በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ ከሚገኙ 36 ቀበሌዎች የሚመጡ አርሶአደሮች በከተማው ውስጥ ምርታቸውን የሚሸጡበት ቦታ ጠፍቶ ለእንግልት መዳረጋቸው የነበረ ጉዳይ ቢሆንም አሁንም እልባት አልተገኘለትም።
ምርታቸውን ተሸክመው ወይም በአህያ ጭነው ወደከተማ ለመግባት የሚሞክሩ ነገር ግን ቀይ ዱላ ተብለው በሚጠሩት ደንብ አስከባሪ ፖሊሶች የሚዋከቡ አርሶአደሮችን ማየት በባህር ዳር ከተማ እየተለመደ የመጣ ትዕይንት ነው።
አርሶአደሮቹ ምርቱ እንዳይበላሽ ምርጫ በማጣት ለተጠቃሚው ሳይሆን ለነጋዴዎች በርካሽ ዋጋ አስረክበው ወደቤታቸው ይመለሳሉ። በዚህም የደከሙበትን ዋጋ ሳያገኙ እንደሚቀሩ በምሬት ያስረዳሉ። ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩበት ብቸኛ የገቢ ምንጫቸው ከሆነው ግብርና እየተጠቀሙ አለመሆኑን አጫውተውናል።
ወ/ሮ እናኑ በቀለ በባህር ዳር የጣና ክፍለ ከተማ ኗሪ ናቸው። እንደ ወ/ሮ እናኑ ገለፃ አትክልት እና ፍራፍሬ ጨምሮ ሌሎች ምርቶች ከባህርዳር ዙሪያ ከሚመጡ አርሶ አደሮች መንገድ ላይ ጠብቀው እንደሚሸምቱ ይናገራሉ።
“ዋጋው ቅናሽ ከመሆኑ በተጨማሪ በማጓጓዝ ሂድት ብዙ ያልተንገላታ ወይም ፍሬሽ በመሆኑ ይመረጣል። ከዚህ ሌላ የማገዶ እንጨት እና የምድጃ ከሰል ከአርሶ አደሩ በርካሽ ዋጋ ይገኛል” ይላሉ ወ/ሮ እናኑ።
አርሶ አደሮቹ ወደ ገበያ ገብተው ምርታቸውን ለነጋዴዎች ካስረከቡ ለሸማቹ ይወደድበታል። በዚህም የተነሳ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች አርሶ አደሮችን ቀጥታ ማግኘት ይመርጣሉ። “ከዚህ በፊት ኪዳነ ምህረት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አርሶ አደሮች በጠዋት መተው በመቆም ሸማቹን ቀጥታ ያገኙ ነበር። አሁን ግን ቦታው ለነጋዴ በመሰጠቱ አርሶ አደሮችን ለማግኘት መንገድ ላይ በጠዋት ለመጠበቅ ተገደናል” ብለዋል ወ/ሮ እናኑ፡፡
አርሶ አደር ይታገሱ መንገሻ የባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ "አንዳሳ" ቀበሌ ኗሪ ናቸው። በማሳቸው ጫት፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች ምርቶች እንደሚያመርቱ ነግረውናል፡፡ የጫት ምርታቸውን ከተማ ወስደው የሚያስረክቡበት ቦታ በመኖሩ አልተቸገሩም። ነገር ግን አትክልትና ፍራፍሬ፣ የምድጃ ከሰል እና ሌሎች ምርቶችን ወደ ባህር ዳር ወስደው ለመሸጥ የመሸጫ ቦታ ባለመኖሩ ተቸግሪያለሁ ብለዋል፡፡
“ወደ ከተማ ስገባ መንገድ ዳር የሚጠብቀኝ ሸማች ካለ እሸጣለሁ። ካልሆነ ግን ወደ ገበያ ወስጄ ለነጋዴ በርካሽ ሸጬ እሄዳለሁ። በከተማው ለአርሶ አደሩ የመሸጫ ቦታ ቢኖረው መልካም ነበር” ሲሉ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።
አርሶአደር ታደሰ ሙላት ደግሞ "ወንጀጣ" ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ ሲሆኑ “ምርታችንን ገበያ ለመሸጥ ስንሞክር ቀይ ዱላ ተብለው የሚጠሩት ደንብ አስከባሪዎች ስለሚከለክሉን ለነጋዴ በርካሽ ለመሸጥ ተገደናል” ይላሉ። እንደ እርሶአደር ታደሰ ገለፃ የመሸጫ ቦታ ዕጥረት የእሳቸው ብቻ ችግር ሳይሆን የቀያቸው ኗሪዎች በአብዛኛው የሚጋሩት ችግር ነው።
በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ ንግድ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ቻላቸው አስማረ የአርሶደሮቹን ቅሬታ ይጋራሉ። “በተለይ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በአጭር ጊዜ ለብልሽት ስለሚጋለጡ አርሶአደሮች አምርተው አንዳይጠቀሙ እየሆኑ ይገኛሉ” ብለዋል። ከአትክልትና ፍራፍሬ በተጨማሪ እህልና ጥራጥሬ ምርቶች በዙሪያ ወረዳው የሚመረቱ በመሆኑ አርሶ አደሮች የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ አንዲሆኑ የመሸጫ ቦታ ችግር እንቅፋት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ ሃላፊው ማብራርያ በከተማው የሚገኙ የገበያ ማዕከላት በከተማ አሰተዳደሩ በኩል የሚተዳደሩ ናቸው። የወረዳው ንግድ ጽ/ቤት በወረዳ አስተዳደደሩ በኩል ከአምስት ዓመት በላይ ጥያቄውን ለባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ቢያቀርብም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም። “የከተማ አስተዳደሩ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብለትም ምላሽ መስጠት ባለመቻሉ ለክልሉ መንግስት አቤት ብለን ጉዳዩን በክልል ካብኔ አይተው ምላሽ እንደሚሰጡ ነግረውናል” ሲሉ ሃላፊው ጨምረው ገልጸውልናል።
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ የመሸጫ ቦታውን ችግር ለመቅረፍ የባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር ለባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ባለመቻሉ ከ36 ቀበሌዎች የሚመጡ አርሶ አደሮች ለእንግልት እየተዳሩጉ ይገኛሉ ብልዋል፡፡ የባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር አሁንም ቢሆን ችግሩን የክልሉ መንግስት የሚያውቀው በመሆኑ የክልሉን መንግስት ምላሽ እየጠበቁ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በከተማዋ ዙሪያ ለሚገኙ የወረዳ አርሶ አደሮች የመሸጫ ቦታ መስጠት የአርሶ አደሮችን የመልካም አስተዳደር ችግር ከመቅረፉ በተጨማሪ በከተማው ለሚስተዋለው የኑሮ ውድነት የራሱ የሆነ ሚና ስለሚኖረው ችግሩ መገታት አለበት ይላሉ የንግድ ፅ/ቤት ኃላፊው፡፡
ባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ንግድ መምሪያ የግብይት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ማሞ ተሰማ በበኩላቸው ለከተማው ዙሪያ አርሶአደሮች በከተማዋ ዉስጥ የገበያ ቦታ እንዲዘጋጅ በያዝነው ዓመት አጋማሽ የስራ መመሪያ ቢሠጥም እስካሁን ድረስ ተግባራዊ አለመደረጉን ገልጸዋል።
“ለአርሶ አደሮች የመሸጫ ቦታ አንዲያዘጋጁ ከተነገራቸው ክፍለከተሞች መካከል አንዱ ብቻ ማዘጋጀቱን የስራ ቡድኑ መሪ ገልጾልናል ፤ ነገር ግን የተዘጋጀው ማእከል አዲስ በመሆኑ የማስተዋወቅ ስራ ያስፈልገዋል” ብለዋል አቶ ማሞ፡፡
የምጣኔ ሃብት ባለሙያ የሆኑት አቶ ደመላሽ አሳየ እንደሚሉት በባህር ዳር ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች ያመረቱትን ምርት በቀጥታ ለከተማው ነዋሪ መሸጣቸው ነዋሪው በንፅፅር በተሻለ ዋጋ እንዲሸምት እድል ይፈጥርለታል ይላሉ፡፡
“በተጨማሪም በአምራቹ እና በተጠቃሚው መካካል የሚደረግ ግብይት በተባባሰው የኑሮ ውድነት ላይ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ሚና ያሳድራል፣ የግብይት ሰንሰለቱንም ያሳጥራል” ብለዋል አቶ ደመላሽ።
በባህር ዳር ከተማ ውስጥ ስድስት ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ሲሆን በከተማዋ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የገበያ ማዕከላት በከተማዋ ነጋዴዎች የተያዙ መሆናቸውን አዲስ ዘይቤ ማረጋጋጥ ችላለች፡፡
ከሌሎች ከተሞች በተለየ ባህር ዳር ከተማ በሳምንት ውስጥ ውስን የሆኑ የገበያ ቀናት የሏትም። ሁሉም ቀናት የገበያ ቀናት ናቸው።