ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በመንገድ ላይ የሚሰሩ ፈጣን ምግቦች እየተለመዱና የተጠቃሚያቸውም ቁጥር እየተበራከተ ይገኛል። የእነዚህ ምግቦች ለምን እየተዘወተሩ እንደመጡ እንዲሁም የምግቦቹ አይነትና አዘገጃጀት ምን ይመስላል የሚለው ቀርቦ ላላየ ወይም ላልተጠቀመ ሰው ጥያቄ መሆኑ አይቀርም። ይህን አዲስ የምግብ ልምድና ተዘውታሪነቱን በተመለከተ ፈጣን የመንገድ ዳር ምግቦች በዋነኝነት ሲዘወተርባቸው በሚታዩት በአዲስ አበባ፣ ሐዋሳና አዳማ ከተማ የሚገኙት የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢዎች ቅኝት አድርገዋል።
ከነዚህ ፈጣን ምግቦች በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች በአብዛኛው የተለመደው እርጥብ የተሰኘውና በመሰረታዊነት (ሌሎች የማባያና ቅመማ ቅመብ ግብአቶችን ሳይጨምር) በዳቦ የሚቀርብ የድንች ሳንዱች ሲሆን በአዳማ ከተማ ደግሞ በአንፃሩ ፔንቸራ የተባለ ፈጣን ምግብ እየተዘወተረ ይገኛል።
ተወዳጁ እርጥብ
ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች መግቢያ በር ፊት ለፊት በረድፍ እርጥብ የሚያዘጋጁ ቤቶች በራፋቸው ላይ አነስተኛ ወንበሮች ደርድረው ደንበኞቻቸውን ይጠብቃሉ። ምግቡን ለተጠቃሚው የሚያዘጋጁት ተደራጅተዉ እንዲሁም በግላቸዉ ነው።
ተማሪ አብነት ዘለቀ እና ጓደኛዉ ሚሊዮን ብርሃኔ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲሆኑ እርጥብ እየተባለ የሚጠራዉን የምግብ ዓይነት አዘውትረው ይጠቀማሉ። ጓደኛሞቹ “በ25 ብር ጠግበን ወደ ዶርማችን እንገባለን ይህም ዋጋዉ አነስተኛ በመሆኑ እና ለረጅም ጊዜ እንዳይርበን ስለሚያደርግ እንመርጠዋለን” በማለት ምግቡን ለምን ምርጫቸው እንዳደረጉት ይናገራሉ።
ከ 400 ሺህ በላይ ሰዎች መኖሪያ የሆነችው የሲዳማ እና የደቡብ ክልሎች የጋራ መናገሻዋ ሐዋሳ ከተማ በጎዳናዎቿ ላይ እንደ ድንች በዳጣ ያሉ የመንገድ ምግቦች ማግኘት የተለመደ ነበር። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን እርጥብ የተባለው ምግብ ሆኗል የሐዋሳን መንገዶች የተቆጣጠረው። እርጥብ ተመራጭ እና በከተማው በየእለቱ ብዙዎች የሚመገቡት ምግብ ሆኗል።
በአብዛኛዉ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መዉጫ በር ላይ፣ በዙሪያዉ ባሉና በሐዋሳ ከተማ የቀን ሰራተኞች እና ተማሪዎች በሚበዙበት ስፍራዎች ባሉ ምግብ ቤቶች እርጥብ የሚሸጡ ነጋዴዎች ይገኛሉ። የነጋዴዎቹ ቁጥር ባለፈው ዓመት ከነበረው በአምስት እጥፍ አድጎ ከ15 በላይ ደርሷል።
