ከ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያውያን በገዳምነት ይጠቀሙበትና ይኖሩበት እንደነበረ የሚጠቀስለት በኢየሩሳሌም የሚገኘው የዴር ሡልጣን ገዳም በተለያየ ጊዜ በተለያዩ አካላት የባለቤትነት ጥያቄ ሲነሣበት መቆየቱ ይታወቃል። በተለይ የግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን የባለቤትነት ጥያቄ ስታነሳ መቆየቷን በተለያዩ ጊዜያት የወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ።
ማኅበረ ቅዱሳን በ2011 ዓ.ም ባሳተመው ‹‹ስምዐ ተዋሕዶ›› መፅሔት ላይ የተለያዩ ሊቃውንትንና የታሪክ ድርሳናትን ዋቢ አድርጎ ስለ ዴር ሡልጣን ገዳም በፃፈው ፅሁፍ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት፣ በአደገበት፣ በአስተማረበት፣ በተሰቀለበት፣ በተቀበረበት እንዲሁም በተነሣበት በጎልጎታ ተራራ የተመሠረተው የዴር ሡልጣን ገዳም በኢትዮጵያውያን ነገሥታት፣ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያን ባለሀብቶች እና መነኰሳት እንደተሠራ የታሪክ መዛግብት እንደሚናገሩ ያትታል። በተጨማሪም እስከ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ ገዳሙን እና በገዳሙ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መነኰሳት በኢትዮጵያ መንግስት ሲረዱ መኖራቸውንም ይጠቅሳል።
በሌላ በኩል ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በፃፉት “ዜና ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም” በተሰኘው መፅሐፍ ገዳሙ ከንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ጀምሮ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ርስት ሆኖ መቆየቱን በመጥቀስ “በዘመን ብዛት እንደ ግብፅ ያሉ ቦታው ይገባኛል ባዮችን አፍርቶ እስከ ዛሬ ድረስ መፍትሔ ያልተበጀለት የውዝግብ ምክንያት ሊሆን መቻሉ ተፅፏል።
በመሆኑም ለአመታት የቀጠለው ውዝግብ በያዝነው ሳምንት አገርሽቶ በቦታው ላይ በግብፃውያን እና በኢትዮጵያውያን መካከል አምባጓሮ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። በቦታው ላይ የነበሩ እማኞች ለአምባጓሮው መነሻ የሆነውን ምክንያት ሲናገሩ ሰኞ ሚያዝያ 10 ሌሊቱን ግብፃውያን ወጣቶች የገዳሙን መግቢያ በር የግብጽ ባንዲራ ቀለም ቀብተው ማደራቸውን እና በዚህ የተቆጡ ኢትዮጵያውያን ለሀገሪቱ ፖሊስ አመልክተው ግብፃውያኑ የቀቡትን ባንዲራ እንዲያጠፉላቸው ቢጠይቁም ህግ አስከባሪዎቹ እስኪደርሱ ግን የግብፃውያኑ እና የኢትዮያውያኑ ቡድን በተለያየ አቅጣጫ በመቆም የተለያዩ ተቃውሞዎች ሲያሰሙ የደረሰው የሀገሪቱ ህግ አስከባሪ ቡድን ወጣቶቹ እንዲበተኑ አድርጎ ጉዳዩም ያለመፍትሄ በይደር መቆየቱን ተናግረዋል።
ይህን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የኢትዮጵያ የኢየሩሳሌም ገዳማት ዋና መጋቢ አባ ዘበዓማን ሳሙኤል፣ ገዳሙ የውዝግብ መነሻ ከመሆኑም ባሻገር ከዘመን ብዛት የተነሣ ማርጀቱ፣ ለዘመናት በውስጡ የሚኖሩ የበላይ ጠባቂ አባቶች ካህናትና መነኰሳት የሚገባቸው እንክብካቤ እየተደረገላቸው አለመሆኑ እና የመሳሰሉት ነገሮች ለገዳሙ የዘመናት ተግዳሮት ሆነው መቆየታቸውን ሲገልፁ፣ “እነዚህንና የመሳሰሉ ችግሮችን እያስተናገደች ያለችው የገዳሙ ባለቤት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳሙን ማደስ እንኳን በማትችልበት መልኩ መብቷን ተነፍጋ ቆይታለች። በእርግጥ የዴር ሡልጣን ገዳም ታሪካዊ እንደመሆኑ መጠን የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የዓለም ቅርስም ጭምር ነው” በማለት ኢትዮጵያ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዚህ ታላቅ ቅርስ ባለቤት መሆናቸው አለም የሚያውቀው