የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ከሰሞኑ በተፈጠረውና ህገወጥ ካለችው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ጉዳይ ጋር በተያያዘ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ላይ ክስ ልትመሰርት እንደሆነ አስታወቀች።
ቤተ ክርስትያኗ በመግለጫዋ እንደገለፀችው ክስ የምትመሰርተው በቤተ ክርስትያኗ ላይ ተፈፅመዋል በተባሉት በደሎች “የመከላከል ኃላፊነት ያለባቸው እና ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ” ባለቻቸው የአዲስ አበባ ኮሚሽን፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ላይ እንደሆነ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ባወገዘችው “ህገ ወጥ ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት” ጉዳይ ዙሪያ በህግ የሚታዩ ጉዳዮችን የሚመለከት ኮሚቴ እና ንዑስ ኮሚቴ አቋቁሟለች። ሰብሳቢውን ጨምሮ አምስት አባላት የሚገኙበት የፍርድ ቤት ጉዳዮችን የሚመራው የችሎትና የክስ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ትላንት ምሽት መግለጫ ሰጥቷል።
ክስ የቀረበባቸው የፀጥታ አካላት ህገ መንግስቱና ሌሎች ህጎች የጣሉባቸውን ግዴታዎች እንዲወጡ ፍርድ ቤት ጥብቅ ትዕዛዝ እንዲያስተላልፍ ቤተ ክርስትያኗ መጠየቋን የንዑስ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሆኑት ጠበቃ እና የህግ ባለሙያ አቶ አንዱዓለም በእውቀቱ ተናግረዋል።
አቶ አንዱዓለም እንደገለፁት በክስ ዝግጅቱ ላይ ተጠሪ የተደረጉ እና በቀጣይ ተከሳሽ የሚሆኑ አካላትን አስታውቀዋል። በዚህም መሰረት ህጋዊ ሰውነት ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ከሳሽ መሆኗን ገልፀው “ህገ ወጥ የጳጳሳት ሹመትን” የመሩት ሶስቱ የቀድሞ አባቶች አባ ሳዊሮስ፣ አባ አውስጣቴዎስ እና አባ ዜና እንዲሁም በይቅርታ ከታለፉት አንድ ተሿሚ በስተቀር 25ቱ ተሿሚዎች እንደሚከሰሱ ተገልጿል።
በተጨማሪም በክሱ ላይ የፈደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪ መደረጋቸውን የገለፁት አቶ አንዱዓለም በእውቀቱ፣ ተጠሪ የተደረጉ አካላት ክስ የቀረበባቸው በመሆኑ በቀጣይ ተከሳሽ ይሆናሉ ብለዋል።
የቤተ ክርስትያኗ አቤቱታ የቀረበው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መሠረታዊ መብቶችና ነፃነት ችሎት ሲሆን፣ ኮሚቴው ተጥሰዋል ያላቸውን የህገ መንግስት አንቀፆች በመጥቀስ በዝርዝር አቅርቧል። የቤተ ክርስትያኗን የችሎትና የክስ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ በሰብሳቢነት የሚመሩት አቶ አንዱዓለም እንደተናገሩት “በህገ መንግስቱ ከለላ ማግኘት የሚገባቸው በደሎች በቤተ ክርስትያኗ፣ ቤተ ክርስትያኗን በሚያገለግሉ አባቶች፣ ካህናት እና ምዕመናን ላይ ተፈፅመዋል” ብለዋል።
ለክሱ መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን ያብራሩት አቶ አንዱዓለም በእውቀቱ የህይወት እና የአካል ደህንነት መብት አደጋ ውስጥ መውደቁ፣ የነፃነት መብት መጣስ፣ የክብር እና የመልካም ስም መብት መጣስ፣ የእኩልነት መብት መጣስ እንዲሁም የሀይማኖት፣ የእምነትና አመለካከት ነፃነት መጣስ ይገኙበታል።
የእኩልነት መብት መጣስን በተመለከተ በተሰጠው ማብራሪያ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት ሁሉም ዜጋ እኩል የህግ ዋስትና መስጠትን ቢደነግግም መንግስት ይህን ሽፋን መስጠት አልቻለም ያሉት የችሎትና የክስ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢው “ይልቁንም ይህን ህገ ወጥ ተግባር ፈፅመዋል ለተባሉት ግለሰቦች የተለየ እጀባ እና ጥበቃ በመስጠት አድልዎ ፈፅሟል” ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በመንግስት ፈንድ የሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙኀን የተለያዩ አመለካከቶችን እንዲያስተላልፉ የተጣለባቸውን ግዴታ አለመወጣታቸው አንዱ የመሰረታዊ መብት ጥሰት እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ያወገዘቻቸው በህገ ወጥ ሲመቱ ላይ የተሳተፉ አካላት “በየትኛውም መገናኛ ብዙኀን መግለጫ ከመስጠት እንዲታቀቡ ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ትዕዛዝ እንዲሰጥ” ቤተ ክርስትያኗ ለፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርባለች።
በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከሰሞኑን በተሰራጨው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “በሰላምና በሐይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ የሰጡት ማብራሪያ” ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ንግግር “አቤቱታ አቅርቦ መብትን ማስከበርን በሚገድብ ሁኔታ የተደረገ ነው” ተብሎ በአጠቃላይ ክሱ ውስጥ ከተጠቀሱ ቅሬታዎች አንዱ ነው።
ማንኛውም ዜጋ በፈለገው ቦታ ተንቀሳቅሶ በነፃነት የመኖር እና የመዘዋወር መብት እንዲሁም ንብረት የማፍራት፣ ንብረቱንም የመጠበቅ እና ያለአግባብ አለመነጠቅ መብቶችም መጣሳቸውንም አቶ አንዱዓለም በእውቀቱ ተናግረዋል። በተጨማሪም መንግስት የሀገርን ባህል፣ ታሪክ እና ቅርስ የመንከባከብ ግዴታውን አለመወጣቱ ተጠቅሷል።
የፍርድ ቤቱ ጉዳይ ሰኞ ጥር 29 ቀን ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ጠበቃ እና የህግ ባለሙያው አቶ አንዱዓለም በእውቀቱ በፌስቡክ ገፃቸው አስፍረዋል።