የሐዋሳዋ ቤዛዊት መስፍን እርጥብ በማዘጋጀትና በመሸጥ ኑሮዋን ትደጉማለች። እርጥብ ከምን እንደሚዘጋጅ ስታስረዳ “ድንች፣ ካሮት፣ ጥቁር ጎመን፣ ሽንኩርት፣ ቃሪያ ዋነኛ ይዘቶቹ ናቸው” ትላለች። አንድ እርጥብን ሰርቶ ለመጨረስ ከ5 እስከ 10 ደቂቃ ድረስ ሊፈጅ ይችላል። አዘገጃጀቱም ሁሉንም ግብዓቶች በአንድ ላይ በማዋሃድ ማብሰልና ቃሪያ ወይም ሚጥሚጣ እንዲሁም ጨው ጨምሮ ማውጣት ነው። እንደ ሳንዱች ዳቦ መሃል በማድረግና ኬቻፕ በመጨመር ለተጠቃሚ ይቀርባል፣ እንደቤዛዊት ገለጻ።
እርጥብ በተመሳሳይ ሁኔታ በተለያዩ የአዲስ አበባ ስፍራዎች በሰፊው እየተለመደ ይታያል። በተለይ ወደ አመሻሹ ላይ የድንች መጥበሻ ማሽኖች ጎልተው የሚታዩባቸው አነስተኛ መጠለያ ቀልሰው እርጥብ፣ እንቁላል ሳንዱች፣ ፈላፈል የሚያዘጋጁ ጥጎች በተለያየ የመዲናዋ የመንገድ ዳርቻዎች ማየት የተለመደ ነው። በነዚህ ቦታዎች ከሚዘጋጁት ምግቦች የተጠቃሚዎች ምርጫ ሆኖ የሚታየው እርጥብ ነው።
በአዲስ አበባ ቃሊቲ አካባቢ በእርጥብ ንግድ የሚታወቀው ብሩክ ወንድምገዛው ስራውን ከ ሁለት አመት በፊት የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በቋሚነት ከሚሰራበት የእርጥብ መሸጫ ቦታ በተጨማሪ እዚያው አካባቢ ሌላ ቅርንጫፍ መክፈት ችሏል።
“ስራውን በጀመርኩበት አጭር ጊዜ አትራፊ ሆኖ አግኝቼዋለው። ከዚያም በላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚያስገርም ሁኔታ እየጨመረ የመጣው የተጠቃሚው ፍላጎት ስራውን ማስፋፋት እንዳለብኝ አሳምኖኛል” ይላል ብሩክ።
የእርጥብ አዘገጃጀት፣ ቅመማና የማብሰያ ግብዓቶች ከቦታ ቦታ የሚለያይ ሲሆን ሁሉም የእርጥብ አይነቶች ግን በመሰረታዊነት ድንችና ዳቦ ይኖራቸዋል። በአብዛኞቹ አዘገጃጀቶች ከዳቦ እና ድንች በተጨማሪ በእንቁላል፣ በአቦካዶና ሌሎች ቅመማ ቅመሞችም ታጅቦ ይቀርባል። እንደ ቃሪያ፣ ሚጥሚጣ፣ ቁንዶ በርበሬ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ያሉ ቅመማ ቅመሞችም በማጣፈጫነት ይጨመሩበታል።
እንደ ብሩክ ማብራሪያ የተለያዩ የአዘገጃጀትና ቅመማ ዘዴዎችን የሞከረ ሲሆን አሁን ላይ በተረዳው መሰረት የድንቹ አጠባበስ መንገድ፣ ጥቅም ላይ የሚውሉት ቅመሞች እንዲሁም በሂደት ተመሳሳይ ጣዕም ለማቅረብ የሚደረግ ጥረት የ እርጥብ ጥፍጥና ምስጢሮች ናቸው።
