ከእለት እለት እያየለ መሄዱን የተያያዘው የኑሮ ውድነት፣ አቅርቦት እንዲመናመን፣ የገንዘብ የመግዛት አቅም እንዲዳከም፣ ገደብ የጣሰ የግብይት ስርዓት እንዲኖር፣ እንዲሁም የአገልግሎት ጥራት እንዲጓደል በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ችግሩ የማህበረሰቡን የኑሮ አጥር መነቅነቅ ከጀመረ ቆይቷል።
በተለይም በአሁን ሰዓት በቀናት ልዩነት በምርቶች ላይ የሚታየው ከፍተኛ የዋጋ ልዩነት በማህበረሰቡ ዘንድ ከስጋትነትና የእለት ተእለት መወያያ ርእስ ከመሆን አልፎ ተስፋ ወደማስቆረጥ የተሸጋገረ ይመስላል። መንግስትም በበኩሉ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መኖሩን በማመን መንስኤው አለም እያስተናገደችው ያለችው የኃያላን ሀገራት ጦርነት እና በሀገሪቱ ውስጥ ሲካሄድ የቆየው የ ‘ህግ የማስከበር ዘመቻ’ መሆኑን ገልጾ መፍትሄው የሀገሪቱን ልማት ማስቀጠል ብቻ መሆኑን ሲናገር ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት መረጃ እንደሚያሳየው የ 2014 ዓ.ም የታህሳስ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 35.1 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ከዚህም ውስጥ የምግብ ፍጆታዎች ግሽበት 41.6 በመቶ ጭማሪ ሲያሳይ የምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶች የዋጋ ግሽበት ደግሞ የ26.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
በተመሳሳይ፣ የጥር ወር የዋጋ ግሽበት እድገት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ34.5 በመቶ ሲጨምር፣ የየካቲት ወር ንፅፅር ደግሞ የ33.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ቁጥሮች የኑሮ ውድነቱን አሳሳቢነት ከመናገራቸው ባለፈ ለኑሮ ውድነቱ ጥያቄ ማህበረሰቡ የሚቀርብለት መልስ የተዛባ መሆኑ እና የሚጨበጥ የመፍትሄ ሃሳብ የሚጠቁም የመንግስት አካል አለመኖሩ ተደማምሮ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እያስገባው መሆኑን ለመታዘብ የማህበራዊ ሚዲያዎችን ዞር ዞር ብሎ መመልከት በቂ ነው።
ከከተማ እሰከ ገጠር የኑሮ ውድነቱ ያላንኳኳበት ስፍራ የለም። በተለየ ሁኔታ ደግሞ የዘይት አቅርቦት እጥረት መከሰቱና ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡ በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍ ያለ ትኩረት አግኝቶ መነጋገሪያነቱ አይሏል። እንዲያውም የኑሮ ውድነቱ ዘይት ላይ ብቻ ያነጣጠረ እስኪመስል ድረስ ሁሉም ቦታ ዘይት ዘይት የሚሉ አቤቱታዎች እና ብሶት አዘል ቀልዶች ተበራክተው የሌሎች ምርቶች የዋጋ ንረት የዘይትን ያህል እንዳልሆነ እንዲመስል አድርጓል።
ይሁን እንጂ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የዋጋ ንረቱ የምግብ አቅርቦቶችን ጨምሮ የታሸጉ ውሃዎች፣ የነዳጅ አቅርቦት፣ የመኖርያ ቤት ኪራይ እና አልባሳትን ሳይቀር ያልዳሰሰው ቦታ የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ የመዝናኛ ቦታዎችን ስንመለከት 'ህዝቡ የኑሮ ውድነቱን እንዴት እየተቋቋመ ነው በዚህ ልክ የሚዝናናው?' የሚል ጥያቄ መፍጠሩ የማይቀር ነው። በከተማው ውስጥ ከሚገኙ እውቅ መዝናኛ ቦታዎች አንድ ሁለቱ ጋር ጎራ ብለን ያነጋገርናቸው ሰዎች ከዚህ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ሃሳብ አካፍለውናል።