ሀቅ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለበት፣ በተቀበረበት እና በተነሣበት ታሪካዊቷ የኢየሩሳሌም ከተማ ኢትዮጵያውያን አስበው እና አስቀድመው ገዳም መመሥረታቸው በዚያ ዘመን የበረውን የኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ሥልጣኔ፣ ብልህነት እና አርቆ አስተዋይነት የሚገለጽበት ቋሚ ምስክር ጭምርም ነው” ያሉት መጋቢው ግብፃውያኑ ያልነበሩበትንና ያልኖሩበትን ይህን ቅዱስ ቦታ ቀምቶ ለመውሰድ ከመንግሥት ጀምሮ እስከ ተራው ሕዝብ ድረስ ዓላማ አድርገው ሲንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ሆነች የኢትዮጵያ መንግሥት ግን እንደሚገባው ይዞታውን ለማስከበር ብዙ ርቀት ሲሄዱ አልታዩም” ብለዋል።
“በመሆኑም በታሪክ ያልነበሩ በጉልበት የራሳቸው ለማድረግ አዲስ ታሪክ ለመፍጠር ሲሯሯጡ መላው ኢትዮጵያውያን ዝም ብለው መመልከት የለባቸውም። ይልቁንም ስለ ዴር ሡልጣን የሚናገሩትን የታሪክ ድርሳናት ወደ ፊት በማምጣት የገዳሙ ባለቤት መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል” ያሉት መጋቢው በኢየሩሳሌም የገዳማት ይዞታዎች ያሏት ኢትዮጵያ መሪዎቿ እንደ ሀገር ከፊት ቀድመው ይዞታዋን በማስከበር ረገድ ከእስራኤል መንግሥት ጋር በመነጋገር ዘመናት ለቆየው ችግር እልባት ሊሰጡት ይገባል” ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በሌላ በኩል የትንሳዔ በዓልን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም አቅንቶ በቦታው የሚገኝ ያብስራ ይባበ የተባለ ወጣት “በእለቱ ከጓደኞቼ ጋር ከዴር ሱልጣን አቅራቢያ የሚገኝ ሌላ ገዳም ውስጥ ነበርን። ግርግር መፈጠሩን ስንሰማ ወደዛው ሄድን፣ በቦታው ስንደርስ ግብፃውያን ገዳሙ ግቢ ውስጥ በጉልበት በመግባት ወረራ በመፈጸማቸውን እና በቦታው በሚኖሩ አበው መነኮሳት እና ጥሪውን ሰምተው በተሰባሰቡ ጥቂት ምዕመናን ትግል ከግቢው እንዲወጡ መደረጋቸውን ሰማን፣ ከዛ በኋላ ገዳሙ ለሰዓታት በጸጥታ አስከባሪዎች ተከቦ ነበር” ሲል ይናገራል።
ያብስራ አክሎም ግብፃውያኑ በግቢ ውስጥ የሽቦ ገመዶችን በመወጠር ተጨማሪ የነሱን ባንዲራ ግቢ ውስጥ ለመስቀል እየተንቀሳቀሱ እንደነበር በመግለፅ፣ በእስራኤል ሐገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ ዴር ሱልጣን የኢትዮጵያ ርስት ገዳም በመሄድ አባቶች በብዙ መሰዋዕትነት ሰርተው ያቆዩትን ርስት ከአበው መነኮሳት እና ከምዕመናን ጋር በመሆን ተገኝተው እንዲጠብቁና መንግስትም ይህን እንዲያግዝ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበላይ አካላት የሆኑት ቅዱስ ሲኖዶስና ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስለ ዴር ሡልጣን የተጻፉ የታሪክ መዛግብትን አደራጅተው በማቅረብ የገዳሙን ታሪካዊ ባለቤትነት እንዲያረጋግጡ መልዕክቱን አስተላልፏል።
የማህበረ ቅዱሳን አዲስ አበባ ማዕከል ፀሃፊ ካሳሁን ምትኩ በበኩሉ በጉዳዩ ላይ ያለውን ምልከታ ሲያካፍለን “በኢየሩሳሌም የዴር ሡልጣን ገዳም የኢትዮጵያ ይዞታ ላይ በግብፅ እየታየ ያለው ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ቅዱስ ሲኖዶስ በየወቅቱ በጽሑፍም ሆነ በቃል ለሚመለከተው ሁሉ በአካል ቀርቦ ከማመልከት የተገታበት ጊዜ የለም፣ እኛ የቤተክርስትያኗ ወጣቶችም ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሕይወታቸውን ሳይቀር መስዋዕት በማድረግ ጠብቀው ያስረከቡንን ቅርስ ለቀጣይ ትውልድ የማስረከብ ኃላፊነታችንን እንወጣለን” ሲል ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከሶስት አመት በፊት ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ከዚህ የገዳም ይዞታ ጋር በተያያዘ ባወጣው መግለጫ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ወርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ “የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ በይዞታችን ላይ አግባብነት የሌለው ሥራን የማደናቀፍና በታሪክም ሆነ በማንኛውም የሰነድ መረጃ የሌለው የባለቤትነት ጥያቄ በማንሳት እየተፈጠረ ያለውን አላስፈላጊ ሁከትና ብጥብጥ ማቆም አለባቸው፤ ዴር ሡልጣን ትናንትም ዛሬም ነገም የኢትዮጵያ ገዳም ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