የአዳማው ፔንቸራ
እንደ እርጥብ ሁሉ በአዳማ ከተማ ከሚዘወተሩና አያሌ ተጠቃሚዎችን እያፈራ የመጣው ለየት ባለ ስያሜ የሚጠራው ፔንቸራ ፈጣን ምግብ ነው።
የ5 መቶ ሺህ ኗሪዎች ከተማ የሆነችው አዳማ እንደበርካታ የኦሮምያ መስሪያ ቤቶች መቀመጫነቷ የኑሮ ውድነቱ ጫና በተለይም በአገልግሎት ዘርፉ ላይ በጉልህ ይታይባታል። ቀድሞ 12 ቀበሌ ማርያም ቤ/ክ ጀርባ አካባቢ ይታይ የነበረው የጎዳና ላይ ምግብ አቅርቦት ልማድ አሁን በሁሉም የከተማዋ ክፍል ተስፋፍቷል።
ማምሻውን በመንገድ ዳር እንደ የተቀቀለ ድንች፣ ንፍሮ፣ ስኳር ድንች የመሳሰሉ የተለያዩ የምግብ አይነቶችን ይዘው ደንበኛ የሚጠብቁ ነጋዴዎችን መመልከት የተለመደ ነበር። ፔንቸራ የተባለው የጎዳና ላይ ምግብም ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም ከቅርብ ግዜ ወዲህ ሰፊ ተወዳጅነት አትርፏል።
ከአስር ዓመት በፊት በአዳማ የመጀመሪያውን የፔንቸራ ንግድ ቤተሰቡ እንደጀመረ የነገረን አብዲ የተባለ ወጣት በአሁን ወቅት የ30፣ የ40 እና የ50 ብር ዋጋ ተምነው ምግቡን እንደሚያቀርቡ ይናገራል። “ስራው በተጀመረበት ወቅት መንገድ ላይ ምግብ መብላት እጅግ ይታፈርበት ነበር” ይላል አብዲ።
“ፔንቸራ በዋናነት የተቀቀለ ድንች ምግብ ነው” የሚለው አብዲ በተጨማሪም ሰላጣ፣ አቮካዶ፣ ቀይ ቦሎቄ፣ ጥቅል ጎመንና ካሮት በጥሬው ተከትፈው እንደሚጨመሩበት ይገልፃል። እንደ ማጣፈጫም ሚጥሚጣ፣ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች እና ዘይት በአናቱ እንደሚቀላቀሉበት ነግሮናል።
እንደ ሌሎቹ ከተሞች ሁሉ በአዳማ ከተማ እነዚህ ፈጣን ምግቦች ተማሪና ሰራተኛ በሚበዛባቸው ቦታዎች ከሌሎች ስፍራዎች በተለየ ሰፊ ተጠቃሚ አላቸው። አዳማ የሚገኘው አዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ዲያስፖራ በር ፊት ለፊት ያለው ቦታም ተመሳሳይ ትዕይንት ያስተናግዳል። ዩኒቨርሲቲው አካባቢ አመሻሽ ላይ ትንንሽ የፕላስቲክ ወንበሮች ተደርድረው ማየት አልያም ሰዎች ተሰብስበው ፔንቸራ ሲበሉ መመልከት የዘወትር ትዕይንት ነው።
“በየጊዜው የተጠቃሚው ቁጥር ሲጨምር ታዝቤያለሁ፤ ጥራቱም ብዛቱም በጣም ጥሩ ነው” የሚለው የአዳማ ዩኒቨርሰቲ ተማሪው ቢንያም፣ ፔንቸራ ወጪው ቀላልና ጣፋጭ ምግብ መሆኑን፣ እሱም አልፎ አልፎ ወደ ማታ ላይ ወደዚህ ስፍራ እንደሚሄድ አጫውቶናል።
እነዚህ የጎዳና ላይ ርካሽ ምግቦች ከቅርብ ግዜ ወዲህ ለምን ተመራጭ ሆኑ?
በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ዉድነት እርጥብ ና ፔንቸራ እንዲሁም ሌሎች ፈጣን ምግቦች ይበልጥ ተመራጭ እንዲሆኑ አድርጓል የሚለው የብዙዎች አስተያየት ነው። የምግቦቹ ዋጋም ተመጣጣኝ መሆኑ ተፈላጊነቱ እንዲጨመር ማድረጉን ተጠቃሚዎች እና በንግዱ ላይ የተሰማሩ ሰራተኞች ይስማሙበታል።
“ከዚህ ቀደም የጀበና ቡና ነበር የማፈላው። የእርጥብ ፈላጊው መጠን መጨመር እና አሰራሩ ቀላል መሆኑ ወደስራው እንድገባ ስቦኛል” ትላለች ስራውን ከጀመረች 8 ወር የሆናት የሐዋሳዋ ቤዛዊት መስፍን።
ተጠቃሚዎች እንደፍላጎታቸው በማንኪያ ብቻ አልያም በአንባሻ ፔንቸራን መብላት ይችላሉ የሚለው አብዲ ደግሞ ከቅርብ ግዜ ወዲህ የፔንቸራን ጤናማነት እና ተመጣጣኝ ዋጋ ሰዎች እየተረዱት እንደሆነ ይናገራል። “አሁን ምግብ ቤት ብትሄዱ ትንሹ የምግብ ዋጋ 50 ብር ነው። ከዋጋ አንጻርም ሆነ በጥራት የእኛ ፔንቸራ ተመራጭ ነው” ይላል አብዲ ስለ ምግቡ ተፈላጊነት ሲያስረዳ።
በአብዲ የስራ ቦታ ላይ ከጓደኞቿ ጋር ፔንቸራ ስትመገብ ያገኘናት ቤተማርያም ሻምበል፣ “ዋጋው ከሌሎች ምግቦች አንጻር ርካሽና ጣፋጭ የሚባል ነው” ትላለች። በቦታው ሌሎች ከ5 በላይ ፔንቸራ ነጋዴዎች ይገኛሉ። በአካባቢው እንደተመለከትነው ምግቡን ቅንጡ የቤት መኪና አቁመው ከሚያዙ እስከ ትንንሽ ልጆች ድረስ ይመገቡታል።
የሀገሪቱ የመጋቢት ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 34.7 በመቶ ሲደርስ የምግብ ዋጋ ግሽበት ብቻውን 43.7 በመቶ ነበር። ይህ እንደሚያመለክተው የዋጋ ግሽበቱ በምግብ ምርቶች ላይ የበረታ ተጽዕኖ እንዳለው ነው። በቅርቡ በዘይት እና ሌሎች የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ላይ የተከሰተው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በምግብ ዋጋ ላይም ከፍተኛ ጭማሪ አምጥቷል። ከዋጋ ንረቱ ጋር በተገናኘ ከዚህ ቀደም ብዙም ተመራጭ ያልነበሩ የጎዳና ላይ ምግቦች በብዙዎች ዘንድ እንደአማራጭ እየተወሰዱ ይገኛሉ።
አሁን ባለው የሃገሪቱ ሁኔታ ለአንድ ሰው በቂ የሆነ መደበኛ ምግብ በሬስቶራንቶች ለመመገብ በትንሹ ከ 100 እና 150 ብር ያላነሰ ገንዘብ ያስፈልጋል። ይህን የዋጋ ጫና ተቋቁሞ በአንድ ቀን ሶስት ጊዜ ይህን ወጪ ማውጣት የሚከብዳቸው በተለይ የአነስተኛ ደሞዝ ተከፋዮችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች እነዚህን ርካሽ ፈጣን የጎዳና ላይ ምግቦች ማዘውተራቸው አያስገርምም።
በአዲስ አበባ በ እርጥብ ንግድ ላይ የተሰማራው ብሩክ እንደሚለው አንድ ሰው ሆዱን ያዝ የሚያደርግለት ምግብ ለማግኘት ካለው ከፍተኛ ወጪ አንፃር በአነስተኛ ዋጋ አጥግቦ የሚመግበውን እርጥብ ተመራጭ ያደርጋል።
“ከዋጋው አነስተኛነት ባለፈ ከእርጥብ ግብዓቶች ዋነኞቹ ዳቦና ድንች ከፍተኛ የኃይል ሰጪና ካርቦሃይድሬት መጠን ያላቸው መሆኑ ደንበኞች በአነስተኛ ዋጋ የሚፈለውን ጥጋብና እርካታ ማግኘት እንዲችሉ አድርጓል” በማለት ብሩክ አስተያየቱን ይሰነዝራል።
