በተለያዩ የጥናት ዘርፎች ለሀገራችን ጉልህ አበርክቶ ከማድረግ አኳያ የ1940ዎቹ የቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ተማሪዎች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ብሎም በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዙሪያ ሰፊ ጥናቶችን በማድረግና መፅሐፍትንም በማበርከት ፕ/ር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ፣ ፕ/ር ታደሰ ታምራት፣ ፕ/ር ሉሌ መልአኩ፣ ሊቀ ሥልጣናት ሐብተማርያም ወርቅነህ (አቡነ መልከ ጼዴቅ)፤ በከፍተኛ ትምህርት፣ በፍልስፍናና ዲፕሎማሲ ዘርፍ ሃገራቸውን በኃላፊነት ጭምር በማገልገልና መፅሐፍትን በማበርከት ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስና ዶ/ር ኃይለ ገብርኤል ዳኜ ፤ በሕግ ዘርፍ ዶ/ር ገብረፃዲቅ ደገፉን፤ በቋንቋና ስነ ልሳን ዘርፍ ደግሞ ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉና ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ ተጠቃሽ የቅድስት ሥላሴ ተማሪዎች ናቸው፡፡ቀደም ብለው ከተሰናበቱን ደ/ር እጓለ አንስቶ ሁሉም በየተራ ወደ ማይቀረው ሲሄዱ የቀሩት ፕ/ር ጌታቸውም በዚሁ ወር ተከትለዋቸዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ የተወለዱት የረርና ከረዩ ውስጥ ሸዋ-ሸንኮራ በሚባል ቦታ ነው። ከመሪ ጌታ ግራዝማች ኃይሌ ወልደየስና ወ/ሮ አሰገደች ወ/ዮሐንስ ግንቦት 24 ቀን 1924 ዓ.ም ነው የተወለዱት። (በርግጥ የልደታቸው ቀንና ዓ.ም እርግጡን ለማወቅ ይቸገራሉ። ለመወሰንም ተቸግረው በ1931 እ.ኤ.አ እና 1933 እ.ኤ.አ ሲፈራረቅ መኖሩን ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ለትምህርት ማስረጃ መወሰን ስለነበረባቸው የልደት ቀናቸውን በግምት 04/19/31 እ.ኤ.አ አድርገውታል።)
ጣልያን ኢትዮጵያን መውረሩን ተከትሎ ጠላት የውልደት መንደራቸውን ሸንኮራን ስላወደመው ቤተሰባቸው ወደ አዲስ አበባ ሸሽቶ መጣ፡፡ በጠላት ወረራ ምክንያት ቀዬአቸውን ለቀው የመጡበት የሐገሪቱ ዋና ከተማ ከሌሎች አካባቢዎች በአንፃራዊነት የተሻለ ትምህርት በመኖሩ ለእሳቸው እንደ ጥሩ አጋጣሚም ነበር፡፡ ግራዝማችና መሪጌታ የሆኑት አባታቸው የግዕዝ ዕውቀት ስለነበራቸው ልጃቸውን ገና ትንሽ ብላቴና ሳሉ ነበር ግዕዝን ማስተማር የጀመሩት፡፡ እድሜያቸው ከፍ ሲል መንፈሳዊ ትምህርትን በቅድስት ስላሴ ለመከታተል እድልን በማግኘታቸው ድቁናን ተቀበሉ።
ወቅቱም ኢትዮጵያ “ከእስክንድርያ እየተሾሙ የሚላኩ ግብፃዊ ፓትርያርኮችን አልቀበልም” በማለቷ የመጀመሪያ የሆኑት ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ የተሸሙበት ነበር፡፡ በኮሌጁ ጥረትና በአዲሱ ፓትያርክ ይሁንታ ዲያቆን ጌታቸው ከሌሎች ሶስት ዲያቆናትና ሶስት መነኮሳት ጋር ሰባት ሆነው ለመንፈሳዊ ትምህርት ወደ እስክንድርያ ማቅናታቸውን ግለ ታሪካቸውን ባሰፈሩበት አንዳፍታ ላውጋችሁ መፅሐፍ ላይ ይገልፃሉ።