ሰይፉ ዘበርጋ በሰላሳዎቹ አጋማሽ የሚገኝ ወጣት ነው “ገንዘብ እኮ አሁን አቅሙ ወርዶ ወርዶ ወድቋል፣ ዛሬ ያለኝ አንድ ሺህ ብር ነገ የመቶ ብር ዋጋ እንኳን አይኖረውም፤ ስለዚህ 'በቃ ነገ ለራሱ ያውቃል፣ ዛሬን መኖር ይሻላል' ወደ ማለት ደርሻለሁ” ሲል ምሬቱን ያስረዳል። ስራ ተሰርቶ የሚመጣው ገንዘብ ከቤት ኪራይ፣ ከትራንስፖርት እና ከጥቂት አስቤዛ ተርፎ እና ተቆጥቦ ጥሪት ለመግዛት የማይታሰብ መሆኑን በመግለፅ፣ “ይህን የአዕምሮ ውጥረት ረገብ የሚያደርገው ደግሞ ከወዳጆች ጋር ሻይ ቡና ማለት ነው” ይላል ሰይፉ።
በዚሁ ጉዳይ ያነጋገርናት ሴት ደግሞ በሀያዎቹ አጋማሽ የምትገኝ ወጣት ስትሆን፣ “ትዳር መስርቼ ኑሮ ከጀመርኩ ሁለት አመቴ ነው፣ የልጅ እናት ነኝ ኑሮው ከባድ ከመሆኑ የተነሳ እንኳን ለመዝናናት የሚወጣ ገንዘብ፣ ከወር ወር ቤትን ቀጥ አድርጎ ማቆየትም ከብዷል። እንደዚህ አይነት መዝናኛ ቦታ ደግሞ በእለት ተእለት ህይወትሽ የሚያስመጣ አጋጣሚ ሊኖር ይችላል” በማለት ማህበረሰቡ በመዝናኛ ቦታዎች መታየቱ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ችሎ ነው ማለት እንዳልሆነ ትናገራለች።
ከእነዚህ እና ከሌሎች አስተያየት ሰጪዎቻችን እንደተረዳነው የገበያው አለመረጋጋትና የኑሮ ውድነት አስጊ ሆኗል። የእህል ዘሮች፣ ዘይት፣ የታሸጉ ምግቦች፣ የአዋቂ እና የህጻናት አልባሳት፣ ንጽህና መጠበቂያዎች እና የመሳሰሉ መሠረታዊ ሸቀጦች በየጊዜው ሲጨምሩ እንጂ ሲቀንሱ አይታይም። ይህ ደግሞ በማህበረሰቡ ላይ የሚያሳድረው ጫና የስነ-ልቦና ጭንቀትንም እንደሚጨምር የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።
የኑሮ ውድነቱ ከስነ-ልቦና አኳያ ግለሰቦች ላይ የሚያሳድረው ጫና ምን ይመስላል ስንል የጠየቅናቸው የስነ-ልቦና ባለሙያዎች ማህበር ፕሮጀክት አስተባባሪ ወ/ሮ ካኪ በቀለ እንዳስረዱን ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዘው የሚመጡ እንደ ጭንቀት እና ፍርሃት ያሉ የስነ-ልቦና ውጣ ውረዶች እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላሉ። “የሰው ልጅ ያለስጋት የመኖር ዋስትናውን ከሚያረጋግጡለት መሳርያዎች መካከል አንዱ ገንዘብ ነው። ታዲያ አንድ ሰው ገቢው እያነሰ ፍላጎቱ ደግሞ ከፍ እያለ ሲሄድ የሚከተሉትን ጭንቀቶች ለመርሳት እንደ መሳርያ ከሚጠቀማቸው ተግባራት መካከል ያለውን ትንሽ ገንዘብ ለጊዜያዊ ደስታ ማባከን ነው” ሲሉ የኑሮ ውድነቱን ተከትሎ በስፋት እየታየ ያለውን የመዝናናት ፍላጎት መንስዔ ያስረዳሉ።
እንደ ባለሙያዋ ገለፃ ገንዘብ ከማግኘት ፍላጎት ይልቅ ወጪን የማስወገድ ፍላጎት ማዳበር (Loss Aversion)፣ ፍርሃት የሚወልደው የመግዛት ፍላጎት (Affect Heuristic)፣ የገንዘብ እጥረት ፍራቻ (Scarcity Heuristic)፣ ገንዘብ የማባከን ውጤት (Cashless Effect)፣ እንዲሁም የውሳኔ መዋዠቅ (Decision Fatigue) በመባል የሚታወቁ ዋና ዋና ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የስነ-ልቦና ጫናዎች አሉ።