በዚህ ኃሳብ የምትስማማው የአዳማዋ ትርሲት፣ “በብዛት ተጠቃሚዎቼ የጋራዥ ሰራተኞች፣ የታክሲ ሹፌሮች፣ ተማሪዎች ሲሆኑ የፔንቸራ ዋጋ ከሌሎች የተለመዱ የምግብ አይነቶች አንጻር ዝቅተኛና ጥሩ ጣዕም ያለውም በመሆኑ ምርጫቸው አድርገውታል” ትላለች።
የተቀቀለ ድንችና ቀይ ቦሎቄ እንዲሁም ሰላጣ የያዘ የአንድ ፔንቸራ ዋጋ 30 ብር ሲሆን ትርሲትን ከሌሎቹ የፔንቸራ ነጋዴዎች ልዩ የሚያደርጋት ከረፋድ 4 ሰዓት ጀምሮ አገልግሎት መስጠቷ ነው። “እኔ ፔንቸራ ለደንበኞቼ የማቀርበው በእንጀራ ነው። ሁሉም ነገር ጨምሯል። በ30 ብር የማቀርበው እጅግ ተጎድቼ ነው” የምትለው ትርሲት በቅርቡ በተከሰተው የምግብ ግብዓቶች ዋጋ ጭማሪ የተነሳ ይህ ስራ ራሱ እየከበዳት እንደሆነ ትናገራለች።
ከአዳማ ምስራቅ ሸዋ ፖሊስ ወደ ነጃሺ መስጊድ የሚወስደው መንገድ ላይ ለይላ አደም ፔንቸራ ትሸጣለች። ለይላ የምግብ ስራ ከጀመረች ብቻ ወደ 10 ዓመት እንደሆናት የምትናገር ሲሆን ድንች ቀቅሎ ከመሸጥ እያሻሻለች እዚህ እንደደረሰች ትናገራለች። “ከ20 ብር ጀምሮ ለደንበኞቻችን ምግቡን እናቀርባለን” የምትለው ለይላ ፔንቸራውን የምታቀርበው እንደደንበኛው ፍላጎት በዳቦ ወይም በእንጀራ ነው። ወቅታዊው የኑሮ ውድነት ለስራዋ ፈተና እንደሆነባት ያልሸሸገችው ለይላ ድንች በኩንታል 2 ሺህ 6 መቶ ብር እንዲሁም 5 ሊትር ዘይት1 ሺህ ብር እንደምትገዛና፣ ሆኖም ግን ደንበኞች እንዳይርቁ እንደህብረተሰቡ አቅም እያቀረበች እንደሆነ ትናገራለች።
ናትናኤል ምትኩ 'አዳማ ገበታ' በሚል ስያሜ የተለያዩ የማህበራዊ ሚድያ አካውንቶቹ በከተማዋ የሚገኙ የተለያዩ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ምግብ ቤቶችንና መሠል የምግብ አገልግሎቶችን እየዞረ ያስተዋውቃል። ናትናኤል በአዳማ መንገዶች ላይ የፈጣን ምግቦች ንግድ መስፋፋቱን ይናገራል።
“ከየትኛውም አገልግሎት ሰጪ ዘርፍ በተሻለ እነኚህ የመንገድ ላይ ምግብ አቅራቢዎች የኑሮ ውድነቱን ተቋቁመውታል” የሚለው ናትናኤል አንደኛው ምክንያቱ ከከፍተኛ ጥራት እና አቀራረብ ይልቅ ለብዛት ትኩረት የሚሰጡ መሆናቸውን ያነሳል። “ከጥሬ እቃ ወጪ በተጨማሪ በአብዛኛው የሰራተኛ ቅጥራቸው አነስተኛ ነው፣ አልያም ሰራተኛ አይቀጥሩም፤ ስለዚህ ይህ ነው የሚባል የተጋነነ ወጪ የለባቸውም። በዚህ የተነሳ የዋጋ ንረቱን ተቋቁመው ይቀጥላሉ” በማለት ናትናኤል አስተያየቱን ይሰጣል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ከፍተኛ የኑሮ ውድነትና የኑሮ ግሽበት አያሌ መገለጫ ያለው ሲሆን እንደ ምግብ ባሉ መሰረታዊ ሰብአዊ ፍላጎቶች ላይ የኑሮ ውድነቱ ያለው ጫና ሲበዛ ደግሞ የህልውና ጥያቄነቱን አሳሳቢ ያደርገዋል። በተለያዩ ከተሞች የሚታየውን ችግር በርካሽ የመንገድ ላይ ፈጣን ምግቦች ተጠቃሚው እየተወጣው ቢገኝም ከዕለት ዕለት እየናረ የመጣው የሸቀጦች ዋጋ እነዚህን ፈጣን ምግቦች በተመጣጣኝ ዋጋ ተጠቃሚው ማግኘት መቀጠል መቻሉን አጠራጣሪ አድርጎታል።