ከ1940ዎቹ አብዛኛውን ጊዜ በግብፅ ያሳለፉት እነ ጌታቸው የመጀመሪያዎቹን ዓመታት በአረብኛ ቋንቋ እጥረትና አስቀድሞም ዲግሪ የሌላቸው በመሆኑ የተሻለ የትምህርት ተቋም ገብተው ከመማር ይልቅ መለስተኛ የመነኮሳት ማሰልጠኛ ውስጥ እንዲያሳልፉ ተደረጉ። ይህም ያሳፈራቸው እነ ጌታቸውና አምሳሉ አክሊሉ (በኃላ ፕሮፌሰር) የተሻለ ትምህርት በዲግሪ ለመማር እንዲችሉ በወቅቱ የነበረውን የዩኒቨርሲቲ ቦርድ በማስፈቀድ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ለመማር መቻላቸውን በ'አንዳፍታ ላውጋችሁ' አውግተውናል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ለኪስ ከሚሰጣቸው ገንዘብ ላይ እየቆጠቡ በቀንና በማታ በሁለት ዩኒቨርሲቲዎች የተለያዩ የትምህርት አይነቶችን መማር ቀጠሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ከ 1952–1957 እ.ኤ.አ ባሉት ዓመታት ጌታቸው በግብፅ ከሚገኝው ኮፕቲክ የሥነ መለኮት ኮሌጅ (Coptic Theological College) የሥነ መለኮት ዲግሪ (B.D.) ከካይሮ አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ (American University of Cairo ) ደግሞ የሶሲዮሎጂ ዲግሪን ጎን ለጎን በመማር ማግኘታቸውን Adam Carter McCollum በ2017 እ.ኤ.አ በአርታኢነት ባሳተመው Studies in Ethiopian Languages, Literature, and History መፅሐፍ ላይ ገልፆአል።
በግብፅ በቆዩባቸው አመታትም የሴም ቋንቋዎችን የመማር ፍላጎት ውስጣቸው ስላደረ ትምህርቱ ወደሚሰጥበት ጀርመን ሀገር በመሔድ ለማጥናት ጀርመንኛ ቋንቋን መማር ጀምረው ነበር።
በነዚያ ረዘም ያሉ የእስክንድርያ ቆይታቸው በሐገር ውስጥ ከነበረው ደከም ያለ የትምህርት አቅርቦት (ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በሀገሪቱ ከተጀመረ ጥቂት አመታትን ብቻ በማስቆጠሩ) በተሻለ ያገኙ ይመስላል። ስላገኙት ትርፍም ሲናገሩ "በግብፅ ሕይወቴ ካገኘሁት የኮሌጅ ትምህርት ሌላ አንደኛ የፖለቲካ ንቃት ሰጥቶኛል ፤ ሁለተኛ የሃይማኖት እምነቴን አስክሮልኛል፤ ሶስተኛ ለመጀመሪያ ጊዜ የወደፊት ሙያዬን እንድመርጥ ዕድል ሰጥቶኛል።" ይላሉ።
የፖለቲካ ንቃታቸው በግብፅ ከነበራቸውን ቆይታ እንደጀመረ የሚናገሩት ፕሮፌሰር እድሜያቸው ገፍቶ እንኳን ስለሃገራቸው የሚያሳስባቸውና በተለያዩ ጊዜያት በሚዲያዎች ፣ በጋዜጦችና በኢንተርኔት መረብ ስለሃገራቸው ወቅታዊ ሁኔታ ሲፅፉ ይታወቃሉ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ገብተው ለምን እንዳልተሳተፉም ሲጠየቁ "በፖለቲካው ውስጥ ስለመሳተፍ አስቤ አላውቅም" ይላሉ።
ከግብፅ በኃላ ጌታቸውና ጓደኛቸው አምሳሉ አክሊሉ ወደ ጀርመን በመጓዝ ትምህርትን ለመቅሰም ሌላ የአለም ክፍልን ለማሰስ ተዘጋጁ። ጌታቸው በጀርመን ለአንድ አመት ያህል በጎቲገን ዩኒቨርስቲ ከተማሩ በኃላ የሴም ቋንቋዎችን በተሟላ መልኩ ለማጥናት ወደ ቱቢገን ዩኒቨርስቲ ገቡ። በቱቢገንም በ"የኢትዮጵያ የሴም ቋንቋዎች የግስ ስርዓት " በሚል (በጀርመንኛ) የመመረቂያ ዲዘርቴሽን ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ በቁ።