በተመሳሳይ ሁኔታ በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው የኑሮ ውድነት በተቀጣሪዎች ላይ በተለይም ደግሞ ዝቅተኛ ደመወዝ በሚከፈላቸው ሠራተኞች ላይ እያሳደረ ያለው ጫና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን(ኢሠማኮ) ከወራት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ጠቅላይ ምክር ቤት 48ኛ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሣሁን ፎሎ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው የኑሮ ውድነት ሠራተኛው ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል። በተለይም ዝቅተኛ ደመወዝ የሚከፈላቸው ሠራተኞች ላይ የኑሮ ጫናው አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች ለሠራተኞች የሚከፍሉት ደመወዝ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ በተገለፀበት ጉባዔ ሠራተኞቹ በሚከፈላቸው ደመወዝ ሕይወታቸውን መምራት አዳጋች እንደሆነባቸውም ተጠቁሟል።
በዚሁ ጉዳይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ የጠየቅናቸው ፕሬዝዳንቱ “በአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ መሠረት ዝቅተኛውን የደመወዝ ወለል የሚወስን ደንብና የደመወዝ ቦርድ ተቋቁሞ እንደ አገር ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል መቀመጥ እንዳለበት የሚደነግግ አዋጅ ከሁለት ዓመት በፊት ቢወጣም እስካሁን ድረስ ደንቡ ወጥቶ ወደ ሥራ ባለመግባቱ በተለይም ዝቅተኛ ደመወዝ የሚከፈላቸው ሠራተኞች ላይ የኑሮ ውድነቱ እጅግ የከፋ ጫና እያሳደረ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው ኮቪድ 19፣ በአገራችን ያለው ጦርነትና በቅርቡ በሩስያና ዩክሬን መካከል እየተካሄድ ያለው ጦርነት ኑሮ ውድነቱን በማባባስ በኩል ትልቅ ሚና እንዳላቸው አቶ ካሳሁን ሲናገሩ፣ “የኑሮ ውድነቱ በሰራተኞች ላይ ያሳደረውን ጫና ለመቀነስ መንግሥት በተቻለ መጠን ለድርጅቶች የውጭ ምንዛሪ በመፍቀድና ሌሎችንም አስፈላጊ እገዛዎችን በማድረግ ሠራተኞች ከስራ ገበታቸው እንዳይቀነሱ ሊያደርግ ይገባል” ብለዋል።
አሁን ላይ አንዳንድ ሠራተኞች ያለ ምግብ ሥራ ላይ ስለሚውሉ ድንገት ራሳቸውን ስተው የመውደቅ አደጋ ሁሉ እየገጠማቸው እንደሆነ መረጃዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ በልቶ ማደር ካልተቻለና ነገሮች በዚህ መልኩ የሚቀጥሉ ከሆነ የኢንዱስትሪ ምርታማነታችን ፈተና ላይ እንደሚወድቅ እና የኑሮ ውድነቱን ከዚህ የከፋ ሊያደርገው እንደሚችልም ፕሬዝዳንቱ ይጠቁማሉ።
ታዲያ “በዚህ ልክ የማይገፋ ተራራ የሆነውን ይሄን የኑሮ ውድነት እንዴት ነው ማስቆም የሚቻለው?” የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ፋሲል ጣሰው፣ “የአቅርቦት ችግር፣ የምርት እጥረት፣ ግሽበት፣ የኑሮ ውድነትና መሰል ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መንስኤያቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲና እቅዶች ድክመት ውጤት ናቸው። በእርግጥ በየቦታው ያሉት ጦርነቶች ለግሽበቱ መንሰኤ መሆናቸው ሀቅ ነው። ነገር ግን ዘይትና ስንዴ ለዓመታት በድጎማ እያስመጡ መቀጠልን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዴት ሊሸከመው እንደሚችልና የውጭ ምንዛሪው ከሌላ አስፈላጊ አቅርቦት ላይ እየተቀነሰ እንደሆነ አምኖ የሚያስረዳና የመፍትሄ ፖሊሲ መዘርጋት የሚችል የመንግስት ሹመኛ ያስፈልጋል” ሲሉ ያስረዳሉ።
