ሚያዝያ 18 ፣ 2014

በባህር ዳር ከተማ ከ 4200 በላይ ደንበኞች ካርድ ሳይሞሉ ለወራት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እየተጠቀሙ እንደሆነ ተነገረ

City: Bahir Darዜናማህበራዊ ጉዳዮች

ካርድ ሳይሞሉ ለወራት የተጠቀሙ የባህር ዳር ከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ቅድመ -ክፍያ ደንበኞች ለውዝፍ ዕዳ፣ ተቋሙም ለኪሳራ መዳረጋቸው ታውቋል

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

በባህር ዳር ከተማ ከ 4200 በላይ ደንበኞች ካርድ ሳይሞሉ ለወራት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እየተጠቀሙ እንደሆነ ተነገረ
Camera Icon

Credit: ESI Africa

ከ4,206 በላይ የባህር ዳር ከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ቅድመ-ክፍያ ደንበኞች ካርድ ሳይሞሉ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እያገኙ መሆኑ ተነገረ። በዚህም ምክንያት በርካታ ደንበኞች ለውዝፍ ዕዳ እንዲሁም የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስሪያ ቤቱም ለኪሳራ መጋለጣቸው ታውቋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ አዲስ ዘይቤ ባደረገችው ማጣራት በርካታ የቅድመ-ክፍያ ተጠቃሚዎች ክፍያ ሳይፈጽሙ (ካርድ ሳይሞሉ) እንደሚጠቀሙ መረጃ ያገኘች ሲሆን ችግሩም በተለያዩ ምክንያቶች በበርካታ ደንበኞች ላይ እንደሚከሰት አገልግሎቱ አረጋግጧል።

የአማራ ክልል የኤሌክትሪክ አግልግሎት የደንበኞች አገልግሎት ሽያጭ ኃላፊ አቶ መንግስቱ ካሴ እንደሚናገሩት የቅድመ ክፍያ አገልግሎት ሂሳብ ሳይከፍሉ ለረጅም ጊዜ መጠቀም በሁለት መንገድ ሊከሰት ይችላል።

ኃላፊው እንደሚናገሩት፣ “በሲስተም ችግር ምክንያት መስመሩ በቂ ኃይል ሳይኖረው ሲቀርና የቆጣሪው የመቆጣጠሪያ በር አካል(valve) ተከፍቶ ሳይዘጋ ይቀራል በዚህ ጊዜ ካርድ ቢጨርስም አገልግሎቱ አይቋረጥም፤ በሌላ በኩል በህገ-ወጥ መንገድ ቆጣሪው እንዳይቆጥር ይደረጋል” ያሉ ሲሆን በዚህም ተቋሙ ለኪሳራ እየተዳረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በተጨማሪም በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው አቶ ሄኖክ ዘላለም የተባሉ ባለሙያ አንዳንድ የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎች ለቀጥታ የፀሃይ ብርሃን (direct sun light) እና አቧራ(dust) ከተጋለጡ ሂሳብ መቁጠራቸውን ሊያቆሙ እንደሚችሉና ወደ ደንበኛው የሚሄደው የኤሌክትሪክ ሃይል ፍሰት ግን እንደማይቋረጥ ይናገራሉ። 

ችግሩን ለመቅረፍ በሲስተም ላይ መረጃዎችን በመሰብሰብ በየስድስት ወሩ ምንም ሂሳብ የማይከፍሉ ደንበኞችን መረጃ  ወደ ዲስትሪክቶች በመላክ ችግሩን ለመቅረፍ እየሰሩ እንደሆነ የደንበኞች አገልግሎት ሽያጭ ኃላፊው ለአዲስ ዘይቤ አስረድተዋል።

በክልሉ ባለፉት ሶስት ወራት 12,370 ደንበኞች ሂሳብ ሳይከፍሉ መገኘታቸውን ከሲስተሙ ማረጋጋጥ እንደተቻለ ቢሮው ሲገልፅ ከዚህም ውስጥ 4,206 የባህር ዳር ደንበኞች እንደሆኑ መረዳት ተችሏል።

ደንበኞች አገልግሎት ኃላፊው እንደሚያሳስቡት ካርድ ሳይሞሉ እየተጠቀሙ የሚገኙ ደንበኞች ለአላስፈላጊ ውዝፍ ዕዳ ሳይጋለጡ በአቅራቢያቸው ለሚገኝ ዲስትሪክት ሄደው ጉዳዩን በማመልከት ችግሩ በቶሎ እንዲፈታ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በሌላ በኩል የክፍያ መሰብሰቢያ ማዕከላት ጥቂት በመሆናቸው ካርድ ለመሙላት እየተንገላቱ እንደሆነ የባህር ዳር ከተማ የአገልግሎቱ የቅድመ-ክፍያ ደንበኞች ቅሬታ ያቀርባሉ።

በባህርዳር ከተማ 22,040 የቅድመ-ክፍያ አገልግሎት ደንበኞች ያሉ ሲሆን የካርድ መሙያ ጣቢያዎች ውስን በመሆናቸው ለእንግልት ተዳርገናል ይላሉ ለአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ቅሬታቸውን ያጋሩ ደንበኞች። ከዚህ ጋር በተያያዘ በካርድ መሙያ ጣቢያዎች ያሉ ረጃጅም ሰልፎችን የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ መታዘብ ችሏል።

“ደንበኞች የሚጉላሉት የመሸጫ ጣቢያዎች እጥረት ሳይሆን ደንበኞች በአብዛኛው ወደ አንዱ የመሸጫ ቦታ ስለሚሰበሰቡ ነው። በተጨማሪም በአብዛኛው ደንበኞች  ቅዳሜ ቀን ብቻ መምጣት ስለሚመርጡ የተፈጠረ ችግር ነው” ይላሉ አቶ መንግስቱ ካሴ ምላሽ ሲሰጡ።

እንደ ደንበኞች አገልግሎት ኃላፊው ማብራርያ ደንበኞች የቅድመ ክፍያ ሽያጭ አገልግሎት ስታንዳርድ መሰረት አንድ የሽያጭ ሰራተኛ ለ5 ሺህ ደንበኞች አግልግሎት እንዲሰጥ ታሳቢ ተደርጓል ቢሉም፤ በከተማዋ በአሁን ወቅት የቅድመ-ክፍያ አገልግሎት 22,040 ተጠቃሚ ያለ ሲሆን በ3 የሽያጭ ሰራተኞች አገልግሎቱ እየተሰጠ እንደሚገኝ ማረጋጋጥ ተችሏል። 

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በፌደራል ደረጃ ብቻ ይሠጥ የነበረውን አገልግሎት ከ2011 ዓ/ም ጀምሮ በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች መስጠት መጀመሩ ይታወሳል። የአማራ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት ከ705,556 በላይ ደንበኞች በማስተናገድ ላይ ይገኛል። በክልሉ መዲና ባህር ዳር ደግሞ 53,690 ደንበኞች ያሉ ሲሆን ከነዚህ ወስጥ 22,040 ያህሉ የቅድመ-ክፍያ ተጠቃሚዎች ሲሆኑ 31,650 ደግሞ የድህረ-ክፍያ ተጠቃሚዎች ናቸው።