ከጀርመን ሀገር ሲመለሱም ዶ/ር ጌታቸው የስራ ዓለም ተሞክሯቸውን ያሟሹት በወቅቱ በከተማ ይፍሩ ይመራ በነበረው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ነው፡፡ ለጥቂት የክረምቱ ወራት ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ካሳለፉ በኃላ መስከረም ሲጠባ ወደ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ለማስተማር ገቡ፡፡ በዩኒቨርሲቲውም ከ1955 - 1967 ዓ.ም. ግዕዝ ፣ የግዕዝ ሥነ ፅሁፍ ፣ የአማርኛ ሰዋሰውና የአፃፃፍ ዘዴ እንዲሁም ዐረቢኛ አስተምረዋል። ከዚህም ባሻገር በሐገር ውስጥ ባለው የመፅሐፍ ቅዱስ ማህበር የማህበሩ ኮሚቴ አባል በመሆን በ1997 እ.ኤ.አ ከተደጋጋሚ እርማት በኃላ በታተመው የመፅሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ ላይ አሻራቸው ትልቅ ነው።
ፕሮፌሰሩ የዕድሜያቸውን ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ያሳለፉት በዊልቼር ላይ ነው፡፡ አብዮቱ ፈንድቶ ንጉሳዊው ዙፋን ከተገረሰሰ በኃላ ወታደራዊው መንግስት አፈሙዙን ሲያዞርባቸው ብዙም አልቆየም፡፡ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ልዕልና በመታገላቸው ጥርሱን የነከሰባቸው "አብዮት" በአንድ አሳቻ ቀን ተኩስ ከፈተባቸው፡፡ ከተኮሰባቸው ብዙ ጥይቶችም አንዷ አከርካሪያቸውን ስላገኘች እስከሚሞቱበት እለት በእግራቸው እንዳይራመዱና በዊልቼር ላይ ተቀምጠው እንዲያሳልፉ አድርጋቸዋለች፡፡
ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፍ ያለባቸውና በባለሙያዎች መጠናት የሚገባቸው መዛግብት በነጮችና በወራሪዎች በመዘረፍ ፣ በጠላት በመውደምና በእድሜ ብዛት አርጅተው በመበላሸት ሲጠፉ ቆይተዋል። እነዚህንም የኢትዮጵያን የብራና ላይ መፅሐፎች ወደ ማይክሮፊልም በመቀየርና መፅሐፍቱን በመተርጎም የተደበቁ ዕውቀቶችን በማውጣትና በመጠበቅ ትልቅ ሊቅ ናቸው። በዚህም ስራቸው ፊሎሎጂስቱ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ከብራናዎች ጋር አሳልፈዋል።
በመጥምቁ ዮሐንስ በተሰየመው የቤኔዲክታውያን ካቶሊኮች መነኮሳት ዩኒቨርስቲ ያቋቋመው (Saint John's University) የማይክሮፊልም ቤተ መፅሐፍት (አሁን Hill Museum & Manuscript Library) ውስጥ ጉልህ ሚናን ተጫውተዋል። በተቋሙ ውስጥ ያሉ ከ5000 በላይ የብራና ላይ ታሪካዊ መዛግብቶች ካታሎግ አዘጋጅተዋል። ይህም ተቋም እእንዲጠሩበት "የገዢዎች ፕሮፌሰር " (Regents Professor ) የሚባለውን በከፍተኛ ማዕረግ እንዲሰጣቸው ወነሰ።
የMACARTHUR FELLOWS PROGRA በስራቸው ፊሎሎጂስቱንና ሊንጉዊስቱን ፕሮፌሰር በ1988 እ.ኤ.አ "ጂኒየስ አዋርድ " ሸልሟቸዋል ። የብሪትሽ አካዳሚም በ1987 እ.ኤ.አ ፌሎው እንዲሆኑ መርጧቸዋል። ይህንንም በማግኘት የመጀመሪያው አፍሪካዊ ናቸው።
