ሚያዝያ 14 ፣ 2014

የማይቀመሰው የፋሲካ የበዓል ገበያ

City: Addis Ababaየአኗኗር ዘይቤወቅታዊ ጉዳዮች

በበአል የገበያውን ሁኔታ በታዘብነው መሰረት የበሬ ሽያጭ ከ25 ሺህ ብር እስከ 120 ሺህ ብር በሚደርስ ዋጋ ለገበያ ቀርቧል

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

የማይቀመሰው የፋሲካ የበዓል ገበያ
Camera Icon

Credit: ilias Kifle

በዚህ ሳምንት መጨረሻ ሚያዝያ 14 የስቅለት በዓል እና ሚያዝያ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. የትንሳኤ በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ይከበራሉ። በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድም የኢድ አል ፈጥር በዓል ሊከበር ጥቂት ቀናት ይቀሩታል። 

የአዲስ ዘይቤ ባልደረባዎች ከአዲስ አበባ፣ ጎንደር እና ደሴ ከተማዎች የበዓላቱን መቃረብ ተከትሎ ለበዓል በስፋት የሚገዙ መሰረታዊ አቅርቦቶችን ዋጋ ታዝበዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ወደ አቃቂ የቁም እንስሳት ገበያ ማዕከል በተደረገው ቅኝት በሁሉም ንግድ ዓይነቶች በሚባል ደረጃ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተስተውሏል። በስፋት በኢትዮጵያ የማህበራዊ ወዳጅነት ምልክት ተደርጎ ለሚወሰደው ቅርጫ የሚገዙት በሬዎች ከ25 ሺህ ብር እስከ 120 ሺህ ብር እየተሸጡ ይገኛሉ። 

በተጨማሪም የበሬ አማካይ ዋጋዎች በመጠን ዝቅተኛ የሆኑት ወይም ለስድስት ሰዎች ቅርጫ ይበቃል ተብሎ የሚገመተው ከ25 ሺህ እስከ 35 ሺህ ብር ተሽጧል። መካከለኛ መጠን ያላቸው ከ40 ሺህ እስከ 60 ሺህ ብር እንዲሁም በነጋዴዎች እይታ ከፍተኛ የሚባሉትና ለ10 ሰዎች ይበቃሉ የሚባሉት ከ60 ሺህ እስከ 120 ሺህ ብር መሸጣቸውን አዲስ ዘይቤ ታዝቧል።

ኣቶ ይታገሱ ሰይፈሚካኤል በአቃቂ ገበያ ለበዓል ሊሸምቱ ሲዟዟሩ አዲስ ዘይቤ አግኝቷቸዋል። “እስካሁን የሰማኋቸው ዋጋዎች የሚቀመሱ አይመስሉም። የሰው ልጅ እኮ የመኪና አደጋ ደርሶበት ከ10 ሺህ ብር በላይ ካሳ አያገኝም፤ እንዴት የበግ ዋጋ 15 ሺህ ብር ይጠራል?” ሲሉ ግርምታቸውን አጋርተውናል።

በተመሳሳይ ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረጉ ሸማቾች የዋጋዎቹ ጉዳይ አሳሳቢ መሆናቸውን ገልፀዋል። “ለበዓል ዋጋ እንደሚጨምር ይጠበቃል ነግር ግን በዚህ ደረጃ ከጨመረ አዲስ አበባ ፆም መግደፍ እና በዓል ማክበር የማይቻልባት ከተማ መሆኗ ነው” ያሉት ደግሞ ወ/ሮ ዝናሽ ይታገሱ የተባሉ ሸማች ናቸው።

በዚሁ የአቃቂ ገበያ፣ በግ እንደየመጠኑ ከ6 ሺህ 800 እስከ 7 ሺህ 300 ብር፤ መካከለኛ የሆኑት ከ8 ሺህ እስከ 9 ሺህ ብር እና ከ10 ሺህ እስከ 12 ሺህ እንዲሁም እንደመጠናቸው ከፍተኛ የሚባሉት እስከ 15 ሺህ ብር እየተሸጡ ይገኛል። 

የፍየል ዋጋም እንደሌሎቹ ሁሉ ዋጋው የናረ ሆኗል። መጠኑ ዝቅተኛ የሆነ ፍየል ከ8 ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር፤ መካከለኛዎቹ ከ11 ሺህ እስከ 15 ሺህ ብር እንዲሁም ከፍተኛው ከ18 ሺህ እስከ 25 ሺህ ብር መሸጣቸውን አዲስ ዘይቤ ተመልክቷል።

በአዲስ አበባ ከተማ የዶሮ ዝቅተኛ ዋጋ 550 እስከ 650 ብር፤ መካከለኛ ዶሮዎች ከ700 እስከ 850 ብር እንዲሁም ከፍተኛ የሚባሉት ዶሮዎች ከ900 እስከ 1 ሺህ 200 ብር መሸጣቸውን ማወቅ ተችሏል። እንቁላል ከ8 ብር እስከ 10 ብር በተለያዩ አካባቢዎች እየተሸጠ ሲሆን፣ ዘይት ባለ አምስት ሊትር ከ 980 ብር እስከ 1 ሺህ 300 ብር፣ ቀይ ሽንኩርት በኪሎ ከ42 ብር እስከ 47 ብር እየተሸጡ ይገኛሉ።

