ግንቦት 27 ፣ 2014

ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ በኮሪያ የሚገኙ ስደተኛ አርቲስቶች ተቃውሞ አሰሙ

City: Addis Ababaባህል ወቅታዊ ጉዳዮች

ኢትዮጵያዊው አርቲስት በረከት የኮሪያ መንግስት ህግ የውጭ ሀገር ዜጋ አርቲስቶችን ያገለለ እንደሆነ በሰልፉ ላይ አስረድቷል

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ በኮሪያ የሚገኙ ስደተኛ አርቲስቶች ተቃውሞ አሰሙ
Camera Icon

Credit: The Korea TImes

የኮሪያ መንግስት ከያዝነው አመት መጀመርያ ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገው የሀገሪቱን አርቲስቶች መብት የሚያስከብር ህግ ማፅደቁ ይታወቃል። ነገር ግን ይህ ህግ የሀገሪቱ ዜጎች ያልሆኑ ነገር ግን ኮሪያ ውስጥ በመስራት ላይ የሚገኙ የውጭ ሀገር ዜጎችን አላገናዘበም በሚል ብዙ አርቲስቶች ስጋታቸውን ለማሰማት ትናንት ግንቦት 25 ቀን ሰላማዊ ሰልፍ አካሄደዋል።

በመሆኑም በኮሪያ የሚገኙ እና በስነጥበብ፣ ሙዚቃ፣ ሞዴሊንግ፣ ሚዲያ፣ ባህል ማስተዋወቅ እና መሰል ጥበባዊ ተግባራት የሚሳተፉ የውጭ ሀገራት ዜጎች ማህበር አባላት የኮፒራይት ጉዳይን ጨምሮ ተዛማች መብቶች እና ህጋዊ ድጋፍ ለማግኘት ለሀገሪቱ የባህል:ስፖርት እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

በሰልፉም ይሻሻላል ተብሎ በሚጠበቀው የህግ ቢል ማዕቀፍ ውስጥ የውጭ ሀገር ዜጋ አርቲስቶች እንዲካተቱ ጠይቀዋል። 

አዲስ ዘይቤ የማህበሩ አባል የሆነውን እና በተቃውሞ ሰልፉ ላይ የተሳተፈው ኢትዮጵያዊ የፎቶ አርቲስት፣ ደራሲ እና የማህበራዊ ተሟጋች በረከት አለማየሁ በጉዳዩ ላይ አነጋግራለች። እ.ኤ.አ በ2014 በስደት ወደ ኮሪያ የተጓዘው በረከት ሰልፉ ያስፈለገበትን ምክንያት ሲያብራራ “መንግስት የዜግነት ልዩነት ሳይገድበው ለሁሉም አርቲስቶች ደህንነቱ የተጠበቀ እና ፍትሃዊ የስራ ሁኔታ እንዲፈጥር ለመጠየቅ ነው” ብሏል። አክሎም የኮሪያ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ እና የድጋፍ ፕሮግራሞችን እድል የሚያገኙት የኮሪያ ዜግነት ያላቸው ስራዎች መሆናቸውን በመጥቀስ “ሀገሪቷ እስከኖርንባት እና እስከሰራንባት ሙያችንን ልታከብር እና በህግ ልታቅፈን ይገባል” ብሏል።

በማህበሩ ውስጥ የኮሪያ ዜጎችም በአባልነት እንደሚገኙ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ከነሱም መካከል “ስኪውድ ጌም” ን ጨምሮ በተለያዩ የኮሪያ ፊልሞች ላይ በመተወን የሚታወቀው ​​ተዋናይ ጆን ዲ ሚካኤል በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ “አዲሱ ህግ በኮሪያ የሚገኙ አርቲስቶችን ሁሉ ማእከል ያደረገ መሆን አለበት፣ እንደዛ ሲሆን ደህንነቱ የተጠበቀ የኪነጥበብ እድገት እንዲኖር ያግዛል” ማለቱ ተነግሯል። 

ሰልፉ የተከሄደው በሰሜን ምስራቅ ሴኡል ዳኢሀንጎ አካባቢ በሚገኘው የኮሪያ የአካል ጉዳተኞች ኪነጥበብ እና የባህል ማዕከል ፊት ለፊት በሚገኘው የህዝብ ቦታ ላይ ሲሆን፣ ኢትዮጵያዊው አርቲስት በረከትም በቦታው ላይ ንግግር ማድረጉ ታውቋል። በንግግሩ ላይም “ይህ ጉዳይ በህጉ የመታቀፍ ጥያቄ ነው፣ ተገልለን መቀጠልን አንፈቅድም” ብሏል። 

በኮሪያ ውስጥ በአርቲስትነት በመስራት የሚያጋጥሙትን ችግሮች የጠቆመን በረከት፣ ይህም ስደተኛ አርቲስቶች ለሥነ ጥበብ የገንዘብ ድጋፍ ለማመልከት ብቁ አለመሆናችንን እና ልዩ የቪዛ ዓይነቶች ላይ የሚጣሉ ገደቦች ሰለባ መሆንን ያካትታል ሲል አስረድቷል።

በረከት በተጨማሪ ሲናገር፣ “እኛ የባህል እና የገንዘብ ካፒታላችንን ኢንቨስት ያደረግን የዚህች ሀገር የውጭ ሀገር ነዋሪዎች እንደ ግብር ከፋይነታችን ከኮሪያውያን ዜጎች እኩል በሀገር አቀፍ የስነጥበብ ድጋፍ መታገዝ መቻል አለብን” በማለት በልዩነት እንዲታዩ እንደማይፈልጉ አስረድቷል።