ “ይህ የማሽን ስህተት ሳይሆን ሆነ ተብሎ የተፈጠረ ነው” ያሉት አቶ መኮንን በሰላማዊ ሰልፋችን ጉዳዩን ገለልተኛ አካል እንዲያጣራው እንጠይቃለን ብለዋል፡፡

የአማራ ተማሪዎች ማኅበር ፕሬዘዳንት አቶ እሸቱ ጌትነት “ጥያቄአችን ተገቢውን ምላሽ እስኪያገኝ እንቀጥላለን” ያለ ሲሆን ሰልፉን አዲስ አበባ ላይ ሊያካሂዱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ እሁድ መጋቢት 18 በሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍም ሁሉም የሀሳቡ ደጋፊዎች ተገኝተው ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ጠይቀዋል፡፡

በሰላማዊ ሰልፉ የሲቪክ ማኅበራት፣ ከምዕከላዊ ስራ አስፈጻሚዎች ጀምሮ እስከ ታች የስራ ዘርፍ ያሉ አካላቶች፣ የዞኑ የትምህርት መምሪያ ኃላፊዎች፣ የዞን አስተዳዳሪዎች (ከንቲባዎች) እና የተለያዩ የመንግሥት ተቋም ኃላፊዎች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል።

የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠር በቂ ዝግጅት እያደረጉ እንዳሉ ገልጸው የሰልፉ ዋና ዓላማ ከተማሪዎች ውጤት ጋር ብቻ የተያያዘ ስለሆነ ማንኛውም ሰው ከአስተባባሪ ጀምሮ እስከ ጸጥታ አካላቶች በዚህ ጉዳይ ባለቤትነታቸውን ማስመስከር ይገባቸዋል ብሏል።

መጋቢት 18 በሚካሄደው ሰልፍ ደብዳቤ ለሁሉም የአማራ ክልል ዞኖች መጻፋቸውን ገልጾ በየከተሞች በሚደረገው ሰልፍ ሞንታርቦ በከተማ አስተዳደር በኩል ድጋፍ እንዲደረግና በሰልፉ ላይ የሚመለከታቸው አካላቶች እርማቱ በገለልተኛ አካል እንዲታረምልን፣ ሃገር እንዲያድኑ ህይታቸውን ሰተው ሲዋጉ ለነበሩ፥ የትምህርት ቁሳቁሶች በሙሉ ተቃጥሎባቸው የሚያነቡት ነገር በሌለበት ሰዓት ሌትም ቀንም ከትምህርት ውጭ ሌላ ነገር ከማይሰማ አካል ጋር ኑ እኩል ተመዘኑ መባሉ ትክክል እንዳልሆነና ትምህርት ሚኒስቴር በጦርነት ቀጠና የነበሩ ተማሪዎችን ግንዛቤ ውስጥ እንዲከት በማድረግ በኩል የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ምስራቅ ጎጃም አንዳንድ ቦታዎች ትምህርት ያቆሙ ተማሪዎች እንዳሉ ገልጾ ትምህርት ሚኒስቴር ፈጣን ምላሽ ካልሰጣቸው ሙሉ ለሙሉ ትምህርት እንደሚያቆሙ ተናግረዋል።

 የአማራ ተማሪዎች ማህበር ዋና አላማው ተማሪዎችን ከ እንደዚህ አይነት ድርጊት መታደግ ነው የሚለው የማህበሩ ፕሬዘዳንት  አቶ እሸቱ ጌትነት ለትምህርት ሚኒስቴር፣ ለክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ለፈተናዎች ኤጄንሲ  በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ያስገቡ ቢሆንም መፍትሄ ባለማግኜታቸው ሰልፍ እንዲወጡ ሰልፉን ያነሳሳው ማህበሩ እንደሆነ ገልጾ የክልሉ መንግስት ያለውን አቅም ተጠቅሞ እነዚህን ተማሪዎች መታደግ ይገባዋል ብሏል።