የአዲስ ዘይቤ የጎንደር ከተማ ቅኝትም ዋጋዎቹ ካለፉት ወራት ጋር ሲነፃፀሩ በሁሉም ዓይነት አስቤዛዎች ላይ ጭማሪ ታይቷል። በጎንደር ከተማ እንቁላል በ9 ብር እየተሸጠ ሲሆን ካለፉት ወራት ጋር ሲነጻጸር የአንድ ብር ጭማሪ አሳይቷል። 

ሽንኩርት በኪሎ 40 ብር ሲሸጥ፣ ካለፈው አንድ ወር ጋር ሲነጻጸር የ 18 ብር ጭማሪ ማሳየቱን አዲስ ዘይቤ ታዝቧል። ዘይት ባለአምስት ሊትር በ1000 ብር ለገበያ የቀረበ ሲሆን ካለፈው መጋቢት ወር ጋር ሲነፃፀር የ 50 ብር ጭማሪ አሳይቷል። 

የዶሮ ገበያን በተመለክተ ከ550 ብር እስከ 750 ብር እንደየመጠናቸው ልዩነት ሲሸጥ ካለፉት ወራት ጋር ሲነፃፀር ከ100 ብር እስከ 200 ብር መጨመሩን በጎንደር ከተማ የገበያ ቅኝት ማየት ተችሏል። 

በጎንደር የፍየል ዋጋ ካለፉት ወራት ጋር ሲነፃፀር እስከ 2 ሺህ ብር የሚደርስ ጭማሪ አሳይቷል። ትልቅ ፍየል 12 ሺህ ብር፣ መካከለኛ 10 ሺህ ብር፣ መጠኑ አነስተኛ የሆነ ፍየል በ8 ሺህ ብር እየተሸጠ ይገኛል። ካለፉት ወራት ጋር ሲነጻጸር የ2 ሺህ ብር ጭማሪ አሳይቷል። 

መጠኑ ትልቅ የሆነ በግ በጎንደር ከተማ 10 ሺህ ብር እየተሸጠ ሲሆን፤ መካከለኛ መጠን በግ በ8 ሺህ 500 ብር እንዲሁም ዝቅተኛው 5 ሺህ 700 ብር በመሸጥ ላይ ነው። የበግ ዋጋ በጎንደር ከተማ ከነበረው ያለፉት ወራት ዋጋ ጋር ሲነፃፀር በ2 ሺህ 500 ብር ጭማሪ አሳይቷል። 

በበሬ ገበያው ትልቅ በሬ ከ75,000 ብር በላይ፤ መካከለኛ 60 ሺህ ብር እና መጠኑ አነስተኛ የሆነ በሬ በ39 ሺህ ብር እየተሸጠ መሆኑን አዲስ ዘይቤ በጎንደር መታዘብ ችሏል።

በደሴ ከተማ ደግሞ የአዲስ ዘይቤ የበዓል ገበያ ቅኝት እንደተመለከተው የዘይት ዋጋ ባለአምስት ሊትር ከ900 እስከ 950 ብር እየተሸጠ መሆኑን ታዝቧል። 

የበግ ዋጋ በደሴ ከተማ ገበያ ላይ ከ5 ሺህ ብር እስከ 6 ሺህ ብር በየመጠናቸው እየተሸጡ መሆኑን አዲስ ዘይቤ በደሴ የገበያ ቅኝት ባደረገበት ወቅት መመልከት ተችሏል። የበሬ ዋጋ ከ40 ሺህ ብር እስከ 50 ሺህ ብር በመሸጥ ላይ ሲሆን የፍየል ዋጋ በደሴ ከተማ እንደየመጠናቸው ከ7 ሺህ እስከ ከ9 ሺህ ብር እየተሸጡ ይገኛሉ። 

ዶሮ በደሴ ከተማ ከ1 ሺህ እስከ 1200 ብር በመሸጥ ላይ አንደሆነ መመልከት ተችሏል። ለበዓል በስፋት ከሚሸመቱት አስቤዛዎች መካከል እንቁላል በደሴ ከተማ በ10 ብር እየተሸጠ ሲሆን ሽንኩርት በኪሎ ከ25 እስከ 30 ብር እየተሸጠ ይገኛል።

በአጠቃላይ ከተደረገው ቅኝት መመልከት እንደተቻለው የዘንድሮው የፋሲካ ገበያ ከፍተኛ የዋጋ ንረት የታየበት ሲሆን በትዝብታችን ያገኘናቸው ተጠቃሚዎችም ይህንን ይመሰክራሉ። 

አዲስ ዘይቤ ለሁሉም የክርስትና ዕምነት ተከታዮች መልካም የትንሳኤ በአል ይመኛል።

አስተያየት