ይሁን እንጂ ልባቸው የሚናፍቀው የሴም ቋንቋ ሊቁ ከሐገራቸዉ ተቋም እውቅና ማግኘትን ነበር። በደርግ ዘመን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥናትና ምርምር ከፍተኛ አስተዋፆ ላበረከቱ የከፍተኛ ኒሻን ሽልማት አዘጋጅቶ ፕሮፌሰሩን አጭቷቸው ነበር። ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀውንም ሽልማት የሚሰጡት በወቅቱ የሐገሪቱ ፕሬዝደንት የነበሩት ሌ/ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ነበሩ፡፡ ይህንንም አስቀድመው ፕሮፌሰሩ ሲያውቁ "በንፁሐን ደም ከተጨማለቀ እጅ ማን ምን ይወስዳል?" በማለት ሽልማቱን ሳይቀበሉ ቀርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሊቀ ሊቃውንት መሓሪ ትርፌ (በኃላ አቡነ ጴጥሮስ) በግብፅ ደግሞ የአቡነ ሽኖዳ ደቀ-መዝሙር የሆኑት ፕሮፌሰር ጌታቸው የባለ ብዙ ቋንቋዎች ችሎታ ባለቤት ነበሩ፡፡ የአማርኛ ፣ ግዕዝ ፣ ቅብጥ (ኮፕቲክ) ፣ ጀርመንኛ ፣ ግሪክኛ፣ ኢብራይስጥ ፣ ላቲን ፣ እንግሊዝኛና አረብኛ ችሎታ አላቸው፡፡
የሴም ቋንቋ ሊቁ ከ250 በላይ ጥናታዊ ፅሁፎችን በተለያዩ ሳይንሳዊ ሕትመቶች ላይ ሲያሳትሙ ከ30 በላይ መፅሐፍትን ከግዕዝ ወደ እንግሊዘኛ በመተርጎም አሳትመዋል። ከእነዚህም ዉስጥ እ.ኤ.አ በ1990 የታትመዉ The Faith of the Unctionists in the Ethiopian Church (Haymanot Masihawit), ፣ በ1991 The Epistle of Humanity of Emperor Zar'a Ya 'aqob (Tomara Tasba't )፣ በ1980 The Martyrdom of St. Peter, Archbishop of Alexandria, Analecta Bollandiana, እንዲሁም በ1982 A New Look at Some Dates on Early Ethiopian History" Le Museon, ጥቂቶቹ ናቸው።
ከዚህም ባሻገር በአማርኛ ቋንቋ፤ ባህረ ሀሳብ ፣ የአባ ባህርይ ድርሰቶች ፣ ደቂቀ እስጢፋኖስ ፣ ስለ ግዕዝ ሥነ ፅሁፍ ከተሰጡ አንዳንድ ማስታወሻዎች ፣ አንዳፍታ ላውጋችሁ ፣ ግዕዝ በቀላሉ በአማርኛ ከታተሙ የፕሮፌሰሩ ስራዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ።
ብሪትሽ አካዳሚ ትልቅ አሻራ ላበረከቱ ምሁራን የሚሰጥ "Edward Ullendorf Medal" የተሰኘ በስማቸው የተሰየመ ሜዳል ያቋቋመላቸው እንግሊዛዊው ፕ/ር Edward Ullendorf ፕ/ር ጌታቸው ላበረከቱት ምሁራዊ አስተዋፅዖ በ1991 Journal of Semitic Studies Monograph ስለእሳችዉ ባሰፈረው ፅሁፍ “የስራዎቹ (የፕ/ር ጌታቸው) አስፈላጊነት ለኢትዮጵያ ስነ ጽሁፍ ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ ኣብያተ ክርስቲያናት ድርሳናት ጥልቀት ጭምር ነው” በማለት አመስግኗቸው ነበር፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በ1996 ዓም በታተመው "ደቂቀ እስጢፋኖስ " የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ መፅሐፍ ላይ ባሰፈሩት ቀዳሚ ቃል እንዲህ ብለው ነበር፦
