ሚያዝያ 20 ፣ 2014

ዝነኛው የዶክተር መርሳሞ የዓሳ ሾርባ

City: Hawassaማህበራዊ ጉዳዮች

ለተለያዩ የጤና እክሎች “ፈዉስን” በሚሰጠው ሾርባቸው የተነሳ “ዶክተር” የሚል ቅፅል ስያሜ ከደንበኞቻቸው ያገኙት መርሳሞ መንግስቱ ለ22 ዓመታት በዚህ ስራ ላይ ቆይተዋል

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ዝነኛው የዶክተር መርሳሞ የዓሳ ሾርባ
Camera Icon

ፎቶ፡ እያሱ ዘካሪያስ

የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አለሙ ብርሃኑ  ማለዳ ማለዳ አሞራ ገደል በሚባለው አካባቢ የሚሸጠውን የዓሳ ሾርባ ለመጠጣት ወደ ቦታው ማቅናት ከጀመሩ አስር ዓመት እንደሆናቸዉ ይናገራሉ። “ላለፉት 10 ዓመታት ወደ እዚህ ስፍራ የምመጣዉ የመጎብኘት ሱስ ኖሮብኝ ሳይሆን የዶ/ር መርሳሞ የሾርባ ምርኮኛ ሆኜ ነዉ ፤ በተለይ በሚጠቀሟቸዉ ቅመማ ቅመሞች የተነሳ ሾርባው ለእኔ ከሌሎች ሊለይብኝ ችሏል” በማለት ይገልፃሉ።

በአሞራ ገደል መዝናኛ ቦታዎች የዓሳ ሾርባን ከሚሸጡ ከሰላሳ በላይ ሰዎች መካከል “ዶክተር” መርሳሞ መንግስቱ  ይገኙበታል። በ1992 ዓ.ም. ወደዚህ ስራ የገቡት ዶክተር መርሳሞ አንድ የዓሳ ሾርባ ሃያ ሳንቲም በመሸጥ ነበር ስራቸውን የጀመሩት። አንድ የአሳ ሾርባ አሁን  ወደ 15 ብር ከፍ ማለቱን የሚናገሩት  ዶክተር መርሳሞ ወደ ዚህ ስራ የገቡት በፊት በነበራቸው የንግድ ሰራ ኪሳራ ስላጋጠማቸው እንደነበር  ያስታዉሳሉ።

በሐዋሳ ከተማ በተለምዶ አሞራ ገደል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በስፋት የዓሳ ምርቶች በመገኘታቸዉ ስፍራዉ የገበያ ማዕከል ሆኖም ያገለግላል። ሐዋሳ ሃይቅ ዳር በሚገኘው በዚህ ቦታ በርካታ ሰዎች በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሲሆን ከሀይቁ የሚገኙ የዓሳ ምርቶችን አንዴ በጥሬ አድርገዉ ሲያሻቸዉ በመጥበስ ከዛ አለፍ ሲል ደግሞ አሳዉን በመቀቀልና ሾርባ በመስራት ለተጠቃሚዎች ይሸጣሉ።  ይህን የለመደዉ ደንበኛ ገና በጠዋቱ ነዉ ወደ ስፍራዉ የሚያቀናዉ። 

ዘወትር በአሞራ ገደል የሚታየው የሻጩ እና የተጠቃሚዉ ትርምስ የዓሳ ገበያ ሳይሆን የበዓል  ግርግር ይመስላል። በዚህ ስፍራ የአካባቢዉ ነዋሪዎችም ሆኑ ሐዋሳን ለማየት የሚመጡ ጎብኚዎች ጭምር የዓሳ ቁርጥ (ፊሌቶ) እና ደረቅ የዓሳ ጥብስ እንዲሁም የዓሳ ሾርባ ለመጠቀም በአካባቢው ይታደማሉ። የዶ/ር መርሳሞ አይነቱ የዓሳ ሾርባ መሸጫ ቦታ መኖሩ ደግሞ አሳ ወዳጆች ወደስፍራው በተደጋጋሚ  እንዲያቀኑ ያደርጋቸዋል።

ከልጅ እስከ አዋቂ በዶ/ር መርሳሞ የሚሰራዉን የዓሳ ሾርባ ለመጠቀም፣ በጠዋቱ ወደ አሞራ ገደል በማቅናት ቦታ ቦታቸዉን ይይዛሉ። የዓሳ ሾርባዉ እስኪደርስ  የመጠጫ ኩባያቸዉን ተሽቀዳድመዉ በመያዝ የሚቀመጡት ተስተናጋጆች “ከሌሎቾ የዓሳ ሾርባ መሸጫዎች የዶ/ር መርሳሞ በምን ተለየ” በማለት ላቀረብንላቸው ጥያቄ ተከታዩን ብለዉናል። 