አያይዘውም መፍትሔ ሁሉ ከመንግስት ሊገኝ ይችላል ብሎ መቀመጥ ልክ አለመሆኑን በመጥቀስ ነገር ግን መንግስት በቅድሚያ የድርሻውን መወጣትና ከሕዝብ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁነቱን ማረጋገጥ እንዳለበት እንዲሁም ለግሽበቱ መፍትሄ ለማምጣት በልማት (economic development)፣ በእድገት (economic growth) እንዲሁም በግሽበት (unadjusted inflation) ዙርያ ጥልቅ ውይይት ማካሄድ እና የመፍትሄ ሃሳብ ማቅረብ እንዳለበት ይናገራሉ።
መጋቢት 27 ቀን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባቀረበው የስምንት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፣ የዋጋ ንረትንና የኑሮ ውድነቱን ያባብሳሉ ተብለው በተጠረጠሩ 104 ሺሕ የሚጠጉ ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ በየደረጃው በተዋቀረ የዋጋ ማረጋጋት፣ ሕገወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ ቁጥጥር ግብረ ኃይል በተደረገ ክትትል ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃ መወሰዱ መገለጹ ይታወሳል።
በተጨማሪም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ እንዳስረዱት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ የምርትና አገልግሎት መቀነስ፣ የብር የመግዛት አቅም መዳከም፣ የፀጥታ ችግር፣ የፍላትና አቅርቦት አለመጣጣም እና በርካታ ችግሮች በአገር አቀፍ ደረጃ ለታየው የኑሮ ውድነት ምክንያት ሆነዋል።
የምክር ቤት አባላቱም መንግሥት በአገር ውስጥ ለሚታየው የኑሮ ውድነት ችግር ሰበብ አስባብ በመፈለግ ወደ ውጭ የመግፋት አባዜ እንደሚታይበት ገልጸው፣ በመንግሥት ባለሥልጣናትና በሕዝቡ መሀል የሚታይ ከፍተኛ የሆነ የኑሮ ልዩነት እንደሚታይና በተለይም ባለሥልጣናት የሚነዷቸው ቅንጡ መኪኖችንና የሚኖሩባቸው ቤቶችን በመጥቀስ፣ ባለሥልጣናቱ የደሃውን ኑሮና ሕመም ሊገነዘቡት አለመቻላቸውን አስረድተው ነበር።
ለቀረቡት ቅሬታዎች ምላሾችን የሰጡት ሚኒስትሩ፣ የመሠረታዊ ሸቀጦች የዋጋ መናር በዋነኝነት በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የዩክሬን የዘይትና ስንዴ አምራቾች ምርት በማቆማቸው፣ ሌሎች አገሮችም በጦርነቱ ምክንያት የምርት እጥረት ይኖራል በሚል ወደ ውጭ ገበያ እየላኩ ባለመሆናቸው፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ጋር የሚመጥን የአቅርቦት ውስንነት መኖር፣ በኬላ መብዛት ምክንያት በሚፈጠር ቀረጥ መናር ሳቢያ ዋጋ በመጨመሩ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝና መሰል ችግሮች ለኑሮ ውድነቱ ምክንያት እንደሆኑ አንስተዋል። በቀጣይም ገበያውን ለማረጋጋት በመንግሥት የሚቀርቡ መሠረታዊ ሸቀጦች ሳይቆራረጡ እንዲገቡ እንደሚደረግ፣ የሸቀጦችን ነፃ እንቅስቃሴ የሚገቱና ለዋጋ ንረቱ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉ በየቦታው የተቋቋሙ አላስፈላጊ ኬላዎችን ለማስቀረት ከክልሎች ጋር በመግባባት ይሠራል ብለዋል።
ለዚህ ግሽበት እንደመንስኤ ከሚጠቀሱት ጉዳዮች መካከል አንዱ ስለሆነው የሩስያ እና የዩክሬን ጦርነት ትንታኔ የሰጠው የቢዝነስ ዴይሊ ዘገባ ጦርነቱ የአለምን የምግብ ቀውስ እንደሚያባብሰው በመጥቀስ በዚህም ሳቢያ በውስጥ ውዝግብና በኢኮኖሚያዊ ውዥንብር በሚታገሉ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ሕዝባዊ አመጽ እንዲቀጣጠል ሊያደርግ እንደሚችል ፅፏል።