" የዛሬው ትውልድ ለፕሮፌሰር ጌታቸው ባለውለታ ነው፤ እነዚህ ለዐዋቂው ለውጪው ዓለም ክፍት ሆነው ለባለቤቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተቆልፈውበት የነበሩ ፅሑፎች ናቸው። እስከዛሬ አንድም ንጉስ ወይም ፕሬዚዳንት እነዚህን ታሪካዊ ሠነዶች አላስተረጎመም አላሳተመም። ጌታቸው በራሱ ጥረት ብቻ እነዚህን ፅሁፎች በአማርኛ እየተረጎመ ለመጀመሪያ ጊዜ ለንባብ ስላበቃውና ስለራሳችን እንድንማር በሩን ስለከፈተልን ከፍተኛ ምስጋና ይገባዋል። በበኩሌ የምጨምረው በዚህ ሳያበቃ እግዚአብሔር ዕድሜውን እና ብርታቱን ሰጥቶት ሌሎቹንም እንዲያበረክትልን ነው። "
መስፍን ይህንን ከተናገሩ ከአስራ ሰባት ዓመታት በኃላ ሐገራቸውን በልዩ ልዩ ጎዳና በትጋት እንዳገለገሉ ሁለቱም ፕሮፌሰሮች በአንድ አመት ተከታትለው ለዘላለሙ ተሰናብተዋል። በቀድሞው ሲዳሞ ክፍለ ሐገር ይርጋለም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከወ/ሮ ምስራቅ አማረ ጋር ጋብቻ በመፈፀም አራት ልጆችን በወሊድ ሁለት ልጆችን ደግሞ በማደጎ ባጠቃላይ ስድስት ልጆችና ዘጠኝ የልጅ ልጆች ያፈሩት የግዕዝ ስነ ፅሁፍ ሊቁ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በ89 ዓመታቸው ሰኔ 4/2013 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ተለይተዋል፡፡
ስርዓተ ቀብራቸውም አርብ ሰኔ 11/2013 ዓ.ም በሃገረ አሜሪካ ኮርጅቪል ሚኒሶታ ግዛት ፤ በቅዱስ ዮሐንስ ገዳም ተከናውኗል፡፡ በስርዓተ ቀብራቸው ማግስት ሰኔ 12/2013 ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን ለርሳቸው በተደረገ ዝክር ላይ ዶ/ር መርሻ አለኸኝ ‹‹ፕሮፌሰር ጌታቸው - ሐራሲ መፅሐፍት›› በሚል ርዕስ ንባብ አቅርበው ነበር፡፡ ረዘም ባለው ንባባቸው ውስጥ እንዲህ ብለው ሊቁን ገልፀዋቸዋል፡፡
“ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በሕይወት ዘመናቸው ያስተማሩን ባሳተሟቸው መፅሐፍቶችና ጽሁፎች ብቻ አይደለም፡፡በአካዳሚያዊ ሥነ ምግባራቸው፤ ለቤተ ክርስቲያናቸውና ሀገራቸው በነበራቸው ፍቅር፣ በቤተሰብ ሕይወታቸው፤ ወዘተ ሁሉ ነበር፡፡ ሌላውን ሁሉ ትተን አካዳሚያዊ ሥነ ምግባራቸውን ብፋ ብናይ ፤ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሊጠኑ ቀርቶ ሊዘረዘሩ የሚያዳግቱ ስራዎችን ሰርተው አበርክተው ሳለ፤ ራሳቸውን ያላስታበዩ፣ ይልቁንም የእግራቸውን ጫማ ጠፍር እንኳን ለመንካት የማንችለውን ልጆቻቸውን አስተምሩኝ ብለው የሚጠይቁ፤ ‘መጻፍ ቀርቶ ገና አንብቤ ያልጨረስኩተማሪ ነኝ’ እያሉ ራሳቸውን ሲገልፁ የነበሩ ትሑት አባታችን ነበሩ፡፡”
የፕሮፌሰሩ ደቀ መዝሙር የሆኑት በአማን ነጸረም “መልአከ ሞት ሆይ፡- መንበረ ጸባዖት ይዘኸው ስትቀርብ ፈጣሪያችንን እንዲህ በልልን፡- ዛሬ አንድ ግለሰብ ፣ ምሁር ፣ ሊቅ ፣ አስተማሪ፣ አጥኚ ፣ መልካም ባልና የልጆች አባት፣ የሴማውያን ልሳናት ተጠሪ ፣የቴዎሎጂ ምሩቅ ፣ የሊቀ ሊቃውንት መሃሪ ትርፌ (ኋላ አቡነ ጵጥሮስ) የሐዲሳት ትርጓሜ ደቀ መዝሙር ሳይሆን ግዙፍ ሕያው ተቋም ከነአዕማዱ ይዤ መጣሁ በል! ተናገር!” ሲሉ ‹‹መልአከ ሞት አደራህን ተናገር›› በሚል ርዕስ ባጋሩት ጽሁፋቸው ውስጥ ፕሮፌሰሩን ይገልጻሉ፡፡