“ወደዚህ ስፍራ መምጣት ከጀመርኩ ከ ሃያ ዓመት በላይ ሆኖኛል ልክ ዶክተሩ ሾርባ መሸጥ ሲጀምሩ ማለት እችላለሁ” ሲል የሚያስታዉሰዉ አስራት ደርሳ ከሌሎች የዓሳ ሾርባ ሻጮች የዶክተሩ የሚለይበትን ሲያብራራ፣ “የሚጨምሯቸዉ ቅመማ ቅመሞች ሾርባውን ጣፋጭ አድርገውታል” ይላል። ሌሎች የዓሳ ሾርባ ሻጮች ውሃ በማብዛት ቀጭን ስለሚያደርጉት ብዙም ጣዕም እንደሌለው በንጽጽር ያስረዳል አስራት። 

ዶክተር መርሳሞ የሚሰሩት የዓሳ ሾርባ በልዩነት የመወደዱ ምስጢር  ከተለያዩ የበሽታ አይነቶች ፈዋሽ መሆኑ ነው ይላሉ ተጠቃሚዎች። ለአብነት ያክል ለብርድ፣ ለጉንፋን፣ ለሳል፣ ለጉልበት መሸማቀቅ እንዲሁም ሌሎችም የጤና እክሎች  “ፈዉስን” መስጠቱ ሾርባውን ዝነኛ አድርጎታል ይባላል። በዚህ የተነሳ የሾርባው አብሳይ መርሳሞ መንግስቱ “ዶክተር” የሚል ቅፅል ስያሜ ከደንበኞቻቸው ሊያገኙ ችለዋል።   

በልምድ የተሰጣቸዉን “ዶክተር” የሚል ስያሜ እንደ መደበኛ ማዕረግ በመቀበል ስራቸዉን ለ 22 ዓመታት በሚገባ እያሳለጡ የሚገኙት መርሳሞ መንግሥቱ ከሌሎች የዓሳ ሾርባ ሻጮች በተለየ ስኬታማ መሆናቸውን ራሳቸውም ይመሰክራሉ። “የማበስለው በጥራት ነው፣ እኔ የምጠቀማቸዉ ቅመማ ቅመሞች ደግሞ ለተለያዩ የበሽታ ዓይነቶች እንደ መድሃኒት ናቸው” ሲሉ ሾርባቸው ተመራጭ ሊሆን የቻለው የእርሳቸው ብቻ በሆነው ምስጢራዊ አቀማመማቸው እንደሆነ ይናገራሉ ።

ለጉንፋን፣ ለብርድ እንዲሁም ለሳንባ በሽታዎች ፍቱን መድሃኒት ነው የተባለለትን ሾርባ ፍለጋ ሰዎች ወደ አሞራ ገደል ይጎርፋሉ። አቶ ሞጊቻ ሸለሞ በሀይለኛ ጉንፋን ታሞ በሾርባው ሊታከም የመጣ አንዱ ተጠቃሚ ነዉ። ሞጊቻ ሲናገር፣ “ለመጀመሪያ ግዜ ወደዚህ ስፍራ የመጣሁት ከሁለት ቀናት በፊት ነበር ፤ ጓደኛዬ ነዉ ለምን ወደ ህክምና ተቋም አልወስድህም ብሎ ያመጣኝ” በማለት እየቀለደ ሰዎች የሾርባውን ፈዋሽነት ምን ያህል እንደሚያምኑበት ያስረዳል።

ሞጊቻ መጀመሪያ ሲመጣ ከ30 በላይ ሰዎች መጠጫ ኩባያ ይዘው ሲጋፉ ተመልክቶ መገረሙን ገልጾ እሱም ሾርባውን ቀምሶ በጣዕሙም ሆነ በውፍረቱ የተለየ መሆኑን ይናገራል። “በሌሎች ቦታዎችም የአሳ ሾርባ የምጠጣ ቢሆንም ይህ ግን ተለይቶብኛል ፤ ከበሽታዬም ሙሉ ለሙሉ ድኛለሁ" ሲል ምስክርነቱን ይሰጣል።

ከሌሎች የአሳ ሾርባ ቤቶች በምን ተለየ ለምንስ የእናንተ ሾርባ ተመራጭ ሊሆን ቻለ ብለን ጥያቄ ያቀረብንላቸዉ ዶክተር መርሳሞ፣ “እኔ የምፈልገዉን ወይም ዉስጤ ሊቀበለዉ የሚችለዉን ነዉ ለደንበኞቼም የማቀርበዉ ፤ ተጠቃሚ አለኝ ብዬ ሾርባዉን አላቀጥነዉም” ያሉት ዶክተር መርሳሞ ለሾርባው ማጣፈጫነት የሚጠቀሟቸውን ቅመማቅመሞች ግን “ምስጢር” ነዉ በማለት ሊነግሩን ፍቃደኛ አልሆኑም። “የኮሮና ቫይረስ በሀገራች በተከሰተበት እና ጥንቃቄ በስፋት በነበረበት ወቅት ተመራጩ የእኔ ሾርባ ቤት ነበር፣ አሁንም ነዉ” በማለት ዘመናትን እና ፈተናዎችን ተቋቁሞ በዝነኝነቱ ስለቀጠለው ሾርባቸው ዶክተር መርሳሞ በኩራት ይናገራሉ። 

አስተያየት