ሩሲያ እና ዩክሬን ስንዴ፣ በቆሎ እና ገብስ ከሚያቀርቡ ከዓለም አምስት ቀዳሚ ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ሲሆኑ፣ በአለም አቀፍ ገበያዎች የሚሸጠውን የሱፍ ዘይት በመሸጥ ¾ ኛ ድርሻ ይይዛሉ። በዚህም ምክንያት የአለም የምግብ ግብዓቶች የዋጋ ግሽበት በ13% አሻቅቦ ከፍተኛውን ሪከርድ ይዟል። ይህን ተከትሎም ጦርነቱ ቢቆም እንኳን የዋጋ ንረቱ ወደነበረበት ለመመለስ በትንሹ ስድስት ወራትን ሊፈጅ እንደሚችል በፅሁፉ ተጠቅሷል።
በዚሁ ዘገባ እንደተገለፀው የኑሮ ውድነቱ መረጋጋት ካልቻለ ከዩክሬኑ እና ራሺያው ጦርነት ባለፈ በውስጥ ግጭት እየታመሰች የምትገኘው ኢትዮጵያ ከመልክዓ ምድሯ አቀማመጥ እና ከታሪካዊ ሁነቶች መረዳት እንደሚቻለው በድርቅ ሊጠቁ ከሚችሉ ሀገራት መካከል አንዷ ልትሆን ትችላለች ተብሏል።
መንግስት የመፍትሄ ሰራዎች ይሰራሉ ማለቱ ብቻ ለማህበረሰቡ መረጋጋት ሊሆን እንደማይችል እና የታቀደው መፍትሄ ተግባራዊ መሆን እንደሚገባው የኢኮኖሚ ምሁራን አፅዕኖት ይሰጣሉ። የኢኮኖሚያዊ ቀውሱ አገዛዘፍ ማህበረሰቡ ከመንግስት የሚቸረውን ማባበያ ያለማንገራገር ተቀብሎ እንዳይኖር እየታገለው የሚገኝ ሲሆን ኢኮኖሚያዊ ትንቅንቁ ማብቂያው መቼ ይሆን የሚለውን መጠበቅ አማራጭ አድርጎታል።
በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ሀሳባቸውን ያካፈሉን ሌላው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ተባባሪ ፕሮፌሰር ደመላሽ ስለሺ፣ “መንግስት የሚጠበቅበት ነገር እንዳለ ሁሉ፣ ነጋዴዎች ደግሞ ሁሉንም ጥፋት መንግሥት ላይ በመጫን እራሳቸውን ከደሙ ንፁህ አድርገው ሊያዩ አይገባም” ይላሉ።
አንዳንድ የከተማ ውስጥ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ የሸቀጥ እቃ አሰራጮች፣ እና ቸርቻሪዎች የኑሮ ውድነቱን ሰበብ በማድረግ በየዘርፉ የሚደረጉ የዋጋ ጭማሪዎች ምክንያታዊ አለመሆን ብቻ ሳይሆን ፈፅሞ የማይገናኙ የብዙ እጥፍ ልዩነት የሚታይባቸው ግልፅ ብዝበዛ ናቸው የሚሉት ባለሙያው፣ “በአንዳንድ ዘርፎች የተደረገውን የተጋነነ ጭማሪ ስንመለከት በነጋዴው ዘንድ ኢሰብዓዊነት እንዴት እንደነገሰና ማንአለብኝነት እንደተንሰራፋ በቀላሉ መረዳት ይቻላል” በማለት ወቀሳቸውን ይሰነዝራሉ።
በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 51 እና 55 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ 2006 ዓ.ም የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃን በአንድ የሚመራ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀቱ የሚታወቅ ሲሆን የዚህ ሕግ አላማ ተደርገው በአዋጅ ቁጥር 813/2006 መግቢያ ላይ ከተቀመጡ ነገሮች አንዱና ዋነኛው ለሸማቹ ማህበረሰብ ጤናማ የሆነ የግብይት ሥርዓት መዘርጋትና ካወጣው ገንዘብ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የንግድ እቃ ወይም አገልገሎት እንዲያገኝ ማስቻል ነው።
ሆኖም ግን ከዚህ አዋጅ እሳቤ እና ጠቅላላ አላማዎች በተለየ መልኩ በተለያዩ ጊዜያት ለሸማቹ ማህበረሰብ ጆሮ የሚሰጥ እና በአዋጁ የተደነገጉ መብቶቹን አክብሮ የሚያስከብርለት ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት ባለመኖሩ ምክንያት በተለያዩ ወቅቶች ቅርፅ እና ምክንያታቸውን እየለዋወጡ የሚከሰቱ የኑሮ ውድነት ሰቆቃዎች ገፈት ቀማሽ ሆኖ ቆይቷል። አሁንም እጅግ በከፋ መልኩ ሁኔታው በተመሳሳይ የቁልቁለት መንገድ ላይ እንደሚገኝ ባለድርሻ አካላትና ምሁራን ያስረዳሉ።