ከዚህ ጋር በተያየዘ አስተያየታቸውን ያካፈሉን የታሪክ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ፀሀይ ምክሬ “በኢየሩሳሌም በሚገኘው የዴር ሱልጣን ገዳማት የኢትዮጵያና የግብጽ የሃይማኖት መሪዎች ውዝግብ ሁለት መቶ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ በዴር ሱልጣን ገዳም ያላት መብት ከግብጽ ወደ አካባቢው መግባት አስቀድሞ ብዙ ዘመናትን ያስቆጠረ እንደሆነ ታሪክ ይመሰክራል” ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ ዶ/ር ፀሀይ ገለፃ በ18ኛው ክፍለ ዘመን ኢብራሂም ጉሃሪ የተባሉ ግብጻዊ የሃይማኖት ሰው ከስምንት ረዳቶቻቸው ጋር ወደ ኢየሩሳሌም በማቅናት የይገባኛል ጥያቄ ካነሱበት ጊዜ ጀምሮ በሁለቱ ሀገራት መካከል ዴር ሱልጣን የውዝግብ ማዕከል ሆኖ ቆይቷል። ኢትዮጵያ በእስራዔል ከ4ኛው ክፍለዘመን አንስቶ ጠንካራ ይዞታ ያላት ሲሆን ዴር ሱልጣን በተሰኘው ገዳም አራት አብያተ ክርስቲያናት የነበራት ኢትዮጵያ በየዘመናቱ በነበሩ ነገስታት ተገቢው ድጋፍ ባለመደረጉ ቤተክርስቲያናቱን ልታጣቸው ችላለች።
አሁን የቀራት በገዳሙ ጣሪያ የሚገኝ አንድ የጸሎት ቦታ ሲሆን ይህንንም ለመንጠቅ በግብጾች በኩል ከፍተኛ ጫና ሲደረግ ቆይቷል። በተለይም የፋሲካ በዓል ሲደርስ ግብጾች በብዛት ወደ ገዳሙ በመምጣት ወረራ የሚፈጽሙበት የተለመደ ተግባራቸው ኢትዮጵያውያን በገዳሙ ያላቸውን መብት የሚጋፋ እንደሆነ የጠቀሱት ተመራማሪው ከ1970 እኤአ ጀምሮ በግብጾች በኩል የሚደረገውን ጫናና ወረራ በመቋቋም የቀረውን ይዞታዋን አስጠብቃ የቆየችው ኢትዮጵያ በየጊዜው የበረታ ጫና ይገጥማታል ብለዋል።
ይሁን እንጂ የተፈጠረውን ውዝግብ በሚመለከት በግብጽ ዜና ጣቢያዎች በኩል በአንፃሩ የወጡት ዘገባዎች ደግሞ ለውዝግቡ መነሻ የሆነው በእየሩሳሌም ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ቁጥጥር ስር በሚገኘው በዴር ሱልጣን ገዳም ውስጥ ኢትዮጵያውያን መነኮሳት በቦታው ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ በመስቀል እና በቦታው ላይ በነበሩ የግብፅ መነኮሳት ላይ ጥቃት በማድረጋቸው እንደሆነ ሪፖርት አድርገዋል።
እነዚህ የግብፅ የዜና ምንጮች እንደዘገቡት ኢትዮጵያውያኑ ባንዲራቸውን ሲሰቅሉ በምላሹ የኢየሩሳሌም ቅድስት መንበር ሜትሮፖሊታን አንባ አንቶኒዮስ የግብፅን ባንዲራ በገዳሙ ላይ በማውለብለብ መመለሳቸውን እና የግብፅ መነኮሳት ደግሞ ኢትዮጵያውያን ባንዲራቸውን እንዲያነሱ እንዲያስገድዱላቸው የእስራኤልን ፖሊስ መጠየቃቸውን በመጥቀስ በገዳሙ ከሁለቱም ወገኖች በመጡ መነኮሳት መካከል የቃላት ሽኩቻ ታይቶ ወደ ዱላ ሳይቀየር የእስራኤል ፖሊስ ጣልቃ መግባቱንም ፅፈዋል።
የግብፅ ታሪክ ምሁራን በበኩላቸው ዴር ሱልጣን ገዳም ሱልጣን ሳላህ አልዲን አል አዩቢ በተባለ የግብፅ ንጉስ መሰየሙን በመጥቀስ ሱልጣኑ በዘመናቸው ኢየሩሳሌምን ይዘው ከነበሩት ክሩሳዳዊያን ጦር ሰራዊት ጋር ባደረገው ጦርነት አሸንፎ ለግብፅ ኮፕቲክ ቤተክርስትያን ማስረከባቸውን ይናገራሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ ሚያዝያ 13 ግብፃውያን ወጣቶች በእስራዔል ፖሊስ ተከበው በበሩ ላይ የተቀባውን የግብጽ ባንዲራ ቀለም ሲያጠፉ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች እና ፎቶዎች በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘዋወሩ ተስተውሏል።